የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ አታሳዝኑ
“የታተማችሁበትን የአምላክን ቅዱስ መንፈስ አታሳዝኑ።”—ኤፌ. 4:30
1. ይሖዋ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ምን አድርጎላቸዋል? እነዚህ ሰዎችስ ምን ኃላፊነት አለባቸው?
ይሖዋ በዚህ አስቸጋሪ ዓለም ውስጥ ለሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ልዩ የሆነ ነገር አድርጎላቸዋል። በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እሱ መቅረብ የሚችሉበትን አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። (ዮሐ. 6:44) አንተም ራስህን ለአምላክ ወስነህ ከዚህ ውሳኔህ ጋር በሚስማማ መንገድ እየኖርክ ከሆነ ወደ ይሖዋ መቅረብ ከቻሉት ግለሰቦች አንዱ ነህ ማለት ነው። በመንፈስ ቅዱስ ስም የተጠመቅክ እንደመሆንህ መጠን ከዚህ መንፈስ ጋር በሚስማማ መንገድ የመኖር ኃላፊነት አለብህ።—ማቴ. 28:19
2. የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
2 ‘ለመንፈስ ብለን የምንዘራ’ ሁላችን አዲሱን ስብዕና ለብሰናል። (ገላ. 6:8፤ ኤፌ. 4:17-24) ያም ቢሆን የአምላክን ቅዱስ መንፈስ እንዳናሳዝን ሐዋርያው ጳውሎስ ምክርና ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል። (ኤፌሶን 4:25-32ን አንብብ።) እስቲ ሐዋርያው የሰጠንን ምክር አንድ በአንድ እንመርምረው። ጳውሎስ የአምላክን መንፈስ ማሳዘን ሲል ምን ማለቱ ነበር? ራሱን ለይሖዋ የወሰነ አንድ ግለሰብ እንዲህ ያለ ነገር ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው? የይሖዋን መንፈስ ላለማሳዘን መጠንቀቅ የምንችለውስ እንዴት ነው?
ጳውሎስ ምን ማለቱ ነበር?
3. በኤፌሶን 4:30 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እንዴት ታብራራዋለህ?
3 እስቲ መጀመሪያ በኤፌሶን 4:30 ላይ የሚገኘውን ጳውሎስ የተናገረውን ሐሳብ እንመልከት። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በቤዛው ነፃ ለምትወጡበት ቀን የታተማችሁበትን የአምላክን ቅዱስ መንፈስ አታሳዝኑ።” ጳውሎስ የሚወዳቸው የእምነት ባልንጀሮቹ መንፈሳዊነታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር እንዲያደርጉ አልፈለገም። እነዚህ ክርስቲያኖች ‘በቤዛው ነፃ ለሚወጡበት ቀን የታተሙት’ በይሖዋ መንፈስ አማካኝነት ነበር። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ፣ ንጹሕ አቋማቸውን ለጠበቁ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ማኅተም ወይም ‘ወደፊት ለሚመጣው ነገር መያዣ’ ነበር፤ አሁንም በዚህ መንገድ ያገለግላል። (2 ቆሮ. 1:22) ይህ ማኅተም የአምላክ ንብረት መሆናቸውንና ወደፊት ሰማያዊ ሕይወት እንደሚያገኙ የሚያመለክት ነው። የታተሙት አጠቃላይ ቁጥር 144,000 ይሆናል።—ራእይ 7:2-4
4. የአምላክን መንፈስ ላለማሳዘን መጠንቀቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
4 አንድ ክርስቲያን የአምላክን መንፈስ ማሳዘኑ ይህን መንፈስ ሙሉ በሙሉ ወደማጣት ሊመራው ይችላል። ይህ ሊሆን እንደሚችል ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ኃጢአት ከፈጸመ በኋላ ከተናገረው ነገር በግልጽ መመልከት ይቻላል። ዳዊት በጸጸት ስሜት ተውጦ ይሖዋን “ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድ” በማለት ለምኖታል። (መዝ. 51:11) በሰማይ የማይሞት ሕይወትን “አክሊል” ማግኘት የሚችሉት “እስከ ሞት ድረስም እንኳ ታማኝ” የሆኑት ቅቡዓን ብቻ ናቸው። (ራእይ 2:10፤ 1 ቆሮ. 15:53) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋማቸውን ለመጠበቅ መንፈስ ቅዱስ ያስፈልጋቸዋል፤ ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቃቸው ደግሞ አምላክ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ላላቸው ሰዎች ያዘጋጀውን የሕይወት ሽልማት ለማግኘት ያስችላቸዋል። (ዮሐ. 3:36፤ ሮም 5:8፤ 6:23) በመሆኑም የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ ላለማሳዘን ሁላችንም መጠንቀቅ ይኖርብናል።
አንድ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስን ሊያሳዝን የሚችለው እንዴት ነው?
5, 6. አንድ ክርስቲያን የይሖዋን መንፈስ ሊያሳዝን የሚችለው እንዴት ነው?
5 ራሳችንን ለአምላክ የወሰንን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የአምላክን መንፈስ ከማሳዘን መቆጠብ እንችላለን። ‘በመንፈስ መመላለሳችንን የምንቀጥልና በመንፈስ የምንኖር ከሆነ’ በተሳሳቱ የሥጋ ምኞቶች አንሸነፍም ብሎም መጥፎ ባሕርያትን እናስወግዳለን፤ ይህም የአምላክን መንፈስ ከማሳዘን እንድንቆጠብ ይረዳናል። (ገላ. 5:16, 25, 26) ይሁንና ይህ አቋማችን ሊለወጥ ይችላል። በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈው ቃሉ የሚያወግዛቸውን ድርጊቶች ወደ መፈጸም የሚያደርስ አካሄድ መከተል ከጀመርን በተወሰነ መጠንም ቢሆን የአምላክን መንፈስ ልናሳዝን እንችላለን፤ እንዲህ ያለውን አካሄድ የምንከተለው ቀስ በቀስ ምናልባትም ሳይታወቀን ሊሆን ይችላል።
6 መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጠን አመራር ተቃራኒ በሆነ አቅጣጫ መሄዳችንን የምንቀጥል ከሆነ ይህን መንፈስም ሆነ የዚህ መንፈስ ምንጭ የሆነውን ይሖዋን እናሳዝናለን። ኤፌሶን 4:26-32ን መመርመራችን እንዴት ዓይነት አኗኗር መከተል እንዳለብን ለማወቅና የአምላክን መንፈስ ከማሳዘን ለመቆጠብ ይረዳናል።
መንፈሱን ከማሳዘን መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው?
7, 8. እውነተኞች መሆን ያለብን ለምን እንደሆነ አብራራ።
7 እውነተኞች መሆን አለብን። ጳውሎስ በኤፌሶን 4:25 ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አሁን ውሸትን ስላስወገዳችሁ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ ምክንያቱም ሁላችንም የአንድ አካል ክፍሎች ነን።” እንደ “አንድ አካል ክፍሎች” አንድነት ያለን በመሆናችን ተንኮለኞች መሆን በሌላ አባባል የእምነት ባልንጀሮቻችንን ሆን ብለን ማሳሳት የለብንም፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረግ ውሸት ከመናገር ተለይቶ አይታይም። እንዲህ ያለ አካሄድ መከተሉን የሚቀጥል ሰው ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ያጣል።—ምሳሌ 3:32ን በNW አንብብ።a
8 አንድ ሰው በተንኮል ተነሳስቶ የሚናገራቸው ወይም የሚያደርጋቸው ነገሮች የጉባኤውን አንድነት ያናጋሉ። በመሆኑም ምንም ስህተት እንዳልተገኘበት እንደ ነቢዩ ዳንኤል ታማኝ መሆን ይኖርብናል። (ዳን. 6:4) እንዲሁም ጳውሎስ፣ ሰማያዊ ተስፋ ላላቸው ክርስቲያኖች የሰጠውን ምክር ልብ ልንል ይገባል፤ ጳውሎስ ‘የክርስቶስ አካል’ ክፍል የሆኑት ሁሉ የአንድ አካል ክፍሎች እንደሆኑና እውነተኛ ከሆኑት የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች ጋር ያላቸውን አንድነት መጠበቅ እንዳለባቸው ገልጿል። (ኤፌ. 4:11, 12) እኛም በምድር ላይ በገነት ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የምናደርግ ከሆነ እውነትን መናገር አለብን፤ እንዲህ ስናደርግ ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበራችን አንድነት አስተዋጽኦ እናደርጋለን።
9. በኤፌሶን 4:26, 27 ላይ የሚገኘውን ምክር በተግባር ማዋላችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
9 ዲያብሎስ በመንፈሳዊነታችን ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚያስችለው አጋጣሚ እንዲያገኝ ባለመፍቀድ ልንቃወመው ይገባል። (ያዕ. 4:7) መንፈስ ቅዱስ ሰይጣንን እንድንቃወም ይረዳናል። ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ቁጣችን ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን መጠንቀቅ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ተቆጡ፤ ነገር ግን ኃጢአት አትሥሩ፤ ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ፤ ዲያብሎስም ስፍራ እንዲያገኝ አትፍቀዱለት።” (ኤፌ. 4:26, 27) እንድንቆጣ ያደረገን በቂ ምክንያት ቢኖረንም እንኳ ወዲያውኑ በልባችን መጸለያችን የአምላክን መንፈስ የሚያሳዝን ነገር ከመፈጸም ይልቅ ራሳችንን በመግዛት ‘የረጋ መንፈስ’ እንዲኖረን ይረዳናል። (ምሳሌ 17:27) እንግዲያው ተቆጥተን በመቆየት ሰይጣን ክፉ ድርጊት ወደመፈጸም እንዲገፋፋን አንፍቀድ። (መዝ. 37:8, 9) ዲያብሎስን መቃወም የምንችልበት አንዱ መንገድ አለመግባባቶችን ኢየሱስ ከሰጠው ምክር ጋር በሚስማማ ሁኔታ ቶሎ መፍታት ነው።—ማቴ. 5:23, 24፤ 18:15-17
10, 11. መስረቅ ወይም ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት መፈጸም የሌለብን ለምንድን ነው?
10 እንድንሰርቅ ወይም ሐቀኝነታችንን እንድናጎድል ለሚቀርብልን ፈተና መሸነፍ የለብንም። ጳውሎስ ስርቆትን አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የሚሰርቅ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፤ ከዚህ ይልቅ ለተቸገረ ሰው ሊሰጥ የሚችለው ነገር እንዲኖረው በእጆቹ መልካም ተግባር እያከናወነ በትጋት ይሥራ።” (ኤፌ. 4:28) አንድ ራሱን የወሰነ ክርስቲያን የሚሰርቅ ከሆነ በአምላክ ስም ላይ ነቀፋ በማምጣት ‘የአምላክን ስም ያሰድባል።’ (ምሳሌ 30:7-9) ድህነትም እንኳ ለመስረቅ ሰበብ ሊሆን አይችልም። አምላክንና ባልንጀራቸውን የሚወዱ ሰዎች ለስርቆት ምክንያት ሊሆን የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ ይገነዘባሉ።—ማር. 12:28-31
11 ጳውሎስ ማድረግ የሌለብንን ነገሮች ብቻ በመናገር ሳይወሰን ልናደርጋቸው የሚገቡ ነገሮችንም ገልጿል። በመንፈስ ቅዱስ የምንኖርና የምንመላለስ ከሆነ ቤተሰባችንን መንከባከብ አልፎ ተርፎም ‘ለተቸገረ ሰው የምንሰጠው ነገር’ ማግኘት እንድንችል ተግተን እንሠራለን። (1 ጢሞ. 5:8) ኢየሱስና ሐዋርያቱ ድሆችን ለመርዳት ገንዘብ ያጠራቅሙ ነበር፤ ይሁንና ከዳተኛው የአስቆሮቱ ይሁዳ ወደ ሣጥኑ ከሚገባው ገንዘብ ይወስድ ነበር። (ዮሐ. 12:4-6) ይሁዳ በመንፈስ ቅዱስ ይመራ እንዳልነበር ምንም ጥርጥር የለውም። እኛም በመንፈስ ቅዱስ የምንመራ ከሆነ ጳውሎስ እንዳደረገው “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር” ጥረት እናደርጋለን። (ዕብ. 13:18) ይህም የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ ከማሳዘን እንድንቆጠብ ይረዳናል።
የአምላክን መንፈስ ከማሳዘን የምንቆጠብባቸው ሌሎች አቅጣጫዎች
12, 13. (ሀ) በኤፌሶን 4:29 ላይ እንደተገለጸው ምን ዓይነት አነጋገርን ልናስወግድ ይገባል? (ለ) ንግግራችን ምን ዓይነት ሊሆን ይገባል?
12 አንደበታችንን መቆጣጠር ይኖርብናል። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል ማንኛውም መልካም ቃል እንጂ የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ።” (ኤፌ. 4:29) እዚህ ላይም ቢሆን ሐዋርያው ማድረግ የሌለብንን ነገር ከመናገር አልፎ ልናደርገው የሚገባንን ነገር ተናግሯል። በአምላክ መንፈስ የምንመራ ከሆነ ‘ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል መልካም የሆነ ቃል ለመናገር’ እንነሳሳለን። ከዚህም በተጨማሪ “የበሰበሰ ቃል” ከአፋችን ማውጣት የለብንም። “የበሰበሰ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል መሽተት የጀመረን ፍሬ፣ ዓሣ ወይም ሥጋ ለማመልከት ተሠርቶበታል። እንዲህ ያለውን ምግብ እንደምንጸየፈው ሁሉ ይሖዋ መጥፎ እንደሆነ የገለጸውን ንግግርም መጥላት ይኖርብናል።
13 ንግግራችን ጨዋነትና ደግነት የሚንጸባረቅበት ማለትም “በጨው የተቀመመ” መሆን ይኖርበታል። (ቆላ. 3:8-10፤ 4:6) አነጋገራችን ከሌሎች የተለየን መሆናችንን የሚያሳይ ሊሆን ይገባል። ስለዚህ “የሚያንጽ” ነገር በመናገር ሌሎችን እንርዳ። እንዲሁም “መጠጊያዬና አዳኜ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአፌ ቃልና የልቤ ሐሳብ፣ በፊትህ ያማረ ይሁን” ብሎ እንደዘመረው መዝሙራዊ ዓይነት አመለካከት እናዳብር።—መዝ. 19:14
14. በኤፌሶን 4:30, 31 መሠረት የትኞቹን ባሕርያት ማስወገድ ይኖርብናል?
14 የመረረ ጥላቻን፣ ንዴትን፣ ስድብንና ክፋትን ሁሉ ማስወገድ ይኖርብናል። ጳውሎስ ክርስቲያኖች የአምላክን መንፈስ እንዳያሳዝኑ ካስጠነቀቀ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ መካከል ይወገድ።” (ኤፌ. 4:30, 31) ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደመሆናችን ሁላችንም አስተሳሰባችንንና ድርጊታችንን ለመቆጣጠር ብርቱ ትግል ማድረግ አለብን። “የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ [እና] ንዴት” እንዲቆጣጠረን ከፈቀድን የአምላክን መንፈስ እናሳዝናለን። የተፈጸመብንን በደል አንድ በአንድ የምንቆጥር፣ ቂም የምንይዝ እንዲሁም ቅር ካሰኘን ሰው ጋር ለመታረቅ እምቢተኞች የምንሆን ከሆነ መንፈስ ቅዱስን እናሳዝናለን። የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ችላ ማለት ከጀመርን በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ወደመሥራት የሚመሩንን ባሕርያት ልናዳብር እንችላለን፤ ይህ ደግሞ አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል።
15. አንድ ሰው ቢበድለን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
15 ደግ፣ ሩኅሩኅና ይቅር ባይ መሆን አለብን። ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ ጽፏል፦ “አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ።” (ኤፌ. 4:32) በተፈጸመብን በደል ስሜታችን በጣም ተጎድቶ ሊሆን ቢችልም እንኳ እኛም እንደ አምላክ ይቅር ባይ እንሁን። (ሉቃስ 11:4) አንድ የእምነት ባልንጀራችን ስለ እኛ መጥፎ ነገር ተናገረ እንበል። ነገሮችን ለማስተካከል ስንል ግለሰቡን ሄደን ስናነጋግረው በጉዳዩ ከልቡ ማዘኑን በመግለጽ ይቅርታ እንድናደርግለት ጠየቀን። በዚህ ጊዜ ይቅርታ ብናደርግለትም ሌላም የሚጠበቅብን ነገር አለ። ዘሌዋውያን 19:18 (የ1954 ትርጉም) “አትበቀልም፣ በሕዝብህም ልጆች ቂም አትያዝ፣ . . . ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ” ይላል።
ጠንቃቆች መሆን ይኖርብናል
16. የይሖዋን መንፈስ ላለማሳዘን ከፈለግን አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ ሊያስፈልገን እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
16 ብቻችንን በምንሆንበት ጊዜም አምላክን የሚያሳዝን ነገር ለማድረግ ልንፈተን እንችላለን። ለአብነት ያህል፣ አንድ ወንድም ተገቢ ያልሆነ ሙዚቃ ያዳምጥ ይሆናል። ውሎ አድሮ ግን “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያወጣቸው ጽሑፎች ላይ የቀረበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ችላ በማለቱ ሕሊናው ይረብሸዋል። (ማቴ. 24:45) ስለ ጉዳዩ ከጸለየ በኋላ በኤፌሶን 4:30 ላይ የሚገኘውን ጳውሎስ የተናገረውን ሐሳብ ያስታውስ ይሆናል። የአምላክን መንፈስ የሚያሳዝን ምንም ነገር ላለመፈጸም በመቁረጥ ከአሁን በኋላ ተገቢ ያልሆነ ሙዚቃ ማዳመጡን ለማቆም ቁርጥ ውሳኔ ያደርጋል። ይህ ወንድም እንዲህ ያለ ዝንባሌ በማሳየቱ ይሖዋ ይባርከዋል። እንግዲያው እኛም የአምላክን መንፈስ ላለማሳዘን ሁልጊዜ እንጠንቀቅ።
17. ጠንቃቆችና የጸሎት ሰዎች ካልሆንን ምን ሊያጋጥመን ይችላል?
17 ሁልጊዜ ጠንቃቆችና የጸሎት ሰዎች ካልሆንን መንፈስ ቅዱስን እንድናሳዝን የሚያደርገንን ርኩስ ወይም መጥፎ ድርጊት ልንፈጽም እንችላለን። መንፈስ ቅዱስ በሰማይ ያለው አባታችን ፈቃድ መገለጫ በመሆኑ ይህንን መንፈስ ማሳዘን ይሖዋን ከማሳዘን ተለይቶ አይታይም፤ ፈጽሞ ይህን ማድረግ እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። (ኤፌ. 4:30) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የአይሁድ ጸሐፍት የኢየሱስ ተአምራት በሰይጣን ኃይል እንደተፈጸሙ አድርገው ተናግረው ነበር። (ማርቆስ 3:22-30ን አንብብ።) እነዚህ የክርስቶስ ጠላቶች ‘መንፈስ ቅዱስን በመሳደባቸው’ ይቅር የማይባል ኃጢአት ሠርተዋል። እኛም እንዲህ እንዳናደርግ እንጠንቀቅ!
18. ይቅር የማይባል ኃጢአት እንዳልሠራን እንዴት ማወቅ እንችላለን?
18 ይቅር የማይባል ኃጢአት መሥራት ጨርሶ የማናስበው ነገር በመሆኑ ጳውሎስ የአምላክን መንፈስ እንዳናሳዝን የሰጠንን ምክር ማስታወስ ይኖርብናል። ይሁንና ከባድ ኃጢአት ሠርተን ቢሆንስ? ንስሐ ከገባንና የሽማግሌዎችን እርዳታ ካገኘን አምላክ ይቅር እንዳለን ብሎም በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት እንዳልሠራን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በተጨማሪም በአምላክ እርዳታ መንፈስ ቅዱስን የሚያሳዝን ምንም ነገር እንደገና ከማድረግ ልንርቅ እንችላለን።
19, 20. (ሀ) ልናስወግዳቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?
19 አምላክ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት በሕዝቦቹ መካከል ፍቅር፣ ደስታና አንድነት እንዲኖር ያደርጋል። (መዝ. 133:1-3) ስለዚህ ጎጂ ሐሜት በማሠራጨት ወይም ወንድሞች በመንፈስ ለተሾሙት እረኞች ያላቸው አክብሮት እንዲቀንስ የሚያደርግ ነገር በመናገር መንፈስ ቅዱስን ከማሳዘን መቆጠብ ይኖርብናል። (ሥራ 20:28፤ ይሁዳ 8) ከዚህ ይልቅ በጉባኤ ውስጥ አንድነትና እርስ በርስ መከባበር እንዲሰፍን ጥረት ማድረግ ይገባናል። በጉባኤ ውስጥ ቡድን በመፍጠር ሌሎችን ማግለል እንደሌለብን ግልጽ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ወንድሞች፣ ሁላችሁም ንግግራችሁ አንድ እንዲሆንና በመካከላችሁ መከፋፈል እንዳይኖር፣ ከዚህ ይልቅ በአስተሳሰብም ሆነ በዓላማ ፍጹም አንድነት እንዲኖራችሁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አጥብቄ አሳስባችኋለሁ።”—1 ቆሮ. 1:10
20 ይሖዋ፣ መንፈስ ቅዱስን የሚያሳዝን ነገር እንዳናደርግ ሊረዳን የሚችል ከመሆኑም በላይ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ነው። እንግዲያው መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት መጸለያችንን እንቀጥል፤ እንዲሁም ይህን መንፈስ ላለማሳዘን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። አሁንም ሆነ ለዘላለም የአምላክን መንፈስ መመሪያ በጥብቅ በመሻት ‘ለመንፈስ ብለን መዝራታችንን’ እንቀጥል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የአምላክን መንፈስ ማሳዘን ሲባል ምን ማለት ነው?
• ራሱን ለይሖዋ የወሰነ ግለሰብ መንፈስ ቅዱስን ሊያሳዝን የሚችለው እንዴት ነው?
• የአምላክን መንፈስ ከማሳዘን መቆጠብ የምንችለው በየትኞቹ አቅጣጫዎች ነው?
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አለመግባባቶችን ጊዜ ሳናጠፋ እንፍታ
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ንግግርህ ከየትኛው ፍሬ ጋር ይመሳሰላል?