“የመንፈስ ፍሬ” አምላክን ያስከብራል
“ብዙ ፍሬ ማፍራታችሁን ብትቀጥሉ . . . በዚህ አባቴ ይከበራል።”—ዮሐ. 15:8
1, 2. (ሀ) ሌሎችን ለማበረታታት ምን አጋጣሚዎች አሉን? (ለ) ይሖዋ እሱን በተሻለ መንገድ ለማገልገል የሚረዳን ምን ስጦታ ሰጥቶናል?
እስቲ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሁለት ሁኔታዎችን እንመልከት፦ አንዲት ክርስቲያን፣ ወጣት የሆነች አንዲት እህት የሆነ ነገር እንዳስጨነቃት ትመለከታለች። በመሆኑም ከእሷ ጋር አገልግሎት ለመውጣት ቀጠሮ ትይዛለች። ከአንዱ ቤት ወደ ሌላኛው ቤት ሲሄዱ በመሃል ጨዋታ ይነሳል፤ በዚህ ወቅት ወጣቷ እህት ያሳሰባትን ጉዳይ መናገር ትጀምራለች። ማታ ላይ ይህች ወጣት እህት በምትጸልይበት ወቅት ጎልማሳ የሆነችው እህት ላሳየቻት ፍቅራዊ አሳቢነት ይሖዋን ታመሰግናለች፤ የምትፈልገው እንዲህ ያለ አሳቢነት ነበር። አሁን ደግሞ ሌላ ምሳሌ እንመልከት፤ በሌላ አገር ሲያገለግሉ የቆዩ አንድ ባልና ሚስት በቅርቡ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ወንድሞች አንድ ቦታ ተሰባስበው ሲጫወቱ እነዚህ ባልና ሚስት ያጋጠማቸውን ተሞክሮ በደስታ ይናገራሉ፤ በዚህ ጊዜ አንድ ወጣት ወንድም በጥሞና ያዳምጣል። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ይህ ወንድም ወደ ሌላ አገር ተመድቦ ለመሄድ በዝግጅት ላይ ሳለ እነዚያን ባልና ሚስት ያስታውሳል፤ የተናገሩት ነገር ሚስዮናዊ የመሆን ፍላጎት እንዲያድርበት እንዳደረገው ትዝ ይለዋል።
2 እነዚህ ሁኔታዎች ሕይወትህን የቀየረ አንድ ሰው አሊያም በሕይወቱ ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳደርክበት ግለሰብ ትዝ እንዲልህ አድርገውህ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ከሰዎች ጋር በሆነ ወቅት ስንጨዋወት የምንናገረው ነገር ሁልጊዜ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል ማለት አይደለም፤ ይሁንና ሌሎችን ለማበረታታትና ለማነጽ የሚያስችሉ አጋጣሚዎች በየዕለቱ እናገኛለን። ችሎታህንና ባሕርያትህን በማሻሻል ወንድሞችህንና እህቶችህን ይበልጥ ለመርዳትና ይሖዋን በተሻለ መንገድ ለማገልገል እንድትጠቀምባቸው ለማድረግ የሚረዳህ ነገር ብታገኝ ምን ይሰማሃል? በጣም አስደሳች አይሆንም ነበር? የሚገርመው ነገር፣ ይሖዋ እንዲህ ያለ ስጦታ ሰጥቶናል፤ ይህ ስጦታ መንፈስ ቅዱስ ነው። (ሉቃስ 11:13) የአምላክ መንፈስ በሕይወታችን ውስጥ ሲሠራ ግሩም የሆኑ ባሕርያትን እንድናፈራ የሚረዳን ሲሆን ይህ ደግሞ በሁሉም የአምልኮታችን ክፍሎች ማሻሻያ እንድናደርግ ያስችለናል። እንዴት ያለ ግሩም ስጦታ ነው!—ገላትያ 5:22, 23ን አንብብ።
3. (ሀ) “የመንፈስ ፍሬ” ማፍራታችን አምላክን የሚያስከብረው እንዴት ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
3 መንፈስ ቅዱስ የሚያፈራቸው ባሕርያት የዚህ መንፈስ ምንጭ የሆነውን የይሖዋ አምላክን ማንነት የሚያንጸባርቁ ናቸው። (ቆላ. 3:9, 10) ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ብዙ ፍሬ ማፍራታችሁን ብትቀጥሉ . . . በዚህ አባቴ ይከበራል” ብሎ በነገራቸው ጊዜ ክርስቲያኖች አምላክን ለመምሰል እንዲጥሩ የሚያነሳሳቸው ዋነኛው ምክንያት ምን እንደሆነ ጠቁሟል።a (ዮሐ. 15:8) “የመንፈስ ፍሬ” እያፈራን ስንሄድ ውጤቱ በአነጋገራችንና በድርጊታችን በግልጽ ይታያል፤ ይህ ደግሞ ለአምላካችን ውዳሴ ያመጣለታል። (ማቴ. 5:16) የመንፈስ ፍሬ፣ የሰይጣን ዓለም ከሚያፈራቸው ባሕርያት የተለየ የሆነው በምን መንገዶች ነው? የመንፈስ ፍሬን ማፍራት የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግ አስቸጋሪ የሚሆንብን ለምን ሊሆን ይችላል? ስለ መጀመሪያዎቹ ሦስት የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች ይኸውም ስለ ፍቅር፣ ደስታና ሰላም እየተወያየን ስንሄድ እነዚህን ጥያቄዎች እንመረምራለን።
በላቀ መሠረታዊ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ ፍቅር
4. ኢየሱስ ለተከታዮቹ ያስተማረው ምን ዓይነት ፍቅር እንዲያሳዩ ነው?
4 የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆነው ፍቅር በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ከሚያንጸባርቁት ፍቅር እጅግ የተለየ ነው። እንዴት? ይህ ፍቅር በላቀ መሠረታዊ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ነው። ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ይህን ልዩነት በግልጽ ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:43-48ን አንብብ።) የሚወዱንን መውደድና ሌሎች እኛን በሚይዙበት መንገድ እነሱን መያዝ ኃጢአተኞችም እንኳ የሚያደርጉት ነገር መሆኑን ገልጿል። እንዲህ ያለው “ፍቅር” ከልብ የመነጨ መሥዋዕትነት መክፈልን አይጠይቅም፤ ከዚህ ይልቅ ብድር ከመመለስ ያለፈ ነገር አይደለም። ‘በሰማያት ላለው አባታችን ልጆች መሆን’ ከፈለግን ከዓለም የተለየን መሆን አለብን። ሰዎችን እነሱ በሚይዙን መንገድ ከመያዝ ይልቅ ይሖዋ እነሱን በሚመለከትበትና በሚይዝበት መንገድ ልንመለከታቸውና ልንይዛቸው ይገባል። ይሁንና ኢየሱስ ባዘዘን መሠረት ጠላቶቻችንን መወደድ የምንችለው እንዴት ነው?
5. ስደት ለሚያደርሱብን ሰዎች ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
5 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንመልከት። ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ እያገለገሉ ሳለ ተይዘው የተደበደቡ ከመሆኑም በላይ ወደ እስር ቤቱ ውስጠኛ ክፍል ገብተው እግራቸው በእግር ግንድ እንዲታሰር ተደረገ። በዚህ ጊዜ የእስር ቤቱ ጠባቂም ሳያሠቃያቸው አልቀረም። የምድር ነውጥ በመከሰቱ ምክንያት ድንገት ከእስር ነፃ ሲሆኑ ሰውየውን ለመበቀል የሚያስችል አጋጣሚ በማግኘታቸው ተደስተው ይሆን? በፍጹም። ሕይወቱ ስላሳሰባቸው በሌላ አባባል ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ስለነበራቸው እሱን ለማዳን ፈጣን እርምጃ ወስደዋል፤ ይህ ደግሞ የእስር ቤቱ ጠባቂም ሆነ መላው ቤተሰቡ አማኞች እንዲሆኑ በር ከፍቷል። (ሥራ 16:19-34) በተመሳሳይም በዘመናችን የሚገኙ በርካታ ወንድሞቻችን ‘ስደት የሚያደርሱባችሁን ባርኩ’ የሚለውን መመሪያ ተከትለዋል።—ሮም 12:14
6. የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ለወንድሞቻችን ፍቅር ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (በገጽ 21 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)
6 ለእምነት ባልንጀሮቻችን ያለን ፍቅር ለሚጠሉን ሰዎች ከምናሳየው ፍቅር የላቀ ነው። “ነፍሳችንን ለወንድሞቻችን አሳልፈን የመስጠት ግዴታ አለብን።” (1 ዮሐንስ 3:16-18ን አንብብ።) ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ በጥቃቅን ጉዳዮች ፍቅር ማሳየት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድን ወንድም የሚያስቀይም ነገር ብንናገር ወይም ብናደርግ ቅድሚያውን ወስደን እንደ በፊቱ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ለማድረግ የምንጥር ከሆነ ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። (ማቴ. 5:23, 24) አንድ ሰው ቢያስቀይመንስ? “ይቅር ባይ” ለመሆን ዝግጁ ነን ወይስ አንዳንድ ጊዜ ቂም የመያዝ አዝማሚያ አለን? (መዝ. 86:5) መንፈስ ቅዱስ የሚያፈራው ጥልቅ ፍቅር “ይሖዋ በነፃ ይቅር” እንዳለን ሌሎችን በነፃ ይቅር በማለት ቀላል የሆኑ ስህተቶችን እንድናልፍ ሊረዳን ይችላል።—ቆላ. 3:13, 14፤ 1 ጴጥ. 4:8
7, 8. (ሀ) ለሰዎች ያለን ፍቅር ለአምላክ ካለን ፍቅር ጋር የተያያዘው እንዴት ነው? (ለ) ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው? (ከታች ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
7 የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ለወንድሞቻችን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ለአምላክ ያለን ፍቅር እያደገ እንዲሄድ በማድረግ ነው። (ኤፌ. 5:1, 2፤ 1 ዮሐ. 4:9-11, 20, 21) መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ፣ በማሰላሰልና በመጸለይ በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ጋር የምናሳልፈው ጊዜ ብርታት የሚሰጠን ከመሆኑም ሌላ በሰማይ ለሚገኘው አባታችን ያለን ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ያደርጋል። እርግጥ ነው፣ ወደ አምላክ ለመቅረብ ጊዜ መግዛት ይኖርብናል።
8 እስቲ ይህን ሁኔታ በምሳሌ እንመልከት፤ የአምላክን ቃል ማንበብ፣ ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰልና ወደ ይሖዋ መጸለይ የሚቻለው በቀን ውስጥ በተወሰነ ሰዓት ላይ ብቻ ነው እንበል። በግልህ ከይሖዋ ጋር የምታሳልፈውን ይህን ጊዜ ምንም ነገር እንዳይሻማብህ ለማድረግ ጥረት አታደርግም ነበር? እውነት ነው፣ ማንም ሰው ወደ አምላክ እንዳንጸልይ ሊያግደን አይችልም፤ እንዲሁም አብዛኞቻችን መጽሐፍ ቅዱስን በፈለግነው ጊዜ ማንበብ እንችላለን። ያም ሆኖ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የምናከናውናቸው በርካታ ነገሮች ከአምላክ ጋር ለብቻችን ለማሳለፍ የመደብነውን ጊዜ እንዳይነኩብን እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ወደ ይሖዋ ለመቅረብ በተቻለህ መጠን በየዕለቱ ሰፋ ያለ ጊዜ ትመድባለህ?
‘ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ደስታ’
9. የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆነው ደስታ ካሉት መገለጫዎች አንዱ ምንድን ነው?
9 የመንፈስ ፍሬ ካሉት ጉልህ ባሕርያት አንዱ ጽኑ መሆኑ ነው። ቀጥለን የምንመለከተው ሁለተኛው የመንፈስ ፍሬ ገጽታ ይኸውም ደስታ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። ደስታ በአስቸጋሪ የአየር ጠባይም ሳይቀር ልምላሜውን ሳያጣ እንደሚቀጥል ችግር የሚቋቋም ተክል ነው። በምድር ዙሪያ የሚገኙ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች ‘ብዙ መከራ ቢደርስባቸውም ቃሉን ከመንፈስ ቅዱስ በሚገኝ ደስታ ተቀብለዋል።’ (1 ተሰ. 1:6) ሌሎች ደግሞ ችግርና እጦት ያጋጥማቸዋል። ሆኖም ይሖዋ “ሙሉ በሙሉ መጽናትና በደስታ መታገሥ [እንዲችሉ]” በመንፈሱ አማካኝነት ኃይል ይሰጣቸዋል። (ቆላ. 1:11) ለመሆኑ የዚህ ደስታ ምንጭ ምንድን ነው?
10. የደስታችን ምንጭ ምንድን ነው?
10 የሰይጣን ዓለም ከሚያቀርበው ‘አስተማማኝነት የሌለው ሀብት’ በተቃራኒ ይሖዋ የሚሰጠን መንፈሳዊ ሀብት ዘላቂ ጥቅም አለው። (1 ጢሞ. 6:17፤ ማቴ. 6:19, 20) ይሖዋ፣ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት የማግኘት አስደሳች ተስፋ ከፊታችን ዘርግቶልናል። የዓለም አቀፉ ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበር አባል በመሆናችንም ደስተኞች ነን። ከሁሉም በላይ ለደስታችን መሠረት የሆነው ከአምላክ ጋር የመሠረትነው ዝምድና ነው። ዳዊት ስደተኛ ሆኖ ለመኖር ቢገደድም ይሖዋን እንዲህ ሲል በመዝሙር አወድሶታል፦ “ምሕረትህ ከሕይወት ይበልጣልና፤ ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል። እንግዲህ፣ በሕይወቴ ዘመን አመሰግንሃለሁ።” እኛም የእሱን ስሜት እንጋራለን። (መዝ. 63:3, 4) ችግሮች ቢደርሱብንም እንኳ ልባችን አምላክን በደስታ ለማወደስ ይገፋፋል።
11. ይሖዋን በደስታ ማገልገላችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
11 ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ!” በማለት አበረታቷቸዋል። (ፊልጵ. 4:4) ክርስቲያኖች ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አገልግሎት በደስታ ማከናወናቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሰይጣን ከይሖዋ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ ባነሳው ጥያቄ ምክንያት ነው። ሰይጣን፣ ማንም ሰው አምላክን በፈቃደኝነት ተነሳስቶ አያገለግለውም የሚል ጥያቄ አስነስቷል። (ኢዮብ 1:9-11) ይሖዋን ደስታ ሳይኖረን እሱን የመታዘዝ ግዴታ እንዳለብን ተሰምቶን ብቻ የምናገለግለው ከሆነ የምናቀርበው የምስጋና መሥዋዕት የተሟላ አይሆንም። እንግዲያው መዝሙራዊው “እግዚአብሔርን በደስታ አገልግሉት፤ በፍስሓ ዝማሬ ፊቱ ቅረቡ” በማለት የሰጠውን ምክር ለመከተል ጥረት እናድርግ። (መዝ. 100:2) በደስታና በፈቃደኝነት የሚቀርብ አገልግሎት አምላክን ያስከብረዋል።
12, 13. አፍራሽ ስሜቶችን ለመዋጋት ምን ማድረግ እንችላለን?
12 እውነቱን ለመናገር፣ ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ ግለሰቦችም እንኳ ተስፋ የሚቆርጡበት እንዲሁም አዎንታዊ አመለካከት ይዘው መቀጠል አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ጊዜ አለ። (ፊልጵ. 2:25-30) እንዲህ ባለ ጊዜ ምን ሊረዳን ይችላል? ኤፌሶን 5:18, 19 እንዲህ ይላል፦ “በመንፈስ መሞላታችሁን ቀጥሉ፤ በመዝሙርና በውዳሴ እንዲሁም በመንፈሳዊ ዝማሬ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በልባችሁም ለይሖዋ የምስጋና መዝሙር አዚሙ።” ይህን ምክር ሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት ነው?
13 አፍራሽ በሆኑ ስሜቶች ስንዋጥ ይሖዋ እንዲረዳን መማጸን እንዲሁም ምስጋና በሚገባቸው ነገሮች ላይ ለማሰላሰል ጥረት ማድረግ እንችላለን። (ፊልጵስዩስ 4:6-9ን አንብብ።) አንዳንዶች የመንግሥቱን መዝሙሮቻችንን በማዳመጥ ሙዚቃውን እየተከተሉ ድምፃቸውን ቀስ አድርገው ማዜማቸው መንፈሳቸውን እንዳደሰላቸውና አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ለማተኮር እንደረዳቸው ተናግረዋል። አንድ ወንድም፣ መጥፎ ትዝታዎች ወደ አእምሮው እየመጡ ይቸገር የነበረ ሲሆን ይህ ሁኔታ ብዙ ጊዜ ለብስጭትና ለተስፋ መቁረጥ ይዳርገው ነበር፤ ይህ ወንድም እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “አዘውትሬ ልባዊ ጸሎት ከማቅረብ በተጨማሪ የተወሰኑ የመንግሥቱን መዝሙሮች በቃሌ ለመያዝ እሞክር ነበር። ማራኪ የሆኑትን እነዚህን ለይሖዋ የሚቀርቡ ውዳሴዎች ጮክ ብዬ ወይም በልቤ መዘመሬ ውስጣዊ ሰላም ሰጥቶኛል። ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለው መጽሐፍ የወጣውም በዚያው ወቅት ነበር። በቀጣዩ ዓመት ይህን መጽሐፍ ሁለት ጊዜ አነበብኩት። ለልቤ ፈዋሽ ዘይት ሆኖልኛል። ይሖዋ ጥረቴን እንደባረከልኝ ይሰማኛል።”
‘አንድ ላይ የሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ’
14. የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆነው ሰላም ካሉት ጉልህ ገጽታዎች አንዱ ምንድን ነው?
14 በብሔራት አቀፍ ስብሰባዎቻችን ላይ የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸው ልዑካን ከክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው ጋር ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ ይደሰታሉ። ይህ ሁኔታ በዛሬው ጊዜ በአምላክ ሕዝቦች መካከል የሚታየው ሰላም ካሉት ገጽታዎች አንዱን ይኸውም ዓለም አቀፍ አንድነታችንን አጉልቶ ያሳያል። ብዙ ጊዜ ሰዎች፣ እርስ በርሳቸው በጠላትነት የሚተያዩ እንደሆኑ አድርገው የሚያስቧቸው ግለሰቦች “አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት” ሲያደርጉ ሲመለከቱ በጣም ይደነቃሉ። (ኤፌ. 4:3) ብዙዎች እንዲህ ያለውን አንድነት ለማስገኘት ምን ለውጥ ማድረግ እንዳስፈለጋቸው ስናስብ በክርስቲያኖች መካከል የሚታየው አንድነት በእርግጥም አስገራሚ ይሆናል።
15, 16. (ሀ) ጴጥሮስ ያደገው ምን ዓይነት አመለካከት በሰፈነበት ማኅበረሰብ ውስጥ ነበር? ይህስ ምን ዓይነት ፈተና አስከትሎበት ነበር? (ለ) ጴጥሮስ አመለካከቱን እንዲያስተካክል ይሖዋ የረዳው እንዴት ነው?
15 የተለያየ አስተዳደግና ባሕል ያላቸውን ሰዎች አንድ ማድረግ አስቸጋሪ ነው። እንዲህ ዓይነቱን አንድነት ለማስገኘት ምን ነገር ማሸነፍ እንዳለብን ማስተዋል እንድንችል በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረውን የሐዋርያው ጴጥሮስን ምሳሌ እንመልከት። ጴጥሮስ፣ ላልተገረዙ አሕዛብ የነበረው አመለካከት ምን እንደነበር ቀጥሎ ከተናገረው ሐሳብ መመልከት ይቻላል፦ “አንድ አይሁዳዊ ከሌላ ዘር ጋር ይቀራረብ ወይም ይወዳጅ ዘንድ ሕጉ እንደማይፈቅድ በሚገባ ታውቃላችሁ፤ ሆኖም አምላክ ማንንም ሰው ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ ማለት እንደማይገባኝ ገልጦልኛል።” (ሥራ 10:24-29፤ 11:1-3) በዘመኑ በብዙዎች ዘንድ ከነበረው አመለካከት አንጻር ጴጥሮስ የእሱ ወገን ለሆኑ አይሁዳውያን ብቻ ፍቅር እንዲያሳይ ሕጉ እንደሚጠብቅበት አድርጎ ያስብ የነበረ ይመስላል። ጴጥሮስ አሕዛብን እንደ ጠላት አድርጎ መመልከት ምንም ችግር እንደሌለው አድርጎ ሳያስብ አልቀረም።b
16 ጴጥሮስ ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ሲገባ ምን ያህል ጨንቆት ሊሆን እንደሚችል አስብ። ቀደም ሲል ለአሕዛብ ጥሩ አመለካከት ያልነበረው ግለሰብ ከእነዚህ ሰዎች ጋር “አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ . . . እርስ በርስ [ተስማምቶ]” መኖር ይችላል? (ኤፌ. 4:3, 16) አዎን፣ ምክንያቱም ጴጥሮስ አመለካከቱን ማስተካከል እንዲጀምርና ለአሕዛብ የነበረውን ጥላቻ እንዲያስወግድ የአምላክ መንፈስ ከጥቂት ቀናት በፊት ልቡን ከፍቶለት ነበር። አምላክ ለሰዎች ያለው አመለካከት በዘራቸው ወይም በዜግነታቸው ላይ የተመካ እንዳልሆነ ይሖዋ በራእይ አማካኝነት ለጴጥሮስ በግልጽ አሳይቶታል። (ሥራ 10:10-15) በመሆኑም ጴጥሮስ ለቆርኔሌዎስ እንዲህ ለማለት ችሎ ነበር፦ “አምላክ እንደማያዳላ በእርግጥ አስተዋልኩ፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።” (ሥራ 10:34, 35) ጴጥሮስ አመለካከቱን ለውጦ ከመላው “የወንድማማች ማኅበር” ጋር አንድ ለመሆን ችሏል።—1 ጴጥ. 2:17
17. የአምላክ ሕዝቦች ያላቸው አንድነት አስደናቂ የሆነው ለምንድን ነው?
17 ጴጥሮስ ያጋጠመው ሁኔታ በዛሬው ጊዜ በአምላክ ሕዝቦች መካከል እየተከናወነ ያለውን አስገራሚ ለውጥ እንድናደንቅ ይረዳናል። (ኢሳይያስ 2:3, 4ን አንብብ።) “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ” በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አመለካከታቸውን ‘ጥሩ ከሆነው፣ ተቀባይነት ካለውና ፍጹም ከሆነው የአምላክ ፈቃድ’ ጋር ለማስማማት ሲሉ ለውጥ አድርገዋል። (ራእይ 7:9፤ ሮም 12:2) በአንድ ወቅት ከእነዚህ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በሰይጣን ዓለም ውስጥ የሚታየው ጥላቻ፣ ጠላትነትና መከፋፈል ተጽዕኖ አሳድሮባቸው ነበር። ይሁንና የአምላክን ቃል በማጥናትና በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ‘ሰላም የሚገኝበትን ነገር ለማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ማድረግን’ ተምረዋል። (ሮም 14:19) ይህን በማድረጋቸው የሚገኘው አንድነት አምላክን ያስከብራል።
18, 19. (ሀ) ለጉባኤው ሰላምና አንድነት እያንዳንዳችን አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
18 በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያለው ሰላምና አንድነት ቀጣይ እንዲሆን እያንዳንዳችን አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው? በበርካታ ጉባኤዎች ውስጥ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ሰዎች ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ከእኛ የተለየ ባሕል ይኖራቸው አሊያም የእኛን ቋንቋ በደንብ መናገር አይችሉ ይሆናል። እነዚህን ወንድሞቻችንን ለማወቅ ጥረት እናደርጋለን? የአምላክ ቃል እንዲህ እንድናደርግ ያበረታታናል። ጳውሎስ፣ አይሁዳዊም ሆነ አሕዛብ ክርስቲያኖች ለሚገኙበት በሮም ላለው ጉባኤ ሲጽፍ “ክርስቶስ እኛን እንደተቀበለን ሁሉ አምላክ ይከበር ዘንድ እናንተም አንዳችሁ ሌላውን ተቀበሉ” ብሏል። (ሮም 15:7) በጉባኤያችሁ ውስጥ ይበልጥ ልታውቀው እንደሚገባ የሚሰማህ ክርስቲያን አለ?
19 መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ እንዲሠራ ሌላስ ምን ማድረግ እንችላለን? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የተቀሩትን የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች እየመረመርን ስንሄድ ለዚህ ጥያቄ መልስ እናገኛለን።
[የግርጌ ማሰታወሻዎች]
a ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሰው ፍሬ ‘የመንፈስ ፍሬን’ እንዲሁም ክርስቲያኖች በመንግሥቱ የስብከት ሥራ አማካኝነት ለአምላክ የሚያቀርቡትን “የከንፈር ፍሬ” ይጨምራል።—ዕብ. 13:15
b ዘሌዋውያን 19:18 “ወገንህን አትበቀል፤ ወይም ምቀኛ አትሁንበት፤ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ይላል። የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች “ወገንህ” እንዲሁም “ባልንጀራህ” የሚሉት አባባሎች የሚያመለክቱት አይሁዳውያንን ብቻ እንደሆነ ያምኑ ነበር። ሕጉ እስራኤላውያን ከሌሎች ብሔራት የተለዩ እንዲሆኑ ያዝዝ ነበር። ያም ሆኖ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች የሚያስፋፉትን አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች በሙሉ ጠላት በመሆናቸው በግለሰብ ደረጃ ሊጠሉ ይገባል የሚለውን አመለካከት አይደግፍም።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ለወንድሞቻችን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
• ለአምላክ የምናቀርበውን አገልግሎት በደስታ ማከናወናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• ለጉባኤው ሰላምና አንድነት አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“እውነተኛዎቹ ክርስቲያኖች እነዚህ ናቸው”
ቢትዊን ሬሲስታንስ ኤንድ ማርተርደም—ጂሆቫስ ዊትነስስ ኢን ዘ ሰርድ ራይክ የተባለው መጽሐፍ አይሁዳዊ የሆነ አንድ ወጣት እስረኛ የሰጠውን ሐሳብ ይዟል፤ ይህ ወጣት ወደ ኖየንጋሜ ማጎሪያ ካምፕ በመጣበት ወቅት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘበትን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦
“ከዳካው የመጣነው አይሁዳውያን፣ ልክ ወደ ካምፑ ስንደርስ ሌሎቹ አይሁዳውያን ያላቸውን ለእኛ ላለማካፈል ሲሉ ሁሉንም ነገር መደበቅ ጀመሩ። . . . [ማጎሪያ ካምፕ] ከመግባታችን በፊት እርስ በርሳችን እንረዳዳ ነበር። እዚህ ግን ሁኔታው የሕይወትና የሞት ጉዳይ ስለሆነ ሁሉም ሰው ስለ ሌሎች ማሰብ ትቶ በዋነኝነት የሚያሳስበው ነገር የራሱን ሕይወት ማቆየት ነበር። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ምን እንዳደረጉ ተመልከቱ። በዚያን ጊዜ የውኃ ቧንቧዎችን ይጠግኑ ስለነበር ሥራቸው በጣም ከባድ ነበር። ቅዝቃዜው አጥንት የሚሰብር ከመሆኑም በላይ በረዶ በሆነ ውኃ ውስጥ ቀኑን ሙሉ ቆመው መዋል ነበረባቸው። ይህን ሁኔታ በጽናት መቋቋም የቻሉት እንዴት እንደሆነ በወቅቱ ማንም ሰው ሊገባው አልቻለም። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይሖዋ ጥንካሬ እንደሰጣቸው ይናገሩ ነበር። ስለሚርባቸው እነሱም ልክ እንደ እኛ የሚሰጣቸውን ዳቦ በጣም ይፈልጉት ነበር። ያም ሆኖ ምን አደረጉ? የተሰጣቸውን ዳቦ በሙሉ ሰበሰቡና ግማሹን ለራሳቸው ከወሰዱ በኋላ የቀረውን ደግሞ ከዳካው አዲስ ለመጡ የእምነት ባልንጀሮቻቸው ሰጧቸው። እነዚህ የእምነት አጋሮቻቸው ሲመጡ የሳሟቸው ከመሆኑም ሌላ ጥሩ አቀባበል አደረጉላቸው። ምግብ ከመብላታቸው በፊት ጸለዩ። ከዚያ በኋላ ሲታዩ ሁሉም ባገኙት ነገር እንደረኩና ደስተኞች እንደሆኑ ያስታውቁ ነበር። ከበሉ በኋላ የረሃብ ስሜት እንደሌላቸው ይናገሩ ነበር። እውነተኛዎቹ ክርስቲያኖች እነዚህ ናቸው ብዬ ያሰብኩት በዚህ ጊዜ ነበር።”
[በገጽ 19 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ስትል በየዕለቱ ከሌሎች እንቅስቃሴዎችህ ላይ ጊዜ ትገዛለህ?