የጳውሎስን ምሳሌ በመከተል መንፈሳዊ እድገት አድርጉ
“መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ።”—2 ጢሞ. 4:7
1, 2. የጠርሴሱ ሳውል በሕይወቱ ውስጥ ምን ለውጦችን አድርጓል? የትኛውን አስፈላጊ ሥራ ማከናወን ጀምሯል?
አስተዋይና ቆራጥ ሰው ቢሆንም አኗኗሩ ‘የሥጋውን ምኞት በማርካት’ ላይ ያተኮረ ነበር። (ኤፌ. 2:3) ከጊዜ በኋላ ስለ ራሱ ሲናገር “ተሳዳቢ፣ አሳዳጅና ዐመፀኛ” እንደነበረ ገልጿል። (1 ጢሞ. 1:13) ይህ ሰው የጠርሴሱ ሳውል ነው።
2 ከጊዜ በኋላ ሳውል በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ለውጥ አደረገ። የቀድሞ አኗኗሩን በመተው ‘ለራሱ የሚጠቅመውን ሳይሆን ለሌሎች የሚጠቅመውን’ ለማድረግ ይጥር ጀመር። (1 ቆሮ. 10:33) ይህ ሰው ቀደም ሲል ይጠላቸው የነበሩትን ሰዎች መውደድ ከመጀመሩም በላይ የዋህ ሆነ። (1 ተሰሎንቄ 2:7, 8ን አንብብ።) ሳውል እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆኛለሁ። ምንም እንኳ ከቅዱሳን ሁሉ ያነስሁ ብሆንም፣ የማይመረመረውን የክርስቶስን ባለጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ ይህ ጸጋ ለእኔ ተሰጠኝ።”—ኤፌ. 3:7, 8
3. የጳውሎስን ደብዳቤዎችና ስለ አገልግሎቱ የሰፈሩትን ዘገባዎች ማጥናታችን ጠቃሚ የሆነው እንዴት ነው?
3 ጳውሎስ በመባልም የሚታወቀው ሳውል ከፍተኛ መንፈሳዊ እድገት አድርጓል። (ሥራ 13:9) እኛም የጳውሎስን ደብዳቤዎችና ስለ አገልግሎቱ የሰፈሩትን ዘገባዎች በማጥናት እንዲሁም የእሱን የእምነት ምሳሌ በመኮረጅ በእውነት ውስጥ ፈጣን እድገት ማድረግ እንችላለን። (1 ቆሮንቶስ 11:1ን እና ዕብራውያን 13:7ን አንብብ።) እነዚህ ደብዳቤዎችና ዘገባዎች ጥሩ የግል ጥናት ልማድ እንድናዳብር፣ ለሰዎች እውነተኛ ፍቅር እንዲኖረን እንዲሁም ስለ ራሳችን ትክክለኛ አመለካከት እንድንይዝ እንዴት እንደሚረዱን እንመልከት።
የጳውሎስ የጥናት ልማድ
4, 5. ጳውሎስ የግል ጥናት በማድረጉ የተጠቀመው እንዴት ነበር?
4 ጳውሎስ ‘የአባቶችን ሕግ በገማልያል እግር ሥር ተቀምጦ’ የተማረ ፈሪሳዊ እንደመሆኑ መጠን ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት የተወሰነ እውቀት ነበረው። (ሥራ 22:1-3፤ ፊልጵ. 3:4-6) ከተጠመቀ በኋላ ወዲያውኑ “ወደ ዐረብ አገር” ሄደ፤ ጳውሎስ የሄደው ወደ ሶርያ ምድረ በዳ ወይም በአረብ ባሕረ ገብ ምድር ላይ ወደሚገኝ ለማሰላሰል የሚመች ጸጥ ያለ አካባቢ ሊሆን ይችላል። (ገላ. 1:17) ምናልባትም ይህን ያደረገው ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን በሚያረጋግጡት የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች ላይ ለማሰላሰል አስቦ ይሆናል። ከዚህም በላይ ከፊቱ ለሚጠብቀው ሥራ ለመዘጋጀት ፈልጎ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 9:15, 16, 20, 22ን አንብብ።) ጳውሎስ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ለማሰላሰል ጥረት አድርጎ ነበር።
5 ጳውሎስ በግል ጥናት አማካኝነት ያገኘው የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀትና ማስተዋል እውነትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተማር አስችሎታል። ለምሳሌ ያህል፣ በጲስድያ ባለችው አንጾኪያ ውስጥ በሚገኝ ምኩራብ ሲያስተምር ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ማስረጃ ለማቅረብ ቢያንስ አምስት ጊዜ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በቀጥታ ጠቅሷል። ከዚህም በላይ ከቅዱሳን መጻሕፍት በቀጥታ ባይጠቅስም ከእነዚህ መጻሕፍት የተወሰዱ ሐሳቦችን ተናግሯል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርቶ ያቀረባቸው ነጥቦች በጣም አሳማኝ ስለነበሩ “ብዙ አይሁድና ወደ ይሁዲ ሃይማኖት ገብተው በመንፈሳዊ ነገር የበረቱ ሰዎች” የበለጠ ለማወቅ ሲሉ “ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሏቸው።” (ሥራ 13:14-44) ከዓመታት በኋላ በሮም የሚኖሩ አይሁዳውያን ጳውሎስ ወዳረፈበት ቦታ በመጡ ጊዜም “ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየመሰከረ ያብራራላቸው ነበር፤ ከሙሴ ሕግና ከነቢያትም በመጥቀስ ስለ ኢየሱስ ሊያሳምናቸው” ሞክሯል።—ሥራ 28:17, 22, 23
6. ጳውሎስ የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሙትም በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል የረዳው ምን ነበር?
6 ጳውሎስ የተለያዩ ችግሮች ባጋጠሙት ጊዜም ቅዱሳን መጻሕፍትን በመመርመር በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው መልእክት ብርታት ያገኝ ነበር። (ዕብ. 4:12) ይህ ሐዋርያ ከመገደሉ በፊት በሮም ታስሮ በነበረበት ወቅት “ጥቅልል መጻሕፍቱን” እንዲሁም “የብራና መጻሕፍቱን” እንዲያመጣለት ጢሞቴዎስን ጠይቆታል። (2 ጢሞ. 4:13) እነዚህ መጻሕፍት ጳውሎስ ጥልቅ ጥናት በሚያደርግበት ጊዜ የሚጠቀምባቸው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች ሳይሆኑ አይቀሩም። ጳውሎስ ቅዱሳን መጻሕፍትን አዘውትሮ በማጥናት ያገኘው እውቀት እንዲጸና ረድቶታል።
7. መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ በማጥናት ምን ጥቅሞች ልታገኝ ትችላለህ?
7 እኛም መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን ማጥናታችንና ባነበብነው ነገር ላይ ዓላማ ባለው መንገድ ማሰላሰላችን በመንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ ይረዳናል። (ዕብ. 5:12-14) መዝሙራዊው የአምላክ ቃል ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ በማለት ዘምሯል:- “ከአእላፋት ብርና ወርቅ ይልቅ፣ ከአፍህ የሚወጣው ሕግ ይሻለኛል። ትእዛዛትህ ምን ጊዜም ስለማይለዩኝ፣ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረጉኝ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ፣ እግሬን ከክፉ መንገድ ሁሉ ከለከልሁ።” (መዝ. 119:72, 98, 101) አንተስ መጽሐፍ ቅዱስን በግልህ አዘውትረህ የማጥናት ልማድ አለህ? መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብና ባነበብከው ነገር ላይ በማሰላሰል በአምላክ አገልግሎት ወደፊት ለሚሰጡህ ኃላፊነቶች ራስህን እያዘጋጀህ ነው?
ሳውል ሰዎችን ይወድ ጀመር
8. ሳውል የአይሁድ እምነት ተከታዮች ያልነበሩ ሰዎችን ምን አድርጓቸው ነበር?
8 ሳውል ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ለሃይማኖቱ ቀናተኛ የነበረ ቢሆንም የአይሁድ እምነት ተከታዮች ላልሆኑ ሰዎች ብዙም ግድ አልነበረውም። (ሥራ 26:4, 5) አንዳንድ አይሁዳውያን እስጢፋኖስን ሲወግሩት በድርጊታቸው ተስማምቶ ተመልክቷቸዋል። ሳውል እስጢፋኖስ መገደሉ ተገቢ ቅጣት እንደሆነ ሳይሰማው አልቀረም፤ በዚህ ወቅት የተመለከተው ነገር ክርስቲያኖችን ማሳደዱ ትክክል እንደሆነ እንዲያስብ አድርጎት ይሆናል። (ሥራ 6:8-14፤ 7:54 እስከ 8:1) በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ታጥቆ ተነሣ፤ ከቤት ወደ ቤት በመግባትም ወንዶችንና ሴቶችን ጐትቶ እያወጣ ወህኒ ቤት ያስገባቸው ነበር።” (ሥራ 8:3) ይህም ሳይበቃው ክርስቲያኖችን ‘በውጭ አገር እስከሚገኙ ከተሞች ድረስ ተከታትሎ አሳዷቸዋል።’—ሥራ 26:11
9. ሳውል ለሰዎች የነበረውን አመለካከት እንዲያስተካክል የረዳው ምንድን ነው?
9 ሳውል በደማስቆ የሚገኙትን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለማሰር ወደዚያ እየተጓዘ ሳለ ጌታ ኢየሱስ ተገለጠለት። ከአምላክ ልጅ የመነጨው ኃይለኛ ብርሃን ሳውል የማየት ችሎታውን እንዲያጣ ስላደረገው የሰው እርዳታ አስፈልጎት ነበር። ይሖዋ፣ በሐናንያ በመጠቀም ሳውል እንደገና ማየት እንዲችል ሲያደርገው ሳውል ለሰዎች የነበረው አመለካከት ሙሉ በሙሉ ተለወጠ። (ሥራ 9:1-30) ይህ ሰው የክርስቶስ ተከታይ ከሆነ በኋላ ልክ እንደ ኢየሱስ ሁሉንም ሰው ለመርዳት ይጥር ነበር። ይህም የዓመጸኝነት ባሕርይውን አስወግዶ “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም” መኖርን ጠይቆበታል።—ሮሜ 12:17-21ን አንብብ።
10, 11. ጳውሎስ ለሰዎች ልባዊ ፍቅር እንዳለው ያሳየው እንዴት ነበር?
10 ጳውሎስ ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት በመመሥረቱ ብቻ ረክቶ አልተቀመጠም። ለሰዎች ልባዊ ፍቅር የማሳየት ፍላጎት የነበረው ሲሆን ክርስቲያናዊው አገልግሎትም ይህን ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ ፈጥሮለታል። በመጀመሪያ ሚስዮናዊ ጉዞው ምሥራቹን በትንሿ እስያ ሰብኳል። ጳውሎስና የአገልግሎት ጓደኞቹ ከባድ ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም ቅን የሆኑ ሰዎች ክርስትናን እንዲቀበሉ በመርዳቱ ሥራ ላይ ትኩረት አድርገዋል። በልስጥራና በኢቆንዮን የነበሩ ተቃዋሚዎች ጳውሎስን ለመግደል የሞከሩ ቢሆንም ከባልደረቦቹ ጋር ወደ እነዚህ ከተሞች በድጋሚ ሄዷል።—ሥራ 13:1-3፤ 14:1-7፤ 19-23
11 ከጊዜ በኋላ ደግሞ ጳውሎስና አብረውት የነበሩት ሰዎች በመቄዶንያ በምትገኘው በፊልጵስዩስ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። በዚያም ልድያ የተባለች ወደ አይሁድ እምነት የተለወጠች ሴት ምሥራቹን ሰምታ ክርስቲያን ሆነች። የከተማዋ ባለ ሥልጣናት ግን ጳውሎስንና ሲላስን በበትር ካስደበደቧቸው በኋላ ወኅኒ ቤት አስገቧቸው። ጳውሎስ ለወኅኒ ቤቱ ጠባቂ የሰበከለት ሲሆን በዚህም የተነሳ እሱና ቤተሰቡ ተጠምቀው የይሖዋ አምላኪዎች መሆን ችለዋል።—ሥራ 16:11-34
12. ዓመጸኛ የነበረው ሳውል አፍቃሪ የሆነ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ እንዲሆን ያነሳሳው ምን ነበር?
12 በአንድ ወቅት አሳዳጅ የነበረው ሳውል ያሳድዳቸው የነበሩትን ሰዎች እምነት የተቀበለው ለምንድን ነው? ዓመጸኛ የነበረው ይህ ግለሰብ፣ ደግና አፍቃሪ ሐዋርያ እንዲሆን ያደረገውስ ምንድን ነው? ይህ ሰው ሌሎች ሰዎች ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ እውነቱን እንዲያውቁ ለመርዳት ሲል ሕይወቱን አደጋ ላይ እንዲጥል ያነሳሳው ምን ነበር? ጳውሎስ ራሱ እንዲህ ሲል መልሱን ሰጥቶናል:- “በጸጋው የጠራኝ እግዚአብሔር፣ በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ እንድሰብክ ልጁን በእኔ ሊገልጥ [ወደደ]።” (ገላ. 1:15, 16) ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ክርስቶስ ኢየሱስ በእርሱ ለሚያምኑና የዘላለምን ሕይወት ለሚቀበሉ ወሰን የሌለው ትዕግሥቱን ከኀጢአተኞች ዋና በሆንሁት በእኔ እንደ ምሳሌ አድርጎ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ።” (1 ጢሞ. 1:16) ይሖዋ፣ ጳውሎስን ይቅር ብሎታል፤ ይህ ሐዋርያ የአምላክን ጸጋና ምሕረት ማግኘቱ ለሰዎች ምሥራቹን በመስበክ ፍቅር እንዲያሳይ ገፋፍቶታል።
13. ለሰዎች ፍቅር እንድናሳይ ሊገፋፋን የሚገባው ምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?
13 ይሖዋ የእኛንም ኃጢአትና ስህተት ይቅር ይላል። (መዝ. 103:8-14) መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአትን ብትቈጣጠር፣ ጌታ ሆይ፤ ማን ሊቆም ይችላል?” በማለት ጠይቋል። (መዝ. 130:3) የአምላክን ምሕረት ባናገኝ ኖሮ ማንኛችንም ብንሆን በቅዱስ አገልግሎት መካፈል የማንችል ከመሆኑም በላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ አይኖረንም ነበር። በእርግጥም አምላክ ለሁላችንም ያሳየን ጸጋ ታላቅ ነው። እንግዲያው እኛም እንደ ጳውሎስ ለሰዎች በመስበክና እውነትን በማስተማር እንዲሁም የእምነት ባልንጀሮቻችንን በማበረታታት ለሰዎች ፍቅር እንዳለን ማሳየት ይገባናል።—የሐዋርያት ሥራ 14:21-23ን አንብብ።
14. አገልግሎታችንን ማስፋትና የተሻልን ሰባኪዎች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
14 ጳውሎስ በስብከቱ ሥራ የበለጠ የመካፈልና የተሻለ የምሥራቹ ሰባኪ የመሆን ፍላጎት የነበረው ሲሆን የኢየሱስ ምሳሌም በጥልቅ ነክቶታል። የአምላክ ልጅ ለሰዎች ያለውን ጥልቅ ፍቅር ካሳየባቸው መንገዶች አንዱ የስብከቱ ሥራ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “መከሩ ብዙ ነው፤ የመከሩ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩ ጌታ፣ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት።” (ማቴ. 9:35-38) ጳውሎስ ራሱ እንዲህ ዓይነት ልመና አቅርቦ ይሆናል፤ ደግሞም ቀናተኛ ሰባኪ በመሆን ካቀረበው ልመና ጋር የሚስማማ እርምጃ ወስዷል። አንተስ? የአገልግሎትህን ጥራት ማሻሻል ትችል ይሆን? ወይም ደግሞ ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩ ሥራ የበለጠ ተሳትፎ ማድረግ ትችላለህ? ምናልባትም በሕይወትህ ውስጥ ማስተካከያዎች በማድረግ አቅኚ ሆነህ ማገልገል ትችል ይሆን? ሰዎች ‘የሕይወትን ቃል እንዲይዙ’ በመርዳት ለእነሱ ልባዊ ፍቅር እንዳለን እናሳይ።—ፊልጵ. 2:16 የግርጌ ማስታወሻ
ጳውሎስ ስለ ራሱ የነበረው አመለካከት
15. ጳውሎስ ስለ ራሱም ሆነ ስለ ሌሎች ክርስቲያኖች ምን አመለካከት ነበረው?
15 ክርስቲያን አገልጋይ የነበረው ጳውሎስ በሌላም መንገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ጳውሎስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በርካታ መብቶች የነበሩት ቢሆንም እነዚህን መብቶች ያገኘው ጥሩ ችሎታ ስላለው እንደሆነ አልተሰማውም። እነዚህን መብቶች ያገኘው በአምላክ ጸጋ እንደሆነ ተገንዝቧል። ጳውሎስ ሌሎች ክርስቲያኖችም ውጤታማ የወንጌሉ ሰባኪዎች እንደሆኑ ያውቅ ነበር። በአምላክ ሕዝቦች መካከል የኃላፊነት ቦታ ቢኖረውም ትሑት ነበር።—1 ቆሮንቶስ 15:9-11ን አንብብ።
16. ጳውሎስ ከግርዘት ጋር በተያያዘ በተነሳው ጉዳይ ላይ ትሕትና ያሳየው እንዴት ነበር?
16 ጳውሎስ፣ በሶሪያ በምትገኘው አንጾኪያ ከተነሳው ችግር ጋር በተያያዘ ምን እንዳደረገ እንመልከት። በዚያ በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ ግርዘትን በሚመለከት መከፋፈል ተፈጥሮ ነበር። (ሥራ 14:26 እስከ 15:2) ጳውሎስ ላልተገረዙ አሕዛብ የመስበኩን ሥራ በግንባር ቀደምትነት እንዲያከናውን ኃላፊነት የተሰጠው እንደመሆኑ መጠን አይሁዳውያን ካልሆኑ ሰዎች ጋር በመግባባት ረገድ ጥሩ ችሎታ እንዳለውና በዚህ የተነሳ ችግሩን ለመፍታት ብቁ እንደሆነ ለማሰብ የሚያበቃ ምክንያት ነበረው። (ገላትያ 2:8, 9ን አንብብ።) ሆኖም ችግሩን ለመፍታት ያደረገው ጥረት መፍትሔ እንዳላስገኘ ሲመለከት ጉዳዩን በኢየሩሳሌም ያለው የበላይ አካል እንዲወያይበት የተደረገውን ውሳኔ በትሕትና ተቀብሏል። የበላይ አካሉ አባላት ጉዳዩን አዳምጠው ውሳኔ ሲያሳልፉ እንዲሁም እሱና ሌሎች ሰዎች መልእክቱን እንዲያደርሱ ሲመርጧቸው የትብብር መንፈስ አሳይቷል። (ሥራ 15:22-31) በዚህ መንገድ ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን ‘ከራሱ በማስበለጥ አክብሯቸዋል።’—ሮሜ 12:10ለ
17, 18. (ሀ) ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ ለነበሩት ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ስሜት ነበረው? (ለ) የኤፌሶን ሽማግሌዎች ጳውሎስን ሲሰናበቱት ያሳዩት ሁኔታ ስለ እሱ ምን ያስተምረናል?
17 ትሑት የነበረው ጳውሎስ ራሱን ከፍ አድርጎ በመመልከት በጉባኤ ውስጥ ከሚገኙት ወንድሞችና እህቶች አልራቀም። ከዚህ ይልቅ ከእነሱ ጋር ይቀራረብ ነበር። ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ መደምደሚያ ላይ ከ20 የሚበልጡ ሰዎችን ስም በመጥቀስ ሰላምታ አቅርቧል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በሌላ ቦታ አልተጠቀሱም፤ ልዩ መብት የነበራቸውም ጥቂቶቹ ናቸው። ያም ሆኖ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ስለነበሩ ጳውሎስ በጥልቅ ይወዳቸው ነበር።—ሮሜ 16:1-16
18 ጳውሎስ ትሑትና ሌሎችን የሚቀርብ ሰው መሆኑ ጉባኤዎቹን አጠናክሯቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህ ሐዋርያ የኤፌሶን ሽማግሌዎችን ለመጨረሻ ጊዜ ባገኛቸው ወቅት የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “አንገቱን ዐቅፈው ሳሙት፤ ከሁሉም በላይ ልባቸውን የነካው፣ ከእንግዲህ ወዲህ ፊቱን እንደማያዩ የተናገራቸው ቃል ነበር።” ጳውሎስ ኩሩና ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሰው ቢሆን ኖሮ ሽማግሌዎቹ እንዲህ ዓይነት ስሜት አይኖራቸውም ነበር።—ሥራ 20:37, 38
19. ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ‘ትሑቶች’ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
19 መንፈሳዊ እድገት ማድረግ የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ጳውሎስ ትሕትናን ማንጸባረቅ ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን እንዲህ ሲል መክሯቸዋል:- “ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቍጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ።” (ፊልጵ. 2:3) ይህንን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ሽማግሌዎች የሚሰጡንን መመሪያ በመከተል እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ከባድ ኃጢአት በሚፈጸምበት ጊዜ የሚያደርጉትን ውሳኔ በማክበር ነው። (ዕብራውያን 13:17ን አንብብ።) ሌላው መንገድ ደግሞ የእምነት ባልንጀሮቻችን የሆኑ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በሙሉ ከፍ አድርገን በመመልከት ነው። አብዛኛውን ጊዜ በይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤዎች ውስጥ የተለያየ ዜግነት፣ ባሕል፣ ዘርና ጎሳ ያላቸው ሰዎች ይገኛሉ። ታዲያ ጳውሎስ እንዳደረገው እኛም ሁሉንም ያለ አድልዎ በፍቅር መያዝ አይኖርብንም? (ሥራ 17:26፤ ሮሜ 12:10ሀ) “ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሆን ዘንድ ክርስቶስ እንደተቀበላችሁ፣ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ” የሚል ማበረታቻ ተሰጥቶናል።—ሮሜ 15:7
የሕይወትን ሩጫ “በጽናት እንሩጥ”
20, 21. የሕይወትን ሩጫ በድል ለማጠናቀቅ ምን ይረዳናል?
20 የክርስቲያኖች ሕይወት ከረጅም ርቀት ሩጫ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ። ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ በዚያ ቀን ለእኔ ይሰጠኛል፤ ደግሞም ለእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሱን መገለጥ ለናፈቁ ሁሉ ነው።”—2 ጢሞ. 4:7, 8
21 የጳውሎስን ምሳሌ መከተላችን የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የምናደርገውን ሩጫ በድል እንድናጠናቅቅ ይረዳናል። (ዕብ. 12:1) እንግዲያው ጥሩ የግል ጥናት ልማድ በማዳበር፣ ሰዎችን ከልባችን በመውደድ እንዲሁም ትሑቶች በመሆን መንፈሳዊ እድገት ማድረጋችንን እንቀጥል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ጳውሎስ ቅዱሳን መጻሕፍትን አዘውትሮ በማጥናቱ የተጠቀመው እንዴት ነው?
• እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሰዎች ልባዊ ፍቅር ማዳበራቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• አድሎ ከማድረግ እንድትርቅ የሚረዱህ የትኞቹ ባሕርያት ናቸው?
• የጳውሎስ ምሳሌ በጉባኤህ ውስጥ ከሚገኙ ሽማግሌዎች ጋር እንድትተባበር የሚረዳህ እንዴት ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ እንዳደረገው ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጥናት ብርታት ማግኘት ትችላለህ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለሌሎች ምሥራቹን በማካፈል ፍቅር አሳይ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ በወንድሞች ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን ያደረገው ምን እንደሆነ ታውቃለህ?