ጽኑ እምነት በመያዝ ምሥራቹን መስበክ
1 በአንደኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹ የመንግሥቱን ምሥራች እንዲሰብኩና ‘አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ’ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) የይሖዋ ምሥክሮች የእሱን መመሪያ አክብደው ስለሚመለከቱ በ20ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበራችን በቁጥር አድጎ በ234 አገሮች የሚገኙ ከ5, 900, 000 በላይ ደቀ መዛሙርትን አካቷል። ለሰማያዊ አባታችን የቀረበ ምንኛ ታላቅ የውዳሴ ድምፅ ነው!
2 አሁን ወደ 21ኛው መቶ ዘመን ገብተናል። ጠላታችን የመንግሥቱን ስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ዋነኛ ሥራችንን ለማስተጓጎል ያሴራል። የግድ አስፈላጊ ባልሆኑ ነገሮችና ጉዳዮች ትኩረታችንን ለመስረቅ፣ ጊዜያችንን ለማባከንና ኃይላችንን ለማሟጠጥ ይህ የነገሮች ሥርዓት የሚያስከትለውን ጫና እንደ መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል። በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ መያዝ ያለበት ነገር ምን እንደሆነ ይህ ሥርዓት እንዲወስንልን ከመፍቀድ ይልቅ አንገብጋቢው ጉዳይ የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ መሆኑን ከአምላክ ቃል አስተውለናል። (ሮሜ 12:2) ይህም ‘በጊዜውም አለጊዜውም ቃሉን እንድንሰብክና አገልግሎታችንን ሙሉ በሙሉ እንድንፈጽም’ የተሰጠንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር መታዘዝን ይጠይቃል።—2 ጢሞ. 4:2, 5
3 ጽኑ እምነት አዳብሩ:- ክርስቲያኖች ‘በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ጽኑ እምነት ኖሯቸውና ምሉዓን ሆነው መቆም’ አለባቸው። (ቆላ. 4:12 NW ) “ጽኑ እምነት” ተብሎ የተተረጎመው ከንቪክሸን የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “አጥብቆ መረዳት ወይም ማመን፤ ከልብ መቀበል” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የአምላክ ትንቢታዊ ቃል የተረጋገጠ መሆኑንና አሁን የመጨረሻው ዘመን ውስጥ በጣም ዘልቀን መግባታችንን ማመን አለብን። ሐዋርያው ጳውሎስ የነበረው ዓይነት ጽኑ እምነት ሊኖረን ይገባል። ምሥራቹ “የሚያምኑትን ሰዎች ሁሉ ማዳን የሚችል የእግዚአብሔር ኃይል ነው” ሲል ተናግሯል።—ሮሜ 1:16 የ1980 ትርጉም
4 ዲያብሎስ በሌሎች ላይ ተጽእኖ ለማሳደርና ሌሎችን ለማሳት፣ ራሳቸው በተሳሳተ ጎዳና ላይ ባሉ ክፉዎችና አታላዮች ይጠቀማል። (2 ጢሞ. 3:13) ስለዚህ ጉዳይ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ በማግኘታችን እውነትን ስለመያዛችን ያለንን ጽኑ እምነት ለማጠናከር አንዳንድ እርምጃዎች እንወስዳለን። የኑሮ ጭንቀቶች ቅንዓታችንን እንዲያቀዘቅዙብን ከመፍቀድ ይልቅ የመንግሥቱን ጥቅሞች በአንደኛ ደረጃ ማስቀመጣችንን እንቀጥላለን። (ማቴ. 6:33, 34) ምናልባትም የዚህ የነገሮች ሥርዓት ማብቂያ ሩቅ እንደሆነ በማሰብ የጊዜውን አጣዳፊነት መዘንጋት አንፈልግም። መጨረሻው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እየቀረበ ነው። (1 ጴጥ. 4:7) በአንዳንድ ቦታዎች አስቀድሞ ከተሰጠው ምሥክርነት አንጻር ምሥራቹን ማዳረሱ እምብዛም ውጤት እንደማያስገኝ ቢሰማንም እንኳ ማስጠንቀቂያውን የማሰማቱ ሥራ መቀጠል አለበት።—ሕዝ. 33:7-9
5 መጨረሻው በተቃረበበት በዚህ ወቅት የሚነሡት ቁልፍ ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው:- ‘ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የሰጠውን ተልእኮ በቁም ነገር እመለከተዋለሁ? ምሥራቹን ስሰብክ መንግሥቱ እውን ስለመሆኑ ጽኑ እምነት እንዳለኝ አሳያለሁ? በዚህ ሕይወት አድን አገልግሎት በተቻለኝ መጠን ከፍተኛ ተሳትፎ ለማድረግ ቆርጫለሁ?’ ወደ መጨረሻው ዘመን ምን ያህል ዘልቀን እንደገባን በመገንዘብ ለራሳችንም ሆነ ለስብከትና ለማስተማር ተልእኳችን ትኩረት መስጠት አለብን። ይህን ማድረጋችን ራሳችንም ሆንን የሚያዳምጡን ሰዎች በሕይወት እንድንተርፍ ያስችላል። (1 ጢሞ. 4:16) ሁላችንም የምሥራቹ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ጽኑ እምነታችንን ይበልጥ ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?
6 የተሰሎንቄ ክርስቲያኖችን ምሰሏቸው:- ሐዋርያው ጳውሎስ የተሰሎንቄ ወንድሞች ያሳዩትን ትጋት በማስታወስ እንዲህ ብሏቸዋል:- “ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም [“በጽኑ እምነትም፣” NW ] እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ በእናንተ ዘንድ ስለ እናንተ እንዴት እንደ ነበርን ታውቃላችሁ። ደግሞ እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችሁ፣ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ።” (1 ተሰ. 1:5, 6) አዎን፣ የተሰሎንቄ ጉባኤ ክርስቲያኖች ከፍተኛ ስደት ቢደርስባቸውም እንኳ በቅንዓት ጽኑ እምነት በመያዝ በመስበካቸው ጳውሎስ አመስግኗቸዋል። ይህን እንዲያደርጉ ያስቻላቸው ነገር ምንድን ነው? በሐዋርያው ጳውሎስና አብረውት በሚያገለግሉ ወንድሞች ላይ የተመለከቱት ቅንዓትና ጽኑ እምነት በእነሱ ላይ ያሳደረው አዎንታዊ ተጽእኖ ቀላል ስላልነበረ ነው። እንዴት?
7 የጳውሎስ እና የጉዞ ጓደኞቹ ሕይወት ራሱ የአምላክ መንፈስ እንዳላቸውና በሚሰብኩት መልእክት ላይ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ይመሰክር ነበር። ጳውሎስና ሲላስ ወደ ተሰሎንቄ ከመምጣታቸው በፊት ፊልጵስዩስ ውስጥ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። ሕግ ፊት ሳይቀርቡ ተደብድበውና እግራቸው ከግንድ ጋር ተጠርቆ ታስረዋል። ሆኖም ይህ ፈታኝ ነገር ቢገጥማቸውም ለምሥራቹ የነበራቸው ቅንዓት አልቀዘቀዘም። መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ከእስራት እንዲፈቱ፣ የወኅኒ ቤት ጠባቂውና ቤተሰቡ ክርስትናን እንዲቀበሉ እንዲሁም እነዚህ ወንድሞች በአገልግሎታቸው እንዲቀጥሉ መንገዱን አዘጋጅቶላቸዋል።—ሥራ 16:19-34
8 ጳውሎስ ከአምላክ መንፈስ ባገኘው ብርታት ወደ ተሰሎንቄ መጣ። እዚያም በግል የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት እየሠራ ለተሰሎንቄ ሰዎች እውነትን ለማስተማር ሙሉ በሙሉ ራሱን አቅርቧል። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ምሥራቹን ከማወጅ ወደኋላ አላለም። (1 ተሰ. 2:9) ጳውሎስ ጽኑ እምነት በመያዝ ያካሄደው ስብከት በተሰሎንቄ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ በማሳደሩ ቀድሞ ይከተሉ የነበረውን ጣዖት አምልኮ እንዲተዉና የእውነተኛው አምላክ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።—1 ተሰ. 1:8-10
9 ስደት መኖሩ አዳዲሶቹ አማኞች ምሥራቹን ሰምተው እርምጃ እንዳይወስዱ አላገዳቸውም። የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ያገኙት አዲስ እምነት ባሳደረባቸው ግፊት እንዲሁም ዘላለማዊ በረከቶችን እንደሚያገኙ ሙሉ በሙሉ በማመን ሞቅ ባለ ስሜት የተቀበሉትን እውነት ለማወጅ ተነሳስተዋል። ጉባኤው ካደረገው ንቁ እንቅስቃሴ የተነሳ ስለ እነሱ እምነትና ቅንዓት የሚናፈሰው ወሬ በሌሎቹ የመቄዶንያ ክፍሎችና አልፎ ተርፎም በአካይያ ተዳርሶ ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች የመጀመሪያ ደብዳቤውን ሲጽፍ መልካም ሥራቸው በይፋ ታውቆ ነበር። (1 ተሰ. 1:7) እንዴት ድንቅ ምሳሌ ነው!
10 ለአምላክና ለሰዎች ባለን ፍቅር መነሳሳት:- እንደ ተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም በዛሬው ጊዜ ምሥራቹን ስንሰብክ በግላችን ጽኑ እምነት መያዝ የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ እነሱን በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- ‘የእምነታችሁን ሥራ በፍቅር ተነሳስታችሁ የደከማችሁትን ድካም ሳናቋርጥ እናስባለን።’ (1 ተሰ. 1:3 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ለይሖዋ አምላክና ምሥራቹን ለሚሰብኩላቸው ሰዎች ጥልቅ የሆነ ልባዊ ፍቅር እንደነበራቸው ግልጽ ነው። ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ‘የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳቸውንም’ እንዲያካፍሉ ያነሳሳቸው እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ነበር።—1 ተሰ. 2:8
11 በተመሳሳይ ለይሖዋና ለሰዎች ያለን ጥልቅ ፍቅር አምላክ እንድንሠራው በሰጠን የስብከቱ ሥራ በተሟላ መልኩ የመሳተፍ ፍላጎት እንዲኖረን ያነሳሳናል። ይህ ዓይነቱ ፍቅር ካለን ምሥራቹን ማዳረስ አምላክ የሰጠን የግል ኃላፊነታችን እንደሆነ እንገነዘባለን። ይሖዋ እኛን ወደ ‘እውነተኛው ሕይወት’ ለመምራት ባደረገልን ነገር ላይ አዎንታዊ በሆነ መንገድና በአድናቆት ማሰላሰላችን በሙሉ ልባችን የምናምንበትን ያንኑ አስደናቂ እውነት ለሌሎች ለመንገር ያነሳሳናል።—1 ጢሞ. 6:19
12 በስብከቱ ሥራ ስንጠመድ ለይሖዋና ለሰዎች ያለን ፍቅር እያደገ መሄድ ይኖርበታል። ይህ ከሆነ ከቤት ወደ ቤት በምናደርገው አገልግሎት ተሳትፏችንን ለማሳደግም ሆነ ክፍት በሆኑልን ሌሎች የምሥክርነት ዘርፎች ሁሉ ለመሳተፍ እንነሳሳለን። ለዘመዶቻችን፣ ለጎረቤቶቻችንና ለምናውቃቸው ሰዎች መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች እንጠቀምባቸዋለን። ምንም እንኳ ብዙ ሰዎች የምንነግራቸውን ምሥራች ላይቀበሉን ቢችሉም እንዲሁም አንዳንዶች የመንግሥቱን ስብከት ለማደናቀፍ ቢጥሩም ውስጣዊ ደስታ አለን። ለምን? ምክንያቱም ስለ መንግሥቱ ለመመሥከርና ሰዎች መዳን እንዲያገኙ ለመርዳት የተቻለንን እንዳደረግን ስለምንገነዘብ ነው። ይሖዋም ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት ይባርክልናል። የኑሮ ጫናዎች በሚከቡን ጊዜም ሆነ ሰይጣን ደስታችንን ለመሸርሸር በሚጥርበት ጊዜ ጽኑ እምነታችንንና ለሌሎች ለመመሥከር ያለንን ቅንዓት መጠበቅ እንችላለን። ሁላችንም ድርሻችንን መወጣታችን በተሰሎንቄ እንደነበረው ጉባኤ ያሉ ጠንካራና ቀናተኛ የሆኑ ጉባኤዎች ያስገኛል።
13 ፈተና ሲገጥማችሁ ተስፋ አትቁረጡ:- ልዩ ልዩ ፈተናዎች ሲያጋጥሙንም ጽኑ እምነት መያዝ ያስፈልገናል። (1 ጴጥ. 1:6, 7) ኢየሱስ የእሱ ተከታዮች ከሆኑ ‘በአሕዛብ ሁሉ የተጠሉ’ እንደሚሆኑ ለደቀ መዛሙርቱ ግልጽ አድርጎላቸዋል። (ማቴ. 24:9) ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ በነበሩበት ጊዜ ይህ ነገር እውነት መሆኑን ተመልክተዋል። በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 16 ላይ የቀረበው ዘገባ ጳውሎስና ሲላስ ውስጠኛው እስር ቤት ተጥለውና እግራቸው ከግንድ ጋር ተጠርቆ እንደነበር ይናገራል። በአብዛኛው ዋናው እስር ቤት መሃሉ ባዶ ሆኖ ዙሪያውን ብርሃንና አየር የሚደርሳቸው ትናንሽ የእስር ቤት ክፍሎች ያሉት ነበር። ውስጠኛው እስር ቤት ግን ብርሃንም ሆነ በቂ አየር አያገኝም። ጳውሎስና ሲላስ በዚህ አስከፊ ማጎሪያ ውስጥ ጨለማውን፣ ሙቀቱንና ክርፋቱን መቻል ነበረባቸው። ከግርፋቱ የተነሳ ጀርባቸው ቆሳስሎ እየደማ ለሰዓታት ከግንድ ጋር ተጠርቀው ያሳለፉትን ስቃይ መገመት ትችላለህ?
14 ጳውሎስና ሲላስ እነዚህ ፈተናዎች ቢደርሱባቸውም እንኳ ታማኝነታቸውን ጠብቀዋል። ልባዊ የሆነ ጽኑ እምነት እንዳላቸው ያሳዩ ሲሆን ይህ ምንም ዓይነት ፈተና ቢደርስባቸውም እንኳ ይሖዋን እንዲያገለግሉ አጠናክሯቸዋል። ጳውሎስና ሲላስ ያሳዩት ጽኑ እምነት “እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ” እንደነበር በሚናገረው በምዕራፍ 16 ቁጥር 25 ላይ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። እንዲያውም ውስጠኛው እስር ቤት የነበሩ ቢሆንም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘታቸውን እርግጠኞች ስለነበሩ ሌሎች እስረኞች ሊሰሙት በሚችሉ መጠን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ዘምረዋል! ዛሬም እምነታችን ሲፈተን የዚህ ዓይነት ጽኑ እምነት ሊኖረን ይገባል።
15 ዲያብሎስ የሚያመጣብን ፈተናዎች በርካታ ናቸው። ለአንዳንዶች ከቤተሰብ የሚመጣ ስደት ሊሆን ይችላል። በርካታ ወንድሞቻችን ሕግ ነክ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ከከሐዲዎች የሚሰነዘር ተቃውሞም ሊያጋጥም ይችላል። ገንዘብ ነክ ችግሮችና መተዳደሪያ የማግኘት ውጥረትም አለ። ወጣቶች በትምህርት ቤት የእኩያዎች ተጽእኖ ያጋጥማቸዋል። እነዚህን ፈተናዎች ስኬታማ በሆነ መንገድ መወጣት የምንችለው እንዴት ነው? ጽኑ እምነት ለመያዝ ምን ያስፈልጋል?
16 ከሁሉም በላይ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ የግል ዝምድና መመሥረት ይኖርብናል። ጳውሎስና ሲላስ በውስጠኛው እስር ቤት በተጣሉበት ወቅት ጊዜያቸውን ያሳለፉት ስለደረሰባቸው ሁኔታ በማማረር ወይም ባጋጠማቸው ሁኔታ በመተከዝ አልነበረም። ጊዜ ሳያባክኑ ወደ አምላክ ከመጸለያቸውም በላይ በመዝሙርም አወድሰውታል። ለምን? ከሰማያዊ አባታቸው ጋር የጠበቀ የግል ዝምድና ስለነበራቸው ነው። መከራ የደረሰባቸው ለጽድቅ ሲሉ እንደሆነና መዳናቸው በይሖዋ ላይ እንደተመካ ተገንዝበዋል።—መዝ. 3:8
17 ዛሬ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን እኛም ይሖዋን መጠባበቅ አለብን። ጳውሎስ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ‘በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችንን ካስታወቅን አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችንንና አሳባችንን እንደሚጠብቅ’ በመናገር አበረታቶናል። (ፊልጵ. 4:6, 7) ይሖዋ ፈተናዎች ሲደርሱብን በራሳችን እንድንወጣቸው እንደማይተወን ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! (ኢሳ. 41:10) ከልብ የመነጨ ጽኑ እምነት ይዘን እስካገለገልነው ድረስ ምን ጊዜም አይተወንም።—መዝ. 46:7
18 ጽኑ እምነት በማሳየት ረገድ ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግልን ሌላው ነገር በይሖዋ አገልግሎት መጠመዳችን ነው። (1 ቆሮ. 15:58) ጳውሎስና ሲላስ የታሰሩት ምሥራቹን በመስበክ ተጠምደው ስለነበረ ነው። በደረሱባቸው ፈተናዎች ምክንያት መስበካቸውን አቁመዋልን? በፍጹም። በእስር ላይ እያሉም ሆነ ከተፈቱ በኋላ መስበካቸውን ቀጥለዋል። ወደ ተሰሎንቄ ተጉዘው ወደ አይሁድ ምኩራብ በመሄድ ‘ከመጻሕፍት እየጠቀሱ ይነጋገሩ ነበር።’ (ሥራ 17:1-3) በይሖዋ ላይ እምነት እንድናሳድር የሚያስችለን አሳማኝ ምክንያት ሲኖረንና እውነትን ለመያዛችን እርግጠኞች ስንሆን ‘በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን የሚችል’ አንድም ነገር አይኖርም።—ሮሜ 8:35-39
19 ጽኑ እምነት ያላቸው ዘመናዊ ምሳሌዎች:- እንደ ጳውሎስና ሲላስ ሁሉ በዘመናችንም ጽኑ እምነት ያሳዩ ጎልተው የሚታዩ ብዙ ምሳሌዎች አሉ። ከኦሽዊትዝ የማጎሪያ ካምፕ በሕይወት የተረፈች አንዲት እህት በዚያ የነበሩ ወንድሞችና እህቶች ስላሳዩት ጽኑ እምነት ተናግራለች። እንዲህ ትላለች:- “አንድ ጊዜ ለምርመራ ቀርቤ ሳለ መኮንኑ እጁን ጨብጦ ወደ እኔ መጣ። ‘ምን ብናደርግባችሁ ነው የሚሻለው? ብትያዙ ግድ አይሰጣችሁም። ወደ እስር ቤት ብንልካችሁ ቅንጣት አያሳስባችሁም። ወደ ማጎሪያ ካምፕ ብንልካችሁ ምንም አያስጨንቃችሁም። ሞት ስንፈርድባችሁ ምንም አትረበሹም። ምን ብናደርግባችሁ ነው የሚሻለው?’ ሲል በቁጣ ተናገረ።” በእንዲህ ዓይነት አስከፊ ሁኔታዎች ሥር ወንድሞቻችን ያሳዩት እምነት ምንኛ እምነት የሚያጠናክር ነው! ጽናት ለማግኘት እንዲረዳቸው ዘወትር ይሖዋን ተጠባብቀዋል።
20 በቅርብ ዓመታት በተከሰተው የጎሳ ጥላቻ ወቅት ብዙ ወንድሞቻችን ያሳዩትን ጽኑ እምነት ፈጽሞ አንዘነጋውም። አደገኛ የሆኑ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም እንኳ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች፣ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው በመንፈሳዊ ተመግበው የማየት ፍላጎት ነበራቸው። ‘በእነሱ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ እንደማይከናወን’ ጽኑ እምነት በመያዝ ሁሉም በታማኝነት ይቀጥላሉ።—ኢሳ. 54:17
21 በተጨማሪም የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላቸው በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ብርቱ እምነትና ጽናት ያሳያሉ። በጓዴሎፕ የሚኖር አንድ ወንድም አማኝ ያልሆነችው ሚስቱ ከፍተኛ ተቃውሞ ታደርስበት ነበር። እሱን ተስፋ ለማስቆረጥና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንዳይገኝ ለማድረግ ብላ ምግብ አታዘጋጅለትም፣ ልብሶቹን አጥባ አትተኩስለትም እንዲሁም መሰፋት ያለበትንም አትሰፋለትም ነበር። ለረጅም ጊዜያት ጭራሽ ሳታነጋግረው ትሰነብታለች። ሆኖም ይህ ወንድም ይሖዋን በማገልገል ረገድ ጽኑ እምነት በማሳየትና እርዳታ ለማግኘት ወደ እሱ በመጸለይ ሁሉንም ነገር በጽናት ማሳለፍ ችሏል። ለምን ያህል ጊዜ? ለ20 ዓመታት ገደማ ነበር። ከዚህ በኋላ ቀስ በቀስ ልቧ እየተለወጠ ሄደ። የኋላ ኋላ የአምላክን መንግሥት ተስፋ በመቀበሏ ትልቅ ደስታ ሊያገኝ ችሏል።
22 በመጨረሻም በየቀኑ ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱትና የእኩዮችን ተጽእኖና ሌሎች ፈተናዎችን ለመጋፈጥ የሚገደዱት ወጣት ወንድሞችና እህቶች የሚያሳዩትን ጠንካራ እምነት መርሳት የለብንም። በትምህርት ቤት ከሌሎች ጋር ተመሳስሎ ለመኖር የሚያጋጥማቸውን ግፊት በተመለከተ አንዲት ወጣት ምሥክር እንዲህ ብላለች:- “ትምህርት ቤት ሁሉም የሚያበረታታችሁ ትንሽ ዓመፀኛ እንድትሆኑ ነው። አንድ አጠያያቂ ነገር ካደረጋችሁ ልጆቹ ለእናንተ ያላቸው አክብሮት ያድጋል።” ወጣቶቻችን የሚገጥማቸው ተጽዕኖ እንዴት ከፍተኛ ነው! የሚገጥማቸውን ፈተና ለመቋቋም በአእምሯቸውም ሆነ በልባቸው ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለባቸው።
23 አብዛኞቹ ወጣቶቻችን ፈተናዎች ቢገጥሟቸውም እንኳ ጽኑ አቋማቸውን በመጠበቅ ረገድ መልካም ተግባር እያከናወኑ ነው። በፈረንሳይ የምትኖር የአንዲት ወጣት እህት ሁኔታ ለዚህ ምሳሌ ይሆናል። አንድ ቀን ከምሳ በኋላ አንዳንድ ወንዶች ልጆች እንድትስማቸው ለማስገደድ ሞከሩ። ሆኖም በልቧ ጸልያ አጥብቃ ስለተቃወመቻቸው ልጆቹ ትተዋት ሄዱ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከእነሱ መካከል አንዱ ተመልሶ መጥቶ ላሳየችው ድፍረት አድናቆት እንዳደረበት ነገራት። የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸውን በረከቶች ማግኘት ከሚፈልጉ ሁሉ ይሖዋ የሚጠብቅባቸውን ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎች በመግለጽ ስለ መንግሥቱ ጥሩ ምሥክርነት ልትሰጠው ችላለች። በተጨማሪም በዚያ የትምህርት ዘመን ለክፍሉ ተማሪዎች ባጠቃላይ ስለምታምንባቸው ነገሮች ለመግለጽ የሚያስችል አጋጣሚ አግኝታለች።
24 ጽኑ እምነት በመያዝ ስለ ፈቃዱ እንዲናገሩ ይሖዋ ከሚጠቀምባቸው ሰዎቸ መካከል በመቆጠራችን ምንኛ ውድ መብት አግኝተናል! (ቆላ. 4:12) በተጨማሪም በአንበሳ የተመሰለው ጠላታችን ሰይጣን ዲያብሎስ ጥቃት ሲሰነዝርብን ጽኑ አቋም እንዳለን የማስመስከር ግሩም አጋጣሚ እናገኛለን። (1 ጴጥ. 5:8, 9) ይሖዋ የመንግሥቱን መልእክት ለምንሰብከው ለእኛም ሆነ መልእክቱን ለሚያዳምጡ ሰዎች መዳን ለማምጣት በመልእክቱ እየተጠቀመ እንዳለ ፈጽሞ አትዘንጉ። የምናደርገው ውሳኔም ሆነ ዕለታዊ አኗኗራችን መንግሥቱን እንደምናስቀድም የሚያሳይ ይሁን። ጽኑ እምነት በመያዝ ምሥራቹን መስበካችንን እንቀጥል!