የክርስቶስን አስተሳሰብ አንጸባርቁ
“ጽናትንና ማጽናኛን የሚሰጠው አምላክ በመካከላችሁ ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ ይስጣችሁ።”—ሮሜ 15:5 Nw
1. የአንድ ሰው ሕይወት በአስተሳሰቡ ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው?
አስተሳሰብ በአንድ ሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያስከትል ይችላል። ግዴለሽነት ወይም ትጋት የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ፣ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ አስተሳሰብ፣ የጠበኝነት ወይም የተባባሪነት መንፈስ የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ፣ ምሬት ወይም አመስጋኝነት የተሞላበት አስተሳሰብ አንድ ሰው ለሚያጋጥሙት ሁኔታዎች በሚሰጠው ምላሽና ሌሎች ሰዎች ለእርሱ በሚኖራቸው ግምት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። አንድ ሰው አስተሳሰቡ ጥሩ ከሆነ በአስቸጋሪ ወቅቶች እንኳን ሳይቀር ደስተኛ ሊሆን ይችላል። መጥፎ አስተሳሰብ ያለው ሰው ደግሞ ኑሮው ጥሩ ቢሆንለት እንኳ ምንም ነገር ትክክል መስሎ አይታየውም።
2. አንድ ሰው አስተሳሰብን የሚማረው እንዴት ነው?
2 ጥሩም ሆነ መጥፎ አስተሳሰቦችን መቅሰም ይቻላል። እንዲያውም ሁለቱም ቢሆኑ በትምህርት የሚገኙ ናቸው። ኮሊየርስ ኢንሳይክሎፔዲያ ገና ስለተወለደ ሕፃን ሲናገር “አንድን ቋንቋ ወይም ሌላ ማንኛውንም ዓይነት ችሎታ በመቅሰም ወይም በመማር የራሱ እንደሚያደርግ ሁሉ ውሎ አድሮ የሚኖረውን አስተሳሰብም የሚያገኘው በመቅሰም ወይም በመማር ነው” ይላል። አስተሳሰብን ልንማር የምንችለው እንዴት ነው? ለዚህ አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ በርካታ ነገሮች ያሉ ቢሆንም አካባቢና የምንቀርባቸው ሰዎች ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኢንሳይክሎፔዲያ “በጣም የምንቀርባቸውን ሰዎች አስተሳሰብ እንቀስማለን ወይም እንደ ስፖንጅ እንመጣለን” በማለት ይናገራል። ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል” በማለት ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር ተናግሯል።—ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33
የትክክለኛ አስተሳሰብ ምሳሌ
3. በአስተሳሰቡ ምሳሌ የሆነው ማን ነው? ልንመስለው የምንችለውስ እንዴት ነው?
3 በሌሎች ነገሮች ምሳሌ እንደሆነን ሁሉ በአስተሳሰብ ረገድም ኢየሱስ ክርስቶስ ልንከተለው የሚገባ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ትቶልናል። “እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:15) ኢየሱስን መምሰል ከፈለግን በመጀመሪያ ስለ እርሱ መማር አለብን።a የኢየሱስን ሕይወት በምንመረምርበት ጊዜ “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና” የሚለውን ሐዋርያው ጴጥሮስ የሰጠውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ የማድረግ ግብ ሊኖረን ይገባል። (1 ጴጥሮስ 2:21) የተቻለንን ያህል ኢየሱስን የመምሰል ግብ ሊኖረን ይገባል። ይህም የእርሱን አስተሳሰብ ማዳበርን ይጨምራል።
4, 5. በሮሜ 15:1-3 ላይ ጎላ ተደርጎ የተገለጸው የትኛው የኢየሱስ አስተሳሰብ ገጽታ ነው? ክርስቲያኖች እርሱን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው?
4 የክርስቶስ ኢየሱስን አስተሳሰብ መያዝ ምን ነገሮችን ይጨምራል? ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ 15ኛ ምዕራፍ ለዚህ ጥያቄ መልስ እንድናገኝ ይረዳናል። ጳውሎስ የዚህ ምዕራፍ መክፈቻ በሆኑት ጥቂት ቁጥሮች ላይ አንዱን የኢየሱስ ጉልህ ባሕርይ ጠቅሷል። እንዲህ አለ:- “እኛም ኃይለኞች [“ብርቱዎች፣” የ1980 ትርጉም ] የሆንን የደካሞችን ድካም እንድንሸከም ራሳችንንም ደስ እንዳናሰኝ ይገባናል። እያንዳንዳችን እንድናንጸው እርሱን ለመጥቀም ባልንጀራችንን ደስ እናሰኝ። ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና፤ ነገር ግን:- አንተን የነቀፉበት ነቀፋ ወደቀብኝ ተብሎ እንደ ተጻፈ ሆነበት።”—ሮሜ 15:1-3
5 ክርስቲያኖች ራሳቸውን ብቻ ለማስደሰት ከመፈለግ ይልቅ የኢየሱስን አስተሳሰብ በመኮረጅ የሌሎችንም ፍላጎት በትሕትና ለማሟላት ዝግጁ እንዲሆኑ ተበረታተዋል። እንዲያውም፣ በትሕትና ሌሎችን ለማገልገል መነሳሳት “ብርቱዎች” የተባሉት ሰዎች ጉልህ ጠባይ ነው። እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ ይበልጥ በመንፈሳዊ ብርቱ የሆነው ኢየሱስ “የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” በማለት ስለ ራሱ ተናግሯል። (ማቴዎስ 20:28) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እኛም በተመሳሳይ “ደካሞች” የሆኑትን ጨምሮ ሌሎች ሰዎችን ለማገልገል መጣጣር ይኖርብናል።
6. ኢየሱስ ተቃውሞና ነቀፋ ሲደርስበት የሰጠውን ምላሽ ልንኮርጅ የምንችለው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስ ያንጸባረቀው ሌላው ጉልህ ባሕርይ ደግሞ ሁልጊዜ ገንቢ የሆነው አስተሳሰቡና ድርጊቱ ነው። ሌሎች ሰዎች የነበራቸው አፍራሽ አስተሳሰብ አምላክን ለማገልገል በነበረው መልካም አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድርበት ፈጽሞ አልፈቀደም። እኛም ተጽዕኖ እንዲያሳድርብን መፍቀድ አይኖርብንም። ኢየሱስ አምላክን በታማኝነት በማገልገሉ ምክንያት ነቀፋና ስደት በደረሰበት ጊዜ ያለ ምንም ማማረር በትዕግሥት ጸንቷል። ‘የሚያንጸውን ነገር በማድረግ’ ባልንጀራቸውን ለማስደሰት የሚጣጣሩ ሁሉ እምነትና አስተዋይነት ከጎደለው ዓለም ተቃውሞ ሊደርስባቸው እንደሚችል ያውቅ ነበር።
7. ኢየሱስ ትዕግሥት ያሳየው እንዴት ነው? እኛም እንዲሁ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
7 ኢየሱስ በሌሎች መንገዶችም ትክክለኛ የሆነ አስተሳሰብ አሳይቷል። ይሖዋ ዓላማዎቹን ደረጃ በደረጃ የሚፈጽምበትን ጊዜ በትዕግሥት ተጠባብቋል። (መዝሙር 110:1፤ ማቴዎስ 24:36፤ ሥራ 2:32-36፤ ዕብራውያን 10:12, 13) በተጨማሪም ኢየሱስ ተከታዮቹን በትዕግሥት ይዟቸዋል። “ከእኔም ተማሩ” ብሏቸዋል። “የዋህ” እንደመሆኑ መጠን የሚሰጠው መመሪያ የሚያንጽና መንፈስን የሚያድስ ነበር። እንዲሁም ‘በልቡ ትሑት’ ስለሆነ ራሱን ከልክ በላይ ከፍ ከፍ የሚያደርግ ወይም ዕብሪተኛ አልነበረም። (ማቴዎስ 11:29) ጳውሎስ የሚከተለውን በተናገረ ጊዜ እነዚህን የኢየሱስ አስተሳሰብ ገጽታዎች እንድንመስል አበረታቶናል:- “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፣ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ።”—ፊልጵስዩስ 2:5-7
8, 9. (ሀ) ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አስተሳሰብ ለማዳበር ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ የተወልንን ምሳሌ ፍጹም በሆነ መንገድ መከተል ቢያቅተን ተስፋ መቁረጥ የማይኖርብን ለምንድን ነው? በዚህ ረገድ ጳውሎስ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?
8 ሌሎችን ማገልገልና ከራሳችን ፍላጎት ይልቅ የእነርሱን ፍላጎት ማስቀደም እንዳለብን መናገሩ ቀላል ነው። ይሁን እንጂ አስተሳሰባችንን በሃቀኝነት በምንመረምርበት ጊዜ ልባችን ሙሉ በሙሉ ከዚያ አባባል ጋር አለመጣጣሙን እንገነዘብ ይሆናል። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? አንደኛ የራስ ወዳድነት ባሕርያትን ከአዳምና ከሔዋን በመውረሳችን ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ የራስ ወዳድነት ምኞትን በሚያራምድ ዓለም ውስጥ የምንኖር በመሆናችን ነው። (ኤፌሶን 4:17, 18) ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አስተሳሰብ ማዳበር ማለት አብሮን ከተወለደው ፍጽምና የጎደለው ባሕርይ ተቃራኒ የሆነ አስተሳሰብ ማዳበር ማለት ነው። ይህ ደግሞ ቁርጥ ያለ እርምጃ መውሰድንና ጥረት ማድረግን ይጠይቃል።
9 ኢየሱስ ከተወው ፍጹም ምሳሌ ተቃራኒ የሆነው አለፍጽምናችን አንዳንድ ጊዜ ተስፋ እንድንቆርጥ ሊያደርገን ይችላል። ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ መያዝ የሚቻል መሆኑ ፈጽሞ ሊያጠራጥረን ይችላል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ የተናገራቸውን የሚከተሉትን የሚያበረታቱ ቃላት ልብ በል:- “በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፣ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም። የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም። በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፣ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።” (ሮሜ 7:18, 19, 22, 23) እውነት ነው፣ ጳውሎስ ያለበት አለፍጽምና እርሱ የሚፈልገውን ያህል የአምላክን ፈቃድ እንዳያደርግ በተደጋጋሚ እንቅፋት ሆኖበታል። ይሁን እንጂ የነበረው አስተሳሰብ ማለትም ለይሖዋና ለሕጉ የነበረው አመለካከትና ስሜት ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ነው። የእኛም አስተሳሰብ እንዲህ ሊሆን ይችላል።
የተሳሳተን አስተሳሰብ ማስተካከል
10. ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች እንዲያዳብሩ ያበረታታቸው የትኛውን አስተሳሰብ ነው?
10 አንዳንዶች የተሳሳተ አስተሳሰባቸውን ማስተካከል ያስፈልጋቸው ይሆንን? አዎን። ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ላይ ታይቷል። ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ትክክለኛ አስተሳሰብ መያዝን በማስመልከት ተናግሯል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “[በመጀመሪያ ትንሣኤ አማካኝነት የሚገኘውን ሰማያዊ ሕይወት] አሁን እንዳገኘሁ ወይም አሁን ፍጹም እንደ ሆንሁ አይደለም፣ ነገር ግን ስለ እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ የተያዝሁበትን ያን ደግሞ እይዛለሁ ብዬ እፈጥናለሁ። ወንድሞች ሆይ፣ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ። እንግዲህ ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ።”—ፊልጵስዩስ 3:12-15፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
11, 12. ይሖዋ ትክክለኛ አስተሳሰብን የሚገልጥልን በምን መንገዶች ነው?
11 እድገት የማድረግን አስፈላጊነት የማይገነዘብ ክርስቲያን አስተሳሰቡ ትክክል እንዳልሆነ ከጳውሎስ ቃላት መገንዘብ ይቻላል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው የክርስቶስን አስተሳሰብ አላዳበረም ማለት ነው። (ዕብራውያን 4:11፤ 2 ጴጥሮስ 1:10፤ 3:14) ይሁን እንጂ ይህ ሰው ያለበት ሁኔታ ፈጽሞ ሊስተካከል አይችልም ማለት ነው? በጭራሽ። በእርግጥ ለውጥ ማድረግ የምንፈልግ ከሆነ አምላክ አስተሳሰባችንን እንድንቀይር ሊረዳን ይችላል። በመቀጠል ጳውሎስ “በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፣ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ [“ከላይ የተጠቀሰውን አስተሳሰብ፣” NW ] ይገልጥላችኋል” በማለት ተናግሯል።—ፊልጵስዩስ 3:15
12 ይሁን እንጂ ይሖዋ ትክክለኛውን አስተሳሰብ እንዲገልጥልን የምንፈልግ ከሆነ እኛም ድርሻችንን መወጣት ይገባናል። “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያወጣቸው ጽሑፎች በመታገዝ የአምላክን ቃል በጸሎት ማጥናት “ልዩ አሳብ” ያላቸው ሰዎች ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዲያዳብሩ ያስችላቸዋል። (ማቴዎስ 24:45) ‘የእግዚአብሔርን ጉባኤ እንዲጠብቁ’ በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙት ክርስቲያን ሽማግሌዎች እርዳታ ለመስጠት ዝግጁዎች ናቸው። (ሥራ 20:28) ይሖዋ አለፍጽምናችንን ግምት ውስጥ የሚያስገባና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ እርዳታ የሚሰጠን በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን! ይህን እርዳታ የምንቀበል እንሁን።
ከሌሎች መማር
13. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ከኢዮብ ዘገባ ስለ ትክክለኛ አስተሳሰብ ምን ትምህርት እናገኛለን?
13 ጳውሎስ ምሳሌ በሚሆኑ ጥንታዊ ታሪኮች ላይ ማሰላሰል አስተሳሰባችንን ለማስተካከል ሊረዳን እንደሚችል ሮሜ ምዕራፍ 15 ላይ ገልጿል። እንዲህ ሲል ጻፈ:- “በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል።” (ሮሜ 15:4) በጥንት ጊዜ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች በአስተሳሰባቸው ላይ አንድ ዓይነት ማስተካከያዎችን ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል ኢዮብ በጥቅሉ ሲታይ ጥሩ አስተሳሰብ ነበረው። በይሖዋ ላይ ክፉ ቃል አልወጣውም፤ እንዲሁም የደረሰበት ሥቃይ በይሖዋ ላይ የነበረውን ትምክህት አላናጋበትም። (ኢዮብ 1:8, 21, 22) ሆኖም ራሱን ጻድቅ አድርጎ ለማቅረብ ሞክሮ ነበር። ይሖዋ በኤሊሁ አማካኝነት ይህን ዝንባሌውን እንዲያስተካክል ረዳው። ኢዮብ በተሰጠው ምክር ቅር ከመሰኘት ይልቅ አስተሳሰቡን መለወጥ እንደሚያስፈልገው በትሕትና ተቀብሎ ወዲያው እርምጃ ወሰደ።—ኢዮብ 42:1-6
14. አስተሳሰባችንን በሚመለከት ምክር ቢሰጠን ኢዮብን ልንመስል የምንችለው እንዴት ነው?
14 አንድ ክርስቲያን ባልንጀራችን አስተሳሰባችንን እንድናስተካክል በደግነት ሐሳብ ቢያቀርብልን ኢዮብ ያሳየው ዓይነት ምላሽ እንሰጣለንን? ኢዮብ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ‘በእግዚአብሔር ላይ አናማርር።’ (ኢዮብ 1:22 የ1980 ትርጉም ) አግባብ ያልሆነ ነገር ቢደርስብን እንኳ ማማረር ወይም ለደረሰብን ችግር ተጠያቂው ይሖዋ እንደሆነ አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ የተሰጠን መብት ምንም ይሁን ምን “የማንጠቅም ባሪያዎች” መሆናችንን በማስታወስ ራሳችንን ጻድቅ አድርገን ለማቅረብ ከመሞከር መታቀብ ይኖርብናል።—ሉቃስ 17:10
15. (ሀ) አንዳንድ የኢየሱስ ተከታዮች ምን ዓይነት የተሳሳተ አስተሳሰብ አንጸባርቀዋል? (ለ) ጴጥሮስ ግሩም አስተሳሰብ እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?
15 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስን ያዳምጡት ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ትክክል ያልሆነ አስተሳሰብ አንጸባርቀዋል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ ነገር ተናገረ። “ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎች በሰሙ ጊዜ:- ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል? አሉ።” ይህን የተናገሩት ሰዎች አስተሳሰባቸው ትክክል እንዳልነበር ግልጽ ነው። የተዛባው አስተሳሰባቸው ኢየሱስን ከመስማት እንዲቆጠቡ አደረጋቸው። ዘገባው “ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም” ይላል። ሁሉም ይህ ዓይነቱ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነበራቸውን? በጭራሽ። ዘገባው እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ኢየሱስም ለአሥራ ሁለቱ:- እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን? አለ። ስምዖን ጴጥሮስ:- ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን?” አለው። ከዚያም ጴጥሮስ “አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” በማለት ራሱ ላነሳው ጥያቄ ራሱ መልስ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 6:60, 66-68) ይህ እንዴት ያለ ግሩም አስተሳሰብ ነው! አንድን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት በተመለከተ የተሰጠው ማብራሪያ ወይም የተደረገው ማስተካከያ መጀመሪያ ላይ ለመቀበል ቢከብደን የጴጥሮስ ዓይነት አስተሳሰብ ማሳየቱ የተሻለ አይሆንም? አንድ ትምህርት መጀመሪያ ላይ ስላልገባን ብቻ ይሖዋን ማገልገል ማቆም ወይም ‘ከጤናማ ቃል ምሳሌ’ ጋር የሚቃረን ነገር መናገር ምንኛ ሞኝነት ነው!—2 ጢሞቴዎስ 1:13
16. በኢየሱስ ዘመን የነበሩ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ምን ዓይነት የሚያስደነግጥ አስተሳሰብ አንጸባርቀዋል?
16 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች የኢየሱስን አስተሳሰብ ሳያንጸባርቁ ቀርተዋል። ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ባስነሳው ጊዜ እርሱን ለማዳመጥ ፈጽሞ የማይፈልጉ መሆናቸው በገሃድ ተረጋገጠ። ትክክለኛ አስተሳሰብ ላለው ማንኛውም ሰው ይህ ተዓምር ኢየሱስ ከአምላክ የተላከ መሆኑን የሚያሳይ ግልጽ ማረጋገጫ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ እናነባለን:- “እንግዲህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ሸንጎ ሰብስበው:- ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶች ያደርጋልና። እንዲሁ ብንተወው ሁሉ በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንን ወገናችንንም ይወስዳሉ አሉ።” ታዲያ የደረሱበት የመፍትሔ ሐሳብ ምን ነበር? “ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ።” ኢየሱስን ለመግደል ከማሴራቸውም በላይ ተዓምር ሠሪ መሆኑን የሚያረጋግጠውን ሕያው ማስረጃም ለማጥፋት ወሰኑ። “የካህናት አለቆችም አልዓዛርን ደግሞ ሊገድሉት ተማከሩ።” (ዮሐንስ 11:47, 48, 53፤ 12:9-11) እኛም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አስተሳሰብ ብናራምድና ሊያስደስተን በሚገባ ነገር ብንበሳጭ ወይም ብንናደድ ምንኛ አስከፊ ይሆናል! እጅግ አደገኛ እንደሆነ የተረጋገጠ ነው!
ክርስቶስ የነበረውን አዎንታዊ አስተሳሰብ መኮረጅ
17. (ሀ) ዳንኤል ድፍረት የሞላበት አስተሳሰብ ያሳየው በምን ሁኔታዎች ውስጥ እያለ ነው? (ለ) ኢየሱስ ድፍረት ያሳየው እንዴት ነበር?
17 የይሖዋ አገልጋዮች አዎንታዊ አስተሳሰብ ይዘው ይኖራሉ። የዳንኤል ጠላቶች ለ30 ቀናት ለንጉሡ ካልሆነ በስተቀር ለየትኛውም አምላክ ወይም ሰው ልመና ማቅረብን የሚከለክል ሕግ እንዲወጣ ባሴሩ ጊዜ ዳንኤል ይህ ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለውን ዝምድና እንደሚነካበት ተገነዘበ። ለ30 ቀናት ወደ አምላክ መጸለዩን ያቆም ይሆን? በጭራሽ። ልክ እንደ ልማዱ ያላንዳች ፍርሃት በቀን ሦስት ጊዜ ወደ ይሖዋ መጸለዩን ቀጠለ። (ዳንኤል 6:6-17) በተመሳሳይም ኢየሱስ ጠላቶቹን በመፍራት ወደኋላ አላለም። በአንድ ሰንበት ቀን እጁ ከሰለለች ከአንድ ሰው ጋር ተገናኘ። ኢየሱስ በሰንበት ቀን ቢፈውስ በቦታው ያሉትን አብዛኞቹን አይሁዳውያን እንደሚያበሳጫቸው ያውቅ ነበር። ስለዚህ በጉዳዩ ላይ ሐሳብ እንዲሰጡ ጥያቄ አቀረበላቸው። ለመመለስ ፈቃደኞች አለመሆናቸውን ባየ ጊዜ ኢየሱስ ወደ ሰውየው ቀረበና ፈወሰው። (ማርቆስ 3:1-6) ኢየሱስ ትክክል ነው ብሎ እስካመነበት ድረስ ተልእኮውን ከመፈጸም ፈጽሞ ወደኋላ አላለም።
18. አንዳንዶች የሚቃወሙን ለምንድን ነው? ይሁን እንጂ አፍራሽ አስተሳሰባቸውን መከላከል የሚኖርብን እንዴት ነው?
18 በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ከተቃዋሚዎች ሊሰነዘርባቸው በሚችለው መጥፎ ምላሽ መሸበር እንደሌለባቸው ያውቃሉ። አለዚያ የኢየሱስን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ አይችሉም። አንዳንዶች እውነታውን ባለመረዳታቸው ሌሎች ደግሞ ለምሥክሮቹ ወይም ለመልእክታቸው ካላቸው ጥላቻ የተነሳ ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን ይቃወማሉ። ይሁን እንጂ በጥላቻ የተሞላው አስተሳሰባቸው በእኛ አዎንታዊ አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ፈጽሞ መፍቀድ አይኖርብንም። በአምልኳችን ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩብን ፈጽሞ መፍቀድ አይኖርብንም።
19. የኢየሱስ ክርስቶስን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?
19 ኢየሱስ እንዲህ ማድረግ ምንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆንበትም እንኳ ለተከታዮቹም ሆነ ለይሖዋ ዝግጅት አዎንታዊ አስተሳሰብ አንጸባርቋል። (ማቴዎስ 23:2, 3) እኛም ምሳሌውን መኮረጅ ይኖርብናል። ወንድሞቻችን ፍጹማን እንዳልሆኑ አይካድም። ይሁን እንጂ እኛም ብንሆን ፍጹማን አይደለንም። በተጨማሪም ከዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ውጭ የተሻሉ አጋሮችንና እጅግ ታማኝ የሆኑ ወዳጆችን የት ልናገኝ እንችላለን? ይሖዋ በጽሑፍ የሰፈረውን የቃሉን ትርጉም ሙሉ በሙሉ አልገለጠልንም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን ከእኛ በተሻለ መንገድ መረዳት የቻለ የሃይማኖት ቡድን አለ? ስለዚህ ሁልጊዜ ትክክለኛው አስተሳሰብ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ ይኑረን። ይህም በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው ይሖዋን እንዴት በትዕግሥት መጠበቅ እንዳለብን ማወቅንም ይጨምራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመው እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለው መጽሐፍ ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ያብራራል።
ልታብራራ ትችላለህ?
• አስተሳሰባችን በአኗኗራችን ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት ነው?
• የኢየሱስ ክርስቶስን አስተሳሰብ ግለጽ።
• ከኢዮብ አስተሳሰብ ምን ልንማር እንችላለን?
• ተቃውሞ በሚገጥመን ጊዜ ሊኖረን የሚገባው ትክክለኛ አስተሳሰብ ምንድን ነው?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትክክለኛ አስተሳሰብ ያለው አንድ ክርስቲያን ሌሎችን ለመርዳት ይጣጣራል
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክን ቃል በጸሎት ማጥናት የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖረን ይረዳናል