በክርስቲያን አገልግሎት የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ
“እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ ... ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”—ማቴዎስ 28:19
1. ክርስቶስ የሰጠው የትኛው ሥራ ነው የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳየው?
ከላይ የተጠቀሰው ኢየሱስ የሰጠው ሥራ ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ፣ ተመላልሶ መጠይቅ ስናደርግና በሁሉም የመንግሥቱ ስብከት ገጽታዎች ስንካፈል በአገልግሎታችን ከሰዎች ጋር የሐሳብ ግንኙነት የመፍጠር ጥረት የሚጠይቅ አጋጣሚ እንዲኖር ያደርጋል። ይህ ሥራ ስለ ይሖዋ አምላክ፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና አሁን ኢየሱስ እየገዛበት ስላለው መሲሐዊ መንግሥት እውነትን የማሳወቁን ኃላፊነት ይጨምራል።—ማቴዎስ 25:31-33
2. ውጤታማ በሆነ መንገድ የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ምን ያስፈልገናል?
2 ውጤታማ በሆነ መንገድ የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ እኛ ራሳችን ለሌሎች የምናስተላልፈውን መልዕክት ልናምንበት ይገባል። በሌላ አነጋገር ይሖዋ ብቻውን እውነተኛ አምላክ ስለመሆኑ፣ መጽሐፍ ቅዱስም በእርግጥ የአምላክ ቃል ስለመሆኑና የአምላክ መንግሥት ብቸኛዋ የሰው ዘር ተስፋ ስለመሆንዋና ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይገባል። በዚህም መንገድ የምናስተምረው ነገር ከልባችን የመነጨ ይሆናል፣ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠውንም ቀጥሎ ያለውን ምክር የምንከተል እንሆናለን፦ “የእውነትን ቃል በቅንዓት [በትክክል] የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፣ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ።”—2 ጢሞቴዎስ 2:15
ያለ ንግግር የሚደረግ የሐሳብ ግንኙነት
3-5. (ሀ) አንድም ቃል ሳንናገር መልዕክት ማስተላለፍ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ይህንን የሚያረጋግጡ ምን ተሞክሮዎች አሉ?
3 ብዙውን ጊዜ የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ቃላት ያስፈልጋሉ። ሆኖም ከሰዎች ጋር ከመነጋገራችን በፊትም ቢሆን በሐሳብና በስሜት ከእነርሱ ጋር ግንኙነት እንደምናደርግ የተረጋገጠ ነው። እንዴት? በአቋማችንና በአለባበሳችን እንዲሁም በአበጣጠራችን ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት አንደ የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህር ቤት ምሩቅ የሆነ ሚስዮናዊ ወደ ተመደበበት አገር በመርከብ ይጓዝ ነበር። በባሕር ላይ ለጥቂት ቀናት ከተጓዙ በኋላ አንድ የማያውቀው ሰው በመርከቡ ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ የተለየ የሆነው ለምን እንደሆነ ጠየቀው። ሚስዮናዊው በውጫዊ መልኩና በጠባዩ በአንድ በሚስብ መንገድ ይኸውም የተለየ አቋም በመያዙና የሚቀረብ ዓይነት ሰው በመሆኑ እንድ መልዕክት አስተላልፎ ነበር። ይህም ሚስዮናዊው ምስክርነት እንዲሰጥ ጥሩ አጋጣሚ ከፍቶለታል።
4 አሁንም እንደገና በመንገድ ላይ በመቆም ለሚተላለፉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ታበረክት የነበረች አንዲት እህት በአጠገብዋ ታልፍ ለነበረች አንዲት ሴት ወዳጃዊ ፈገግታ አሳየቻት። ይህች ሴት ዝም ብላ ወደ ባቡር ጣቢያ የሚወስደውን ደረጃ መውረድ ጀመረች፣ በኋላ ግን አሳቧን ቀየረችና ወደ እህት ተመልሳ በመሄድ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት ጠየቀች። የማረካት ነገር ምን ነበር? የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ እንድትወስድ ጥያቄ ባይቀርብላትም መንገድ ለመንገድ ከምታገለግለው እህት ወዳጃዊ ፈገግታ አግኝታ ነበር።
5 ሦስተኛው ምሳሌ፦ በቡድን የሆኑ ወጣት ምስክሮች በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ ይመገቡ ነበር፤ አንድ የማያውቁት ሰው ወደ ጠረጴዛቸው መጥቶ ለበሉት ምግብ ሲከፍልላቸው በጣም ተገረሙ። ይህን ያደረገው ለምን ነበር? በጠባያቸው በጣም ተደንቆ ነበር። እነዚህ ወጣት ክርስቲያኖች ለእንግዳው ሰው ምንም ቃል ሳይናገሩ አምላክን የሚፈሩ ግለሰቦች መሆናቸውን የሚያሳይ መልዕክት አስተላልፈው ነበር። በግልጽ እንደሚታወቀው በጠባያችን፣ በአለባበሳችንና የወዳጅነት ባሕርይ በማሳየታችን ቃል ከመናገራችን በፊትም ቢሆን ለሰዎች መልዕክት ማስተላለፍ እንችላለን።—ከ1 ጴጥሮስ 3:1, 2 ጋር አወዳድር
መልዕክት ለማስተላለፍ ምክንያቱን እያወያዩ ማስረዳት አስፈላጊ ነው
6. በምክንያት እያወያዩ ማስረዳት የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን በምሳሌ አስረዳ።
6 በቃል ምሥራቹን ለሰዎች ለማስተላለፍ ያልኩትን ተቀበሉ በማለት ሳይሆን ከእነርሱ ጋር ምክንያቱን እያወያዩ ለመነጋገር መዘጋጀት ይኖርብናል። ጳውሎስ የምሥራቹን ሊያካፍላቸው ከሞከራቸው ሰዎች ጋር በምክንያት እያወያየ ያስረዳ እንደነበረ በተደጋጋሚ እናነባለን። (ሥራ 17:2, 17፤ 18:19) የእርሱን ምሳሌ ልንከተል የምንችለው እንዴት ነው? እየተባባሱ የሚሄዱት የዓለም ሁኔታዎች አንዳንዶች ለሰው ዘር የሚያስብ ሁሉን የሚችልና አፍቃሪ የሆነ አምላክ መኖሩን እንዲጠራጠሩ አድርጓቸው ሊሆን ይችላል። ቢሆንም አምላክ ለሁሉም ጊዜ እንዳለው በመግለጽ ምክንያቱን ልናስረዳቸው እንችላለን። (መክብብ 3:1-8) ለምሳሌ ያህል ገላትያ 4:4 አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ልጁን ወደ ምድር እንደላከ ይናገራል። ልጁንም የላከው ይህን እንደሚያደርግ በመጀመሪያ ቃል ከገባ በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ነበር። በተመሳሳይም እርሱ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ሥቃይንና ክፋትን ሁሉ ያስወግዳል። ከዚህም በላይ የአምላክ ቃል ለዚህን ያህል ረጅም ጊዜ አምላክ ክፋት እንዲቀጥል የፈቀደበት አስገዳጅ ምክንያት እንዳለው ያሳያል። (ከዘፀዓት 9:16 ጋር አወዳድር) በእነዚህ ጉዳዮች በምክንያት መወያየት ይህንንም ምክንያታችንን በምሳሌዎችና ጠንካራ በሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎች መደገፍ ቅን የሆኑ ሰዎችን የክፋት መብዛት ይሖዋ የለም ለማለት ወይም ስለ ነገሩ ምንም አይጨነቅም ብሎ ለመከራከር ሊያገለግል እንደማይችል እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል።—ሮሜ 9:14-18
7, 8. በምክንያት እያወያዩ ማስረዳት ከአንድ ወግ አጥባቂ አይሁዳዊ ጋር ለመነጋገር የሚረዳን እንዴት ነው?
7 ምናልባት ከቤት ወደ ቤት ስትሄድ የቤቱ ባለቤት “እኔ አይሁዳዊ ነኝ፤ ምንም ፍላጎት የለኝም” ቢልህ፣ እንዴት አድርገህ ልትቀጥል ትችላለህ? አንድ ወንድም እንደሚከተለው ብሎ በመቅረብ እንደተሳካለት ገልጿል፦ ‘መቼም አምላክ ከተጠቀመባቸው ታላላቅ ነቢያት አንዱ ሙሴ ነው ብለው እንደሚያምኑ እርግጠኛ ነኝ። በዘዳግም 31:29 ላይ “ከሞትሁ በኋላ . . . ካዘዝኋችሁም ፈቀቅ እንድትሉ አውቃለሁና። ክፉ ነገር ያገኛችኋል” ብሎ መናገሩንስ ያውቃሉ? ሙሴ እውነተኛ ነቢይ ስለነበር የተናገራቸው ቃላት እውነት ሆነዋል። እነዚህ ቃላት አምላክ መሲሑን ወደ አይሁዶች በላከው ጊዜ ተፈጽመው ይሆን? አይሁዶችስ እርሱን ያልተቀበሉት በዚህ ምክንያት ይሆን? ምክንያቱ ይህ ሊሆን ይችላል። እንግዲያው ጉዳዩ ይህ ከሆነና እነርሱ ስህተት ሠርተው ከነበረ እርስዎና እኔ ያንኑ ስህተት የምንፈጽምበት ምክንያት ይኖራልን?’
8 በተጨማሪም አይሁዶች በተለይ በዚህ መቶ ዘመን ውስጥ በሕዝበ ክርስትና እጅ መሰቃየታቸውንም ጭምር አስታውስ። ስለዚህ ለቤቱ ባለቤት እኛ በዚህ ተካፋይ አለመሆናችንን ልትገልጽለት ትፈልግ ይሆናል። ለምሳሌ እንዲህ ለማለት ትፈልግ ይሆናል፦ ‘ሂትለር በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የይሖዋ ምስክሮች በአይሁዶች ላይ የተደረገውን አድማ መቃወማቸውን ያውቃሉ? ከዚህም ሌላ “ሃይል ሂትለር” (አዳኛችን ሂትለር ነው) ለማለትና በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ገብቶ ለማገለገል እምቢ ብለው ነበር።’a
9, 10. አንድን በመሠቃያ ሲኦል የሚያምን ሰው ለመርዳት በምክንያት ማወያየት የሚጠቅመው እንዴት ነው?
9 በእሳታማ ሲኦል የሚያምንን አንድን ሰው ለማነጋገር በምትሞክርበት ጊዜ አንድ ግለሰብ በመሠቃያ ሲኦል ውስጥ ለዘላለም የሚሠቃይ ከሆነ የማትሞት ነፍስ አለችው ማለት ነው ብለህ በመጠየቅ ልታወያየው ትችላለህ። በመሠቃያ ሲኦል የሚያምነው ሰው በዚህ በቀላሉ ይስማማል። ቀጥለህ ስለ አዳምና ሔዋን የሚናገረውን የፍጥረት ታሪክ ጥቀስለትና በዚህ ታሪክ ውስጥ ስለማትሞት ነፍስ የተጠቀሰ ነገር እንዳለ በደግነት ጠይቀው። ምክንያት እያቀረብክ ማስረዳትህን በመቀጠል መጽሐፍ ቅዱስ አዳም ነፍስ እንደሆነ ወደሚናገርበት ወደ ዘፍጥረት 2:7 እንዲያተኩር አድርግ። አዳም የሠራው ኃጢአት ስለሚያስከትለው ውጤት አምላክ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህ።” (ዘፍጥረት 3:19) ስለዚህ ነፍስ የነበረው አዳም ወደ አፈር ተመለሰ።
10 በተጨማሪም በዘፍጥረት ታሪክ ውስጥ አምላክ በየትም ቦታ በእሳት ውስጥ ገብቶ ለዘላላም ስለ መሠቃየት እንዳልጠቀሰ እንዲያስተውል ልታደርገውም ትችላለህ። አምላክ አዳም ከተከለከለው ፍሬ እንዳይበላ ባስጠነቀቀው ጊዜ “ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) እዚህ ላይ እሳታማ ሲኦል አልተጠቀሰም። የአዳም ኃጢአት የሚያስከትለው ሞትን ወይም ‘ወደ አፈር መመለስን’ሳይሆን ዘላለማዊ ሥቃይን ቢሆን ኖሮ ከፍትሕ አንፃር አምላክ ይህን በግልጽ አይነግረውም ነበርን? ከሆነ፣ በጥንቃቄና በደግነት የተደረገ ምክንያታዊ ውይይት ቅን የሆነው ግለሰብ የግል እምነቱ የሚጋጭ መሆኑን እንዲመለከት ሊረዳው ይችላል። የአምላክን ቃል እውነት ለሌሎች ስናካፍል በምክንያት እያወያዩ የማስረዳትን አስፈላጊነት አንዘንጋ።—ከ2 ጢሞቴዎስ 2:24-26፤ 1 ዮሐንስ 4:8, 16 ጋር አወዳድር
ውጤታማ በሆነ መንገድ ሐሳብ ለማስተላለፍ የሚያስፈልጉ ባሕርዮች
11-13. ውጤታማ በሆነ መንገድ መልዕክት ለማስተላለፍ ሊረዱን የሚችሉት ክርስቲያናዊ ባሕርዮች የትኞቹ ናቸው?
11 የመንግሥቱን እውነቶች ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተላለፍ ምን ባሕርዮችን መኮትኮት ያስፈልገናል? የኢየሱስ ምሳሌ ስለዚህ ምን ይነግረናል? በማቴዎስ 11:28-30 ላይ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት እናነባለን። በዚህ ላይ ኢየሱስ ከሰዎች ጋር ግንኙነት ለማድረግ ከተጠቀመባቸው ቁልፍ የሆነውን አንዱን ውጤታማ ዘዴ እንመለከታለን። እርሱ የዋህ በልቡም ትሑት ነበር። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እፎይታ የሚያመጣ ሆኖ አግኝተውታል። ሐዋርያው ጳውሎስም ለኤፌሶን ሽማግሌዎች ወደ እነርሱ ከመጣበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ለጌታ እየተገዛ “በትህትና ሁሉ” እንደኖረ ስለነገራቸው ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ነው።—ሥራ 20:19
12 ዘወትር አቅምን የማወቅንና የትህትናን ጠባይ በማሳየታችን ሌሎች ሰዎች እኛንም እፎይታን የምናመጣ ሆነን ያገኙናል፤ ከእነርሱም ጋር ለመነጋገርም ቀላል ይሆንልናል። ከዚህ የተለየ ዓይነት ዝንባሌ ካለን በእኛና ልናነጋግራቸው በምንሞክራቸው ሰዎች መካከል ግድግዳ ሊፈጥር ይችላል። በእርግጥም “ጥበብ አቅማቸውንና ቦታቸውን በሚያውቁ ዘንድ ነች።”—ምሳሌ 11:2 አዓት
13 ውጤታማ በሆነ መንገድ መልዕክቱን ለማስተላለፍ ትዕግሥተኞችና ዘዴኞች መሆን ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በማርስ ኮረብታ ላይ በፊቱ ተሰብስበው ለነበሩት ፈላስፎች ምስክርነት በሚሰጥበት ጊዜ ዘዴኛ እንደነበር የተረጋገጠ ነው። ምሥራቹን እነርሱ ሊረዱት በሚችሉት መንገድ አቀረበላቸው። (ሥራ 17:18, 22-31) ከአድማጮቻችን ጋር በተሳካ ሁኔታ ለመነጋገር ከፈለግን ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች እንደሚከተለው በማለት የሰጠውን ምክር መፈጸም ይገባናል፦ “ንግግራችሁ ጣዕም የለሽ ሳይሆን ሁል ጊዜ በጸጋ ይሁን፤ የምታገኙትን ሰው እንዴት በተሻለ መንገድ እንደምታነጋግሩት ተማሩ።” (ቆላስይስ 4:6 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ንግግራችን ሁልጊዜ ጥሩ ጣዕም ያለው መሆን ይኖርበታል። እንደዚህ ያለው ንግግር የአድማጮቻችንን አእምሮ ይከፍታል፣ ማስተዋል የጎደለው አነጋገር ግን አእምሮአቸውን እንዲዘጉ ያደርጋቸዋል።
14. በተረጋጋ ሁኔታ ማወያየት ለሌሎች መልዕክት ለማስተላለፍ የሚረዳን እንዴት ነው?
14 ሁል ጊዜ የተረጋጋን መስለን ለመታየት እንፈልጋለን። ይህ አድማጫችንን የተረጋጋ እንዲሆን ይረዳዋል። የተዝናኑ ወይም የተረጋጉ መሆን እኔ ብቻ መናገር አለብኝ በማለት ከመጠን በላይ አለመጨነቅ ማለት ነው። ከዚህ ይልቅ ባልተጣደፈ ሁኔታ በመናገርና ወዳጅነትን በሚያሳዩ ጥያቄዎች አድማጮቻችን ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ዕድል እንሰጣቸዋለን። በተለይ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ስንመሰክር ሌላው ሰው እንዲናገር ማበረታታቱ አስተዋይነት ነው። አንድ ምስክር ከአንድ የሮማ ካቶሊክ ቄስ አጠገብ ተቀምጦ በአውሮፕላን ይጓዝ ነበር። ምስክሩ ከአንድ ሰዓት ለሚበልጥ ጊዜ ቄሱን በዘዴ በጥያቄዎች ያዋክበው ነበር። ቄሱም መልስ እየሰጠ አብዛኛውን ጊዜ ይናገር ነበር። ሆኖም በሚለያዩበት ጊዜ ቄሱ አያሌ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወሰደ። እንደዚህ ያለው ትዕግሥት ያለበት አቀራረብ ሌላውን አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ ማለትም ነገሮችን በሌላው ዓይን የማየት ባሕርይ ተግባራዊ እንድናደርግ ይረዳናል።
15, 16. ራስን በሌላው ቦታ ማስቀመጥ ግንኙነት ለማድረግ የሚረዳን እንዴት ነው ?
15 ነገሮችን በሌላው ዓይን ማየት ሲባል ራሳችንን በሌሎች ቦታ ማስቀመጥ ማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከጻፈው ለማየት እንደሚቻለው እርሱ ራስን በሌላው ቦታ የማስቀመጥን ባሕርይ ሙሉ በሙሉ ተገንዝቦ ነበር፦ “ ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን የሚበልጡትን እንድጠቅም እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ። አይሁድንም እጠቅም ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፣ ከሕግ በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ፣ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፣ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንሁ፣ ሕግ የሌላቸውን እጠቅም ዘንድ፣ ያለ እግዚአብሔር ሕግ ሳልኖር ነገር ግን በክርስቶስ ሕግ በታች ሳለሁ፣ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደሌለኝ ሆንሁ፤ ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁ፤ በሁሉም መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ።”—1 ቆሮንቶስ 9:19-22
16 በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስን ለመምሰል ዘዴኞች፣ አስተዋዮችና ጥሩ ተመልካቾች መሆን ይኖርብናል። ራስን በሌላው ቦታ ማስቀመጥ ለአድማጮቻችን እነርሱ በሚያስቡበትና በሚሰማቸው መንገድ እውነት ለማስተላለፍ ይረዳናል። ከቅዱሳን ጽሑፎች ምክንያቱን ማስረዳት የተባለው መጽሐፍ በዚህ በኩል ብዙ እርዳት ይሰጠናል። ወደ አገልግሎት በምትሄድበት ጊዜ ሁሉ አይለይህ።
ፍቅር—የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ይረዳል
17. ከሁሉም የክርስቲያን ባሕርዮች እውነትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተላለፍ በጣም ጠቃሚ የሆነው የትኛው ነው? የሚገለጸውስ እንዴት ነው?
17 መልዕክት ለሌሎች በማስተላለፍ በኩል ውጤታማ ግንኙነት ለማድረግ የአስተሳሰብ ትሕትና፣ ትዕግሥትና ራስን በሌላው ቦታ ማስቀመጥ አስፈላጊ ናቸው። ከሁሉም በላይ ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር የሌሎችን ልብ በመንካት እንዲሳካልን ይረዳናል። ኢየሱስ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም” ለነበሩ ሰዎች አዝኖላቸው ነበር። ኢየሱስ “ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” ብሎ እንዲናገር ያነሣሣው ፍቅር ነበር። (ማቴዎስ 9:36፤ 11:28) እኛም ሰዎች እረፍት እንዲያገኙና በሕይወት መንገድ ላይ እንዲጓዙ የምንረዳው ስለምናፈቅራቸው ነው። እኛ የያዝነው የፍቅር መልዕክት ነው፤ ስለዚህ በፍቅራዊ መንገድ መናገራችንን እንቀጥል። ይህ ፍቅር በወዳጃዊ ፈገግታ፣ በደግነትና በጨዋነት፣ በደስታና በግለት ይገለጣል።
18. ጳውሎስ ጌታውን እንደመሰለ እኛም እርሱን ልንመስል የምንችለው እንዴት ነው?
18 በዚህ በኩል ሐዋርያው ጳውሎስ ጌታውን ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ነው። ብዙ ጉባኤዎችን በማቋቋም ያን ያህል የተሳካለት ለምን ነበር? በነበረው ቅንዓት ምክንያት ነውን? አዎን ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ብቻ ሳይሆን ባሳየው ፍቅርም ምክንያት ነው። በተሰሎንቄ ተቋቁሞ የነበረውን አዲስ ጉባኤ በተመለከተ የተናገረውን የሚከተለውን የፍቅር መግለጫ ንግግር ልብ በሉ፦ “ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፣ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፣ እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፣ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና።” ጳውሎስን መምሰል ከሌሎች ጋር የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ በምናደርገው ጥረት ይረዳናል።—1 ተሰሎንቄ 2:7, 8
19. ለስብከቱ ጥሩ ምላሽ የማይሰጥ ክልል ተስፋ ሊያስቆርጠን የማይገባው ለምንድን ነው?
19 ከሌሎች ጋር የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ የምንችለውን ሁሉ ካደረግን በኋላ ማግኘት የነበረብንን ውጤት ሳናገኝ ብንቀር ተስፋ መቁረጥ ይኖርብናልን? በፍጹም አይኖርብንም። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (የይሖዋ ምስክሮች የቀድሞ ስም ነው) ሰዎች እውነት እንዲቀበሉ በእንግሊዝኛ ሦስት h(ኤች)የተባለው ፊደል እንዲኖራቸው ያስፈልጋል ይሉ ነበር። ይህም ሲባል honest፣ humble፣ እና hungry ወይም ሐቀኛ፣ ትሑትና የተራቡ መሆን ይኖርባቸዋል ማለት ነው። ቅንነት የጎደላቸው፣ ሐቀኛ ያልሆኑ ሰዎች ለእውነት ጥሩ አመለካከት ይኖራቸዋል ብለን ለመጠበቅ ወይም ጠማማና ኩሩ የሆኑ ግለሰቦች ምሥራቹን ይሰማሉ ብለን ለመጠበቅ አንችልም። ከዚህም በተጨማሪ አንድ ግለሰብ በመጠኑ የሐቀኝነትና የትሕትና ባሕርይ ቢኖረውም በመንፈሳዊ የተራበ ካልሆነ እውነትን መቀበሉ የማይመስል ነው።
20. ጥረታችን ሁሉ ከንቱ አልቀረም ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?
20 በክልልህ ውስጥ የምታገኛቸው አብዛኞቹ ሰዎች ከሦስቱ h (ኤች) ውስጥ አንዱ ወይም ሁለቱ እንደሚጎድላቸው አያጠራጥርም። ነቢዩ ኤርምያስ ተመሳሳይ ነገር አጋጥሞት ነበር። (ኤርምያስ 1:17-19፤ ከማቴዎስ 5:3 ጋር አወዳድር) ያም ሆኖ ግን ጥረታችን ከንቱ አይሆንም። ለምን? ምክንያቱም የይሖዋን ስምና መንግሥት አሳውቀናል። በስብከታችንና በግንባር ቀርበን በማነጋገራችን ክፉዎችን እናስጠነቅቃለን። (ሕዝቅኤል 33:33) እንዲሁም እውነትን ለሌሎች ለማስተላለፍ በምናደርገው ጥረት ራሳችንን የምንጠቅም መሆናችንን በፍጹም አትርሳ። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) እምነታችን ጠንካራ እንደሆነ እንዲቀጥልና የመንግሥት ተስፋችንም ብሩሕ እንዲሆን እናደርጋለን። ከዚህም በላይ ጽኑ አቋማችንን እንጠብቃለን፣ በዚህም ልቡን ደስ እንዲለው በማድረግ የይሖዋ አምላክን ስም እንቀድሳለን።—ምሳሌ 27:11
21. ለማጠቃለል ያህል ምን ሊባል ይቻላል?
21 ለማጠቃለል፦ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ መልዕክትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተላለፍ ማለት ነው። የሐሳብ ግንኙነት የማድረግ ጥበብ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፤ ግንኙነት በሚቋረጥበት ጊዜም ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል። ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ዋነኞቹ ግንኙነት ፈጣሪዎች መሆናቸውንና ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘመናችን አንድ የመገናኛ መሥመር እንዳቋቋመ ተመልክተናል። በተጨማሪም በሰውነት አቋማችንና በጠባያችን ለሌሎች መልዕክት በማስተላለፍ የሐሳብና የስሜት ግንኙነት ለማድረግ እንደምንችል ተመልክተናል። በምክንያት እያወያዩ ነገሮችን ማስረዳት ከሰዎች ጋር ለመነጋገር በምናደርገው ሙከራ ከፍተኛ ሚና እንዳለውና ውጤታማ በሆነ መንገድ ግንኙነት ለማድረግ አቅማችን የምናውቅና ትሑቶች መሆን እንደሚያስፈልገን፣ ራስን በሌላው ቦታ የማስቀመጥን ባሕርይ እንድናሳይ፣ ትዕግሥተኞች እንድንሆንና ከሁሉም በላይ ደግሞ በፍቅር ከተሞላ ልብ መቀስቀስ እንዳለብን ተምረናል። እነዚህን ባሕርዮች ከኮተኮትንና የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን ከተከተልን የተሳካልን የሐሳብ ግንኙነት አድራጊ ክርስቲያኖች እንሆናለን።—ሮሜ 12:8-11
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የአይሁድ እምነት ተከታዮችንና ሌሎችን ስለማነጋገር ተጨማሪ ሐሳቦችን ለማግኘት ከቅዱሳን ጽሑፎች ምክንያቱን ማስረዳት የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 21-24 ተመልከት።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ቃል ከመነገሩ በፊት መልዕክት ማስተላለፍ የሚጀመረው በምን መንገድ ነው?
◻ ምክንያቱን ውጤታማ በሆነ መንገድ በማወያየት ግንኙነት ስለማድረግ የተጠቀሱ አንዳንድ ምሳሌዎች ምንድን ናቸው?
◻ ኢየሱስ ክርስቶስን ጳውሎስ ውጤታማ በሆነ መንገድ ግንኙነት ለማድረግ ያስቻሏቸው የትኞቹ ጠባዮች ናቸው?
◻ የሚገኙት ውጤቶች ዝግተኞች ቢሆኑ ተስፋ መቁረጥ የማያስፈልገን ለምንድን ነው?