በንግግራችሁና በጠባያችሁ ምሳሌ ሁኑ
1 ጢሞቴዎስ በንግግሩና በጠባዩ ምሳሌ እንዲሆን ሐዋርያው ጳውሎስ አጥብቆ መክሮታል። (1 ጢሞ. 4:12) እኛም በተለይ በአገልግሎት በምንሠማራበት ጊዜ በንግግራችንና በጠባያችን ምሳሌ መሆን ይኖርብናል፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን የምናገኛቸውን ሰዎች ልብ ለመንካት ወይም ላለመንካት ወሳኝ ሊሆን ይችላል።
2 አክብሮትን፣ አሳቢነትን፣ ደግነትን፣ ትህትናንና ዘዴኛነትን ጨምሮ ሌሎች መልካም ባሕርያትን ማሳየት ይኖርብናል። እነዚህን ባሕርያት በማንጸባረቅ የእኛ ድርጊት የሌሎችን ስሜት ሊነካ እንደሚችል መገንዘባችንን እናሳያለን። በአገልግሎት የምናሳያቸው መልካም ባሕርያት ከምግብ ማጣፈጫ ቅመሞች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ምግቡ ጥሩ ቢሆንም እንኳ እነዚህ ማጣፈጫዎች ካልተጨመሩበት አንዳችም ጣዕም ላይኖረውና የመብላት ፍላጎትን የማያነሳሳ ሊሆን ይችላል። ከሌሎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት መልካም ጠባይ ሳናሳይ መቅረታችን የሚኖረው ውጤት ከዚህ የተለየ አይደለም።— ቆላ. 4:6
3 በንግግራችሁ ምሳሌ ሁኑ፦ የወዳጅነት ስሜት የሚንጸባረቅበት ፈገግታና ሞቅ ያለ ሰላምታ ምሥራቹን ለማቅረብ የግድ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ናቸው። መግቢያችን ከልብ በመነጨ የጋለ ስሜት ከታጀበ የቤቱ ባለቤት ስለ እርሱ ከልብ እንደምናስብ እንዲገነዘብ እንረዳዋለን። ሲናገር በጥሞና አዳምጠው፤ እንዲሁም ለሚሰነዝረው አስተያየት ተገቢውን አክብሮት አሳይ። ንግግርህ ዘዴ የታከለበትና ለዛ ያለው ይሁን።— ከሥራ 6:8 ጋር አወዳድር።
4 አልፎ አልፎ ሰው የሚያመናጭቁና ጠበኛ ሰዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ጴጥሮስ ‘በየዋህነትና ጥልቅ አክብሮት’ እንድንናገር ጠበቅ አድርጎ አሳስቦናል። (1 ጴጥ. 3:15 አዓት፤ ሮሜ 12:17, 18) ኢየሱስ አንድ የቤት ባለቤት ኃይለ ቃል በመናገር የመንግሥቱን መልእክት ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልሆነ ከገለጸ ‘የእግራችንን ትቢያ አራግፈን’ እንድንሄድ ነግሮናል። (ማቴ. 10:14) እንደነዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ምሳሌ የሚሆን ጠባይ ማሳየታችን የኋላ ኋላ የተቃዋሚውን ልብ ሊያለሰልሰው ይችላል።
5 በጠባያችሁ ምሳሌ ሁኑ፦ ሰው በሚበዛባቸው ጎዳናዎች ላይና በሕዝብ ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ምሥራቹን በምንሰብክበት ጊዜ ባለመጮህ ወይም ካላደመጣችሁን ብለን ችክ ባለማለት እንዲሁም የመተላለፊያ መንገዶችን ባለመዝጋት የአሳቢነት ስሜት ማሳየታችን የተገባ ነው። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ቤት በምንሄድበትም ጊዜ ላሳዩን የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አድናቂዎች በመሆን አጋጊያጣችን ተገቢ መሆን አለበት፤ ሥርዓታማ እንግዶችም መሆን ይኖርብናል። ከእኛ ጋር ወደ አገልግሎት የሚወጡ ልጆች ለቤቱ ባለቤትና ለንብረቶቹ አክብሮት የሚያሳዩ እንዲሁም ሥርዓታማና ውይይቱን በጥሞና የሚከታተሉ መሆን ይኖርባቸዋል። የልጆቹ ሥርዓታማ አለመሆን መጥፎ አመለካከት ሊያሳድር ይችላል።— ምሳሌ 29:15
6 የሰውነት አያያዛችን የአምላክ ቃል አገልጋዮች መሆናችንን በግልጽ የሚያሳውቅ መሆን ይኖርበታል። አለባበሳችንና የጠጉር አያያዛችን ዝርክርክና ሥርዓታማ ያልሆነ ወይም ደግሞ በጣም ትኩረት የሚስብና ጌጣጌጥ የበዛበት መሆን የለበትም። የሰውነት አያያዛችን ሁልጊዜ ‘ለምሥራቹ የሚገባ’ ዓይነት መሆን ይኖርበታል። (ከፊልጵስዩስ 1:27 ጋር አወዳድር።) ለሰውነት አያያዛችንንና ለአገልግሎት ስለምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች በመጠንቀቅ ሌሎች እንዳይደናቀፉ ወይም በአገልግሎታችን ላይ አንዳች ነቀፋ እንዳይሰነዘር እናደርጋለን። (2 ቆሮ. 6:3, 4) በንግግራችንና በጠባያችን ምሳሌ መሆናችን የመንግሥቱን መልእክት ይበልጥ ማራኪ የሚያደርገው ከመሆኑም በላይ ለይሖዋ ክብር ያመጣል።— 1 ጴጥ. 2:12