አንደበታችሁን በመቆጣጠር ፍቅርና አክብሮት አሳዩ
“ከእናንተ እያንዳንዱ ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ ይውደድ፤ ሚስትም ባሏን ታክብር።” —ኤፌሶን 5:33
1, 2. ያገቡ ሰዎች በሙሉ የትኛውን አስፈላጊ ጥያቄ ራሳቸውን ሊጠይቁ ይገባል? ለምንስ?
በሚያምር ወረቀት የታሸገና “በጥንቃቄ ይያዙት” የሚል ጽሑፍ የተለጠፈበት ጥቅልል ተሰጣችሁ እንበል። ይህንን ጥቅልል እንዴት ትይዙታላችሁ? ጉዳት እንዳይደርስበት የተቻላችሁን ያህል ጥንቃቄ እንደምታደርጉ ምንም ጥርጥር የለውም። ስጦታ የሆነውን የጋብቻ ዝግጅትስ እንዴት ትመለከቱታላችሁ?
2 እስራኤላዊቷ መበለት ኑኃሚን ዖርፋና ሩት የተባሉትን ወጣት ሴቶች “ይሖዋ ስጦታ ይስጣችሁ፤ ለእያንዳንዳችሁ በባላችሁ ቤት፣ የዕረፍት ሥፍራ ይስጣችሁ” ብላቸው ነበር። (ሩት 1:3-9 NW) መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ሚስትን አስመልክቶ ሲናገር “ቤትና ሀብት ከወላጆች ይወረሳሉ፤ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት” ይላል። (ምሳሌ 19:14) ያገባችሁ ከሆናችሁ የትዳር ጓደኞቻችሁን ከይሖዋ እንደተቀበላችሁት ስጦታ አድርጋችሁ ልትመለከቷቸው ይገባል። አምላክ የሰጣችሁን ስጦታ የምትይዙት እንዴት ነው?
3. ባሎችም ሆኑ ሚስቶች የትኛውን የሐዋርያው ጳውሎስ ምክር ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል?
3 ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ክርስቲያኖች ሲጽፍ “ከእናንተ እያንዳንዱ ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ ይውደድ፤ ሚስትም ባሏን ታክብር” ብሎ ነበር። (ኤፌሶን 5:33) ባሎችም ሆኑ ሚስቶች በአንደበት አጠቃቀማቸው ረገድ ይህንን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
‘ዕረፍት ከሌላት ክፉ ነገር’ ተጠበቁ
4. ምላስ፣ በጎ ወይም ጎጂ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት ነው?
4 የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ ምላስን በተመለከተ “የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት” በማለት ተናግሯል። (ያዕቆብ 3:8) ያዕቆብ አንድ ጠቃሚ ሐቅ ተገንዝቦ ነበር:- ዕረፍት የሌላት ወይም ያልተገራች ምላስ አጥፊ ናት። ይህ ደቀ መዝሙር በግዴለሽነት መናገርን ‘በሰይፍ ከመውጋት’ ጋር የሚያመሳስለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንደሚያውቅ አያጠራጥርም። በሌላ በኩል ደግሞ ይኸው ምሳሌ “የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 12:18) በእርግጥም ቃላት ከፍተኛ ኃይል አላቸው። ሌሎችን ሊጎዱ ወይም ደግሞ ፈውስ ሊያመጡ ይችላሉ። የምትናገሩት ነገር በትዳር ጓደኞቻችሁ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? ለትዳር ጓደኞቻችሁ ይህን ጥያቄ ብታቀርቡላቸው ምን ብለው ይመልሳሉ?
5, 6. አንዳንዶች አንደበታቸውን መቆጣጠር አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው የሚያደርጉ ምን ነገሮች አሉ?
5 ሌላውን ሰው የሚጎዳ አነጋገር ቀስ በቀስ በትዳራችሁ ውስጥ ዘልቆ እየገባ ከሆነ ሁኔታውን ማስተካከል ትችላላችሁ። ሆኖም ጥረት ማድረግ ያስፈልጋችኋል። ለምን? አንደኛ ነገር ፍጹም ካልሆነው ሥጋችን ጋር ትግል አለብን። የወረስነው ኃጢአት በአስተሳሰባችንም ሆነ እርስ በርስ በምንነጋገርበት መንገድ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳድራል። ያዕቆብ “በንግግሩ የማይሰናከል ማንም ሰው ቢኖር እርሱ ሰውነቱን ሁሉ መቈጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው” ሲል ጽፏል።—ያዕቆብ 3:2
6 ከሰብዓዊ አለፍጽምና በተጨማሪ ያደግንበት ቤተሰብ ሁኔታም አንደበታችንን አላግባብ በመጠቀም ረገድ የሚጫወተው ሚና አለ። ‘ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ራሳቸውን የማይገዙና ጨካኝ’ የሆኑ ወላጆች ያሳደጓቸው ሰዎች አሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-3) አብዛኛውን ጊዜ በእንደዚህ ዓይነት ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ልጆች ትልቅ ሰው በሚሆኑበት ወቅት ተመሳሳይ ባሕርይ ያሳያሉ። በእርግጥ፣ ፍጹማን አለመሆናችንም ሆነ አስተዳደጋችን መጥፎ መሆኑ ሌሎችን በሚጎዳ መንገድ ለመናገር ሰበብ አይሆንም። ሆኖም እነዚህን ነጥቦች መገንዘባችን፣ አንዳንዶች መጥፎ ነገር ላለመናገር አንደበታቸውን መቆጣጠር በጣም አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል።
‘ሐሜትን አስወግዱ’
7. ጴጥሮስ “ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ” ብሎ ክርስቲያኖችን ሲመክር ምን ማለቱ ነበር?
7 በጋብቻ ውስጥ ሌላውን ሰው በሚጎዳ መንገድ እንድንናገር ምክንያት የሆነን ነገር ምንም ይሁን ምን እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ለትዳር ጓደኛችን ፍቅርና አክብሮት እንደጎደለን ሊጠቁም ይችላል። በመሆኑም ጴጥሮስ “ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ” በማለት ክርስቲያኖችን መምከሩ ተገቢ ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:1) “ሐሜት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “የዘለፋ አነጋገር” የሚል ትርጉም አለው። ‘በሰዎች ላይ የቃላት ውርጅብኝ ማዥጎድጎድ’ የሚል ሐሳብም ያስተላልፋል። ይህ ፍቺ ያልተገራ አንደበት የሚያስከትለውን ውጤት በሚገባ ይገልጻል!
8, 9. ዘለፋ የተቀላቀለበት ንግግር ምን ሊያስከትል ይችላል? የትዳር ጓደኛሞች የዚህ ዓይነቱን ንግግር ሊያስወግዱ የሚገባው ለምንድን ነው?
8 ዘለፋ ያን ያህል ጉዳት ያለው አይመስል ይሆናል፤ ሆኖም አንድ ባል ወይም አንዲት ሚስት እንዲህ ባለ መንገድ ሲናገሩ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቡ። የትዳር ጓደኛን የማትረባ፣ ሰነፍ ወይም ራስ ወዳድ ብሎ መጥራት የግለሰቡ ወይም የግለሰቧ አጠቃላይ ስብዕና እንዲህ ባለ የሚያቃልል ቃል ሊገለጽ ይችላል ብሎ እንደመናገር ይቆጠራል። ይህ ፍቅር የጎደለው ድርጊት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። የትዳር ጓደኛን ጉድለቶች አጉልተው ስለሚያሳዩ የተጋነኑ አነጋገሮችስ ምን ማለት ይቻላል? “ሁሌ እንደዘገየህ/እንደዘገየሽ ነው” ወይም “ጭራሽ እኮ አትሰማኝም/አትሰሚኝም” እንደሚሉት ያሉ አባባሎች የተጋነኑ አይደሉም? እንዲህ ያለው አነጋገር ሌላኛው ግለሰብ ራሱን ለመከላከል ሙግት እንዲገጥም ያነሳሳዋል። ይህ ደግሞ የጦፈ ጭቅጭቅ እንዲነሳ ሊያደርግ ይችላል።—ያዕቆብ 3:5
9 ዘለፋ የተቀላቀለበት ንግግር በጋብቻ ውስጥ ውጥረት እንዲሰፍን የሚያደርግ ሲሆን ይህም የከፋ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። ምሳሌ 25:24 “ከጨቅጫቃ ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመኖር፣ በጣራ ማእዘን ላይ መኖር ይሻላል” ይላል። ይኸው አባባል ጨቅጫቃ ለሆነ ባልም ይሠራል። ባልም ሆነ ሚስት በአሽሙር የሚናገሩ ከሆነ ውሎ አድሮ ግንኙነታቸው ሊሸረሸርና ባልየው አሊያም ሚስትየው እንደማይወደዱ ወይም ሊወደዱ የማይገባቸው ሰዎች እንደሆኑ ሊሰማቸው ይችላል። በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው አንደበታችንን መቆጣጠር በጣም አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
“ምላስን መግራት”
10. አንደበትን መግታት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
10 ያዕቆብ 3:8 “ምላስን መግራት የሚችል ማንም ሰው የለም” ይላል። ያም ቢሆን ግን፣ አንድ ጋላቢ የፈረሱን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በልጓም እንደሚጠቀም ሁሉ እኛም ምላሳችንን ለመግራት የቻልነውን ያህል መጣር ይኖርብናል። “አንደበቱን ሳይገታ፣ ልቡን እያሳተ ሃይማኖተኛ ነኝ የሚል ሰው፣ ራሱን ያታልላል፤ ሃይማኖቱም ከንቱ ነው።” (ያዕቆብ 1:26፤ 3:2, 3) ይህ ጥቅስ፣ አንደበታችሁን የምትጠቀሙበት መንገድ በቁም ነገር ሊታሰብበት የሚገባ መሆኑን ያመለክታል። ይህ ጉዳይ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ባላችሁ ግንኙነት ላይ ብቻ ሳይሆን በግላችሁ ከይሖዋ አምላክ ጋር ባላችሁ ግንኙነትም ላይ ጭምር ተጽዕኖ ያሳድራል።—1 ጴጥሮስ 3:7
11. ቀላል የነበረው አለመግባባት ተጋግሎ የጦፈ ጭቅጭቅ እንዳይፈጠር ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
11 ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ስለምትነጋገሩበት መንገድ ትኩረት ሰጥታችሁ ማሰባችሁ ጥበብ ነው። በመካከላችሁ ውጥረት ከሰፈነ ሁኔታውን ለማርገብ ሞክሩ። ከዘፍጥረት 27:46 እስከ 28:4 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን በይስሐቅና በርብቃ ሕይወት ውስጥ የተከሰተ ሁኔታ እንመልከት። “ርብቃ ይስሐቅን፣ ‘ዔሳው ባገባቸው በኬጢያውያን ሴቶች ምክንያት መኖር አስጠልቶኛል፤ ያዕቆብም ከዚሁ አገር ከኬጢያውያን ሴቶች ሚስት የሚያገባ ከሆነ፣ ሞቴን እመርጣለሁ’ አለችው።” በዚህ ወቅት ይስሐቅ ጠንከር ያለ ምላሽ እንደሰጣት የሚጠቁም ነገር የለም። ከዚህ ይልቅ ልጃቸው ያዕቆብ፣ አምላክን የምትፈራና ርብቃን የማታሳዝን ሚስት እንዲፈልግ ላከው። በአንድ ባልና ሚስት መካከል አለመግባባት ተፈጠረ እንበል። የትዳር ጓደኛቸውን ከመውቀስ ይልቅ በችግሩ ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ቀላል የነበረው አለመግባባት ወደ ጦፈ ጭቅጭቅ እንዳይቀየር ያደርጋል። ለምሳሌ፣ “ከእኔ ጋር መሆን ደስ አይልህም!” ከማለት ይልቅ “ሰፋ ያለ ጊዜ አብረን ማሳለፍ ብንችል ደስ ይለኝ ነበር” ማለት ይቻላል። ግለሰቡን ከመውቀስ ይልቅ በችግሩ ላይ ትኩረት አድርጉ። ማን ትክክል እንደሆነና ጥፋተኛው ማን እንደሆነ ከመናገር ተቆጠቡ። ሮሜ 14:19 “ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችንም የምንተናነጽበትን ማንኛውንም ጥረት እናድርግ” ይላል።
‘መራርነትን እንዲሁም ቊጣና ንዴትን’ አስወግዱ
12. አንደበታችንን መቆጣጠር እንድንችል ምን ብለን መጸለይ ይኖርብናል? ለምንስ?
12 አንደበታችንን መቆጣጠር ስለምንናገረው ነገር ጠንቃቆች በመሆን ብቻ አይወሰንም። የምንናገረው ነገር አስተሳሰባችንንና ስሜታችንን ያንጸባርቃል። ኢየሱስ “መልካም ሰው በልቡ ከሞላው መልካም ነገር መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ከሞላው ክፉ ነገር ክፉውን ያወጣል፤ ሰው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን በአፉ ይናገራልና” ብሏል። (ሉቃስ 6:45) እንግዲያው አንደበታችሁን ለመቆጣጠር ዳዊት እንዳደረገው “አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” ብላችሁ መጸለይ ያስፈልጋችሁ ይሆናል።—መዝሙር 51:10
13. መራርነት እንዲሁም ቁጣና ንዴት ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ወደ መናገር ሊመራን የሚችለው እንዴት ነው?
13 ጳውሎስ፣ የኤፌሶን ክርስቲያኖች ሌሎችን የሚጎዳ አነጋገርን እንዲያስወግዱ ብቻ ሳይሆን ክፉ እንዲናገሩ የሚገፋፋቸውን ስሜትም እንዲያሸንፉ መክሯቸዋል። “መራርነትን ሁሉ፣ ቊጣና ንዴትን፣ ጭቅጭቅና ስድብን ከማንኛውም ክፋት ጋር ከእናንተ ዘንድ አስወግዱ” በማለት ጽፏል። (ኤፌሶን 4:31) ጳውሎስ ‘ከጭቅጭቅና ከስድብ’ በፊት ‘መራርነትን፣ ቊጣንና ንዴትን’ መጥቀሱ ልብ ሊባል ይገባል። በቁጣ ገንፍለን ሌሎችን የሚጎዳ ነገር የምንናገረው በውስጣችን የታመቀ ምሬት ሲኖር ነው። ስለዚህ ‘በጣም ከመማረሬ የተነሳ ውስጤ በንዴት ተሞልቷል? “ግልፍተኛ” ነኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው። (ምሳሌ 29:22) እንደዚህ ዓይነት ችግር ካለብህ እነዚህን ዝንባሌዎች ለማሸነፍና ራስህን በመቆጣጠር በቁጣ ገንፍለህ ከመናገር መቆጠብ እንድትችል እንዲረዳህ ወደ አምላክ ጸልይ። መዝሙር 4:4 “ስትቈጡ ኀጢአት አትሥሩ፤ በዐልጋችሁም ላይ ሳላችሁ፣ ልባችሁን መርምሩ፤ ጸጥም በሉ” ይላል። በቁጣ ልትገነፍልና ራስህን መቆጣጠር ሊያቅትህ እንደሚችል ከተሰማህ፣ በምሳሌ 17:14 ላይ የሚገኘውን “ጠብ ከመጫሩ በፊት ከነገር ራቅ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ አድርግ። ሁኔታው እስኪረጋጋ ድረስ ለጊዜው ዞር በል።
14. ቂም መያዝ በጋብቻ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት ነው?
14 ጳውሎስ “መራርነት” ብሎ በገለጸው ስሜት የተነሳ የምንቆጣና የምንናደድ ከሆነ እነዚህን ባሕርያት ማስወገዱ ቀላል አይሆንም። ጳውሎስ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል፣ አንድ ግለሰብ “ዕርቅ ለማውረድ አሻፈረኝ እንዲል የሚያደርግ የምሬት መንፈስ” እንዲሁም ‘የተፈጸመበትን በደል እንዲቆጥር የሚያደርገው የእልኸኝነት ስሜት’ እንዳለው ያሳያል። አንዳንድ ጊዜ ጥቅጥቅ እንዳለ ጉም በባልና ሚስት መካከል ጥላቻ ይሰፍንና ሁኔታው በዚህ መንገድ ለረጅም ጊዜ ይዘልቃል። በዚህ ወቅት ያደረባቸውን ቅሬታ በአግባቡ መፍታት ካልቻሉ በመካከላቸው መናናቅ ሊፈጠር ይችላል። ሆኖም ላለፉ ስሕተቶች ቂም ይዞ መቆየት ትርጉም የለውም። የተፈጸመውን ነገር ወደ ኋላ ተመልሶ ማስተካከል አይቻልም። ስሕተት የፈጸመውን ሰው ይቅር ካልነው በደሉንም መርሳት ይገባናል። ፍቅር “በደልን አይቈጥርም።”—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5
15. ሻካራ ቃላት መናገር አመል የሆነባቸው ሰዎች አነጋገራቸውን ለማስተካከል ምን ሊረዳቸው ይችላል?
15 ባደጋችሁበት ቤተሰብ ውስጥ ሻካራ ንግግር የተለመደ ከነበረና እናንተም እንዲህ ያለው አነጋገር ልማድ ከሆነባችሁ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? በዚህ ረገድ ለውጥ ማድረግ ትችላላችሁ። በሕይወታችሁ ውስጥ በተለያዩ መስኮች አንዳንድ ነገሮችን ላለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርጋችኋል። ታዲያ አነጋገራችሁን በተመለከተ ገደብ የምታበጁት ምን ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው? ሌሎችን የሚጎዱ ቃላት ከመናገራችሁ በፊት ራሳችሁን ትገታላችሁ? በኤፌሶን 4:29 ላይ የሚገኘውን “የማይረባ ቃል ከአፋችሁ አይውጣ” የሚለውን መመሪያ መከተላችሁ ተገቢ ነው። ይህን ለማድረግ ‘አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር አውልቃችሁ በመጣል የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው መልበስ’ ይኖርባችኋል።—ቈላስይስ 3:9, 10
‘መመካከር’ የግድ አስፈላጊ ነው
16. ኩርፊያ ጋብቻውን የሚጎዳው እንዴት ነው?
16 ባልና ሚስት መኮራረፋቸው ምንም ጥቅም የማያስገኝ ከመሆኑም በላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። አንደኛው ወገን የሚያኮርፈው የትዳር ጓደኛውን ለመቅጣት በማሰብ ብቻ ላይሆን ይችላል፤ አንዳንድ ጊዜ ብስጭት ወይም ተስፋ መቁረጥ አንድን ሰው እንዲያኮርፍ ያደርገው ይሆናል። ያም ቢሆን ግን፣ እርስ በርስ ለመነጋገር ፈቃደኛ አለመሆን ውጥረቱን የሚያባብሰው ከመሆኑም በላይ የተፈጠረውን ችግር በመፍታት ረገድ የሚፈይደው ነገር አይኖርም። አንዲት ሚስት “ተኳርፈን ከቆየን በኋላ እንደገና መነጋገር ስንጀምር ተፈጥሮ የነበረውን ችግር አንስተን በመወያየት ለመፍታት ሙከራ አናደርግም” ብላለች።
17. በጋብቻቸው ውስጥ ውጥረት ያጋጠማቸው ክርስቲያኖች ምን ማድረግ አለባቸው?
17 በጋብቻ ውስጥ የተፈጠረው አለመግባባት ለረጅም ጊዜ ከዘለቀ ውጥረቱን ማርገብ የሚቻልበት መንገድ አንድ ብቻ ነው። ምሳሌ 15:22 “ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል” ይላል። ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ቁጭ ብላችሁ በጉዳዩ ላይ መወያየት ይኖርባችኋል። በተቻላችሁ መጠን ልባችሁን ከፍታችሁ የትዳር ጓደኛችሁ የሚናገረውን በትኩረት አዳምጡ። እንዲህ ማድረግ የማይቻል ከመሰላችሁ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙትን ሽማግሌዎች እርዳታ ለምን አትጠይቁም? እነዚህ ወንድሞች የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ያላቸው ከመሆኑም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ልምድ አካብተዋል። እንደ እነርሱ ያሉት ወንዶች “ከነፋስ መከለያ፣ ከወጀብም መጠጊያ” ናቸው።—ኢሳይያስ 32:2
በትግሉ ማሸነፍ ትችላላችሁ
18. በሮሜ 7:18-23 ላይ ስለ የትኛው ትግል ተገልጿል?
18 አንደበታችንን መግታትም ሆነ የምናደርገውን ነገር መቆጣጠር ትግል ይጠይቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከራሱ ጋር የሚያደርገውን ትግል ሲገልጽ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በእኔ፣ ማለትም ኀጢአተኛ በሆነው ተፈጥሮዬ ውስጥ ምንም በጎ ነገር እንደማይኖር ዐውቃለሁ፤ በጎ የሆነውን የማድረግ ምኞት አለኝ፤ ነገር ግን ልፈጽመው አልችልም። የማደርገው ላደርገው የምፈልገውን በጎ ነገር አይደለም፤ ዳሩ ግን ለማድረግ የማልፈልገውን ክፉ ነገር ነው። ላደርገው የማልፈልገውን ነገር የማደርገው ከሆነ፣ ያን የማደርገው እኔ ራሴ ሳልሆን፣ የሚያደርገው በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኀጢአት ነው።” ‘በብልቶቻችን ውስጥ በሚሠራው የኀጢአት ሕግ’ የተነሳ አንደበታችንንም ሆነ ሌሎች የሰውነታችንን ክፍሎች ተገቢ ባልሆነ መንገድ የመጠቀም ዝንባሌ አለን። (ሮሜ 7:18-23) ያም ቢሆን ግን ይህንን ችግር ለማሸነፍ መታገል አለብን፤ ደግሞም በአምላክ እርዳታ በትግሉ ማሸነፍ እንችላለን።
19, 20. የኢየሱስ ምሳሌ፣ ባሎችም ሆኑ ሚስቶች አንደበታቸውን እንዲገቱ የሚረዳቸው እንዴት ነው?
19 በፍቅርና በመከባበር በተሞላ ትዳር ውስጥ አሳቢነት የጎደላቸው ሻካራ ቃላት አይሰሙም። ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ረገድ የተወውን ምሳሌ አስቡ። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በነበረው ግንኙነት አንድም ጊዜ ቢሆን የዘለፋ ቃል አልወጣውም። በምድር ላይ በኖረበት የመጨረሻ ምሽት እንኳ ሐዋርያቱ ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ ሲከራከሩ የአምላክ ልጅ አልተቆጣቸውም። (ሉቃስ 22:24-27) መጽሐፍ ቅዱስ “ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ” የሚል ምክር ይሰጣል።—ኤፌሶን 5:25
20 ሚስቶችስ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? መጽሐፍ ቅዱስ “ሚስትም ባሏን ታክብር” ይላል። (ኤፌሶን 5:33) ባሏን የምታከብር ሚስት የዘለፋ ቃል እየተናገረች ትጮህበታለች? ጳውሎስ “ይህን እንድታውቁ እወዳለሁ፤ የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ ነው፤ የሴትም ራስ ወንድ ነው፤ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር ነው” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ክርስቶስ፣ ራሱ ለሆነው ለይሖዋ እንደሚገዛ ሁሉ ሚስትም ራሷ ለሆነው ለባሏ ልትገዛ ይገባል። (ቈላስይስ 3:18 የ1954 ትርጉም) ፍጽምና የሌለው ማንኛውም ሰው ኢየሱስን ፍጹም በሆነ መንገድ መኮረጅ ባይችልም፣ ባሎችም ሆኑ ሚስቶች የክርስቶስን ‘ፈለግ ለመከተል’ መጣራቸው አንደበታቸውን አላግባብ ላለመጠቀም በሚያደርጉት ትግል እንዲያሸንፉ ይረዳቸዋል።—1 ጴጥሮስ 2:21
ምን ትምህርት አግኝተሃል?
• ዕረፍት የሌላት ምላስ በትዳር ውስጥ ጉዳት ልታስከትል የምትችለው እንዴት ነው?
• ምላስን መግራት አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?
• አነጋገራችንን ለመቆጣጠር ምን ሊረዳን ይችላል?
• በትዳራችሁ ውስጥ ውጥረት ሲያጋጥማችሁ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሽማግሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እርዳታ ይሰጣሉ