የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 55—2 ጢሞቴዎስ
ጸሐፊው:- ጳውሎስ
የተጻፈበት ቦታ:- ሮም
ተጽፎ ያለቀው:- በ65 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
ጳውሎስ በሮም በድጋሚ ታስሯል። ይሁን እንጂ ለሁለተኛ ጊዜ በታሰረበት ወቅት የነበረበት ሁኔታ ከመጀመሪያው እጅግ የከፋ ነበር። ወቅቱ 65 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ነበር። በሐምሌ ወር 64 ከክርስቶስ ልደት በኋላ፣ በሮም ከተማ ይገኙ ከነበሩት 14 ቀበሌዎች ውስጥ በአሥሩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ ከባድ የእሳት ቃጠሎ ተከስቶ ነበር። እንደ ሮማዊው ታሪክ ጸሐፊ ታሲተስ አባባል ከሆነ ንጉሠ ነገሥት ኔሮ “ቃጠሎው የተነሳው ትእዛዝ በመሰጠቱ ምክንያት እንደሆነ የሚገልጸውን አደገኛ ወሬ ማፈን አልቻለም። በመሆኑም ኔሮ ይህን ወሬ ለማስቀረት ሲል፣ ተጠያቂዎቹ ሕዝቡ ክርስቲያኖች እያለ የሚጠራቸው . . . ወገኖች እንደሆኑ በመናገር ጥፋቱን በእነርሱ ላይ ካላከከ በኋላ እጅግ አሰቃቂ የሆነ ሥቃይ እንዲደርስባቸው አድርጓል። . . . በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተወነጀሉ ሲሆን የተከሰሱትም ከተማዋን በማቃጠላቸው ሳይሆን ለሰው ዘር ጥላቻ አላችሁ በሚል ነበር። መሳቂያና መሳለቂያ ሆነው ተገድለዋል። የአራዊት ቆዳ ካለበሷቸው በኋላ በውሻዎች ተቦጫጭቀው እንዲሞቱ ይደረጉ ወይም በመስቀል ላይ እንዲቸነከሩ አሊያም ደግሞ ሲመሽ መብራት ሆነው እንዲያገለግሉ በእሳት ይቃጠሉ ነበር። ኔሮ የአትክልት ስፍራዎቹን ለዚህ ትርዒት ማሳያ እንዲሆኑ ፈቅዶ ነበር። . . . እነዚህ ሰዎች ይገደሉ የነበረው ለሕዝቡ ጥቅም በማሰብ እንደሆነ ለማስመሰል ቢሞከርም ዓላማው የአንድን ሰው ጭካኔ ለማርካት ስለነበር ድርጊቱ ብዙዎችን አሳዝኗል።”a
2 ጳውሎስ በሮም በድጋሚ የታሰረው ኃይለኛ የስደት ማዕበል በተነሳበት በዚህ ወቅት ሳይሆን አይቀርም። በዚህ ጊዜ በሰንሰለት ታስሮ ነበር። ከእስር እፈታለሁ የሚል ተስፋም አልነበረውም፤ ከዚህ ይልቅ የመጨረሻ ፍርዱንና የሚገደልበትን ዕለት እየተጠባበቀ ነበር። ሊጠይቁት የሚመጡት ሰዎችም ጥቂት ነበሩ። ደግሞም ማንኛውም ሰው ክርስቲያን መሆኑን በግልጽ ማሳወቁ እንዲያዝና ተሠቃይቶ እንዲሞት ሊያደርገው ስለሚችል በራስ ላይ አደጋ መጋበዝ ነበር። ጳውሎስ ከኤፌሶን ሊጠይቀው የመጣውን ሰው በማመስገን እንደሚከተለው ሲል የጻፈውም ለዚህ ነው:- “ጌታ ለሄኔሲፎሩ ቤተ ሰዎች ምሕረትን ይስጥ፤ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ቸርነት አድርጎልኛል፤ በታሰርሁበትም ሰንሰለት አላፈረም። እንዲያውም ወደ ሮም በመጣ ጊዜ ፈልጎ ፈልጎ አገኘኝ።” (2 ጢሞ. 1:16, 17) የሞት ጥላ ያንዣብብበት የነበረው ጳውሎስ ስለ ራሱ ሲናገር “በክርስቶስ ኢየሱስ ቃል በተገባው የሕይወት ተስፋ መሠረት፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ” መሆኑን ገልጿል። (1:1) ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር በአንድነት የመኖር ተስፋ እንደተዘረጋለት ያውቅ ነበር። በዚያን ጊዜ በነበሩት ዋና ዋና ከተሞች ይኸውም ከኢየሩሳሌም አንስቶ እስከ ሮምና ምናልባትም እስከ ስፔን ድረስ ርቆ በመሄድ ሰብኳል። (ሮሜ 15:24, 28) ሩጫውን በታማኝነት ፈጽሟል።—2 ጢሞ. 4:6-8
3 ይህ ደብዳቤ የተጻፈው ጳውሎስ በሰማዕትነት ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ በ65 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን በኤፌሶን እንዲቆይ አበረታቶት ስለነበረ ደብዳቤው በተጻፈበት ጊዜም ጢሞቴዎስ እዚያው ሳይሆን አይቀርም። (1 ጢሞ. 1:3) በዚህኛው ደብዳቤ ላይ ጳውሎስ ወደ እሱ በቶሎ እንዲመጣ ጢሞቴዎስን ሁለት ጊዜ ያሳሰበው ሲሆን ማርቆስንም ይዞት እንዲመጣ እንዲሁም ጳውሎስ በጢሮአዳ የተወውን በርኖስና ጥቅልል መጻሕፍቱን እንዲያመጣለት ጠይቆታል። (2 ጢሞ. 4:9, 11, 13, 21) አሳሳቢ በሆነ ወቅት የተጻፈው ይህ ደብዳቤ ለጢሞቴዎስ የሚሆን ጠንካራ ማበረታቻ የያዘ ሲሆን ከዚያ በኋላ ባሉት ዘመናት ሁሉ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ማበረታቻ መስጠቱን ቀጥሏል።
4 የአንደኛ ጢሞቴዎስ መጽሐፍ ትክክለኛና የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል መሆኑን ለማሳየት የቀረቡት ማስረጃዎች ለሁለተኛ ጢሞቴዎስም ይሠራሉ። ደብዳቤው በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ይኖር የነበረውን ፖሊካርፕን ጨምሮ በቀደምት ጸሐፊዎች ዘንድ ተቀባይነት ከማግኘቱም በላይ ይገለገሉበት ነበር።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
10 “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ . . . [እንዲሁም] ይጠቅማሉ።” ጠቃሚ የሆኑት በምን መንገድ ነው? ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ እንዲህ በማለት መልሱን ይነግረናል:- “ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።” (3:16, 17) ‘ማስተማር’ ያለው ጠቀሜታ በዚህ መንገድ በደብዳቤው ላይ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ጽድቅ ወዳዶች በሙሉ የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ለመሆን በሚያደርጉት ጥረት እንዲሁም “የእውነትን ቃል በትክክል እንደሚያስረዳ” በአምላክ ዘንድ የተመሠከረለት ሠራተኛ ለመሆን የተቻላቸውን ሁሉ በሚያደርጉበት ጊዜ ደብዳቤው የያዘውን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ይፈልጋሉ። ጢሞቴዎስ በኖረበት ዘመን በኤፌሶን እንደነበሩት ሰዎች ሁሉ በአሁኑ ጊዜም ‘በማይረባና ትርጉም የለሽ በሆነ ክርክር’ የሚካፈሉ፣ ‘ሁልጊዜ ቢማሩም እውነትን ወደ ማወቅ ፈጽሞ ሊደርሱ ያልቻሉ’ እንዲሁም በራስ ወዳድነት በመነሳሳት እነሱ እንደሚፈልጉት ጆሮአቸውን የሚያሳክክ ትምህርት በሚያስተምሯቸው አስተማሪዎች በመደገፍ “ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት” የሚቃወሙ ሰዎች አሉ። (2:15, 23፤ 3:7፤ 4:3, 4) በካይ የሆነውን ይህን ዓለማዊ ተጽዕኖ ለማስወገድ በእምነትና በፍቅር ‘የጤናማ ትምህርትን ምሳሌ መያዝ’ አስፈላጊ ነው። ከዚህም በላይ “የእግዚአብሔር ሰው” እንደሆነው እንደ ጢሞቴዎስ ያሉ በጉባኤ ውስጥም ሆነ ከጉባኤ ውጪ ያሉትን ‘ለማስተማር ብቃት ያላቸው’ ሰዎች ከምንጊዜውም በላይ በአስቸኳይ ይፈለጋሉ። ይህን ኃላፊነት በመሸከም ‘በገርነት ለማስተማር ብቃት ያላቸው’ እንዲሁም ‘በታላቅ ትዕግሥትና በማስተማር’ ጥበብ ቃሉን የሚሰብኩ ደስተኞች ናቸው!—1:13፤ 2:2, 24, 25፤ 4:2
11 ጳውሎስ እንደገለጸው ጢሞቴዎስ፣ ከሎይድና ከኤውንቄ ፍቅራዊ ማሠልጠኛ በማግኘቱ ‘ከሕፃንነቱ ጀምሮ’ ቅዱሳን መጻሕፍትን ማወቅ ችሏል። ‘ከሕፃንነት ጀምሮ’ የሚለው ሐረግ በዛሬው ጊዜ ለልጆች ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት መሰጠት መጀመር ያለበት መቼ እንደሆነ ይጠቁማል። ይሁን እንጂ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በልጅነት የተቀጣጠለው ቅንዓት እየቀዘቀዘ መሄድ ቢጀምርስ? ጳውሎስ፣ ግብዝነት የሌለበት እምነት በመያዝ ‘በኀይልና በፍቅር እንዲሁም ራስን በመግዛት መንፈስ’ ይህንን ቅንዓት እንደገና ማቀጣጠል እንደሚያስፈልግ ምክር ሰጥቷል። “በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ” እንዲሁም ወንጀልና የሐሰት ትምህርት እንደሚኖር ጳውሎስ ተናግሯል። ሁላችንም በተለይ ደግሞ ወጣቶች ‘ነገርን ሁሉ በልክ ማድረግና አገልግሎታችንን መፈጸም’ የሚገባን በዚህ የተነሳ ነው።—3:15፤ 1:5-7፤ 3:1-5፤ 4:5 የ1954 ትርጉም
12 የምናገኘው ሽልማት ጥረት ቢደረግለት የማያስቆጭ ነው። (2:3-7) ከዚህ ጋር በተያያዘ ጳውሎስ “ከሙታን የተነሣውን፣ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፤ የእኔም ወንጌል ይኸው ነው” በማለት በአምላክ መንግሥት ዘር ላይ እንድናተኩር አበረታቶናል። የጳውሎስ ተስፋ ከዚህ ዘር ጋር በአንድነት መኖር ነበር። ቆየት ብሎ ደግሞ የሚገደልበትን ጊዜ በተመለከተ የድል አድራጊነት መንፈስ በሚንጸባረቅበት መንገድ እንዲህ ብሏል:- “ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ በዚያ ቀን ለእኔ ይሰጠኛል፤ ደግሞም ለእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሱን መገለጥ ለናፈቁ ሁሉ ነው።” (2:8፤ 4:8) በታማኝነት በማገልገል ያሳለፏቸውን በርካታ ዓመታት ወደኋላ መለስ ብለው በመመልከት ጳውሎስ እንዳለው ለመናገር የሚችሉ ሁሉ ምንኛ ደስተኞች ናቸው! ይሁን እንጂ ይህ የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በመናፈቅ በአሁኑ ጊዜ በታማኝነት ማገልገልን ይጠይቃል፤ እንዲሁም ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ ሲጽፍ የነበረው ዓይነት የመተማመን ስሜት ማሳየት ያስፈልጋል:- “ጌታ ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል፤ ወደ ሰማያዊው መንግሥቱም በሰላም ያደርሰኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።”—4:18
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በሞሰስ ሃዳስ በ1942 የተዘጋጀው ዘ ኮምፕሊት ዎርክስ ኦቭ ታሲተስ ገጽ 380-381