ይሖዋን የሚያስከብር አስደሳች ሠርግ
ዌልሽ እና ኤልዚ በ1985 በደቡብ አፍሪካ ስዌቶ ተጋቡ። አሁን ዚንዚ ከምትባል ሴት ልጃቸው ጋር አንዳንዴ የሠርጋቸውን አልበም እየተመለከቱ ያንን አስደሳች ቀን በትዝታ ይቃኛሉ። ዚንዚ ፎቶግራፉን በመመልከት በሠርጉ ላይ ተገኝነተው የነበሩትን ሰዎች ማንነት ለይቶ መናገር የሚያስደስታት ሲሆን በተለይ ደግሞ እናቷ እንደዚያ አምሮባት ለብሳ የተነሳቻቸውን ፎቶግራፎች ማየት ትወዳለች።
የሠርጉ ሥነ ሥርዓት የጀመረው በስዌቶ የሕዝብ አዳራሽ በተሰጠ የጋብቻ ንግግር ነው። ከዚያም ክርስቲያን ወጣቶች አራት ቡድን ሆነው እየተቀባበሉ ለአምላክ የውዳሴ መዝሙር ዘመሩ። ቀጥሎ የመንግሥቱ ጣዕመ ዜማ ዝግ ባለ መጠን ተከፍቶ እየተሰማ እንግዶች የተዘጋጀውን ምግብ ተመገቡ። የአልኮል መጠጥ አልቀረበም እንዲሁም ጆሮ የሚያደነቁር ሙዚቃም ሆነ ጭፈራ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እንግዶቹ እርስ በርስ በመጫወትና ሙሽሮቹን እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት አስደሳች ጊዜ አሳልፈዋል። በአጠቃላይ የሠርጉ ሥነ ሥርዓት የፈጀው ሦስት ሰዓት ገደማ ነው። ሬመንድ የተባለ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ “ምንጊዜም የማይረሳ ጥሩ ትዝታ ጥሎብኝ ያለፈ ሠርግ ነው” በማለት ገልጿል።
ዌልሽ እና ኤልዚ በተጋቡበት ወቅት ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ፈቃደኛ ሠራተኞች ነበሩ። አቅማቸው የሚፈቅደው ቀለል ያለ ዝግጅት ማድረግ ነበር። አንዳንድ ክርስቲያኖች ድል ያለ ሠርግ መደገስ የሚያስከትለውን ወጪ ለመሸፈን ሲሉ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን አቋርጠው ሰብዓዊ ሥራ ለመያዝ መርጠዋል። ይሁን እንጂ ዌልሽ እና ኤልዚ ልከኛ ሠርግ ለማዘጋጀት በመምረጣቸው ምንም አልተፀፀቱም፤ ምክንያቱም ዚንዚ እስከተወለደችበት ጊዜ ድረስ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አምላክን ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ አስችሏቸዋል።
ይሁንና ሙሽሮች በሠርጋቸው ላይ ዓለማዊ ዘፈንና ጭፈራ እንዲኖር ቢመርጡስ? የወይን ጠጅ ወይም ሌሎች የአልኮል መጠጦች እንዲቀርቡ ቢወስኑስ? ድል ያለ ሠርግ ለመደገስ የሚያስችል አቅም ቢኖራቸውስ? ዝግጅቱ አምላክን ለሚያመልኩ ሰዎች ጥቅም የሚያስገኝ አስደሳች ጊዜ እንደሚሆን ማረጋገጥ የሚችሉት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” የሚል ትእዛዝ ስለሚሰጥ እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ረጋ ብሎ ማጤን ያስፈልጋል።—1 ቆሮንቶስ 10:31
ፈንጠዝያን ማስወገድ
ሠርግ ከተባለ የደስታ ጊዜ እንደሚሆን የታወቀ ነው። ሆኖም ወደ ሌላኛው ጽንፍ መሄድና ገደብ የለሽ ፈንጠዝያ እንዲኖር ማድረግ የባሰ አደገኛ ነው። የይሖዋ ምሥክር ባልሆኑ በብዙ ሰዎች ሠርግ ላይ አምላክን የማያስከብሩ ነገሮች ይደረጋሉ። ለምሳሌ ያህል እስኪሰክሩ ድረስ አልኮል መጠጣት የተለመደ ነው። የሚያሳዝነው እንዲህ ያለው ነገር በአንዳንድ ክርስቲያኖች ሠርግ ላይ መታየቱ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ብዙ መጠጣት ለፍላፊ ያደርጋል’ ሲል ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 20:1 የ1980 ትርጉም ) “ለፍላፊ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ቃል “ከፍተኛ ሁካታን” ያመለክታል። የአልኮል መጠጥ አንድን ሰው ለፍላፊ የሚያደርገው ከሆነ አንድ ላይ የተሰበሰቡ ብዙ ሰዎች የአልኮል መጠጥ በብዛት ሲጠጡ ምን ሊከሰት እንደሚችል አስቡት! ይህን የመሰሉ አጋጣሚዎች መጽሐፍ ቅዱስ “ስካር፣ ዘፋኝነትና [“ፈንጠዝያና፣” NW ] ይህንም የሚመስል” ሲል ወደ ሚዘረዝራቸው ‘የሥጋ ሥራዎች’ ቀስ በቀስ ሊለወጡ እንደሚችሉ ግልጽ ነው። እነዚህን ድርጊቶች የፈጸመ ማንኛውም ግለሰብ ንስሐ የማይገባ ከሆነ በአምላክ መንግሥት ግዛት ሥር የሚገኘውን የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ብቁ አይሆንም።—ገላትያ 5:19-21
“ፈንጠዝያ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ትንሽ ሞቅ ያላቸው ወጣቶች እያፏጩ፣ እየጨፈሩና እየዘፈኑ ለሰልፍ የወጡበትን ሁከት የበዛበት አውራ ጎዳና ለማመልከት ተሠርቶበታል። በሠርጉ ላይ የአልኮል መጠጥ እንደልብ ከቀረበና ጆሮ የሚያደነቁር ሙዚቃና ቅጥ ያጣ ጭፈራ ካለ ሠርጉ ወደ ፈንጠዝያ እንዳይለወጥ በጣም ያሰጋል። በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ደካማ የሆኑ ሰዎች እንደዚህ ባለው ሁኔታ ሥር በቀላሉ ሊፈተኑና ‘ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት ወይም ቁጣ’ የመሳሰሉ ሌሎች የሥጋ ሥራዎች ወደ መፈጸም ሊገፋፉ ይችላሉ። እነዚህ የሥጋ ሥራዎች በአንድ ክርስቲያናዊ ሠርግ ላይ ጥቁር ነጥብ እንዳይጥሉ ለመከላከል ምን ሊደረግ ይችላል? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ ስለሚገኝ አንድ ሠርግ እንመርምር።
ኢየሱስ የተገኘበት ሠርግ
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በገሊላ ቃና በተደረገ አንድ ሠርግ ላይ እንዲገኙ ተጋብዘው ነበር። እነርሱም ግብዣውን ተቀብለው በሠርጉ ላይ የተገኙ ሲሆን እንዲያውም ኢየሱስ ሠርጉ አስደሳች እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ አበርክቷል። የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜ በጣም ጥራት ያለውን የወይን ጠጅ ተአምራዊ በሆነ መንገድ አቀረበላቸው። ኢየሱስ በዋለለት ውለታ በጣም ተደስቶ የነበረው ሙሽራና ቤተሰቦቹ ከሠርጉ የተረፈውን የወይን ጠጅ ሠርጉ ካለፈ በኋላም ለተወሰነ ጊዜ እንደሚጠቀሙበት ምንም ጥርጥር የለውም።—ዮሐንስ 2:3-11
ኢየሱስ ከተገኘበት ከዚህ ሠርግ በርካታ ቁም ነገሮችን መገብየት እንችላለን። በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ሳይጠሩ በሠርጉ ግብዣ ላይ አልተገኙም። ተጋብዘው እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (ዮሐንስ 2:1, 2) በተመሳሳይም ስለ ሠርግ ግብዣ በሚገልጹ ሁለት ምሳሌዎች ላይ ኢየሱስ እንግዶቹ በሠርጉ ላይ የተገኙት ስለተጋበዙ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተናግሯል።—ማቴዎስ 22:2-4, 8, 9፤ ሉቃስ 14:8-10
በአንዳንድ አገሮች በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለ ማንም ሰው በአንድ የሠርግ ግብዣ ላይ እንዲገኝ ቢጋበዝም ባይጋበዝም መገኘት ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ነገር የገንዘብ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ሀብታም ያልሆኑ ሙሽሮች ቁጥሩ በውል ላልተወሰነ ሕዝብ የሚበቃ ምግብና መጠጥ ለማዘጋጀት ሲሉ ዕዳ ውስጥ ሊዘፈቁ ይችላሉ። በመሆኑም ክርስቲያን ሙሽሮች የተወሰነ ቁጥር ላለው እንግዳ መጠነኛ ግብዣ ለማዘጋጀት ቢወስኑ ያልተጋበዙ ክርስቲያኖች ውሳኔያቸውን ሊረዱላቸውና ሊያከብሩላቸው ይገባል። በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን ውስጥ ያገባ አንድ ሰው 200 እንግዶች በሠርጉ ላይ እንዲገኙለት መጥራቱን ያስታውሳል። ይሁን እንጂ 600 ሰዎች በሠርጉ ላይ በመገኘታቸው የተዘጋጀው ምግብ ወዲያው አለቀ። ሳይጠሩ ከተገኙት ሰዎች መካከል በሠርጉ ዕለት በአውቶቡስ እየተዘዋወሩ ኬፕ ታውንን ሲጎበኙ የነበሩ ጎብኚዎች ይገኙበታል። የቡድኑ አስጎብኚ የሴቷ ሙሽራ የሩቅ ዘመድ ስለነበረ ሙሽራዋን ወይም ሙሽራውን ሳያማክር ሲያስጎበኛቸው የነበሩትን ሁሉ ይዞ የመገኘት መብት እንዳለው ተሰምቶት ነበር!
አንድ እውነተኛ የኢየሱስ ተከታይ ማንኛውም ሰው መገኘት እንደሚችል በግልጽ ካልተነገረ በስተቀር ባልተጠራበት የሠርግ ግብዣ ላይ ተገኝቶ ለተጠሩ እንግዶች የተዘጋጀውን ምግብና መጠጥ ከመብላትና ከመጠጣት ይቆጠባል። ሳይጠሩ ለመሄድ የሚጓጉ ሰዎች ‘በዚህ የሠርግ ግብዣ ላይ መገኘቴ ለአዲሶቹ ተጋቢዎች ፍቅር እንደሌለኝ አያሳይምን? በሌሎች ላይ ችግር ልፈጥርና ከዝግጅቱ ሊያገኙት የሚችሉትን ደስታ እንዲያጡ ምክንያት ልሆን አልችልምን?’ ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ይገባቸዋል። የሰው ችግር የሚገባው አንድ ክርስቲያን ለምን አልተጋበዝኩም ብሎ ከመቀየም ይልቅ በፍቅር ተገፋፍቶ ሙሽሮቹን እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እንዲሁም ይሖዋ እንዲባርካቸው ያለውን መልካም ምኞት የሚገልጽ መልእክት መላክ ይችላል። እንዲያውም በሠርጋቸው ዕለት ያገኙትን ደስታ ከፍ ለማድረግ ሲል ለሙሽሮቹ ስጦታ ለመላክ ሊያስብ ይችል ይሆናል።—መክብብ 7:9፤ ኤፌሶን 4:28
በኃላፊነት የሚጠየቀው ማን ነው?
አፍሪካ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች በእድሜ ትልቅ የሆኑ ዘመዶች ሠርጉን ለመደገስ ኃላፊነት መውሰዳቸው የተለመደ ጉዳይ ነው። ሠርጉን ለመደገስ ከሚያስፈልጋቸው ወጪ ስለሚገላግላቸው ተጋቢዎቹ ለዚህ በጣም አመስጋኝ ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም አንድ ችግር ቢከሰት በኃላፊነት ከመጠየቅ እንደሚያድናቸው ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ተጋቢዎቹ ዘመዶቻቸው በቅን ልቦና ተነሳስተው የሚዘረጉላቸውን ማንኛውንም ዓይነት እርዳታ ከመቀበላቸው በፊት የግል ፍላጎታቸውን የሚያከብሩላቸው መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።
ኢየሱስ “ከሰማይ የወረደ” የአምላክ ልጅ ቢሆንም እንኳን በቃና በተዘጋጀው ሠርግ ላይ ኃላፊነት ወስዶ አብዛኛውን ነገር እንደተቆጣጠረ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም። (ዮሐንስ 6:41) ከዚህ ይልቅ አንድ ሌላ ሰው ‘አሳዳሪ’ ሆኖ እንዲሠራ የተሾመ መሆኑን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይገልጽልናል። (ዮሐንስ 2:8) ይህ ሰው በበኩሉ ለአዲሱ የቤተሰብ ራስ ማለትም ለሙሽራው ተጠያቂ ነበር።—ዮሐንስ 2:9, 10
ክርስቲያን የሆኑ ዘመዶች በአምላክ የተሾመውን የአዲሱን ቤተሰብ ራስ ማክበር አለባቸው። (ቆላስይስ 3:18-20) በሠርጉ ላይ ስለሚከናወኑት ነገሮች ኃላፊነት ሊወስድ የሚገባው እሱ ነው። የሚቻል ከሆነ ሙሽራው የሙሽራይቱን፣ የወላጆቹንና የአማቾቹን ፍላጎት በማስተናገድ ረገድ ምክንያታዊ መሆኑን ማሳየት እንዳለበት የታወቀ ነው። ያም ሆኖ ዘመዶች ከተጋቢዎቹ ፍላጎት የሚቃረን ዝግጅት ካላደረግን ብለው ካስቸገሩ ተጋቢዎቹ በዚህ በኩል የእነሱን ድጋፍ እንደማይቀበሉ አክብሮት በተሞላበት መንገድ ሊያስረዷቸውና ልከኛ በሆነ ወጪ የራሳቸውን ዝግጅት ማድረግ ሊኖርባቸው ይችላል። በዚህ መንገድ መጥፎ ትዝታ ሊጥሉባቸው የሚችሉ ነገሮች እንዳይከሰቱ ማድረግ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በአፍሪካ በተደረገ አንድ ክርስቲያናዊ ሠርግ ላይ አስተናባሪ ሆኖ የሠራው አንድ የማያምን ዘመድ ለሞቱት ቅድመ አያቶች ክብር ሲባል ጽዋቸውን እንዲያነሱ የሠርጉን ታዳሚዎች ጋብዟል!
አንዳንድ ጊዜ የሠርጉ ሥነ ሥርዓት ከመጠናቀቁ በፊት ሙሽሮቹ ወደ ጫጉላ ሽርሽር ይሄዳሉ። እንደዚህ ባለው ጊዜ ሙሽራው የመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች በሚገባ የሚያስጠብቁና ሥነ ሥርዓቱ በተገቢው ሰዓት እንዲጠናቀቅ የሚቆጣጠሩ ሰዎች በኃላፊነት መመደብ ይኖርበታል።
በደንብ የታሰበበት ዕቅድ እና ሚዛናዊነት
መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተገኘበትን ሠርግ ግብዣ ብሎ ስለጠራው በጣም ጥሩ ጥሩ ምግቦች በብዛት ቀርበው እንደነበር ግልጽ ነው። የወይን ጠጅም በብዛት እንደነበረ ተገልጿል። ተስማሚ ሙዚቃና ሥርዓታማ ጭፈራ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም ይህ የአይሁድ ማኅበራዊ ኑሮ የተለመደ ገጽታ ነበር። ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ በተናገረው የታወቀ ምሳሌ ላይ ይህንን ጠቁሟል። በታሪኩ ውስጥ የተጠቀሰው ባለጸጋ አባት ንስሐ በገባው ልጁ መመለስ በጣም ስለተደሰተ “እንብላም ደስም ይበለን” ብሎ ነበር። ግብዣው ላይ “የመሰንቆና የዘፈን ድምፅ” እንደነበረም ኢየሱስ ገልጿል።—ሉቃስ 15:23, 25
ይሁን እንጂ በቃና በተዘጋጀው ሠርግ ላይ ሙዚቃና ጭፈራ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ የጠቀሰው ነገር የለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሠርግ በዘገበው በየትኛውም ታሪክ ላይ ጭፈራ መኖሩ አልተገለጸም። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በኖሩት የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ዘንድ ጭፈራ ለማዳመቂያ ያህል የሚደረግ እንጂ የሠርጉ አብይ ገጽታ የነበረ አይመስልም። ከዚህ ምን ልንማር እንችላለን?
በአፍሪካ አንዳንድ ክርስቲያኖች በጠሩት የሠርግ ግብዣ ላይ ከፍተኛ ድምፅ ያላቸው ኤሌክትሮኒክስ የድምፅ መሣሪያዎችን ተጠቅመዋል። ሙዚቃው በጣም ከመጮኹ የተነሳ ተጋባዦች እንደልብ እርስ በርሳቸው መነጋገር አልቻሉም። አንዳንድ ጊዜ በድግሱ ላይ ምግብ አንሶ ጭፈራው ግን ከቁጥጥር ውጪ ሲሆን ይስተዋላል። እንደዚህ ያሉ ድግሶችን የሠርግ ግብዣ ከማለት ይልቅ ለጭፈራ የተዘጋጁ ፓርቲዎች ማለቱ ይቀላል። ከዚህ በተጨማሪ በጣም ጮክ ብሎ የሚሰማው ሙዚቃ ብዙውን ጊዜ ሳይጠሩ ዘው ብለው የሚገቡ ችግር ፈጣሪ ሰዎችን ይስባል።
መጽሐፍ ቅዱስ በዘገባቸው የሠርግ ድግሶች ላይ ሙዚቃና ጭፈራ እንደነበረ ጎልቶ የተጠቀሰ ነገር አለመኖሩ ይሖዋን የሚያስከብር ሠርግ የማዘጋጀት ዕቅድ ላላቸው ተጋቢዎች ይህ ጥሩ መመሪያ ሊሆንላቸው አይገባም? እንዲያውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ አፍሪካ በሚደረጉ በአንዳንድ የሠርግ ድግሶች ላይ ሚዜ እንዲሆኑ የተመረጡ ክርስቲያን ወጣቶች ከሙሽሮቹ ጋር በመሆን ለሚያሳዩት ጭፈራ በጣም ውስብስብ የሆኑ የዳንስ ዓይነቶች በመለማመድ ረጅም ሰዓት ያጠፋሉ። ወራት በሚፈጀው በዚህ ልምምድ ይህ ነው የማይባል ጊዜ አሳልፈዋል። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች በስብከቱ ሥራ፣ የግል ጥናትና ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን በመሳሰሉ ‘ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች’ ለመካፈል ‘ጊዜ መዋጀት’ ያስፈልጋቸዋል።—ኤፌሶን 5:16፤ ፊልጵስዩስ 1:10
ኢየሱስ በተአምር ከለወጠው የወይን ጠጅ መጠን አንጻር ሲታይ በቃና የተደረገው ሠርግ ትልቅ ይመስላል። ይሁን እንጂ ዝግጅቱ ሁከት የበዛበትና በአንዳንድ የአይሁድ ሠርጎች ላይ እንደሚስተዋለው ተጋባዦቹ የአልኮል መጠጥ ከልክ በላይ እንዳልጠጡ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዮሐንስ 2:10) እንዴት? ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ተገኝቶ ነበር። ‘ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡ ጋር አትቀመጥ’ የሚለውን አምላክ ስለ መጥፎ ጓደኝነት የሰጠውን ትእዛዝ ለመጠበቅ ከማንም ይበልጥ ጠንቃቃ ነበር።—ምሳሌ 23:20፣ የ1980 ትርጉም
ስለዚህ ተጋቢዎቹ በሠርጋቸው ላይ የወይን ጠጅ ወይም ሌሎች የአልኮል መጠጦች እንዲኖሩ የሚወስኑ ከሆነ ኃላፊነት ያላቸው ግለሰቦች በጥብቅ እንዲቆጣጠሩት ማድረግ አስፈላጊ ነው። ሙዚቃ እንዲኖር ከወሰኑም ተስማሚ የሆኑ ጣዕመ ዜማዎችን ራሳቸው መርጠው የድምፁን መጠን የሚቆጣጠር አንድ ሰው በኃላፊነት መመደብ አለባቸው። እንግዶች እንዲቆጣጠሩትና አጠያያቂ የሆኑ ዘፈኖች እንዲዘፈኑ እንዲያደርጉ ወይም የድምፁን መጠን ከልክ በላይ እንዲለቁት መፍቀድ አይገባም። ጭፈራ የሚኖር ከሆነ ሥርዓት ባለውና ዝግ ባለ የድምፅ መጠን ማድረግ ይቻላል። የማያምኑ ዘመዶች ወይም ያልጎለመሱ ክርስቲያኖች የብልግና ወይም የጾታ ስሜት የሚያነሣሡ የዳንስ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ቢጀምሩ ሙሽራው ሙዚቃው እንዲለወጥ ማድረግ ወይም ዳንሱ እንዲያቆም በዘዴ መጠየቅ ሊኖርበት ይችላል። ካልሆነ ሠርጉ ቅጥ አጥቶ ወደ ረብሻ ሊለወጥና ለአንዳንዶች የመሰናከያ ምክንያት ሊሆን ይችላል።—ሮሜ 14:21
ብዙ ክርስቲያን የወንድ ሙሽሮች አንዳንድ ዘመናዊ የዳንስ ዓይነቶች፣ ጆሮ የሚያደነቁሩ ሙዚቃዎችና በገፍ የሚቀርቡ የአልኮል መጠጦች ችግር ማስከተላቸው እንደማይቀር በመገንዘብ እነዚህ ነገሮች በሠርጋቸው ላይ እንዳይኖሩ ወስነዋል። ይህን የመሰለ ውሳኔ ያደረጉ አንዳንድ ወንድሞች ትችት ደርሶባቸዋል። ይሁን እንጂ በአምላክ ቅዱስ ስም ላይ አንዳች ነቀፋ እንዳይከሰት ለመከላከል ባላቸው ፍላጎት የወሰዱት ይህ እርምጃ ሊያስመሰግናቸው ይገባል። በሌላ በኩል አንዳንድ የወንድ ሙሽሮች ተገቢ የሆኑ የሙዚቃ ዓይነቶች እንዲኖሩ፣ በተወሰነ ጊዜም ጭፈራ እንዲኖርና ከልክ ያላለፈ የአልኮል መጠጥ እንዲኖር ዝግጅት አድርገዋል። ያም ሆነ ይህ በሠርጉ ላይ እንዲኖር ለፈቀደው ነገር በኃላፊነት የሚጠየቀው የወንድ ሙሽራው ነው።
በአፍሪካ አንዳንድ ጉልምስና የጎደላቸው ሰዎች ሥርዓታማ የሆነውን የክርስቲያኖች ሠርግ ከቀብር ሥነ ሥርዓት ተለይቶ አይታይም በማለት ያጣጥላሉ። ሆኖም ይህ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት አይደለም። ኃጢአተኛ የሥጋ ሥራዎች ጊዜያዊ ደስታ ያስገኙ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በክርስቲያኖች ኅሊና ላይ ጠባሳ እንዲሁም በአምላክ ስም ላይ ነቀፋ ጥለው ያልፋሉ። (ሮሜ 2:24) በሌላ በኩል ግን የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እውነተኛ ደስታ ያስገኛል። (ገላትያ 5:22) ብዙ ክርስቲያን ባልና ሚስቶች አስደሳችና “በአንዳች ነገር ማሰናከያ” የማይጥል የነበረውን ሠርጋቸውን መለስ ብለው ሲያስቡ ልባቸው በደስታ ይሞላል።—2 ቆሮንቶስ 6:3
ዌልሽ እና ኤልዚ የማያምኑ ዘመዶቻቸው ሠርጋቸው ላይ በእንግድነት ከተገኙ በኋላ የሰጧቸው ብዙ አስደሳች አስተያየቶች እስከ አሁን ትዝ ይሏቸዋል። አንድ ዘመዳቸው እንዲህ ሲል አስተያየት ሰጥቷል:- “ጩኸት በበዛባቸው የዘመኑ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች ላይ መገኘት በጣም ስልችት ብሎናል። እንዲህ ባለ ለዛ ያለው ሠርግ ላይ መገኘታችን አስደስቶናል።”
ከሁሉም በላይ ደግሞ አስደሳችና ሥርዓታማ የሆኑ ክርስቲያናዊ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች የጋብቻ መሥራች ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ክብር ያመጣሉ።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የሠርግ ግብዣን በተመለከተ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነገሮች
• አንድ የማያምን ዘመዳችሁ ንግግር እንዲያደርግ የምትጋብዙ ከሆነ በንግግሩ ጣልቃ ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ልማዶችን እንደማይናገር እርግጠኞች ናችሁን?
• ሙዚቃ የሚኖር ከሆነ ተገቢ የሆኑ ዘፈኖችን ብቻ መርጣችኋልን?
• የሙዚቃው የድምፅ መጠንስ ልከኛ ነው?
• ጭፈራ እንዲኖር የምትፈልጉ ከሆነ ሥርዓት ባለው መንገድ ይደረጋል?
• የአልኮል መጠጥ የሚቀርበው በልክ ብቻ ነው?
• ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች በአግባብ መዳረሱን ይቆጣጠራሉ?
• የግብዣው ሥነ ሥርዓት የሚጠናቀቅበትን ምክንያታዊ የሆነ ሰዓት ወስናችኋል?
• ሁሉ ነገር በሥርዓት መካሄዱን እስከ መጨረሻ ድረስ የሚከታተሉ ኃላፊነት የተሰጣቸው ወንድሞች ይገኛሉ?