በተሰሎንቄ ለምሥራቹ መታገል
ቴሳሎኒኪ ወይም ሳሎኒካ ተብላ በዛሬው ጊዜ የምትጠራው ተሰሎንቄ በሰሜን ምሥራቅ ግሪክ የምትገኝና ሞቅ ያለ እንቅስቃሴ የሚካሄድባት የወደብ ከተማ ናት። ይህች ከተማ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ታሪክ ውስጥ በተለይም የአሕዛብ ሐዋርያ የሆነው ጳውሎስ ካከናወነው አገልግሎት ጋር በተያያዘ ጉልህ ስፍራ ነበራት።—የሐዋርያት ሥራ 9:15፤ ሮም 11:13
ጳውሎስና የጉዞ ጓደኛው ሲላስ በ50 ዓ.ም. ገደማ ወደ ተሰሎንቄ ሄደው ነበር። ጳውሎስ በሁለተኛው የሚስዮናዊ ጉዞው ላይ ነበር፤ በዚህ ወቅት፣ ዛሬ አውሮፓ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች ለመጀመሪያ ጊዜ የመስበክ አጋጣሚ አግኝተዋል።
ጳውሎስና ሲላስ ተሰሎንቄ ሲደርሱ የመቄዶንያ ትልቅ ከተማ በሆነችው በፊልጵስዩስ የደረሰባቸው ድብደባና እስራት ገና ከአእምሮአቸው አልወጣም። እንዲያውም ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ካጋጠመው ሁኔታ በኋላ “የአምላክን ምሥራች” በተሰሎንቄ ለመስበክ ከራሱ ጋር “ከፍተኛ ትግል” ማድረግ እንዳስፈለገው ከጊዜ በኋላ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ነግሯቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 2:1, 2) በተሰሎንቄስ፣ ከፊልጵስዩስ የተሻለ ሁኔታ ያጋጥማቸው ይሆን? የያዙት መልእክት በዚህች ከተማ ተቀባይነት ያገኝ ይሆን? ፍሬስ ያገኙ ይሆን? እስቲ መጀመሪያ ስለዚህች ጥንታዊት ከተማ አንዳንድ ነገሮችን እንመልከት።
በጦርነት የተሞላ ታሪክ ያላት ከተማ
ተሰሎንቄ የሚለው ስም የመጣው “ቴሰሊያውያን” እና “ድል” የሚል ትርጉም ካላቸው ሁለት የግሪክኛ ቃላት ሲሆን ቃሉ ትግልንና ውጊያን ያመለክታል። የታላቁ እስክንድር አባት የሆነው የመቄዶንያው ንጉሥ ዳግማዊ ፊሊፕ፣ በማዕከላዊ ግሪክ ባለችው በቴሰሊ የሚገኝን አንድ ጎሳ በ352 ዓ.ዓ. ድል እንዳደረገ በስፋት ይታመናል። ለዚህ ድል መታሰቢያ እንዲሆንም ከሴት ልጆቹ አንዷን ቴሳሎኒኪ (ተሰሎንቄ) ብሎ እንደሰየማት ይነገራል፤ ቴሳሎኒኪም የወንድሟ የእስክንድር ተተኪ የሆነውን ካሳንደርን ከጊዜ በኋላ አገባች። በ315 ዓ.ዓ. ገደማ ካሳንደር፣ ከካልሲዲሲ ባሕረ ገብ መሬት በስተምዕራብ የቆረቆራትን ከተማ በሚስቱ ስም ሰየማት። ቴሳሎኒኪ (ተሰሎንቄ) በጦርነት ስትታመስ የኖረች አገር ናት።
ያም ቢሆን ተሰሎንቄ የበለጸገች ከተማ ነበረች። የኤጅያን ባሕር ካሉት ምርጥ ወደቦች አንዱ የተሰሎንቄ ወደብ ነበር። በሮማውያን ዘመን ቪያ ኢግናቲያ የሚባለው የታወቀ አውራ ጎዳና ይህችን ከተማ አቋርጦ ያልፍ ነበር። ተሰሎንቄ ለባሕርም ሆነ ለየብስ ጉዞ ወሳኝ ቦታ ላይ ስለነበረች ሮማውያን ከሚጠቀሙባቸው የንግድ መስመሮች አንዷ ሆና አገልግላለች። የከተማዋ ብልጽግና ባለፉት ዘመናት በሙሉ የጎት፣ የስላቭ፣ የፍራንክ፣ የቬኒሺያ እና የቱርክ ሕዝቦች ዓይናቸውን እንዲጥሉባት አድርጓል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ከተማዋን የተቆጣጠሩት በኃይል በመሆኑ ለብዙ ደም መፋሰስ ምክንያት ሆነዋል። እስቲ አሁን ደግሞ ጳውሎስ ወደዚህች ከተማ በሄደበት ወቅት በምሥራቹ የተነሳ የተጀመረውን ትግል እንመልከት።
ጳውሎስ ወደ ተሰሎንቄ ሄደ
ጳውሎስ ወደ አንድ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሄድ በአብዛኛው ቀድሞ የሚያናግረው አይሁዳውያንን ነበር፤ ይህን የሚያደርገውም አይሁዳውያን ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ያላቸው እውቀት ውይይት ለመጀመር መንገድ ስለሚከፍትና ምሥራቹን ለመረዳት ስለሚያቀልላቸው ነው። አንድ ምሁር እንደገለጹት ይህ የጳውሎስ ልማድ ለአገሩ ሰዎች ያለውን አሳቢነት የሚጠቁም አሊያም ደግሞ አይሁዳውያንንና ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን ሌሎች ሰዎች “እንደ መሸጋገሪያ በመጠቀም ለአሕዛብ [ለመስበክ]” ጥረት እንደሚያደርግ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።—የሐዋርያት ሥራ 17:2-4
በመሆኑም ጳውሎስ፣ ተሰሎንቄ ሲደርስ መጀመሪያ ወደ ምኩራብ በመግባት “ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ [ከአይሁዳውያን] ጋር ተወያየ፤ ክርስቶስ መከራ መቀበሉና ከሞት መነሳቱ የግድ አስፈላጊ እንደነበር ማስረጃ እየጠቀሰ በማብራራትና በማስረዳት ‘ይህ እኔ እያሳወቅኳችሁ ያለሁት ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ ነው’ አላቸው።”—የሐዋርያት ሥራ 17:2, 3, 10
ጳውሎስ ስለ መሲሑ ማንነትና ስለሚጫወተው ሚና የተናገረው ሐሳብ አወዛጋቢ ነበር። እሱ የገለጸው መከራ የተቀበለና የተገደለ መሲሕ፣ አይሁዳውያን ከሚጠብቁት ድል አድራጊና ጦረኛ መሲሕ ፈጽሞ የተለየ ነበር። ጳውሎስ አይሁዳውያንን ለማሳመን ሲል ከእነሱ ጋር ‘ይወያይ፣’ ‘ማስረጃ እየጠቀሰ ያብራራ’ እንዲሁም ‘ያስረዳ’ ነበር፤ እነዚህ አንድ ውጤታማ አስተማሪ ተለይቶ የሚታወቅባቸው ዘዴዎች ናቸው።a ይሁን እንጂ ጳውሎስ እነዚህን አስደናቂ ትምህርቶች ሲያካፍላቸው አድማጮቹ ምን ምላሽ ሰጡ?
ችግሮች ቢኖሩም ፍሬያማ የሆነ አገልግሎት
አንዳንድ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ በርካታ ግሪካውያን እንዲሁም “ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል የታወቁ ሴቶች” የጳውሎስን መልእክት ተቀበሉ። በመቄዶንያ የሚገኙ ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ ስለነበራቸው “የታወቁ ሴቶች” መባላቸው በእርግጥም የተገባ ነው። ሴቶች በመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ይሠሩ፣ የራሳቸው ንብረት ይኖራቸው፣ አንዳንድ የዜግነት መብቶች ይሰጧቸው እንዲሁም በንግድ እንቅስቃሴዎች ይካፈሉ ነበር። ሌላው ቀርቶ የክብር ሐውልቶች ይቆሙላቸው ነበር። በፊልጵስዩስ የነበረችው ሊዲያ የተባለች ነጋዴ ምሥራቹን እንደተቀበለች ሁሉ በተሰሎንቄ ያሉ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ሴቶችም (ትልቅ ቦታ ያላቸው ሰዎች ሚስቶች ወይም ከተከበሩ ቤተሰቦች የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ) ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል።—የሐዋርያት ሥራ 16:14, 15፤ 17:4
ይሁንና አይሁዳውያኑ ይህን ሲያዩ በቅናት ስለበገኑ “በገበያ ስፍራ ከሚውሉ ሥራ ፈቶች መካከል አንዳንድ ክፉ ሰዎችን አሰባስበው አሳደሙ፤ ከተማዋንም በሁከት አመሷት።” (የሐዋርያት ሥራ 17:5) አይሁዳውያኑ ያሳደሟቸው ምን ዓይነት ሰዎች ነበሩ? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር፣ እነዚህ ሰዎች “ወራዳና የማይረቡ” እንደሆኑ ገልጸዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “እነዚህ ሰዎች ስለተነሳው ጉዳይ ምንም ግድ የነበራቸው አይመስልም፤ እንደ ሌሎች ሁከት ፈጣሪዎች ሁሉ ስሜታዊና ማንኛውንም ዓይነት የዓመፅ ድርጊት ለመፈጸም የተዘጋጁ ነበሩ።”
እነዚህ ሰዎች “ጳውሎስና ሲላስንም አምጥተው ለረብሻ የተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ለማቅረብ የያሶንን [ጳውሎስን በእንግድነት የተቀበለውን ሰው] ቤት ሰብረው ገቡ።” ይሁንና ጳውሎስን እዚያ አላገኙትም። በመሆኑም “ያሶንንና አንዳንድ ወንድሞችን እየጎተቱ ወስደው የከተማዋ ገዥዎች ፊት በማቅረብ እንዲህ እያሉ ጮኹ፦ ‘ዓለምን ሁሉ ያናወጡት እነዚያ ሰዎች እዚህም አሉ።’”—የሐዋርያት ሥራ 17:5, 6
ተሰሎንቄ የመቄዶንያ ዋና ከተማ በመሆኗ የራስ ገዝ አስተዳደር ነበራት። ይህ መስተዳድር ደግሞ በከተማዋ ውስጥ ለሚነሱ ችግሮች እልባት የሚሰጥ የሕዝብ ምክር ቤት ነበረው። “የከተማዋ ገዥዎች” ወይም “ፓለታርክ”b የተባሉት ሰዎች ሥርዓት የማስከበር እንዲሁም ሮም ጣልቃ እንድትገባና ከተማዋ ያላትን መብቶች እንድታጣ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን የመከላከል ኃላፊነት ያለባቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት ናቸው። በመሆኑም እነዚህ ባለሥልጣናት፣ “ሁከት ፈጣሪዎች” የከተማዋን ሰላም እያደፈረሱት እንዳለ የሚገልጸውን ክስ ሲሰሙ እንደሚደናገጡ የታወቀ ነው።
የጳውሎስና የሲላስ ተቃዋሚዎች በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ “እነዚህ ሰዎች በሙሉ ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ እያሉ የቄሳርን ሕግ የሚቃረን ነገር ያደርጋሉ” የሚል በጣም ከባድ የሆነ ክስ ሰነዘሩባቸው። (የሐዋርያት ሥራ 17:7) ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንታኔ የሚሰጥ አንድ ጽሑፍ እንደገለጸው ይህ ክስ ጳውሎስና ሲላስ፣ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ “ሕዝብን እንዳሳመፁና እንዳነሳሱ” የሚገልጽ ነበር፤ የሮም ንጉሠ ነገሥታት ደግሞ “በግዛታቸው ውስጥ ባለ በየትኛውም ቦታ ከእነሱ እውቅና ውጭ [የሌላ] ንጉሥ ስም እንዲጠራ አይፈቅዱም ነበር።” ከዚህም ሌላ ጳውሎስ፣ ንጉሥ እንደሆነ የተናገረለት ኢየሱስ ሕዝብን በማሳመፅ ተከስሶ በሮም ባለሥልጣናት መገደሉ አሁን የተሰነዘረው ክስ እውነት እንዲመስል ያደርገዋል።—ሉቃስ 23:2
የከተማዋ ገዥዎች ይህን ሲሰሙ ተቆጡ። ሆኖም ለቀረበው ክስ በቂ ማስረጃ ስላልነበረና የተከሰሱት ሰዎችም ሊገኙ ስላልቻሉ “ያሶንንና ሌሎቹን የዋስትና ገንዘብ እንዲያስይዙ ካደረጓቸው በኋላ ለቀቋቸው።” (የሐዋርያት ሥራ 17:8, 9) ያሶንና ሌሎቹ ክርስቲያኖች የከፈሉት የዋስትና ገንዘብ ጳውሎስ ከተማዋን ለቆ እንደሚወጣና ድጋሚ ተመልሶ ረብሻ እንደማይፈጥር ማረጋገጫ መስጠታቸውን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ “ሰይጣን መንገድ [እንደዘጋበትና]” ወደዚህች ከተማ እንዳይመለስ እንዳገደው ሲናገር ይህን ሁኔታ መጥቀሱ ሊሆን ይችላል።—1 ተሰሎንቄ 2:18
በተሰሎንቄ በተፈጠረው ሁኔታ የተነሳ ጳውሎስና ሲላስ በምሽት ወደ ቤርያ ተላኩ። በዚያም ጳውሎስ ፍሬያማ አገልግሎት አከናወነ፤ ይሁንና ይህ ያስቆጣቸው በተሰሎንቄ ያሉት አይሁዳውያን ተቃዋሚዎቹ፣ 80 ኪሎ ሜትር የሚሆነውን ርቀት ተጉዘው ወደ ቤርያ በመሄድ ሕዝቡን ለማነሳሳትና ተቃውሞ እንዲነሳ ለማድረግ ሞከሩ። በመሆኑም ጳውሎስ ብዙም ሳይቆይ ወደ አቴንስ አቀና፤ ለምሥራቹ የሚደረገው ትግል ግን በዚህ አላበቃም።—የሐዋርያት ሥራ 17:10-14
አዲስ የተቋቋመው ጉባኤ ያጋጠመው ትግል
ደስ የሚለው ነገር በተሰሎንቄ ጉባኤ ተቋቋመ፤ በዚያ ያሉ ክርስቲያኖች ያጋጠማቸው ተፈታታኝ ሁኔታ ግን ስደት ብቻ አልነበረም። እነዚህ ክርስቲያኖች የሚኖሩት ጣዖት አምላኪ በሆኑና ሥነ ምግባር በጎደላቸው ሰዎች መካከል መሆኑ ጳውሎስን ስጋት ላይ ጥሎት ነበር። ወንድሞቹ የሚደርስባቸውን ፈተና መቋቋም ይችሉ ይሆን?—1 ተሰሎንቄ 2:17፤ 3:1, 2, 5
የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በከተማዋ ውስጥ በሚከናወኑት ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች መካፈላቸውን ሲያቆሙ የቀድሞ ወዳጆቻቸው እንደሚጠሏቸውና እንደሚነሱባቸው ያውቁ ነበር። (ዮሐንስ 17:14) ከዚህም በተጨማሪ ተሰሎንቄ እንደ ዙስ፣ አርጤምስና አፖሎ ያሉት የግሪክ አማልክት እንዲሁም ሌሎች የግብጽ አማልክት ቤተ መቅደሶች የሞሉባት ከተማ ነበረች። የንጉሠ ነገሥት አምልኮ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ከመሆኑም ሌላ ሁሉም ሰው በዚህ የአምልኮ ሥርዓት እንዲካፈል ይጠበቅበት ነበር። በአምልኮ ሥርዓቱ ላይ ለመካፈል ፈቃደኛ አለመሆን በሮም ላይ እንደማመፅ ይቆጠራል።
የጣዖት አምልኮ፣ ዓይን ያወጣ የፆታ ብልግና እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አድርጓል። የተሰሎንቄ ጠባቂ አምላክ እንደሆነ የሚታመነው የካቢረስ አምልኮ፣ ከዳዮናይሰስ እና ከአፍሮዳይት እንዲሁም ከግብጿ አይስስ የአምልኮ ሥርዓት የሚያመሳስለው ነገር አለ፤ ለሁሉም በሚደረገው የአምልኮ ሥርዓት ላይ መረን የለቀቀ ፈንጠዝያ የሚታይ ከመሆኑም ሌላ ልቅ የፆታ ብልግና ይፈጸም ነበር። ቅምጥ መያዝና ዝሙት አዳሪነት በተሰሎንቄ በጣም የተለመዱ ነገሮች ነበሩ። ዝሙት በሕዝቡ ዘንድ እንደ ኃጢአት የሚታይ ነገር አልነበረም። የማኅበረሰቡ አስተሳሰብ የተቀረጸው በሮማውያን ባሕል ነው፤ አንድ ጽሑፍ ስለዚህ ባሕል ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ዜጎች፣ ማንኛውንም የሕዝቡን የሥጋ ፍላጎት እንዲያረኩ ተብለው ወደ ተቀመጡት ወንዶችና ሴቶች በመሄድ ምኞታቸውን ማርካት ይችሉ ነበር፤ የሕክምና ባለሙያዎችም ቢሆን እነዚህ ምኞቶች መገደብ እንደሌለባቸው ይመክሩ ነበር።” ከዚህ አንጻር፣ ጳውሎስ በተሰሎንቄ የነበሩ ክርስቲያኖችን ‘ከዝሙት እንዲርቁ’ እንዲሁም ‘ለፍትወተ ሥጋ ከመጎምጀት’ እና ‘ከርኩሰት’ እንዲጠበቁ የመከራቸው ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም።—1 ተሰሎንቄ 4:3-8
ትግሉን በድል ተወጥተዋል
በተሰሎንቄ የነበሩ ክርስቲያኖች ለእምነታቸው ከባድ ትግል ማድረግ ነበረባቸው። እነዚህ ክርስቲያኖች ተቃውሞና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያጋጠሟቸው ከመሆኑም ሌላ የሚኖሩት የጣዖት አምልኮና የሥነ ምግባር ብልግና በተስፋፋበት ማኅበረሰብ ውስጥ ነበር፤ ያም ቢሆን ‘የእምነት ሥራ በማከናወናቸው’ እንዲሁም ‘በፍቅር’ ተነሳስተው በመድከማቸውና ‘ጽናት’ በማሳየታቸው ብሎም ምሥራቹን በስፋት ለማሰራጨት አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ጳውሎስ አመስግኗቸዋል።—1 ተሰሎንቄ 1:3, 8
በ303 ዓ.ም. በሮም ግዛት ውስጥ በነበሩ ክርስቲያኖች ላይ ከባድ የስደት ማዕበል ተነሳ። የዚህ ስደት ዋነኛ ቆስቋሽ በተሰሎንቄ ይኖር የነበረውና ከተማዋን ግሩም በሆኑ ሕንፃዎች ያስዋባት ቄሳር ጋሌርየስ ነበር። እሱ ካሠራቸው ሕንፃዎች የአንዳንዶቹ ፍርስራሾች በአሁኑ ጊዜ የቱሪስት መስህብ ናቸው።
በዛሬው ጊዜ በቴሳሎኒኪ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይህ ጨካኝ የክርስትና ጠላት ባስገነባቸው ሕንፃዎች ፊት ለፊት ቆመው ምሥራቹን ለሰዎች ይሰብካሉ። በ20ኛው መቶ ዘመን የስብከቱን ሥራ ሲያከናውኑ ከባድ ተቃውሞ ያጋጠማቸው ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ በዚህች ከተማ ይህን ሥራ በቅንዓት የሚያከናውኑ 60 ያህል የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ይገኛሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች የሚያደርጉት ጥረት ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ምሥራቹን ለማስፋፋት ይደረግ የነበረው ትግል ዛሬም እንደቀጠለና አሁንም ቢሆን በዚህ ትግል ድል እየተገኘ እንዳለ ያሳያል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ጳውሎስ፣ አሁን በመዝሙር 22:7፤ 69:21፤ ኢሳይያስ 50:6፤ 53:2-7፤ ዳንኤል 9:26 ላይ የሚገኙትን ጥቅሶች እንደ ማስረጃ አቅርቦ ሊሆን ይችላል።
b ይህ ቃል በግሪክ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ውስጥ አይገኝም። ይሁንና በተሰሎንቄ አካባቢ የተገኙት ሰነዶች ይህን ቃል መጥቀሳቸው የሐዋርያት ሥራ ዘገባ ትክክል እንደሆነ ያረጋግጣል፤ ከእነዚህ ሰነዶች አንዳንዶቹ የተዘጋጁት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነው።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ቪያ ኢግናቲያ
መቄዶንያ
ፊልጵስዩስ
አምፊጶሊስ
ተሰሎንቄ
ቤርያ
ቴሰሊ
ኤጅያን ባሕር
አቴና
[በገጽ 20 እና 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ከላይ፦ ቴሳሎኒኪ በዛሬው ጊዜ
ከታች፦ መተላለፊያ፤ በገበያ ስፍራው የሚገኘው የሮማውያን መታጠቢያ ቤት
[ምንጭ]
Two bottom left images: 16th Ephorate of Prehistoric and Classical Antiquities, copyright Hellenic Ministry of Culture and Tourism
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጋሌርየስ ቅስት አቅራቢያ የሚገኘው ሕንፃ፤ የቄሳር ጋሌርየስ ምስል፤ በጋሌርየስ ቅስት አቅራቢያ ምሥራቹ ሲሰበክ
[ምንጭ]
Middle image: Thessalonica Archaeological Museum, copyright Hellenic Ministry of Culture and Tourism
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]
Head medallion: © Bibliothèque nationale de France; stone inscription: Thessalonica Archaeological Museum, copyright Hellenic Ministry of Culture and Tourism