የጥናት ርዕስ 2
“አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ”
“ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።”—ሮም 12:2
መዝሙር 88 መንገድህን አሳውቀኝ
ማስተዋወቂያa
1-2. ከተጠመቅን በኋላ ምን ማድረጋችንን መቀጠል ይኖርብናል? አብራራ።
ቤትህን የምታጸዳው በየስንት ጊዜው ነው? በዚህ ቤት መኖር ከመጀመርህ በፊት ቤቱን በደንብ እንዳጸዳኸው ምንም ጥያቄ የለውም። ይሁንና ከዚያ በኋላ ችላ ብትለውስ? ወዲያውኑ መልሶ መቆሸሹ አይቀርም። ቤትህ ምንጊዜም እንዳማረበት እንዲቆይ አዘውትረህ ማጽዳት ይኖርብሃል።
2 ከአስተሳሰባችንና ከባሕርያችን ጋር በተያያዘም ቀጣይነት ያለው ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። ከመጠመቃችን በፊት “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን [ለማንጻት]” ስንል በሕይወታችን ውስጥ አስፈላጊውን ለውጥ እንዳደረግን ምንም ጥያቄ የለውም። (2 ቆሮ. 7:1) ሆኖም አሁንም ቢሆን፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘እየታደስን እንድንሄድ’ የሰጠውን ምክር መከተል ይኖርብናል። (ኤፌ. 4:23) ይሁንና በቀጣይነት ጥረት ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? የዚህ ዓለም ቆሻሻ ወዲያውኑ ሊበክለን ስለሚችል ነው። በይሖዋ ፊት እንዳማረብን ለመኖር ከፈለግን አስተሳሰባችንን፣ ባሕርያችንንና ምኞታችንን አዘውትረን መመርመር ይኖርብናል።
‘አእምሯችሁን ማደሳችሁን’ ቀጥሉ
3. ‘አእምሯችንን ማደስ’ ማለት ምን ማለት ነው? (ሮም 12:2)
3 አእምሯችንን ለማደስ ወይም አስተሳሰባችንን ለመቀየር ምን ማድረግ ያስፈልገናል? (ሮም 12:2ን አንብብ።) ለምሳሌ አንድን ቤት ማደስ ሲባል በቤቱ ውስጥ አንዳንድ ጌጣጌጦችን ማስቀመጥ ማለት አይደለም። በተመሳሳይም ‘አእምሯችንን ማደስ’ ማለት ጥቂት መልካም ነገሮችን በመሥራት ሕይወታችንን ማስጌጥ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ውስጣዊ ማንነታችንን በጥልቀት መመርመር እንዲሁም የይሖዋን መሥፈርቶች በተቻለ መጠን በጥብቅ ለመከተል አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ይኖርብናል። ይህን ማድረግ ያለብን አንዴ ብቻ ሳይሆን በቀጣይነት ነው።
4. ይህ ሥርዓት አስተሳሰባችንን እንዳይቀርጸው ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
4 ፍጹማን ስንሆን በምናደርገው ነገር ሁሉ ምንጊዜም ይሖዋን ማስደሰት እንችላለን። እስከዚያው ድረስ ግን ይሖዋን ለማስደሰት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። በሮም 12:2 ላይ ጳውሎስ፣ አእምሯችንን በማደስና የአምላክን ፈቃድ መርምሮ በማረጋገጥ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዴት እንደገለጸው ልብ በል። እጃችንን አጣጥፈን ይህ ሥርዓት እንዲቀርጸን ከመፍቀድ ይልቅ እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል፦ ‘ከዓለም አስተሳሰብ ይልቅ የአምላክ አስተሳሰብ በግቦቼና በውሳኔዎቼ ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ እየፈቀድኩ ነው?’
5. የይሖዋን ቀን ምን ያህል አቅርበን እንደምንመለከት መገምገም የምንችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉን ተመልከት።)
5 እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ይሖዋ ‘የእሱን ቀን መምጣት በአእምሯችን አቅርበን እንድንመለከት’ ይፈልጋል። (2 ጴጥ. 3:12) ስለዚህ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘አኗኗሬ የዚህ ሥርዓት መጨረሻ ምን ያህል እንደቀረበ እንደተገነዘብኩ የሚያሳይ ነው? ከትምህርትና ከሥራ ጋር በተያያዘ የማደርጋቸው ውሳኔዎች በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ የምሰጠው ለይሖዋ አገልግሎት እንደሆነ ያሳያሉ? ይሖዋ ለእኔም ሆነ ለቤተሰቤ የሚያስፈልገንን ነገር እንደሚያሟላልን እተማመናለሁ? ወይስ ሁልጊዜ ስለ ቁሳዊ ነገሮች እጨነቃለሁ?’ ይሖዋ ሕይወታችንን ከእሱ ፈቃድ ጋር ለማስማማት ጥረት ስናደርግ ምን ያህል እንደሚደሰት እስቲ አስበው።—ማቴ. 6:25-27, 33፤ ፊልጵ. 4:12, 13
6. ምን ማድረጋችንን መቀጠል ይኖርብናል?
6 አስተሳሰባችንን አዘውትረን በመገምገም አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ይኖርብናል። ጳውሎስ “በእምነት ውስጥ መሆናችሁን ለማረጋገጥ ዘወትር ራሳችሁን ፈትሹ፤ ማንነታችሁን ለማወቅ ዘወትር ራሳችሁን መርምሩ” በማለት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን መክሯቸዋል። (2 ቆሮ. 13:5) “በእምነት ውስጥ” መሆን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘትና አልፎ አልፎ አገልግሎት ከመውጣት ያለፈ ነገርን ይጠይቃል። አስተሳሰባችንን፣ ዝንባሌያችንን እና ውስጣዊ ግፊታችንንም ይጨምራል። በመሆኑም የአምላክን ቃል በማንበብ፣ የይሖዋን አስተሳሰብ ለማዳበር ጥረት በማድረግ እንዲሁም ሕይወታችንን ከእሱ ፈቃድ ጋር ለማስማማት አስፈላጊውን ማስተካከያ ሁሉ በማድረግ አእምሯችንን ማደሳችንን መቀጠል ይኖርብናል።—1 ቆሮ. 2:14-16
“አዲሱን ስብዕና ልበሱ”
7. በኤፌሶን 4:31, 32 መሠረት ሌላስ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ይህን ማድረግ ከባድ የሆነውስ ለምንድን ነው?
7 ኤፌሶን 4:31, 32ን አንብብ። በአስተሳሰባችን ላይ ለውጥ ከማድረግ በተጨማሪ “አዲሱን ስብዕና መልበስ” ይኖርብናል። (ኤፌ. 4:24) ይህም ጥረት ይጠይቃል። የመረረ ጥላቻን፣ ቁጣን፣ ንዴትን እንዲሁም ሌሎች መጥፎ ባሕርያትን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረግ ከባድ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አንዳንድ መጥፎ ባሕርያት ሥር የሰደዱ ናቸው። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ሰዎች ‘በቀላሉ የሚቆጡ’ እንደሆኑ ይናገራል። (ምሳሌ 29:22) ሥር የሰደዱ ባሕርያትን ለማስወገድ ከተጠመቅን በኋላም ጥረት ማድረግ ሊጠይቅብን ይችላል። ቀጣዩ ተሞክሮ ይህን ያሳያል።
8-9. የስቲቨን ተሞክሮ አሮጌውን ስብዕና ማውለቃችንን መቀጠል እንደሚያስፈልገን የሚያሳየው እንዴት ነው?
8 ስቲቨን የተባለ አንድ ወንድም ቁጣውን በመቆጣጠር ረገድ ችግር ነበረበት። እንዲህ ብሏል፦ “ከተጠመቅኩ በኋላም ግልፍተኝነቴን ለመተው ጥረት ማድረግ አስፈልጎኝ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ቀን ከቤት ወደ ቤት በመሄድ መጽሐፍ ቅዱስን እየሰበክሁ ሳለሁ ከመኪናዬ ውስጥ ሬዲዮ ሲሰርቅ ያገኘሁትን ሌባ አሯሩጬ ለመያዝ ሞክሬ ነበር። ልይዘው ስል ሬዲዮውን ጥሎ አመለጠ። የተሰረቀብኝን ሬዲዮ እንዴት እንዳስጣልኩ አብረውኝ ለነበሩት ስነግራቸው በአገልግሎት ቡድኑ ውስጥ የነበረ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ‘ስቲቨን፣ ሌባውን ይዘኸው ቢሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?’ ብሎ ጠየቀኝ። ይህ ጥያቄ ቆም ብዬ እንዳስብና ሰላማዊ ለመሆን ይበልጥ ጥረት እንዳደርግ አነሳስቶኛል።”b
9 የስቲቨን ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ አንድን መጥፎ ባሕርይ እንዳሸነፍነው ቢሰማንም እንኳ ባልጠበቅነው ጊዜ ብቅ ሊል ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ ተስፋ ልትቆርጥ ወይም ጥሩ ክርስቲያን እንዳልሆንክ ሊሰማህ አይገባም። ሐዋርያው ጳውሎስም እንኳ “ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው” በማለት በሐቀኝነት ተናግሯል። (ሮም 7:21-23) ቤታችን በየጊዜው እንደሚቆሽሽ ሁሉ ፍጹማን ያልሆኑ ክርስቲያኖች በሙሉ አልፎ አልፎ ብቅ ከሚሉ መጥፎ ባሕርያት ጋር በየጊዜው መታገል ያስፈልጋቸዋል። ምንጊዜም ንጽሕናችንን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
10. ከመጥፎ ባሕርያት ጋር መዋጋት የምንችለው እንዴት ነው? (1 ዮሐንስ 5:14, 15)
10 ይሖዋ እንደሚሰማህና እንደሚረዳህ በመተማመን የሚያታግልህን ባሕርይ በተመለከተ ጸልይ። (1 ዮሐንስ 5:14, 15ን አንብብ።) ይሖዋ ያንን ባሕርይ በተአምራዊ መንገድ ባያስወግድልህም እንኳ ለዚያ መጥፎ ባሕርይ እጅ እንዳትሰጥ ሊያበረታህ ይችላል። (1 ጴጥ. 5:10) በሌላ በኩል ደግሞ፣ አሮጌው ስብዕና እንዲያገረሽብህ ሊያደርጉህ ከሚችሉ ነገሮች በመራቅ ከጸሎትህ ጋር የሚስማማ እርምጃ ውሰድ። ለምሳሌ ያህል፣ ለማስወገድ እየሞከርክ ያለኸውን ባሕርይ ጥሩ አስመስለው የሚያቀርቡ ፊልሞችንና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ከመመልከት ወይም እንዲህ ያሉ መጻሕፍትን ከማንበብ ተቆጠብ። በተጨማሪም አእምሮህ በመጥፎ ምኞቶች ላይ እንዲያውጠነጥን አትፍቀድለት።—ፊልጵ. 4:8፤ ቆላ. 3:2
11. አዲሱን ስብዕና መልበሳችንን ለመቀጠል የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን?
11 አሮጌውን ስብዕና ያስወገድክ ቢሆንም እንኳ አዲሱን ስብዕና መልበስህ አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ስለ ይሖዋ ባሕርያት ለመማርና እሱን ለመምሰል ግብ አውጣ። (ኤፌ. 5:1, 2) ለምሳሌ የይሖዋን ይቅር ባይነት ጎላ አድርጎ የሚያሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ስታነብ ‘እኔስ ሌሎችን ይቅር እላለሁ?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ይሖዋ ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች የሚያሳየውን ርኅራኄ በተመለከተ ስታነብ ‘እኔስ የተቸገሩ የእምነት ባልንጀሮቼ ጉዳይ ያሳስበኛል? ይህንንስ በተግባር አሳያለሁ?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። አዲሱን ስብዕና በመልበስ አእምሮህን ማደስህን ቀጥል፤ ደግሞም ይህን ማድረግ ጊዜ ሊወስድብህ እንደሚችል አምነህ ተቀበል።
12. ስቲቨን መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንዳለው በራሱ ሕይወት የተመለከተው እንዴት ነው?
12 ቀደም ሲል የተጠቀሰው ስቲቨን ቀስ በቀስ አዲሱን ስብዕና መልበስ ችሏል። እንዲህ ብሏል፦ “ከተጠመቅኩበት ጊዜ አንስቶ ለድብድብ የሚጋብዙ ብዙ ሁኔታዎች አጋጥመውኛል። ለጠብ ሊያነሳሱኝ የሚሞክሩ ሰዎች ሲያጋጥሙኝ ትቻቸው መሄድን አሊያም ነገሩን በሌላ መንገድ ለማብረድ ጥረት ማድረግን ተምሬያለሁ። ባለቤቴን ጨምሮ ብዙ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙኝ የወሰድኳቸውን እርምጃዎች ተመልክተው አመስግነውኛል። አንዳንድ ጊዜ ያደረግኩት ለውጥ እኔ ራሴም ይገርመኛል! እንዲህ ዓይነት የባሕርይ ለውጥ በማድረጌ ልመሰገን የሚገባኝ እኔ አይደለሁም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነ ይሰማኛል።”
ከመጥፎ ምኞቶች ጋር መዋጋታችሁን ቀጥሉ
13. መጥፎ ምኞቶችን ለማሸነፍ ምን ይረዳናል? (ገላትያ 5:16)
13 ገላትያ 5:16ን አንብብ። ይሖዋ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ስንታገል እኛን ለመርዳት ቅዱስ መንፈሱን አትረፍርፎ ይሰጠናል። የአምላክን ቃል ስናጠና መንፈስ ቅዱስ ተጽዕኖ እንዲያደርግብን እንፈቅዳለን። በስብሰባዎች ላይ ስንገኝም መንፈስ ቅዱስን እናገኛለን። በእነዚህ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንደ እኛው ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ከሚጥሩ ወንድሞችና እህቶች ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንችላለን፤ ይህ ደግሞ ያበረታታናል። (ዕብ. 10:24, 25፤ 13:7) በተጨማሪም ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ አንድን ድክመት ለማሸነፍ እንዲረዳን ስንጠይቀው ከዚያ ድክመት ጋር መታገላችንን ለመቀጠል የሚያስችለንን ኃይል በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ይሰጠናል። በእነዚህ እንቅስቃሴዎች መካፈላችን መጥፎ ምኞቶቻችን እንዲወገዱ ላያደርግ ቢችልም እንኳ እነዚህን ምኞቶች እንድንፈጽም የሚገፋፋንን ስሜት ለመቋቋም ይረዳናል። ገላትያ 5:16 እንደሚለው በመንፈስ የሚመላለሱ ሰዎች ‘የሥጋን ምኞት ከቶ አይፈጽሙም።’
14. ጥሩ ምኞቶችን ለማዳበር ጥረት ማድረጋችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?
14 በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የመካፈል ጥሩ ልማድ ካዳበርን በኋላ ይህን ልማድ ይዘን መቀጠላችን እንዲሁም ጥሩ ምኞቶችን ለማዳበር ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም ጨርሶ የማይተኛ ጠላት አለን። ይህ ጠላት፣ መጥፎ ነገሮችን እንድንፈጽም የሚያነሳሳን ግፊት ነው። ከተጠመቅን በኋላም እንኳ፣ ልንርቃቸው የሚገቡ ነገሮች ሊማርኩን ይችላሉ። ከእነዚህ ነገሮች መካከል ቁማር፣ የመጠጥ ሱስ ወይም ፖርኖግራፊ ይገኙበታል። (ኤፌ. 5:3, 4) አንድ ወጣት ወንድም እንዲህ በማለት በሐቀኝነት ተናግሯል፦ “ለሌሎች ወንዶች የፍቅር ስሜት ያድርብኝ ነበር፤ ይህን ማሸነፍ በጣም አታግሎኛል። ይህ ስሜት ውሎ አድሮ የሚጠፋ መስሎኝ ነበር፤ ግን አሁንም ድረስ ያታግለኛል።” ያደረብህ መጥፎ ምኞት በቀላሉ አልጠፋ ካለህ ምን ሊረዳህ ይችላል?
15. መጥፎ ምኞቶች “በሰው ሁሉ ላይ” እንደሚደርሱ ማወቃችን የሚያበረታታን ለምንድን ነው? (ሥዕሉን ተመልከት።)
15 በቀላሉ ከማይጠፋ መጥፎ ምኞት ጋር እየታገልክ ከሆነ ብቻህን እንዳልሆንክ አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ “በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም” ይላል። (1 ቆሮ. 10:13ሀ) ይህ ሐሳብ የተጻፈው በቆሮንቶስ ለሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች ነው። ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ ቀደም ሲል አመንዝሮች፣ ግብረ ሰዶማውያንና ሰካራሞች ነበሩ። (1 ቆሮ. 6:9-11) እነዚህ ክርስቲያኖች ከተጠመቁ በኋላ ከየትኛውም መጥፎ ምኞት ጋር መታገል ያላስፈለጋቸው ይመስልሃል? እንደዚያ ሊሆን አይችልም። ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቢሆኑም ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ናቸው። አልፎ አልፎ ከመጥፎ ምኞቶች ጋር መታገል እንዳስፈለጋቸው ምንም ጥያቄ የለውም። ይህ እኛንም ሊያበረታታን ይገባል። ለምን? ምክንያቱም እየታገልከው ያለኸው መጥፎ ምኞት ምንም ይሁን ምን፣ ሌላ ክርስቲያን ይህን ምኞት አሸንፎታል። በእርግጥም ‘በዓለም ዙሪያ በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያሉት ወንድሞችህ ተመሳሳይ መከራ እየደረሰባቸው እንዳለ ተገንዝበህ በእምነት ጸንተህ መቆም’ ትችላለህ።—1 ጴጥ. 5:9
16. ምን ብለን እንዳናስብ መጠንቀቅ ይኖርብናል? ለምንስ?
16 ‘እያጋጠመኝ ያለውን ፈተና ማንም ሰው ሊረዳው አይችልም’ ብለህ ከማሰብ ተቆጠብ። እንደዚህ ብለህ ማሰብህ ያለህበት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ እንዲሁም መጥፎ ምኞቶችህን ማሸነፍ እንደማትችል እንዲሰማህ ሊያደርግ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ሐሳብ ይዟል። እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ፈተና ሲደርስባችሁ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።” (1 ቆሮ. 10:13ለ) ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው፣ ያደረብን መጥፎ ምኞት በቀላሉ የማይጠፋ ቢሆንም እንኳ በጽናት ልንቋቋመው እንችላለን። በይሖዋ እርዳታ፣ ይህን ምኞት ከመፈጸም መታቀብ እንችላለን።
17. መጥፎ ምኞቶች እንዳይፈጠሩብን መከላከል ባንችልም እንኳ ምን ማድረግ እንችላለን?
17 ምንጊዜም ይህን አስታውስ፦ ፍጹማን ስላልሆንን መጥፎ ምኞቶች ጨርሶ እንዳይፈጠሩብን ማድረግ አንችል ይሆናል። ሆኖም ዮሴፍ ከጶጢፋር ሚስት በፍጥነት እንደሸሸ ሁሉ እኛም መጥፎ ምኞቶች ሲፈጠሩብን እነሱን ለማስወገድ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንችላለን። (ዘፍ. 39:12) መጥፎ ምኞቶች ቢፈጠሩብንም ምኞቶቹን ላለመፈጸም መምረጥ እንችላለን!
ቀጣይነት ያለው ጥረት
18-19. አእምሯችንን ለማደስ ጥረት በምናደርግበት ጊዜ የትኞቹን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን?
18 አእምሯችንን ማደስ አስተሳሰባችንንና ምግባራችንን ከይሖዋ ፈቃድ ጋር ለማስማማት ቀጣይነት ያለው ጥረት ማድረግን ይጠይቃል። ይህን ለማድረግ አንዳንድ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ራሳችንን አዘውትረን መገምገም ይኖርብናል፦ ‘የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን ውስጥ መሆኑን እንደማምን አኗኗሬ ያሳያል? አዲሱን ስብዕና በመልበስ ረገድ ማሻሻያ እያደረግኩ ነው? መጥፎ ምኞቶችን እንድፈጽም የሚገፋፋኝን ስሜት መቋቋም እንድችል የይሖዋ መንፈስ ሕይወቴን እንዲመራው እየፈቀድኩ ነው?’
19 ራስህን በምትገመግምበት ወቅት ከራስህ ፍጽምና አትጠብቅ፤ ከዚህ ይልቅ ያደረግከውን ማሻሻያ ለማስተዋል ሞክር። አሁንም ተጨማሪ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ካስተዋልክ ተስፋ አትቁረጥ። ከዚህ ይልቅ በፊልጵስዩስ 3:16 ላይ የሚገኘውን ምክር ተከተል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ምንም ያህል እድገት ያደረግን ብንሆን በዚሁ መንገድ በአግባቡ ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥል።” እንዲህ ካደረግን፣ አእምሯችንን ማደሳችንን ለመቀጠል የምናደርገውን ጥረት ይሖዋ እንደሚባርክልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
መዝሙር 36 ልባችንን እንጠብቅ
a ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻቸው እንዳይፈቅዱ አሳስቧቸዋል። ይህ ምክር ለእኛም ይጠቅመናል። ይህ ክፉ ዓለም በሆነ መንገድ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ለዚህም ሲባል፣ አስተሳሰባችን ከአምላክ ፈቃድ ጋር እንዳልተጣጣመ ባስተዋልን ቁጥር ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልገናል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።
b በሐምሌ 1, 2015 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘውን “ሕይወቴ ከድጡ ወደ ማጡ ሄዶ ነበር” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c የሥዕሉ መግለጫ: አንድ ወጣት ወንድም ‘ከፍተኛ ትምህርት ልከታተል ወይስ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ልግባ?’ ብሎ ሲያስብ።