የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ሐምሌ 2019
ከሐምሌ 1-7
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ቆላስይስ 1-4
“አሮጌውን ስብዕና ገፋችሁ ጣሉ እንዲሁም አዲሱን ስብዕና ልበሱ”
(ቆላስይስ 3:5-9) ስለዚህ በምድር ያሉትን የአካል ክፍሎቻችሁን ግደሉ፤ እነሱም የፆታ ብልግና፣ ርኩሰት፣ ልቅ የሆነ የፍትወት ስሜት፣ መጥፎ ፍላጎትና ጣዖት አምልኮ የሆነው ስግብግብነት ናቸው። 6 በእነዚህ ነገሮች ምክንያት የአምላክ ቁጣ ይመጣል። 7 እናንተም በቀድሞ ሕይወታችሁ በዚህ መንገድ ትኖሩ ነበር። 8 አሁን ግን ቁጣን፣ ንዴትን፣ ክፋትንና ስድብን ሁሉ ከእናንተ አስወግዱ፤ ጸያፍ ንግግርም ከአፋችሁ አይውጣ። 9 አንዳችሁ ሌላውን አትዋሹ። አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፋችሁ ጣሉ፤
የዓለምን መንፈስ ሳይሆን የአምላክን መንፈስ ተቀበሉ
12 ባሕርዬና ምግባሬ የትኛውን መንፈስ ያንጸባርቃል? (ቆላስይስ 3:8-10, 13ን አንብብ።) የዓለም መንፈስ የሥጋ ሥራዎችን ያስፋፋል። (ገላ. 5:19-21) የምንመራው በየትኛው መንፈስ እንደሆነ በትክክል የሚታወቀው ነገሮች ሰላም በሆኑበት ጊዜ ሳይሆን ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ ነው፤ ለምሳሌ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ችላ ቢሉን፣ ቅር ቢያሰኙን አልፎ ተርፎም ቢበድሉን እውነተኛ ማንነታችን ይታያል። በተጨማሪም ቤት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ በየትኛው መንፈስ እንደምንመራ ግልጽ ይሆናል። በዚህ ረገድ ራሳችንን መመርመራችን ተገቢ ነው። ‘ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የክርስቶስን ዓይነት ስብዕና ይበልጥ እያንጸባረቅኩ ነበር ወይስ ቀድሞ የነበረኝ መጥፎ አነጋገርና ምግባር አገርሽቶብኛል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።
13 የአምላክ መንፈስ ‘አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፈን እንድንጥል’ እንዲሁም “አዲሱን ስብዕና” እንድንለብስ ይረዳናል። ይህም ይበልጥ አፍቃሪና ደጎች እንድንሆን ያደርገናል። ቅር እንድንሰኝ የሚያደርገን ምክንያት እንዳለን ቢሰማንም እርስ በርስ በነፃ ይቅር ለመባባል እንነሳሳለን። ተገቢ ያልሆነ ነገር እንደተፈጸመብን ሲሰማን “የመረረ ጥላቻ” በሚንጸባረቅበት እንዲሁም “ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ” በተቀላቀለበት መንገድ ምላሽ አንሰጥም። ከዚህ ይልቅ ‘ከአንጀት የምንራራ’ ለመሆን ጥረት እናደርጋለን።—ኤፌ. 4:31, 32
(ቆላስይስ 3:10-14) እንዲሁም ከፈጣሪው አምሳል ጋር በሚስማማ ሁኔታ በትክክለኛ እውቀት አማካኝነት እየታደሰ የሚሄደውን አዲሱን ስብዕና ልበሱ፤ 11 በዚህ ሁኔታ ግሪካዊ ወይም አይሁዳዊ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ የባዕድ አገር ሰው፣ እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ነፃ ሰው ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነገር ነው፤ እንዲሁም በሁሉም ነው። 12 እንግዲህ የአምላክ ምርጦች፣ ቅዱሳንና የተወደዳችሁ እንደመሆናችሁ መጠን ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ። 13 አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ። 14 ይሁንና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ላይ ፍቅርን ልበሱ፤ ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነውና።
ተለውጣችኋል?
18 የአምላክ ቃል አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ እንዲረዳን መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብና ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማግኘት ይኖርብናል፤ ነገር ግን ይህ የመጀመሪያ እርምጃ ብቻ ነው። ብዙ ሰዎች አልፎ አልፎ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ስለሚያነቡ ምን እንደሚል በደንብ ያውቃሉ። ምናልባትም በአገልግሎት ላይ እንዲህ ያሉ ሰዎች አጋጥመውህ ይሆናል። እንዲያውም አንዳንዶች ጥቅሶችን በቃላቸው መናገር ይችላሉ። ሆኖም ይህ እውቀት በአስተሳሰባቸው ወይም በአኗኗራቸው ላይ ያን ያህል ለውጥ ላያመጣ ይችላል። ለመሆኑ የጎደላቸው ነገር ምንድን ነው? አንድ ሰው የአምላክ ቃል በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድርበትና እንዲለውጠው ከፈለገ ቃሉ ልቡ ውስጥ ዘልቆ እንዲገባ ሊፈቅድለት ይገባል። በመሆኑም ጊዜ ወስደን በተማርነው ነገር ላይ ማሰላሰል ያስፈልገናል። ራሳችንን እንዲህ በማለት መጠየቃችን ጥሩ ነው፦ ‘ይህ እውቀት ሃይማኖታዊ ትምህርት ከመሆን ባለፈ ለእኔ ጥቅም እንደሚያስገኝ ተገንዝቤያለሁ? እውነት መሆኑን በራሴ ሕይወት መመልከት ችያለሁ? በተጨማሪም የተማርኩትን ነገር ለሌሎች ለማስተማር ብቻ ሳይሆን በራሴ ሕይወት ጭምር እጠቀምበታለሁ? ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እያናገረኝ እንዳለ ይሰማኛል?’ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ማሰላሰላችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል። ለእሱ ያለን ፍቅርም እያደገ ይሄዳል። ልባችን ሲነካ ደግሞ አስደሳች ለውጦችን ማድረግ እንችላለን።—ምሳሌ 4:23፤ ሉቃስ 6:45
19 የአምላክን ቃል በየዕለቱ ማንበባችንና በዚያ ላይ ማሰላሰላችን ቀደም ሲል በተወሰነ መጠን የወሰድናቸውን እርምጃዎች በቀጣይነት ማድረጋችንን እንድቀጥል ያነሳሳናል፤ ይኸውም ‘አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፈን እንድንጥል እንዲሁም በትክክለኛ እውቀት አማካኝነት እየታደሰ የሚሄደውን አዲሱን ስብዕና እንድንለብስ’ ይረዳናል። (ቆላ. 3:9, 10) አዎ፣ የአምላክን ቃል በትክክል ስንረዳና የተረዳነውን ነገር በተግባር ላይ ለማዋል ስንጥር አዲሱን ስብዕና በመልበስ ረገድ ይሳካልናል። አዲሱን ክርስቲያናዊ ስብዕና መልበሳችን ደግሞ በሰይጣን መሠሪ ወጥመዶች ውስጥ እንዳንወድቅ ያደርገናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ቆላስይስ 1:13, 14) እሱ ከጨለማው ሥልጣን ታድጎን ወደሚወደው ልጁ መንግሥት አሻግሮናል፤ 14 ልጁም ቤዛውን በመክፈል ነፃ እንድንወጣ ይኸውም የኃጢአት ይቅርታ እንድናገኝ አድርጎናል።
it-2 169 አን. 3-5
የአምላክ መንግሥት
‘የሚወደው ልጁ መንግሥት።’ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ ከአሥር ቀናት በኋላ ማለትም በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስን በደቀ መዛሙርቱ ላይ አፈሰሰ፤ ይህም ኢየሱስ ‘ወደ አምላክ ቀኝ ከፍ ከፍ እንደተደረገ’ ለደቀ መዛሙርቱ አረጋግጦላቸዋል። (ሥራ 1:8, 9፤ 2:1-4, 29-33) በዚህ መንገድ ‘አዲሱ ቃል ኪዳን’ በእነሱ ላይ መሥራት ጀመረ፤ እነሱም አዲስ የሆነው “ቅዱስ ብሔር” ማለትም የመንፈሳዊ እስራኤል መሠረት ሆኑ።—ዕብ 12:22-24፤ 1ጴጥ 2:9, 10፤ ገላ 6:16
በአባቱ ቀኝ የተቀመጠው ክርስቶስ የዚህ ጉባኤ ራስ ሆነ። (ኤፌ 5:23፤ ዕብ 1:3፤ ፊልጵ 2:9-11) ቅዱሳን መጻሕፍት፣ በ33 ዓ.ም. ከዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት አንስቶ በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ የሚገዛ መንፈሳዊ መንግሥት እንደተቋቋመ ያመለክታሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ ለነበሩ የአንደኛው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያን ጊዜም መንግሥት እንደነበረው ሲገልጽ “[አምላክ] ከጨለማው ሥልጣን ታድጎን ወደሚወደው ልጁ መንግሥት አሻግሮናል” ብሏል።—ቆላ 1:13፤ ከሥራ 17:6, 7 ጋር አወዳድር።
በ33 ዓ.ም. ከዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት አንስቶ መግዛት የጀመረው የክርስቶስ መንግሥት በመንፈሳዊ እስራኤል ላይ የሚገዛ መንፈሳዊ መንግሥት ነው፤ መንፈሳዊ እስራኤል የሚለው አገላለጽ የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች እንዲሆኑ በአምላክ መንፈስ የተወለዱ ክርስቲያኖችን ያመለክታል። (ዮሐ 3:3, 5, 6) እነዚህ በመንፈስ የተወለዱ ክርስቲያኖች ሰማያዊ ሽልማታቸውን ሲያገኙ፣ የክርስቶስ መንፈሳዊ መንግሥት ምድራዊ ተገዢዎች መሆናቸው አብቅቶ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ነገሥታት ይሆናሉ።—ራእይ 5:9, 10
(ቆላስይስ 2:8) በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዓለም መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁም በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ፤
ለገላትያ፣ ለኤፌሶን፣ ለፊልጵስዩስና ለቈላስይስ ሰዎች የተጻፉት ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች
2:8—ጳውሎስ ክርስቲያኖች እንዲርቋቸው ያስጠነቀቃቸው ‘የዚህ ዓለም መሠረታዊ ሕግጋት’ ምንድን ናቸው? እነዚህ ሕግጋት የሰይጣንን ዓለም ያዋቀሩትና የሚመሩት ወይም የሚያንቀሳቅሱት መሠረታዊ ነገሮች ወይም ደንቦች ናቸው። (1 ዮሐ. 2:16) ከእነዚህም መካከል የዚህ ዓለም ፍልስፍና፣ ፍቅረ ንዋይ እንዲሁም የሐሰት ሃይማኖቶች ይገኙበታል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከሐምሌ 8-14
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ተሰሎንቄ 1-5
“እርስ በርስ ተበረታቱ እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ”
(1 ተሰሎንቄ 5:11-13) ስለዚህ አሁን እያደረጋችሁት እንዳለው እርስ በርስ ተበረታቱ እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ። 12 እንግዲህ ወንድሞች፣ በመካከላችሁ በትጋት እየሠሩና በጌታ ሥራ አመራር እየሰጧችሁ ያሉትን እንዲሁም ምክር እየለገሷችሁ ያሉትን እንድታከብሯቸው እንለምናችኋለን፤ 13 በተጨማሪም በሚያከናውኑት ሥራ የተነሳ በፍቅር ለየት ያለ አሳቢነት እንድታሳዩአቸው እንለምናችኋለን። እርስ በርሳችሁ ሰላማዊ ግንኙነት ይኑራችሁ።
‘በመካከላችሁ በትጋት እየሠሩ ያሉትን አክብሯቸው’
12 በጉባኤ ውስጥ ‘አመራር መስጠት’ ከማስተማር የበለጠ ነገርን ይጨምራል። በ1 ጢሞቴዎስ 3:4 ላይ “የሚያስተዳድር” ተብሎ የተተረጎመው ቃልም ‘አመራር መስጠት’ ከሚለው አገላለጽ ጋር ተመሳሳይ ትርጉም አለው። ጳውሎስ፣ የበላይ ተመልካች “ልጆቹን ታዛዥና የታረመ ጠባይ ያላቸው አድርጎ በማሳደግ የራሱን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳድር ሊሆን ይገባዋል” በማለት ተናግሯል። እዚህ ላይ የገባው “የሚያስተዳድር” የሚለው ቃል ልጆቹን ማስተማርን ብቻ ሳይሆን በቤተሰቡ ውስጥ አመራር መስጠትንና “ልጆቹን ታዛዥ” አድርጎ ማሳደግን እንደሚጨምር ግልጽ ነው። አዎን፣ ሽማግሌዎች ግንባር ቀደም ሆነው ጉባኤውን በመምራት ሁሉም የጉባኤው አባላት ለይሖዋ ታዛዥ እንዲሆኑ ይረዷቸዋል።—1 ጢሞ. 3:5
‘በመካከላችሁ በትጋት እየሠሩ ያሉትን አክብሯቸው’
19 ለአንተ ተብሎ የተዘጋጀ ስጦታ ቢሰጥህ ምን ታደርጋለህ? በዚህ ስጦታ በመጠቀም ለተደረገልህ ነገር አድናቆት እንዳለህ አታሳይም? ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶችን’ በመስጠት አንተን የሚጠቅም ዝግጅት አድርጓል። ለእነዚህ ስጦታዎች አድናቆት እንዳለህ ማሳየት ከምትችልባቸው መንገዶች አንዱ ሽማግሌዎች የሚሰጧቸውን ንግግሮች በጥሞና ማዳመጥና የጠቀሷቸውን ነጥቦች ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ማድረግ ነው። በተጨማሪም በስብሰባዎች ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ በማድረግ አድናቆትህን ማሳየት ትችላለህ። እንዲሁም ሽማግሌዎች ግንባር ቀደም ሆነው በሚያከናውኗቸው እንደ መስክ አገልግሎት ባሉ እንቅስቃሴዎች መካፈል ትችላለህ። አንድ ሽማግሌ ከሰጠህ ምክር ጥቅም አግኝተህ ከሆነ ይህንን ለሽማግሌው ለምን አትነግረውም? ለሽማግሌው ቤተሰቦችስ አድናቆትህን ለምን አትገልጽላቸውም? አንድ ሽማግሌ የጉባኤ ሥራዎችን በትጋት ማከናወን የቻለው ቤተሰቦቹ ከእሱ ጋር የሚያሳልፉትን ጊዜ መሥዋዕት ስላደረጉ እንደሆነ አስታውስ።
(1 ተሰሎንቄ 5:14) በሌላ በኩል ደግሞ ወንድሞች፣ ይህን እናሳስባችኋለን፦ በሥርዓት የማይሄዱትን አስጠንቅቋቸው፤ የተጨነቁትን አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ።
“በተግባርና በእውነት” እንዋደድ
13 ደካሞችን ደግፍ። “ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ” ለሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ የምንሰጠው ምላሽ ፍቅራችን እውነተኛ መሆን አለመሆኑን ያሳያል። (1 ተሰ. 5:14) በአንድ ወቅት ደካማ የነበሩ በርካታ ሰዎች ከጊዜ በኋላ በእምነት ጠንካሮች ይሆናሉ፤ አንዳንዶች ግን በትዕግሥት ቀጣይ የሆነ ድጋፍ ማግኘት ይፈልጋሉ። ይህም አበረታች የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማካፈልን፣ አብረውን አገልግሎት እንዲወጡ መጋበዝን ሌላው ቀርቶ ጊዜ ወስዶ ማዳመጥን ሊጨምር ይችላል። በተጨማሪም አንድን ወንድም ወይም አንዲትን እህት እንዲሁ በደፈናው “ጠንካራ” ወይም “ደካማ” ብሎ ከመፈረጅ ይልቅ ሁላችንም ጠንካራና ደካማ ጎን እንዳለን መገንዘብ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስም እንኳ ድክመት እንዳለበት አምኖ ተቀብሏል። (2 ቆሮ. 12:9, 10) በመሆኑም ሁላችንም የእምነት ባልንጀሮቻችን ድጋፍ ያስፈልገናል።
ኢየሱስን በትሕትናውና በርኅራኄው ምሰሉት
16 ርኅራኄ የሚንጸባረቅበት ንግግራችን፦ ለሌሎች ከርኅራኄ የመነጨ አሳቢነት ካለን ‘የተጨነቁትን ነፍሳት ለማጽናናት’ እንነሳሳለን። (1 ተሰ. 5:14) እንዲህ ያሉ ሰዎችን ለማበረታታት ምን ማለት እንችላለን? ከልባችን እንደምናስብላቸው በመግለጽ መንፈሳቸው እንዲታደስ እናደርጋለን። ከልብ እንደምናደንቃቸው በመናገር መልካም ባሕርያትና ችሎታዎች እንዳሏቸው እንዲያስተውሉ ማድረግ ይቻላል። ይሖዋ ወደ ልጁ የሳባቸው ውድ እንደሆኑ አድርጎ ስለሚመለከታቸው እንደሆነ ልናስታውሳቸው እንችላለን። (ዮሐ. 6:44) እንዲሁም ይሖዋ “ልባቸው ለተሰበረ” ወይም ‘መንፈሳቸው ለተሰበረ’ አገልጋዮቹ በጥልቅ እንደሚያስብ በእርግጠኝነት እንግለጽላቸው። (መዝ. 34:18) በርኅራኄ የምንናገረው ነገር ማጽናኛ ለሚፈልጉ ሰዎች ፈውስ ሊያስገኝላቸው ይችላል።—ምሳሌ 16:24
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(1 ተሰሎንቄ 4:3-6) የአምላክ ፈቃድ እንድትቀደሱና ከፆታ ብልግና እንድትርቁ ነው። 4 ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን አካል በመቆጣጠር እንዴት በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት ሊያውቅ ይገባል። 5 ይህም አምላክን እንደማያውቁት አሕዛብ ስግብግብነት በሚንጸባረቅበት ልቅ የፍትወት ስሜት አይሁን። 6 ማንም ሰው በዚህ ጉዳይ ከገደቡ ማለፍና ወንድሙን መጠቀሚያ ማድረግ አይኖርበትም፤ ምክንያቱም አስቀድመን እንደነገርናችሁና በጥብቅ እንዳስጠነቀቅናችሁ ይሖዋ በእነዚህ ነገሮች ሁሉ የተነሳ የቅጣት እርምጃ ይወስዳል።
እስከተዋደዱ ድረስ ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት መፈጸም ምን ስህተት አለው?
ለአንድ ክርስቲያን ደግሞ ዝሙት መፈጸም የመንፈሳዊ ወንድሙን ወይም እህቱን መብት መጋፋት ወይም መተላለፍ ጭምር ይሆንበታል። (1 ተሰሎንቄ 4:3-6) ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ አገልጋይ ነን የሚሉ ሰዎች ካላገቡት ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት ቢፈጽሙ የክርስቲያን ጉባኤን ያረክሳሉ። (ዕብራውያን 12:15, 16) እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ዝሙት የፈጸመው ሰው ንጹሕ የሥነ ምግባር አቋም እንዳይኖረውና ያላገባ ከሆነ ደግሞ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናውን ጠብቆ ትዳር መመሥረት እንዳይችል ያደርጉታል። ከዚህም በላይ የራሳቸውን ቤተሰብ መልካም ስም ያጎድፋሉ፤ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ዝሙት የፈጸመውን ሰው ቤተሰብ ይበድላሉ። በመጨረሻም የጽድቅ ሕግጋቱንና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በመጣስ አምላክን ስላሳዘኑት ለእርሱ አክብሮት እንደሌላቸው ያሳያሉ። (መዝሙር 78:40, 41) ይሖዋ፣ ንስሐ የማይገቡ ግለሰቦችን ለፈጸሟቸው እንዲህ ለመሰሉ መጥፎ ድርጊቶች ‘ይበቀላቸዋል።’ (1 ተሰሎንቄ 4:6) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከዝሙት እንድንሸሽ’ ቢነግረን ምን ያስገርማል?—1 ቆሮንቶስ 6:18
(1 ተሰሎንቄ 4:15-17) የይሖዋን ቃል መሠረት አድርገን የምንነግራችሁ ይህ ነውና፤ ጌታ እስከሚገኝበት ጊዜ ድረስ በሕይወት የምንኖር በሞት አንቀላፍተው ያሉትን በምንም መንገድ አንቀድምም፤ 16 ምክንያቱም ጌታ ራሱ በትእዛዝ ድምፅ፣ በመላእክት አለቃ ድምፅና በአምላክ መለከት ድምፅ ከሰማይ ይወርዳል፤ ከክርስቶስ ጋር አንድነት ኖሯቸው የሞቱትም ቀድመው ይነሳሉ። 17 ከዚያም በሕይወት ቆይተን የምንተርፈው እኛ በአየር ላይ ከጌታ ጋር ለመገናኘት ከእነሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ በዚህም መንገድ ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።
‘መዳናችሁ እየቀረበ ነው’!
14 የማጎጉ ጎግ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር ከጀመረ በኋላ ምን ይከናወናል? የማቴዎስና የማርቆስ ዘገባዎች ተመሳሳይ ሐሳብ ይዘዋል፦ “[የሰው ልጅ] መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፣ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ ለእሱ የተመረጡትን ይሰበስባል።” (ማር. 13:27፤ ማቴ. 24:31) እዚህ ላይ የተገለጸው መሰብሰብ፣ ቅቡዓኑ መቀባት የጀመሩበትን ጊዜም ሆነ በምድር የቀሩት ታማኝ ቅቡዓን የመጨረሻው ማኅተም የሚደረግባቸውን ጊዜ አያመለክትም። (ማቴ. 13:37, 38) ይህ ማኅተም የሚደረግባቸው ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ነው። (ራእይ 7:1-4) ታዲያ ኢየሱስ የጠቀሰው የመሰብሰብ ሥራ ምንድን ነው? ከ144,000ዎቹ መካከል የቀሩት በሰማይ ሽልማታቸውን ስለሚያገኙበት ጊዜ መናገሩ ነበር። (1 ተሰ. 4:15-17፤ ራእይ 14:1) ይህ ክንውን የሚፈጸመው የማጎጉ ጎግ ጥቃት መሰንዘር ከጀመረ በኋላ ነው። (ሕዝ. 38:11) ከዚያም ኢየሱስ “በዚያ ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ደምቀው ያበራሉ” በማለት የተናገረው ሐሳብ ይፈጸማል።—ማቴ. 13:43
15 ይህ ሲባል ታዲያ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ይነጠቃሉ” ማለት ነው? ብዙ የሕዝበ ክርስትና አባላት “መነጠቅ” የሚለው ትምህርት ክርስቲያኖች ሥጋዊ አካላቸውን እንደለበሱ ከምድር መወሰዳቸውን እንደሚያመለክት ያምናሉ። ከዚያም ኢየሱስ በሚታይ መንገድ በመመለስ ምድርን እንደሚገዛ ይጠብቃሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ” እንደሚታይ እንዲሁም ኢየሱስ “በሰማይ ደመና” እንደሚመጣ በግልጽ ይናገራል። (ማቴ. 24:30) ሁለቱም አገላለጾች የሚያመለክቱት በዓይን የማይታይ ሁኔታን ነው። በተጨማሪም “ሥጋና ደም የአምላክን መንግሥት አይወርስም።” በመሆኑም ወደ ሰማይ የሚወሰዱ ሰዎች “የመጨረሻው መለከት በሚነፋበት ወቅት ድንገት፣ በቅጽበተ ዓይን [መለወጥ]” ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:50-53ን አንብብ።) በምድር የቀሩት ታማኝ ቅቡዓን በቅጽበት ወደ ሰማይ ይሰበሰባሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከሐምሌ 15-21
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ተሰሎንቄ 1-3
“የዓመፀኛው መገለጥ”
(2 ተሰሎንቄ 2:6-8) በገዛ ራሱ ጊዜ ይገለጥ ዘንድ አሁን የሚያግደው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ። 7 እርግጥ ሚስጥራዊ የሆነው ይህ ዓመፅ አሁንም እየሠራ ነው፤ ሆኖም ሚስጥር ሆኖ የሚቆየው አሁን አግዶት ያለው ነገር ከመንገድ እስኪወገድ ድረስ ብቻ ነው። 8 ከዚያ በኋላ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያስወግደውና የእሱ መገኘት ይፋ በሚሆንበት ጊዜ እንዳልነበረ የሚያደርገው ዓመፀኛ ይገለጣል።
it-1 972-973
ለአምላክ ማደር
ጳውሎስ “ሚስጥራዊ የሆነው ይህ ዓመፅ” በማለት የጠራው ምንድን ነው? ይህ ከይሖዋ “ቅዱስ ሚስጥር” ጋር ሙሉ በሙሉ የሚቃረን ሌላ ሚስጥር ነው። ይህ ‘ሚስጥራዊ የሆነ ዓመፅ’ ነው። ይህ “የዓመፅ ሰው” በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን ሙሉ በሙሉ ስላልተቋቋመና ማንነቱ ግልጽ ስላልነበር ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ሚስጥር ነበር። ይህ “ሰው” በይፋ ከተቋቋመ በኋላም ቢሆን ለአብዛኛው የሰው ዘር ማንነቱ ሚስጥር ሆኖ ቀጥሏል፤ ምክንያቱም ክፋቱን የሚፈጸመው ማንነቱን ደብቆና ለአምላክ ያደረ በመምሰል ነው። እንዲያውም በትክክል ለአምላክ ካደሩ ሰዎች መካከል የሚነሳ ከሃዲ ነው። ጳውሎስ “ሚስጥራዊ የሆነው ይህ ዓመፅ” በእሱ ዘመንም እንደነበር ተናግሯል፤ ምክንያቱም ውሎ አድሮ የዚህ ከሃዲ ቡድን አባላት የሚሆኑት ዓመፀኞች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ተጽዕኖ እያሳደሩ ነበር። በመጨረሻም ይህ የዓመፅ ሰው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መገኘት ይፋ በሚሆንበት ጊዜ ይወገዳል። ይህ ከሃዲ ማለትም ሰይጣን የሚጠቀምበት ይህ “ሰው” “አምላክ ተብሎ ከሚጠራ ወይም ከሚመለክ ነገር (በግሪክኛ ሴባዝማ) ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ” ያደርጋል። በመሆኑም የሰይጣን መሣሪያ የሆነው ይህ ዋነኛ የአምላክ ተቃዋሚ ከፍተኛ የሆነ ማታለል ኃይል አለው፤ እንዲሁም የእሱ ዓይነት ድርጊት በሚፈጽሙ ሰዎች ሁሉ ላይ ጥፋት ይመጣባቸዋል። “የዓመፅ ሰው” ይህን ያህል የሚሳካለት፣ ክፋቱን የሚፈጽመው ለአምላክ ያደረ መስሎ ስለሆነ ነው።—2ተሰ 2:3-12፤ ከማቴ 7:15, 21-23 ጋር አወዳድር።
(2 ተሰሎንቄ 2:9-12) ሆኖም የዓመፀኛው መገኘት የሰይጣን ሥራ ሲሆን ይህም የሚፈጸመው በተአምራት፣ በሐሰተኛ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ሁሉ 10 እንዲሁም ለማታለል ማንኛውንም ዓይነት የክፋት ዘዴ በመጠቀም ነው። ወደ ጥፋት እያመሩ ያሉት ሰዎች ይድኑ ዘንድ የእውነት ፍቅር በውስጣቸው ስለሌለ ይህ ሁሉ እንደ ቅጣት ይደርስባቸዋል። 11 በዚህም ምክንያት አምላክ ሐሰት የሆነውን ያምኑ ዘንድ አታላይ በሆነ ተጽዕኖ ተሸንፈው እንዲስቱ ይፈቅዳል፤ 12 ይህን የሚያደርገው እውነትን ከማመን ይልቅ በዓመፅ ስለሚደሰቱ ሁሉም እንዲፈረድባቸው ነው።
it-2 245 አን. 7
ውሸት
ይሖዋ አምላክ፣ ሐሰት የሆነውን ነገር የሚወዱ ሰዎች “አታላይ በሆነ ተጽዕኖ” እንዲሸነፉና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሚናገረው ምሥራች ይልቅ ‘ሐሰት የሆነውን እንዲያምኑ’ ይፈቅዳል። (2ተሰ 2:9-12) ከበርካታ ዘመናት በፊት የኖረው እስራኤላዊው ንጉሥ አክዓብ የደረሰበት ነገር ለዚህ ምሳሌ ይሆናል። ሐሰተኛ ነቢያት፣ በራሞትጊልያድ ላይ ቢዘምት ድል እንደሚቀዳጅ ለአክዓብ ነገሩት፤ የይሖዋ ነቢይ የሆነው ሚካያህ ግን ጥፋት እንደሚመጣበት ነገረው። ይሖዋ፣ አንድ መንፈሳዊ ፍጡር በአክዓብ ነቢያት አፍ ላይ “አሳሳች መንፈስ” እንዲሆን እንደፈቀደ ሚካያህ በራእይ ተመልክቶ ነበር። ይህ ሲባል ይህ መንፈሳዊ ፍጡር፣ ነቢያቱ እውነት ከመናገር ይልቅ እነሱ ራሳቸው የፈለጉትንና አክዓብ መስማት የፈለገውን ነገር እንዲናገሩ አድርጓል ማለት ነው። አክዓብ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም የእነሱን ውሸት ለማመን መረጠ፤ ይህም ሕይወቱን አስከፍሎታል።—1ነገ 22:1-38፤ 2ዜና 18
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(2 ተሰሎንቄ 1:7, 8) መከራን የምትቀበሉት እናንተ ግን ጌታ ኢየሱስ ከኃያላን መላእክቱ ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ ከእኛ ጋር እረፍት ይሰጣችኋል፤ 8 የሚገለጠውም በሚንበለበል እሳት ነው፤ በዚያን ጊዜ አምላክን በማያውቁትና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ለሚገልጸው ምሥራች በማይታዘዙት ላይ የበቀል እርምጃ ይወስዳል።
it-1 834 አን. 5
እሳት
ጴጥሮስ “አሁን ያሉት ሰማያትም ሆኑ ምድር ለእሳት . . . ተጠብቀው ይቆያሉ” ሲል ጽፏል። በዚህ ጥቅስ ዙሪያ ያለው ሐሳብና ሌሎች ጥቅሶች እንደሚጠቁሙት ጴጥሮስ ይህን የተናገረው ቃል በቃል በእሳት መጥፋትን ለመግለጽ ሳይሆን ዘላለማዊ ጥፋትን ለማመልከት ነው። በኖኅ ዘመን የደረሰው የጥፋት ውኃ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎችን ብቻ እንጂ ቃል በቃል ሰማይንና ምድርን አላጠፋም፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከኃያላን መላእክቱ ጋር በሚንበለበል እሳት በሚገለጥበት ጊዜም ለዘላለም የሚጠፉት ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎችና እነሱ ያሉበት ክፉ ሥርዓት ናቸው።—2ጴጥ 3:5-7, 10-13፤ 2ተሰ 1:6-10፤ ከኢሳ 66:15, 16, 22, 24 ጋር አወዳድር።
(2 ተሰሎንቄ 2:2) በመንፈስ በተነገረ ቃል ወይም በቃል መልእክት ወይም ደግሞ ከእኛ የተላከ በሚመስል ደብዳቤ አማካኝነት የይሖዋ ቀን ደርሷል ብላችሁ በማሰብ የማመዛዘን ችሎታችሁ በቀላሉ አይናወጥ፤ ደግሞም አትደናገጡ።
it-1 1206 አን. 4
በመንፈስ መመራት
‘በመንፈስ የተነገሩ ቃላት’—እውነተኛ እና ሐሰተኛ። ኒውማ (መንፈስ) የሚለው የግሪክኛ ቃል ሐዋርያት በጻፏቸው አንዳንድ ደብዳቤዎች ላይ ለየት ባለ መንገድ ተሠርቶበታል። ለምሳሌ ያህል፣ በ2 ተሰሎንቄ 2:2 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ “በመንፈስ በተነገረ ቃል [ቃል በቃል “መንፈስ”] ወይም በቃል መልእክት ወይም ደግሞ ከእኛ የተላከ በሚመስል ደብዳቤ አማካኝነት የይሖዋ ቀን ደርሷል ብላችሁ በማሰብ የማመዛዘን ችሎታችሁ በቀላሉ አይናወጥ፤ ደግሞም አትደናገጡ” በማለት በተሰሎንቄ ያሉትን ወንድሞቹን አሳስቧቸዋል። ጳውሎስ ኒውማ (መንፈስ) የሚለውን ቃል የተጠቀመበት፣ ሐሳብ ለማስተላለፍ ከሚያስችል መንገድ (ለምሳሌ፣ ‘የቃል መልእክት’ ወይም ‘ደብዳቤ’) ጋር በተያያዘ እንደሆነ በግልጽ መረዳት ይቻላል። በዚህም ምክንያት በላንገ የተዘጋጀው ኮሜንተሪ ኦን ዘ ሆሊ ስክሪፕቸርስ (ገጽ 126) ይህን ጥቅስ በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “ሐዋርያው ይህን ሲል በመንፈስ መሪነት የተነገረ የሚመስል መልእክትን፣ ሐሰት የሆነ ትንቢትን፣ አንድ ነቢይ የተናገረውን ነገር ማመልከቱ ነበር።” (ተርጓሚና አርታኢ፦ ፊሊፕ ሻፍ፣ 1976) በቪንሰንት የተዘጋጀው ወርድ ስተዲስ ኢን ዘ ኒው ቴስታመንት እንዲህ ይላል፦ “በመንፈስ። መለኮታዊ ራእይ እንዳዩ የሚገልጹ ሰዎች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በሚናገሯቸው ትንቢቶች።” (1957 ጥራዝ 4 ገጽ 63) አንዳንድ ትርጉሞች፣ በዚህም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ላይ ኒውማ የሚለውን ቃል “መንፈስ” ብለው የሚተረጉሙት ቢሆንም ሌሎች ትርጉሞች ግን “በመንፈስ መልእክት” (AT)፣ “በትንቢት” (JB)፣ “በመንፈስ መሪነት” (D’Ostervald; Segond [ፈረንሳይኛ])፣ “በመንፈስ የተነገረ ቃል” (NW) ብለው የተረጎሙት በዚህ ምክንያት ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከሐምሌ 22-28
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ጢሞቴዎስ 1-3
“ለመልካም ሥራ ተጣጣሩ”
(1 ጢሞቴዎስ 3:1) ይህ ቃል እምነት የሚጣልበት ነው፦ የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣር ሰው መልካም ሥራን ይመኛል።
መንፈሳዊ እድገት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማሃል?
3 አንደኛ ጢሞቴዎስ 3:1ን አንብብ። እዚህ ላይ ‘መጣጣር’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ፣ አንድን ነገር ምናልባትም በቀላሉ የማይደረስበትን ነገር ለመያዝ መንጠራራት የሚል መልእክት ያስተላልፋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ቃል የተጠቀመው መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ጥረት እንደሚጠይቅ ለማጉላት ነው። በጉባኤው ውስጥ ወደፊት ሊያከናውን ስለሚችለው ነገር እያሰበ ያለን አንድ ወንድም ወደ አእምሯችን እናምጣ። በአሁኑ ጊዜ የጉባኤ አገልጋይ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ክርስቲያናዊ ባሕርያት ማዳበር እንዳለበት ይገነዘባል። መጀመሪያ፣ የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ለማሟላት ይጥራል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ለማሟላት ግብ ያወጣል። ይህ ወንድም፣ የጉባኤ አገልጋይም ሆነ ሽማግሌ ለመሆን ጥረት በሚያደርግበት ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነት ለመሸከም የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ለማሟላት ተግቶ ይሠራል።
(1 ጢሞቴዎስ 3:13) በተገቢው ሁኔታ የሚያገለግሉ ወንዶች ለራሳቸው መልካም ስም የሚያተርፉ ከመሆናቸውም በላይ በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ስላላቸው እምነት አፋቸውን ሞልተው ለመናገር የሚያስችል ነፃነት ያገኛሉና።
km 9/78 4 አን. 7
“መልካም ስም የሚያተርፉ” ወንዶች
7 ከዚህ አንጻር ጳውሎስ ስለ እነዚህ ወንዶች ሲናገር “መልካም ስም የሚያተርፉ” ያለው ለምን እንደሆነ መረዳት አይከብድም። ይህ አገላለጽ፣ አንዳንዶች እንደሚሉት በቤተ ክርስቲያን የሥልጣን ተዋረድ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ ማግኘትን የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ “በተገቢው ሁኔታ የሚያገለግሉ” የጉባኤ አገልጋዮች የይሖዋንና የኢየሱስን በረከት እንዲሁም የጉባኤውን አክብሮትና ድጋፍ እንደሚያገኙ የሚያሳይ ነው። በመሆኑም “በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ስላላቸው እምነት አፋቸውን ሞልተው ለመናገር የሚያስችል ነፃነት” ይኖራቸዋል። ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ስለሚወጡ በሚያከናውኑት መልካም ሥራ አድናቆት ያተርፋሉ፤ ጠንካራ እምነት ያላቸው ከመሆኑም ሌላ በድፍረት ወይም ነቀፋን ሳይፈሩ ስለ እምነታቸው ይናገራሉ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(1 ጢሞቴዎስ 1:4) በተጨማሪም ለፈጠራ ወሬዎችና ለትውልድ ሐረግ ቆጠራ ትኩረት እንዳይሰጡ እዘዛቸው። እንዲህ ያሉ ነገሮች ለግምታዊ ሐሳቦች በር ከመክፈት ውጭ የሚያስገኙት ፋይዳ የለም፤ አምላክ እምነትን ለማጠናከር ከሚሰጠው ነገር ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም።
it-1 914-915
የትውልድ ሐረግ ቆጠራ
ስለ እነዚህ ጉዳዮች ማጥናትና መወያየት ትርጉም አልነበረውም፤ በተለይ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈበት ወቅት እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ እርባና ቢስ ነበር። በወቅቱ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩት አይሁዳውያንና አሕዛብ በአምላክ ዘንድ ምንም ልዩነት ስላልነበራቸው፣ አንድ ሰው የማን ዘር እንደሆነ ለማረጋገጥ የትውልድ ሐረግ መዝገቡን ማስቀመጡ አስፈላጊ አልነበረም። (ገላ 3:28) የትውልድ ሐረግ መዝገቦቹ ደግሞ ክርስቶስ ከዳዊት የዘር ሐረግ መምጣቱን በበቂ ሁኔታ አረጋግጠዋል። ከዚህም ሌላ ጳውሎስ ይህን ማሳሰቢያ ከጻፈ ብዙም ሳይቆይ የኢየሩሳሌም ከተማም ሆነች የአይሁዳውያን መዝገቦች ጠፍተዋል። አምላክ እነዚህ መዝገቦች ተጠብቀው እንዲቆዩ አላደረገም። ከዚህ አንጻር ጢሞቴዎስና ሌሎች የጉባኤው አባላት ከዘር ሐረግ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ምርምር በማድረግና በመወዛገብ ጊዜ እንዳያባክኑ ጳውሎስ ሰግቶ ነበር፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋቸው ለእምነታቸው ምንም የሚጨምረው ነገር አልነበረም። ከትውልድ ሐረግ ጋር በተያያዘ ክርስቲያኖችን በዋነኝነት የሚያሳስባቸው ክርስቶስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጠው የትውልድ ሐረግ ሲሆን ይህን በተመለከተ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ በቂ ማስረጃ ይዟል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ሌሎች የትውልድ ሐረግ ዝርዝሮችም መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ አንጻር ትክክለኛ ዘገባ እንደያዘ ያረጋግጣሉ፤ ይህም መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት መጽሐፍ እንደሆነ ምሥክር ይሆናል።
(1 ጢሞቴዎስ 1:17) እንግዲህ ለማይጠፋውና ለማይታየው፣ እሱ ብቻ አምላክ ለሆነው ለዘላለሙ ንጉሥ ክብርና ግርማ ለዘላለም ይሁን። አሜን።
“እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው”
15 ሌላው ለይሖዋ ብቻ የተሰጠ የማዕረግ ስም ‘የዘመናት ንጉሥ’ የሚለው ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:17፤ ራእይ 15:3 አ.መ.ት) ይህ ምን ማለት ነው? ሁኔታው ከእኛ የመረዳት አቅም በላይ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ ጥንትም ሆነ ወደፊት ዘላለማዊ አምላክ ነው። መዝሙር 90:2 “ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ” ይላል። በመሆኑም ይሖዋ መጀመሪያም መጨረሻም የለውም። በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ነገር ወደ ሕልውና ከመምጣቱ በፊት የነበረ በመሆኑ “በዘመናት የሸመገለ” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው! (ዳንኤል 7:9, 13, 22) ይሖዋ ሉዓላዊ ጌታ ሊሆን አይገባውም ብሎ ሊከራከር የሚችል ይኖራል?
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከሐምሌ 29–ነሐሴ 4
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ጢሞቴዎስ 4-6
“ለአምላክ ማደር ወይስ ሀብት ማሳደድ?”
(1 ጢሞቴዎስ 6:6-8) እንደ እውነቱ ከሆነ ለአምላክ ያደርን መሆናችንና ባለን ነገር ረክተን መኖራችን ትልቅ ጥቅም ያስገኛል። 7 ወደ ዓለም ያመጣነው ምንም ነገር የለምና፤ ምንም ነገር ይዘን መሄድም አንችልም። 8 ስለዚህ ምግብና ልብስ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።
ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር መማር
ለጳውሎስ ደስታና እርካታ አስተዋጽኦ ያበረከተው ዋነኛው ነገር ያለኝ ይበቃኛል የሚለው አስተሳሰብ ነው። ይሁን እንጂ ያለኝ ይበቃኛል ሲባል ምን ማለት ነው? በቀላል አማርኛ መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች ረክቶ መኖር ማለት ነው። ጳውሎስ ይህንን አስመልክቶ የአገልግሎት ጓደኛው ለነበረው ለጢሞቴዎስ እንዲህ ብሎታል:- “ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፣ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል።”—1 ጢሞቴዎስ 6:6-8
ጳውሎስ ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ባሕርይ ለአምላክ ያደሩ ከመሆን ጋር አያይዞ እንደገለጸው ልብ በል። እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ለአምላክ በማደር ማለትም ለአምላክ የምናቀርበውን አገልግሎት በአንደኛ ደረጃ በማስቀመጥ እንጂ ንብረት ወይም ሃብት በማካበት አለመሆኑን ተገንዝቧል። “ምግብና ልብስ” ማግኘቱ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ እንዲከታተል ከመርዳት ያለፈ ቦታ የላቸውም። በመሆኑም ጳውሎስ ያለኝ ይበቃኛል እንዲል ያስቻለው ምስጢር በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆን በይሖዋ መታመኑ ነበር።
(1 ጢሞቴዎስ 6:9) ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ ግን ፈተናና ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ፤ እንዲሁም ሰዎችን ጥፋትና ብልሽት ውስጥ በሚዘፍቁ ከንቱና ጎጂ በሆኑ ብዙ ምኞቶች ይያዛሉ።
ባለጸጋ ለመሆን ቆርጦ መነሳት ሊጎዳህ የሚችለው እንዴት ነው?
እርግጥ ነው፣ ብዙዎቹ ሰዎች ሀብትን በማሳደድ ምክንያት አይሞቱም። ሆኖም ባለጸጋ ለመሆን በሚያደርጉት ጥረት ተውጠው በሕይወት ውስጥ እውነተኛ እርካታ ሳያገኙ እንዲሁ ሲደክሙ ይኖራሉ። እንደዚሁም ከሥራቸው ወይም ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥማቸው ውጥረት፣ መሥራት እስኪያቅታቸው ድረስ እንዲጨነቁና እንቅልፍ እንዲያጡ እንዲሁም በከባድ ራስ ምታት ወይም የሆድ ዕቃ ቁስለት እንዲሠቃዩ ካደረጋቸው በሕይወታቸው ደስተኞች አይሆኑም፤ እነዚህ የጤና ችግሮች የአንድን ሰው ዕድሜ ሊያሳጥሩት ይችላሉ። ደግሞም አንድ ሰው ቅድሚያ በሚሰጣቸው ነገሮች ረገድ ለውጥ ማድረግ እንዳለበት የኋላ ኋላ ቢገነዘብ እንኳ ሁኔታው ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ እንደሚባለው ሊሆንበት ይችላል። የትዳር ጓደኛውን አመኔታ መልሶ ላያገኝ ይችላል፤ እንዲሁም ልጆቹ ስሜታቸው ተጎድቶና የራሱ ጤንነትም ተቃውሶ ይሆናል። ምናልባት ከእነዚህ ጉዳቶች ውስጥ አንዳንዶቹን መጠገን የሚቻል ቢሆንም እንኳ ይህን ለማድረግ በጣም ብዙ ልፋት ይጠይቃል። በእርግጥም እንዲህ ዓይነት ሰዎች ‘ራሳቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።’—1 ጢሞቴዎስ 6:10
(1 ጢሞቴዎስ 6:10) የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነውና፤ አንዳንዶች በዚህ ፍቅር ተሸንፈው ከእምነት ጎዳና ስተው ወጥተዋል፤ እንዲሁም ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።
ስኬታማ ለመሆን የሚረዱ ስድስት መንገዶች
በመጀመሪያው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ገንዘብ የስኬት ቁልፍ ነው ብለው ሀብትን በጦፈ ስሜት የሚያሳድዱ ሰዎች ጉምን ለመጨበጥ ከመሞከር የማይተናነስ ነገር እያደረጉ ነው። እነዚህ ሰዎች ተስፋ ከመቁረጣቸውም በተጨማሪ ራሳቸውን ለብዙ ችግር ይዳርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሰዎች ሀብትን በጦፈ ስሜት ሲያሳድዱ ብዙውን ጊዜ ከቤተሰባቸውና ከወዳጆቻቸው ጋር ያላቸውን ዝምድና መሥዋዕት ያደርጋሉ። ሌሎች ደግሞ ከሥራ ጫና ብቻ ሳይሆን ከጭንቀት ወይም ከስጋት የተነሳ እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ። መክብብ 5:12 “ጥቂትም ይሁን ብዙ ቢበላ፣ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤ የሀብታም ሰው ብልጽግና ግን እንቅልፍ ይነሣዋል” በማለት ይናገራል።
ገንዘብ ጨካኝ ጌታ ብቻ ሳይሆን አታላይም ጭምር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ “ሀብት [ስላለው] የማታለል ኃይል” ተናግሯል። (ማርቆስ 4:19 NW) በሌላ አነጋገር፣ ሀብት ደስታ የሚያስገኝ ይመስላል፣ ይሁን እንጂ ደስታ አያስገኝም። ከዚህ ይልቅ የበለጠ የማግኘት ጉጉት ይፈጥራል። መክብብ 5:10 “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም” ይላል።
በአጭሩ፣ የገንዘብ ፍቅር ለውድቀት የሚዳርግ ከመሆኑም በላይ ውሎ አድሮ ወደ ሐዘንና ብስጭት አልፎ ተርፎም ወደ ወንጀል ይመራል። (ምሳሌ 28:20) ከደስታና ከስኬት ጋር ይበልጥ ቁርኝት ያላቸው ነገሮች ለጋስነት፣ ይቅር ባይነት፣ የሥነ ምግባር ንጽሕና፣ ፍቅርና መንፈሳዊነት ናቸው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(1 ጢሞቴዎስ 4:2) ይህም የሚሆነው በጋለ ብረት የተተኮሰ ያህል ሕሊናቸው የደነዘዘባቸው ግብዝ ሰዎች በሚናገሩት ውሸት የተነሳ ነው።
በአምላክ ፊት ጥሩ ሕሊና መያዝ
17 ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጥሩ ሕሊና ይኑራችሁ” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 3:16) የሚያሳዝነው ግን ይሖዋ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተደጋጋሚ ችላ የሚሉ ሰዎች ሕሊና፣ ውሎ አድሮ እነሱን ማስጠንቀቅ ያቆማል። ጳውሎስ እንዲህ ያሉት ሰዎች “በጋለ ብረት የተተኮሰ ያህል ሕሊናቸው የደነዘዘባቸው” እንደሆኑ ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 4:2) የጋለ ብረት አቃጥሎህ ያውቃል? እንዲህ ዓይነት ነገር ካጋጠመህ ቆዳህ በጣም ስለሚቃጠል ይደነዝዛል። በተመሳሳይም አንድ ሰው በተደጋጋሚ መጥፎ ነገር የሚፈጽም ከሆነ ሕሊናው ‘ስለሚደነዝዝ’ ከጊዜ በኋላ መሥራቱን ያቆማል።
(1 ጢሞቴዎስ 4:13) እኔ እስክመጣ ድረስ ለሰዎች ለማንበብ፣ አጥብቀህ ለመምከርና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ።
it-2 714 አን. 1-2
ለሰዎች ማንበብ
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ በጥቅልል መልክ የተዘጋጁት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በብዙዎች እጅ አይገኙም ነበር፤ በመሆኑም ቅዱሳን መጻሕፍት በሕዝብ ፊት ይነበቡ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እሱ የላካቸው ደብዳቤዎች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በሕዝብ ፊት እንዲነበቡ እንዲሁም ጉባኤዎቹ ደብዳቤዎቹን ተለዋውጠው ለወንድሞች እንዲያነቡላቸው አዝዞ ነበር። (ቆላ 4:16፤ 1ተሰ 5:27) ጳውሎስ ወጣት የበላይ ተመልካች ለሆነው ለጢሞቴዎስ ምክር ሲሰጥ “ለሰዎች ለማንበብ፣ አጥብቀህ ለመምከርና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ” ብሏል።—1ጢሞ 4:13
ለሰዎች ወይም በሕዝብ ፊት የሚያነብ ሰው አቀላጥፎ የማንበብ ችሎታ ሊኖረው ይገባል። (ዕን 2:2 ግርጌ) ለሰዎች የሚያነብ ሰው ለአድማጮቹ ትምህርት እያስተላለፈ ነው፤ በመሆኑም የሚያነበውን ነገር በደንብ ማስተዋል እንዲሁም የጸሐፊውን ዓላማ በሚገባ መረዳት ያስፈልገዋል፤ በተጨማሪም ለአድማጮች የተሳሳተ መልእክት እንዳያስተላልፍ መጠንቀቅ ይኖርበታል። ራእይ 1:3 ላይ እንደተጠቀሰው ትንቢቱን ጮክ ብሎ የሚያነብ እንዲሁም ቃሉን የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፉትን ነገሮች የሚጠብቁት ደስተኞች ይሆናሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ