ክርስቲያኖች ያላቸው አንድነት አምላክን ያስከብራል
“የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት አድርጉ።”—ኤፌ. 4:3
1. በኤፌሶን የሚገኙት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ለአምላክ ክብር ያመጡት እንዴት ነበር?
በጥንቷ ኤፌሶን የሚገኘው የክርስቲያን ጉባኤ የነበረው አንድነት እውነተኛ አምላክ ለሆነው ለይሖዋ ክብር አምጥቶ ነበር። ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ በሚካሄድባት በኤፌሶን የሚኖሩ አንዳንድ ክርስቲያን ወንድሞች ባለጸጋዎች ከመሆናቸው የተነሳ ባሪያዎች ያላቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ ባሪያዎች ምናልባትም በድህነት የሚኖሩ እንደነበሩ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። (ኤፌ. 6:5, 9) በሌላ በኩል አንዳንዶቹ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በምኩራባቸው ውስጥ ለሦስት ወራት ባስተማረበት ጊዜ እውነትን የተቀበሉ አይሁዳውያን ናቸው። ሌሎች ደግሞ አርጤምስን የሚያመልኩና አስማት የሚሠሩ ሰዎች ነበሩ። (ሥራ 19:8, 19, 26) ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው እውነተኛ ክርስትና ከተለያየ አገርና የኅብረተሰብ ክፍል የመጡ ሰዎችን አንድ አድርጓል። ጳውሎስ ጉባኤው ያለው አንድነት ይሖዋን እንደሚያስከብር ተገንዝቦ ነበር። ሐዋርያው “ለእሱ በጉባኤው . . . አማካኝነት ክብር ይሁን” በማለት ጽፏል።—ኤፌ. 3:21
2. የኤፌሶን ክርስቲያኖች ያላቸው አንድነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ ያደረገው ምን ነበር?
2 ይሁንና በኤፌሶን ጉባኤ ውስጥ የሚታየው እንዲህ ያለው አስደሳች አንድነት አደጋ ላይ ወድቆ ነበር። ጳውሎስ ሽማግሌዎቹን “ከእናንተ ከራሳችሁ መካከል እንኳ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች ይነሳሉ” ሲል አስጠንቅቋቸው ነበር። (ሥራ 20:30) በተጨማሪም አንዳንድ ወንድሞች ጳውሎስ ‘በማይታዘዙት ልጆች ላይ እንደሚሠራ’ የገለጸውን መከፋፈል የሚፈጥር መንፈስ ሙሉ በሙሉ አላስወገዱም ነበር።—ኤፌ. 2:2፤ 4:22
አንድነት ላይ ትኩረት የሚያደርግ ደብዳቤ
3, 4. ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ለአንድነት ትኩረት የሰጠው እንዴት ነው?
3 ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች ተስማምተውና ተባብረው መሥራታቸውን መቀጠል እንዲችሉ ከተፈለገ እያንዳንዳቸው አንድነታቸውን ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ተገንዝቦ ነበር። ሐዋርያው ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ደብዳቤ እንዲጽፍ አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት የመራው ሲሆን ደብዳቤውም ትኩረት ያደረገው በአንድነት ላይ ነበር። ለምሳሌ ጳውሎስ፣ አምላክ “ሁሉንም ነገሮች . . . እንደገና በክርስቶስ አንድ ላይ ለመጠቅለል” ዓላማ እንዳለው ጽፏል። (ኤፌ. 1:10) በተጨማሪም ክርስቲያኖችን፣ አንድን ሕንጻ ለመገንባት ከሚያገለግሉ የተለያዩ ድንጋዮች ጋር በማነጻጸር እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ሕንጻው በሙሉ ከእሱ ጋር አንድ ላይ በመሆን ስምም ሆኖ እየተጋጠመ የይሖዋ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ለመሆን በማደግ ላይ ነው።” (ኤፌ. 2:20, 21) ከዚህም በላይ ጳውሎስ አይሁዳዊና አሕዛብ የሆኑ ክርስቲያኖች በሙሉ አንድ መሆናቸውን ጎላ አድርጎ የጠቀሰ ሲሆን ሁሉንም የፈጠራቸው አምላክ መሆኑን ወንድሞችን አስታውሷቸዋል። “በሰማይና በምድር ያለ እያንዳንዱ ቤተሰብ ስያሜውን ያገኘው” ከይሖዋ እንደሆነ ገልጿል።—ኤፌ. 3:5, 6, 14, 15
4 ኤፌሶን ምዕራፍ 4ን በምንመረምርበት ጊዜ አንድነት እንዲኖር ጥረት ማድረግ ይጠይቃል የምንለው ለምን እንደሆነ፣ ይሖዋ አንድ እንድንሆን የሚረዳን እንዴት እንደሆነና አንድነታችንን ጠብቀን ለመኖር የትኞቹን አስተሳሰቦች ማዳበር እንዳለብን እንመለከታለን። ከዚህ ጥናት ይበልጥ ጥቅም እንድታገኝ ምዕራፍ 4ን ሙሉውን እንድታነበው እናበረታታሃለን።
አንድነትን ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
5. መላእክት አምላክን አንድ ሆነው ማገልገል የቻሉት ለምንድን ነው? አንድነታችንን መጠበቅ ለእኛ ይበልጥ ተፈታታኝ የሚሆንብን ለምን ሊሆን ይችላል?
5 ጳውሎስ በኤፌሶን የሚገኙት ወንድሞቹ “የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት” እንዲያደርጉ መክሯቸዋል። (ኤፌ. 4:3) በዚህ ረገድ ጥረት ማድረግ ያለውን አስፈላጊነት ለመረዳት የአምላክን መላእክት ሁኔታ እንመልከት። በምድር ላይ ያሉ ሁለት ሕያዋን ነገሮች ፍጹም አንድ ዓይነት ሊሆኑ አይችሉም፤ ከዚህ በመነሳት ይሖዋ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መላእክትን አንዳቸው ከሌላው የተለዩ እንዲሆኑ አድርጎ ፈጥሯቸዋል ብለን መደምደም እንችላለን። (ዳን. 7:10) ያም ሆኖ ይሖዋን አንድ ሆነው ማገልገል ይችላሉ፤ ምክንያቱም ሁሉም እሱን ይሰማሉ እንዲሁም ፈቃዱን ያደርጋሉ። (መዝሙር 103:20, 21ን አንብብ።) ታማኝ የሆኑ መላእክት የተለያዩ ባሕርያት ያሏቸው ሲሆን ክርስቲያኖች ደግሞ ከዚህም ባሻገር የተለያዩ ድክመቶች አሏቸው። ይህ ደግሞ አንድነትን መጠበቅ ይበልጥ ተፈታታኝ እንዲሆን ያደርጋል።
6. ከእኛ የተለየ ድክመት ካለባቸው ወንድሞች ጋር ተባብረን ለመሥራት የትኞቹ ባሕርያት ሊረዱን ይችላሉ?
6 ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ተባብረው ለመሥራት በሚሞክሩበት ጊዜ በቀላሉ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ገር የሆነ ሆኖም የማርፈድ ልማድ ያለው አንድ ወንድም፣ ቀጠሮ አክባሪ ቢሆንም በቀላሉ ከሚቆጣ ወንድም ጋር ይሖዋን ቢያገለግል ምን ሊፈጠር ይችላል? ሁለቱም ወንድሞች የሌላው ባሕርይ ተገቢ እንዳልሆነ በማሰብ አንዳቸው ሌላውን ይወቅሱ ይሆናል፤ ይሁንና ሁለቱም ወንድሞች የራሳቸው ባሕርይ ከሌላው ባልተናነሰ ችግር እንዳለው ሊዘነጉ ይችላሉ። ታዲያ እንዲህ ያሉ ሁለት ወንድሞች ስምም ሆነው በአንድነት ሊያገለግሉ የሚችሉት እንዴት ነው? ጳውሎስ ከታች ባለው ጥቅስ ላይ የገለጻቸው ባሕርያት እንዴት ሊረዷቸው እንደሚችሉ ልብ በሉ። ከዚያም እነዚህን ባሕርያት በማዳበር በመካከላችን አንድነት እንዲኖር አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ እንሞክር። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከተጠራችሁበት ጥሪ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ በፍጹም ትሕትናና ገርነት፣ በትዕግሥት እንዲሁም እርስ በርሳችሁ በፍቅር በመቻቻል ኑሩ፤ አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት አድርጉ።”—ኤፌ. 4:1-3
7. ፍጽምና ከጎደላቸው ክርስቲያኖች ጋር በአንድነት ለማገልገል ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
7 ፍጽምና ከጎደላቸው ክርስቲያኖች ጋር በአንድነት አምላክን ማገልገል መማር እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮችን ያቀፈው አካል አንድ ብቻ ነው። ጳውሎስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል፦ “በተጠራችሁ ጊዜ በአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት፣ አንድ ጥምቀት አለ፤ ደግሞም የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ።” (ኤፌ. 4:4-6) የይሖዋ መንፈስና በረከት አምላክ እየተጠቀመበት ካለው ብቸኛ የወንድማማች ማኅበር ጋር ተያይዞ ተጠቅሷል። በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ግለሰብ ቢያስቀይመን እንኳ ወዴት መሄድ እንችላለን? የዘላለም ሕይወትን ቃል መስማት የምንችልበት ሌላ የትም ቦታ የለም።—ዮሐ. 6:68
‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ አንድነት እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደርጋሉ
8. ክርስቶስ አንድነታችንን ሊያናጉ የሚችሉ ተጽዕኖዎችን መቋቋም እንድንችል ምን ዝግጅት አድርጎልናል?
8 ኢየሱስ ጉባኤውን አንድ ለማድረግ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ያዘጋጀው እንዴት እንደሆነ ጳውሎስ በምሳሌ ሲያስረዳ በጥንት ዘመን የሚኖሩ ወታደሮች የነበራቸውን ልማድ ጠቅሷል። አንድ ድል አድራጊ ወታደር ከሌላ አገር የማረከውን ሰው የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት ሚስቱን የሚያግዝ ባሪያ እንዲሆን ያደርገው ነበር። (መዝ. 68:1, 12, 18) በተመሳሳይም ኢየሱስ ዓለምን ድል ሲያደርግ በርካታ ፈቃደኛ ባሪያዎችን አግኝቷል። (ኤፌሶን 4:7, 8ን አንብብ።) በምሳሌያዊ ሁኔታ ምርኮኛ የሆኑትን እነዚህን ሰዎች የተጠቀመባቸው እንዴት ነው? “አንዳንዶቹን ሐዋርያት፣ አንዳንዶቹን ነቢያት፣ አንዳንዶቹን ወንጌላውያን፣ አንዳንዶቹን ደግሞ እረኞችና አስተማሪዎች አድርጎ ሰጠ፤ ይህንም ያደረገው ቅዱሳንን እንዲያስተካክሉ፣ ሌሎችን እንዲያገለግሉና የክርስቶስን አካል እንዲገነቡ ነው፤ ይህም ሁላችንም በእምነት . . . ወደሚገኘው አንድነት . . . እስክንደርስ ነው።”—ኤፌ. 4:11-13
9. (ሀ) ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ አንድነታችንን ጠብቀን ለመኖር የሚረዱን እንዴት ነው? (ለ) እያንዳንዱ የጉባኤ አባል ለወንድማማች ማኅበሩ አንድነት አስተዋጽኦ ማበርከት የሚኖርበት ለምንድን ነው?
9 እነዚህ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ አፍቃሪ እረኞች በመሆን አንድነታችንን እንድንጠብቅ ይረዱናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ በሁለት ወንድሞች መካከል “የፉክክር መንፈስ” እንዳለ ካስተዋለ እነሱን “በገርነት መንፈስ ለማስተካከል” በግል ምክር በመስጠት ለጉባኤው አንድነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። (ገላ. 5:26 እስከ 6:1) እነዚህ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ አስተማሪዎች እንደመሆናቸው መጠን በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖረን ይረዱናል። በዚህ መንገድ አንድነት እንዲኖር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ከመሆኑም ሌላ ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና እንድናድግ ይረዱናል። ጳውሎስ ይህን ማድረጋቸው አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ከእንግዲህ ሕፃናት መሆን የለብንም፤ በማዕበል የምንነዳ ይመስል በማንኛውም የትምህርት ነፋስ፣ በሰዎች የማታለያ ዘዴና በተንኮል በተወጠነ አሳሳች ሐሳብ የምንንገዋለልና ወዲያና ወዲህ የምንል መሆን የለብንም።” (ኤፌ. 4:13, 14) እያንዳንዱ የአካላችን ክፍል አስፈላጊ የሆነውን ነገር በማቅረብ ሌላውን እንደሚያንጽ ሁሉ እያንዳንዱ ክርስቲያንም ለወንድማማች ማኅበሩ አንድነት አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርበታል።—ኤፌሶን 4:15, 16ን አንብብ።
አዲስ ዓይነት አስተሳሰብ አዳብሩ
10. ሥነ ምግባር የጎደለው ባሕርይ አንድነታችንን ሊያናጋ የሚችለው እንዴት ነው?
10 ጳውሎስ በኤፌሶን ለሚገኙ ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ አራተኛ ምዕራፍ የጎለመስን ክርስቲያኖች በመሆን አንድነታችንን ለመጠበቅ ቁልፉ ፍቅር ማሳየት መሆኑን እንደሚጠቁም አስተውላችኋል? ሐዋርያው ፍቅር ማሳየት ምን እንደሚጨምር ቀጥሎ አብራርቷል። ለምሳሌ ያህል፣ የፍቅርን መንገድ የሚከተል ሰው ከዝሙትና ከብልግና ይርቃል። ጳውሎስ ‘አሕዛብ እንደሚመላለሱ እነሱም እንዳይመላለሱ’ ወንድሞቹን አሳስቧቸዋል። ጳውሎስ የጠቀሳቸው ሰዎች ‘የሥነ ምግባር ስሜታቸው የደነዘዘ’ ከመሆኑም ሌላ “ራሳቸውን ለብልግና አሳልፈው ሰጥተዋል።” (ኤፌ. 4:17-19) በሥነ ምግባር ያዘቀጠው ይህ ዓለም አንድነታችንን አደጋ ላይ ይጥላል። ሰዎች በቀልዱም፣ በዘፈኑም ሆነ በመዝናኛው ውስጥ ከዝሙት ጋር የተያያዙ ነገሮችን ማስገባታቸው የተለመደ ሆኗል፤ ከዚህም በላይ እንዲህ ያለውን ድርጊት በድብቅ ወይም በግልጽ ይፈጽማሉ። አንድ ክርስቲያን ግን ሌሎችን ማሽኮርመሙ እንኳ ከይሖዋና ከጉባኤው ሊያርቀው ይችላል፤ ማሽኮርመም የማግባት ሐሳብ ሳይኖርህ ለአንድ ሰው የፍቅር ስሜት ማሳየትን ይጨምራል። እንዲህ ማድረግ በቀላሉ ዝሙት ወደ መፈጸም ሊመራ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ማሽኮርመም አንድን ባለትዳር ምንዝር እንዲፈጽም ሊያደርገው ይችላል፤ ይህ ደግሞ ልጆች ከወላጆች እንዲነጠሉ እንዲሁም በደል የተፈጸመበት የትዳር ጓደኛ ከአጋሩ እንዲለያይ ሊያደርግ ስለሚችል አሳዛኝ መዘዝ ያስከትላል። በእርግጥም ዝሙት መከፋፈልን ይፈጥራል! ጳውሎስ “እናንተ ግን ክርስቶስን የተማራችሁት እንደዚህ አይደለም” ማለቱ ምንኛ የተገባ ነው!—ኤፌ. 4:20, 21
11. መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ለውጥ እንዲያደርጉ ያበረታታል?
11 ጳውሎስ መከፋፈል የሚፈጥር አስተሳሰብን በማስወገድ ከሌሎች ጋር ተስማምተን ለመኖር የሚያስችለንን አመለካከት ማዳበር እንደሚኖርብን አበክሮ ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “ከቀድሞ አኗኗራችሁ ጋር የሚስማማውንና አታላይ በሆነው ምኞቱ እየተበላሸ የሚሄደውን አሮጌውን ስብዕናችሁን አውልቃችሁ መጣል አለባችሁ፤ . . . አእምሯችሁን በሚያሠራው ኃይል እየታደሳችሁ መሄድ አለባችሁ፤ እንዲሁም እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና መልበስ ይኖርባችኋል።” (ኤፌ. 4:22-24) ‘አእምሯችንን በሚያሠራው ኃይል መታደስ’ የምንችለው እንዴት ነው? ከአምላክ ቃል እንዲሁም የጎለመሱ ክርስቲያኖች ከተዉት ግሩም ምሳሌ በምናገኘው ትምህርት ላይ በአድናቆት ስሜት የምናሰላስል ከሆነ “እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውን” አዲሱን ስብዕና መልበስ እንችላለን፤ እርግጥ ይህን ማድረግ ጥረት ይጠይቃል።
አዲስ ዓይነት አነጋገር አዳብሩ
12. እውነትን መናገር ለአንድነት አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው? አንዳንዶች እውነትን መናገር የሚከብዳቸው ለምንድን ነው?
12 በቤተሰብ ወይም በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የአንድ አካል ክፍሎች በመሆናቸው እርስ በርሳቸው እውነትን መነጋገራቸው አስፈላጊ ነው። ግልጽ በሆነ እንዲሁም ሐቀኝነትና ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ መነጋገር ሰዎችን ያቀራርባል። (ዮሐ. 15:15) ይሁንና አንድ ሰው ወንድሙን ቢዋሸውስ? ወንድሙ ስለ ጉዳዩ በሚያውቅበት ጊዜ በመካከላቸው የነበረው የመተማመን ስሜት ይቀንሳል። ከዚህ አንጻር ጳውሎስ “እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ ምክንያቱም ሁላችንም የአንድ አካል ክፍሎች ነን” ያለበትን ምክንያት መረዳት ይቻላል። (ኤፌ. 4:25) መዋሸት ልማድ የሆነበት ሰው በተለይ ደግሞ ከልጅነቱ ጀምሮ ያደገበት ከሆነ እውነትን መናገር ሊከብደው ይችላል። ይሁን እንጂ ግለሰቡ ለመለወጥ የሚያደርገውን ጥረት ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ከመሆኑም በላይ ይረዳዋል።
13. ስድብን ማስወገድ ሲባል ምን ነገሮችን ይጨምራል?
13 የምንናገርበትን መንገድ በመቆጣጠር በጉባኤም ሆነ በቤተሰባችን ውስጥ መከባበርና አንድነት እንዲኖር የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንድናደርግ ይሖዋ ያስተምረናል። “የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ። የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ መካከል ይወገድ።” (ኤፌ. 4:29, 31) ሌሎችን የሚያስቀይም አነጋገርን ማስወገድ የምንችልበት አንዱ መንገድ ለሌሎች አክብሮት የተሞላበት አመለካከት እንዲኖረን ጥረት ማድረግ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ሚስቱን የሚሳደብና የሚያንቋሽሽ ባል ለእሷ ያለውን አመለካከት ለማስተካከል ጥረት ማድረግ አለበት፤ በተለይ ደግሞ ይሖዋ ሴቶችን በአክብሮት የሚይዝበትን መንገድ ሲማር እሱም እንዲህ ማድረጉ አስፈላጊ ነው። አምላክ አንዳንድ ሴቶችን በመንፈስ ቅዱስ በመቀባት ከክርስቶስ ጋር ነገሥታት የመሆን መብት እንኳ ሰጥቷቸዋል። (ገላ. 3:28፤ 1 ጴጥ. 3:7) በሌላ በኩል ደግሞ ባሏ ላይ የመጮኽ ልማድ ያላት አንዲት ሴት፣ ኢየሱስ የሚያስቆጣ ነገር ሲያጋጥመው ራሱን የተቆጣጠረው እንዴት እንደሆነ መማሯ ለባሏ ያላትን አመለካከት እንድትለውጥ ሊገፋፋት ይገባል።—1 ጴጥ. 2:21-23
14. ቁጣን አለመቆጣጠር አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?
14 ከስድብ ጋር ተያያዥነት ያለው ሌላው መጥፎ ባሕርይ ቁጣን አለመቆጣጠር ነው። ይህም የአንድ አካል ክፍሎች በሆኑ ሰዎች መካከል መለያየት ሊፈጥር ይችላል። ቁጣ ልክ እንደ እሳት ነው። በቀላሉ ከቁጥጥር ውጪ ሊሆንና ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። (ምሳሌ 29:22) አንድ ወንድም ሌላ ሰው በሚያሳዝነው ጊዜ ቅሬታውን መግለጹ ተገቢ ቢሆንም ከግለሰቡ ጋር ያለውን ውድ ዝምድና ላለማጣት ቁጣውን መቆጣጠር ይኖርበታል። ክርስቲያኖች ቂም ባለመያዝና ጉዳዩን ዳግመኛ ከማንሳት በመቆጠብ ይቅር ባዮች ለመሆን ጥረት ማድረግ አለባቸው። (መዝ. 37:8፤ 103:8, 9፤ ምሳሌ 17:9) ጳውሎስ የኤፌሶን ክርስቲያኖችን ሲመክራቸው “ተቆጡ፤ ነገር ግን ኃጢአት አትሥሩ፤ ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ፤ ዲያብሎስም ስፍራ እንዲያገኝ አትፍቀዱለት” ብሏል። (ኤፌ. 4:26, 27) ቁጣን አለመቆጣጠር ዲያብሎስ በጉባኤው ውስጥ መከፋፈል አልፎ ተርፎም ግጭት ለመፍጠር አጋጣሚ እንዲያገኝ ያደርገዋል።
15. የእኛ ንብረት ያልሆነውን ነገር መውሰድ ምን ሊያስከትል ይችላል?
15 የሌሎችን ንብረት ከመውሰድ መቆጠብ ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ ያደርጋል። ጳውሎስ “የሚሰርቅ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ” ብሏል። (ኤፌ. 4:28) በጥቅሉ ሲታይ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል የመተማመን መንፈስ አለ። አንድ ክርስቲያን የእሱ ያልሆነውን ነገር በመውሰድ ይህን የመተማመን መንፈስ የሚያደፈርስ ከሆነ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለውን አስደሳች አንድነት ያናጋዋል።
ለአምላክ ያለን ፍቅር አንድ አድርጎናል
16. አንድነታችንን ለማጠናከር የሚያንጽ ቃል መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
16 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አንድነት ሊኖር የቻለው አባላቱ በሙሉ ለአምላክ ባላቸው ፍቅር ተገፋፍተው ሌሎችን በፍቅር በመያዛቸው ነው። ይሖዋ ላሳየን ደግነት ያለን አድናቆት የሚከተለውን ምክር በተግባር ለማዋል ልባዊ ጥረት እንድናደርግ ያነሳሳናል፦ “እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል ማንኛውም መልካም ቃል [ተናገሩ]፤ . . . አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ።” (ኤፌ. 4:29, 32) ይሖዋ እንደ እኛ ያሉ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎችን በደግነት ይቅር ይላል። እኛስ ሌሎች ፍጹማን ባለመሆናቸው ምክንያት የሚሠሯቸውን ስህተቶች ይቅር ማለት አይኖርብንም?
17. ለአንድነታችን አስተዋጽኦ ለማበርከት ልባዊ ጥረት ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
17 የአምላክ ሕዝቦች ያላቸው አንድነት ይሖዋን ያስከብራል። የአምላክ መንፈስ ለዚህ አንድነት አስተዋጽኦ እንድናደርግ በተለያዩ መንገዶች ይረዳናል። የመንፈሱን አመራር መቃወም እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ጳውሎስ “የአምላክን ቅዱስ መንፈስ አታሳዝኑ” በማለት ጽፏል። (ኤፌ. 4:30) አንድነት ልንንከባከበው የሚገባ ውድ ሀብት ነው። በዚህ አንድነት ውስጥ ለታቀፉ ሁሉ ደስታ የሚያመጣ ሲሆን ይሖዋንም ያስከብራል። “ስለዚህ የተወደዳችሁ ልጆች በመሆን አምላክን የምትኮርጁ ሁኑ። . . . [እንዲሁም] በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ።”—ኤፌ. 5:1, 2
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• በክርስቲያኖች መካከል አንድነት እንዲኖር አስተዋጽኦ የሚያደርገው ምን ዓይነት አስተሳሰብ ነው?
• ሥነ ምግባራችን ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?
• አነጋገራችን ከሌሎች ጋር ተባብረን ለመሥራት የሚረዳን እንዴት ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከተለያየ አገርና የኅብረተሰብ ክፍል የመጡ ሰዎች አንድ ሆነዋል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማሽኮርመም ያለውን አደጋ ትገነዘባለህ?