ሳውል ክርስቲያኖችን ያሳደደው ለምን ነበር?
‘በኢየሩሳሌም ደግሞ እንዳደረግሁት የናዝሬቱን ኢየሱስ ስም የሚቃወም ብዙ ነገር አደርግ ዘንድ የሚገባኝ ይመስለኝ ነበር። ከካህናት አለቆችም ሥልጣን ተቀብዬ ከቅዱሳን ብዙዎችን በወህኒ አሳሰርኳቸው። ደቀ መዛሙርቱ እንዲገደሉም አብሬ ድምፅ ሰጥቻለሁ። በምኩራብም ሁሉ አየቀጣሁ እምነታቸውን እንዲክዱ ላስገድዳቸው ሞክሬአለሁ። በእነሱ ላይ በጣም ተቆጥቼም ወደ ሌሎች ከተሞች ጭምር በመሄድ አሳድዳቸው ነበር።’ —ሥራ 26:9-11
እንዲህ በማለት የተናገረው ሐዋርያው ጳውሎስ በመባል ጭምር የሚታወቀው የጠርሴሱ ሳውል ነው። በእርግጥ ይህን በተናገረበት ጊዜ ተለውጦ ነበር። አሁን የክርስትና ተቃዋሚ ሳይሆን ክርስትናን በቅንዓት ከሚያስፋፉት አንዱ ሆኗል። ነገር ግን በፊት ክርስቲያኖችን እንዲያሳድድ ሳውልን ያነሳሳው ምን ነበር? ይህን ድርጊት ‘ያደርግ ዘንድ እንደሚገባው’ ያሰበው ለምን ነበር? ከእሱስ ታሪክ ምን ትምህርት ሊገኝ ይችላል?
የእስጢፋኖስ በድንጋይ መወገር
ሳውል በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ብቅ የሚለው እስጢፋኖስን ከገደሉት ሰዎች ጋር በመጠቀስ ነው። “[እስጢፋኖስን] ከከተማም ወደ ውጪ አውጥተው ወገሩት። ምሥክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ።” “ሳውልም በሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።” (ሥራ 7:58, 60) እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ ወደ መውሰድ የመራው ምን ነበር? ከኪልቅያ የሆኑትን አንዳንዶች ጨምሮ አይሁዳውያን ከእስጢፋኖስ ጋር ይከራከሩ ነበር፤ ነገር ግን ሊቋቋሙት አልቻሉም። የኪልቅያ ሰው የነበረው ሳውል በመካከላቸው ይኑር ኣይኑር የተገለጸ ነገር የለም። ያም ሆነ ይህ አምላክን ተሳድቧል በሚል እስጢፋኖስን ለመክሰስና ሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ለማቅረብ የሐሰት ምሥክሮችን ተጠቅመዋል። (ሥራ 6:9-14) በሊቀ ካህናቱ የሚመራው ይህ ሸንጎ የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሆኖ ያገለግል ነበር። የመጨረሻው ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ባለሥልጣን እንደመሆኑ መጠን አባሎቹም ንጹህ ሃይማኖታዊ ሕግ ነው ብለው ለያዙት ነገር የቆሙ ነበሩ። በእነሱ አመለካከት እስጢፋኖስ ሞት ይገባው ነበር። ሕጉን አትጠብቁም በማለት እንደተዳፈራቸው ቆጥረውት ነበር፤ ነገር ግን ተዳፍሯቸው ነበርን? (ሥራ 7:53) ሕጉን እንዴት እንደሚጠብቁ ሊያሳዩት ቆርጠው ነበር!
ሳውል ከነበረው ጽኑ እምነት አንፃር በዚህ ሐሳብ መስማማቱ የሚጠበቅ ነገር ነው። እርሱ ፈሪሳዊ ነበር። ይህ እምነት ደግሞ ሕጉንና ባህሉን በጥብቅ መከተልን ይጠይቃል። የክርስትና እምነት በኢየሱስ አማካኝነት ስለሚገኝ አዲስ የመዳን መንገድ ስለሚያስተምር የዚህ እምነት ተቃራኒ ተደርጎ ታይቷል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዳውያን መሲሑ አንገሽግሿቸው ከነበረው የሮማውያን አገዛዝ ቀንበር ነፃ የሚያወጣቸው ታላቅ ንጉሥ ይሆናል ብለው ጠብቀው ነበር። በታላቁ ሳንሄድሪን ፊት ተሳዳቢ ነው ተብሎ ተከሶ ቀርቦ የነበረውና የተፈረደበት፣ በኋላም ልክ እንደተረገመ ወንጀለኛ በመከራ እንጨት ላይ የተሰቀለው ሰው መሲሕ ነው ማለት ለአእምሮአቸው ሙሉ በሙሉ እንግዳ፣ ተቀባይነት የሌለው እና የሚያስጸይፍ ነበር።
ሕጉ በእንጨት ላይ የሚሰቀል ሰው “በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ” እንደሆነ ይገልጻል። (ዘዳግም 21:22, 23፤ ገላትያ 3:13) እንደ ሳውል አመለካከት ከሆነ “እነዚህ ቃላት በግልጽ በኢየሱስ ላይ የሚሠሩ ናቸው” በማለት ፍሬዴሪክ ኤፍ ብሩስ አስተያየት ሰጥተዋል። “እሱ በአምላክ እርግማን ውስጥ ሆኖ ሞቷል። ስለሆነም እነሱ እንደሚገምቱት የአምላክ በረከት ልዩ በሆነ መንገድ ያረፈበት መሲሕ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ኢየሱስ መሲሕ ነው ብሎ መናገር አምላክን እንደ መስደብ ይቆጠራል፤ እንዲህ ብለው የሚናገሩ ሰዎች እንደ ተሳዳቢ ተቆጥረው ስቃይ ሊደርስባቸው ይገባል።” ሳውል ራሱ በኋላ እንደገለጸው “የተሰቀለው ክርስቶስ” የሚለው ትምህርት “ለአይሁድ ማሰናከያ” ነበር።—1 ቆሮንቶስ 1:23
እንዲህ ላለው ትምህርት ሳውል የሚሰጠው ምላሽ በሚቻለው አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሞ መቃወም ነበር። እንዲያውም ይህን ትምህርት ለማጥፋት ማንኛውም የኃይል እርምጃ መወሰድ ነበረበት። ይህ ደግሞ አምላክ የሚፈልገው ነገር እንደሆነ እርግጠኛ ነበር። ሳውል የነበረውን አመለካከት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፣ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፣ ያለ ነቀፋ ነበርሁ።” “የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፣ ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር።”—ፊልጵስዩስ 3:6፤ ገላትያ 1:13, 14
ዋነኛ አሳዳጅ
ከእስጢፋኖስ ሞት በኋላ ሳውል ተባባሪ ብቻ መሆኑ ቀርቶ ራሱ ዋነኛ አሳዳጅ ሆነ። በአሳዳጅነቱ የታወቀ ስለነበረ ይሆናል ከተለወጠ በኋላም እንኳ ከደቀ መዛሙርት ጋር ለመተባበር በፈለገ ጊዜ “ሁሉም ደቀ መዝሙር እንደሆነ ስላላመኑ ፈሩት።” በእርግጥ ክርስቲያን እንደሆነ ግልጽ በሆነ ጊዜ የሱ መለወጥ ደቀ መዛሙርቱ እንዲደሰቱና አምላክን እንዲያመሰግኑ አድርጓቸዋል። ያስደሰታቸው ቀድሞ ተቃዋሚ የነበረ አንድ ሰው የልብ ለውጥ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን “ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፣ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል” ሲባል መስማታቸው ነው።—ሥራ 9:26፤ ገላትያ 1:23, 24፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
ደማስቆ ከኢየሩሳሌም 220 ኪሎ ሜትር ማለትም የሰባት ወይም የስምንት ቀን የእግር መንገድ ያህል ርቃ ትገኛለች። ቢሆንም ግን ሳውል “ደቀ መዛሙርት[ን] እንዲገድላቸው ገና እየዛተ” ወደ ሊቀ ካህኑ ሄደና በደማስቆ ላሉት ምኩራቦች ደብዳቤ እንዲጽፍለት ጠየቀው። ለምን? ሳውል በዚህ “መንገድ” ያለን ማንኛውንም ሰው እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት እንዲችል ነው። ሳውልም በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ‘ቤተ ክርስቲያንን እያፈረሰ ወደ ሁሉም ቤት እየገባ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጎተተ ወደ ወህኒ ይሰጥ’ ነበር። ሌሎቹንም ‘ወደየምኩራቡ እየጎተተ’ እና ‘ድምፁን እየሰጠ’ (ቃል በቃል “የድምፅ መስጫ ጠጠር በመጣል”) እንዲገደሉ ደግፏል።—ሥራ 8:3፤ 9:1, 2, 14፤ 22:5, 19፤ 26:10፣ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ
አንዳንድ ምሁራን ሳውል ከገማልያል የተማረውን ትምህርትና አሁን ያገኘውን ሥልጣን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከተራ የሕግ ተማሪነት ተነስቶ በአይሁድ ማህበረሰብ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን እስከመያዝ ደርሷል ብለው ያምናሉ። ለምሳሌ አንድ ጸሐፊ ምናልባት ሳውል በኢየሩሳሌም ምኩራብ አስተማሪ ሳይሆን አልቀረም ብለው ገምተዋል። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ ሳውል ‘ድምፁን እየሰጠ’ ሲል በችሎት አባልነት ማለቱ ይሁን ወይም ክርስቲያኖች እንዲገደሉ በግሰብ ደረጃ የሞራል ድጋፍ ሰጠ ማለቱ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም።a
በመጀመሪያ ላይ ሁሉም ክርስቲያኖች አይሁዳውያን ወይም ወደ አይሁድነት የተለወጡ በመሆናቸው ሳውል ክርስትናን በአይሁድ እምነት ውስጥ ያለ የክህደት እንቅስቃሴ አድርጎ ሳይረዳው አልቀረም፤ እንዲሁም የክርስትናን አማኞች ማስተካከል የአይሁድ እምነት ባለሥልጣኖች ኀላፊነት እንደሆነ ቆጥሮታል። ምሁሩ አርለንድ ጄ ሃልትግሬን እንዲህ ብለዋል:- “አሳዳጅ የነበረው ጳውሎስ ክርስትናን ከአይሁድ እምነት ውጪ ያለ ተቀናቃኝ ሃይማኖት አድርጎ ስለተመለከተው ብቻ ይቃወመዋል ማለት የማይመስል ነው። እሱም ሆነ ሌሎቹ ሰዎች የክርስትና እንቅስቃሴ አሁንም በአይሁድ ሥልጣን ሥር ነው ብለው ሳያስቡ አልቀረም።” ስለዚህ የእሱ ሐሳብ ከእምነታቸው ወጥተው የባዘኑትን አይሁዳውያን በተቻለው አቅም ቀጥ ብለው ወደ ጥንት ወደ ጠዋቱ እምነታቸው እንዲመለሱ ማስገደድ ነበር። (ሥራ 26:11) ቀላል ሆኖ ያገኘው አንደኛው መንገድ ማሰር ነበር። ሌላኛው ደግሞ ወደ ምኩራብ እየጎተተ የሃይማኖታዊ መምህራንን ሥልጣን የማይታዘዝን ሰው በመቅጣት የተለመደውን የማስተካከያ እርምጃ ወደሚፈጽሙት ሦስት ዳኞች ወዳሉት ወደ የትኛውም የአካባቢው ፍርድ ቤት መውሰድ ነበር።
እርግጥ ነው ወደ ደማስቆ በሚያመራው መንገድ ላይ ኢየሱስ ለሳውል መገለጡ ይህ ድርጊት እንዲያቆም አድርጓል። ኃይለኛ የክርስትና ተቃዋሚ የነበረው ሳውል በድንገት ተለውጦ የክርስትና ጠበቃ ሆነ። ወዲያው በደማስቆ ያሉ አይሁዶች ሞቱን ይመኙ ጀመር። (ሥራ 9:1-23) ከብዙ ዓመታት በፊት አሳዳጅ ሳለ ያስፈጸማቸው ብዙ ነገሮች እንደ ክርስቲያንነቱ በሳውል ላይ ደርሰው ሊያሰቃዩት ነው። በመሆኑም ከዓመታት በኋላ “አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ” ለማለት ችሏል።— 2 ቆሮንቶስ 11:24
ቅንዓት አቅጣጫውን ሊስት ይችላል
ከተለወጠ በኋላ ይበልጥ ጳውሎስ በመባል የሚታወቀው ሳውል “አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም” ነበርኩ በማለት ጽፏል። “ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ።” (1 ጢሞቴዎስ 1:13) ስለዚህ አንድ ሰው አንድን ሃይማኖት በቅንነት መከተሉና ለሃይማኖቱ ቀናተኛ መሆኑ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ዋስትና አይሆነውም። ሳውል ቀናተኛና ኅሊናው አድርግ የሚለውን ነገር የሚያደርግ ሰው ነበር። ሆኖም ይህ ትክክለኛ አላደረገውም። ቅንዓቱ ከፍተኛ ቢሆንም ትክክለኛውን አቅጣጫ የተከተለ አልነበረም። (ከሮሜ 10:2, 3 ጋር አወዳድር።) ይህ እኛም ጉዳዩን በጥሞና እንድናስብበት ሊያደርገን ይገባል።
ዛሬ ብዙዎች አምላክ ከእነሱ የሚፈልገው ነገር ጥሩ ሰው መሆን ብቻ እንደሆነ አድርገው ያምናሉ። ግን እንደዚያ ነውን? እያንዳንዱ ሰው “ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ” የሚለውን የጳውሎስን ጥብቅ ምክር ቢሰማ ጥሩ ነው። (1 ተሰሎንቄ 5:21) ይህም ማለት የአምላክን የእውነት ቃል ትክክለኛ እውቀት ለመቅሰም ጊዜ መዋጀትና ሙሉ በሙሉ ከዚያ ጋር ተስማምቶ መኖር ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስን በምንመረምርበት ጊዜ ለውጦች ማድረግ እንዳለብን ከተገነዘብን በምንም ዓይነት ሳንዘገይ አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግ አለብን። ምናልባትም አብዛኞቻችን እንደ ሳውል ተሳዳቢዎች፣ አሳዳጆች ወይም አንገላቾች ላንሆን እንችላለን። ሆኖም እንደ እርሱ የአምላክን ሞገስ ልናገኝ የምንችለው ከእምነትና ከትክክለኛ እውቀት ጋር የሚስማማ ድርጊት ካደረግን ብቻ ነው።—ዮሐንስ 17:3, 17
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በኤሚል ሹረር የተዘጋጀው ዘ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ጅዊሽ ፒፕል ኢን ዚ ኤጅ ኦቭ ጂሰስ ክራይስት (175ከዘአበ-135እዘአ) የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ከሆነ ምንም እንኳን በሚሽናህ ላይ ስለ ታላቁ ሳንሄድሪን ወይም ሰባ አንድ አባላት ስላሉት ሳንሄድሪን ምንም የተዘገበ ነገር ባይኖርም 23 አባሎች ስላሏቸው ስለ ትንንሾቹ ሳንሄድሪኖች ግን ጥቃቅን ዝርዝሮች እንኳን ተገልጸዋል። የሕግ ተማሪዎች በትንንሾቹ ሳንሄድሪኖች በሚታዩት ከባባድ ጉዳዮች ላይ ለመካፈልና ተከሳሹን በመቃወም ሳይሆን በመደገፍ ለመናገር እንዲችሉ ይፈቀድላቸው ነበር። ከባባድ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ ግን ሁለቱንም ማድረግ ይችሉ ነበር።