ግርማ ሞገስ—ለራስ ውዳሴ ወይስ ለአምላክ ክብር?
ዜኖፎን የሚባል አንድ ታዋቂ የግሪክ ጄኔራል “አንድ መሪ ከተገዥዎቹ የተሻለ መሆኑ ብቻ አይበቃም። ስሜታቸውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የሚያስችል ኃይል ሊኖረው ይገባል” ብሎ ነበር። ዛሬ ብዙዎች እንዲህ የመሰለውን “ኃይል” ግርማ ሞገስ ብለው ይጠሩታል።
እርግጥ ነው ግርማ ሞገስ ያላቸው ሁሉም ሰብዓዊ መሪዎች አይደሉም። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ስብዕና ያላቸው መሪዎች ችሎታቸውን የሚጠቀሙበት ሕዝቡ ለእነርሱ ያደረ እንዲሆንና ለግል ጥቅማቸው እንዲገዛ ለማድረግ ነው። በዚህ ረገድ በሰፊው የሚታወቀው የዘመናችን ምሳሌ ታዋቂው አዶልፍ ሂትለር ሳይሆን አይቀርም። ዊልያም ኤል ሺረር ዘ ራይዝ ኤንድ ፎል ኦቭ ዘ ሰርድ ራይክ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “[በ1933] ሂትለር ለብዙሃኑ የጀርመን ሕዝብ ከአንድ መሪ የሚጠበቀውን ግርማ ሞገስ የተላበሰ ወይም በቅርቡ ሊላበስ የሚችል መሪ ነበር። ሂትለር መለኮታዊ ተልእኮ ተሰጥቶት የመጣ ይመስል ሕዝቡ ለቀጣዮቹ ሁከት የነገሠባቸው አሥራ ሁለት ዓመታት በጭፍን ተከትሎታል።”
ሃይማኖታዊ ታሪክም እንዲሁ ሰዎችን ለእነርሱ ያደሩ እንዲሆኑ በማድረግ ወደ ጥፋት በነዷቸው ግርማ ሞገስ ያላቸው መሪዎች የተሞላ ነው። ኢየሱስ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች:- እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ” ሲል አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 24:4, 5) ግርማ ሞገስ የነበራቸው የሐሰት ክርስቶሶች ብቅ ያሉት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብቻ አልነበረም። በ1970ዎቹ ጂም ጆንስ የተባለ ሰው “ፒፕልስ ቴምፕል” ለተባለ ቡድን “መሲህ” ነኝ ብሎ ነበር። ይህ ሰው “ሰዎችን የመሳብ ልዩ ኃይል ያለው” “ግርማ ሞገስ የተላበሰ የቤተ ክርስቲያን ሰው” እንደሆነ ይነገርለት የነበረ ሲሆን በ1978 ብዙ ሰዎች በጅምላ ሆነው የገዛ ሕይወታቸውን እንዲያጠፉ አነሳስቷል። ይህም በታሪክ ከተፈጸሙት ተመሳሳይ ድርጊቶች ሁሉ የከፉ ናቸው ከተባሉት መሃል የሚፈረጅ ሆኗል።a
ግርማ ሞገስ ጎጂ ስጦታ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለሁሉም ጥቅም ሲል ለሰዎች ሁሉ ስለሚሰጠው ልዩ ስጦታ ወይም ስጦታዎች ይናገራል። ይህን ስጦታ የሚያመለክተው ግሪክኛ ቃል ካሪስማ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 17 ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። አንድ ግሪካዊ ምሁር ቃሉን እንደሚከተለው በማለት ተርጉመውታል:- ‘ነፃና ይገባናል የማንለው ስጦታ፣ ምንም ላለፋበት ሰው በጸጋ የሚሰጥና በጥረቱ ሊያገኘው ወይም ሊደርስበት የማይችል በአምላክ ጸጋ የሚገኝ ነገር ነው።’
ስለዚህ ከቅዱስ ጽሑፉ አንጻር ስንመለከተው ካሪስማ ይገባናል በማንለው የአምላክ ደግነት ምክንያት የተቀበልነው ስጦታ ነው። አምላክ በደግነት ከሰጠን ስጦታዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ለእሱ ውዳሴ ለማምጣትስ ልንጠቀምባቸው የምንችለው እንዴት ነው? ከእነዚህ የደግነት ስጦታዎች ውስጥ ሦስቱን እንመልከት።
ዘላለማዊ ሕይወት
ከሁሉ የሚበልጠው ስጦታ የዘላለም ሕይወት ስጦታ መሆኑ ምንም አያጠራጥርም። ጳውሎስ ለሮም ጉባኤ ሲጽፍ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ [ካሪስማ] ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው” ብሏል። (ሮሜ 6:23) ይህ “ደመወዝ” (ሞት) ፈልገነው ባይሆንም እንኳ በኃጢአተኛው ተፈጥሯችን ምክንያት የተከፈለን ነገር መሆኑን ማስተዋል ይገባናል። በሌላ በኩል ደግሞ አምላክ የዘረጋልን የዘላለም ሕይወት በሥራችን ልናገኘው የማንችለው ፈጽሞ ይገባናል የማንለው ነገር ነው።
የዘላለም ሕይወት ስጦታ እንደ ውድ ሀብት አድርገን ልንቆጥረውና ሌሎችም እንዲያገኙት ልናደርገው የሚገባ ነገር ነው። ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁና እርሱንም እንዲያገለግሉ በመርዳት የዘላለም ሕይወት ስጦታ እንዲቀበሉ ልናደርግ እንችላለን። ራእይ 22:17 እንዲህ ይላል:- “መንፈሱና ሙሽራይቱም:- ና ይላሉ። የሚሰማም:- ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ።”
ሌሎች ሰዎችን ወደዚህ ሕይወት ሰጭ ውኃ ልንመራቸው የምንችለው እንዴት ነው? ዋነኛው መንገድ በአብዛኛው መጽሐፍ ቅዱስን በአገልግሎታችን ላይ ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠቀም ነው። በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ሰዎች ስለ መንፈሳዊ ነገሮች አያስቡም ወይም አያነቡም። ቢሆንም ‘ጆሮውን የምናነቃቃለት’ ሰው አናጣም። (ኢሳይያስ 50:4) ‘የአምላክ ቃል ሕያውና የሚሠራ’ ስለሆነ በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ባለው ለሥራ የማንቀሳቀስ ኃይል ልንተማመን እንችላለን። (ዕብራውያን 4:12) የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ያዘለው ተግባራዊ ጥበብም ይሁን የሚሰጠው ማጽናኛና ተስፋ ወይም ስለ ሕይወት ዓላማ የያዘው ማብራሪያ የሰዎችን ልብ ሊነካና ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ እንዲጓዙ ሊያደርግ ይችላል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች “ና” እንድንል ሊረዱን ይችላሉ። ነቢዩ ኢሳይያስ በዚህ መንፈሳዊ ጨለማ በዋጠው ዘመን ይሖዋ በሕዝቡ ላይ ‘ብርሃንን እንደሚያወጣ’ አስቀድሞ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 60:2) የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሚያወጣቸው ጽሑፎች ከይሖዋ የሚገኘውን ይህን በረከት የሚያንጸባርቁ ሲሆን በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን የመንፈሳዊ ብርሃን ምንጭ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይመራሉ። ጽሑፎቹ ለግለሰቦች ታዋቂነት የቆሙ አይደሉም። የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት መግቢያ እንደሚያብራራው “የመጠበቂያ ግንብ ዓላማ የይሖዋን አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ከፍ ከፍ ማድረግ ነው። . . . ደሙን በማፍሰስ ለሰው ዘሮች የዘላለም ሕይወት መንገድ በከፈተውና በአሁኑ ጊዜ በመግዛት ላይ በሚገኘው በአምላክ በተሾመው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት እንዲኖረን ያበረታታል።”
አንዲት ለብዙ ዓመታት በአገልግሎቷ ውጤታማ የነበረች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነች ክርስቲያን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ሰዎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ በመርዳት ረገድ የሚያበረክቱትን ጥቅም ስትገልጽ “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶችን ማንበብና ማድነቅ ሲጀምሩ ፈጣን እድገት ያደርጋሉ። እነዚህ መጽሔቶች ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ በመርዳት ረገድ በዋጋ ሊተመን የማይችል ጠቀሜታ ያበረከቱልኝ ጽሑፎች ናቸው” ብላለች።
የአገልግሎት መብቶች
ጢሞቴዎስ ልዩ ትኩረትን የሚሻ ሌላ ስጦታም የተቀበለ ክርስቲያን ደቀ መዝሙር ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ “በትንቢት ከሽማግሌዎች እጅ መጫን ጋር የተሰጠህን፣ በአንተ ያለውን የጸጋ ስጦታ [ካሪስማ] ቸል አትበል” ሲል ነግሮታል። (1 ጢሞቴዎስ 4:14) ይህ ስጦታ ምን ነበር? ጢሞቴዎስ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ መሾሙን የሚመለከት ነበር። ይህ ስጦታ ጢሞቴዎስ ኃላፊነት ተሰምቶት በቁም ነገር ሊይዘው የሚገባው የአገልግሎት መብት ነበር። ጳውሎስ በዚያው ምዕራፍ “ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ። ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፣ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና” ሲል መክሮታል።—1 ጢሞቴዎስ 4:13, 16
ዛሬም ቢሆን ሽማግሌዎች የአገልግሎት መብቶቻቸውን በአድናቆት ሊመለከቷቸው ይገባል። ጳውሎስ እንዳመለከተው ይህን ሊያደርጉ የሚችሉበት አንዱ መንገድ ‘ለትምህርታቸው በመጠንቀቅ’ ነው። ግርማ ሞገስ ያላቸው ዓለማዊ መሪዎች የሚያደርጉትን ባለመኮረጅ የሰዎች ትኩረት በእነሱ ሳይሆን በአምላክ ላይ እንዲያርፍ ያደርጋሉ። ምሳሌያቸው የሆነው ኢየሱስ ተወዳዳሪ የሌለው አስተማሪና የሚስብ ስብዕና የነበረው ሰው እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ በትሕትና ለአባቱ ክብር ሰጥቷል። “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም” ሲል ተናግሯል።—ዮሐንስ 5:41፤ 7:16
ኢየሱስ ለሚያስተምረው ነገር የአምላክን ቃል ባለ ሥልጣን አድርጎ በመጥቀስ ለሰማያዊ አባቱ ክብር ሰጥቷል። (ማቴዎስ 19:4-6፤ 22:31, 32, 37-40) በተመሳሳይም ጳውሎስ የበላይ ተመልካቾች ‘በማስተማሩ ሥራቸው በታመነው ቃል የሚጸኑ መሆን እንዳለባቸው’ አበክሮ ተናግሯል። (ቲቶ 1:9) ሽማግሌዎች የሚሰጧቸው ንግግሮች በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በጥብቅ የተመሠረቱ እንዲሆኑ ካደረጉ እንደ ኢየሱስ “እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም” ያሉ ያህል ሊሆን ይችላል።—ዮሐንስ 14:10
ሽማግሌዎች ‘በታመነው ቃል ሊጸኑ’ የሚችሉት እንዴት ነው? በንግግሮቻቸውና በስብሰባ ክፍሎቻቸው ላይ የሚጠቀሙባቸውን ጥቅሶች በማብራራትና በማጉላት አድማጮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ ነው። ተዋናይ የሚያስመስሉ መግለጫዎችን ወይም የሚያስቁ አባባሎችን ከልክ በላይ ማብዛት አድማጮች በአምላክ ቃል ላይ ሳይሆን በተናጋሪው ችሎታ ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋቸዋል። በሌላ በኩል ግን ልብ የሚነኩትና አድማጮችን ለሥራ የሚያነሣሡት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ናቸው። (መዝሙር 19:7-9፤ 119:40፤ ከሉቃስ 24:32 ጋር አወዳደር።) እንዲህ ያሉ ንግግሮች እምብዛም በሰዎቹ ላይ እንዳይተኮር ስለሚያደርጉ ለአምላክ ላቅ ያለ ክብር ይሰጣሉ።
ሽማግሌዎች ይበልጥ ውጤታማ አስተማሪዎች ሊሆኑ የሚችሉበት ሌላው መንገድ አንዳቸው ከሌላው በመማር ነው። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንደረዳው ሁሉ አንዱ ሽማግሌ ሌላውን ሊያግዘው ይችላል። “ብረት ብረትን ይስለዋል፣ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል።” (ምሳሌ 27:17፤ ፊልጵስዩስ 2:3) ሽማግሌዎች እርስ በርስ ሐሳብ በመለዋወጥ ሊጠቀሙ ይችላሉ። በቅርቡ የተሾመ አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል:- “አንድ ተሞክሮ ያካበተ ሽማግሌ የሕዝብ ንግግር እንዴት እንደሚዘጋጅ ቁጭ ብሎ አሳየኝ። ሲዘጋጅ ጥልቅ ምርምር ያደረገባቸውን መልስ የማይሰጥባቸው ጥያቄዎች፣ ማብራሪያዎች፣ ምሳሌዎች ወይም አጫጭር ተሞክሮዎች ይጨምራል። የምሰጣቸው ንግግሮች ደረቅና አሰልቺ እንዳይሆኑ እንዴት የተለያዩ ነገሮችን መጨመር እንደምችል ከዚህ ሽማግሌ ተምሬአለሁ።”
ሽማግሌዎችም እንሁን የጉባኤ አገልጋዮች ወይም አቅኚዎች የአገልግሎት መብቶች ያሉን ሁላችንም ስጦታዎቻችንን ከፍ አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል። ጳውሎስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ‘በእሱ ያለውን የእግዚአብሔርን ስጦታ [ካሪስማ] እንደ እሳት እንዲያቀጣጥል’ ጢሞቴዎስን አሳስቦታል። ይህ በተለይ ጢሞቴዎስ የነበሩትን አንዳንድ ልዩ የሆኑ የመንፈስ ስጦታዎችን የሚጨምር ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 1:6) በእስራኤላውያን ቤቶች ውስጥ የሚገኘው እሳት አብዛኛውን ጊዜ የተዳፈነ ፍም ነበር። ይህን ፍም ‘በማቀጣጠል’ እንዲነድና የበለጠ ሙቀት እንዲሰጥ ማድረግ ይቻል ነበር። እኛም ልባችንንና ጉልበታችንን በተሰጠን የሥራ ኃላፊነት ላይ እንድናደርግና የተቀበልነውን ማንኛውንም ዓይነት መንፈሳዊ ስጦታ ልክ እንደ እሳት እንድናቀጣጥል ማበረታቻ ተሰጥቶናል።
ለሌሎች የምናካፍላቸው መንፈሳዊ ስጦታዎች
ጳውሎስ በሮም ለሚገኙት ወንድሞቹ የነበረው ፍቅር እንደሚከተለው በማለት እንዲጽፍ አነሣሥቶታል:- “ትጸኑ ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታ [ካሪስማ] እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እናፍቃለሁና፤ ይህንም ማለቴ በመካከላችን ባለች በእናንተና በእኔ እምነት አብረን በእናንተ እንድንጽናና ነው።” (ሮሜ 1:11, 12) ጳውሎስ ሌሎችን በማነጋገር እምነታቸውን ማጠንከር መቻላችንን እንደ መንፈሳዊ ስጦታ አድርጎ ተመልክቶታል። ይህን መሳዩን መንፈሳዊ ስጦታ መለዋወጡ እምነታችንን ያጠነክራል፤ እንዲሁም እርስ በርስ ለመበረታታት ያስችለናል።
ይህ ደግሞ አስፈላጊ ነገር ነው። በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ስንኖር ሁላችንም በአንድ ነገር ወይም በሌላ ውጥረት ያጋጥመናል። ይሁን እንጂ አዘውትረን ማበረታቻዎችን መለዋወጣችን እንድንጸና ይረዳናል። እርስ በርስ መለዋወጥ ማለትም ማበረታቻ መስጠትና መቀበል መንፈሳዊ ጥንካሬን ጠብቆ ለማቆየት በጣም አስፈላጊ ነው። እርግጥ ሁላችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ማበረታቻ ማግኘት ቢያስፈልገንም ሁላችንም አንዳችን ሌላውን ለመገንባት እንችላለን።
የተከዙ የእምነት አጋሮቻችንን ካስተዋልን “ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን።” (2 ቆሮንቶስ 1:3-5) መጽናናት ለሚለው የገባው የግሪክኛ ቃል (ፓራክሌሲስ) ቃል በቃል ሲተረጎም “ከጎኔ ቁም” ማለት ነው። በሚያስፈልግበት ጊዜ ለወንድማችን ወይም ለእህታችን የእርዳታ እጃችንን በመዘርጋት ከጎናቸው እንቆማለን። እኛም በሚያስፈልገን ሁሉ ይህን ፍቅራዊ ድጋፍ እንደምናገኝ ምንም ጥርጥር የለውም።—መክብብ 4:9, 10፤ ከሥራ 9:36-41 ጋር አወዳድር።
በተጨማሪም ሽማግሌዎች የሚያደርጓቸው ፍቅራዊ የእረኝነት ጉብኝቶች ከፍተኛ ጥቅም አላቸው። አንዳንድ ጊዜ ትኩረት በሚያሻ ጉዳይ ላይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለመስጠት የሚደረጉ የእረኝነት ጉብኝቶች ቢኖሩም አብዛኛዎቹ የእረኝነት ጉብኝቶች ግን ለማበረታታትና ‘ልብን ለማጽናናት’ የሚያስችሉ አጋጣሚዎች ናቸው። (ቆላስይስ 2:2) የበላይ ተመልካቾች እነዚህን የመሳሰሉ እምነትን የሚያጠነክሩ ጉብኝቶች በሚያደርጉበት ጊዜ መንፈሳዊ ስጦታን እያካፈሉ መሆናቸው የተረጋገጠ ነው። ልክ እንደ ጳውሎስ ይህን የመሰለውን ስጦታ ማካፈል የሚክስ ሆኖ ያገኙታል። እንዲሁም ወንድሞቻቸውን “ለማየት እንዲናፍቁ” ሊያደርጋቸው ይችላል።—ሮሜ 1:11
የሚከተለውን ተሞክሮ የተናገረው በስፔይን የሚገኝ አንድ ሽማግሌ ሁኔታ ይህ ጉዳይ እውነት መሆኑን ያሳያል:- “የ11 ዓመቱ ሪካርዶ ለስብሰባዎችም ሆነ በአጠቃላይ ለጉባኤ ምንም ፍላጎት አልነበረውም። ስለዚህ የሪካርዶን ወላጆች ልጃቸውን እንዳነጋግረው እንዲፈቅዱልኝ ጠየቅኋቸው። እነሱም ደስ እያላቸው ተስማሙ። ቤታቸው የሚገኘው ከእኔ ቤት ለአንድ ሰዓት ያህል የመኪና ጉዞ በሚጠይቅ ተራራማ አካባቢ ነበር። ሪካርዶ እሱን ለመርዳት ብዬ ባደረግሁት ነገር ስለ ተደሰተ አፋጣኝ ምላሽ ሰጠ። ብዙም ሳይቆይ ያልተጠመቀ አስፋፊ በመሆን የጉባኤው ጠንካራ አባል ሆነ። በተፈጥሮው ቁጥብ የነበረው ጠባዩ ደስተኛና ይበልጥ ወዳጃዊ በሆነ ባሕርይ ተተካ። በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ አንዳንዶች ‘ሪካርዶ ምን አግኝቶ ነው?’ በማለት ጠይቀዋል። ገና ለመጀመሪያ ጊዜ ያዩት ይመስል ነበር። ስለዚያ እጅግ ወሳኝ ስለነበረ የእረኝነት ጉብኝት ሳስብ ከሪካርዶ ይበልጥ የተጠቀምኩት እኔ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ወደ መንግሥት አዳራሹ ሲገባ ፊቱ ይፈካል፤ እየሮጠ መጥቶ ሰላም ይለኛል። መንፈሳዊ እድገት ሲያደርግ መመልከት የሚያስደስት ነበር።”
እንደዚህ የመሰሉ የእረኝነት ጉብኝቶች ትልቅ በረከት እንደሚያስገኙ ምንም ጥርጥር የለውም። እንደነዚህ ያሉት ጉብኝቶች ኢየሱስ “ጠቦቶቼን ጠብቅ” ብሎ ከተናገረው ጋር የሚስማሙ ናቸው። (ዮሐንስ 21:16) እርግጥ ነው እነዚህን የመሰሉ መንፈሳዊ ስጦታዎች ሊያካፍሉ የሚችሉት ሽማግሌዎች ብቻ አይደሉም። በጉባኤ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ሰው ሌላውን ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ሊያነሣሣ ይችላል። (ዕብራውያን 10:23, 24) አንድን ተራራ የሚወጡ ሰዎች እርስ በርስ በገመድ እንደሚታሠሩ ሁሉ እኛም በመንፈሳዊ ነገሮች ተሳስረናል። ወደድንም ጠላን የምናደርገውም ሆነ የምንናገረው ነገር ሌሎችን ይነካል። አሽሙር ያዘለ አስተያየት ወይም ሻካራ ትችት አንድ አድርጎ ያስተሣሠረንን ሰንሰለት ያላላል። (ኤፌሶን 4:29፤ ያዕቆብ 3:8) በሌላ በኩል ደግሞ አበረታች የሆኑ የተመረጡ ቃላትን መናገርና ፍቅራዊ እርዳታ መስጠት ወንድሞቻችን ያሉባቸውን ችግሮች እንዲወጡ ሊረዷቸው ይችላሉ። በዚህ መንገድ አንዳችን ለሌላው ዘላቂ ጥቅም ያላቸውን መንፈሳዊ ስጦታዎች ማካፈል እንችላለን።—ምሳሌ 12:25
የአምላክን ክብር በተሟላ መንገድ ማንጸባረቅ
እያንዳንዱ ክርስቲያን በተወሰነ ደረጃ ግርማ ሞገስ እንደሚኖረው የተረጋገጠ ነው። በዋጋ ሊተመን የማይችለው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ተሰጥቶናል። በተጨማሪም አንዳችን ለሌላው ልናካፍለው የምንችላቸው መንፈሳዊ ስጦታዎችም አሉን። እንዲሁም ሌሎችን ትክክለኛ ዓላማ እንዲኖራቸው ለመቀስቀስና ለመገፋፋት ልንጥር እንችላለን። አንዳንዶች ደግሞ የአገልግሎት መብቶችን የመሳሰሉ ተጨማሪ ስጦታዎች አሏቸው። እነዚህ ሁሉ ስጦታዎች ይገባናል የማንለው የአምላክ ደግነት መግለጫዎች ናቸው። ያሉን ስጦታዎች በሙሉ ከአምላክ የተቀበልናቸው ስለሆኑ ምንም የምንኩራራበት ምክንያት የለም።—1 ቆሮንቶስ 4:7
ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ራሳችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቅ ይገባል:- “ያለኝን ማራኪ ተሰጥኦ ‘የበጎ ስጦታና የፍጹም በረከት ሁሉ’ ምንጭ ለሆነው ለይሖዋ ክብር ለማምጣት እጠቀምበታለሁን? (ያዕቆብ 1:17) ችሎታዬና ሁኔታዬ በፈቀደልኝ መጠን ሌሎችን በማገልገል የኢየሱስን ምሳሌ እከተላለሁን?”
ሐዋርያው ጴጥሮስ በዚህ ረገድ ያለብንን ኃላፊነት ሲያጠቃልል እንደሚከተለው ብሏል:- “ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፣ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ [ካሪስማ] እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤ ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፣ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢሆን፣ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ . . . በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ።”—1 ጴጥሮስ 4:10, 11
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ጂም ጆንስን ጨምሮ በአጠቃላይ 913 ሰዎች ሞተዋል።
[ምንጭ]
Corbis-Bettmann
UPI/Corbis-Bettmann