“የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ”
ክርስቲያኖች የጦር መሣሪያ ይታጠቃሉን? እንደዚህ ያለ መሣሪያ መታጠቅ የሚኖርባቸውስ ለምንድ ነው? ክርስቲያኖች ሰላም ወዳዶች አይደሉምን? (2 ጢሞቴዎስ 2:24) አዎ፣ ናቸው። ይሁን እንጂ እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ በአንድ ውጊያ ውስጥ ገብተዋል። በዚህ ውጊያ ለመግደል ሳይሆን ለማሸነፍ ይታገላሉ።
ሰይጣን ባያምፅ ኖሮ እንዲህ ዓይነቱ ትግል ባላስፈለገም ነበር። ይሁን እንጂ ሰይጣን አመፀ። በአመፁም አዳምንና ሔዋንን እንዲተባበሩት አደረገ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የዚህ ዓለም ሥርዓት “በክፉው” ገዥ በሰይጣን ዲያብሎስ ሥር ወድቋል። (1 ዮሐንስ 5:19) የፅንፈ ዓለም የበላይ ገዥ ለመሆን መብት ላለው ለይሖዋ ራሳቸውን ያስገዙ ሰዎች ሁሉ ከዓለምና ከገዥዋ የሚደርስባቸውን ተፅእኖ መቋቋም አለባቸው። ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው ደህንነት መዋጋት አለባቸው። በዚህም ምክንያት ከዚህ የሚከተለው ጥብቅ ማሳሰቢያ ለክርስቲያኖች ተሰጥቶአቸዋል፦ “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።”—ኤፌሶን 6:11
የጦር ዕቃ
ተገቢውን ጥበቃ ለማግኘት እንድንችል ሙሉው “የእግዚአብሔር ዕቃ ጦር” እንደሚያስፈልገን ልብ እንበል። እንግዲያው እያንዳንዳችን ለመንፈሳዊ ውጊያ ምን ያህል የታጠቅን መሆናችንን ለመመርመር በሐዋርያው ጳውሎስ የተገለጸውን የዚህን ዕቃ ጦር እያንዳንዱን ክፍል እንመልከት።—ኤፌሶን 6:14-17
“ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ ቁሙ” (ኤፌሶን 6:14ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ወታደሮች እስከ አስራ አምስት ሳንቲ ሜትር ስፋት ያለው ከቆዳ የተሠራ ቀበቶ ይታጠቁ ነበር። ይህ መታጠቂያ ወገባቸውን ለመጠበቅ ይረዳ ነበር። አንድ ወታደር መታጠቂያውን ማጥበቁ ወደ ጦርነት ለመሄድ መዘጋጀቱን ያመለክት ነበር።
ስለዚህ መለኮታዊ እውነት ከወታደር መታጠቂያ ጋር መመሳሰሉ ምንኛ ተገቢ ነው! የአምላክን የእውነት ቃል እንደ ወገብ መታጠቂያ አጥብቀን መያዝ የሚገባን መሆኑን የሚያስገነዝብ ምሳሌ ነው። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ጥልቅ ሐሳቦች ማሰላሰል ይኖርብናል ማለት ነው። ይህም ውሸትና አታላይ በሆኑ ሐሳቦች እንዳንሳሳት ይጠብቀናል። ከዚህም ከይሖዋ አፍ የወጡት ቃላት በመንፈሳዊ ጠንካሮች እንድንሆንና በፍጹም አቋማችን እንድንጸና ይደግፈናል።
“የጽድቅን ጥሩር ለብሳችሁ” (ኤፌሶን 6:14ለ) አንድ ወታደር ጥሩር መልበሱ በጣም አስፈላጊ የሆነውን የሰውነት ክፍል ማለትም ልቡን ይጠብቅለት ነብር። አምላክ ከሰጠን መንፈሳዊ የጦር መሣሪያዎች አንዱ የሆነው ጽድቅም ልባችንን ይጠብቅልናል። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ልብ ውስጣዊ ማንነታችንን ማለትም ስሜታችንን፣ ሐሳባችንን፣ ምኞታችንንና ፍላጎታችንን ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ ልብ ወደ ክፋት የማዘንበል ባሕርይ እንዳለው ስለሚናገር የይሖዋን የጽድቅ ሕግጋት ለመጠበቅ ያለንን ቆራጥነት መኮትኮት ያስፈልገናል። (ኤርምያስ 17:9) አምላክን መታዘዝ ለታይታ ብቻ የሚደረግ የግብዝነት ባሕርይ መሆን የለበትም። ከውስጥ የሚመነጭ መሆን ይገባዋል። ይህን ለማድረግ ጽድቅን አጥብቀን የምናፈቅርና አመጽን የምንጠላ መሆን ይኖርብናል። (መዝሙር 45:7) እንዲህ በማድረጋችንም ልባችን ይጠበቃል።
“በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ።” (ኤፌሶን 6:15) እግሮቻችሁ ይህን ጫማ አድርገዋልን? አዘውትረው ምሥራቹን ወደምታውጁበት ወደ መስክ አገልግሎት ይወስዷችኋልን? የስብከትና የማስተማር ችሎታችሁን ለማሻሻል ጥረት ታደርጋላችሁን? እውነት ነው፣ አንዳንድ የአገልግሎት ቀበሌዎች ለስብከታችን ጥሩ አቀባበል አያሳዩም። አንዳንድ ግለሰቦች ግድ የለሾች፣ ተቃዋሚዎች፣ አነስተኛ ወይም ምንም ፍላጎት የሌላቸው ይሆኑ ይሆናል። እንዲያውም መስበካችን ስደት ሊያስከትልብን ይችል ይሆናል። ሆኖም ክርስቲያኖች ጸንተው በመቆም የሰይጣንን ጥቃት ለመቋቋም የሚያስችላቸውን የጽናት ባህርይ ያዳብራሉ። ጳውሎስ ስደት ቢደርስበትም ቀናተኛ ሰባኪ ነበር። እኛም ጳውሎስ ክርስቶስን እንደ መሰለ እርሱን እንድንመስል ተመክረናል።—1 ቆሮንቶስ 11:1
የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ ሥራ በትጋት መካፈላችን በምሥራቹ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክራል። ከዚህም በላይ የይሖዋ መንፈስ በእኛ በኩል የአምላክን ፈቃድ እንዲፈጽም ያስችለዋል። እንዲያውም ይህ ሥራ የመላእክትና የይሖዋ አምላክ የሥራ ባልደረቦች እንድንሆን ያስችለናል። (1 ቆሮንቶስ 3:9፤ ራዕይ 14:6) በተጨማሪም የጌታ ሥራ የበዛልን ስለምንሆን የተደላደልንና የማንነቃነቅ እንድንሆን ያደርገናል። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ይህም በጣም ጥሩ መከላከያ ይሆንልናል።
“የእምነትን ጋሻ አንሡ።” (ኤፌሶን 6:16) በጥንት ጊዜ አንድ ወታደር ትልቅ ጋሻ በመያዝ ከሚወረወሩበት ቀስቶችና ጦሮች ራሱን ይከላከል ነበር። ጋሻ ይዞ ባይከላከል ግን በመጥፎ ሁኔታ ሊቆስል ወይም ሊገደል ይችላል። ከጦርና ከቀስት ይበልጥ አደገኛ የሆኑ መሣሪያዎች በክርስቲያኖች ላይ ይወረወራሉ። እነዚህም መሣሪያዎች “የሚንበለበሉት የክፉው ፍላጻዎች” ናቸው። እነዚህም ሰይጣን እምነታችንን ለማዳከምና ለመግደል የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች በሙሉ ይጨምራሉ። ከእነዚህ መካከል ስደት፣ ውሸት፣ አሳሳች ዓለማዊ ፍልስፍናዎች፣ ስለ ሥጋዊ ሀብት ማሰብ እና የጾታ ብልግና ለመፈጸም መፈተን ይገኙበታል። ራሳችንን ከእነዚህ መሣሪያዎች ሁሉ ለመጠበቅ ትልቅ ጋሻ ያስፈልገናል። ማንኛውም የሰውነታችን ክፍል ለአደጋ የተጋለጠና በቀላሉ የሚጎዳ መሆን የለበትም።
አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ጠንካራ እምነት ነበራቸው። ልጅ መውለድ የሚችሉበት እድሜ ካለፈ በኋላም እንኳ ዘር እንደሚያገኙ አምላክ የሰጣቸውን ተስፋ አምነዋል። በኋላም አብርሃም ከሚወዳት ሚስቱ ከሣራ የወለደውን አንድ ልጁን ይስሐቅን መስዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ የቀረበለትን ጥያቄ በመታዘዙ አስደናቂ እምነት ያለው መሆኑን አሳይቶአል። አብርሃም እጁን በይስሐቅ ላይ እንዳያነሳ ይሖዋ ከለከለው። በምትኩም ሌላ መሥዋዕት አቀረበለት። አብርሃም ግን ለመታዘዝ ዝግጁ ነበር። ለምን ቢባል ይሖዋ ልጁን ከሞት እንደሚያስነሳው እና ስለ እርሱ የገባውን ተስፋ እንደሚፈጽምለት በይሖዋ ላይ ፍጹም እምነት ስለነበረው ነው።—ሮሜ 4:16-21፤ ዕብራውያን 11:11, 12, 17-19
ሙሴም ለእኛ የሚያስፈልገን ዓይነት እምነት ነበረው። እርሱ በግብፅ የነበረውን ሀብት ትቶ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር መከራ መቀበልን መረጠ። ለምን? ይሖዋ እንዳለና ለእሥራኤላውያን መዳን እንደሚያመጣላቸው ስላመነ ነው። የሙሴ እምነት በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ “የማይታየውን ብድራቱን ትኩር ብሎ እንዲመለከት” አስችሎታል።—ዕብራውያን 11:6, 24-27
እኛስ? በይሖዋ ላይ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል እምነት አለንን? ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና በጣም ቅርብ ከመሆኑ የተነሳ ልክ እንደምናየው ሆኖ ይሰማናልን? ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ይዘን ለመቆየት ችግሮችን ለመቋቋም ወይም መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች እንሆናለንን? (ዕብራውያን 11:1) እንዲህ ከሆነ የሚንበለበሉት የሰይጣን ፍላፃዎች የእምነት ጋሻችንን በስተው ለማለፍ ኃይል አይኖራቸውም።
“የመዳንን ራስ ቁር ተቀበሉ” (ኤፌሶን 6:17ሀ) የአንድ ወታደር የራስ ቁር ጭንቅላቱን በመጠበቅ የሐሳብና የነርቮች አስተባባሪ የሆነውን አንጎሉን ከአደጋ ይከላከልለት ነበር። ክርስቲያናዊ የመዳን ተስፋም አእምሮን ስለሚጠብቅ ከራስ ቁር ጋር ተመሳስሎአል። የክርስቲያን አእምሮ በትክክለኛ እውቀት የታደሰ ቢሆንም አሁንም ደካማና ፍጽምና የሌለው ግለሰብ ክፍል ነው። (ሮሜ 7:18፤ 12:2) አእምሮአችን እምነት የሚያጠፉትን የዚህ ዓለም እርኩስ አስተሳሰቦች እንዲመገብ ብንፈቅድ በመዳን ተስፋ ላይ ያለን ትምክህት ደብዝዞ ይጠፋል። በሌላ በኩል ደግሞ አእምሮአችንን የሚያጠነክረውን የአምላክ ቃል አዘውትረን ከመገብነው ተስፋችን ብሩህና ግልጽ እንደሆነ ይኖራል። የመዳን ራስ ቁርህ ሊወድቅ በማይችልበት ሁኔታ አጥብቀህ አጥልቀኸዋልን?
“የመንፈስንም ሠይፍ ያዙ፣ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።” (ኤፌሶን 6:17ለ) ከሁሉ የሚበልጠው የመከላከል ዘዴ አስቀድሞ ማጥቃት ነው የሚባለው አነጋገር በክርስቲያናዊ ውጊያም እውነት ነው። እግሮቻችን በሰላም ወንጌል ተጫምተው በማያምኑ ሰዎች መካከል በምንመላለስበት ጊዜ አላንዳች መሣሪያ አልተተውንም። የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ኃይለኛ መንፈሣዊ ሠይፍ ሆኖ በማገልገል መንፈሳዊ ውሸትንና ማታለያዎችን በመቆራረጥ ቅን ልብ ያላቸው ግለሰቦች ሰዎች መንፈሳዊ ነፃነት እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።—ዮሐንስ 8:31, 32
ኢየሱስ በዲያብሎስ በተፈተነ ጊዜ የዚህን መሣሪያ ኃይለኛነት አሳይቷል። ኢየሱስ በምድረ በዳ በተፈተነ ጊዜ የአምላክን ቃል በመጠቀም “ተጽፎአል” እያለ በመጥቀስ ከሰይጣን የተሰነዘሩትን ሦስት ጥቃቶች ተቋቁሞአል። (ማቴዎስ 4:1-11) የዚህን ሰይፍ አጠቃቀም በሚገባ ከተማርን የዋህ ሰዎች ከሰይጣን መዳፍ እንዲላቀቁ ልንረዳበት እንችላለን። የጉባኤ ሽማግሌዎችም የመንጋውን እምነት ለማበላሸት ከሚሞክሩ ሰዎች መንጋውን ለመጠበቅ በአምላክ ቃል ይጠቀማሉ።—ሥራ 20:28-30
አንድ ወታደር በሠይፍ የመጠቀምን ችሎታ እንዲሁ በቀላሉ አያገኝም። በሰይፍ በሚገባ ለመጠቀም እንዲችል ለዚህ ሥልጠና ራሱን ወስኖ ለረጅም ጊዜ መለማመድ ይኖርበታል። በተመሳሳይም በመንፈሳዊው ውጊያ በአምላክ ቃል በሚገባ ለመጠቀም አዘውትሮ ማጥናት እና በመስክ አገልግሎትም በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀምን መለማመድ ያስፈልጋል። “የእውነትን ቃል በቅንነት የምንናገር” እንድንሆን በምንችለው ሁሉ መንፈሳዊ ተዋጊዎች ለመሆን የሚያስችሉንን አስፈላጊ ጥረቶች ሁሉ እናድርግ።—2 ጢሞቴዎስ 2:15
ዘወትር ጸልዩ፣ ጽኑ
ሁሉም የመንፈሣዊ ዕቃ ጦር ክፍሎች ለአምላክ ያለንን ፍጹም አቋም ጠብቀን እንድንቆም በጣም ያስፈልጉናል። ይሁን እንጂ ይህን ዕቃ ጦር እንደለበስን መቆየት እንዴት እንችላለን? አዘውትሮ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አስቀድሞ መዘጋጀት፣ በስብሰባ ጊዜያት በጥሞና ማዳመጥና በትጋት መሳተፍ የጦር ዕቃችንን እንደለበስን እንድንቆይ ይረዳናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ ዕብራውያን 10:24, 25) በተጨማሪም አዘውትሮ በቅንዓት በመስክ አገልግሎት መሳተፍና ከጥሩ ክርስቲያኖች ጋር ባልንጀራ መሆን የማጥቂያና የመከላከያ መንፈሳዊ መሣሪያዎቻችንን በጥሩ ሁኔታ ይዘን ለመቆየት ይረዳናል።—ምሳሌ 13:20፤ ሮሜ 15:15, 16፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33
ትክክለኛ የአእምሮ ዝንባሌ መያዝም በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ዓለም ትኩረታችንን ለመሳብ በሚያቀርብልን ማታለያዎች ለመሳብ ፈቃደኞች መሆን የለብንም። ከዚህ ይልቅ ‘ጤናማ ዐይን’ ይኑረን። (ማቴዎስ 6:19-24) ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል ጽድቅን መውደድ እና አመጻን መጥላትን መማር አለብን። (ዕብራውያን 1:9) እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከአምላክ የተሰጠንን መንፈሳዊ ዕቃ ጦር እንደያዝን እንድንቆይ ይረዱናል።
ጳውሎስ ስለ እያንዳንዱ የጦር ዕቃ በዝርዝር ካስረዳ በኋላ እንዲህ በማለት ደመደመ፦ “በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ።” (ኤፌሶን 6:18) ታማኝ ወታደሮች ከአዝማቻቸው ጋር ዘወትር ይገናኛሉ፣ ትዕዛዝም ይቀበላሉ። እኛም ክርስቲያን ወታደሮች እንደመሆናችን መጠን ከበላይ ገዢያችን ከይሖዋ ጋር ‘የአሕዛብ አዛዥ’ አድርጎ በሾመው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መገናኘት ያስፈልገናል። (ኢሳይያስ 55:4) ይህ ግንኙነት ሊደረግ የሚችለው እንዲሁ ከላይ በሚቀርብ ጸሎት ሳይሆን ከይሖዋ ጋር ያለንን ጥልቅ ቅርርብ እና ዝምድና በሚያንፀባርቅ ከልብ የሚቀርብ ጸሎትና ምልጃ አማካኝነት ነው። አዘውትረን ከይሖዋ ጋር በመገናኘታችን በውጊያው እንድንቀጥል የሚያስችለንን ጥንካሬ ይሰጠናል።
ኢየሱስ “እኔ ዓለምን አሸንፌአለሁ” ብሎአል። (ዮሐንስ 16:33) እኛም እንድናሸንፍ ይሖዋ ይፈልጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ሊሞት በተቃረበበት ጊዜ “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፣ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፣ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ።” ለማለት ችሎ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 4:7) እኛም በውጊያው የድርሻችንን በመሥራት እንዲሁ ለማለት የምንፈልግ ከሆነ የአምላክን የጦር ዕቃ ሁሉ በመልበስ የዲያብሎስን ሽንገላ እንቃወም።—ኤፌሶን 6:11