ቃላት ጎጂ መሣሪያ በሚሆኑበት ጊዜ
“ያለ ጥንቃቄ የተነገረ ቃል እንደ ሰይፍ ያቆስላል።”—ምሳሌ 12:18 የ1980 ትርጉም
“በተጋባን በጥቂት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ” አለች ኤለንa “የጥላቻ ቃላት፣ እኔን የሚያንቋሽሹና የሚያዋርዱ ቃላት ይሰነዘሩብኝ ጀመር። ባለቤቴን ፈጽሞ መቋቋም አልቻልኩም። በጣም ፈጣን የሆነ አእምሮውና ምላሱ የተናገርኩትን ሁሉ ማጣመም ይችላል።”
ኤለን በትዳር ሕይወቷ በሙሉ ምንም ዓይነት ጠባሳ የማይተውና ሰዎች ሊያዩላት የማይችሉት ስውር ጥቃት ሲደርስባት ኖሯል። ዓመታት እያለፉ ቢሄዱም እንኳ ይህ ችግሯ ሊወገድላት አለመቻሉ በጣም የሚያሳዝን ነው። “ከተጋባን ይኸው 12 ዓመት ሆኖናል” ትላለች። “እኔን ለመንቀፍ፣ የአሽሙር ወይም የስድብ ቃል ሳይናገር የቀረበት አንድም ቀን የለም።”
መጽሐፍ ቅዱስ ምላስ ‘ሊገራ የማይችል የሚገድል መርዝ የሞላበት . . . ክፋት ነው’ ማለቱ ነገሩን ከልክ በላይ ማጋነኑ አይደለም። (ያዕቆብ 3:8፤ ከመዝሙር 140:3 ጋር አወዳድር።) ይህ እውነት የሚሆነው በተለይ በትዳር ውስጥ ነው። ሊዛ የተባለች አንዲት ሚስት “‘በትርና ድንጋይ እንጂ ቃል አጥንት ሊሰብር አይችልም’ የሚለኝ ሰው በጣም የተሳሳተ ነው” ብላለች።— ምሳሌ 15:4
ባሎችም የቃላት ጥቃት ሊደርስባቸው ይችላል። ከትሬሲ ጋር ትዳር ከመሠረተ አራት ዓመት የሆነውና ለፍቺ የተዘጋጀው ማይክ “ሁልጊዜ ውሸታም፣ ደደብ ወይም ከዚህ የከፋ ሌላ ቃል ከምትናገርና ከምትሳደብ ሴት ጋር መኖር ምን እንደሚመስል ታውቃላችሁ?” ሲል ጠይቋል። “የምትሰነዝርብኝን ቃላት በጨዋ ሰዎች መካከል ለመናገር አልደፍርም። ላነጋግራት የማልችለውና ሥራ ቦታ የማመሸው በዚህ ምክንያት ነው። እቤት ቶሎ ከመግባት እንዲህ ማድረግ ይሻለኛል።”— ምሳሌ 27:15
ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “ጩኸትም መሳደብም ሁሉ . . . ከእናንተ ዘንድ ይወገድ” ሲል የመከረው ያለ በቂ ምክንያት አይደለም። (ኤፌሶን 4:31) ይሁን እንጂ “መሳደብ” ምንድን ነው? ጳውሎስ ከፍ ባለ ድምፅ መናገር ከሆነው ከ“ጩኸት” [በግሪክኛ ክራውገ] የተለየ እንደሆነ አመልክቷል። “ስድብ” [በግሪክኛ ብላስፌምያ] ይበልጥ የሚያመለክተው የተነገረውን ቃል መልእክት ነው። በእብሪተኝነት፣ በጥላቻ፣ ለማዋረድ ወይም ለመዝለፍ ተብሎ የተነገረ ከሆነ፣ ጮክ ብሎ ተነገረም በሹክሹክታ ያው ስድብ ነው።
የሚያቆስሉ ቃላት
የባሕር ሞገድ ጠንካራ የነበረውን አለት ሊሸረሽር እንደሚችል ሁሉ ሻካራ ንግግርም አንድን ትዳር ሊያዳክም ይችላል። ዶክተር ዳንኤል ጎልማን እንደጻፉት “ሻካራ ንግግር በረዘመና በከረረ መጠን የሚያስከትለው አደጋም በዚያው መጠን የከፋ ይሆናል። . . . ነቀፋ ወይም ትችት ልማድ ሲሆን አንድ ባል ወይም ሚስት ስለ ትዳር ጓደኛቸው መጥፎ ውሳኔ ላይ የደረሱ መሆናቸውን የሚያመለክት ስለሚሆን የአደጋ ምልክት ነው።” ባልና ሚስት በመካከላቸው የነበረው ፍቅር እየተመናመነ ሲሄድ አንድ መጽሐፍ እንዳለው “በስሜት ሳይሆን በሕግ ብቻ የተጋቡ ይሆናሉ።” ከጊዜ በኋላ ደግሞ ይኸው የሕግ ጋብቻቸውም ይፈርሳል።
ይሁን እንጂ የስድብ ንግግር የሚጎዳው ትዳሩን ብቻ አይደለም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “በልብ ሐዘን ግን ነፍስ ትሰበራለች” ይላል። (ምሳሌ 15:13) የስድብ ውርጅብኝ የሚፈጥረው ውጥረት በአንድ ሰው ላይ ከፍተኛ የጤና ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል በዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ (ዩ ኤስ ኤ) የተደረገ አንድ ጥናት ዘወትር ስድብ የሚሰነዘርባት ሴት ለጉንፋን፣ ለፊኛ ችግሮች፣ ለጨጓራና ለአንጀት መታወክ እንዲሁም ይስት በተባሉት ተሕዋስያን ለመለከፍ ይበልጥ የተጋለጠች ልትሆን እንደምትችል አረጋግጧል።
የአፍም ሆነ የጉልበት ዱላ ችለው ያሳለፉ ብዙ ሴቶች ከቡጢ ይልቅ ቃል የበለጠ እንደሚያቆስል ተናግረዋል። በቨርሊ እንዲህ ብላለች:- “ዱላው የሚያደርስብኝ ሰንበርና ጠባሳ ከጊዜ በኋላ ይድንና ይጠፋል። ስለ መልኬ፣ ስለ ምግብ አሠራሬ፣ ስለ ልጆች አያያዜ የሚናገረውን መጥፎ ነገር ግን ፈጽሞ፣ ፈጽሞ ልረሳ አልችልም።” ጁልያም እንዲሁ ተሰምቷታል:- “ምን ዓይነቷ ሞኝ ነች ልትሉኝ እንደምትችሉ አውቃለሁ። ቢሆንም አእምሮዬን ለበርካታ ሰዓቶች የሚያሠቃይ ነገር ከሚናገር ቢመታኝ ይሻለኝ ነበር።”
ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች እወደዋለሁ የሚሉትን ሰው የሚያጥላሉትና የሚያዋርዱት ለምንድን ነው? የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ጥያቄ ላይ ያተኩራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ስሞች ተለውጠዋል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“አእምሮዬን ለበርካታ ሰዓቶች የሚያሠቃይ ነገር ከሚናገር ቢመታኝ ይሻለኝ ነበር”
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ሁልጊዜ ውሸታም፣ ደደብ ወይም ከዚህ የከፋ ሌላ ቃል ከምትናገርና ከምትሳደብ ሴት ጋር መኖር ምን እንደሚመስል ታውቃላችሁ?”