ፀረ ክርስቶስ ማን ነው?
ፍሬድሪክ ኒትሽ የሚባል የ19ኛው መቶ ዘመን ፈላስፋ ከሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹ መካከል አንዱን ፀረ ክርስቶስ ብሎ ሰይሞት ነበር።
በመካከለኛው ዘመን የኖሩ ነገሥታት ብዙውን ጊዜ ተፎካካሪዎቻቸውን ፀረ ክርስቶሶች እያሉ ይጠሯቸው ነበር።
ጀርመናዊው የተሃድሶ መሪ ማርቲን ሉተር የሮምን የካቶሊክ ጳጳሳት ፀረ ክርስቶሶች ብሏቸው ነበር።
“ፀረ ክርስቶስ” የሚለው ስያሜ ለረጅም ጊዜ ለነገሥታትም ሆነ ለፊልሞች የተሠራበት ሐረግ ነው፤ ስለሆነም ፀረ ክርስቶስ ማን ነው? ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው። ለመሆኑ ይህ አባባል በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛ ምን ትርጉም አለው? ፀረ ክርስቶስ የሚለው ሐረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አምስት ጊዜ ያህል ስለሚገኝ የፀረ ክርስቶስን ማንነት ለማወቅ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዞር ማለታችን የተገባ ነው።
ፀረ ክርስቶስ ተገለጠ
“ፀረ ክርስቶስ” የሚለውን ቃል የተጠቀመው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ሐዋርያው ዮሐንስ ብቻ ነው። ይህ ሐዋርያ ፀረ ክርስቶስን የገለጸው እንዴት ነው? በስሙ በተሰየመው የመጀመሪያ መልእክቱ ላይ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “ልጆቼ ሆይ፣ ይህ የመጨረሻው ሰዓት ነው፤ እንደሰማችሁትም ፀረ ክርስቶስ እየመጣ ነው፤ አሁንም እንኳ ብዙ ፀረ ክርስቶሶች መጥተዋል፤ ከዚህም በመነሳት ይህ የመጨረሻው ሰዓት መሆኑን እናውቃለን። በእኛ መካከል ነበሩ፤ ሆኖም ከእኛ ወገን ስላልነበሩ ትተውን ሄደዋል። . . . ኢየሱስን፣ ክርስቶስ አይደለም ብሎ ከሚክድ በቀር ውሸታም ማን ነው? ይህ አብንና ወልድን የሚክደው ፀረ ክርስቶስ ነው።”—1 ዮሐንስ 2:18, 19, 22
ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ ሆን ብሎ ውሸት የሚናገር እንዲሁም ያስተማራቸውን ትምህርቶች የሚያጣምም ሁሉ ፀረ ክርስቶስ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር
ከዚህ ጥቅስ ምን እንማራለን? ዮሐንስ “ብዙ ፀረ ክርስቶሶች” በማለት የጠቀሰው ሐሳብ ፀረ ክርስቶስ አንድን ግለሰብ ሳይሆን ብዙዎችን የሚያመለክት እንደሆነ ይጠቁማል። ፀረ ክርስቶስ ተብለው የሚፈረጁት ሰዎች ወይም ድርጅቶች ሐሰትን ያስፋፋሉ፤ ኢየሱስ፣ ክርስቶስ ወይም መሲሕ መሆኑን ይክዳሉ፤ እንዲሁም በአምላክና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል ያለውን ዝምድና በተመለከተ እውነቱን ለማጣመም ይጥራሉ። በተጨማሪም ክርስቶስ ነን ወይም የእሱ ወኪሎች ነን ብለው ይናገራሉ፤ ይሁን እንጂ “ትተውን ሄደዋል” ስለሚል ከእውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያፈነገጡ ናቸው። በተጨማሪም ዮሐንስ ደብዳቤውን በጻፈበት ጊዜ ይህ ቡድን እንደነበር ጥርጥር የለውም፤ ይህ ወቅት “የመጨረሻው ሰዓት” ማለትም የሐዋርያት ዘመን ማብቂያ የተቃረበበት ጊዜ እንደሆነ ይታመናል።
ዮሐንስ ፀረ ክርስቶስን አስመልክቶ ሌላስ ምን የጻፈው ነገር አለ? ዮሐንስ የሐሰት ነቢያትን በተመለከተ እንደሚከተለው በማለት አስጠንቅቋል፦ “ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የሚመሠክር በመንፈስ የተነገረ ቃል ሁሉ ከአምላክ የመነጨ ነው። ሆኖም ስለ ኢየሱስ የማይመሠክር በመንፈስ የተነገረ ቃል ሁሉ ከአምላክ የሚመነጭ አይደለም። ይህ በመንፈስ የተነገረ ቃል ከፀረ ክርስቶስ የሚመነጭ ነው፤ ፀረ ክርስቶስ እንዲህ ያሉ ነገሮችን እንደሚናገር ሰምታችኋል፤ አሁንም እንኳ ይህ ቃል በዓለም ላይ እየተነገረ ነው።” (1 ዮሐንስ 4:2, 3) ከዚያም ዮሐንስ በሁለተኛ መልእክቱ ላይ “ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መምጣቱን አምነው የማይቀበሉ ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ወጥተዋልና። እንዲህ ያለ ሰው አሳችና ፀረ ክርስቶስ ነው” በማለት ይህን ነጥብ በድጋሚ ተናግሯል። (2 ዮሐንስ 7) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ ሆን ብሎ ውሸት የሚናገር እንዲሁም ያስተማራቸውን ትምህርቶች የሚያጣምም ሁሉ ፀረ ክርስቶስ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር።
“ሐሰተኛ ነቢያት” እና “የዓመፅ ሰው”
ዮሐንስ እንደነዚህ ስላሉት ሃይማኖታዊ አታላዮች ከመጻፉ ከረጅም ጊዜ በፊት ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን እንዲህ በማለት መክሯቸዋል፦ “በውስጣቸው ነጣቂ ተኩላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው ወደ እናንተ ከሚመጡ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ።” (ማቴዎስ 7:15) ሐዋርያው ጳውሎስም በተመሳሳይ በተሰሎንቄ የነበሩትን ክርስቲያኖች እንደሚከተለው በማለት አስጠንቅቋቸው ነበር፦ “ማንም ሰው በምንም መንገድ አያሳስታችሁ፤ ምክንያቱም በመጀመሪያ ክህደቱ ሳይመጣና የጥፋት ልጅ የሆነው የዓመፅ ሰው ሳይገለጥ ያ ቀን [የይሖዋ ቀን] አይመጣም።”—2 ተሰሎንቄ 2:3
ስለዚህ ሐሰተኛ ነቢያትና ከሃዲዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ቢሆን የክርስቲያን ጉባኤን ለማዳከም እየጣሩ ነበር። ዮሐንስ “ፀረ ክርስቶስ” በማለት የጠራው ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ ውሸት የሚናገሩትንና ያስተማራቸውን ትምህርቶች የሚያጣምሙትን ሁሉ ነው። ጳውሎስ እነሱን “የጥፋት ልጅ” ብሎ መጥራቱ ይሖዋ ለእነሱ ያለውን አመለካከት የሚያሳይ ነው።
በዛሬው ጊዜ ፀረ ክርስቶሶች ከሚያደርጓቸው ነገሮች ራቁ
በዛሬው ጊዜም ፀረ ክርስቶስ ተብለው የሚፈረጁት ሰዎችና ድርጅቶች ክርስቶስንም ሆነ የእሱን ትምህርቶች ይቃወማሉ። አባት ስለሆነው ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ሰዎች ግራ እንዲጋቡ ለማድረግ ሆን ብለው የሐሰት ትምህርቶችንና ማታለያዎችን ያስፋፋሉ። እንዲህ ከመሰሉት ሃይማኖታዊ ማታለያዎች ራሳችንን እንድንጠብቅ የሚያነሳሱ በቂ ምክንያቶች አሉን፤ እስቲ ከእነዚህ መካከል ሁለቱን እንመልከት።
ለብዙ መቶ ዘመናት አብያተ ክርስቲያናት አብና ልጁ አንድ አካል ናቸው በማለት የሥላሴን ትምህርት ሲያስተምሩ ኖረዋል። በመሆኑም ፀረ ክርስቶስ የይሖዋ አምላክንና የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት ሰውሮታል። ይህ ሚስጥር ቅን የሆኑ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያበረታታው ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል ወደ አምላክ መቅረብ እንዳይችሉ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 11:1፤ ያዕቆብ 4:8
አብያተ ክርስቲያናት ይሖዋ የተባለው የአምላክ የግል ስም የማይገኝባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንዲጠቀሙ በማበረታታት ሰዎች የአብንና የልጁን ማንነት በተመለከተ ይበልጥ ግራ እንዲጋቡ አድርገዋል። ይህን ያደረጉት በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ላይ 7,000 ጊዜ ያህል ሰፍሮ የሚገኘውን ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ከትርጉሞቻቸው ውስጥ በማውጣት ነው። ውጤቱስ ምን ሆነ? የእውነተኛው አምላክ ማንነት ይበልጥ ሚስጥር እየሆነ መጣ።
በሌላ በኩል ደግሞ ቅን ልብ ያላቸው ብዙ ሰዎች ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም ማወቃቸው ወደ አምላክ ይበልጥ እንዲቀርቡ አድርጓቸዋል። የሪቻርድ ተሞክሮ ይህን የሚያሳይ ነው። ይህ ሰው ከሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረገውን ውይይት በማስታወስ እንዲህ ይላል፦ “ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የእውነተኛው አምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን አሳዩኝ። አምላክ ስም እንዳለው ማወቄ በጣም አስገረመኝ፤ ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ ነገር ሰምቼ አላውቅም።” ሪቻርድ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር ተስማምቶ ለመኖርና ይሖዋን ለማስደሰት ሲል ለውጥ ማድረግ ጀመረ። “የአምላክን ስም ማወቄ ከእሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንድመሠርት ረድቶኛል” ብሏል።
ለብዙ መቶ ዘመናት ፀረ ክርስቶስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በመንፈሳዊ ጨለማ እንዲዳክሩ አድርጓቸዋል። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የፀረ ክርስቶስን እውነተኛ ማንነት ለይተን ማወቅ እንዲሁም ከሚያስፋፋቸው ሃይማኖታዊ ውሸቶችና ማታለያዎች ነፃ መውጣት ችለናል።—ዮሐንስ 17:17