የእውነተኛ ደስታ ‘አዘገጃጀት መመሪያ’
ግሩም ጣዕም ያለው ምግብ ለማዘጋጀት ጥሩ የምግብ አዘገጃጀት መመሪያና የተዋጣለት የወጥ ቤት ሠራተኛ ያስፈልጋሉ! ስለ ደስታም ስናነሳ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ደስታ፣ በሕይወታችን ውስጥ የሚከሰቱ የተለያዩ ነገሮች ድምር ውጤት እንጂ አንድን ሁኔታ ብቻ ተከትሎ የሚመጣ ስሜት አይደለም። ደስታ ከሚያስገኙልን ነገሮች መካከል ሥራ፣ ጨዋታ፣ ከቤተሰብና ከጓደኛ ጋር የምናሳልፈው ጊዜ እንዲሁም መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ይገኙበታል። ከዚህ ስሜት ጋር እምብዛም ግንኙነት ያላቸው የማይመስሉ እንደ አስተሳሰብ፣ ምኞትና የሕይወት ግቦች ያሉ ነገሮችም ለደስታ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ።
ደስ የሚለው ነገር የእውነተኛውን ደስታ ‘አዘገጃጀት መመሪያ’ ራሳችን ማውጣት አያስፈልገንም። ለምን? ምክንያቱም ፈጣሪያችን ድንቅ የሆነ የመመሪያ መጽሐፍ ሰጥቶናል፤ ይህ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በ2,377 ቋንቋዎችና ቀበሌኛዎች ተተርጉሟል። በዓለም ላይ እንዲህ ባለ መጠን የታተመ ሌላ ጽሑፍ የለም!
መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በመሰለ አስገራሚ መጠን መሰራጨቱ፣ አምላክ የሁሉም ሰው ደስታና መንፈሳዊ ደኅንነት እንደሚያሳስበው ያረጋግጣል። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35፤ 17:26, 27) በቃሉ ውስጥ “እኔ . . . የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ . . . ነኝ” ብሏል። ትእዛዙን ካከበርንም ሰላማችን “እንደ ወንዝ” እንደሚሆን ቃል ገብቶልናል።—ኢሳይያስ 48:17, 18
ይሖዋ የገባው ይህ ቃል ባለፈው ርዕስ ላይ የተጠቀሱትን “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት ያስታውሰናል። (ማቴዎስ 5:3 NW) እዚህ ላይ የተጠቀሰው መንፈሳዊነት ሃይማኖተኛ መስሎ መታየት ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊነታችን በመላ አኗኗራችን ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። እንዲሁም አምላክ እኛ ራሳችንን ከምናውቀው በላይ እንደሚያውቀን በመገንዘብ እርሱን ለማዳመጥና ከእርሱ ለመማር ፈቃደኛ መሆናችንን ያንጸባርቃል። ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ያጠና ኤረል የተባለ ሰው “መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ እንዳምን ያደረገኝ ከሁሉ የሚበልጠው ምክንያት በውስጡ ያሉትን ትምህርቶች በሥራ ላይ ማዋል የሚያስገኘው መልካም ውጤት ነው!” ብሏል። ለምሳሌ ያህል ቁሳዊ ሀብትንና መዝናኛን እንደማሳደድ ስላሉት ጉዳዮች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ግሩም ምክር እንመልከት።
ስለ ገንዘብ የተሰጠ ጠቃሚ መመሪያ
ኢየሱስ “የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ” አይደለም ብሏል። (ሉቃስ 12:15) አዎን፣ በተለይ በአምላክ ዓይን እውነተኛ ማንነትህ የሚለካው ባንክ ውስጥ ባለህ የገንዘብ መጠን አይደለም። እንዲያውም ሀብት ማሳደድ በአብዛኛው ለጭንቀት ይዳርጋል፤ ይህ ደግሞ ደስታ የሚያሳጣ ከመሆኑም በላይ በጣም አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች መዋል የሚገባውን ጊዜ ይሰርቃል።—ማርቆስ 10:25፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:10
በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ሪቻርድ ራየን የተባሉ የሥነ ልቦና ፕሮፌሰር እንደገለጹት፣ ሰዎች በቁሳዊ ነገሮች እርካታ ለማግኘት በጣሩ መጠን የባሰ ደስታቸውን እያጡ ይሄዳሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊው ሰሎሞን ይህንን በተመለከተ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም” ብሏል። (መክብብ 5:10) ይህን ሁኔታ ትንኝ በሚነድፈን ጊዜ ሰውነታችንን ሲያሳክከን ከሚከሰተው ነገር ጋር ማመሳሰል ይቻላል፤ የተነደፈውን ቦታ ባከክነው ቁጥር የባሰ እያሳከከን ስለሚሄድ እናቆስለዋለን።
መጽሐፍ ቅዱስ ጠንክረን እንድንሠራና በድካማችን ፍሬ እንድንረካ ያበረታታናል። (መክብብ 3:12, 13) እንዲህ በማድረግ ለራሳችን ያለንን አክብሮት ከፍ ማድረግ እንችላለን፤ ይህ ደስተኛ ለመሆን የሚያስፈልገው ሌላው ዋነኛ ቅመም ነው። እንዲሁም ለሕይወት ጠቃሚ በሆኑ መዝናኛዎች መደሰት እንችላለን። ነገር ግን በገንዘብ ሊገኙ በሚችሉ አንዳንድ ነገሮች መዝናናትና ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ ላይ ያተኮረ ሕይወት መምራት ልዩነት አላቸው።
መዝናኛን በልክ ማድረግ ይገባል
ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት ማዳበራችን ከመዝናኛዎችና ከሌሎች አስደሳች እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ጥቅም እንድናገኝ ያስችለናል። ኢየሱስ ምግብና መጠጥ በተዘጋጀባቸው ግብዣዎች ላይ መገኘት ያስደስተው ነበር። (ሉቃስ 5:29፤ ዮሐንስ 2:1-10) ሆኖም እነዚህ ነገሮች ዋነኞቹ የደስታው ምንጮች አልነበሩም። በጣም ይደሰት የነበረው መንፈሳዊ ነገሮችን በማከናወን ነው፤ ይህም ሌሎች ስለ አምላክና እርሱ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ እንዲማሩ መርዳትን ይጨምራል።—ዮሐንስ 4:34
ንጉሥ ሰሎሞን ደስታ ያስገኛሉ የሚባሉ ነገሮችን ለማየት ሞክሯል። እንዲያውም “በተድላ ውስጥ ተዘፍቄ ራሴን አስደስታለሁ” ብሎ ነበር። ይህ ሀብታም ንጉሥ በደስታ ይዋኝ የነበረው እንዲያው ላይ ላዩን አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ሙሉ በሙሉ ተዘፍቆበት ነበር! ይሁንና ከዚያ በኋላ ምን ተሰማው? “ያም ከንቱ ነበር” በማለት ጽፏል።—መክብብ 2:1 ኒው ኢንግሊሽ ባይብል
ተድላ የሚያሳድዱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የከንቱነት ስሜት የሚሰማቸው ከመሆኑም በላይ እርካታ የላቸውም። እንዲያውም ተመራማሪዎች በተወሰኑ ሰዎች ላይ ጥናት አካሂደው የነበረ ሲሆን ጥናቱ የተካሄደባቸው ሰዎች ትርጉም ያለው ሥራን በመሥራት፣ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግና ከቤተሰብ ጋር ጊዜ በማሳለፍ የሚያገኙት ደስታ ተድላን በማሳደድ ከሚያገኙት ደስታ ልቆ ተገኝቷል።
ለጋስና አመስጋኝ ሁን
ደስተኛ ሰዎች የራስ ወዳድነት ሳይሆን የለጋስነትና ለሌሎች የማሰብ ዝንባሌ አላቸው። ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ከቁሳዊ ነገሮች በተጨማሪ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ለሰዎች መለገስ እንችላለን፤ ይህ ደግሞ በተለይ በቤተሰብ ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ነገር ነው። ባልና ሚስት ትዳራቸውን ጠንካራና አስደሳች ለማድረግ አብረው ጊዜ ማሳለፍ አለባቸው፤ ወላጆችም ልጆቻቸውን ለማነጋገር፣ እንደሚወዷቸው የሚያሳዩ ነገሮችን ለማድረግና ለማሠልጠን በቂ ጊዜ መመደብ ይገባቸዋል። የቤተሰብ አባላት እንዲህ ባሉ መንገዶች ልግስና ካሳዩ የሚሳካላቸው ከመሆኑም በላይ ቤታቸው የደስታ ምንጭ ይሆንላቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ጊዜያቸውንም ይሁን ጉልበታቸውን በመስጠት አሊያም በሌላ መንገድ ሲረዱህ ‘ታመሰግናቸዋለህ?’ (ቈላስይስ 3:15) እንደዚህ ማድረጋችን ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ በጎ ተጽዕኖ የሚኖረው ከመሆኑም በላይ ለራሳችንም ደስታ ይጨምርልናል። አንድ ሰው ከልቡ ቢያመሰግንህ በጣም ደስ አይልህም?
አመስጋኝ መሆን የተደረጉልንን መልካም ነገሮች ለማስተዋልም ይረዳናል። በሪቨርሳይድ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ አንዲት ተመራማሪ፣ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገበት ጥናት የሚያካሂዱባቸው ሰዎች “የምስጋና ማስታወሻ” እንዲያዘጋጁ ማለትም እንዲያመሰግኑ የሚያነሳሷቸውን ነገሮች የሚመዘግቡበት ማስታወሻ እንዲኖራቸው ጠየቋቸው። በጣም የሚገርመው ነገር ጥናት የተደረገባቸው ሰዎች ይበልጥ ደስተኞች ሊሆኑ እንደቻሉ ከስድስት ሳምንታት በኋላ በግልጽ ታየ።
ከዚህ ምን ትምህርት ታገኛለህ? ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ያገኘሃቸውን መልካም ነገሮች አትዘንጋ። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን “ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ . . . በማናቸውም ሁኔታ አመስግኑ” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጣል። (1 ተሰሎንቄ 5:16, 18) ይህን ማሳሰቢያ በሥራ ላይ ለማዋል ግን ያገኘናቸውን መልካም ነገሮች ለማስታወስ ከልብ መጣር እንደሚገባን የተረጋገጠ ነው። ለምን እንዲህ ለማድረግ ግብ አታወጣም?
ፍቅርና ተስፋ—ለደስታ በጣም የሚያስፈልጉ ነገሮች
ሰዎች ከውልደታቸው እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ ፍቅር ይፈልጋሉ የሚለው አነጋገር ትክክል ነው። ሰዎች ፍቅር ካላገኙ ይኮሰምናሉ። ነገር ግን ፍቅር ምንድን ነው? በዛሬው ጊዜ ሰዎች ለቃሉ የፈለጉትን ፍቺ እየሰጡት ያሉ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ በሚከተሉት ውብ ቃላት ይገልጸዋል:- “ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው። ፍቅር አይመቀኝም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፣ በደልን አይቈጥርም። ፍቅር ከእውነት ጋር እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም። ፍቅር ሁልጊዜ ይታገሣል፤ ሁልጊዜ ያምናል፤ ሁልጊዜ ተስፋ ያደርጋል፤ ሁልጊዜ ጸንቶ ይቆማል።”—1 ቆሮንቶስ 13:4-8
እውነተኛ ፍቅር ከራስ ወዳድነት ፍጹም የራቀ ነው! በመሆኑም ከራሱ ይልቅ የሌሎችን ደስታ ያስቀድማል። የሚያሳዝነው እንዲህ ያለው ፍቅር ብርቅ እየሆነ መጥቷል። ኢየሱስም ስላለንበት ሥርዓት ማብቂያ ትንቢት ሲናገር “የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል” ብሏል።—ማቴዎስ 24:3, 12፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ የፍቅር ተምሳሌት የሆነውን ፈጣሪ የሚያዋርድ በመሆኑ ለዘላለም አይቀጥልም! (1 ዮሐንስ 4:8) በቅርቡ አምላክ በጥላቻ የተሞሉ ወይም ስግብግብነት የሚያጠቃቸውን ሰዎች ሁሉ ከምድር ገጽ ያስወግዳል። ከላይ የተጠቀሰውን ዓይነት ፍቅር ለማሳየት የሚጥሩትን ሰዎች ብቻ በሕይወት እንዲኖሩ ያደርጋል። ይህም በምድር ዙሪያ ሰላምና ደስታ እንዲሰፍን ምክንያት ይሆናል። “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ እንደሚፈጸም ምንም አያጠራጥርም።—መዝሙር 37:10, 11
እያንዳንዱን ቀን ‘በሐሤት’ ስትኖር ይታይህ! መጽሐፍ ቅዱስ “በተስፋ ደስተኞች ሁኑ” ማለቱ ምንም አያስገርምም! (ሮሜ 12:12) አምላክ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ስላዘጋጀው አስደናቂ ተስፋ ይበልጥ መማር ትፈልጋለህ? ከሆነ እባክህ የሚቀጥለውን ርዕስ አንብብ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ስለ ስኬት የሚነገሩ ታሪኮች—ምን ያህል እውነት ናቸው?
ችግር ባለበት ቤት ውስጥ ቢያድጉም እንኳ ያጋጠሟቸውን ከባድ መከራዎች ሁሉ አልፈው ባለጸጋ መሆን ስለቻሉ ሰዎች የሚናገሩ በማስረጃ ያልተረጋገጡ ታሪኮችን አልፎ አልፎ እንሰማለን። “አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያሉት ታሪኮች፣ እነዚህ ሰዎች አስከፊ የልጅነት ሕይወት ቢያሳልፉም እንደተሳካላቸው አሊያም ደግሞ እንዲህ ያለ ሕይወት ማሳለፋቸው ያጋጠማቸውን መጥፎ ሁኔታ ታግለው እንዲያሸንፉ እንደረዳቸው ለመግለጽ እንደ ማስረጃ ተደርገው ይጠቀሳሉ” በማለት ሳን ፍራንሲስኮ ክሮኒክል የተባለ ጋዜጣ ደስታን በተመለከተ ባወጣው ዘገባ ላይ ገልጿል። አክሎም እንዲህ ብሏል:- “በጥናት እንደተረጋገጠው፣ እነዚህ ሰዎች እውነተኛ ደስታ እንዳላቸው የተሰጠው ማብራሪያ እውነትነት አጠያያቂ ነው። ያገኙት ነገር ቢኖር ብልጽግና ብቻ ነው።”
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ደስታ ለጥሩ ጤንነት የሚያበረክተው አስተዋጽዖ
ደስታ ፍቱን መድኃኒት ነው። “ደስታ ወይም ከዚህ ስሜት ጋር ተያያዥነት ያላቸው እንደ ተስፋ፣ ብሩህ አመለካከትና እርካታ የመሰሉ አእምሯዊ ሁኔታዎች በልብና በደም ዝውውር ችግር፣ በሳምባና በስኳር በሽታ፣ በደም ግፊት፣ በጉንፋን እንዲሁም በመተንፈሻ አካል ላይኛ ክፍል ኢንፌክሽን የመያዝ አጋጣሚን ሊቀንሱ ወይም በእነዚህ በሽታዎች በእጅጉ ከመጠቃት ሊጠብቁ ይችላሉ” በማለት ታይም መጽሔት ዘግቧል። በተጨማሪም በሆላንድ አገር ባሉ ዕድሜያቸው በገፋ የተወሰኑ ሕሙማን ላይ ከዘጠኝ ለሚበልጡ ዓመታት የተደረገው ጥናት አስደናቂ ውጤት አስገኝቷል! ጥናቱ ደስተኛ መሆንና አዎንታዊ አመለካከት መያዝ የመሞትን አጋጣሚ 50 በመቶ እንደሚቀንስ አረጋግጧል!
የአእምሮ ሁኔታ እንዴት በአካል ላይ ተጽዕኖ እንደሚያደርግ እስከ አሁን ድረስ አልታወቀም። ነገር ግን አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ኮርቲሶል የተባለው ውጥረት የሚያስከትል ሆርሞን በሰውነታቸው ውስጥ በዝቅተኛ መጠን እንደሚገኝ በጥናት ተረጋግጧል፤ ይህ ሆርሞን በሽታ የመከላከል አቅምን እንደሚያሳጣ ይታወቃል።
[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥሩ የምግብ አዘገጃጀት መመሪያ መጠቀም ጣፋጭ ምግብ ለማዘጋጀት እንደሚያስችል ሁሉ መለኮታዊ መመሪያን መታዘዝም ደስታ ያስገኛል