ቂም አትያዙ
አንድ ሰው ሲበድለን ቂም አለመያዝ ከማንኛውም ነገር ይልቅ ተፈታታኝ ሊመስል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚህ ላለው ሁኔታ ተግባራዊ የሆነ ምክር ይዟል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ” በማለት ጽፏል።—ኤፌሶን 4:26
አንድ ሰው ሲበድለን በተወሰነ ደረጃ መቆጣት ያለ ነገር ነው። ጳውሎስ “ተቆጡ” ማለቱ አንዳንድ ጊዜ፣ ምናልባትም ተገቢ ያልሆነ ነገር በሚፈጸምብን ወይም ፍትህ በሚዛባብን ጊዜ መናደዱ መጥፎ አለመሆኑን ያሳያል። (ከ2 ቆሮንቶስ 11:29 ጋር አወዳድር።) ቢሆንም ነገሩን ሳንፈታው እንዲሁ ከተውነው ቁጣው ተገቢ ቢሆንም እንኳ አደገኛ ውጤቶች ሊያስከትልና ከባድ ኃጢአት ወደመፈጸም ሊመራ ይችላል። (ዘፍጥረት 34:1–31፤ 49:5–7፤ መዝሙር 106:32, 33) ታዲያ ቁጣ ቁጣ ሲልህ ምን ማድረግ ትችላለህ?
አብዛኛውን ጊዜ ቀላል በደል ከሆነ ሁኔታውን በራስህ መፍታትና ‘ዝም ማለት’ ወይም በደሉን የፈጸመብህን ሰው ቀርበህ በጉዳዩ ላይ መነጋገር ትችላለህ። (መዝሙር 4:4፤ ማቴዎስ 5:23, 24) በዚህም ሆነ በዚያ ቂም አድጎ አሳዛኝ ውጤቶችን እንዳያፈራ ጉዳዩን በፍጥነት መፍታት ከሁሉ የተሻለ ነው።—ኤፌሶን 4:31
ይሖዋ ሌላው ቀርቶ እንደፈጸምን የማናስታውሳቸውን ኃጢአቶች በነፃ ይቅር ይለናል። እኛን መሰል የሆነ ሰው ትንሽ ሲበድለን ይቅር ማለት አይገባንምን?—ቆላስይስ 3:13፤ 1 ጴጥሮስ 4:8
“ይቅር ማለት” የሚለው የግሪክኛ ቃል ጥሬ ትርጉሙ “መተው” ማለት ነው። ስለዚህ ይቅር ባይነት በደሉን አቅልሎ መመልከት ወይም ችላ ብሎ ማለፍ ማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ የቃሉ ትርጉም ቂም መያዝ ሸክም ከመጨ መርና የክርስቲያን ጉባኤን አንድነት ከማናጋት በቀር ምንም እንደማይጠቅም በመረዳት “መተው” ማለት ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ቂም መያዝ ለጤንነትህ በጣም አደገኛ ሊሆን ይችላል።—መዝሙር 103:9