“እንደ ብርሃን ልጆች በመሆን መመላለሳችሁን ቀጥሉ”
“ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና [ታማኝነት አዓት] እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።” — ኤፌሶን 4:24
1. የይሖዋ አምላኪዎች ምን ዓይነት በረከት አግኝተዋል? ለምንስ?
ይሖዋ አምላክ “የብርሃናት አባት” ነው። “በእርሱም ዘንድ ጨለማ የለም። (ያዕቆብ 1:17፤ 1 ዮሐንስ 1:5) ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለራሱ ሲናገር “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፣ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ብሎአል። (ዮሐንስ 8:12) ስለዚህ የይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎችና የልጁ ተከታዮች የአእምሮ፣ የሥነ ምግባርና የመንፈስ ብርሃን አግኝተዋል። በዓለምም ውስጥ ‘እንደ ብርሃናት ያበራሉ።’ — ፊልጵስዩስ 2:15
2. በአምላክ ሕዝቦችና በዓለም መካከል ምን ዓይነት የጎላ ልዩነት እንደሚኖር አስቀድሞ ተነግሮ ነበር?
2 ነቢዩ ኢሳይያስ ከብዙ ዘመናት በፊት ይህን በዓለምና በይሖዋ አምላኪዎች መካከል የሚታየውን የጎላ ልዩነት በመንፈስ ተገፋፍቶ ተንብዮ ነበር:- “እነሆ ጨለማ ምድርን፣ ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል። ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ይወጣል፣ ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል።” እንዲያውም ከአምላክ የራቀው የሰው ልጅ በሙሉ “በጨለማው ዓለም ገዥዎች” ሥልጣንና ተጽእኖ ሥር እንደሆነ ተነግሮአል። — ኢሳይያስ 60:2፤ ኤፌሶን 6:12
3. ጳውሎስ የሰጠው ወቅታዊ ምክር ትኩረታችንን በጣም ሊስብ የሚገባው በምን ምክንያቶች የተነሳ ነው?
3 ክርስቲያን ጓደኞቹ በሙሉ እንዲህ ካለው ጨለማ ርቀው መኖራቸው ሐዋርያ ጳውሎስን በጣም አሳስቦት ነበር። ‘እንደ አሕዛብ . . . እንዳይመላለሱና’ ‘እንደ ብርሃን ልጆች’ እንዲመላለሱ አጥብቆ አሳስቦአቸዋል። (ኤፌሶን 4:17፤ 5:8) በተጨማሪም ይህን ለማድረግ እንዴት ሊሳካላቸው እንደሚችል ገልጾላቸዋል። በዛሬው ዘመን አሕዛብን የሸፈነው ጨለማና ጭጋግ ከጥንቱ የበለጠ ድቅድቅ ሆኖአል። ዓለም በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ የውርደት ማጥ ውስጥ በይበልጥ ሰምጧል። የይሖዋ አምላኪዎች የሚያካሂዱት ውጊያ ይበልጥ ከባድ እየሆነባቸው ሄዶአል። ስለዚህ ጳውሎስ የሚናገረውን ነገር ለማወቅ ከልብ እንፈልጋለን።
ስለ ክርስቶስ ተማሩ
4. ጳውሎስ “ክርስቶስን እንዲህ አልተማራችሁትም” ብሎ ሲናገር በአእምሮው የያዘው ምንን ነበር?
4 ሐዋርያው ጳውሎስ ዓለም የሚያሳድዳቸውን ከንቱ ነገሮችና ርኩሰቶች ከገለጸ በኋላ ትኩረቱን በኤፌሶን ይኖሩ ወደነበሩት ክርስቲያን ባልደረቦቹ ዞር ያደርጋል። (ኤፌሶን 4:20, 21ን አንብብ) ጳውሎስ በዚህች ከተማ ሶስት ዓመት ያህል ሲሰብክና ሲያስተምር ስለቆየ በዚያ ጉባዔ ከነበሩት ብዙ ክርስቲያኖች ጋር ይተዋወቃል። (ሥራ 20:31–35) ስለዚህ “እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም” ሲል የኤፌሶን ክርስቲያኖች ከቁጥር 17 እስከ 19 የገለጻቸውን መጥፎ ድርጊቶች የሚፈቅድ፣ የተበረዘና የተከለሰ እውነት ያልተማሩ መሆናቸውን እንደሚያውቅ መናገሩ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ አርዓያ የሆነለትን እውነተኛ የክርስትና አኗኗር በትክክል እንደተማሩ ያውቅ ነበር። በዚህም ምክንያት የብርሃን ልጆች ነበሩ እንጂ እንደ አሕዛብ በጨለማ የሚመላለሱ አልነበሩም።
5. ላይ ላዩን በእውነት ውስጥ በመኖርና እውነት በውስጣችን በማደሩ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
5 ስለዚህ ክርስቶስን በትክክለኛው መንገድ ተምሮ ማወቅ ምንኛ አስፈላጊ ነው! ክርስቶስን በተሳሳተ ሁኔታ ማወቅ የሚቻልባቸው መንገዶች አሉን? አዎ፣ በእርግጥ አሉ። ጳውሎስ ቀደም ሲል በኤፌሶን 4:14 ላይ ወንድሞችን “እንደ ስህተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደፊት አይገባንም” በማለት ወንድሞችን አስጠንቅቆ ነበር። ስለ ክርስቶስ የተማሩ ቢሆኑም እንኳን በዓለም መንገድ መመላለሳቸውን ያልተዉና ሌሎችም እንደነርሱ በዓለም መንገድ እንዲመላለሱ ለማግባባት የሚሞክሩ አንዳንዶች እንደነበሩ ከዚህ መረዳት ይቻላል። እውነት በውስጣችን እንዲያድር በማድረግ ፈንታ አንዳንዶች እንደሚሉት እኛ በእውነት ውስጥ እንዳለን ብቻ ብንናገር አደጋ እንደሚኖረው ይህ ያሳየናልን? በጳውሎስ ዘመን እውነትን ላይ ላዩን ብቻ ያወቁት ሰዎች ሌሎች መጥተው በቀላሉና በፍጥነት ወስደዋቸዋል። ዛሬም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም። የኤፌሶን ክርስቲያኖች እንዲህ ያለው ሁኔታ እንዳይደርስባቸው ክርስቶስን ‘የሰሙና በኢየሱስ አማካይነት የተማሩ’ መሆን ያስፈልጋቸው እንደነበረ ጳውሎስ ተናግሯል። — ኤፌሶን 4:21
6. በዛሬው ጊዜ ክርስቶስን ለማወቅ፣ ለመስማትና ከእርሱም የተማርን ለመሆን የምንችለው እንዴት ነው?
6 ጳውሎስ የተጠቀመባቸው “ማወቅ”፣ “መስማት” እና “መማር” የሚሉት ቃላት ሁሉም በትምህርት ቤት የሚሰጠውን የሚመስል የጥናትና የትምህርት ሂደት የሚያመለክቱ ናቸው። እርግጥ ዛሬ ኢየሱስን በቀጥታ ለመስማት ወይም ከእርሱ በቀጥታ ለመማር አንችልም። ይሁን እንጂ በታማኝና ልባም ባሪያው አማካኝነት መላውን ምድር የሚያቅፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ዘመቻ በማካሄድ ላይ ነው። (ማቴዎስ 24:45–47፤ 28:19, 20) በባሪያው ክፍል የሚቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ አዘውትረን ብንወስድ፣ በግላችንም ሆነ በጉባዔ በትጋት ብናጠና፣ ብናሰላስልና የተማርነውን ሁሉ ሥራ ላይ ብናውል ክርስቶስን ተገቢ በሆነ መንገድና በትክክል ልናውቀው እንችላለን። ሁላችንም “ሰምተነዋል ከእርሱም ተምረናል” ለማለት እንድንችል በሁሉም የትምህርት መስጫ ዝግጅቶች እንጠቀም።
7. ጳውሎስ “እውነትም በኢየሱስ አለ” ሲል በተናገራቸው ቃላት ምን አስፈላጊ ቁም ነገር ተገልጾአል?
7 ጳውሎስ ስለመማሩ ሂደት ጠበቅ አድርጎ ከገለጸ በኋላ በኤፌሶን 4:21 ላይ “እውነትም በኢየሱስ እንዳለ” ሲል የተናገረውን ቃል ልብ ማለት ያስፈልጋል። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ጳውሎስ በጽሑፎቹ ውስጥ ኢየሱስ የሚለውን የተፀውኦ ስም ብቻውን የተጠቀመባቸው ጊዜያት በጣም ጥቂት እንደሆኑ ያመለክታሉ። በእርግጥም ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ኢየሱስን በስሙ የጠራው እዚህ ቦታ ላይ ብቻ ነው። ታዲያ ይህ የተለየ ትርጉም ይኖረዋልን? ምናልባት ጳውሎስ ኢየሱስ ሰው በነበረበት ጊዜ ያሳየውን ምሳሌ መጠቆሙ ይሆናል። ኢየሱስ አንድ ጊዜ ስለራሱ ሲናገር “እኔ መንገድና እውነት፣ ሕይወትም ነኝ” ብሎ መናገሩን እናስታውስ። (ዮሐንስ 14:6፤ ቆላስይስ 2:3) ኢየሱስ “እኔ . . . እውነት ነኝ” ያለው እውነትን በመናገርና በማስተማር ብቻ ሳይወሰን ለእውነት ስለኖረና ለእውነት አብነት ስለሆነ ነው። አዎ፣ እውነተኛው ክርስትና እንዲሁ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን የአኗኗር መንገድ ነው። “ክርስቶስን መማር” እውነትን ተግባራዊ እያደረጉ በመኖር ረገድ እርሱን ለመምሰል መማርን ይጨምራል። የኢየሱስን አርአያ በመከተል አኗኗርህን ቀርጸሃልን? በየዕለቱ ፈለጉን በጥብቅ ትከተላለህን? የብርሃን ልጆች በመሆን ልንመላለስ የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው።
“አሮጌውን ሰው ማስወገድ
8. ጳውሎስ በኤፌሶን 4:22, 24 ላይ ምን ምሳሌ ጠቅሶአል? ይህስ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
8 ጳውሎስ ክርስቶስን እንዴት ለመማርና እንደ ብርሃን ልጆች ሆነን ለመመላለስ እንዴት እንደምንችል ሲያመለክት በኤፌሶን 4:22–24 ላይ ልንከተላቸው የሚገቡ ሦስት የተለያዩ እርምጃዎች እንዳሉ ይገልጻል። ከሶስቱ የመጀመሪያው የሚከተለው ነው:- “አታልሎ ወደ ኃጢአት በሚመራ ምኞት የተበላሸውን አስቀድሞ ትኖሩበት የነበረውን አሮጌውን ሰውነት አስወግዱ።” (ኤፌሶን 4:22 የ1980 ትርጉም) “አስወግዱ” (“አውልቁ” ኪንግደም ኢንተርሊንየር ) እና “ልበሱ” (ቁጥር 24) ልብስ ማውለቅንና መልበስን በአእምሮአችን እንድንስል የሚያደርጉ አገላለጾች ናቸው። ይህ ጳውሎስ አዘውትሮ የተጠቀመበት በጣም ጥሩ የሆነ የሰምና ወርቅ አነጋገር ነው። (ሮሜ 13:12, 14፤ ኤፌሶን 6:11–17፤ ቆላስይስ 3:8–12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:8) ልብሳችን ከቆሸሸ ወይም ስንበላ ምግብ ተንጠባጥቦበት ከተበላሸ ወዲያው እንቀይረዋለን። መንፈሳዊነታችን ትንሽ ቆሽሾ ከሆነስ የዚህኑ ያህል መጨነቅ አይገባንምን?
9. አንድ ሰው አሮጌውን ሰው የሚያስወግደው በምን መንገድ ነው?
9 ታዲያ አንድ ሰው አሮጌውን ሰውነት የሚያስወግደው እንዴት ነው? “አስውግዱ” የሚለው ግሥ በግሪክኛው ቋንቋ የነበረው ሰዋስዋዊ አገባብ አንድ ጊዜ ብቻ ወይም ለአንዴና ለሁልጊዜ የተፈጸመን ድርጊት የሚያመለክት ነው። ይህም “አሮጌው ሰውነት” ቀድሞ እንኖርበት ከነበረው አኗኗር ጋር ሙሉ በሙሉና በቁርጠኝነት መወገድ እንዳለበት ይነግረናል። ለሌላ ጊዜ የምናስተላልፈው ወይም የምናመነታበት እርምጃ አይደለም። ለምን?
10. አንድ ሰው አሮጌውን ሰው በማስወገድ ረገድ ቆራጥ መሆንና ጽኑ አቋም ሊኖረው የሚገባው ለምንድን ነው?
10 “የሚበላሸው” [አዓት] የሚለው አነጋገር “አሮጌው ሰው” ዘወትር ከመጥፎ ወደ ባሰ መጥፎነት እያዘቀጠ የሚሄድ መሆኑንና የሥነ ምግባር ርኩሰቱ እየተባባሰ የሚሄድ መሆኑን ያመለክታል። እንደ እውነቱ ከሆነ መላው የሰው ልጅ መንፈሳዊ ብርሃን ለመቀበል እምቢተኛ በመሆኑ ወደ ከፍተኛ አዘቅት በማሽቆልቆል ላይ ይገኛል። ይህም ‘የአታላይ ምኞቶች’ ውጤት እንደሆነ ጳውሎስ ተናግሮአል። ሥጋዊ ምኞቶች ምንም ጉዳት የሌላቸው መስለው በመጨረሻ ላይ ግን ጥፋት ሊያስከትሉ የሚችሉ ስለሆኑ አታላዮች ናቸው። (ዕብራውያን 3:13) ካልተገቱ እድፈትና ሞት ያስከትላሉ። (ሮሜ 6:21፤ 8:13) አሮጌው ሰውነት የቆሸሸ አሮጌ ልብስ ወልቆ እንደሚጣል ሙሉ በሙሉና ወሳኝ በሆነ መንገድ ወልቆ መጣል የሚኖርበት በዚህ ምክንያት ነው።
አዲስ “የአእምሮ መንፈስ”
11. መንፈሳዊ እድሳት መጀመር ያለበት ከየት ነው?
11 ከጭቃ ማጥ ውስጥ የወጣ ሰው የቆሸሹትን ልብሶቹን አውልቆ ከመጣሉ በተጨማሪ ንፁሕ ልብስ ከመልበሱ በፊት ገላውን ጥሩ አድርጎ መታጠብ ያስፈልገዋል። ጳውሎስም መንፈሳዊ ብርሃን ለማግኘት መወሰድ የሚኖርበት ሁለተኛ እርምጃ ይህ እንደሆነ ገልጾአል። “አእምሮአችሁን በሚያንቀሳቅሰው ኃይል መታደስ ይኖርባችኋል።” (ኤፌሶን 4:23 አዓት) ቀደም ሲል በቁጥር 17 እና 18 አሕዛብ “በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ” እና “በልቡና ጨለማ” ውስጥ እንደሚገኙ ገልጾአል። ስለዚህ የመታደሱ ሥራ መጀመር የሚኖርበት የዕውቀትና የመረዳት ማኅደር በሆነው አእምሮ ላይ መሆን ይኖርበታል። ይህንን ለማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? አእምሮአችንን የሚያንቀሳቅሰውን ኃይል አዲስ በማድረግ እንደሆነ ጳውሎስ ገልጾአል። ይህ ኃይል ምንድን ነው?
12. አእምሮን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል ምንድን ነው?
12 ጳውሎስ የጠቀሰው አእምሮአችንን የሚያንቀሳቅስ ኃይል መንፈስ ቅዱስ ነውን? አይደለም። “አእምሮአችሁን የሚያንቀሳቅስ ኃይል” የሚለው ሐረግ ቃል በቃል ሲተረጎም “የአእምሮአችሁ መንፈስ” ማለት ነው። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የሰው አካል ክፍል እንደሆነ ወይም የሰው ንብረት እንደሆነ የተገለጸበት ቦታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። “መንፈስ” የሚለው ቃል መሠረታዊ ትርጉም “ትንፋሽ” ማለት ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “አንድ ሰው አንድ ዓይነት ዝንባሌ፣ ጠባይ፣ ወይም ስሜት እንዲያሳይ ወይም አንድ ዓይነት መንገድ እንዲከተል ወይም አንድ ዓይነት እርምጃ እንዲወስድ የሚያደርገውን ኃይል ለማመልከት ይሠራበታል።” (ጠለቅ ብሎ ማስተዋል ጥራዝ 2 ገጽ 1026) ስለዚህ “የአእምሮ መንፈስ” አእምሮአችንን፣ የአእምሮአችንን አቅጣጫና ዝንባሌ የሚያንቀሳቅሰው ወይም የሚያነሳሳው ኃይል ነው።
13. የአእምሮአችን ዝንባሌ አዲስ መሆን የሚኖርበት ለምንድን ነው?
13 ፍጹም ያልሆነው አእምሮአችን በተፈጥሮው የሚያዘነብለው ሥጋዊ፣ ግዑዝና ቁሳዊ ወደሆኑ ነገሮች ነው። (መክብብ 7:20፤ 1 ቆሮንቶስ 2:14፤ ቆላስይስ 1:21፤ 2:18) አንድ ሰው አሮጌውን ሰው ከመጥፎ ልማዶቹ ጋር አውልቆ ቢጥልም እንኳን ኃጢአተኛ የሆነው የአእምሮ ዝንባሌው ካልተለወጠ ውሎ አድሮ ትቶት ወደነበረው ልማድ እንዲመለስ ያስገድደዋል። ማጨስ፣ ከመጠን በላይ መጠጣት ወይም ሌሎች መጥፎ ልማዶችን ለመተው የሞከሩ ብዙ ሰዎች የሚያጋጥማቸው ሁኔታ ይህ አይደለምን? አእምሮአቸውን በሚያንቀሳቅሰው ኃይል ለመታደስ ምንም ዓይነት ጥረት ሳያደርጉ ሲቀሩ የቀድሞው ልማዳቸው ማገርሸቱ የማይቀር ይሆናል። ትክክለኛ የሆነ ማንኛውም ለውጥ በአእምሮ ላይ የሚደረገውን ለውጥ የሚጨምር መሆን ይኖርበታል። — ሮሜ 12:2
14. አእምሮን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል ሊታደስ የሚችለው እንዴት ነው?
14 ታዲያ አንድ ሰው ይህ ኃይል አእምሮውን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የሚገፋፋ እንዲሆንለት አዲስ ሊያደርገው የሚችለው እንዴት ነው? “መታደስ” የሚለው ቃል በግሪክኛው ጽሑፍ በአሁን ጊዜ የተነገረ ሲሆን የማያቋርጥን ድርጊት ያመለክታል። ስለዚህ አእምሮን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል የሚታደሰው ያለማቋረጥ የአምላክን ቃል በማጥናትና የሚያንቀሳቅሰው ኃይል መታደስ አለበት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በማሰላሰል ነው። የሳይንስ ሊቃውንት እንደሚነግሩን በአንጎላችን ውስጥ በኤሌክትሪክ ወይም በኬሚካል መልክ የሚተላለፈው መረጃ ሲናፕስስ የሚባሉ ብዙ መገናኛዎችን እያቆራረጠ ከኒውሮን ወደ ኒውሮን ይጓዛል። ዘ ብሬይን የተባለው መጽሐፍ እንደሚናገረው “በኤሌክትሪክ ወይም በኬሚካል መልክ የሚተላለፈው መልእክት አንድ ዓይነት አሻራ ትቶ ሲያልፍ በነርቩ ሲናፕስ ላይ አንድ ዓይነት ማስታወሻ ይቀራል።” ይኸው ምልክት ሌላ ጊዜ በዚሁ በኩል ሲያልፍ የነርቭ ሴሎች ወዲያው ስለሚያውቁት በበለጠ ፍጥነት ምላሽ ይሰጣሉ። ይህም ከጊዜ በኋላ በግለሰቡ ውስጥ አዲስ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲፈጠር ያደርጋል። ጤናማ የሆነ መንፈሳዊ መረጃ ወደ አእምሮአችን ባስገባን መጠን አዲስ ዓይነት የአስተሳሰብ ሥርዓት ይገነባል። አእምሮአችንን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል አዲስ ይሆናል። — ፊልጵስዩስ 4:8
“አዲሱን ሰው ልበሱ”
15. አዲሱ ሰው አዲስ የሆነው በምን መንገድ ነው?
15 በመጨረሻም ጳውሎስ እንዲህ ይላል:- “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና [ታማኝነት አዓት] እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ [ፈቃድ አዓት] የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።” (ኤፌሶን 4:24) አዎ፣ አንድ ክርስቲያን አዲሱን ሰው መልበስ ይኖርበታል። እዚህ ላይ “አዲስ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ከጊዜ አንጻር አዲስ መሆኑን ሳይሆን በጥራት ረገድ አዲስ መሆኑን ነው። ይህም ማለት አዲስ የሆነው በቅርብ ጊዜ የመጣ ነገር ስለሆነ አይደለም ማለት ነው። ‘እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የተፈጠረ’ ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆነ ትኩስ ባሕርይ ነው። ጳውሎስ በቆላስይስ 3:10 ላይ በተመሳሳይ አነጋገር ተጠቅሞ “የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል . . . የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል” ብሎአል። ይህ አዲስ ሰው ወይም ባሕርይ የሚገኘው እንዴት ነው?
16. አዲሱ ሰው የሚፈጠረው ‘እንደ አምላክ ፈቃድ ነው’ ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
16 ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹ ሰብዓውያን ባልና ሚስት የሆኑትን አዳምንና ሔዋንን የፈጠረው በራሱ መልክና ምሳሌ ነበር። ከእንስሳትና ከአራዊት የሚለዩአቸውም በጣም ከፍ የሚያደርጉአቸው ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ባሕርያት ተሰጥተዋቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:26, 27) የእነዚህ ሰዎች አለመታዘዝ መላውን የሰው ልጅ በኃጢአትና በአለፍጽምና ውስጥ የዘፈቀው ቢሆንም የአዳም ዘሮች የሆንን ሁሉ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ባሕርያትን የማንጸባረቅ ችሎታ አለን። በቤዛዊው መሥዋዕት የሚያምኑ ሁሉ አሮጌውን ሰው አስወግደው “ለእግዚአብሔር ልጆች በሚሆን ክብርና ነፃነት” እንዲደሰቱ የአምላክ ፈቃድ ነው። — ሮሜ 6:6፤ 8:19–21፤ ገላትያ 5:1, 24
17. ጽድቅና ታማኝ ሆኖ መቆም አዲሱ ሰው ተለይቶ የሚታወቅባቸው ጉልህ ባሕርያት የሆኑት ለምንድን ነው?
17 ጳውሎስ የአዲሱ ሰው መለያ ምልክት አድርጎ ለይቶ የጠቀሳቸው ሁለት ባሕርያት እውነትኛ ጽድቅና ታማኝነት ናቸው። ይህም አዲሱ ሰው በፈጣሪው ምሳሌ የሚታደስ መሆኑን ያጎላል። መዝሙር 145:17 “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው። በሥራውም ሁሉ ቸር [ታማን ሆኖ የሚቆም አዓት] ነው” ሲል ይነግረናል። ራእይ 16:5ም ስለ ይሖዋ ሲናገር “ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ፣ ቅዱስ [ታማኝ አዓት] ሆይ፣ . . . ጻድቅ ነህ” ይላል። በእርግጥም የአምላክን ክብር እያንጸባረቅን በተፈጠርንበት ሁኔታ አምላክን መስለን ለመኖር ከፈለግን የጽድቅና በታማኝነት የመቆም ባሕርይ ሊኖረን ይገባል። አምላክ “በዘመናችን ሁሉ አለፍርሃት በቅድስናና [በታማኝነትና አዓት] በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን” በማለት በመንፈስ ተነሳስቶ ይሖዋን እንዳወደሰው እንደ አጥማቂው ዮሐንስ አባት እንደ ዘካርያስ እንሁን። — ሉቃስ 1:74, 75
እንደ ብርሃን ልጆች በመሆን መመላለሳችሁን ቀጥሉ
18. ጳውሎስ የዓለምን መንገድ እውነተኛ ገጽታ እንድንመለከት የረዳን እንዴት ነው?
18 በኤፌሶን 4:17–24 ላይ የሚገኙትን የጳውሎስ ቃላት በዝርዝር በመመርመራችን ብዙ ነገር ለመገንዘብ ችለናል። ጳውሎስ ከ17 እስከ 19 በሚገኙት ቁጥሮች ላይ የዓለምን መንገድ ትክክለኛ ገጽታ እንድናውቅ ረድቶናል። በዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች አምላክን ለማወቅ እምቢተኞች ስለሆኑና ልባቸውን ስላደነደኑ ከእውነተኛው የሕይወት ምንጭ ራሳቸውን አርቀዋል። በዚህም ምክንያት እውነተኛ ዓላማ ወይም የጉዞ አቅጣጫ ስለሌላቸው ጥረታቸው ሁሉ መናና ከንቱ ሆኖ ይቀራል። ከመቸውም ጊዜ ይበልጥ በሥነ ምግባራዊም ሆነ በመንፈሳዊ ውድቀት እያዘቀጡ ሄደዋል። ምንኛ የሚያሳዝን ሁኔታ ነው! ይህም እንደ ብርሃን ልጆች ሆነን በመመላለስ ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እንድናደርግ የሚገፋፋ እንዴት ያለ ጠንካራ ምክንያት ነው!
19. በመጨረሻ ላይ እንደ ብርሃን ልጆች ሆነን በመመላለስ እንድንቀጥል ከጳውሎስ ምን ምክር አግኝተናል?
19 ከዚያም በቁጥር 20 እና 21 ላይ በእውነት ውስጥ ከመኖርና ከእውነት ጋር ከመተዋወቅ አልፈን ልክ እንደ ኢየሱስ እውነትን ተግባራዊ እያደረግን ለመኖር ከፈለግን እውነትን በቁም ነገር ማጥናት እንደሚያስፈልገን ጳውሎስ አበክሮ ይገልጻል። በመጨረሻም ከቁጥር 22–24 ላይ በቆራጥነትና በጸና አቋም አሮጌውን ሰው አውልቀንና ጥለን አዲሱን ሰው እንድንለብስ ያሳስበናል። ይህን በምናደርግበት ጊዜ ሁሉ መንፈሳዊ ዝንባሌያችንን ጤናማና መንፈሳዊ ወደ ሆኑ አቅጣጫዎች ለመመለስ መጣራችንን መቀጠል ይኖርብናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደ ብርሃን ልጆች ሆነን በምንመላለስበት ጊዜ ሁሉ የይሖዋን እርዳታ መፈለግ ይኖርብናል። “በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና።” — 2 ቆሮንቶስ 4:6
ታስታውሳለህን?
◻ በዘመናችን ‘ክርስቶስን ለመማር’ የምንችለው እንዴት ነው?
◻ አሮጌው ሰው በቆራጥነት መወገድ ያለበት ለምንድን ነው?
◻ አእምሮን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል ምንድን ነው? የሚታደሰውስ እንዴት ነው?
◻ አዲሱ ሰው ተለይቶ የሚታወቅባቸው ባሕርያት ምንድን ናቸው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ:- “እኔ መንገድና እውነት፣ ሕይወትም ነኝ” አለ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“አሮጌውን ሰው ከቁጣው፣ ከንዴቱ፣ ከክፋቱ፣ ከስድብና ከብልግና አነጋገሩ እንዲሁም ከውሸቱ ጋር አውልቃችሁ ጣሉ።” — ቆላስይስ 3:8, 9
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና [ታማኝነት አዓት] እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ [ፈቃድ አዓት] የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።” — ኤፌሶን 4:24