የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ግንቦት 2019
ከግንቦት 6-12
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ቆሮንቶስ 4-6
“ተስፋ አንቆርጥም”
(2 ቆሮንቶስ 4:16) ስለዚህ ተስፋ አንቆርጥም፤ ምንም እንኳ ውጫዊው ሰውነታችን እየመነመነ ቢሄድም ውስጣዊው ሰውነታችን ከቀን ወደ ቀን እየታደሰ እንደሚሄድ ምንም ጥርጥር የለውም።
ሰውነታችን ቢዝልም መንፈሳችን አይደክምም
16 መንፈሳዊ ጤንነታችንን መንከባከብ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። ከይሖዋ አምላክ ጋር የቅርብ ወዳጅነት እያለንም እንኳ ሰውነታችን ሊዝል ቢችልም እርሱን ማምለክ ፈጽሞ አድካሚ አይሆንብንም። ይሖዋ “ለደከመው ብርታት ይሰጣል፤ ለዛለው ጉልበት ይጨምራል።” (ኢሳይያስ 40:28, 29) የዚህን እውነተኝነት በሕይወቱ የተመለከተው ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ተስፋ አንቈርጥም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየጠፋ ቢሄድም እንኳ፣ ውስጣዊው ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል።”—2 ቆሮንቶስ 4:16
17 “ዕለት ዕለት” የሚለውን አባባል ተመልከት። ይህ አባባል ይሖዋ ካደረገልን ዝግጅቶች በየዕለቱ መጠቀም እንዳለብን ያሳያል። ለ43 ዓመታት በታማኝነት ያገለገለች አንዲት ሚስዮናዊ አካላዊ ድካምና ተስፋ መቁረጥ የተሰማት ወቅት ነበር። ይሁን እንጂ መንፈሷ ደክሞ አያውቅም። እንዲህ ትላለች፦ “የዕለቱ እንቅስቃሴዬን ከመጀመሬ በፊት ወደ ይሖዋ የምጸልይበትና ቃሉን የማነብበት ጊዜ ማግኘት እንድችል በማለዳ የመነሳት ልማድ አለኝ። በየዕለቱ የምከተለው ይህ ልማድ እስካሁን ድረስ እንድጸና ረድቶኛል።” ያለማቋረጥ አዎን፣ “ዕለት ዕለት” ወደ ይሖዋ የምንጸልይና ግሩም በሆኑት ባሕርያቱና በሰጠን ተስፋዎች ላይ የምናሰላስል ከሆነ ችግሮችን ተቋቁመን የምናሳልፍበት ኃይል እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
(2 ቆሮንቶስ 4:17) የሚደርስብን መከራ ጊዜያዊና ቀላል ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድና ዘላለማዊ የሆነ ክብር ያስገኝልናል፤
it-1-E 724-725
ጽናት
በተጨማሪም ክርስቲያናዊ ተስፋችን ማለትም ከኃጢአት ተላቅቀን ለዘላለም የመኖር ተስፋችን ሁልጊዜ እንዲታየን ማድረግ አስፈላጊ ነው። አሳዳጆቻችን ቢገድሉን እንኳ ይህን ተስፋ ሊያሳጡን አይችሉም። (ሮም 5:4, 5፤ 1ተሰ 1:3፤ ራእይ 2:10) በአሁኑ ጊዜ የሚደርስብን መከራ ከዚህ ታላቅ ተስፋ ፍጻሜ ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። (ሮም 8:18-25) ማንኛውም መከራ በወቅቱ ምንም ያህል ከባድ ቢሆን ከዘላለማዊነት ጋር ሲወዳደር “ጊዜያዊና ቀላል” ነው። (2ቆሮ 4:16-18) አንድ ሰው ፈተናዎች ጊዜያዊ መሆናቸውን ማሰቡና ክርስቲያናዊ ተስፋውን አጥብቆ መያዙ ተስፋ ቆርጦ ለይሖዋ አምላክ ያለውን ታማኝነት እንዳያጓድል ይጠብቀዋል።
(2 ቆሮንቶስ 4:18) ስለዚህ ዓይናችን እንዲያተኩር የምናደርገው በሚታዩት ነገሮች ላይ ሳይሆን በማይታዩት ነገሮች ላይ ነው። የሚታዩት ጊዜያዊ ናቸውና፤ የማይታዩት ግን ዘላለማዊ ናቸው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(2 ቆሮንቶስ 4:7) ይሁን እንጂ ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነው ኃይል ከእኛ ሳይሆን ከአምላክ የመነጨ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ይህ ውድ ሀብት በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን።
“የይሖዋ ፊት በደስታ እንዲያበራ” አድርጉ
የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ዴቪድ ስፕሌን ከላይ ባለው ጥቅስ ላይ የተመሠረተ ንግግር አቀረበ። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ውድ ሀብት የተባለው ምንድን ነው? እውቀት ወይም ጥበብ ነው? “አይደለም” በማለት ተናጋሪው መልሷል። ከዚያም “ሐዋርያው ጳውሎስ የጠቀሰው ውድ ሀብት ‘እውነትን በመግለጥ’ የምናከናውነው ‘አገልግሎት’” መሆኑን ገለጸ። (2 ቆሮንቶስ 4:1, 2, 5) ተማሪዎቹ ለአምስት ወራት ያገኙት ሥልጠና በአገልግሎቱ ለሚሰጣቸው ልዩ ተልዕኮ የሚያዘጋጃቸው እንደነበረ ወንድም ስፕሌን አስታውሷቸዋል። ይህን ኃላፊነታቸውን ከፍ አድርገው ሊመለከቱት ይገባል።
ወንድም ስፕሌን ‘የሸክላው ዕቃ’ የሚያመለክተው ደካማ የሆነውን ሥጋችንን እንደሆነ ያብራራ ሲሆን ከሸክላ የተሠራን ዕቃ ከወርቅ ከተሠራ ዕቃ ጋር አወዳድሯል። ከወርቅ የተሠሩ ዕቃዎች አገልግሎት ላይ የሚውሉት አልፎ አልፎ ነው። በሌላ በኩል ግን የሸክላ ዕቃዎች ሁልጊዜ አገልግሎት ላይ ይውላሉ። አንድን ውድ ነገር በወርቅ ዕቃ ውስጥ ካስቀመጥን በውስጡ የተቀመጠውን ውድ ሀብት ያህል ለወርቁ ዕቃም ትኩረት መስጠታችን አይቀርም። ወንድም ስፕሌን “እናንተም የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሳችሁ መሳብ እንደማትፈልጉ ግልጽ ነው” ብሏል። አክሎም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ሚስዮናውያን እንደመሆናችሁ መጠን ሰዎች በይሖዋ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ትፈልጋላችሁ። እናንተ ቦታችሁን የምታውቁ የሸክላ ዕቃዎች ናችሁ።”
(2 ቆሮንቶስ 6:13) ስለዚህ ልጆቼን እንደማናግር ሆኜ አናግራችኋለሁ፤ እናንተም በአጸፋው ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱ።
የወንድማማችነት ፍቅራችሁ እያደገ ይሂድ
7 እኛስ? የወንድማማችነት ፍቅር በማሳየት ረገድ ‘ልባችንን ወለል አድርገን መክፈት’ የምንችለው እንዴት ነው? በዕድሜ እኩያሞች የሆኑ ወይም ተመሳሳይ ዘር ያላቸው ሰዎች በቀላሉ ይቀራረቡ ይሆናል። እንዲሁም በመዝናኛ ረገድ ተመሳሳይ ምርጫ ያላቸው ሰዎች አብረው ብዙ ጊዜ ማሳለፋቸው የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ ከአንዳንድ ክርስቲያኖች ጋር ተመሳሳይ ፍላጎት ያለን መሆኑ ከሌሎቹ ጋር እንዳንቀራረብ የሚያደርገን ከሆነ ‘ልባችንን ወለል አድርገን መክፈት’ ያስፈልገናል። እንደሚከተለው በማለት ራሳችንን መጠየቃችን ጥበብ ነው፦ ‘የቅርብ ወዳጆቼ ካልሆኑ ወንድሞችና እህቶች ጋር የማገለግለው ወይም ከእነሱ ጋር በሌሎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች የምካፈለው ከስንት አንዴ ነው? በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ የማገኛቸው አዳዲስ ሰዎች ጓደኞቼ ለመሆን ብቁ መሆናቸውን በጊዜ ሂደት ማሳየት እንዳለባቸው በማሰብ ከእነሱ ጋር ያለኝ ግንኙነት የተገደበ እንዲሆን አደርጋለሁ? ልጅ አዋቂ ሳልል ሁሉንም የጉባኤ አባላት ሰላም እላለሁ?’
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(2 ቆሮንቶስ 4:1-15) ስለዚህ በተደረገልን ምሕረት የተነሳ ይህ አገልግሎት ስላለን ተስፋ አንቆርጥም። 2 ከዚህ ይልቅ አሳፋሪ የሆኑትን ስውር ነገሮች ትተናል፤ በተንኮል አንመላለስም፤ የአምላክንም ቃል አንበርዝም፤ ነገር ግን እውነትን በመግለጥ በአምላክ ፊት የሰውን ሁሉ ሕሊና በሚማርክ መንገድ ራሳችንን ብቁ አድርገን እናቀርባለን። 3 እንግዲህ የምናውጀው ምሥራች በእርግጥ የተሸፈነ ከሆነ የተሸፈነው ወደ ጥፋት እያመሩ ላሉት ነው፤ 4 የአምላክ አምሳል ስለሆነው ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውና ክብራማ የሆነው ምሥራች የሚፈነጥቀው ብርሃን በእነሱ ላይ እንዳያበራ የዚህ ሥርዓት አምላክ የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ አሳውሯል። 5 እኛ የምንሰብከው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ መሆኑንና እኛም ስለ ኢየሱስ ስንል የእናንተ ባሪያዎች መሆናችንን እንጂ ስለ ራሳችን አይደለምና። 6 “በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይብራ” ያለው አምላክ ነውና፤ ስለሆነም በክርስቶስ ፊት አማካኝነት፣ በልባችን ውስጥ ስለ አምላክ አስደናቂ እውቀት ይፈነጥቅ ዘንድ በልባችን ላይ ብርሃን አብርቷል። 7 ይሁን እንጂ ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነው ኃይል ከእኛ ሳይሆን ከአምላክ የመነጨ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ይህ ውድ ሀብት በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን። 8 በየአቅጣጫው ብንደቆስም መፈናፈኛ አናጣም፤ ግራ ብንጋባም መውጫ ቀዳዳ አናጣም፤ 9 ስደት ቢደርስብንም አልተተውንም፤ በጭንቀት ብንዋጥም አንጠፋም። 10 የኢየሱስ ሕይወት በእኛም ሰውነት እንዲገለጥ በኢየሱስ ላይ የደረሰውን ለሞት ሊዳርግ የሚችል መከራ ዘወትር በሰውነታችን እንሸከማለን። 11 የኢየሱስ ሕይወት ሟች በሆነው ሥጋችንም ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆን ለኢየሱስ ስንል ዘወትር ከሞት ጋር እንፋጠጣለንና። 12 ስለሆነም በእኛ ላይ ሞት፣ በእናንተ ላይ ግን ሕይወት እየሠራ ነው። 13 “አመንኩ፤ ስለዚህም ተናገርኩ” ተብሎ ተጽፏል። እኛም እንዲህ ዓይነት የእምነት መንፈስ ስላለን እናምናለን፤ ስለዚህም እንናገራለን፤ 14 ኢየሱስን ያስነሳው እሱ፣ እኛንም ከኢየሱስ ጋር እንደሚያስነሳንና ከእናንተ ጋር አንድ ላይ በፊቱ እንደሚያቀርበን እናውቃለን። 15 ይህ ሁሉ የሆነው ለእናንተ ሲባል ነውና፤ ይኸውም ብዙ ሰዎች ለአምላክ ክብር ምስጋና እያቀረቡ ስለሆነ የተትረፈረፈው ጸጋ ይበልጥ እንዲበዛ ነው።
ከግንቦት 13-19
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ቆሮንቶስ 7-10
“የእርዳታ አገልግሎታችን”
(2 ቆሮንቶስ 8:1-3) ወንድሞች፣ በመቄዶንያ ላሉት ጉባኤዎች ስለተሰጠው የአምላክ ጸጋ እንድታውቁ እንፈልጋለን። 2 ከባድ ፈተና ደርሶባቸው በመከራ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ታላቅ ደስታ የነበራቸው ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ልግስና አሳይተዋል፤ ይህን ያደረጉት በጣም ድሆች ሆነው ሳለ ነው። 3 እንደ አቅማቸው እንዲያውም ከአቅማቸው በላይ እንደሰጡ እመሠክርላቸዋለሁና፤
“እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳል”
ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመጀመሪያ የነገራቸው የመቄዶንያ ሰዎች ለእርዳታ ማሰባሰብ ጥረቱ ስለሰጡት በምሳሌነት የሚጠቀስ አፋጣኝ ምላሽ ነበር። ጳውሎስ “እነርሱ ብዙ መከራና ፈተና ደርሶባቸዋል፤ ይሁን እንጂ ደስታቸው ታላቅ ስለሆነ ምንም እንኳ በጣም ድኾች ቢሆኑ ከፍ ያለ ልግስና አድርገዋል” በማለት ጽፏል። የመቄዶንያ ሰዎች መጎትጎት አላስፈለጋቸውም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ “የመርዳት ዕድል እንዳይነፈጋቸውም አጥብቀው ለመኑን” ብሏል። የመቄዶንያ ሰዎች በደስታ ልግስና ያሳዩት እነሱ ራሳቸው “በጣም ድኾች” ሆነው እያሉ መሆኑን ማወቃችን ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ ያደርገዋል።—2 ቆሮንቶስ 8:2-4 የ1980 ትርጉም
የእርዳታ አገልግሎት
ወቅቱ 46 ዓ.ም. ገደማ ሲሆን ይሁዳ በረሃብ ተጠቅታለች። ከፍተኛ የእህል እጥረት ስላለ የምግብ ዋጋ የማይቀመስ ሆኗል፤ በመሆኑም በይሁዳ ያሉት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እህል ለመግዛት የሚያስችል አቅም አልነበራቸውም። የምግብ እጥረቱ እጅግ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል። ሆኖም እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ማንኛውም የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ከዚያ በፊት ባላየው መንገድ የይሖዋን እጅ ሊያዩ ነው። እንዴት?
(2 ቆሮንቶስ 8:4) ምክንያቱም እነዚህ ወንድሞች ለቅዱሳን በልግስና በመስጠት፣ በእርዳታ አገልግሎቱ ለመካፈል መብት እንዲሰጣቸው በራሳቸው ፍላጎት ተነሳስተው ይለምኑን እንዲያውም ይማጸኑን ነበር።
የእርዳታ አገልግሎት
4 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ የክርስቲያኖች አገልግሎት ሁለት ገጽታዎች እንዳሉት ገልጿል። ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ቢሆንም የተናገረው ነገር በዛሬው ጊዜ ላሉ የክርስቶስ “ሌሎች በጎች” ጭምር ይሠራል። (ዮሐ. 10:16) የአገልግሎታችን አንዱ ገጽታ “የማስታረቅ አገልግሎት” ይኸውም የስብከቱና የማስተማሩ ሥራ ነው። (2 ቆሮ. 5:18-20፤ 1 ጢሞ. 2:3-6) ሌላው ገጽታ ደግሞ ለእምነት ባልንጀሮቻችን ስንል የምናከናውነው አገልግሎት ነው። ጳውሎስ ይህን አገልግሎት ‘የእርዳታ አገልግሎት’ በማለት ጠርቶታል። (2 ቆሮ. 8:4) “የማስታረቅ አገልግሎት” እና ‘የእርዳታ አገልግሎት’ በሚሉት በሁለቱም አገላለጾች ላይ “አገልግሎት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ዲያኮኒያ ነው። ታዲያ ይህ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?
5 ጳውሎስ በሁለቱም ቦታዎች ላይ አንድ ዓይነት የግሪክኛ ቃል መጠቀሙ የእርዳታውን ሥራ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከሚከናወኑ ሌሎች አገልግሎቶች ጋር እንደፈረጀው የሚያሳይ ነው። ቀደም ሲል እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፦ “ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፤ ሁሉም አገልግሎት የሚቀርበው ግን ለአንድ ጌታ ነው፤ በተጨማሪም ልዩ ልዩ ሥራዎች አሉ፤ ሆኖም . . . እነዚህን ሁሉ ነገሮች የሚያከናውነው ያው አንድ መንፈስ ነው።” (1 ቆሮ. 12:4-6, 11) እንዲያውም ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ የሚከናወኑትን የተለያዩ አገልግሎቶች ‘ከቅዱስ አገልግሎት’ ጋር አያይዞ ገልጿቸዋል። (ሮም 12:1, 6-8) ከዚህ አንጻር፣ ሐዋርያው የተወሰነ ጊዜውን “ቅዱሳንን ለማገልገል” መመደቡ አስፈላጊ እንደሆነ የተሰማው መሆኑ አያስገርምም!—ሮም 15:25, 26
6 ጳውሎስ የእርዳታ ሥራ፣ ክርስቲያኖች የሚያከናውኑት አገልግሎትና ለይሖዋ የሚያቀርቡት አምልኮ ክፍል የሆነበትን ምክንያት እንዲገነዘቡ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ረድቷቸዋል። ያቀረበውን ማስረጃ እንመልከት፦ እርዳታ የሚሰጡ ክርስቲያኖች ይህን የሚያደርጉት “ስለ ክርስቶስ ለሚገልጸው ምሥራች ተገዢዎች [ስለሆኑ]” እንደሆነ ተናግሯል። (2 ቆሮ. 9:13) ክርስቲያኖች የክርስቶስን ትምህርት በሥራ ማዋል ስለሚፈልጉ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ይረዳሉ። ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች ለወንድሞቻቸው ሲሉ የሚያከናውኑት የደግነት ተግባር “አምላክ [የሰጣቸው] የላቀ ጸጋ” መገለጫ እንደሆነ ተናግሯል። (2 ቆሮ. 9:14፤ 1 ጴጥ. 4:10) ከዚህ አንጻር፣ የታኅሣሥ 1, 1975 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) የተቸገሩ ወንድሞቻችንን ስለማገልገል (የእርዳታ ሥራን ይጨምራል) የሚከተለውን ሐሳብ መስጠቱ የተገባ ነው፦ “ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዚህ ዓይነቱ አገልግሎት ከፍ ያለ ቦታ እንደሚሰጡ ፈጽሞ ልንጠራጠር አይገባም።” በእርግጥም የእርዳታ ሥራ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ‘የቅዱስ አገልግሎት’ ክፍል ነው።—ሮም 12:1, 7፤ 2 ቆሮ. 8:7፤ ዕብ. 13:16
(2 ቆሮንቶስ 9:7) አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ።
የመንግሥቱ ሥራዎች ወጪ የሚሸፈንበት መንገድ
10 አንደኛ፣ ይሖዋን ስለምንወድና “በፊቱ ደስ የሚያሰኙትን ነገሮች” ማድረግ ስለምንፈልግ በፈቃደኝነት መዋጮ እናደርጋለን። (1 ዮሐ. 3:22) ይሖዋ፣ ከልቡ ተነሳስቶ ደስ እያለው በሚሰጥ አገልጋዩ ይደሰታል። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ስለሚሰጡት ስጦታ የጻፈውን ሐሳብ እስቲ እንመርምር። (2 ቆሮንቶስ 9:7ን አንብብ።) አንድ እውነተኛ ክርስቲያን የሚሰጠው ቅር እያለው ወይም ግድ ስለሆነበት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ስጦታ የሚሰጠው ‘በልቡ ስላሰበ’ ወይም ልቡ ስለፈቀደ ነው። በሌላ አባባል ልግስና የሚያደርገው ምን እንደሚያስፈልግና ይህንን ለማሟላት ምን ማድረግ እንደሚችል ካሰበበት በኋላ ነው። “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ” እንዲህ ያለ ሰጪ በይሖዋ ዘንድ ተወዳጅ ነው። አንድ ሌላ ትርጉም “አምላክ መስጠት የሚወዱ ሰዎችን ይወዳል” ይላል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(2 ቆሮንቶስ 9:15) በቃላት ሊገለጽ ለማይችለው ነፃ ስጦታው አምላክ የተመሰገነ ይሁን።
‘በቃላት ሊገለጽ የማይችለው የአምላክ ነፃ ስጦታ’ ግድ ይበላችሁ
2 ጳውሎስ፣ አምላክ ቃል የገባቸው አስደናቂ ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጸሙ ዋስትና የሚሆነው የክርስቶስ ፍጹም መሥዋዕት እንደሆነ ስለሚያውቅ ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:20ን አንብብ።) ‘በቃላት ሊገለጽ የማይችለው ይህ ነፃ ስጦታ’ ይሖዋ በኢየሱስ በኩል የሚያደርግልንን መልካም ነገሮች በሙሉ እንዲሁም የሚያሳየንን ታማኝ ፍቅር ያካትታል። በእርግጥም ስጦታው እጅግ አስደናቂ በመሆኑ የሰው ልጆች ሙሉ በሙሉ በሚረዱት መንገድ መግለጽ አስቸጋሪ ነው። እንዲህ ያለ ልዩ ስጦታ በመቀበላችን ምን ሊሰማን ይገባል? ደግሞስ ከይሖዋ ያገኘነው ስጦታ ረቡዕ፣ መጋቢት 23, 2016 የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር ስንዘጋጅ ምን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል?
(2 ቆሮንቶስ 10:17) “ሆኖም የሚኩራራ በይሖዋ ይኩራራ።”
g99-E 7/8 20-21
መኩራራት ስህተት ነው?
በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “መኩራራት፣ መመካት” ተብሎ የተተረጎመው ከኻውመ የተባለው ግስ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ በሆነ መንገድ ተሠርቶበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ “የሚኩራራ በይሖዋ ይኩራራ” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 10:17) ይህም ይሖዋ አምላካችን በመሆኑ መኩራራትን ማለትም እሱ ባተረፈው መልካም ስም መመካትን ያመለክታል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(2 ቆሮንቶስ 7:1-12) ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እነዚህ ተስፋዎች ስላሉን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤ እንዲሁም አምላክን በመፍራት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርግ። 2 በልባችሁ ውስጥ ቦታ ስጡን። እኛ ማንንም አልበደልንም፤ ማንንም አላበላሸንም፤ ማንንም መጠቀሚያ አላደረግንም። 3 ይህን የምለው ልኮንናችሁ አይደለም። ከዚህ በፊት እንደነገርኳችሁ በልባችን ውስጥ ስለሆናችሁ ብንሞትም ሆነ ብንኖር አብረን ነን። 4 እናንተን በግልጽ ለማናገር ነፃነት ይሰማኛል። በእናንተ በጣም እኮራለሁ። እንዲሁም እጅግ ተጽናንቻለሁ፤ በመከራችንም ሁሉ ደስታዬ ወሰን የለውም። 5 መቄዶንያ በደረስን ጊዜ በሁሉም አቅጣጫ መከራ ደረሰብን እንጂ ሰውነታችን ምንም እረፍት አላገኘም፤ በውጭ ጠብ፣ በውስጥ ፍርሃት ነበረብን። 6 ይሁንና ያዘኑትን የሚያጽናናው አምላክ፣ ቲቶ በመካከላችን በመገኘቱ እንድንጽናና አደረገን፤ 7 የተጽናናነውም እሱ በመካከላችን በመገኘቱ ብቻ ሳይሆን እሱ በእናንተ ምክንያት ባገኘው መጽናኛ ጭምር ነው፤ ተመልሶ በመጣ ጊዜ እኔን ስለመናፈቃችሁ፣ ስለተሰማችሁ ጥልቅ ሐዘንና ለእኔ ስላላችሁ ልባዊ አሳቢነት ነግሮናል፤ ስለዚህ ከበፊቱ ይበልጥ ደስ ብሎኛል። 8 በደብዳቤዬ አሳዝኛችሁ ቢሆን እንኳ በዚህ አልጸጸትም። መጀመሪያ ላይ ብጸጸት እንኳ፣ ደብዳቤው እንድታዝኑ ያደረጋችሁ ለአጭር ጊዜ ብቻ እንደሆነ ስለተረዳሁ 9 አሁን የምደሰተው እንዲያው በማዘናችሁ ሳይሆን ሐዘናችሁ ለንስሐ ስላበቃችሁ ነው። ያዘናችሁት ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ነውና፤ በመሆኑም በእኛ የተነሳ ምንም ጉዳት አልደረሰባችሁም። 10 ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ማዘን ለመዳን የሚያበቃ ንስሐ ያስገኛልና፤ ይህ ደግሞ ለጸጸት አይዳርግም፤ የዚህ ዓለም ሐዘን ግን ሞት ያስከትላል። 11 አምላካዊ በሆነ መንገድ ማዘናችሁ እንዴት ለተግባር እንዳነሳሳችሁ ተመልከቱ! አዎ፣ አቋማችሁን ለማስተካከል እርምጃ እንድትወስዱ አነሳስቷችኋል፤ ደግሞም እንዴት ያለ ቁጣ፣ እንዴት ያለ ፍርሃት፣ እንዴት ያለ ጉጉት፣ እንዴት ያለ ቅንዓት እንዳስገኘ ተመልከቱ! በእርግጥም ስህተታችሁን ለማረም እርምጃ እንድትወስዱ አድርጓችኋል። በዚህ ጉዳይ ንጹሕ መሆናችሁን በሁሉም ረገድ አስመሥክራችኋል። 12 ምንም እንኳ ለእናንተ ብጽፍም የጻፍኩት በደል ለሠራው ወይም በደል ለተፈጸመበት ሰው ብዬ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ለመልእክታችን በጎ ምላሽ ለመስጠት የምታደርጉት ጥረት በእናንተ ዘንድና በአምላክ ፊት ግልጽ ሆኖ እንዲታይ ነው።
ከግንቦት 20-26
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ቆሮንቶስ 11-13
“ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ”
(2 ቆሮንቶስ 12:7) እንዲህ ያሉ አስደናቂ ነገሮች ስለተገለጡልኝ ብቻ ማንም ሰው ለእኔ ከፍ ያለ ግምት ሊኖረው አይገባም። እንዳልታበይ ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ ተሰጠኝ፤ ይህም እንዳልታበይ ዘወትር የሚያሠቃየኝ የሰይጣን መልአክ ነው።
ድክመቶች ቢኖሩንም ብርቱዎች መሆን
አንድ ሌላ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ደግሞ ‘የሥጋ መውጊያ’ የሆነበትን የማያቋርጥ ችግር እንዲያስወግድለት ይሖዋን ጠይቆት ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ ችግር እንዲወገድለት አምላክን ሦስት ጊዜ ለምኖታል። የጳውሎስ ችግር ምንም ይሁን ምን እንደ እሾህ እረፍት ይነሳው ስለነበር በይሖዋ አገልግሎት የሚያገኘውን ደስታ እንዲያጣ አድርጎት ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ይህንን ችግር፣ ማቆሚያ ከሌለው ሥቃይ ወይም ዘወትር በጥፊ ከመመታት ጋር አመሳስሎታል። ይሖዋ ለጳውሎስ ምን መልስ ሰጠው? “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” ብሎታል። ይሖዋ የጳውሎስን የሥጋ መውጊያ አላስወገደለትም። ጳውሎስ ከዚህ ችግር ጋር መታገል የነበረበት ቢሆንም “ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ” ብሏል። (2 ቆሮ. 12:7-10) ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር?
(2 ቆሮንቶስ 12:8, 9) ይህ ነገር ከእኔ እንዲርቅ ጌታን ሦስት ጊዜ ለመንኩት። 9 እሱ ግን “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ምክንያቱም ኃይሌ ፍጹም የሚሆነው በምትደክምበት ጊዜ ነው” አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል በእኔ ላይ እንደ ድንኳን እንዲኖር እጅግ ደስ እያለኝ በድክመቴ እኩራራለሁ።
ይሖዋ “ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስ” ይሰጣቸዋል
17 አምላክ ለጳውሎስ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” የሚል ምላሽ ሰጥቶታል። ጳውሎስም “ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ [“እንደ ድንኳን በእኔ ላይ ያድር ዘንድ፣” NW]፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ” ሊል ችሏል። (2 ቆሮንቶስ 12:9፤ መዝሙር 147:5) በዚህ የተነሳ ከለላ የሚሆነው የአምላክ ብርቱ ኃይል በክርስቶስ በኩል ልክ እንደ ድንኳን በእርሱ ላይ አድሮ ነበር። በዛሬው ጊዜ፣ ይሖዋ በተመሳሳይ መንገድ ለጸሎታችን መልስ ይሰጠናል። ጥበቃውን ልክ እንደ ድንኳን በአገልጋዮቹ ላይ ይዘረጋል።
18 እውነት ነው፣ አንድ ድንኳን ዝናብ እንዳይዘንብ ወይም ነፋስ እንዳይነፍስ ማድረግ አይችልም፤ ይሁንና ከእነዚህ ነገሮች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ይጠብቀናል። በተመሳሳይም እንደ መጠለያ የሚሆንልን “የክርስቶስ ኀይል” መከራ እንዳያጋጥመን ወይም ችግር እንዳይደርስብን አይከላከልልንም። ሆኖም ይህ ዓለም ከሚያመጣቸው ጎጂ ነገሮችና ገዥው ሰይጣን ከሚሰነዝርብን ጥቃት መንፈሳዊ ጥበቃ እንድናገኝ ይረዳናል። (ራእይ 7:9, 15, 16) በመሆኑም ‘ከአንተ እንዲወገድልህ’ ከጠየቅኸው መከራ ጋር እየታገልህ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ የምታደርገውን ትግል እንደሚረዳልህና ‘ለጩኸትህ’ መልስ እንደሚሰጥ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ኢሳይያስ 30:19፤ 2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።”—1 ቆሮንቶስ 10:13፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7
(2 ቆሮንቶስ 12:10) ስለሆነም ስለ ክርስቶስ ስል በድክመት፣ በስድብ፣ በእጦት፣ በስደትና በችግር ደስ እሰኛለሁ። ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና።
‘ለደከመው ኃይል ይሰጣል’
8 ኢሳይያስ 40:30ን አንብብ። ምንም ዓይነት ችሎታ ቢኖረን በራሳችን ጥንካሬ ልናከናውን የምንችለው ነገር ውስን ነው። ይህ ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባ ሐቅ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙ ነገሮችን ማከናወን ይችል የነበረ ቢሆንም የሚፈልገውን ሁሉ እንዳያደርግ የሚያግዱት ነገሮች ነበሩ። ይህን ሁኔታ በተመለከተ ወደ አምላክ ሲጸልይ ያገኘው ምላሽ “ኃይሌ ፍጹም የሚሆነው በምትደክምበት ጊዜ ነው” የሚል ነበር። ጳውሎስ፣ ይሖዋ ምን ሊለው እንደፈለገ ገብቶታል። “ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ” በማለት የተናገረውም ለዚህ ነው። (2 ቆሮ. 12:7-10) ይሁንና ጳውሎስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር?
9 ጳውሎስ ከእሱ በላይ ኃይል ካለው አካል እርዳታ ካላገኘ በቀር ማከናወን የሚችለው ነገር ውስን እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ሐዋርያው በሚደክምበት ጊዜ የሚያስፈልገውን ኃይል የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ሊሰጠው ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ በራሱ ጥንካሬ ፈጽሞ ሊያከናውን የማይችላቸውን ነገሮች እንዲያከናውን የአምላክ መንፈስ ኃይል ይሰጠዋል። ለእኛም እንዲሁ ሊያደርግልን ይችላል። በእርግጥም ይሖዋ፣ ቅዱስ መንፈሱን ሲሰጠን ብርቱዎች መሆን እንችላለን!
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(2 ቆሮንቶስ 12:2-4) የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነ አንድ ሰው አውቃለሁ፤ ይህ ሰው ከ14 ዓመት በፊት ወደ ሦስተኛው ሰማይ ተነጠቀ፤ የተነጠቀው በሥጋ ይሁን ከሥጋ ውጭ አላውቅም፤ አምላክ ግን ያውቃል። 3 አዎ፣ እንዲህ ያለ ሰው አውቃለሁ፤ በሥጋ ይሁን ከሥጋ ውጭ አላውቅም፤ አምላክ ግን ያውቃል፤ 4 ይህ ሰው ወደ ገነት ተነጥቆ በአንደበት ሊገለጹ የማይችሉና ሰው እንዲናገራቸው ያልተፈቀዱ ቃላት ሰማ።
የአንባቢያን ጥያቄዎች
በ2 ቆሮንቶስ 12:2 ላይ የተጠቀሰው “ሦስተኛው ሰማይ” የሚያመለክተው “አዲስ ሰማያት” ተብለው የተገለጹት ኢየሱስ ክርስቶስና 144,000ዎቹ የሚያስተዳድሩትን መሲሐዊ መንግሥት ሳይሆን አይቀርም።—2 ጴጥ. 3:13
“ሦስተኛው ሰማይ” የተባለው ይህ መንግሥት ከፍ ያለ ወይም የላቀ አገዛዝ ስለሆነ ነው።
ጳውሎስ በራእይ “ተነጥቆ” የተወሰደበት “ገነት” (1) ወደፊት ቃል በቃል በምድር ላይ የሚኖረውን ገነት፣ (2) ምድር ገነት በምትሆንበት ጊዜ የሚኖረውንና አሁን ካለው መንፈሳዊ ገነት እጅግ የላቀ የሚሆነውን መንፈሳዊ ገነት እንዲሁም (3) በሰማይ ያለውን “የአምላክ ገነት” የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። ወደፊት በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ሦስቱም በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ይኖራሉ።
(2 ቆሮንቶስ 13:12 ግርጌ) እርስ በርስ በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተለዋወጡ።
it-2-E 177
መሳሳም
‘የተቀደሰ አሳሳም።’ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች “በተቀደሰ አሳሳም” (ሮም 16:16፤ 1ቆሮ 16:20፤ 2ቆሮ 13:12፤ 1ተሰ 5:26) ወይም “በፍቅር እርስ በርስ በመሳሳም” (1ጴጥ 5:14) ሰላምታ ይለዋወጡ ነበር፤ እንዲህ ዓይነት ሰላምታ የሚለዋወጡት ተመሳሳይ ፆታ ያላቸው ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። በመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ዘንድ የተለመደ የነበረው ይህ ሰላምታ፣ የጥንቶቹ ዕብራውያን ከነበራቸው በመሳሳም ሰላምታ የመለዋወጥ ልማድ ጋር ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። ቅዱሳን መጻሕፍት ስለዚህ ሰላምታ ዝርዝር ነገር ባይነግሩንም ክርስቲያኖች “በተቀደሰ አሳሳም” ወይም “በፍቅር እርስ በርስ በመሳሳም” ሰላምታ መለዋወጣቸው በጉባኤው ውስጥ ያለውን ፍቅርና አንድነት የሚያሳይ መሆን አለበት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(2 ቆሮንቶስ 11:1-15) በመጠኑ ምክንያታዊነት ቢጎድለኝ እንድትታገሡኝ እፈልጋለሁ። ደግሞም እየታገሣችሁኝ ነው! 2 በአምላክ ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፤ እኔ ራሴ እንደ አንዲት ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ አቀርባችሁ ዘንድ ለአንድ ባል አጭቻችኋለሁ። 3 ሆኖም እባቡ ሔዋንን በተንኮሉ እንዳታለላት ሁሉ እናንተም አስተሳሰባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ልታሳዩ የሚገባውን ቅንነትና ንጽሕና በሆነ መንገድ እንዳታጡ እፈራለሁ። 4 አንድ ሰው መጥቶ እኛ የሰበክንላችሁን ሳይሆን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክላችሁ ወይም ከተቀበላችሁት መንፈስ የተለየ ዓይነት መንፈስ ቢያመጣ ወይም ከተቀበላችሁት ምሥራች የተለየ ሌላ ምሥራች ቢናገር እንዲህ ያለውን ሰው በቸልታ ታልፉታላችሁ ማለት ነው። 5 እኔ ከእናንተ የተራቀቁ ሐዋርያት በምንም ነገር የማንስ አይመስለኝም። 6 የተዋጣልኝ ተናጋሪ ባልሆን እንኳ እውቀት አይጎድለኝም፤ ይህን በሁሉም መንገድ እንዲሁም በሁሉም ነገር አሳይተናችኋል። 7 ወይስ እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን ዝቅ አድርጌ የአምላክን ምሥራች ለእናንተ ያለዋጋ በደስታ መስበኬ እንደ ኃጢአት ተቆጥሮብኝ ይሆን? 8 እናንተን ለማገልገል ከሌሎች ጉባኤዎች ቁሳዊ እርዳታ በመቀበሌ እነሱን አራቁቻለሁ። 9 ከእናንተ ጋር ሳለሁ ተቸግሬ በነበረበት ጊዜ ከመቄዶንያ የመጡት ወንድሞች የጎደለኝን ነገር በሙሉ በሚገባ ስላሟሉልኝ ለማንም ሸክም አልሆንኩም። አዎ፣ እስካሁን ድረስ በእናንተ ላይ በምንም መንገድ ሸክም አልሆንኩም፤ ወደፊትም ሸክም አልሆንም። 10 የክርስቶስ እውነት በውስጤ እስካለ ድረስ በአካይያ ክልሎች ሁሉ በዚህ ነገር እንዳልኩራራ ምንም ነገር ሊያግደኝ አይችልም። 11 ይህን ያደረግኩት ለምንድን ነው? ስለማልወዳችሁ ነው? እንደምወዳችሁ አምላክ ያውቃል። 12 ይሁንና ከእኛ ጋር እኩል ለመሆን የሚፈልጉትና እኛም ሐዋርያት ነን ብለው የሚኩራሩት ሰዎች ለዚህ የሚሆን መሠረት እንዳያገኙ አሁን እያደረግኩት ያለሁትን ወደፊትም አደርጋለሁ። 13 እንዲህ ያሉት ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን የሚለውጡ ሐሰተኛ ሐዋርያትና አታላይ ሠራተኞች ናቸውና። 14 ይህም ምንም አያስደንቅም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣልና። 15 ስለዚህ አገልጋዮቹም የጽድቅ አገልጋዮች ለመምሰል ራሳቸውን ቢለዋውጡ ምንም አያስገርምም። ሆኖም ፍጻሜያቸው እንደ ሥራቸው ይሆናል።
ከግንቦት 27–ሰኔ 2
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ገላትያ 1-3
“ፊት ለፊት ተቃወምኩት”
(ገላትያ 2:11-13) ይሁን እንጂ ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምኩት፤ ምክንያቱም ግልጽ የሆነ ስህተት ሠርቶ ነበር። 12 የተወሰኑ ሰዎች ከያዕቆብ ዘንድ ከመምጣታቸው በፊት ከአሕዛብ ወገን ከሆኑ ሰዎች ጋር ይበላ ነበር፤ እነሱ ከመጡ በኋላ ግን ከተገረዙት ወገን የሆኑትን በመፍራት ይህን ማድረጉን አቁሞ ራሱን ከአሕዛብ አገለለ። 13 የቀሩት አይሁዳውያንም በዚህ የግብዝነት ድርጊት ከእሱ ጋር ተባበሩ፤ በርናባስም እንኳ በእነሱ የግብዝነት ድርጊት ተሸንፎ ነበር።
ስለ ፍትሕ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት አለህ?
16 ገላትያ 2:11-14ን አንብብ። ጴጥሮስ የሰው ፍርሃት ወጥመድ ሆኖበት ነበር። (ምሳሌ 29:25) ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት በሚገባ ቢያውቅም በኢየሩሳሌም ባለው ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ የተገረዙ አይሁዳውያን ምን ይሉኛል የሚል ፍርሃት አደረበት። በ49 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም በተደረገው ስብሰባ ላይ ተገኝቶ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ በአንጾኪያ ጴጥሮስን በግልጽ የተቃወመው ሲሆን ግብዝነቱንም አጋልጧል። (ሥራ 15:12፤ ገላ. 2:13) ታዲያ ጴጥሮስ የሠራው ስህተት በቀጥታ የሚነካቸው ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን የፍትሕ መጓደል ሲመለከቱ ምን ተሰማቸው? በዚህ ተሰናክለው ይሆን? ጴጥሮስስ በሠራው ስህተት የተነሳ፣ ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸውን መብቶቹን ያጣ ይሆን?
(ገላትያ 2:14) ሆኖም ከምሥራቹ እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ እየተጓዙ እንዳልሆኑ ባየሁ ጊዜ ኬፋን በሁሉም ፊት እንዲህ አልኩት፦ “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ ሳለህ እንደ አይሁዳውያን ሳይሆን እንደ አሕዛብ የምትኖር ከሆነ ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች እንደ አይሁዳውያን ልማድ እንዲኖሩ እንዴት ልታስገድዳቸው ትችላለህ?”
ይሖዋን የሚወዱ ‘ዕንቅፋት የለባቸውም’
12 ጴጥሮስ ሰውን ይፈራ ነበር፤ በዚህም የተነሳ በከፍተኛ ሁኔታ የተደናቀፈባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ ያም ሆኖ ኢየሱስንና ይሖዋን በታማኝነት ማገልገሉን ቀጥሏል። ለምሳሌ፣ ጌታውን ከአንዴም ሦስቴ በሰዎች ፊት ክዶታል። (ሉቃስ 22:54-62) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ጴጥሮስ የተገረዙ አይሁዳውያን ክርስቲያኖችን ከአሕዛብ ከመጡት አማኞች አስበልጦ እንደሚመለከት የሚያሳይ ክርስቲያናዊ ያልሆነ ድርጊት ፈጽሟል። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ በጉባኤው ውስጥ የመደብ ልዩነት ሊታይ እንደማይገባ በግልጽ ተገንዝቦ ነበር። የጴጥሮስ አመለካከት ትክክል አልነበረም። የጴጥሮስ አድራጎት በወንድማማች ማኅበሩ ውስጥ መቃቃር እንዲፈጠር ከማድረጉ በፊት ጳውሎስ ጴጥሮስን ፊት ለፊት ገሥጾታል። (ገላ. 2:11-14) ጴጥሮስ ስሜቱ እጅግ ከመጎዳቱ የተነሳ ለሕይወት የሚያደርገውን ሩጫ አቋርጧል? በፍጹም። ጳውሎስ የሰጠውን ምክር በቁም ነገር ያሰበበት ከመሆኑም ሌላ ምክሩን በተግባር አውሏል እንዲሁም በሩጫው ቀጥሏል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ገላትያ 2:20) እኔ አሁን ከክርስቶስ ጋር በእንጨት ላይ ተቸንክሬአለሁ። ከዚህ በኋላ የምኖረው እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር አንድ ሆኖ የሚኖረው ክርስቶስ ነው። አሁን በሥጋ የምኖረውን ሕይወት የምኖረው በወደደኝና ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ በሰጠው በአምላክ ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው።
“ብዙ መከራ” ቢኖርም አምላክን በታማኝነት አገልግሉ
20 ስውር ስለሆኑ ጥቃቶችስ ምን ማለት ይቻላል? ለምሳሌ ያህል፣ የተስፋ መቁረጥ ስሜትን መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ለማድረግ ከሚረዱን በጣም ጠቃሚ ዘዴዎች አንዱ በቤዛው ዝግጅት ላይ ማሰላሰል ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም ያደረገው ይህንኑ ነው። አንዳንድ ጊዜ፣ ጎስቋላ ሰው እንደሆነ ይሰማው ነበር። ያም ቢሆን ክርስቶስ የሞተው ፍጹም ለሆኑ ሰዎች ሳይሆን ለኃጢአተኞች እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ጳውሎስም ከእነዚህ ኃጢአተኞች አንዱ እንደሆነ ያውቃል። እንዲያውም “አሁን በሥጋ የምኖረውን ሕይወት የምኖረው በወደደኝና ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ በሰጠው በአምላክ ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው” ሲል ጽፏል። (ገላ. 2:20) በእርግጥም ጳውሎስ በቤዛው ላይ እምነት ነበረው። ቤዛው በግለሰብ ደረጃ እሱን እንደሚጠቅመው ተሰምቶት ነበር።
21 አንተም ቤዛውን ይሖዋ በግልህ እንደሰጠህ ስጦታ አድርገህ የምትመለከተው ከሆነ በእጅጉ ትጠቀማለህ። እርግጥ ይህ ሲባል፣ የሚሰማህ የተስፋ መቁረጥ ስሜት በቅጽበት ይጠፋል ማለት አይደለም። አንዳንዶቻችን አዲሱ ዓለም ውስጥ እስክንገባ ድረስ፣ ሰይጣን ከሚጠቀምበት እንዲህ ካለው ስውር ጥቃት ጋር መታገል ይኖርብን ይሆናል። ሆኖም ሽልማቱን የሚያገኙት ተስፋ ሳይቆርጡ የጸኑ እንደሆኑ አስታውስ። የአምላክ መንግሥት ሰላምን ወደሚያሰፍንበትና ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ ወደሚያደርግበት ክብራማ ጊዜ በጣም ቀርበናል። በብዙ መከራዎች ውስጥ ማለፍ ቢኖርብህም እንኳ ወደዚህ መንግሥት ለመግባት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።
(ገላትያ 3:1) እናንተ ማስተዋል የጎደላችሁ የገላትያ ሰዎች! ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በእንጨት ላይ ተቸንክሮ ፊት ለፊት ያያችሁት ያህል በዓይነ ሕሊናችሁ ተስሎ ነበር፤ ታዲያ አሁን አፍዝ አደንግዝ ያደረገባችሁ ማን ነው?
it-1-E 880
ለገላትያ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ
ጳውሎስ “እናንተ ማስተዋል የጎደላችሁ የገላትያ ሰዎች” ሲል በገላትያ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኙትን ከጋሊክ ዘር የመጡ ሰዎች ብቻ ለይቶ መጥቀሱ አይደለም። (ገላ 3:1) ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ በገላትያ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ ለሚገኙና የአይሁድን እምነት የሚያራምዱ ሰዎች ተጽዕኖ እንዲያሳድሩባቸው ለፈቀዱ አንዳንድ ክርስቲያኖች ተግሣጽ መስጠቱ ነበር፤ ይህን እምነት የሚያራምዱት አይሁዳውያን፣ አዲሱ ቃል ኪዳን ባስገኘው ‘በእምነት አማካኝነት የሚገኝ ጽድቅ’ ፋንታ የሙሴን ሕግ በመከተል የራሳቸውን ጽድቅ ለመመሥረት እየሞከሩ ነበር። (2:15 እስከ 3:14፤ 4:9, 10) ጳውሎስ በጻፈላቸው ‘በገላትያ ባሉት ጉባኤዎች’ (1:2) ውስጥ፣ አይሁዳዊ ዘር ያላቸውም ሆነ አይሁዳዊ ያልሆኑ ክርስቲያኖች ይገኙ ነበር፤ አይሁዳዊ ካልሆኑት ክርስቲያኖች መካከል ወደ ይሁዲነት የተለወጡ የተገረዙ ሰዎችና ያልተገረዙ አሕዛብ ይገኙበታል፤ ከእነዚህ አንዳንዶቹ ደግሞ የኬልቲክ ዝርያ ያላቸው እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም። (ሥራ 13:14, 43፤ 16:1፤ ገላ 5:2) እነዚህ ሁሉ ሰዎች የሚኖሩት ገላትያ ተብሎ በሚጠራው ክልል ውስጥ ስለነበር የገላትያ ክርስቲያኖች ተብለው ተጠርተዋል። ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው በዚህ የሮም ክልል ደቡባዊ ክፍል ለሚኖሩና በደንብ ለሚያውቃቸው ክርስቲያኖች እንጂ በሰሜናዊው ክፍል ለሚገኙትና ጨርሶ ለማያውቃቸው ሰዎች አይደለም፤ ጳውሎስ ወደዚህ ክልል ሄዶ የሚያውቅ እንኳ አይመስልም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ገላትያ 2:11-21) ይሁን እንጂ ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምኩት፤ ምክንያቱም ግልጽ የሆነ ስህተት ሠርቶ ነበር። 12 የተወሰኑ ሰዎች ከያዕቆብ ዘንድ ከመምጣታቸው በፊት ከአሕዛብ ወገን ከሆኑ ሰዎች ጋር ይበላ ነበር፤ እነሱ ከመጡ በኋላ ግን ከተገረዙት ወገን የሆኑትን በመፍራት ይህን ማድረጉን አቁሞ ራሱን ከአሕዛብ አገለለ። 13 የቀሩት አይሁዳውያንም በዚህ የግብዝነት ድርጊት ከእሱ ጋር ተባበሩ፤ በርናባስም እንኳ በእነሱ የግብዝነት ድርጊት ተሸንፎ ነበር። 14 ሆኖም ከምሥራቹ እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ እየተጓዙ እንዳልሆኑ ባየሁ ጊዜ ኬፋን በሁሉም ፊት እንዲህ አልኩት፦ “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ ሳለህ እንደ አይሁዳውያን ሳይሆን እንደ አሕዛብ የምትኖር ከሆነ ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች እንደ አይሁዳውያን ልማድ እንዲኖሩ እንዴት ልታስገድዳቸው ትችላለህ?” 15 በትውልዳችን አይሁዳውያን እንጂ ከአሕዛብ ወገን እንደሆኑት ኃጢአተኞች ያልሆንነው እኛ፣ 16 አንድ ሰው የሚጸድቀው ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ እንደሆነ እንገነዘባለን። ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን በክርስቶስ በማመን እንድንጸድቅ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል፤ ምክንያቱም ሕግን በመጠበቅ መጽደቅ የሚችል ሰው የለም። 17 እኛ በክርስቶስ አማካኝነት መጽደቅ በመፈለጋችን እንደ ኃጢአተኞች ተደርገን ከታየን፣ ታዲያ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነው ማለት ነው? በጭራሽ! 18 በአንድ ወቅት እኔው ራሴ ያፈረስኳቸውን እነዚያኑ ነገሮች መልሼ የምገነባ ከሆነ ሕግ ተላላፊ መሆኔን አሳያለሁ ማለት ነው። 19 ለአምላክ ሕያው መሆን እችል ዘንድ በሕጉ በኩል ለሕጉ ሞቻለሁና። 20 እኔ አሁን ከክርስቶስ ጋር በእንጨት ላይ ተቸንክሬአለሁ። ከዚህ በኋላ የምኖረው እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር አንድ ሆኖ የሚኖረው ክርስቶስ ነው። አሁን በሥጋ የምኖረውን ሕይወት የምኖረው በወደደኝና ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ በሰጠው በአምላክ ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው። 21 የአምላክን ጸጋ ወደ ጎን ገሸሽ አላደርግም፤ ጽድቅ የሚገኘው በሕግ አማካኝነት ከሆነማ ክርስቶስ የሞተው እንዲያው በከንቱ ነው።