በቤተሰብና በጉባኤ ውስጥ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ
“ንግግራችሁ ሁልጊዜ፣ በጨው እንደ ተቀመመ፣ በጸጋ ይሁኑ”—ቆላስይስ 4:6
1. አምላክ ሔዋንን ከእርሱ ጋር ባስተዋወቀበት ጊዜ አዳም ምን አለ?
“እንደ ደሴት የሆነ ማንም ሰው የለም፤ . . . ሁሉም ሰው የአንድ አካል ክፍል ነው።” ይህንን የጻፈው ከአያሌ መቶ ዘመናት በፊት የኖረ አንድ አስተዋይ የስነ ጽሑፍ ሰው ነው። ይህንን ሲናገር ፈጣሪ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም” በማለት ለአዳም የተናገረው ቃል እውነት መሆኑን ማረጋገጡ ብቻ ነበር። አዳም ለሁሉም እንስሳት ስም አውጥቶላቸው ስለነበር የንግግርና የቋንቋ ስጦታ ነበረው ማለት ነው። ይሁን እንጂ አዳም ሐሳቡን ሊገልጽለት የሚችል ሰብዓዊ ፍጡር በአጠገቡ አልነበረም። አምላክ ውብ የነበረችውን ሔዋንን ሚስቱ አድርጎ ሲያስተዋውቀው “ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት” ብሎ አዳም በደስታ መናገሩ ምንም የሚያስደንቅ አይሆንም። በዚህ መንገድ የመጀመሪያው ቤተሰብ ሲመሠረት አዳም ከሌላ ሰው ጋር የንግግር ግንኙነት ማድረግ ጀመረ።—ዘፍጥረት 2:18, 23
2. ቁጥጥር የማይደረግበት ቴሌቪዥንን የማየት ልማድ ምን ጉዳት ሊያስከትል ይችላል?
2 የቤተሰብ ክልል የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ አመቺ የሆነ ቦታ ነው። እንዲያውም የቤተሰብ ኑሮ የተሳካ መሆኑ የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ በመቻል ላይ የተመካ ነው። ይሁን እንጂ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ጊዜና ጥረትን ይጠይቃል። በዛሬው ጊዜ ከዋናዎቹ የጊዜ ሌቦች አንዱ ቴሌቪዥን ነው። ቴሌቪዥን ቢያንስ በሁለት መንገዶች ጎጂ መሣሪያ ሊሆን ይችላል። በአንድ በኩል የቤተሰብ አባሎች በቴሌቪዥን ተማርከው የእርሱ ሱሰኞች እንዲሆኑ ስለሚያደርጋቸው እርስ በርሳቸው የሐሳብ ግንኙነት እንዳያደርጉ እንቅፋት ሊሆንባቸው ይችላል። በሌላም በኩል ቴሌቪዥን አለመግባባትና ቅራኔ በሚኖርበት ጊዜ እንደ መሸሸጊያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። አንዳንድ ባልና ሚስቶች ችግሮቻቸውን ተወያይተው ለመፍታት ከመጣር ፋንታ ተኮራርፈው ቴሌቪዥን ማየትን መርጠዋል። ስለዚህ ቴሌቪዥን ዋነኛው የጋብቻ አፍራሽ ለሆነው የሐሳብ ግንኙነት አለመኖር አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። ቴሌቪዥን ማየትን በሁለተኛ ቦታ የማስቀመጥ ችግር የሚያጋጥማቸው ሰዎች ቴሌቪዥኑን ጨርሶ ከቤት ለማጥፋት ቢያስቡበት ጥሩ ይሆናል። —ማቴዎስ 5:29፤ 18:9
3. አንዳንዶች ቴሌቪዥንን የሚያዩበትን ጊዜ በመወሰናቸው የተጠቀሙት እንዴት ነው?
3 በቴሌቪዥን አጠቃቀም ላይ ቅነሳ ሲደረግ ወይም ጭራሹኑ ከቤት ሲወገድ የተገኙትን በረከቶች የሚገልጹ አስደሳች ሪፖርቶች እየደረሱን ነው። አንድ ቤተሰብ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከቀድሞው የበለጠ እርስ በርሳችን እንነጋገራለን . . . የበለጠ የመጽሐፍ ቅዱስ ምርምር እናደርጋለን. . . አብረን እንጫወታለን. . . ሁሉም የመስክ አገልግሎታችን ገጽታዎች ተሻሽለዋል።” አንድ ሌላ ቤተሰብም ቴሌቪዥንን ከቤታቸው ካስወገዱ በኋላ እንዲህ አሉ፦ “ያዳንነው ገንዘባችንን ብቻ አይደለም [በኬብል የሚተላለፍ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ኮንትራት ነበራቸው]፣ ቤተሰባችን በይበልጥ ለመቀራረብ ችሎአል። በጊዜያችን ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን ለመሥራት ችለናል። በፍጹም ሰልችቶን አያውቅም።”
መመልከት፣ መናገርና ማዳመጥ
4. ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው አድናቆታቸውን ሊገላለጡ የሚችሉት እንዴት ሊሆን ይችላል?
4 በቤተሰብ ውስጥ የሐሳብና የስሜት ግንኙነት የሚደረግባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። በቃል ሳይነጋገሩ የሐሳብና የስሜት ግንኙነት ማድረግ ይቻላል። ሁለት ሰዎች ፊት ለፊት በመተያየት ብቻ ሐሳብ ለሐሳብ ሊገናኙ ይችላሉ። አብሮ መሆን የአሳቢነትን መንፈስ ሊያስተላልፍ ይችላል። የትዳር ጓደኞች ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት ከሌለ በስተቀር ረዘም ላለ ጊዜ ተለያይተው መቆየት የለባቸውም። ባልና ሚስት በጋብቻ ማሠሪያ ውስጥ ባላቸው የተቀራረበ ግንኙነት በመደሰት አንዳቸው ሌላውን ሊያስደስቱ ይችላሉ። ምንም ሳይናገሩ ከሰዎችም ጋር ይሁን ለብቻቸው በሚሆኑበት ጊዜ እርስ በርሳቸው በመፈቃቀርና በመከባበር፣ በአለባበሳቸውና በጠባያቸው ተገቢ ባሕርይ በማሳየት አንዳቸው ለሌላው ጥልቅ አድናቆት እንዳላቸው ሊገልጹ ይችላሉ። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን ይህንን በሚከተሉት ቃላት ገልጾታል፦ “ምንጭህ ብሩክ ይሁን፤ ከጉብዝናህም ሚስት ጋር ደስ ይበልህ።”—ምሳሌ 5:18
5, 6.ባሎች ከሚስቶቻቸው ጋር የሐሳብ ግንኙነት የማድረጉን አስፈላጊነት ሊያስቡበት የሚገባው ለምንድን ነው?
5 የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ አንዱ ለፍላፊ ሌላው ደግሞ አዳማጭ መሆንን ሳይሆን እርስ በርስ መነጋገር፣ መወያየት የሐሳብ ልውውጥ ማድረግን ይጠይቃል። ስሜትን በመግለጽ በኩል ከወንዶች ይልቅ አንዳንድ ሴቶች የተሻሉ ቢሆኑም ባሎች ዝምተኛ መሆን ይኖርባቸዋል ማለት አይደለም። የንግግር ግንኙነት አለመኖር በብዙ ትዳሮች ላይ ዋነኛው ችግር እንደሆነ ክርስቲያን ባሎች መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ስለዚህም የሐሳብ መገናኛ መሥመራቸውን ክፍት አድርገው ለማቆየት ተግተው መሥራት ይኖርባቸዋል። በእርግጥ ይህን ማድረግ የሚችሉት እነርሱና ሚስቶቻቸው ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን 5:25-33 ላይ የሰጠውን መልካም ምክር የሚከተሉ ከሆነ ነው። አንድ ባል ሚስቱን እንደ ገዛ ሥጋው አድርጎ የሚወድድ ከሆነ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለእርስዋም ደኅንነትና ደስታ ያስባል። ይህንንም ለማድረግ የሐሳብ ግንኙነት መኖሩ የግድ አስፈላጊ ነው።
6 አንድ ባል ሚስቴ እንደምወዳትና እንደማደንቃት አውጥቼ ባልናገር እንኳን መገመት ወይም ማሰብ ትችላለች ብሎ ማሰብ የለበትም። በእርግጥ እንደሚወዳት ሊያረጋግጥላት ያስፈልጋል። ለእርስዋ ያለውን አድናቆትና ፍቅር በተለያዩ መንገዶች ሊያሳይ ይችላል። የፍቅር ቃላት በመናገር፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ ስጦታዎችን በመስጠት፣ እንዲሁም እርስዋን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በሚገባ እንድታውቅ በማድረግ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ሚስቱ ራስዋን በተገቢ ሁኔታ በማስዋብ፣ ለቤተሰብዋ ስትል በታታሪነት በመስራት ወይም ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የሙሉ ልብ ድጋፍ በመስጠትና በመሳሰሉት ጉዳዮች ለምታደርገው ጥረት የሚሰማውን አድናቆት መግለጽ ይኖርበታል። እንዲሁም አንድ ባል በ1 ጴጥሮስ 3:7 ላይ ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘ከሚስቱ ጋር በእውቀት ስለመኖር’ የሰጠውን ምክር ለመፈጸም ሲል ሁለቱንም በሚመለከቱ የጋራ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር፣ እርስዋን እንደ ደካማ ዕቃ አድርጎ በማክበር ስሜትዋንና ችግሮችዋን ሊረዳላት ይገባል። —ምሳሌ 31:28, 29
7. አንዲት ሚስት ከባልዋ ጋር ሐሳብ ለሐሳብ የመገላለጥ ምን ግዴታ አለባት?
7 በተመሳሳይ አንዲት ሚስት በኤፌሶን 5:22-24 ላይ ስለ መገዛት የተሰጠውን ምክር ለመፈጸም ስትል ከባልዋ ጋር ያላትን የንግግር ግንኙነት መሥመር ክፍት ስለማድረግ ጉዳይ ማሰብ ያስፈልጋታል። በአነጋገርዋም ሆነ በጠባይዋ ለባልዋ “ጥልቅ አክብሮት” ማሳየት ያስፈልጋታል። የብቻዋን እርምጃ መውሰድ ወይም ፍላጎቶቹን ችላ ማለት አይገባትም። (ኤፌሶን 5:33) ምንጊዜም ቢሆን በእርስዋና በባልዋ መካከል የምሥጢር ውይይት መደረግ ይኖርበታል።—ከምሳሌ 15:22 ጋር አወዳድር
8. የሐሳብ መገናኛ መሥመሮችን ክፍት እንዲሆኑ ሚስቶች ምን ለማድረግ ፈቃደኞች መሆን ይኖርባቸዋል?
8 ከዚህም በላይ አንዲት ሚስት ለራስዋ ማዘንዋን ለማሳየት ስትል በዝምታ ከመሰቃየት መቆጠብ ይኖርባታል። አለመግባባት ካለ ተስማሚ ጊዜ መርጣ ጉዳዩን ገልጣ መናገር ይገባታል። አዎን፣ ከንግሥት አስቴር ትምህርት ውሰድ። ንግሥት አስቴር ለባልዋ ማሳወቅ የሚኖርባት የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነበራት። በጥበብና በዘዴ ወዲያውኑ እርምጃ መውሰድዋ ለአይሁዶች ደኅንነትን አስገኝቶአል። የተጎዳንበት ወይም የምንጎዳበት ሁኔታ ካለ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ለራሳችንም ሆነ ለትዳር ጓደኛችን በጣም ጠቃሚ ነው። ዘዴና አምላካዊ የሆነ የተጫዋችነት ባሕርይ ከኖረ እርስበርስ ለመነጋገርና ለመወያየት ቀላል ይሆናል።— አስቴር 4:15 እስከ 5:8
9. የሐሳብ ግንኙነት በማድረግ ረገድ ማዳመጥ ምን ሚና አለው?
9 የንግግር መሥመርን ክፍት ለማድረግ አንዱ ሲናገር ሌላው ማዳመጥና ገና ያልተነገረውን ነገር ልብ ለማለት ጥረት ማድረግ የሁለቱም ወገን ግዴታ ነው። ይህንንም ለማድረግ እየተናገረ ያለውን በትኩረት ማዳመጥ አስፈላጊ ይሆናል። የተነገረውን ፍሬ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን ስሜቱን ይኸውም የአነጋገሩን ሁኔታ በትኩረት መከታተል አስፈላጊ ነው። ብዙውን ጊዜ ባሎች በዚህ በኩል ጉድለት ይታይባቸዋል። ሚስቶች ባሎቻቸው ሳያዳምጧቸው በመቅረታቸው ሊበሳጩ ይችላሉ። ሚስቶችም ቢሆኑ ወደ መደምደሚያው ዘሎ ከማለፍ ለመራቅ በጥንቃቄ ማዳመጥ ያስፈልጋቸዋል። “ጠቢብ ሰው በማዳመጥ ተጨማሪ ትምህርቶችን ያገኛል።”—ምሳሌ 1:5 አዓት
በወላጆችና በልጆች መካከል ሊኖር የሚገባው የሐሳብና የስሜት ግንኙነት
10. ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በተገቢ ሁኔታ የሐሳብ ግንኙነት እንዲኖራቸው ምን ለማድረግ ፈቃደኞች መሆን ይኖርባቸዋል?
10 ወላጆችና ልጆችም የሐሳብና የስሜት ግንኙነት ለማድረግ የሚቸገሩበት ሁኔታ አለ። ‘ልጅን በሚሄድበት መንገድ ለማሰልጠን’ የሐሳብና የስሜት መገናኛ መስመር መፍጠርን ይጠይቃል። ይህን ማድረግ ‘በዕድሜ በሚገፉበትም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ እንዳይል’ ያስችለዋል። (ምሳሌ 22:6) አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ለዓለም ከሚያስረክቡባቸው ምክንያቶች አንዱ በልጆቹ የጉርምስና ዕድሜ የሐሳብና የስሜት ግንኙነት መቋረጡ ነው። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ዘወትር የሐሳብና የስሜት ግንኙነት የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው በዘዳግም 6:6, 7 ላይ እንደሚከተለው ጎላ ተደርጎ ተገልጿል፦ “እኔ ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው።” አዎን ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ ሊኖራቸው ይገባል። ስለ ልጆቻቸው ሲሉ መስዋዕቶችን ለመክፈል ፈቃደኞች መሆን ይኖርባቸዋል።
11. ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ሊነጋገሩባቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
11 ወላጆች ሆይ፣ ልጆቻችሁን ይሖዋ እንደሚያፈቅራቸው፣ እናንተም እንደዚሁ እንደምታፈቅሯቸው ማስገንዘብ አለባችሁ። (ምሳሌ 4:1-4) ለእነርሱ አእምሮአዊ፣ ስሜታዊ፣ አካላዊና መንፈሳዊ እድገት ስትሉ ምቾታችሁንና ደስታችሁን መስዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች መሆናችሁን እንዲያዩ አድርጉ። ይህን ሁሉ ለማድረግ ራስን በሌላው ቦታ አድርጎ መመልከት ያስፈልጋል። ይህም ወላጆች ነገሮችን በልጆቻቸው አመለካከት የማየት ችሎታ ሊኖራቸው ይገባል ማለት ነው። ወላጆች ስስት የሌለበት ፍቅር ካሳያችኋቸው በእናንተና በልጆቻችሁ መካከል ጠንካራ የአንድነት ማሠሪያ እንዲኖር ልታደርጉ ትችላላችሁ። እንዲሁም ምሥጢራቸውን ለጓደኞቻቸው በማካፈል ፋንታ ለእናንተ እንዲያካፍሉ ታበረታቷቸዋላችሁ።—ቆላስይስ 3:14
12. ወጣቶች ከወላጆቻቸው ጋር በነፃነት መነጋገር የሚገባቸው ለምንድን ነው?
12 በሌላም በኩል ወጣቶች ከወላጆቻችሁ ጋር የሐሳብና የስሜት ግንኙነት የማድረግ ግዴታ አለባችሁ። እነርሱ ያደረጉላችሁን ነገሮች ማድነቃችሁ በእነርሱ ላይ እምነት ለመጣል ይረዳችኋል። የእነርሱ እርዳታና ድጋፍ ያስፈልጋችኋል። ከእነርሱ ጋር በነፃነት የምትነጋገሩና ሐሳብ የምትለዋወጡ ከሆነ ይህንን ማድረጉ ቀላል ይሆንላቸዋል። ለምን የዕድሜ ዕኩዮቻችሁን ዋነኛ የምክር ምንጭ ታደርጋላችሁ? እኩዮቻችሁ ከወላጆቻችሁ ጋር ሲነፃፀሩ ምንም ያደረጉላችሁ ነገር የለም። ከእናንተ የተሻለ የሕይወት ተሞክሮ የላቸውም። የጉባኤ አባሎች ካልሆኑ ደግሞ ለዘላቂ ደኅንነታችሁ አያስቡም።
በጉባኤ ውስጥ ካሉት ጋር የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ
13, 14. በክርስቲያኖች መካከል ጥሩ የንግግር ግንኙነት ስለማድረግ የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?
13 ሌላው ተፈታታኝ ሁኔታ በጉባኤው ውስጥ ካሉት ወንድሞቻችሁ ጋር ያላችሁን የሐሳብና የስሜት መገናኛ መሥመር ሁልጊዜ ክፍት ማድረጉ ነው። ‘መሰብሰባችንን’ እንዳንተው ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል። የምንሰበሰበው ለምን ዓላማ ነው? “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ለመነቃቃት” ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ እርስበርስ መነጋገርና ሐሳብ ለሐሳብ መለዋወጥ ያስፈልጋል። (ዕብራውያን 10:24, 25) ስሜታችሁን የጎዳ ሰው ቢኖር ከስብሰባ ለመቅረት ምክንያት ሊሆናችሁ አይገባም። በማቴዎስ 18:15-17 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ኢየሱስ የሰጠውን ምክር እንደ መሠረታዊ ሥርዓት አድርጋችሁ በመከተል የንግግር ግንኙነት የምታደርጉበትን መሥመር ክፍት አድርጉ። ጎድቶኛል ብላችሁ ከምታስቡት ሰው ጋር ተነጋገሩ።
14 ከአንድ ወንድም ጋር ቅራኔ በሚፈጠርበት ጊዜ በቆላስይስ 3:13 ላይ የሚገኘውን “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር ተባባሉ፤ [ይሖዋ በነፃ (አዓት)] ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተከተል። ይህ ምክር አንድን ሰው ከማኩረፍ ይልቅ እርሱን ማነጋገር እንደሚያስፈልግ የሚያሳስብ ነው። እንዲሁም አንድ ሰው ስሜቱን ቀዝቀዝ እንዳደረገብህ ሆኖ ከተሰማህ በማቴዎስ 5:23, 24 ላይ የሚገኘውን ምክር ተከተል። ከወንድምህ ጋር ተነጋግረህ ሰላም ለመፍጠር ሞክር። ይህን ለማድረግ ፍቅርና ትህትና ይጠይቅብህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ለራስህም ሆነ ለወንድምህ ስትል የኢየሱስን ምክር የመከተል ግዴታ አለብህ።
ምክርና ማበረታቻ
15. ክርስቲያኖች ምክር ለመስጠት በሚችሉበት ቦታ ላይ ሲሆኑ ምክርን ከመስጠት ወደኋላ ማለት የማይኖርባቸው ለምንድን ነው?
15 እርስ በርስ የመነጋገርና ሐሳብ ለሐሳብ የመገላለጥ ግዴታ በገላትያ 6:1 ላይ የሚገኘውን የጳውሎስ ምክር መከተልን ይጨምራል፦ “ወንድሞች ሆይ፣ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፣ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ።” የራሳችንን አቅምና ሁኔታ ማወቃችን አንድ ሰው በአነጋገራችን ወይም በጠባያችን የሠራነውን ስህተት ሲጠቅስልን እንድንቀበለው ሊያደርገን ይገባል። በእርግጥ ሁላችንም መዝሙራዊው ዳዊት “ጻድቅ በምሕረትህ ይገሥጸኝ፣ ይዝለፈኝም፤ የኃጢአተኛ ዘይት ግን ራሴን አይቅባ” ብሎ በጻፈበት ጊዜ የነበረው ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል። (መዝሙር 141:5) በተለይ ሽማግሌዎች የግል አስተሳሰባቸውን ይዘው ድርቅ ከማለት ይልቅ እርማቶችን ለመቀበል ዝግጁ በመሆንና ‘የወዳጅ ማቁሰል የታመነ’ መሆኑን በማስታወስ በትህትና ረገድ ቀዳሚ ምሳሌዎች መሆን ይኖርባቸዋል።—ምሳሌ 27:6
16. ወጣት ንግግር አቅራቢዎች ምን ዓይነት ምክር መቀበል ይኖርባቸዋል?
16 ወጣቶች ገንቢ የሆነ ምክርና ሐሳብ ሊሰጡአቸው ከሚችሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ምክርንና መመሪያን ቢጠይቁ የጥበብና አቅምን የማወቅ መንገድ ነው። ሽማግሌዎችም ቢሆኑ ከዚህ ሊጠቀሙ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ሽማግሌ በሰጠው ንግግር በራእይ 7:16, 17 ላይ የተገለጹት ያለመራብና ያለመጠማት ተስፋዎች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለሌሎች በጎች የሚፈጸሙላቸው ተስፋዎች እንደሆኑ ገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ተስፋ በአብዛኛው የሚፈጸመው በአሁን ዘመን እንደሆን ተገልጾአል። (ራእይ—ታላቁ መደምደሚያ ቀርቧል! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 126-8 ተመልከት) ንግግሩን ያዳምጥ የነበረ አንድ ሽማግሌ ነገሩን ሊጠቅስለት እንደሚያስፈልግ ተሰማው። ሆኖም እርሱ ከመናገሩ በፊት ንግግሩን የሰጠው ወንድም ራሱ ስልክ ደውሎ ንግግሩን የሚያሻሽልበት ሐሳብ እንዲሰጠው ጠየቀው። አዎን፣ ምክር ለመቀበል ፍላጎት እንዳለን በመናገር ሊረዱን ለሚፈልጉት ሰዎች ነገሩን ቀላል እናድርግላቸው። ስሜታችን በቀላሉ የሚጎዳ ወይም አትንኩኝ ባይ አንሁን።
17. የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ወንድሞቻችንን ለማነጽ ሊያገለግል የሚችለው እንዴት ነው?
17 ንጉሥ ሰለሞን ለውይይታችን የሚጠቅም አንድ መሠረታዊ ሥርዓት ገልጿል። እርሱም እንዲህ አለ፦ “ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል፣ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን።” (ምሳሌ 3:27) ወንድሞቻችንን የመውደድ ዕዳ አለብን። ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፣ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና” ብሏል። (ሮሜ 13:8) ስለዚህ የማጽናኛ ቃሎችን በመናገር ለጋሶች ሁኑ። አንድ ወጣት ዲያቆን ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ንግግር ሰጥቶ ከሆነ አመስግኑት። አንዲት እህት በቲኦክራቲክ አገልግሎት ትምህርት ቤት የተሰጣትን ክፍል ለማቅረብ የምትችለውን ሁሉ ጥረት አድርጋ ከሆነ ባደረገችው ጥረት ምን ያህል እንደተደሰታችሁ ንገሩአት። አብዛኛውን ጊዜ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የተቻላቸውን ያህል ለማድረግ ይጣጣራሉ። ፍቅር የተሞላበት የአድናቆት ቃል ሲሰሙ ደግሞ ይበረታታሉ።
18. ከልክ በላይ በራስ የመመካት ሁኔታ በሚታይበት ጊዜ ምን ማድረጉ ደግነት ነው?
18 በሌላው በኩል ደግሞ አንድ ወጣት ንግግር አቅራቢ ብዙ ችሎታ ሊኖረው ይችላል፤ ሆኖም ወጣት በመሆኑ ምክንያት ከሚገባው በላይ በራሱ ሊመካ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ምን ዓይነት ማስገንዘቢያ ሊሰጠው ያስፈልጋል? አንድ የበሰለ ሽማግሌ ባቀራረቡ ላይ ለሚታዩት ጥሩ ነጥቦች ቢያመሰግነውና ለወደፊቱ ግን የራስን አቅምንና ሁኔታ የማወቅን ባሕርይ እንዴት ሊኮተኩት እንደሚችል አንዳንድ ሐሳቦችን ቢያቀርብለት ደግነት አይሆንምን? እንደዚህ ያለው ማስገንዘቢያ ወንድማዊ ፍቅር እንዳለ ያሳያል፣ ወጣቶችም እንዲህ ዓይነቱን ባሕርይ ሥር ሳይሰድ አስቀድመው እንዲያስወግዱት ይረዳቸዋል።
19. ሽማግሌዎችና የቤተሰብ ራሶች ሐሳባቸውን የሚገልጹ መሆን የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
19 ሽማግሌዎች ጠቃሚ ስለሆኑ ጉዳዮች እርስ በርሳቸው ሐሳብ ይለዋወጣሉ፣ ለጉባኤውም እንዲህ ዓይነቱን ሐሳብ ያስተላልፋሉ። እርግጥ ከፍርድ ጉዳዮች ጋር ግንኙነት ያላቸውን በምሥጢር የሚያዙ ጉዳዮች ከመግለጥ ይጠነቀቃሉ። ሆኖም ከመጠን በላይ ምሥጢረኛ መሆን አለመተማመንንና ተስፋ መቁረጥን አስከትሎ የጉባኤውን ወይም የቤተሰብን ሞቅ ያለ መንፈስ ሊጎዳ ይችላል። ለምሳሌ ያህል ሁሉም ሰው የሚያንጽ ዜና ቢሰማ ይደሰታል። ልክ ሐዋርያው ጳውሎስ መንፈሳዊ ስጦታን ለማካፈል እንደተመኘ ሁሉ ሽማግሌዎችም ለሌሎች የሚያንጹ ሐሳቦችን ለማስተላለፍ መጓጓት ይኖርባቸዋል።—ምሳሌ 15:30፤ 25:25፤ ሮሜ 1:11, 12
20. የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት የሚያብራራው የትኛውን የሐሳብ ግንኙነት መስክ ነው?
20 አዎን፣ እርስበርስ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ በክርስቲያን ጉባኤም ሆነ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚህም በላይ በጣም አስፈላጊ የሚሆንበት ሌላ ክልል አለ። ይህም የክርስቲያን አገልግሎት ክልል ነው። በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት በዚህ በጣም አስፈላጊ በሆነ ሥራ ላይ ሐሳባችንን የመግለጥና የመነጋገር ችሎታችንን ልናሻሽል የምንችልባቸውን መንገዶች እንመረምራለን።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ በቤተሰብ መካከል የሚፈጠረውን ተደጋጋሚ መሰናክል ለማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?
◻ ባሎችና ሚስቶች ሐሳብ ለሐሳብ ለመለዋወጥ የሚያጋጥማቸውን ተፈታታኝ ሁኔታ ማሸነፍ የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ ወላጆችና ልጆች የትውልድ መራራቅን ሊያስወግዱ የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ በጉባኤና በቤተሰቦች ውስጥ ያለው የንግግር ግንኙነት የሚያንጽ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥሩ የሐሳብና የስሜት ግንኙነት የቤተሰብ ደኅንነትንና ደስታን ያስገኛል