ራስህን ከልክ በላይ አታስጨንቅ
“ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።” (ማቴዎስ 6:34) ሩጫና ውጥረት በበዛበት በዛሬው ኅብረተሰብ ውስጥ ስንኖር ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው ይህ ምክር ለሁላችንም ተግባራዊ ጥቅም ይሰጣል።
ይሁን እንጂ ችግሮች፣ ውሳኔዎች፣ ግዴታዎችና ኃላፊነቶች እያሉብን ከጭንቀት ነፃ ልንሆን እንችላለን? በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በጭንቀትና በውጥረት ተውጠው ይንገላታሉ። ሥቃይ የሚያስታግሱና እንቅልፍ የሚያስወስዱ መድኃኒቶች ብዙ ሚልዮን ዶላር የሚታፈስበት ንግድ የሆኑት አለ ምክንያት አይደለም።
ገደቡ የት ላይ ነው?
ያሉብን ግዴታዎች፣ ሥራዎች፣ ውሳኔዎችና ችግሮች አጣዳፊ ሆኑም አልሆኑ አስቀድመን እቅድ ማውጣትና መዘጋጀት ይኖርብናል። አንድን ሥራ ወይም ፕሮጀክት ከመጀመራችን በፊት ‘ተቀምጠን ኪሳራችንን’ እንድናሰላ መጽሐፍ ቅዱስ ያበረታታናል። (ሉቃስ 14:28-30) ይህም ያሉትን አማራጮች በጥንቃቄ ማመዛዘንን፣ ሊከሰቱ ስለሚችሉ ውጤቶች ከወዲሁ ማሰብን እንዲሁም ከጊዜ፣ ከጉልበትና ከገንዘብ አንጻር አስቀድሞ ወጪውን ማስላትን ይጨምራል።
አንድ ሰው ሊከሰቱ ስለሚችሉ ነገሮች አስቀድሞ በጥንቃቄ ማሰቡ ተገቢ ቢሆንም ሊፈጠር ስለሚችለው ስለ እያንዳንዱ ጥቃቅን ነገር ለማሰብ መሞከር ግን ያዳግታል፤ ደግሞም ጠቃሚ አይደለም። ለምሳሌ ያህል ለቤተሰብህ ደህንነት ካለህ አሳቢነት የተነሳ በመኖሪያ ቤትህ ውስጥ እሳት ቢነሳ ምን ሊደረግ እንደሚቻል ታስብ ይሆናል። እሳት መነሳቱን የሚጠቁም መሣሪያና እሳት ማጥፊያ መሣሪያ ትገዛና ታስቀምጣለህ። በየት በኩል ማምለጥ እንደሚቻል አስቀድመህ ልትወስንና በዚያ መሠረት ልምምድ ልታደርጉ ትችላላችሁ። ይሁን እንጂ ማስተዋል የታከለበት ተግባራዊ እቅድ ማውጣት መጠኑንና ገደቡን ወዳለፈ ጭንቀት ተለውጧል የሚባለው መቼ ነው? አእምሮህ ገና ለገና ሊከሰቱ ይችላሉ ብለህ በምታስባቸው ግምታዊ ሐሳቦች ላይ ማውጠንጠን ሲጀምር ያን ጊዜ መጨነቅ ጀምረሃል ማለት ነው። አንድ ልታደርገው የሚገባ ነገር እንዳለ ወይም ቤተሰብህን ከአደጋ ለመጠበቅ የወሰድከው እርምጃ በቂ እንዳልሆነ የሚሰማህ ስሜት እረፍት ሊነሳህ ይችላል። እነዚህ ራስህ የምትፈጥራቸው ጭንቀቶች እንቅልፍ ሊያሳጡህ ይችላሉ።
ሙሴ በፈርዖን ፊት በቀረበ ጊዜ
ይሖዋ አምላክ ነቢይ አድርጎ ለሾመው ለሙሴ ከባድ የሥራ ኃላፊነት ሰጥቶት ነበር። በመጀመሪያ ሙሴ ወደ እስራኤላውያን ዘንድ ሄዶ እነርሱን ከግብፅ መርቶ ለማውጣት ይሖዋ የሾመው መሆኑን ማሳመን ነበረበት። ከዚያም ሙሴ በፈርዖን ፊት ቀርቦ እስራኤላውያንን እንዲለቅ መጠየቅ ነበረበት። በመጨረሻም ሙሴ በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ በምድረ በዳ መምራትና ጠላት ሕዝቦች ይኖሩበት ወደነበረው ምድር ማስገባት ነበረበት። (ዘጸአት 3:1-10) ይህ በጣም የሚያስፈራ ኃላፊነት ቢሆንም ሙሴ አላስፈላጊ በሆነ ጭንቀት ተውጦ ነበርን?
ሙሴ በርካታ አሳሳቢ ጥያቄዎች ወደ አእምሮው መጥተው እንደነበር ግልጽ ነው። “እነሆ፣ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ:- የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ ባልሁም ጊዜ:- ስሙስ ማን ነው? ባሉኝ ጊዜ፣ ምን እላቸዋለሁ?” በማለት ይሖዋን ጠይቋል። (ዘጸአት 3:13, 14) በተጨማሪም ሙሴ፣ ፈርዖን ባያምነው ምን እንደሚያደርግ አሳስቦት ነበር። አሁንም ይሖዋ ለነቢዩ ምላሽ ሰጥቶታል። ሌላው የመጨረሻው የሙሴ ችግር “አፈ ትብ” አለመሆኑ ነበር። ይህ ችግር ምን መፍትሄ ሊኖረው ይችላል? እንደ ሙሴ ሆኖ እንዲናገር ይሖዋ አሮንን ሰጠው።—ዘጸአት 4:1-5, 10-16
ሙሴ ለጥያቄዎቹ በተሰጠው መልስ መሠረት በመዘጋጀትና በአምላክ ላይ በመታመን ይሖዋ እንዳዘዘው ማድረግ ጀመረ። በፈርዖን ፊት በሚቀርብበት ጊዜ ምን ነገር ሊፈጠር እንደሚችል በማሰብ አእምሮውን ከማስጨነቅ ይልቅ ሙሴ እንደተባለው ‘እንዲሁ አደረገ።’ (ዘጸአት 7:6) ሙሴ ራሱን ከልክ በላይ አስጨንቆ ቢሆን ኖሮ እምነቱ ሊዳከምና የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ድፍረት ሊያጣ ይችል ነበር።
ሙሴ የተሰጠውን ኃላፊነት አጥጋቢ በሆነ መንገድ ለመወጣት እንዲችል የተጠቀመበት ሚዛኑን የጠበቀ አካሄድ ሐዋርያው ጳውሎስ “ጤናማ አእምሮ” ብሎ ለጠቀሰው ነገር ምሳሌ የሚሆን ነው። (2 ጢሞቴዎስ 1:7፤ ቲቶ 2:2-6 NW) ሙሴ ጤናማ አእምሮ ባይኖረው ኖሮ በተሰጠው ከባድ ኃላፊነት የተነሳ ከልክ በላይ ሊጨነቅና እስከ ጭራሹም ኃላፊነቱን አልቀበልም እስከማለት ሊደርስ ይችል ነበር።
ሐሳብህን ተቆጣጠር
በዕለታዊ ሕይወትህ ውስጥ የእምነት ፈተና ወይም መከራ ሲደርስብህ ምን ታደርጋለህ? ከፊትህ የተደቀኑትን እንቅፋቶች ወይም ተፈታታኝ ሁኔታዎች በማሰብ ብቻ በፍርሃት ትዋጣለህ? ወይስ ሚዛናዊ አመለካከት ትይዛለህ? አንዳንዶች እንደሚሉት ‘ገና ድልድዩ ጋ ሳትደርስ አትሻገር።’ ምናባዊውንም ድልድይ መሻገር አስፈላጊ ላይሆን ይችላል! ታዲያ ገና ይሆናል በሚል ፍራቻ ለምን በጭንቀት ትሠቃያለህ? መጽሐፍ ቅዱስ “ሰውን የልቡ ኃዘን [“ጭንቀት፣” NW] ያዋርደዋል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 12:25) ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው ውሳኔ ከማድረግ ይልቅ ዛሬ ነገ እያለ አንድን ጉዳይ ማጓተቱ ወደ ባሰ ችግር ውስጥ እንዲገባ ሊያደርገው ይችላል።
ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ አላስፈላጊ ጭንቀት መንፈሳዊ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ ነው። ሀብት ያለው የማታለል ኃይልና “የዚህ ዓለም አሳብ [“ጭንቀት፣” NW] ‘ለመንግሥቱ ቃል’ ያለንን አድናቆት ሙሉ በሙሉ ሊያንቀው እንደሚችል ኢየሱስ ክርስቶስ አመልክቷል። (ማቴዎስ 13:19, 22) እሾኽ ቡቃያው አድጎ እንዳያፈራ እንደሚያደርግ ሁሉ ከልክ በላይ መጨነቅም መንፈሳዊ እድገት እንዳናደርግና ለአምላክ ክብር በሚያመጣ መንገድ ፍሬ እንዳናፈራ ሊያግደን ይችላል። እንዲያውም አንዳንዶች ራሳቸው የፈጠሩት አፍራሽ የሆነ ጭንቀት ራሳቸውን ለይሖዋ እንዳይወስኑ አድርጓቸዋል። ‘ራሴን ስወስን ከገባሁበት ቃል ጋር ተስማምቶ መኖር ቢያቅተኝስ?’ ብለው ይፈራሉ።
ሐዋርያው ጳውሎስ በምናደርገው መንፈሳዊ ውጊያ ‘አእምሮን ሁሉ ማርከን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እንድናደርግ’ ነግሮናል። (2 ቆሮንቶስ 10:5) ቀንደኛ ጠላታችን የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ በሚያስጨንቁን ነገሮች ተጠቅሞ እኛን ተስፋ ለማስቆረጥና በአካላዊ፣ በስሜታዊና በመንፈሳዊ እኛን ለማዳከም ከፍተኛ ፍላጎት አለው። ሰይጣን የመወላወል ዝንባሌ ያላቸውን ዝንጉ ሰዎች እንዴት ወጥመድ ውስጥ ማስገባት እንደሚችል በሚገባ ያውቃል። ጳውሎስ “ለዲያብሎስ ፈንታ አትስጡ” በማለት ክርስቲያኖችን ያስጠነቀቀውም ለዚህ ነው። (ኤፌሶን 4:27) ሰይጣን “የዚህ ዓለም አምላክ” እንደመሆኑ መጠን ‘የማያምኑትን ሰዎች አሳብ በማሳወር’ በኩል ተሳክቶለታል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) የእኛንም አሳብ እንዲቆጣጠር ፈጽሞ መፍቀድ አይኖርብንም!
እርዳታ ማግኘት ይቻላል
አንድ ልጅ ችግር ሲያጋጥመው ወደሚያፈቅረው አባቱ ዘንድ በመሄድ መመሪያና ማጽናኛ ሊያገኝ ይችላል። በተመሳሳይም እኛ ችግሮቻችንን ይዘን ወደ ሰማያዊው አባታችን ወደ ይሖዋ ልንሄድ እንችላለን። እንዲያውም ይሖዋ ሸክማችንንና ጭንቀታችንን በእርሱ ላይ እንድንጥል ግብዣ አቅርቦልናል። (መዝሙር 55:22) አንድ ልጅ አባቱ አንድ ጊዜ ዋስትና ከሰጠው በኋላ በገጠመው ችግር ዳግመኛ እንደማይጨነቅ ሁሉ እኛም ሸክማችንን ሁሉ በይሖዋ ላይ እርግፍ አድርገን እንጥላለን።—ያዕቆብ 1:6
ጭንቀታችንን በይሖዋ ላይ ልንጥል የምንችለው እንዴት ነው? ፊልጵስዩስ 4:6, 7 መልሱን ይሰጠናል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” አዎን፣ ይሖዋ የምናቀርበውን ያልተቋረጠ ጸሎትና ምልጃ ሰምቶ አእምሯችን አስፈላጊ ባልሆኑ ጭንቀቶች እንዳይረበሽ ሊከላከል የሚችል ውስጣዊ ሰላም ሊሰጠን ይችላል።—ኤርምያስ 17:7, 8፤ ማቴዎስ 6:25-34
ሆኖም ከጸሎታችን ጋር ተስማሚ የሆነ ሥራ ለማከናወን እንድንችል በአካልም ሆነ በአእምሮ ራሳችንን ማግለል አይኖርብንም። (ምሳሌ 18:1) ከዚያ ይልቅ ከችግሮቻችን ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና መመሪያዎች መመርመራችን የተገባ ይሆናል። እንዲህ በማድረግ በራሳችን ማስተዋል ከመደገፍ እንርቃለን። (ምሳሌ 3:5, 6) ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ ጉዳዮችንና የተለያዩ ችግሮችን በተመለከተ በቂ መረጃዎችን ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስንና የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎችን መመልከት ይችላሉ። በተጨማሪም ሁልጊዜ እኛን ለማነጋገር ደከመን ሰለቸን የማይሉ ጥበብና ተሞክሮ ያላቸው ሽማግሌዎችና የጎለመሱ ክርስቲያኖች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ስላሉልን ተባርከናል። (ምሳሌ 11:14፤ 15:22) እንደ እኛ ስሜታዊ ውጥረት ውስጥ ያልገቡና ስለ ጉዳዩ አምላካዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ችግራችንን በሌላ አቅጣጫ እንድንመለከተው ሊረዱን ይችላሉ። ምንም እንኳ ውሳኔ ማድረጉን ለእኛ ቢተዉልንም ከፍተኛ የማበረታቻና የድጋፍ ምንጭ ሊሆኑልን ይችላሉ።
“አምላክን መጠባበቅ”
በሐሳባችን የምንፈጥራቸው ችግሮች የሚያስከትሉት ጭንቀት ሳይጨመር እንኳ በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመወጣት የምናደርገው ትግል የሚፈጥርብን ውጥረት ራሱ ቀላል እንዳልሆነ ማንም አይክድም። ገና ለገና ሊከሰት ይችል ይሆናል በሚል ሐሳብ የምንጨነቅና በፍርሃት የምንዋጥ ከሆነ በጸሎትና በምልጃ ወደ ይሖዋ እንቅረብ። መመሪያና ጥበብ ለማግኘትና ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዲኖርህ ወደ ይሖዋ ቃልና ድርጅት ዞር በል። ምንም ዓይነት ሁኔታ ያጋጥመን ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ እናገኛለን።
መዝሙራዊው ከፍተኛ የልብ ሐዘንና የመረበሽ ስሜት ባደረበት ጊዜ “ነፍሴ ሆይ፣ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? [“አምላክን ተጠባበቂ፣” NW] የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 42:11) ይህ የእኛንም ስሜት የሚያንጸባርቅ ይሁን።
አዎን፣ በእርግጥ ሊከሰት ይችላል ብለህ ለምትጠብቀው ነገር እቅድ አውጣ፤ ገና ለገና ሊከሰት ይችላል በሚል የሚያሳስብህን ጉዳይ ደግሞ ለይሖዋ ተውለት። “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።”—1 ጴጥሮስ 5:7
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንደ ዳዊት ሸክምህንና ጭንቀትህን ሁሉ በይሖዋ ላይ ትጥላለህ?