ውዳቂው ስጋችንን አንቆ የያዘውን ኃጢአት መዋጋት
“ ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፣ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።”—ሮሜ 8:6
1. ሰዎች የተፈጠሩት ለምን አላማ ነበር?
“እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” (ዘፍጥረት 1:27) መልክ የአንድ ነገር ወይም የአንድ ምንጭ ነጸብራቅ ነው። በመሆኑም ሰዎች የተፈጠሩት የአምላክ ክብር ነጸብራቅ እንዲሆኑ ነው። እንደ ፍቅር፣ በጎነት፣ ፍትሕና መንፈሳዊነትን የመሰሉ አምላካዊ ባሕርያትን በኑሯቸው ሁሉ በማንጸባረቅ ለፈጣሪ ውዳሴና ክብር ያመጣሉ፤ ለራሳቸውም ደስታና እርካታ ያገኛሉ።—1 ቆሮንቶስ 11:7፤ 1 ጴጥሮስ 2:12
2. የመጀመሪያዎቹ ሰብአውያን ባልና ሚስት ዒላማውን የሳቱት እንዴት ነው?
2 ፍጹማን ሆነው የተፈጠሩት የመጀመሪያዎቹ ሰብአውያን ባልና ሚስት ይህን ኃላፊነት ለመፈጸም የሚያስችል የተሟላ ብቃት ነበራቸው። ጥራት ያለው ነጸብራቅ እስኪሰጡ ድረስ በደንብ እንደተወለወሉ መስታወቶች የአምላክን ክብር እጅግ ብሩህና ፍጹም በሆነ መንገድ የማንጸባረቅ ችሎታ ነበራቸው። ይሁን እንጂ ሆን ብለው የፈጣሪያቸውንና የአምላካቸውን ትእዛዝ ለማፍረስ በመረጡ ጊዜ ያ ዕፁብ ድንቅ መልክ ጎደፈ። (ዘፍጥረት 3:6) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአምላክን ክብር ፍጹም በሆነ መንገድ ማንጸባረቃቸው አከተመለት። የአምላክ ክብር የጎደላቸው ሆኑ። በአምላክ መልክ የተፈጠሩበትን አላማ ሳቱ። በሌላ አነጋገር ኃጢአት ሠሩ።a
3. የኃጢአት ትክክለኛ ተፈጥሮአዊ ባሕርይ ምንድን ነው?
3 ይህም ሰው ሲፈጠር የነበረውን የአምላክን መልክና ክብር ያጎደፈበትን የኃጢአትን ተፈጥሮአዊ ባሕርይ በትክክል እንድናስተውል ይረዳናል። ኃጢአት ሰውን ያረክሳል፤ በመንፈሳዊና በሥነ ምግባር እንዲቆሽሽና እንዲጎድፍ ያደርጋል። የአዳምና የሔዋን ዝርያዎች የሆኑት የሰው ልጆች በሙሉ ያን የጎደፈና የቆሸሸ አቋም ይዘው ተወልደዋል። አምላክ እንደ ልጆቹ መጠን ከእነርሱ የሚጠብቀውን ነገር አሟልተው የያዙ አልሆኑም። ውጤቱስ ምን ሆነ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።”—ሮሜ 5:12፤ ከኢሳይያስ 64:6 ጋር አወዳድር።
ኃጢአት ውዳቂው ሥጋችንን አንቆ ይዞታል
4-6. (ሀ) በዛሬው ጊዜ አብዛኛዎቹ ሰዎች ስለ ኃጢአት ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው? (ለ) በዘመናችን ሰዎች ለኃጢአት ያላቸው አመለካከት ምን ውጤት አስከትሏል?
4 በዛሬው ጊዜ አብዛኛዎቹ ሰዎች ራሳቸውን እንደቆሸሹ፣ እንደጎደፉ ወይም ኃጢአተኛ እንደሆኑ አድርገው አይመለከቱም። እንዲያውም ኃጢአት የሚለው ቃል ከአብዛኛዎቹ ሰዎች የቃላት ማኅደር ውስጥ ጠፍቷል። ስለ ስህተቶች፣ በንዝህላልነት ስለተፈጸሙ ድርጊቶችና ሳያመዛዝኑ ስለ ወሰዱአቸው መጥፎ እርምጃዎች ይናገሩ ይሆናል። ስለ ኃጢአትስ? ፈጽሞ አይናገሩም ማለት ይቻላል! የሶሽዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት አለን ዎልፌ እንደታዘቡት እስከ አሁንም ድረስ በአምላክ እናምናለን ብለው የሚናገሩት ሰዎችም እንኳን ለእነርሱ “የአምላክ ትምህርቶች የሥነ ምግባር ደንቦች ከመሆን ይልቅ የሥነ ምግባር እምነቶች ጥርቅም ናቸው። 10 ትእዛዛት አድርገው ሳይሆን ‘10 አስተያየቶች’ አድርገው ይመለከቷቸዋል።”
5 እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የሚያስከትለው ውጤት ምንድን ነው? የኃጢአትን መኖር አለመቀበልን ወይም ቢያንስ ቢያንስ ቸል ማለትን ያስከትላል። ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በመለየት ረገድ እጅግ የተዛባ አመለካከት ያለውን ትውልድ ሊያፈራ ችሏል። የራሳቸውን የጠባይ ደረጃዎች ለማውጣት ነጻነት የሚሰማቸውንና የፈለጉትን ቢያደርጉ በማንም ተጠያቂ እንደማይሆኑ የሚሰማቸውን ሰዎች አፍርቷል። እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች የሚወስዱት እርምጃ ትክክል ነው ወይም አይደለም ብለው የሚወስኑበት ብቸኛ መስፈርት ጥሩ ስሜት መሰማቱ ነው።—ምሳሌ 30:12, 13፤ ከዘዳግም 32:5, 20 ጋር አወዳድር።
6 ለምሳሌ ያህል በአንድ የቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ ላይ ወጣቶች የመንፈሳዊ እድገት ጸር የሆኑ ሰባት ኃጢአቶች ስለሚባሉት ነገሮች ያላቸውን አመለካከት እንዲገልጹ ተጋብዘው ነበር።b ሐሳባቸውን ይገልጹ ከነበሩት ወጣቶች አንዱ “ኩራት ኃጢአት አይደለም” ሲል ተናገረ። “ስለ ራስህ ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ያስፈልጋል” ብሏል። ሌላዋ ወጣት ደግሞ ስለ ስንፍና ስትናገር “አንዳንድ ጊዜ እንደዚያ መሆን ጥሩ ነው። . . . አንዳንድ ጊዜ ራስን ዘና ማድረግና ለብቻህ የምታሳለፈው ጊዜ መኖሩ ጥሩ ነው።” ቃለ መጠይቁን ያቀርብ የነበረው ሰውም እንኳን እንዲህ ሲል አስተያየቱን ቁልጭ አድርጎ ገልጿል፦ ‘ሰባቱ ለመንፈሳዊ እድገት ጸር የሆኑ ነገሮች መጥፎ ድርጊቶች አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ ስሜትን ሊረብሹና ከፍተኛ ደስታ ሊሰጡ የሚችሉ ማንኛውም ሰው የግድ የሚፈጽማቸው ነገሮች ናቸው።’ ኃጢአት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ እንደጠፋ ሁሉ የጥፋተኝነትም ስሜት አብሮ ጠፍቷል። የጥፋተኝነት ስሜት አንድ ሰው መጥፎ ሠርቶ የሚሰማው ጥሩ ስሜት ተቃራኒ ነው።—ኤፌሶን 4:17–19
7. መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት ሰዎች በኃጢአት የተነኩት እንዴት ነው?
7 ከዚህ ሁሉ ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ሮሜ 3:23) ሐዋርያው ጳውሎስም እንኳን ይህን ሐቅ አምኖ ተቀብሏል፦ “በእኔ ወይም በእኔ ሥጋዊ ባሕርይ ምንም መልካም ነገር እንደሌለ ዐውቃለሁ፤ ምክንያቱም ምንም እንኳ መልካም ነገር የማድረግ ፍላጎት ቢኖረኝም ያንን መልካም ነገር የማድረግ ችሎታ የለኝም። ማድረግ የምፈልገውን መልካም ነገር አላደርግም፤ ዳሩ ግን የማልፈልገውን ክፉ ነገር አደርጋለሁ።” (ሮሜ 7:18, 19 የ1980 ትርጉም) እዚህ ላይ ጳውሎስ ስለ ዕድሉ ማላዘኑ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የሰው ዘር ምን ያህል የአምላክ ክብር እንደጎደለው ሙሉ በሙሉ በመገንዘቡ ኃጢአት ውዳቂው ሥጋችንን ምን ያህል አንቆ እንደያዘው ተሰምቶት ነበር። “እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?” ብሏል።—ሮሜ 7:24
8. ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ አለብን? ለምንስ?
8 ስለዚህ ጉዳይ ያለህ አመለካከት ምንድን ነው? ከአዳም ዘሮች አንዱ እንደመሆንህ መጠን ልክ እንደ ማንኛውም ሰው ፍጹም አለመሆንህን ትቀበል ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ እውቀት አስተሳሰብህንና አኗኗርህን እንዴት ነክቶታል? ነገሩን የሕይወት እውነታ እንደሆነ ብቻ አድርገህ በመመልከት ያሻህን ማድረግህን ትቀጥላለህን? ወይስ ውዳቂው ሥጋችንን አንቆ የያዘውን ኃጢአት ለመዋጋት የማያቋርጥ ጥረት በማድረግ በሁሉም ነገር የምትችለውን ያህል የአምላክን ክብር በደማቅ ብርሃን ለማንጸባረቅ ትጥራለህ? ጳውሎስ የተናገረውን ግምት ውስጥ በማስገባት እያንዳንዳችን ይህን ጉዳይ በቁም ነገር ልናስብበት ይገባል፦ “እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፣ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፣ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።”—ሮሜ 8:5, 6
ስለ ሥጋ ማሰብ
9. “ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት” ማለት የሆነው ለምንድን ነው?
9 ጳውሎስ “ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነው” ሲል ምን ማለቱ ነበር? “ሥጋ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙውን ጊዜ የዓመፀኛው የአዳም ዘር በመሆን ‘በዓመፃ የተፀነሰውን’ ሰው በአለፍጽምና አቋሙ ለማመልከት ተሠርቶበታል። (መዝሙር 51:5፤ ኢዮብ 14:4) በመሆኑም ጳውሎስ ክርስቲያኖች አእምሮአቸው በኃጢአተኝነት ዝንባሌዎችና ግፊቶች እንዲሁም ፍጹም ባልሆነው በውዳቂው ሥጋችን ፍላጎቶች ላይ እንዳያተኩር መምከሩ ነበር። ግን ለምን? ጳውሎስ በሌላ ቦታ ላይ የሥጋ ሥራ ምን እንደሆነ ከገለጸልን በኋላ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ አክሎ ተናግሯል፦ “እንደነዚህ ያሉትን [ልማድ] የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።”—ገላትያ 5:19–21
10. “ማሰብ” ሲባል ምን ማለት ነው?
10 ይሁን እንጂ አንድን ነገር በማሰብና ልማደኛ ሆኖ በማድረግ መካከል ትልቅ ልዩነት የለም እንዴ? እውነት ነው፣ ስለ አንድ ነገር ማሰብ ሁልጊዜ ድርጊቱን ወደ መፈጸም አይመራም። ይሁን እንጂ ማሰብ ሲባል ለአንድ አፍታ አስቦ ወዲያው መተው ማለት ብቻ አይደለም። ጳውሎስ የተጠቀመው ፍሮኔማ የሚለውን የግሪክኛ ቃል ነው፤ ይህም “የአስተሳሰብ ስልትን፣ የአእምሮን የትኩረት አቅጣጫ፣ . . . ዓላማን፣ ምኞትን፣ ጥረትን” ያመለክታል። ስለዚህ “ስለ ሥጋ ማሰብ” ማለት በውዳቂው ሥጋ ምኞቶች ቁጥጥርና ተጽዕኖ ሥር መሆን፣ ለእርሱ ተገዢ መሆንና በምኞቶቹ መመራት ማለት ነው።—1 ዮሐንስ 2:16
11. ቃየን ስለ ሥጋ ያስብ የነበረው እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ነበር?
11 ለዚህ ነጥብ ቃየን የወሰደው እርምጃ ጥሩ ማስረጃ ይሆነናል። ቅናትና ቁጣ በቃየን ልብ ውስጥ ማቆጥቆጥ ሲጀምሩ ይሖዋ አምላክ እንዲህ ሲል አስጠነቀቀው፦ “ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅህ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፣ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት።” (ዘፍጥረት 4:6, 7) በቃየን ፊት ምርጫ ተደቅኖ ነበር። የአእምሮውን የትኩረት አቅጣጫ፣ ዓላማውንና ምኞቱን በመልካም ነገር ላይ በማድረግ ‘መልካም አደረገን’? ወይስ ስለ ሥጋ በማሰብና አእምሮው በልቡ ውስጥ ባደሩት ዝንባሌዎች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ቀጠለ? ይሖዋ እንደገለጸው ኃጢአት ቃየን ከፈቀደላት በድንገት ልታጠምደውና ልትይዘው ‘በደጁ እያደባች ነበር።’ ሥጋዊ ፍላጎቱን ከመታገልና ‘በላዩ ላይ ከመንገሥ ይልቅ’ ቃየን በቁጥጥሩ ሥር እንዲያስገባውና በመጨረሻም ወደ ጥፋት እንዲያደርሰው ፈቀደለት።
12. “በቃየን መንገድ” ላለመሄድ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
12 በዛሬው ጊዜ ያለነው እኛስ? ይሁዳ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች መካከል ስለነበሩ አንዳንድ ሰዎች የተሰማውን ኀዘን ሲናገር እንዳለው ‘በቃየን መንገድ መሄድ’ እንደማንፈልግ አያጠራጥርም። (ይሁዳ 11) ምኞቶቻችንን ሳይበዛ ማርካት ወይም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመሥመር ትንሽ ወጣ ማለት ያን ያህል ጉዳት የለውም ብለን መደምደምና ማሰብ ፈጽሞ አይገባንም። ከዚህ ይልቅ ወደ ልባችንና ወደ አእምሮአችን ሊመጣ የሚችለውን አምላካዊ ያልሆነና የሚበክል ተጽዕኖ ለይተን ለማወቅ ንቁዎች መሆንና ሥር ከመስደዱ በፊት ወዲያውኑ ማስወገድ ይኖርብናል። ውዳቂ ሥጋችንን አንቆ የሚይዘውን ኃጢአት መዋጋት የምንጀምረው በውስጥ ካለው ሐሳብ ነው።—ማርቆስ 7:21
13. አንድ ሰው “በራሱ ምኞት” ሊፈተን የሚችለው እንዴት ነው?
13 ለምሳሌ ያህል የሚሰቀጥጥ ወይም የሚያሳዝን ትዕይንት ወይም መጥፎ መልእክት የሚያስተላልፍ ወይም የጾታ ብልግናን ስሜት የሚያነሳሳ ምስል በጨረፍታ ተመልክተህ ይሆናል። በመጽሐፍ ወይም በመጽሔት ላይ ያለ ሥዕል፣ በፊልም ወይም በቴሌቪዥን የታየ ትዕይንት፣ በማስታወቀያ ሰሌዳ ላይ የተለጠፈ ማስታወቂያ ወይም ከዚያም አልፎ በእውን ሲፈጸም የታየ ነገር ሊሆን ይችላል። ይህ ሊያጋጥም የሚችልና የሚያጋጥም ነገር ስለሆነ በዚህ መረበሽ አያስፈልገንም። ይሁን እንጂ ይህ ምስል ወይም ትዕይንት የታየው ለጥቂት ሰኮንዶች ብቻ ሊሆን ቢችልም እንኳ በአእምሮ ውስጥ ሊመላለስ ይችላል፤ በየጊዜው ውል እያለ ሊያስቸግርህ ይችላል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ምን ታደርጋለህ? ይህን ሐሳብ ለመዋጋትና ከአእምሮህ ለማስወጣት ወዲያውኑ እርምጃ ትወስዳለህን? ወይስ ምናልባት ያጋጠመህን ሁኔታ በየጊዜው በማስታወስ ያ ሐሳብ በአእምሮህ ውስጥ እንዲቀመጥ ትፈቅድለታለህ? ይህን ማድረግ ማለት ያዕቆብ ቀጥሎ ለገለጻቸው እርስ በእርሳቸው እንደ ሰንሰለት ለተሳሰሩ ክንውኖች ራስን ማጋለጥ ማለት ነው፦ “እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።” ጳውሎስ “ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና” ሲል የተናገረው በዚህ ምክንያት ነው።—ያዕቆብ 1:14, 15፤ ሮሜ 8:6
14. በየዕለቱ የሚቀርቡልን ነገሮች ምንድን ናቸው? ምን ስሜት ማሳየትስ ይገባናል?
14 የጾታ ብልግና፣ ዓመፅና ፍቅረ ነዋይ በሚወደሱበትና በመጻሕፍት፣ በመጽሔቶች፣ በፊልሞች፣ በቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ተወዳጅነትን ባተረፉ ሙዚቃዎች በይፋና በስፋት በሚቀርቡበት ዓለም ውስጥ የምንኖር እንደ መሆናችን መጠን በየቀኑ ቃል በቃል የመጥፎ ሐሳቦችና አመለካከቶች ውርጅብኝ ይወርድብናል። ለዚህ ሁኔታ የምትሰጠው ምላሽ ምንድን ነው? እነዚህ ነገሮች ሁሉ የሳቅና የደስታ ስሜት ይቀሰቅሱብሃልን? ወይስ “በዓመጸኞች አሳፋሪ ድርጊት እየተሠቀቀ ይኖር የነበረው . . . በክፉ ሥራቸው ምክንያት ጻድቅ ነፍሱ” የተጨነቀችው ጻድቁ ሎጥ የተሰማውን ዓይነት ስሜት ይሰማሃል? (2 ጴጥሮስ 2:7, 8 የ1980 ትርጉም) ውዳቂው ሥጋችንን አንቆ የያዘውን ኃጢአት ለማሸነፍ በምናደርገው ውጊያ ድል አድራጊዎች ለመሆን መዝሙራዊው ያደረገውን ለማድረግ ቆርጠን መነሣት አለብን፦ “በዓይኔ ፊት ክፉን ነገር አላኖርሁም፤ ሕግ ተላላፊዎችን ጠላሁ።”—መዝሙር 101:3
ስለ መንፈስ ማሰብ
15. የኃጢአትን ማነቆ ለመዋጋት ምን እርዳታ አለን?
15 ውዳቂውን ሥጋችንን አንቆ የያዘውን ኃጢአት ለመዋጋት የሚረዳን ነገር ጳውሎስ “ስለ መንፈስ ማሰብ . . . ሕይወትና ሰላም ነው” በማለት የተናገረው ነገር ነው። (ሮሜ 8:6) ስለዚህ በሥጋ መዳፍ ውስጥ ከመግባት ይልቅ አእምሮአችን በመንፈስ ግፊት ሥር እንዲሆንና የመንፈስ ነገሮች በውስጣችን እንዲፋፉ ማድረግ አለብን። እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው? ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 4:8 ላይ በዝርዝር አስቀምጧቸዋል፦ “በቀረውስ፣ ወንድሞች ሆይ፣ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፣ እነዚህን አስቡ።” ዘወትር ልናስብባቸው የሚገቡን ነገሮች ምን እንደሆኑ ጠጋ ብለን በመመልከት በይበልጥ እናስተውላቸው።
16. ጳውሎስ በየትኞቹ ባሕርያት ‘ማሰባችንን እንድንቀጥል’ አበረታቶናል? እያንዳንዳቸውስ ምን ማለት ናቸው?
16 በመጀመሪያ ደረጃ ጳውሎስ ስምንት የሥነ ምግባር ባሕርያትን ዘርዝሯል። እርግጥ ነው ክርስቲያኖች ሁልጊዜ ስለ ቅዱስ ጽሑፋዊ ወይም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ትምህርቶች ብቻ እንዲያስቡ የተገደቡ አለመሆናቸውን እናውቃለን። አእምሮአችን ሊያተኩር የሚችልባቸው ብዙ ርዕሰ ጉዳዮች አሉ። ይሁን እንጂ ቁም ነገሩ እነዚህ ነገሮች ጳውሎስ ከገለጻቸው ባሕርያት ጋር መጣጣም ያለባቸው መሆኑ ነው። ጳውሎስ የጠቀሳቸው ‘ነገሮች’ አንድ በአንድ ትኩረታችን ያሻቸዋል። እስቲ በየተራ እንመልከታቸው።
◻ “እውነተኛ” ሲባል የአንድ ነገር እውነት ወይም ውሸት መሆን ማለት ብቻ አይደለም። እውነት መናገር፣ ትክክለኛ ነገር ማድረግ፣ የሚታመን፣ እንዲሁ የሚመስል ሳይሆን ትክክለኛ የሆነ ነገር ማለት ነው።—1 ጢሞቴዎስ 6:20
◻ “ጭምትነት ያለበት” የሚለው አባባል ክብደትና ክብር የሚያሰጡ ነገሮችን ያመለክታል። ባለጌ የሚያሰኙ ወይም ዝቅተኛ ግምት የሚያሰጡ ሳይሆኑ የሰውን አክብሮት የሚያተርፉ፣ ከፍ ብለን ወይም እንደ ጨዋ ተደርገን እንድንታይ የሚያበቁ ነገሮች ናቸው።
◻ “ጽድቅ የሆነውን ነገር” ማለት የሰውን ሳይሆን የአምላክን የአቋም ደረጃዎች ማሟላት ማለት ነው። የዓለም ሰዎች አእምሮአቸው በክፋት ውጥኖች የተሞላ ነው፤ እኛ ግን በአምላክ ዓይን ጽድቅ የሆኑ ነገሮችን እናስባለን፤ በእነርሱም እንደሰታለን።—ከመዝሙር 26:4 እና ከአሞፅ 8:4–6 ጋር አወዳድር።
◻ “ ንጹሕ የሆነውን ነገር” ማለት በሥነምግባር (በጾታ ወይም በሌሎች ነገሮች) ብቻ ሳይሆን በሐሳብና በውስጣዊ የልብ ዓላማ ጭምር የጠራና ቅዱስ መሆን ማለት ነው። “ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት” ሲል ያዕቆብ ተናግሯል። “ንጹሕ” የሆነው ኢየሱስ ልንመለከተው የሚገባ ፍጹም ምሳሌያችን ነው።—ያዕቆብ 3:17፤ 1 ዮሐንስ 3:3
◻ “ፍቅር ያለበትን” ሲባል ሌሎችን ለፍቅር የሚቀሰቅስና የሚያነሳሳ ነገር ነው። አእምሮአችንን ጥላቻን፣ መራርነትንና ጠብ በሚያነሳሱ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ከማድረግ ይልቅ “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ” ተብለን ታዘናል።—ዕብራውያን 10:24
◻ “መልካም ወሬ ያለበትን” ማለት “ጥሩ ስም ያለው” ወይም “ጥሩ የሚነገርለት” ማለት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አድራጊ ግስ ሆኖ ሲሠራበት ማነጽና ማመስገን የሚል ትርጉምም አለው። አእምሮአችን ወራዳና አስጸያፊ በሆኑ ነገሮች ላይ ሳይሆን ጤናማና ገንቢ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር እናደርጋለን።—ኤፌሶን 4:29
◻ “በጎነት” በመሠረቱ “ጥሩነት” ወይም “መልካም ሥነ ምግባር” ማለት ነው። ነገር ግን የማንኛውም ነገር ጥሩ ባሕርይ ማለትም ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር ጎን ለጎን የሚሄዱ የሌሎች ሰዎችን ውድ ባሕርያት፣ ጥሩ ጥሩ ጎኖችና ችሎታቸውን ማድነቅ እንችላለን።
◻ “ ምስጋና” — ምስጋናው ከአምላክ ወይም እርሱ ከሚቀበለው ባለ ሥልጣን የመጣ ከሆነ በእርግጥም የሚያስመሰግኑ ነገሮች ናቸው።—1 ቆሮንቶስ 4:5፤ 1 ጴጥሮስ 2:14
ሕይወትና ሰላም እንደምናገኝ የተገባልን ቃል
17. “ስለ መንፈስ ማሰብ” ምን በረከቶችን ያስገኛል?
17 የጳውሎስን ምክር ስንከተልና “እነዚህን ነገሮች ማሰባችንን ስንቀጥል [አዓት]” “ስለ መንፈስ ማሰብ” ቀና ይሆንልናል። ውጤቱ አምላክ ቃል በገባልን አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት በረከት ማግኘት ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሰላምንም ያስገኛል። (ሮሜ 8:6) ለምን? ምክንያቱም አእምሮአችን ከክፉ የሥጋዊ ነገሮች ተጽዕኖ ስለሚጠበቅና ጳውሎስ በገለጸው በሥጋና በመንፈስ መካከል ባለው ከባድ ውጊያ መሠቃየታችን ስለሚያከትምለት ነው። በተጨማሪም የሥጋን ተጽዕኖ ስንከላከል ከአምላክ ጋር ሰላም ይኖረናል። “ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና።”—ሮሜ 7:21–24፤ 8:7
18. ሰይጣን እያካሄደ ያለው ውጊያ ምንድን ነው? እኛስ ድል መቀዳጀት የምንችለው እንዴት ነው?
18 ሰይጣንና ወኪሎቹ የምናንጸባርቀውን የአምላክ ክብር ለማጉደፍ የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው። ሥጋዊ ምኞቶች በመጨረሻ ከአምላክ ጋር ቅራኔ ወደ መፍጠርና ወደ ሞት እንደሚመሩ ስለሚያውቁ አእምሮአችንን በሥጋዊ ምኞቶች በመደብደብ ለመቆጣጠር ይጥራሉ። ሆኖም በዚህ ውጊያ ድል መቀዳጀት እንችላለን። ልክ እንደ ጳውሎስ ውዳቂው ሥጋችንን አንቆ የያዘውን ኃጢአት ለመዋጋት የምንችልባቸውን ስልቶች በመስጠት ስለሚረዳን “በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” በማለት መናገር እንችላለን።—ሮሜ 7:25
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአት” የሚለውን ቃል ለማመልከት በጥቅሉ ቻታ የተባለውን የዕብራይስጥ ግሥና ሃማርታኖ የተባለውን የግሪክኛ ግሥ ይጠቀማል። ሁለቱም ቃላት “መሳት” የሚል ፍቺ ያላቸው ሲሆን ይህ ቃል አንድን ግብ ዳር አለማድረስ ወይም አንድን ዒላማ ወይም ያነጣጠሩበትን ነገር አለመምታት የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል።
b በተለምዶ ሰባቱ የመንፈሳዊ እድገት ጸር የሚባሉት ነገሮች ኩራት፣ መጎምጀት፣ በጾታ ስሜት መብከንከን፣ ቅናት፣ ሆዳምነት፣ ቁጣና ስንፍና ናቸው።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ ኃጢአት ምንድን ነው? ውዳቂው ሥጋችንን አንቆ ለመያዝ የሚችለውስ እንዴት ነው?
◻ ‘ስለ ሥጋ የማሰብን’ ዝንባሌ መዋጋት የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ‘ስለ መንፈስ የማሰብን’ ባሕርይ ለማዳበር ምን ማድረግ እንችላለን?
◻ “ስለ መንፈስ ማሰብ” ሕይወትንና ሰላምን የሚያስገኘው እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቃየን ሥጋዊ ዝንባሌዎች እንዲያሸንፉትና ወደ ጥፋት እንዲመሩት ፈቅዷል
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ መንፈስ ማሰብ ሕይወትና ሰላም ያስገኛል