ምዕራፍ 21
የአምላክ መንግሥት ጠላቶቹን ያጠፋል
1, 2. (ሀ) ንጉሣችን ከ1914 ጀምሮ እየገዛ መሆኑን የሚያረጋግጡ ምን ማስረጃዎች አሉ? (ለ) በዚህ ምዕራፍ ላይ የትኞቹን ነጥቦች እንመረምራለን?
የአምላክ መንግሥት በጠላቶቹ መካከል በሚገዛበት ወቅት እየፈጸማቸው ያሉትን ነገሮች መለስ ብለን መመልከታችን እምነታችንን አጠናክሮልናል። (መዝ. 110:2) ንጉሣችን በገዛ ፈቃዱ የሚያገለግል የሰባኪዎች ሠራዊት አደራጅቷል። ተከታዮቹን በመንፈሳዊና በሥነ ምግባራዊ ሁኔታ አጥርቷል እንዲሁም አንጽቷል። የመንግሥቱ ጠላቶች እኛን ለመከፋፈል ያልፈነቀሉት ድንጋይ ባይኖርም በዛሬው ጊዜ ዓለም አቀፋዊ አንድነት አለን። እነዚህና እስካሁን የተመለከትናቸው መንግሥቱ ያከናወናቸው ሌሎች በርካታ ነገሮች ንጉሣችን ከ1914 ጀምሮ በጠላቶቹ መካከል እየገዛ መሆኑን የሚያረጋግጡ ጠንካራ ማስረጃዎች ናቸው።
2 የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ደግሞ ከዚህ ይበልጥ አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን ያከናውናል። መንግሥቱ ‘ሲመጣ’ ጠላቶቹን “ያደቅቃል፤ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል።” (ማቴ. 6:10፤ ዳን. 2:44) ይህ ከመሆኑ በፊት ግን መፈጸም ያለባቸው ሌሎች ወሳኝ ነገሮች አሉ። እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው? የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጡናል። ከፊታችን ምን ክንውኖች እንደሚጠብቁን ለማወቅ ከእነዚህ ትንቢቶች አንዳንዶቹን እስቲ እንመርምር።
“ያልታሰበ ጥፋት” ከመምጣቱ በፊት የሚፈጸሙ ነገሮች
3. በቅርቡ እንደሚፈጸሙ ከምንጠብቃቸው ነገሮች መካከል የመጀመሪያው ምንድን ነው?
3 ሰላምን ማወጅ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ በቅርቡ እንደሚፈጸሙ ከምንጠብቃቸው ነገሮች መካከል የመጀመሪያውን ገልጿል። (1 ተሰሎንቄ 5:2, 3ን አንብብ።) ጳውሎስ በዚህ ደብዳቤ ላይ ስለ “ይሖዋ ቀን” የተናገረ ሲሆን ይህ ቀን የሚጀምረው ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ ላይ በሚመጣው ጥፋት ነው። (ራእይ 17:5) ሆኖም የይሖዋ ቀን ከመጀመሩ ትንሽ ቀደም ብሎ ብሔራት “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” ይላሉ። ይህ አገላለጽ አንድ ጊዜ የሚነገር አዋጅን አሊያም ተከታታይ የሆኑ ትኩረት የሚስቡ መግለጫዎችን ሊያመለክት ይችላል። የሃይማኖት መሪዎች በዚህ አዋጅ ይካፈሉ ይሆን? የዓለም ክፍል እንደመሆናቸው መጠን ከብሔራት ጋር ሆነው “ሰላም” እንዳለ መግለጻቸው አይቀርም። (ኤር. 6:14፤ 23:16, 17፤ ራእይ 17:1, 2) ሰላምና ደህንነት እንዳለ የሚገልጸው ይህ አዋጅ የይሖዋ ቀን ሊጀምር እንደተቃረበ ይጠቁማል። የአምላክ መንግሥት ጠላቶች ከጥፋቱ “በምንም ዓይነት አያመልጡም።”
4. ጳውሎስ ‘ሰላምና ደህንነት ሆነ’ ስለሚለው አዋጅ የተናገረውን ትንቢት ትርጉም መረዳታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
4 የዚህን ትንቢት ትርጉም መረዳታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? ጳውሎስ “እናንተ . . . በጨለማ ውስጥ ስላልሆናችሁ ሌሊቱ ድንገት እንደሚነጋበት ሌባ፣ ያ ቀን ድንገት አይደርስባችሁም” ብሏል። (1 ተሰ. 5:3, 4) ከአብዛኛው ሕዝብ በተለየ እኛ በአሁኑ ጊዜ ያሉት ሁኔታዎች ወዴት እንደሚያመሩ እናስተውላለን። ስለ ሰላምና ደህንነት የሚገልጸው ትንቢት የሚፈጸመው በምን መንገድ ነው? ይህ ጊዜው ሲደርስ የምናየው ይሆናል። እንግዲያው “ነቅተን እንኑር እንዲሁም የማስተዋል ችሎታችንን እንጠብቅ።”—1 ተሰ. 5:6፤ ሶፎ. 3:8
የታላቁ መከራ መጀመር
5. ‘ታላቁ መከራ’ የሚጀምረው እንዴት ነው?
5 በሃይማኖት ላይ የሚሰነዘር ጥቃት። ጳውሎስ “‘ሰላምና ደህንነት ሆነ!’ ሲሉ . . . ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል” ብሎ እንደጻፈ አስታውስ። የመብረቅ ብልጭታ እንደታየ ወዲያው ነጎድጓድ እንደሚሰማ ሁሉ “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” የሚለውን አዋጅ ተከትሎም በድንገት “ያልታሰበ ጥፋት” ይመጣል። ጥፋቱ የሚመጣው በማን ላይ ነው? መጀመሪያ የምትጠፋው በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ የምታመለክተውና “አመንዝራዋ” በመባልም የምትታወቀው “ታላቂቱ ባቢሎን” ናት። (ራእይ 17:5, 6, 15) ሕዝበ ክርስትናና ሌሎች የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ ሲጠፉ ‘የታላቁ መከራ’ የመጀመሪያ ምዕራፍ ይጀምራል። (ማቴ. 24:21፤ 2 ተሰ. 2:8) ይህ ክስተት ለብዙዎች ድንገተኛ ይሆንባቸዋል። ለምን? እስከዚያ ጊዜ ድረስ አመንዝራዋ “ንግሥት” እንደሆነችና “ሐዘንም ፈጽሞ [እንደማይደርስባት]” ስለምታስብ ነው። ይሁንና የታመነችባቸው ሁሉ እንደከዷት በድንገት ትገነዘባለች። አመንዝራዋ “በአንድ ቀን” የሆነ ያህል በቅጽበት ትወገዳለች።—ራእይ 18:7, 8
6. ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ ላይ ጥቃት የሚሰነዝረው ማን ወይም ምንድን ነው?
6 ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ ላይ ጥቃት የሚሰነዝረው ማን ወይም ምንድን ነው? “አሥር ቀንዶች” ያሉት “አውሬ” ነው። የራእይ መጽሐፍ ይህ አውሬ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን እንደሚያመለክት ያሳያል። አሥሩ ቀንዶች ደግሞ ይህን “ደማቅ ቀይ አውሬ” የሚደግፉትን በአሁኑ ጊዜ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ያመለክታሉ። (ራእይ 17:3, 5, 11, 12) ጥቃቱ ምን ያህል ከባድ ይሆናል? የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል የሆኑት መንግሥታት የአመንዝራዋን ሀብት ይበዘብዛሉ፣ ሥጋዋን ይበላሉ፤ “ሙሉ በሙሉም በእሳት ያቃጥሏታል።”—ራእይ 17:16ን አንብብ።a
7. ኢየሱስ በማቴዎስ 24:21, 22 ላይ የተናገረው ትንቢት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? ወደፊትስ ምን ፍጻሜ ይኖረዋል?
7 ቀኖቹን ማሳጠር። ንጉሣችን በዚህ ወቅት ማለትም ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ ምን እንደሚፈጸም ነግሮናል። ኢየሱስ “ለተመረጡት ሲባል ቀኖቹ ያጥራሉ” ብሏል። (ማቴዎስ 24:21, 22ን አንብብ።) ኢየሱስ የተናገረው ይህ ትንቢት በ66 ዓ.ም. በተወሰነ መጠን ፍጻሜውን አግኝቷል፤ በዚያ ወቅት ይሖዋ፣ የሮም ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ የሰነዘረው ጥቃት ‘እንዲያጥር’ አድርጓል። (ማር. 13:20) ይህ ሁኔታ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የነበሩት ክርስቲያኖች እንዲተርፉ መንገድ ከፍቷል። ታዲያ በመጪው ታላቅ መከራ ወቅት በዓለም ዙሪያ ምን ይከናወናል? ይሖዋ፣ እውነተኛው ሃይማኖት ከሐሰት ሃይማኖት ጋር እንዳይጠፋ ሲል የተባበሩት መንግሥታት በሃይማኖት ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት ‘ለማሳጠር’ በንጉሣችን ይጠቀማል። በዚህ መንገድ የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች በሙሉ ሲጠፉ እውነተኛው አንድ ሃይማኖት ግን ይተርፋል። (መዝ. 96:5) ይሄኛው የታላቁ መከራ ምዕራፍ ከተጠናቀቀ በኋላ ምን እንደሚፈጸም ደግሞ እስቲ እንመልከት።
ወደ አርማጌዶን የሚመሩ ክስተቶች
8, 9. ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ምን ዓይነት ክስተት እንደሚኖር የሚያሳይ ሊሆን ይችላል? ሰዎች እነዚህን ነገሮች ሲመለከቱ ምን ይሰማቸዋል?
8 ኢየሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት የተናገረው ትንቢት ከአርማጌዶን በፊት ባለው ጊዜ፣ ትልቅ ትርጉም ያላቸው የተለያዩ ክስተቶች እንደሚኖሩ ይጠቁማል። ከዚህ በመቀጠል የምንመረምራቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ክስተቶች በማቴዎስ፣ በማርቆስ እንዲሁም በሉቃስ ወንጌሎች ላይ ተጠቅሰዋል።—ማቴዎስ 24:29-31ን አንብብ፤ ማር. 13:23-27፤ ሉቃስ 21:25-28
9 በሰማይ አካላት ላይ የሚታይ ምልክት። ኢየሱስ “ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ” በማለት ተናግሯል። ሰዎች ብርሃን ወይም መመሪያ ለማግኘት ወደ ሃይማኖት መሪዎች ዘወር ማለታቸው እንደሚያከትም ግልጽ ነው። በዚህ ትንቢት ላይ ኢየሱስ፣ በሰማይ እንግዳ ነገሮች እንደሚታዩም መግለጹ ይሆን? ሊሆን ይችላል። (ኢሳ. 13:9-11፤ ኢዩ. 2:1, 30, 31) ሰዎች እነዚህን ነገሮች ሲመለከቱ ምን ይሰማቸው ይሆን? “የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ይጨነቃሉ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሉቃስ 21:25፤ ሶፎ. 1:17) ‘ከነገሥታት’ እስከ “ባሪያዎች” ያሉ የአምላክ መንግሥት ጠላቶች “ከፍርሃትና በዓለም ላይ የሚመጡትን ነገሮች ከመጠበቅ የተነሳ ይዝለፈለፋሉ።” እንዲሁም መሸሸጊያ ለማግኘት ይሮጣሉ፤ ይሁን እንጂ ከንጉሣችን ቁጣ ለማምለጥ የሚያስችላቸው መደበቂያ አያገኙም።—ሉቃስ 21:26፤ 23:30፤ ራእይ 6:15-17
10. ኢየሱስ ምን ዓይነት ፍርድ ይሰጣል? የአምላክ መንግሥት ደጋፊዎችም ሆኑ ተቃዋሚዎች ፍርዱን ሲሰሙ ምን ያደርጋሉ?
10 ፍርድ መስጠት። ከዚህ በኋላ የአምላክ መንግሥት ጠላቶች በሙሉ ጭንቀታቸውን የሚያባብስ ነገር ለመመልከት ይገደዳሉ። ኢየሱስ “የሰው ልጅ በታላቅ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል” በማለት ተናግሯል። (ማር. 13:26) ኢየሱስ ኃይሉን በሚያሳይ እንዲህ ባለ እንግዳ የሆነ መንገድ መገለጡ ፍርድ ለመስጠት መምጣቱን የሚጠቁም ነው። ኢየሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት የተናገረው የዚሁ ትንቢት ሌላ ክፍል በዚህ ወቅት የሚሰጠውን ፍርድ በተመለከተ ዝርዝር ሐሳቦችን ይዟል። ይህን ሐሳብ ኢየሱስ ስለ በጎችና ፍየሎች በተናገረው ምሳሌ ላይ እናገኘዋለን። (ማቴዎስ 25:31-33, 46ን አንብብ።) የአምላክ መንግሥት ታማኝ ደጋፊዎች ‘በጎች’ እንደሆኑ ይፈረድላቸዋል፤ እነሱም ‘መዳናቸው እየቀረበ እንደሆነ’ ስለሚገነዘቡ ‘ራሳቸውን ቀና ያደርጋሉ።’ (ሉቃስ 21:28) የአምላክ መንግሥት ተቃዋሚዎች ግን ‘ፍየሎች’ እንደሆኑ ይፈረድባቸዋል፤ ፍየሎቹም ‘የዘላለም ጥፋት’ እንደሚጠብቃቸው ስለሚገነዘቡ “በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ።”—ማቴ. 24:30፤ ራእይ 1:7
11. ወደፊት የሚፈጸሙትን ነገሮች ስንመረምር ልናስታውሰው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
11 ኢየሱስ ‘በሕዝቦች ሁሉ’ ላይ ከፈረደ በኋላ የአርማጌዶን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት የሚፈጸሙ ሌሎች ወሳኝ ክንውኖችም ይኖራሉ። (ማቴ. 25:32) ከእነዚህ ክንውኖች ሁለቱን ይኸውም የጎግን ጥቃት እና የቅቡዓኑን መሰብሰብ ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን። ይሁንና እነዚህን ክንውኖች ስንመረምር የአምላክ ቃል እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙበትን ጊዜ እንደማይናገር ማስታወስ ይኖርብናል። እንዲያውም አንደኛው ክንውን የሚፈጸምበት ጊዜ ሌላኛው ከሚፈጸምበት ጊዜ ጋር በተወሰነ መጠን ተመሳሳይ የሚሆን ይመስላል።
12. ሰይጣን በአምላክ መንግሥት ላይ ምን ዓይነት መጠነ ሰፊ ጥቃት ይከፍታል?
12 መጠነ ሰፊ ጥቃት። የማጎጉ ጎግ በቅቡዓን ቀሪዎችና አጋሮቻቸው በሆኑት ሌሎች በጎች ላይ ጥቃት ይሰነዝራል። (ሕዝቅኤል 38:2, 11ን አንብብ።) ሰይጣን በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ላይ የሚሰነዝረው ይህ ጥቃት፣ ከሰማይ ከተወረወረ ጀምሮ በቅቡዓኑ ላይ ሲያካሂድ የነበረው ጦርነት የመጨረሻ ክፍል ይሆናል። (ራእይ 12:7-9, 17) ቅቡዓኑ፣ ክርስቶስ ወዳነጻው የክርስቲያን ጉባኤ መሰብሰብ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ሰይጣን መንፈሳዊ ብልጽግናቸውን ለማጥፋት ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም ሙከራው ከንቱ ሆኗል። (ማቴ. 13:30) ያም ቢሆን የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች በሙሉ ከጠፉ በኋላ የአምላክ ሕዝቦች “ቅጥር፣ መቀርቀሪያና በር በሌላቸው ሰፈሮች” የሚኖሩ ስለሚመስሉ ሰይጣን እነሱን ለማጥፋት ጥሩ አጋጣሚ እንዳገኘ ይሰማዋል። ክፉ የሆኑ ተከታዮቹን፣ በመንግሥቱ ደጋፊዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ያነሳሳቸዋል።
13. ይሖዋ በምድር ያሉ አገልጋዮቹን ለመታደግ ምን እርምጃ ይወስዳል?
13 ሕዝቅኤል በዚህ ወቅት ምን እንደሚፈጸም ገልጿል። ጎግን በተመለከተ ትንቢቱ እንዲህ ይላል፦ “አንተ ከስፍራህ ይኸውም ርቆ ከሚገኘው የሰሜን ምድር ትመጣለህ፤ አንተና ከአንተ ጋር ያሉ ብዙ ሕዝቦች ትመጣላችሁ፤ ሁሉም በፈረሶች ላይ የተቀመጡ፣ ታላቅ ጉባኤና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት ናቸው። ምድርን እንደሚሸፍን ደመና ሆነህ በሕዝቤ . . . ላይ ትመጣለህ።” (ሕዝ. 38:15, 16) ማንም የሚያቆመው የሌለ የሚመስለው ይህ ወረራ ሲጀመር ይሖዋ ምን ያደርግ ይሆን? “ታላቅ ቁጣዬ ይነድዳል” እንዲሁም “ሰይፍ እጠራለሁ” ብሏል። (ሕዝ. 38:18, 21፤ ዘካርያስ 2:8ን አንብብ።) ይሖዋ በምድር ያሉ አገልጋዮቹን ለመታደግ ሲል ጣልቃ ይገባል። በዚህ ጊዜ የአርማጌዶን ጦርነት ይጀምራል።
14, 15. ሰይጣን መጠነ ሰፊ ጥቃት መሰንዘር ከጀመረ በኋላ በሆነ ወቅት ላይ ምን ሌላ ክንውን ይፈጸማል?
14 በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ይሖዋ ሕዝቡን እንዴት እንደሚጠብቃቸው ከመመልከታችን በፊት፣ ትኩረት የሚስብ ሌላ ክስተት እንመርምር። ይህ ክንውን የሚፈጸመው ሰይጣን መጠነ ሰፊ ጥቃት መሰንዘር ከጀመረ በኋላ ሆኖም ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ የአርማጌዶን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። በአንቀጽ 11 ላይ እንደተገለጸው ይህ ክንውን የቅቡዓን ቀሪዎች መሰብሰብ ነው።
15 የቅቡዓኑ መሰብሰብ። ማቴዎስም ሆነ ማርቆስ ኢየሱስ ‘ስለተመረጡት’ ይኸውም በመንፈስ ስለተቀቡት ክርስቲያኖች የተናገረውን ሐሳብ የመዘገቡት የአርማጌዶን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ከሚፈጸሙት ተከታታይ ክስተቶች አንዱ እንደሆነ አድርገው ነው። (አንቀጽ 7ን ተመልከት።) ኢየሱስ፣ ራሱን ንጉሥ እንደሆነ አድርጎ በመግለጽ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል፦ “እሱም መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፣ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ ለእሱ የተመረጡትን ይሰበስባል።” (ማር. 13:27፤ ማቴ. 24:31) ኢየሱስ እዚህ ላይ የተናገረው ስለ የትኛው የመሰብሰብ ሥራ ነው? በምድር ላይ ባሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ላይ የመጨረሻውን ማኅተም ስለማድረግ አይደለም፤ ምክንያቱም ይህ የሚሆነው ታላቁ መከራ ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ነው። (ራእይ 7:1-3) ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ የተናገረው በመጪው ታላቅ መከራ ወቅት ስለሚፈጸም ክንውን ነው። በመሆኑም ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት መሰንዘር ከጀመረ በኋላ በሆነ ወቅት ላይ ቅቡዓን ቀሪዎች ወደ ሰማይ የሚሰበሰቡ ይመስላል።
16. ትንሣኤ ያገኙት ቅቡዓን በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ምን ሚና ይኖራቸዋል?
16 ይህ የቅቡዓን ቀሪዎች መሰብሰብ፣ ቀጥሎ ከሚከናወነው ነገር ይኸውም ከአርማጌዶን ጦርነት ጋር ምን ግንኙነት አለው? ቅቡዓኑ የሚሰበሰቡበት ጊዜ እንደሚጠቁመው የአምላክ ጦርነት የሆነው አርማጌዶን ከመጀመሩ በፊት ቅቡዓን በሙሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ። በሰማይም 144,000ቹ የክርስቶስ ተባባሪ ገዢዎች ከኢየሱስ ጋር ሆነው “በብረት በትር” በመጠቀም የአምላክን መንግሥት ጠላቶች በሙሉ እንዲያጠፉ ሥልጣን ይሰጣቸዋል። (ራእይ 2:26, 27) ከዚያም ትንሣኤ ያገኙት ቅቡዓን ከኃያላን መላእክት ጋር በመሆን ተዋጊውን ንጉሥ ክርስቶስን ተከትለው የይሖዋን ሕዝብ ለማጥፋት ካሰፈሰፈው “ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት” ጋር ውጊያ ይገጥማሉ። (ሕዝ. 38:15) የኃይል እርምጃ የሚወሰድበት ይህ ውጊያ ሲካሄድ አርማጌዶን ጀመረ ማለት ነው!—ራእይ 16:16
የታላቁ መከራ ታላቅ መደምደሚያ
17. ‘ፍየል’ እንደሆኑ የተፈረደባቸው ሰዎች በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ምን ይሆናሉ?
17 ፍርዱን ማስፈጸም። የአርማጌዶን ጦርነት የታላቁ መከራ የመጨረሻው ምዕራፍ ይሆናል። በዚህ ወቅት ኢየሱስ ተጨማሪ ኃላፊነት ይሰጠዋል። ‘በሕዝቦች ሁሉ’ ላይ ከመፍረድ በተጨማሪ በብሔራት ላይ የቅጣት እርምጃ ይወስዳል፤ ይኸውም ቀደም ሲል ‘ፍየሎች’ እንደሆኑ በፈረደባቸው ሰዎች ሁሉ ላይ ፍርዱን ያስፈጽማል። (ማቴ. 25:32, 33) ንጉሣችን ‘በረጅም ስለታም ሰይፍ ብሔራትን ይመታል።’ ፍየል እንደሆኑ የተፈረደባቸው ሰዎች በሙሉ ‘ነገሥታትም’ ሆኑ “ባሪያዎች” “ወደ ዘላለም ጥፋት . . . ይሄዳሉ።”—ራእይ 19:15, 18፤ ማቴ. 25:46
18. (ሀ) ‘በጎች’ እንደሆኑ ከተፈረደላቸው ሰዎች ጋር በተያያዘ ሁኔታዎቹ በአስገራሚ መንገድ የሚለወጡት እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ድሉን የሚያጠናቅቀው እንዴት ነው?
18 ኢየሱስ ‘በጎች’ እንደሆኑ ከፈረደላቸው ሰዎች ጋር በተያያዘ ግን ሁኔታዎቹ በአስገራሚ መንገድ ይለወጣሉ! ‘በፍየል’ በተመሰለው የሰይጣን ታላቅ ሠራዊት ሊጨፈለቁ የነበሩት መከላከያ የሌላቸው የሚመስሉ ‘በጎች’ ማለትም “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ከጠላት ጥቃት ተርፈው ‘ታላቁን መከራ ያልፋሉ።’ (ራእይ 7:9, 14) ከዚያም ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ጠላት የሆኑ ሰዎችን በሙሉ ድል ካደረገና ካጠፋቸው በኋላ ሰይጣንንና አጋንንቱን ወደ ጥልቁ ይወረውራቸዋል። በዚያም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ በማያደርጉበት እንደ ሞት ያለ ሁኔታ ውስጥ ለአንድ ሺህ ዓመት ይቆያሉ።—ራእይ 6:2ን እና 20:1-3ን አንብብ።
ራሳችንን ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
19, 20. ከኢሳይያስ 26:20 እና 30:21 የምናገኘውን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
19 ወደፊት ለሚመጡት ምድርን የሚያናውጡ ክንውኖች ራሳችንን ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የወጣ አንድ መጠበቂያ ግንብ “ለመዳን ታዛዥነት አስፈላጊ” እንደሆነ ገልጾ ነበር። እንዲህ የምንልበት ምክንያት ምንድን ነው? ይሖዋ፣ በጥንቷ ባቢሎን በምርኮ ለነበሩት አይሁዳውያን የሰጠው ማሳሰቢያ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። ይሖዋ፣ ባቢሎን ድል እንደምትሆን ትንቢት ተናግሮ ነበር፤ ታዲያ የአምላክ ሕዝቦች ለዚህ ወቅት መዘጋጀት የሚችሉት እንዴት ነበር? ይሖዋ “ሕዝቤ ሆይ፣ ሂድ ወደ ውስጠኛው ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ከኋላህ ዝጋ። ቁጣው እስኪያልፍ ድረስ ለጥቂት ጊዜ ተሸሸግ” ብሏቸዋል። (ኢሳ. 26:20) “ሂድ፣” “ግባ፣” “ዝጋ” እና “ተሸሸግ” የሚሉት በዚህ ጥቅስ ላይ ያሉት ግሶች በሙሉ በትእዛዝ መልክ የቀረቡ መሆናቸውን ልብ በል። ይህንን ትእዛዝ ተግባራዊ ያደረጉ አይሁዳውያን በጎዳናዎቹ ላይ ከነበሩት ወራሪ ወታደሮች ሸሽተው ቤታቸው ገብተው እንደሚሆን የታወቀ ነው። መዳናቸው የይሖዋን መመሪያዎች በመታዘዛቸው ላይ የተመካ ነበር።b
20 ከዚህ ሐሳብ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? እንደ እነዚያ የጥንት የአምላክ አገልጋዮች ሁሉ እኛም በቅርቡ ከሚመጡት ክንውኖች መትረፋችን የተመካው የይሖዋን መመሪያዎች በመታዘዛችን ላይ ነው። (ኢሳ. 30:21) እነዚህን መመሪያዎች የምናገኘው ደግሞ በጉባኤ በኩል ነው። በመሆኑም የሚሰጠንን መመሪያ ከልብ የመታዘዝ ልማድ ማዳበር ይኖርብናል። (1 ዮሐ. 5:3) በአሁኑ ጊዜ የሚሰጡንን መመሪያዎች የምንታዘዝ ከሆነ ወደፊት እንዲህ ማድረግ ቀላል ይሆንልናል፤ ይህም የአባታችንን የይሖዋንና የንጉሣችንን የኢየሱስን ጥበቃ ያስገኝልናል። (ሶፎ. 2:3) አምላክ የሚያደርግልን ጥበቃ፣ የአምላክ መንግሥት ጠላቶቹን በሙሉ ሲያስወግድ የዓይን ምሥክሮች ለመሆን ያስችለናል። ያ ክንውን ፈጽሞ ከአእምሯችን እንደማይጠፋ ጥርጥር የለውም!
a ‘የታላቂቱ ባቢሎን’ ጥፋት በዋነኝነት የሚያመለክተው የሃይማኖት ተቋማት እንደሚጠፉ እንጂ ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በጅምላ እንደሚገደሉ አይደለም ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ይመስላል። በመሆኑም አብዛኞቹ የታላቂቱ ባቢሎን የቀድሞ ተከታዮች ከጥፋቱ የሚተርፉና በዘካርያስ 13:4-6 ላይ እንደተገለጸው በግልጽ ከሃይማኖት ለመራቅ የሚሞክሩ ይመስላል።
b ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 1 የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 282-283 ተመልከት።