የጥናት ርዕስ 32
ፍቅራችሁ እየጨመረ ይሂድ
“ፍቅራችሁ . . . ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲሄድ መጸለዬን እቀጥላለሁ።”—ፊልጵ. 1:9
መዝሙር 106 ፍቅርን ማዳበር
የትምህርቱ ዓላማa
1. የፊልጵስዩስን ጉባኤ ያቋቋሙት እነማን ናቸው?
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሲላስ፣ ሉቃስና ጢሞቴዎስ በፊልጵስዩስ ከተማ የመንግሥቱን መልእክት ለማዳመጥ ፈቃደኛ የሆኑ በርካታ ሰዎችን አግኝተው ነበር። እነዚህ አራት ቀናተኛ ወንድሞች በዚህች ከተማ ጉባኤ እንዲቋቋም አደረጉ፤ ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ አንድ ላይ መሰብሰብ የጀመሩ ሲሆን የሚሰበሰቡትም ሊዲያ በተባለች እንግዳ ተቀባይ የሆነች ክርስቲያን ቤት ሳይሆን አይቀርም።—ሥራ 16:40
2. ጉባኤው ምን አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጠመው?
2 ብዙም ሳይቆይ ግን አዲስ የተቋቋመው ጉባኤ አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጠመው። ሰይጣን የእውነት ጠላቶችን በማነሳሳት፣ እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች የሚያከናውኑት የስብከት ሥራ ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲገጥመው አደረገ። ጳውሎስና ሲላስ ተይዘው በበትር ከተደበደቡ በኋላ እስር ቤት ተጣሉ። በኋላም ከእስር ሲፈቱ አዲሶቹን ደቀ መዛሙርት በመጎብኘት አበረታቷቸው። ከዚያም ጳውሎስ፣ ሲላስና ጢሞቴዎስ ከተማዋን ለቀው ሄዱ፤ ሉቃስ ግን እዚያው የቀረ ይመስላል። ታዲያ አዲሱ ጉባኤ እንዴት ሆነ? አዲሶቹ አማኞች በይሖዋ መንፈስ እርዳታ እሱን በቅንዓት ማገልገላቸውን ቀጠሉ። (ፊልጵ. 2:12) በእርግጥም ጳውሎስ በእነሱ ለመኩራት የሚያበቃ ምክንያት ነበረው!
3. በፊልጵስዩስ 1:9-11 ላይ እንደተገለጸው ጳውሎስ ስለ የትኞቹ ጉዳዮች ጸልዮአል?
3 ከአሥር ዓመት ገደማ በኋላ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለሚገኘው ጉባኤ ደብዳቤ ጻፈ። ይህን ደብዳቤ ስታነብ ጳውሎስ ለወንድሞቹ የነበረውን ጥልቅ ፍቅር ማስተዋልህ አይቀርም። ጳውሎስ “ክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ዓይነት ጥልቅ ፍቅር እናንተ ሁላችሁም በጣም [ትናፍቁኛላችሁ]” ብሏቸዋል። (ፊልጵ. 1:8) ስለ እነሱ እንደሚጸልይም በደብዳቤው ላይ ነግሯቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ፍቅራቸው እየጨመረ እንዲሄድ፣ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይተው እንዲያውቁ፣ እንከን የማይገኝባቸው እንዲሆኑ፣ ሌሎችን እንዳያሰናክሉ እንዲሁም የጽድቅ ፍሬ ማፍራታቸውን እንዲቀጥሉ ጳውሎስ ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። ጳውሎስ የጻፈው ከልብ የመነጨ ሐሳብ በዛሬው ጊዜም እንደሚጠቅመን ጥያቄ የለውም። እስቲ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ምን እንደጻፈ እናንብብ። (ፊልጵስዩስ 1:9-11ን አንብብ።) ከዚያም የሰጣቸውን ምክሮች ብሎም እነዚህን ምክሮች እንዴት ተግባራዊ ልናደርግ እንደምንችል እንመለከታለን።
ፍቅራችሁ እየጨመረ ይሂድ
4. (ሀ) በ1 ዮሐንስ 4:9, 10 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) አምላክን ምን ያህል ልንወደው ይገባል?
4 ይሖዋ፣ ልጁ ወደ ምድር መጥቶ ለእኛ ኃጢአት ሲል እንዲሞት በማድረግ ታላቅ ፍቅሩን አሳይቶናል። (1 ዮሐንስ 4:9, 10ን አንብብ።) አምላክ ያሳየው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እኛም እሱን እንድንወደው ያነሳሳናል። (ሮም 5:8) አምላክን ምን ያህል ልንወደው ይገባል? ኢየሱስ ለአንድ ፈሪሳዊ የተናገረው ሐሳብ መልሱን ይሰጠናል፤ ኢየሱስ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ” ብሏል። (ማቴ. 22:36, 37) አምላክን የምንወደው በተከፈለ ልብ መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ ለእሱ ያለን ፍቅር በየቀኑ እየጨመረ እንዲሄድ እንፈልጋለን። ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖችን ‘ፍቅራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ’ ሊሄድ እንደሚገባ ነግሯቸዋል። እኛስ ለአምላክ ያለን ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ምን ማድረግ እንችላለን?
5. ፍቅራችን እያደገ እንዲሄድ የሚረዳን ምንድን ነው?
5 አምላክን ለመውደድ እሱን ማወቅ ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር የማያሳይ አምላክን አያውቅም፤ ምክንያቱም አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። (1 ዮሐ. 4:8) ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ አምላክ “ትክክለኛ እውቀትና ጥልቅ ግንዛቤ” ባገኘን መጠን ለእሱ ያለን ፍቅር ይበልጥ እያደገ እንደሚሄድ ተናግሯል። (ፊልጵ. 1:9) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በጀመርንበት ወቅት ስለ አምላክ ግሩም ባሕርያት ያገኘነው ውስን እውቀት እሱን እንድወደው አድርጎናል። ስለ ይሖዋ ይበልጥ እየተማርን ስንሄድ ደግሞ ለእሱ ያለን ፍቅር ይበልጥ እየጨመረ መጥቷል። ከዚህ አንጻር፣ ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በአምላክ ቃል ላይ ማሰላሰል በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ነገር መሆኑ የሚያስገርም አይደለም!—ፊልጵ. 2:16
6. ፍቅራችን እየጨመረ እንዲሄድ ማድረግ የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ ከ1 ዮሐንስ 4:11, 20, 21 ምን እንማራለን?
6 አምላክ ያሳየን ታላቅ ፍቅር ወንድሞቻችንን እንድንወድ ያነሳሳናል። (1 ዮሐንስ 4:11, 20, 21ን አንብብ።) ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መውደድ ያን ያህል ጥረት የሚጠይቅብን ነገር እንዳልሆነ ይሰማን ይሆናል። ደግሞስ ሁላችንም ይሖዋን ለማምለክና ግሩም ባሕርያቱን ለመምሰል ጥረት እናደርግ የለ? በተጨማሪም ሕይወቱን ለእኛ እስከ መስጠት የሚያደርስ ታላቅ ፍቅር ያሳየንን የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን። ይሁን እንጂ እርስ በርስ እንድንዋደድ የተሰጠንን ትእዛዝ ማክበር አንዳንድ ጊዜ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። በፊልጵስዩስ ጉባኤ ውስጥ የተከሰተ አንድ ሁኔታ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል።
7. ጳውሎስ ለኤዎድያን እና ለሲንጤኪ ከሰጠው ምክር ምን ትምህርት እናገኛለን?
7 ኤዎድያን እና ሲንጤኪ ከሐዋርያው ጳውሎስ ‘ጎን ተሰልፈው’ በቅንዓት ያገለገሉ እህቶች ናቸው። ሆኖም እነዚህ እህቶች በመካከላቸው በተፈጠረ ቅራኔ የተነሳ ተራርቀው የነበረ ይመስላል። ጳውሎስ እነዚህ እህቶች ለነበሩበት ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ኤዎድያንን እና ሲንጤኪን በስም ጠቅሶ “አንድ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖራቸው” ቀጥተኛ ምክር ሰጥቷቸዋል። (ፊልጵ. 4:2, 3) ጳውሎስ ለመላው ጉባኤም “ምንጊዜም ማንኛውንም ነገር ሳታጉረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ” የሚል ምክር መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶታል። (ፊልጵ. 2:14) ጳውሎስ የሰጠው ግልጽ ምክር፣ እነዚያ ታማኝ እህቶች ብቻ ሳይሆኑ የጉባኤው አባላት በሙሉ በመካከላቸው ያለውን ፍቅር እንዲያጠናክሩ ረድቷቸው መሆን አለበት።
8. ወንድሞቻችንን መውደድ አስቸጋሪ እንዲሆንብን የሚያደርገው ዋነኛው ነገር ምንድን ነው? ይህን ዝንባሌ ለማሸነፍ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
8 እንደ ኤዎድያን እና ሲንጤኪ ሁሉ እኛም ለሌሎች ፍቅር ማዳበር ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርገው ዋነኛው ነገር በድክመታቸው ላይ ትኩረት ማድረጋችን ሊሆን ይችላል። ሁላችንም በየዕለቱ ስህተት እንሠራለን። በወንድሞቻችን ስህተት ላይ ካተኮርን ለእነሱ ያለን ፍቅር እየቀዘቀዘ ይሄዳል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድም አብሮን የስብሰባ አዳራሹን ከማጽዳት ይልቅ ሌላ ነገር ሲሠራ ብናየው እንበሳጭ ይሆናል። ይህ ወንድም የሠራቸውን ሌሎች ስህተቶች መቁጠር ብንጀምር ይበልጥ እየተበሳጨን ስለምንሄድ ለእሱ ያለን ፍቅር ይቀንሳል። አንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ የሚከተለውን እውነታ ማሰብህ ጠቃሚ ነው፦ ይሖዋ የእኛንም ሆነ የወንድማችንን ድክመት ያውቃል። ድክመታችንን እያወቀም እንኳ እኛንም ሆነ ወንድማችንን ይወደናል። ስለዚህ እኛም የይሖዋን ምሳሌ በመከተል ፍቅር ማሳየትና ለወንድሞቻችን አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ይኖርብናል። ወንድሞቻችንን ለመውደድ ልባዊ ጥረት ስናደርግ በመካከላችን ያለው አንድነት ይጠናከራል።—ፊልጵ. 2:1, 2
‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች’
9. ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች’ ካላቸው መካከል አንዳንዶቹን ጥቀስ።
9 ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በጻፈው ደብዳቤ ላይ በፊልጵስዩስ የነበሩትን ጨምሮ ለሁሉም ክርስቲያኖች “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ፊልጵ. 1:10) አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ከተባሉት መካከል የይሖዋ ስም መቀደስ፣ የዓላማው መፈጸም እንዲሁም የጉባኤው ሰላምና አንድነት ይገኙበታል። (ማቴ. 6:9, 10፤ ዮሐ. 13:35) ሕይወታችን በዋነኝነት ያተኮረው በእነዚህ አስፈላጊ ነገሮች ላይ ከሆነ ይሖዋን እንደምንወደው እያሳየን ነው።
10. ይሖዋ እንከን የማይገኝብን እንደሆንን አድርጎ እንዲመለከተን ምን ማድረግ አለብን?
10 ጳውሎስ ‘እንከን የማይገኝብን እንድንሆንም’ መክሮናል። ይህ ሲባል ፍጹም መሆን አለብን ማለት አይደለም። የይሖዋ አምላክን ያህል እንከን የለሽ መሆን እንደማንችል የታወቀ ነው። ሆኖም ፍቅራችን እየጨመረ እንዲሄድ የተቻለንን ሁሉ የምናደርግና ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይተን የምናውቅ ከሆነ ይሖዋ እንከን የማይገኝብን እንደሆንን አድርጎ ይመለከተናል። ፍቅራችንን ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ደግሞ ሌሎችን ላለማሰናከል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ነው።
11. ሌሎችን ላለማሰናከል መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው?
11 “ሌሎችን እንዳታሰናክሉ” የሚለው ምክር በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ማሳሰቢያ ነው። ለመሆኑ ሌሎችን ልናሰናክል የምንችለው እንዴት ነው? የመዝናኛ ምርጫችን፣ አለባበሳችን ሌላው ቀርቶ ሰብዓዊ ሥራችን እንኳ ሌሎችን ሊያሰናክል ይችላል። የምናደርገው ነገር በራሱ ስህተት ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የምናደርገው ምርጫ የሌላን ሰው ሕሊና የሚረብሽና ግለሰቡ እንዲሰናከል የሚያደርግ ከሆነ ጉዳዩን አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። ኢየሱስ ከበጎቹ መካከል አንዱን ከምናሰናክል፣ የወፍጮ ድንጋይ በአንገታችን ታስሮ ባሕር ውስጥ ብንጣል እንደሚሻለን ተናግሯል!—ማቴ. 18:6
12. አቅኚ የሆኑ አንድ ባልና ሚስት ከተዉት ምሳሌ ምን እንማራለን?
12 አቅኚ የሆኑ አንድ ባልና ሚስት የኢየሱስን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ያደረጉት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። እነዚህ አቅኚዎች ባሉበት ጉባኤ ውስጥ በቅርቡ የተጠመቁ አንድ ባልና ሚስት አሉ። እነዚህ ባልና ሚስት ያደጉት ጥብቅ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ስለሆነ ክርስቲያኖች ጤናማ የሚባል ፊልም ለማየትም እንኳ ሲኒማ ቤት መግባታቸው ስህተት እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። በመሆኑም አቅኚዎቹ ባልና ሚስት ሲኒማ ቤት እንደገቡ ሲያውቁ ደነገጡ። አቅኚዎቹ ባልና ሚስት ይህን ሲገነዘቡ አዲሶቹ ክርስቲያኖች ሕሊናቸውን በማሠልጠን ሚዛናዊ አመለካከት እስኪያዳብሩ ድረስ ሲኒማ ቤት ላለመግባት ወሰኑ። (ዕብ. 5:14) እነዚህ አቅኚዎች እንዲህ ያለ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ እርምጃ በመውሰድ፣ በቅርብ የተጠመቁትን ባልና ሚስት በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም እንደሚወዷቸው አሳይተዋል።—ሮም 14:19-21፤ 1 ዮሐ. 3:18
13. አንድን ሰው ወደ ኃጢአት የሚመራው ነገር ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው?
13 ለሌሎች ማሰናከያ የምንሆንበት ሌላም አቅጣጫ አለ፤ ይህም ወደ ኃጢአት ሊመራቸው የሚችል ነገር ማድረግ ነው። ለመሆኑ እንዲህ ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው? አንድ ምሳሌ እንውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠና አንድ ሰው፣ ለረጅም ጊዜ ከባድ ትግል ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ከመጠጥ ሱስ መላቀቅ ቻለ። ይህ ሰው ሱሱ እንዳያገረሽበት ሲል ሙሉ በሙሉ ከመጠጥ ለመራቅ ወሰነ። ከዚያም ፈጣን እድገት አድርጎ ተጠመቀ። አንድ ቀን አንድ ወንድም ጋበዘውና መጠጥ እንዲጠጣ ለማበረታታት በቅንነት እንዲህ አለው፦ “አሁን’ኮ ክርስቲያን ስለሆንክ የይሖዋ መንፈስ አለህ። ከመንፈስ ቅዱስ ገጽታዎች አንዱ ደግሞ ራስን መግዛት ነው። ራስን መግዛትን ካዳበርክ በልኩ መጠጣት ሊያስፈራህ አይገባም።” ይህ አዲስ ወንድም እንዲህ ያለውን የተሳሳተ ምክር ቢቀበል ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም!
14. ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በፊልጵስዩስ 1:10 ላይ የሚገኙትን ምክሮች ተግባራዊ እንድናደርግ የሚረዱን እንዴት ነው?
14 ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በፊልጵስዩስ 1:10 ላይ የሚገኙትን ምክሮች ተግባራዊ እንድናደርግ በተለያዩ መንገዶች ይረዱናል። አንደኛ፣ በዚያ የሚቀርብልን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ይሖዋ ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ አድርጎ የሚመለከተውን ነገር እንድናስታውስ ይረዳናል። ሁለተኛ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል መማራችን እንከን የማይገኝብን ለመሆን ያስችለናል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ስብሰባዎች “ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች” ያነቃቁናል። (ዕብ. 10:24, 25) በየጊዜው ከወንድሞቻችን የምናገኘው ማበረታቻ ለአምላካችንና ለእምነት ባልንጀሮቻችን ያለን ፍቅር ይበልጥ እየጨመረ እንዲሄድ ያደርጋል። ልባችን ለአምላክና ለወንድሞቻችን ባለን ፍቅር ሲሞላ ደግሞ እነሱን ላለማሰናከል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን።
“የተትረፈረፈ የጽድቅ ፍሬ” ማፍራታችሁን ቀጥሉ
15. ‘የተትረፈረፈ የጽድቅ ፍሬ ማፍራት’ ሲባል ምን ማለት ነው?
15 የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች “የተትረፈረፈ የጽድቅ ፍሬ” እንዲያፈሩ ጳውሎስ አጥብቆ ጸልዮአል። (ፊልጵ. 1:11) እዚህ ላይ “የጽድቅ ፍሬ” የተባለው ነገር ለይሖዋና ለሕዝቡ ያላቸውን ፍቅር እንደሚጨምር ግልጽ ነው። ከዚህም ሌላ በኢየሱስ ላይ ስላላቸው እምነትና አስደናቂ ስለሆነው ተስፋቸው ለሌሎች መናገርን ይጨምራል። በፊልጵስዩስ 2:15 ላይ ደግሞ ጳውሎስ ሌላ ምሳሌ ተጠቅሟል፤ ክርስቲያኖች “በዚህ ዓለም ውስጥ እንደ ብርሃን አብሪዎች” እንደሚያበሩ ተናግሯል። ይህ ተስማሚ ምሳሌ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “የዓለም ብርሃን ናችሁ” ብሏቸው ነበር። (ማቴ. 5:14-16) በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ሌሎችን ‘ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ’ ተከታዮቹን ያዘዛቸው ሲሆን “እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 28:18-20፤ ሥራ 1:8) በጣም አስፈላጊ በሆነው በዚህ ሥራ በትጋት ስንካፈል “የጽድቅ ፍሬ” እናፈራለን።
16. ፊልጵስዩስ 1:12-14 አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥርም እንኳ እንደ ብርሃን አብሪዎች ማብራት እንደምንችል የሚያሳየው እንዴት ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)
16 ምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን እንደ ብርሃን አብሪዎች ማብራት እንችላለን። አንዳንድ ጊዜ፣ ምሥራቹን እንዳናውጅ እንቅፋት እንደሆነ የሚሰማን ነገር ለመስበክ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ይከፍት ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት ሮም ውስጥ የቁም እስረኛ ነበር። ይሁን እንጂ እስረኛ መሆኑ፣ ለጠባቂዎቹና ሊጠይቁት ለሚመጡ ሰዎች እንዳይሰብክ አላገደውም። ጳውሎስ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ በቅንዓት ሰብኳል፤ ይህም ወንድሞች “የአምላክን ቃል ያለፍርሃት ለመናገር” የሚያስችል የልበ ሙሉነት ስሜትና ድፍረት እንዲኖራቸው አድርጓል።—ፊልጵስዩስ 1:12-14ን አንብብ፤ 4:22
17. አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ፍሬ ማፍራት እንደሚቻል የሚያሳይ ዘመናዊ ምሳሌ ተናገር።
17 በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሐዋርያው ጳውሎስ የተወዉን የድፍረት ምሳሌ እየተከተሉ ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች የሚኖሩት በይፋ ወይም ከቤት ወደ ቤት መስበክ በማይቻልባቸው አገሮች በመሆኑ ምሥራቹን ለመስበክ ሌሎች ዘዴዎችን መጠቀም አስፈልጓቸዋል። (ማቴ. 10:16-20) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ባለበት አንድ አገር ውስጥ የሚያገለግል የወረዳ የበላይ ተመልካች፣ አስፋፊዎቹ ሊሰብኩ የሚችሉበት የየራሳቸው የአገልግሎት ክልል እንዳላቸው ይኸውም ለዘመዶቻቸው፣ ለጎረቤቶቻቸው፣ አብረዋቸው ለሚማሩና ለሚሠሩ ሰዎች እንዲሁም ለሚያውቋቸው ሌሎች ሰዎች መስበክ እንደሚችሉ ሐሳብ ሰጣቸው። በሁለት ዓመት ውስጥ፣ በዚያ ወረዳ ያሉ ጉባኤዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ። እኛ የምንኖረው ምሥራቹን በነፃነት መስበክ በታገደበት አገር ውስጥ ላይሆን ይችላል። ያም ቢሆን ብልህ ከሆኑት ከእነዚህ ወንድሞችና እህቶች የምንማረው ጠቃሚ ትምህርት አለ፦ ይሖዋ ማንኛውንም እንቅፋት ለመወጣት የሚያስችል ኃይል እንደሚሰጠን በመተማመን፣ በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ምንጊዜም እንፈልግ።—ፊልጵ. 2:13
18. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?
18 ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በዛሬው ጊዜ፣ ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የሚገኙትን ምክሮች በተግባር ለማዋል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይተን ለማወቅ፣ እንከን የማይገኝብን ለመሆን፣ ሌሎችን ላለማሰናከል እንዲሁም የጽድቅ ፍሬ ለማፍራት ጥረት እናድርግ። እንዲህ ካደረግን ፍቅራችን እየጨመረ ይሄዳል፤ እንዲሁም አፍቃሪ የሆነውን አባታችንን ይሖዋን እናስከብራለን።
መዝሙር 17 “እፈልጋለሁ”
a ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ ለወንድሞቻችን ያለንን ፍቅር ማጠናከር ያስፈልገናል። ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የተጻፈው ደብዳቤ፣ ተፈታታኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንኳ ፍቅራችን እየጨመረ እንዲሄድ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል።
b የሥዕሉ መግለጫ፦ ወንድሞች የስብሰባ አዳራሹን ሲያጸዱ ጆ የተባለው ወንድም ሥራውን ትቶ ከአንድ ወንድምና ከልጁ ጋር ማውራት ጀመረ። ምንጣፉን እያጸዳ ያለው ማይክ በዚህ ተበሳጨ። በመሆኑም ‘ቆሞ ማውራቱን ትቶ ሥራውን አይሠራም!’ ብሎ አሰበ። በኋላ ላይ ግን ጆ አንዲትን በዕድሜ የገፉ እህት በአሳቢነት ሲረዳቸው ማይክ ተመለከተ። ማይክ ይህን ሲመለከት፣ በወንድሙ ጥሩ ባሕርያት ላይ ይበልጥ ማተኮር እንዳለበት አስታወሰ።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ ምሥራቹን በነፃነት መስበክ በማይቻልበት አገር ውስጥ የሚኖር አንድ ወንድም ለአንድ የሚያውቀው ሰው የመንግሥቱን መልእክት በዘዴ ሲመሠክር። በኋላ ላይ ደግሞ በሥራ ቦታው በእረፍት ሰዓቱ ላይ ለሥራ ባልደረባው ሲመሠክር ይታያል።