የጥናት ርዕስ 10
‘አሮጌውን ስብዕና ገፈህ መጣል’ ትችላለህ
“አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፋችሁ ጣሉ።”—ቆላ. 3:9
መዝሙር 29 እንደ ስማችን መኖር
ማስተዋወቂያa
1. መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከመጀመርህ በፊት ሕይወትህ ምን ይመስል ነበር?
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከመጀመርህ በፊት ሕይወትህ ምን ይመስል ነበር? ብዙዎቻችን ያንን ሕይወታችንን ማሰብ እንኳ አንፈልግም። አስተሳሰባችንና ስብዕናችን የተቀረጸው በዚህ ሥርዓት እሴቶች ማለትም ዓለም ትክክል እና ስህተት ብሎ ባወጣቸው መሥፈርቶች ነበር። “በዓለም ውስጥ ያለተስፋና ያለአምላክ” እንኖር ነበር። (ኤፌ. 2:12) መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ግን ይህ ሁሉ ታሪክ ሆነ!
2. መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ምን ተገነዘብክ?
2 መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና የሰማዩ አባትህ በጣም እንደሚወድህ ተማርክ። ይሖዋን ለማስደሰት እንዲሁም የእሱን አገልጋዮች ያቀፈው ቤተሰብ አባል ለመሆን በአኗኗርህና በአመለካከትህ ላይ ትልቅ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ተገነዘብክ። በሕይወትህ ውስጥ ላቅ ያሉትን የእሱን መሥፈርቶች መከተል እንዳለብህ አወቅህ።—ኤፌ. 5:3-5
3. በቆላስይስ 3:9, 10 መሠረት ይሖዋ ምን እንድናደርግ ይፈልጋል? በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
3 ፈጣሪያችንና ሰማያዊ አባታችን የሆነው ይሖዋ፣ የቤተሰቡ አባላት ሊያሳዩት የሚገባውን ምግባር የመወሰን መብት አለው። ደግሞም ከመጠመቃችን በፊት “አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ [ገፈን ለመጣል]” ጥረት እንድናደርግ ይጠብቅብናል።b (ቆላስይስ 3:9, 10ን አንብብ።) ይህ ርዕስ መጠመቅ ለሚፈልጉ ሰዎች የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች ያብራራል፦ (1) ‘አሮጌው ስብዕና’ ምንድን ነው? (2) ይሖዋ አሮጌውን ስብዕና ገፈን እንድንጥለው ያሳሰበን ለምንድን ነው? (3) ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው? ይህ የጥናት ርዕስ የተጠመቅንም ብንሆን የአሮጌው ስብዕና ባሕርያት እንዳያገረሹብን ለመከላከል ይረዳናል።
‘አሮጌው ስብዕና’ ምንድን ነው?
4. ‘አሮጌው ስብዕና’ ያለው ሰው ምን ዓይነት ምግባር ያሳያል?
4 ‘አሮጌው ስብዕና’ ያለው ሰው በጥቅሉ ሲታይ አስተሳሰቡና ድርጊቱ ሥጋዊ ነው። ራስ ወዳድ፣ ግልፍተኛ፣ ምስጋና ቢስና ኩሩ ሊሆን ይችላል። ፖርኖግራፊ እንዲሁም የብልግና እና የዓመፅ ፊልሞች ማየት ያስደስተዋል። ይህ ሰው አንዳንድ ጥሩ ባሕርያት እንዳሉት የታወቀ ነው፤ በተናገረው ወይም ባደረገው መጥፎ ነገር የሚጸጸትበት ጊዜም ይኖራል። ያም ሆኖ የአስተሳሰብና የምግባር ለውጥ ለማድረግ ተነሳሽነቱ የለውም።—ገላ. 5:19-21፤ 2 ጢሞ. 3:2-5
5. አሮጌውን ስብዕና ሙሉ በሙሉ ገፈን መጣል እንችላለን? አብራራ። (የሐዋርያት ሥራ 3:19)
5 ፍጹማን አይደለንም፤ በመሆኑም ማናችንም ብንሆን መጥፎ ሐሳቦችንና ምኞቶችን ከልባችንና ከአእምሯችን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አንችልም። በኋላ ላይ የሚጸጽተንን ነገር የምናደርግበት ወይም የምንናገርበት ጊዜ አለ። (ኤር. 17:9፤ ያዕ. 3:2) ያም ቢሆን አሮጌውን ስብዕና ገፈን መጣላችን ሥጋዊ አስተሳሰቦችና ልማዶች በእኛ ላይ ኃይል እንዳይኖራቸው ያደርጋል። ከዚያ በኋላ ስብዕናችን ይቀየራል።—ኢሳ. 55:7፤ የሐዋርያት ሥራ 3:19ን አንብብ።
6. ይሖዋ የአሮጌውን ስብዕና መጥፎ ሐሳቦችና ልማዶች ገፈን እንድንጥል የሚያሳስበን ለምንድን ነው?
6 ይሖዋ መጥፎ ሐሳቦችንና ልማዶችን እንድናስወግድ የሚያሳስበን በጣም ስለሚወደን ነው፤ በሕይወታችን ደስተኛ እንድንሆንም ይፈልጋል። (ኢሳ. 48:17, 18) ለመጥፎ ምኞቶች እጅ የሚሰጡ ሰዎች ራሳቸውንም ሆነ የሚወዷቸውን ሰዎች እንደሚጎዱ ያውቃል። መዘዙ ለእኛም ሆነ ለሌሎች መትረፉ ያሳዝነዋል።
7. በሮም 12:1, 2 መሠረት ያሉን አማራጮች ምንድን ናቸው?
7 ስብዕናችንን ለመቀየር ስንወስን አንዳንድ ወዳጆቻችንና ቤተሰቦቻችን ያፌዙብን ይሆናል። (1 ጴጥ. 4:3, 4) ‘የፈለግከውን የማድረግ መብት እኮ አለህ! ሌሎች እንዲመሩህ ለምን ትፈቅዳለህ?’ ይሉን ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የይሖዋን መሥፈርቶች የማይቀበሉ ሰዎችም በሌሎች ተጽዕኖ ሥር ናቸው። በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም እንዲቀርጻቸው እየፈቀዱ ነው። (ሮም 12:1, 2ን አንብብ።) ሁላችንም ያሉን አማራጮች ሁለት ናቸው፦ አሮጌውን ስብዕና ለብሰን ለመቀጠል ከመረጥን በኃጢአትና በሰይጣን ዓለም ቁጥጥር ሥር እንሆናለን። ሌላኛው አማራጭ ደግሞ ይሖዋ እንዲለውጠንና የተሻለ ስብዕና ለማዳበር እንዲረዳን መፍቀድ ነው።—ኢሳ. 64:8
አሮጌውን ስብዕና ‘ገፈህ መጣል’ የምትችለው እንዴት ነው?
8. መጥፎ አስተሳሰቦችንና ልማዶችን ለማስወገድ ምን ይረዳናል?
8 ይሖዋ መጥፎ አስተሳሰቦችንና ልማዶችን ለማስወገድ ጊዜና ጥረት እንደሚጠይቅብን ያውቃል። (መዝ. 103:13, 14) ሆኖም በቃሉ፣ በመንፈሱና በድርጅቱ አማካኝነት ማንነታችንን ለመቀየር የሚያስፈልገንን ጥበብ፣ ብርታትና እርዳታ ይሰጠናል። እስካሁንም ብዙ እንደረዳህ ጥያቄ የለውም። ከዚህ በኋላም አሮጌውን ስብዕና ገፈህ ለመጣልና ለጥምቀት ብቁ ለመሆን ጥረት ማድረግህን መቀጠል ይኖርብሃል፤ ለዚህ የሚረዱህን ጠቃሚ እርምጃዎች እስቲ እንመልከት።
9. የአምላክ ቃል ምን ለማድረግ ይረዳሃል?
9 በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመህ ራስህን በደንብ መርምር። የአምላክ ቃል እንደ መስታወት ነው፤ አስተሳሰብህን፣ አነጋገርህንና ድርጊትህን ለመገምገም ይረዳሃል። (ያዕ. 1:22-25) ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪህና ከሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች ጥሩ ምክር ማግኘት ትችላለህ። ለምሳሌ፣ ጥቅሶችን ተጠቅመው ጠንካራና ደካማ ጎኖችህን ለይተህ እንድታውቅ ይረዱሃል። መጥፎ ልማዶችን ለማስወገድ የሚረዳ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር ከጽሑፎቻችን ላይ እንዴት ማግኘት እንደምትችል ያሳዩሃል። ይሖዋም ቢሆን ሁልጊዜ አንተን ለመርዳት ዝግጁ ነው። ልብህን ስለሚያውቅ ከማንም በተሻለ ሊረዳህ የሚችለው እሱ ነው። (ምሳሌ 14:10፤ 15:11) ስለዚህ ወደ እሱ የመጸለይና ቃሉን በየቀኑ የማጥናት ልማድ አዳብር።
10. ከኢሊ ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን?
10 የይሖዋ መሥፈርቶች እንደሚበጁህ ራስህን አሳምን። ይሖዋ የሚጠይቀን ነገር ሁሉ ለእኛው ጥቅም ነው። የእሱን መሥፈርቶች የሚከተሉ ሁሉ ለራሳቸው አክብሮት ይኖራቸዋል፣ ሕይወታቸው ትርጉም ያለው ይሆናል እንዲሁም እውነተኛ ደስታ ያገኛሉ። (መዝ. 19:7-11) በአንጻሩ ግን የይሖዋን መሥፈርቶች ችላ የሚሉ ሰዎች የሥጋ ሥራዎች የሚያስከትሉትን መዘዝ ያጭዳሉ። ኢሊ የተባለ ሰው የአምላክን መሥፈርቶች መጣስ ስለሚያስከትለው መዘዝ ምን እንዳለ እንመልከት። ኢሊ ያደገው በእውነት ቤት ነው። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ ግን ከመጥፎ ጓደኞች ጋር ገጠመ። በዚህም የተነሳ ዕፅ መውሰድ፣ ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት መምራትና መስረቅ ጀመረ። ኢሊ በጊዜ ሂደት ቁጡና ጠበኛ እየሆነ እንደመጣ ተናግሯል። “በአጭሩ፣ አንድ ክርስቲያን ሊያደርጋቸው እንደማይገባ የተማርኳቸውን ነገሮች በሙሉ እፈጽም ጀመር” በማለት በሐቀኝነት ተናግሯል። ያም ሆኖ ኢሊ ልጅ እያለ የተማራቸውን ነገሮች አልረሳም። ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን እንደገና ማጥናት ጀመረ። መጥፎ ልማዶቹን ለማስወገድ ብርቱ ጥረት ካደረገ በኋላ በ2000 ተጠመቀ። ታዲያ በይሖዋ መሥፈርቶች መመራቱ የጠቀመው እንዴት ነው? ኢሊ “አሁን የአእምሮ ሰላምና ንጹሕ ሕሊና አለኝ” ብሏል።c ይህ ተሞክሮ እንደሚያሳየው የይሖዋን መሥፈርቶች ችላ የሚሉ ሰዎች የሚጎዱት ራሳቸውን ነው። ይሖዋ እንዲህ ያሉ ሰዎችንም ቢሆን ለውጥ እንዲያደርጉ ለመርዳት ፈቃደኛ ነው።
11. ይሖዋ የትኞቹን ነገሮች ይጠላል?
11 ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች ጥላ። (መዝ. 97:10) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ይሖዋ ‘ትዕቢተኛ ዓይን፣ ውሸታም ምላስና ንጹሕ ደም የሚያፈሱ እጆችን’ ይጠላል። (ምሳሌ 6:16, 17) በተጨማሪም “ይሖዋ ዓመፀኞችንና አታላዮችን ይጸየፋል።” (መዝ. 5:6) ይሖዋ በኖኅ ዘመን የነበረውን በዓመፅ የተሞላ ዓለም እንዲያጠፋ ያነሳሳው ለእነዚህ ባሕርያትና ድርጊቶች ያለው ከፍተኛ ጥላቻ ነው። (ዘፍ. 6:13) እስቲ ሌላም ምሳሌ እንመልከት። ይሖዋ ምንም ያልበደሏቸውን ሚስቶቻቸውን በመፍታት ክህደት የሚፈጽሙ ሰዎችን እንደሚጠላ በነቢዩ ሚልክያስ አማካኝነት ተናግሯል። ይሖዋ እንዲህ ያሉ ሰዎች የሚያቀርቡትን አምልኮ አይቀበልም፤ ለድርጊታቸውም ተጠያቂ ያደርጋቸዋል።—ሚል. 2:13-16፤ ዕብ. 13:4
12. ‘ክፉ የሆነውን መጸየፍ’ ሲባል ምን ማለት ነው?
12 ይሖዋ “ክፉ የሆነውን [እንድንጸየፍ]” ይፈልጋል። (ሮም 12:9) ‘መጸየፍ’ የሚለው ቃል ጥልቅ ስሜትን የሚገልጽ ቃል ነው፤ አንድን ነገር አጥብቆ መጥላት፣ በዚያ ነገር መዘግነን ማለት ነው። የተበላሸ ምግብ ብላ ብትባል የሚሰማህን ስሜት ማሰብ ትችላለህ። ገና ስታስበው እንኳ ይዘገንንሃል። ይሖዋ ከሚጠላቸው ነገሮች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ ሐሳቡ እንኳ ሊዘገንነን ይገባል።
13. አስተሳሰባችንን መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው?
13 አስተሳሰብህን ጠብቅ። አስተሳሰባችን በድርጊታችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል። ኢየሱስ ወደ ከባድ ኃጢአት የሚመሩ ሐሳቦችን እንድናስወግድ ያስተማረን ለዚህ ነው። (ማቴ. 5:21, 22, 28, 29) ፍላጎታችን የሰማዩን አባታችንን ማስደሰት እንደሆነ ግልጽ ነው። እንግዲያው ማንኛውም መጥፎ ሐሳብ ወደ አእምሯችን ሲገባ በዚያው ቅጽበት ማስወጣታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!
14. ንግግራችን ስለ እኛ ምን ያሳያል? ራሳችንንስ ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?
14 አንደበትህን ተቆጣጠር። ኢየሱስ “ከአፍ የሚወጣ ሁሉ ከልብ ይወጣል” ብሏል። (ማቴ. 15:18) በእርግጥም ንግግራችን ውስጣዊ ማንነታችንን በግልጽ ያሳያል። ስለዚህ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘እውነቱን መናገሬ ችግር ውስጥ የሚያስገባኝ ቢሆንም እንኳ ከመዋሸት እቆጠባለሁ? ከትዳር ጓደኛዬ ውጭ ማንንም ላለማሽኮርመም እጠነቀቃለሁ? የብልግና ንግግርን እንደ ተላላፊ በሽታ እርቃለሁ? አንድ ሰው ሲያበሳጨኝ በረጋ መንፈስ እመልሳለሁ?’ በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰልህ ጠቃሚ ነው። ንግግርህ ልብስ ላይ ካሉ ቁልፎች ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ ቁልፉን ስትፈታው ልብሱን ማውለቅ ቀላል ይሆናል። በተመሳሳይም ስድብን፣ ውሸትንና የብልግና ንግግርን ለማስወገድ የቻልከውን ያህል ስትጥር አሮጌውን ስብዕና ገፎ መጣል ቀላል ይሆንልሃል።
15. አሮጌውን ስብዕናችንን ‘በእንጨት ላይ መቸንከር’ ሲባል ምን ማለት ነው?
15 ቆራጥ እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ ሁን። ሐዋርያው ጳውሎስ አኗኗራችንን መቀየራችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማሳየት ከፍተኛ ኃይል ያለው መግለጫ ተጠቅሟል። አሮጌውን ስብዕናችንን ‘በእንጨት ላይ መቸንከር’ እንዳለብን ጽፏል። (ሮም 6:6) በሌላ አባባል ክርስቶስ ያደረገውን ማድረግ አለብን። ይሖዋ የሚጠላቸውን ዝንባሌዎችና ልማዶች መግደል ይኖርብናል። ይህን እርምጃ ካልወሰድን ንጹሕ ሕሊናም ሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋ አይኖረንም። (ዮሐ. 17:3፤ 1 ጴጥ. 3:21) ይሖዋ እኛ እንዲመቸን ሲል መሥፈርቶቹን ዝቅ እንደማያደርግ አስታውስ። ስብዕናችንን መቀየርና ከእሱ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን መኖር ያለብን እኛ ነን።—ኢሳ. 1:16-18፤ 55:9
16. ሥጋዊ ድክመቶችህን መዋጋትህን መቀጠል ያለብህ ለምንድን ነው?
16 ሥጋዊ ምኞቶችን መዋጋትህን ቀጥል። ከተጠመቅህ በኋላም ከሥጋዊ ምኞቶችህ ጋር የምታደርገው ውጊያ አያቆምም። የማሪስዩን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ማሪስዩ ወጣት እያለ ግብረ ሰዶማዊ ሆነ። ከጊዜ በኋላ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ተገናኝቶ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በሕይወቱ ውስጥ ለውጥ ካደረገ በኋላ በ2002 ተጠመቀ። ለብዙ ዓመታት ይሖዋን ያገለገለ ቢሆንም “አሁንም ቢሆን ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶች እንዳያሸንፉኝ መታገል የሚያስፈልገኝ ጊዜ አለ” ብሏል። ሆኖም ይህ ተስፋ እንዲያስቆርጠው አልፈቀደም። እንዲህ ብሏል፦ “ለእነዚህ ምኞቶች ባለመሸነፍ ይሖዋን ማስደሰት እንደምችል ማወቄ ብርታት ይሰጠኛል።”d
17. ከናቢሃ ተሞክሮ አንተን ያበረታታህ ምንድን ነው?
17 እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ጸልይ፤ እንዲሁም በራስህ ጥንካሬ ሳይሆን በይሖዋ መንፈስ ተማመን። (ገላ. 5:22፤ ፊልጵ. 4:6) አሮጌውን ስብዕና ገፈን ለመጣልና እንዳወለቅነው ለመቀጠል ቆራጥ መሆን ያስፈልገናል። ናቢሃ የተባለችን ሴት ተሞክሮ እንመልከት። ገና የስድስት ዓመት ልጅ እያለች አባቷ ጥሏት ሄደ። “ይህ . . . ስሜቴን በጣም ጎድቶታል” ብላለች። ናቢሃ እያደገች ስትሄድ ቁጡና ጠበኛ ሰው ሆነች። ዕፅ ማዘዋወር ጀመረች፤ በዚህም የተነሳ የተወሰኑ ዓመታት ታስራለች። እሷ ወዳለችበት እስር ቤት ሄደው የሚሰብኩ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠኗት ጀመር። ናቢሃ በሕይወቷ ውስጥ ትላልቅ ለውጦች ማድረግ ጀመረች። “አንዳንድ መጥፎ ልማዶቼን መተው አልከበደኝም። . . . ከሲጋራ ሱስ መላቀቅ ግን በጣም ከባድ ሆኖብኝ ነበር” ብላለች። ናቢሃ ከሱሷ ለመላቀቅ ከአንድ ዓመት በላይ ቢያታግላትም በመጨረሻ ተሳካላት። የረዳት ምንድን ነው? “ከሁሉ በላይ . . . ማጨስ ለመተው ያስቻለኝ ወደ ይሖዋ ያለማሰለስ መጸለዬ ነበር” ብላለች። አሁን ሌሎችን እንዲህ እያለች ታበረታታለች፦ “እኔ ይሖዋን ለማስደሰት ስል ለውጥ ማድረግ ከቻልኩ ማንኛውም ሰው ይህን ማድረግ እንደማያቅተው እርግጠኛ ነኝ!”e
ለጥምቀት ብቁ መሆን ትችላለህ
18. በ1 ቆሮንቶስ 6:9-11 መሠረት በርካታ የአምላክ አገልጋዮች ምን ማድረግ ችለዋል?
18 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ ከክርስቶስ ጋር አብረው እንዲገዙ ይሖዋ የመረጣቸው አንዳንድ ወንዶችና ሴቶች የመጥፎ ልማዶች ባሪያ ነበሩ። አንዳንዶቹ አመንዝሮች፣ ግብረ ሰዶማውያንና ሌቦች ነበሩ። ሆኖም በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ስብዕናቸውን መለወጥ ችለዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11ን አንብብ።) ዛሬም በተመሳሳይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ እርዳታ በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ ማድረግ ችለዋል።f ሥር የሰደዱ መጥፎ ልማዶችን አሸንፈዋል። የእነሱ ምሳሌ እንደሚያረጋግጠው፣ አንተም ስብዕናህን በመቀየርና መጥፎ ልማዶችህን በማሸነፍ ለጥምቀት ብቁ መሆን ትችላለህ።
19. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
19 መጠመቅ የሚፈልጉ ሰዎች አሮጌውን ስብዕና ገፈው በመጣል ብቻ መወሰን የለባቸውም፤ አዲሱን ስብዕና ለመልበስም ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። በቀጣዩ ርዕስ ላይ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነና ሌሎች በዚህ ረገድ እንዴት እንደሚረዱን እንመለከታለን።
መዝሙር 41 እባክህ ጸሎቴን ስማ
a ለጥምቀት ብቁ ለመሆን በስብዕናችን ላይ ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኞች መሆን አለብን። ይህ ርዕስ አሮጌው ስብዕና የሚገለጽባቸው ባሕርያት የትኞቹ እንደሆኑ፣ እነዚህን ባሕርያት ገፈን መጣል ያለብን ለምን እንደሆነ እንዲሁም ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል። በቀጣዩ ርዕስ ላይ ደግሞ ከተጠመቅን በኋላም አዲሱን ስብዕና መልበሳችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ‘አሮጌውን ስብዕና ገፍፎ መጣል’ ማለት ይሖዋን የሚያሳዝኑ አመለካከቶችንና ዝንባሌዎችን ማስወገድ ማለት ነው። አንድ ሰው ይህን ማድረግ መጀመር ያለበት ከመጠመቁ በፊት ነው።—ኤፌ. 4:22
c ሙሉውን ታሪክ ለማንበብ በሚያዝያ 1, 2012 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል—‘ወደ ይሖዋ መመለስ ነበረብኝ’” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
d ሙሉውን ታሪክ ለማንበብ በግንቦት 1, 2012 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል—‘በጣም ደግ ነበሩ’” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
e ሙሉውን ታሪክ ለማንበብ በጥቅምት 1, 2012 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል—‘ቁጡና ጠበኛ ሆንኩ’” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
f “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
g የሥዕሉ መግለጫ፦ መጥፎ ዝንባሌዎችንና ልማዶችን ለማስወገድ የምናደርገው ጥረት፣ አሮጌ ልብስን ገፎ ከመጣል ጋር ሊመሳሰል ይችላል።