ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ማክበር
“ሁሉን አክብሩ . . . እግዚአብሔርን ፍሩ፣ ንጉሥን አክብሩ።”—1 ጴጥሮስ 2:17
1. (ሀ) ከአምላክና ከክርስቶስ በተጨማሪ ለእነማን ክብር መስጠቱ ተገቢ ነው? (ለ) በ1 ጴጥሮስ 2:17 መሠረት ለሰዎች ክብር የሚሰጠው በምን መስኮች ነው?
ይሖዋ አምላክንና ኢየሱስ ክርስቶስን የማክበር ግዴታ እንዳለብን ተመልክተናል። እነርሱን ማክበር ትክክለኛ፥ ፍቅርና ጥበብ ያለበት ድርጊት ነው። ሆኖም የአምላክ ቃል በተጨማሪ የሰው ልጆችንም ማክበር እንደሚኖርብን ይናገራል። “ሁሉንም ዓይነት ሰዎች አክብሩ ተብለናል”። (1 ጴጥሮስ 2:17 አዓት) ይህ ጥቅስ የሚደመደመው “ንጉሥን አክብሩ” በማለት ስለሆነ ክብር የሚሰጠው በሹመታቸው ምክንያት ክብር ሊቀበሉ ለሚገባቸው ሰዎች ነው ማለት ነው። ታዲያ ማክበር የሚኖርብን እነማንን ነው? ሊከበሩ የሚገባቸው ሰዎች ቁጥር ብዙዎች ከሚያስቡት በላይ ሊሆን ይችላል። ለሌሎች ሰዎች ክብር መስጠት ተገቢ የሚሆንባቸው አራት መስኮች አሉ ለማለት እንችላለን።
የፖለቲካ ገዥዎችን ማክበር
2. በ1 ጴጥሮስ 2:17 ላይ የተጠቀሰው “ንጉሥ” ማንኛውንም ሰብዓዊ ንጉሥ ወይም የፖለቲካ ገዥ እንደሚያመለክት እንዴት እናውቃለን?
2 ከእነኚህ መስኮች የመጀመሪያው ዓለማዊ መንግሥታትን የሚመለከት ነው። የፖለቲካ ገዥዎችን ማክበር ያስፈልገናል። ጴጥሮስ ንጉሥን “አክብሩ ሲል” በመከረ ጊዜ ስለ ፖለቲካዊ ገዥዎች መናገሩ ነበር የምንለው ለምንድን ነው? ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ስላለ ሁኔታ መናገሩ ስለነበረ ነው። ከዚህ ቀደም ብሎ “ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን፣ ከሁሉ በላይ ነውና፤ ለመኳንንትም ቢሆን፣ . . . ከእርሱ ተልከዋልና ተገዙ” ብሎአል። (1 ጴጥሮስ 2:13, 14) ስለዚህ ጴጥሮስ እንድናከብረው የመከረን “ንጉሥ” ሰብዓዊ ነገሥታትንና የፖለቲካ ገዥዎችን ያመለክታል።
3. “የበላይ ባለሥልጣኖች” እነማን ናቸው? ምንስ ሊሰጣቸው ይገባል?
3 ሐዋርያው ጳውሎስም በተመሳሳይ “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ” ሲል አዝዞአል። እነዚህ “የበላይ ባለ ሥልጣኖች” የፖለቲካ ገዥዎችና የመንግሥት ባለሥልጣኖች ናቸው እንጂ ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ አይደሉም። ጳውሎስም ይህን በመገንዘብ ቀጥሎ “ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ። . . . ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ” ብሎአል። አዎ፣ እነዚህ አምላክ የፖለቲካ ሥልጣን እንዲኖራቸው የፈቀደላቸው ሰዎች ክብር ሊቀበሉ ይገባል።—ሮሜ 13:1, 7
4. (ሀ) የፖለቲካ ገዥዎችን እንዴት ማክበር ይቻላል? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ ለገዥዎች ክብር በመስጠት ረገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል?
4 የፖለቲካ ገዥዎችን የምናከብረው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ እነርሱን በጥልቅ ማክበር ነው። ( ከ1 ጴጥሮስ 3:15 ጋር አወዳድር ) ክፉ ሰዎች ቢሆንም እንኳን ስለተሰጣቸው ሥልጣን መከበር ይገባቸዋል። ሮማዊው ታሪክ ጸሐፊ ታሲተስ ፊሊክስ ስለተባለው ገዥ ሲገልጽ “ምንም ዓይነት ቅጣት ወይም ጉዳት ሳይደርስበት ማንኛውንም ዓይነት ክፉ ድርጊት ሊፈጽም እንደሚችል የሚያስብ ሰው ነበር” ብሎአል። ሆኖም ጳውሎስ በፊልክስ ፊት የመከላከያ ክርክሩን ባቀረበ ጊዜ ንግግሩን የከፈተው በአክብሮት ቃላት ነበር። በተመሳሳይም ጳውሎስ ለንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳ ዳግማዊ ሲናገር “ዛሬ በፊትህ ስለምመልስ ራሴን እጅግ እንደ ተመረቀ አድርጌ እቈጥረዋለሁ” ብሎአል። ይህን የተናገረው አግሪጳ የቅርብ የሥጋ ዘመዱን አግብቶ እንደሚኖር እያወቀ ነበር። በተጨማሪም ጳውሎስ ፊስጦስ ጣዖት አምላኪ እንደሆነ ቢያውቅም “ክቡር ፊስጦስ ሆይ!” ብሎታል።—ሥራ 24:10፤ 26:2, 3, 24, 25
5. ለመንግሥት ባለሥልጣኖች አክብሮት የሚሰጥበት ምን ሌላ መንገድ አለ? ይህንንስ በማድረግ ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ ምሳሌ የሆኑት እንዴት ነው?
5 የመንግሥት ባለሥልጣኖችን ማክበራችንን ከምናሳይባቸው መንገዶች አንዱ ሐዋርያው ጳውሎስ ለመንግሥት ባለሥልጣኖች የሚገባቸውን ስለመስጠት በጻፈው ቃል ተገልጾአል። “ግብር ለሚገባው ግብርን፣ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን . . . ስጡ” ብሎአል። (ሮሜ 13:7) የይሖዋ ምስክሮች እንዲህ ያለውን ክብር የሚሰጡት በአንድ የተወሰነ አገር ውስጥ ብቻ አይደለም። በጣልያን አገር ላ ስታምፓ የተባለው ጋዜጣ “ማንም ሊያገኛቸው የማይችል ታማኝ ዜጎች ናቸው። ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ታክስ አያጭበረብሩም ወይም የማያመቻቸውን ሕግ አይጥሱም” ብሎአል። የፓልም ቢች፣ ፍሎሪዳ፣ ዩ ኤስ ኤ ዘ ፖስት የተባለ ጋዜጣም ስለ የይሖዋ ምሥክሮች ሲናገር “ግብራቸውን በሚገባ ይከፍላሉ፤ ከአገሪቱ ዜጎች ሁሉ የበለጡ ሐቀኛ ዜጎች ናቸው” ብሎአል።
ለአሰሪዎች አክብሮት ማሳየት
6. ሐዋርያው ጳውሎስና ጴጥሮስ ክብር መስጠት ይገባል ያሉት ለማን ጭምር ነው?
6 ሁለተኛው አክብሮት የምናሳይበት አካባቢ የሥራ ቦታችን ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም ሆነ ጴጥሮስ ክርስቲያኖች ሁሉ የሥራ አለቆቻቸው ወይም የበላዮቻቸው የሆኑትን ሰዎች ማክበር የሚገባቸው መሆኑን አጠንክረው ተናግረዋል። ጳውሎስ እንዲህ ብሎአል፤ “የእግዚአብሔር ስምና ትምህርቱ እንዳይሰደብ፣ ከቀንበር በታች ያሉቱ ባሪያዎች ሁሉ ለገዙአቸው ጌቶች ክብር ሁሉ እንደተገባቸው ይቊጠሩአቸው። የሚያምኑም ጌቶች ያሉአቸው፣ ወንድሞች ስለሆኑ አይናቁአቸው፣ ነገር ግን በመልካም ሥራቸው የሚጠቀሙ የሚያምኑና የተወደዱ ስለሆኑ፣ ከፊት ይልቅ ያገልግሉ።” ጴጥሮስም “ሎሌዎች ሆይ፣ ለበጎዎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለጠማሞች ደግሞ በፍርሃት ሁሉ ተገዙ” ብሎአል።—1 ጢሞቴዎስ 6:1, 2፤ 1 ጴጥሮስ 2:18፤ ኤፌሶን 6:5፤ ቆላስይስ 3:22, 23
7. (ሀ) “ባሮች” “ለጌቶቻቸው” ተገቢ አክብሮት እንዲያሳዩ የተሰጠው ምክር በዘመናችን የሚሰራው እንዴት ነው? (ለ) ክርስቲያን አሠሪዎች ያሉአቸው ክርስቲያን ሠራተኞች ምን ለማድረግ መጠንቀቅ ይገባቸዋል?
7 እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ ባርነት ተስፋፍቶ የሚገኝ አይደለም። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች በባሪያና በባሪያ አሳዳሪ መካከል የነበረውን ግንኙነት ይመራላቸው የነበረው ሥርዓት ዛሬም በአሠሪና ሠራተኛ መካከል ለሚኖረው ግንኙነት ይሠራል። ስለዚህ ክርስቲያን ቅጥረኛ ሠራተኞች አስቸጋሪ ለሆኑ አሠሪዎቻቸው እንኳን ክብር የመስጠት ግዴታ አለባቸው። አሠሪው የእምነት ባልደረባ ከሆነስ? ሠራተኛው በዚህ ዝምድናው ምክንያት የተለየ ሞገስ ለማግኘት ከመፈለግ ይልቅ ክርስቲያን አሠሪውን በይበልጥ ለማገልገል መፈለግ ይኖርበታል። በምንም መንገድ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት መፈለግ አይኖርበትም።
በቤተሰብ ክልል ውስጥ አክብሮት ማሳየት
8, 9. (ሀ) ልጆች ማንን እንዲያከብሩ ይፈለግባቸዋል? (ለ) ልጆች እንዲህ ያለውን አክብሮት ማሳየት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው? እንዴትስ ሊያሳዩ ይችላሉ?
8 ሶስተኛው ክብር መስጠት አስፈላጊ የሚሆንበት አካባቢ የቤተሰብ ክልል ነው። ለምሳሌ ልጆች ወላጆቻቸውን የማክበር ኃላፊነት አለባቸው። ይህ ለሙሴ በተሰጠው ሕግ ብቻ የታዘዘ አይደለም። በክርስቲያኖች ላይም የተጣለ ግዴታ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፎአል “ልጆች ሆይ፣ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፣ ይህ የሚገባ ነውና። . . . አባትህንና እናትህን አክብር።”—ኤፌሶን 6:1, 2፤ ዘፀአት 20:12
9 ልጆች ወላጆቻቸውን ማክበር የሚኖርባቸው ለምንድን ነው? አምላክ ለወላጆቻቸው ሥልጣን ስለሰጣቸው እንዲሁም ወላጆቻቸው ስለወለዱአቸውና ከሕጻንነታቸው ጀምረው ተንከባክበው ስላሳደጉአቸው ወላጆቻቸውን ማክበር ይገባቸዋል። ልጆች ወላጆቻቸውን የሚያከብሩት እንዴት ነው? ለወላጆቻቸው በመታዘዝና ለእነርሱም በመገዛት ነው። (ምሳሌ 23:22, 25, 26፤ ቆላስይስ 3:20) ያደጉ ልጆች እንዲህ ያለውን ክብር መስጠታቸው ለሸመገሉ ወላጆቻቸውና አያቶቻቸው ቁሳዊና መንፈሣዊ እርዳታ እንዲሰጡ ሊጠይቅባቸው ይችላል። ይህም ግዴታቸው የገዛ ልጆቻቸውን ከመንከባከብ፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ከመገኘትና በመስክ አገልግሎት ከመካፈል ኃላፊነታቸው ጋር መመዛዘን ይኖርበታል።—ኤፌሶን 5:15-17፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8፤ 1 ዮሐንስ 3:17
10. ሚስቶች ማንን የማክበር ግዴታ አለባቸው? ይህንንስ የሚያደርጉት በምን መንገዶች ነው?
10 ሆኖም በቤተሰብ ውስጥ ሌሎችን የማክበር ኃላፊነት ያለባቸው ልጆች ብቻ አይደሉም። ሚስቶች ባሎቻቸውን ማክበር ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ “ሚስትም ባልዋን ትፍራ” ብሎአል። (ኤፌሶን 5:33፤ 1 ጴጥሮስ 3:1, 2) ባሎችን ’መፍራት’ ማክበርን እንደሚጨምር የታወቀ ነው። ሣራ ባልዋን አብርሃምን “ጌታዬ” እያለች ታከብረው ነበር። (1 ጴጥሮስ 3:6) ስለዚህ ሚስቶች ሣራን ምሰሉ። የባሎቻችሁን ውሣኔ በመቀበልና ውሣኔያቸው እንዲሳካ ጥረት በማድረግ አክብሩአቸው። በባሎቻችሁ ሸክም ላይ ተጨማሪ ሸክም ከመጨመር ይልቅ ሸክማቸው እንዲቀልላቸው በመርዳት እንደምታከብሩአቸው ታሳያላችሁ።
11. ክብር በማሳየት ረገድ ባሎች ምን ግዴታ አለባቸው? ለምንስ?
11 ባሎችስ? በአምላክ ቃል “እንዲሁም እናንተ ባሎች ሆይ፣ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል፣ አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው” ተብለው ታዝዘዋል። (1 ጴጥሮስ 3:7) ይህ በእርግጥም ማንኛውም ባል ሊያስብበት የሚገባ ነገር ነው። ሚስት “ውድ፣ ተሰባሪ፣ በጥንቃቄ መያዝ የሚገባው” የሚል ጽሕፈት እንደተለጠፈበት ዕቃ ልትቆጠር ትችላለች። ስለዚህ ባሎች ለሚስቶቻቸው አሳቢ በመሆን አክብሮት ካላሳዩአቸው ጸሎታቸው ስለሚታገድ ከይሖዋ አምላክ ጋር ያላቸው ዝምድና ይበላሽባቸዋል። በእርግጥ የቤተሰብ አባሎች እርስ በርሳቸው ቢከባበሩ ሁሉም ተጠቃሚዎች ይሆናሉ።
በጉባኤ ውስጥ
12. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ክብር የማሳየት ኃላፊነት ያለባቸው እነማን ናቸው? (ለ) ክብር መቀበል ተገቢ መሆኑን ኢየሱስ ያሳየው እንዴት ነው?
12 ሁሉም ክርስቲያኖች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አክብሮት የማሳየት ግዴታ አለበት። “እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ” የሚል ምክር ተሰጥቶናል። (ሮሜ 12:10) ኢየሱስ ከምሳሌዎቹ በአንዱ ክብር መቀበል ትክክል መሆኑን አመልክቶአል። ለግብዣ በተጠራን ጊዜ አስተናጋጃችን ከፍተኛ ቦታ ላይ ሲያስቀምጠን በተጋበዙት ሰዎች ሁሉ ፊት ክብር እንድናገኝ አስቀድመን ዝቅተኛ ቦታ ላይ እንድንቀመጥ ተናግሮአል። (ሉቃስ 14:10) ሁላችንም መከበር የምንወድ ከሆነ እኛም ለሌሎች አሳቢነት በማሳየት ልናከብራቸው አይገባንምን? ግን አክብሮት የምናሳየው እንዴት ነው?
13. በጉባኤ ውስጥ ላሉ ሌሎች ሰዎች ክብር ከምንሰጥባቸው መንገዶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
13 ለጥሩ ሥራ የአድናቆት ወይም የምሥጋና ቃል መናገር ክብር እንደመስጠት ይቆጠራል። ስለዚህ አንድ ሰው ለሰጠው ንግግር ወይም በጉባኤ ስብሰባ ላይ ለሰጠው ሐሳብ በማመስገን እርስ በርሳችን ልንከባበር እንችላለን። ከዚህም በላይ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን የጠለቀ አክብሮት በማሳየትና ራሳችንን ዝቅ በማድረግ እርስ በርሳችን ልንከባበር እንችላለን። (1 ጴጥሮስ 5:5) ይህን በማድረጋችንም የተከበሩና ውድ የይሖዋ አገልጋዮች እንደሆኑ አድርገን እንደምንመለከታቸው እናረጋግጣለን።
14. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞች ለእህቶች ተገቢ አክብሮት ሊሰጡ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ሥጦታ መስጠት ክብር ከምናሳይባቸው መንገዶች አንዱ እንደሆነ እንዴት ለማወቅ እንችላለን?
14 ሐዋርያው ጳውሎስ ወጣቱን ጢሞቴዎስን በዕድሜ ገፋ ያሉ ክርስቲያን እህቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት እህቶችን ደግሞ እንደ ሥጋ እህቶች “በፍጹም ንጽሕና” እንዲያያቸው መክሮአል። አዎ፣ ወንድሞች ከእህቶች ጋር በማይገባ ሁኔታ ከመቀራረብና ከመዳፈር ሲጠነቀቁ አክብሮት አሳዩአቸው ማለት ነው። ጳውሎስ በመቀጠል “በእውነት ባልቴት የሆኑትን ባልቴቶች አክብር” ሲል ጽፎአል። ችግረኛ መበለት ከምትከበርበት መንገዶች አንዱ ቁሳዊ እርዳታ መስጠት ነው። ይሁን እንጂ ለዚህ ዓይነቱ እርዳታ ብቁ እንድትሆን “መልካም ሥራ በማድረግ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል።” (1 ጢሞቴዎስ 5:2-10) ቁሳዊ ሥጦታ በመስጠት ረገድ ሉቃስ በሚሊጢን ደሴት ይኖር ስለነበሩ ሰዎች “በብዙ ክብርም ደግሞ አከበሩን፣ በተነሣንም ጊዜ በመርከብ ላይ የሚያስፈልገንን ነገር አኖሩልን” ሲል ጽፎአል። (ሥራ 28:10) ስለዚህ ቁሳዊ ሥጦታ በመስጠት አክብሮት መስጠት ይቻላል ማለት ነው።
15. (ሀ) አክብሮት እንድናሳይ የተለየ ኃላፊነት ያለብን ለማን ነው? (ለ) ለሚመሩን አክብሮት ከምናሳይባቸው መንገዶች አንዱ ምንድን ነው?
15 ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፈውን ደብዳቤ በመቀጠል “በመልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች፣ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙት፣ እጥፍ ክብር ይገባቸዋል” ብሎአል። (1 ጢሞቴዎስ 5:17)ሽማግሌዎችን ወይም የበላይ ተመልካቾችን በምን መንገድ ልናከብር እንችላለን? ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ” ብሎአል። (1 ቆሮንቶስ 11:1) ጳውሎስ እርሱን እንድንመስል የሰጠውን ምክር ከተከተልን እርሱን አከበርነው ማለት ነው። ይህ ሁኔታ በመካከላችን ሆነው ለሚመሩንም ይሠራል። አርዓያቸውን በመከተል እነርሱን ለመምሰል በጣርን መጠን ክብር ሰጠናቸው ማለት ነው።
16. ለሚመሩን ወንድሞች አክብሮት የምናሳይባቸው ሌሎች መንገዶች ምንድን ናቸው?
16 ለበላይ ተመልካቾች ክብር ከምናሳይባቸው መንገዶች አንዱ የሚከተለውን ምክር በሥራ ማዋል ነው። “ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ። እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፣ ይህንኑ በደስታ እንጂ በሐዘን እንዳያደርጉት።” (ዕብራውያን 13:17) ልጆች ወላጆቻቸውን በመታዘዝ እንደሚያከብሩአቸው ሁሉ በመካከላችን ሆነው የሚመሩንንም በመታዘዝና ለእነርሱም በመገዛት እንደምናከብራቸው እናሳያለን። በተጨማሪም ጳውሎስንና ባልንጀሮቹን ደጎቹ የሚሊጢን ደሴት ነዋሪዎች በቁሳዊ ሥጦታ እንዳከበሩአቸው ሁሉ የማኅበሩ ተጓዥ ወኪሎችም ብዙ ጊዜ ሥጦታ በመቀበል ተከብረዋል። ይሁን እንጂ ሥጦታ እንዲሰጣቸው መጠየቅ ወይም ቢሰጣቸው ደስ እንደሚላቸው መጠቆም ወይም ሥጦታ እንደሚያስፈልጋቸው መናገር አይገባቸውም።
17. የበላይ ተመልካችነት መብት ያላቸው ወንድሞች ክብር በመስጠት ረገድ ምን ግዴታ አለባቸው?
17 በሌላው በኩል ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ወይም በክልል ወይም በወረዳ ደረጃ ወይም በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮዎች ወይም በቤተሰብ ደረጃ፣ በአጠቃላይ በቲኦክራቲካዊው ድርጅት ውስጥ በማንኛውም የበላይ ተመልካችነት ደረጃ የሚያገለግሉ ሁሉ በሥራቸው ያሉትን የማክበር ግዴታ አለባቸው። ይህንንም ለማድረግ አዛኝነትና ራስን በሌላው ቦታ አድርጎ የመመልከት መንፈስ ያስፈልጋል። በማንኛውም ጊዜ ሊቀረቡ የሚችሉ፣ የዋሆች፣ በልባቸውና በአእምሮአቸው እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ትሁቶች መሆን ይገባቸዋል።—ማቴዎስ 11:29, 30
እርስ በርሳችሁ ለመከባበር ተጣጣሩ
18. (ሀ) ለሰዎች ሁሉ የሚገባቸውን አክብሮት እንዳንሰጥ ምን ነገር ሊያግደን ይችላል? (ለ) አፍራሽ ወይም ስህተት ፈላጊ ዝንባሌ ሊኖረን የማይገባው ለምንድን ነው?
18 ሁላችንም ብንሆን እርስ በርሳችን እንዳንከባበር የሚያግደን ኃይል ስላለ ለመከባበር ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። የሚያግደን ወይም የሚያደናቅፈን ኃይል ፍጹም ያልሆነው ልባችን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነው” ይላል። (ዘፍጥረት 8:21) ለሌሎች ተገቢ አክብሮት እንዳናሳይ እንቅፋት ከሚሆኑብን ነገሮች አንዱ አፍራሽና ስህተት ፈላጊ አስተሳሰብ መያዝ ነው። ሁላችንም የይሖዋ ምህረትና ጸጋ የሚያስፈልገን ደካማና ፍጹም ያልሆንን ሰዎች ነን። (ሮሜ 3:23, 24) ይህን በመገንዘብ የወንድሞቻችንን ደካማ ጎን ብቻ ከመመልከት ወይም ወንድሞቻችን ለሚያደርጉት ነገር መጥፎ ትርጉም ከመስጠት እንጠንቀቅ።
19. ማንኛውንም ዓይነት አፍራሽ ዝንባሌ እንድናሸንፍ የሚረዳን ምንድን ነው?
19 እንዲህ ላለው አፍራሽ አስተሳሰብ መድኃኒቱ ፍቅርና ራስን መግዛት ነው። ለወንድሞቻችን የአዛኝነት፣ የታማኝነትና መልካም የሆነውን የመመልከት ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል። ጥሩ ጠባያቸውን ማየት ይኖርብናል። ያልገባን ወይም ግልጽ ያልሆነልን ነገር ካለ ወንድሞቻችንን በመጥፎ ከመጠርጠር ይልቅ ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ ብለን ማሰብ ይኖርብናል። “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ” የሚለውን የጴጥሮስ ምክር እንከተል።(1 ጴጥሮስ 4:8) ለወንድሞቻችን የሚገባቸውን ክብር ለመስጠት ከፈለግን እንዲህ ዓይነት ፍቅር ሊኖረን ይገባል።
20, 21. (ሀ) እርስ በርሳችን እንዳንከባበር ዕንቅፋት የሚሆንብን ሌላው ዝንባሌ ምንድን ነው? (ለ) ይህንንስ ዝንባሌ እንድናሸንፍ የሚረዳን ምንድን ነው?
20 ለሌሎች አክብሮት እንዳናሳይ እንቅፋት ከሚሆኑብን ነገሮች ሌላው ደግሞ የሆደባሻነት ወይም ቶሎ የመጎዳት ጠባይ ወይም ጥቃቅን ነገሮችን የመከታተል መንፈስ ነው። ጥቃቅን ነገሮችን መከታተል አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ሠዓሊዎች ቀለማትን፣ ሙዚቀኞች ደግሞ ድምጾችን መከታተል የሞያቸው ክፍል ነው። ከሌሎች ጋር ባለን ግኑኝነት ረገድ በትንሹ የምንጎዳ፣ ጥቃቅን ነገሮችን የምንከታተል ወይም አትንኩኝ ባይ መሆን ግን ከራስ ወዳድነት የሚመጣ፣ ለግላችን ሰላም የሚያሳጣና ለሌሎች አክብሮት እንዳናሳይ የሚያግደን ጠባይ ነው።
21 በዚህ ረገድ ጥሩ ምክር የሚሆነን በመክብብ 7:9 ላይ ያለው ቃል ነው። “በነፍስህ ለቁጣ [ለመጎዳት(አዓት)] ችኩል አትሁን፣ ቁጣ [ቶሎ መጎዳት] በሰነፍ ብብት ያርፋልና።” ስለዚህ ለመቀየም ወይም ለመጎዳት መቸኮል ጥበብ፣ ምክንያታዊነትና ፍቅር እንደጎደለን ያሳያል። ሁላችንም ካልተጠነቀቅን አፍራሽ አስተሳሰብ በመያዝ ወይም ስህተት ፈላጊዎች በመሆን ቶሎ በመጎዳት ውዳቂው ዝንባሌያችን ለሚገባቸው ሁሉ ክብር እንዳንሰጥ እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል።
22. አክብሮት የመስጠት ግዴታችንን እንዴት ብለን ለማጠቃለል እንችላለን?
22 በእርግጥ ለሌሎች አክብሮት የምናሳይበት ብዙ ምክንያት አለን። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው አክብሮት የምናሳይባቸው ብዙ፣ ብዙ መንገዶች አሉ። በማንኛውም ጊዜ ተጠንቅቀን ካልተጠባበቅን የራስ ወዳድነት ወይም አፍራሽ የሆነ አስተሳሰብ ለሌሎች አክብሮት እንዳናሳይ እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። በተለይ በቤተሰብ ክልል ውስጥ፣ ባልና ሚስቶች አንዳቸው ለሌላው፣ ልጆች ለወላጆቻቸው አክብሮት ለማሳየት መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። በጉባኤ ውስጥ ደግሞ ለእምነት ባልደረቦቻችንና በተለይም በበላይ ተመልካችነት ቦታ ላይ ሆነው በመካከላችን ለሚደክሙት ወንድሞች አክብሮት የማሳየት ግዴታ አለብን። በእነዚህ መስኮች ሁሉ ተገቢውን ክብር መስጠታችን እኛኑ ይጠቅመናል። ኢየሱስ እንዳለው “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው።”—ሥራ 20:35
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የመንግሥት ባለሥልጣኖችን የምናከብረው ለምንና እንዴት ነው?
◻ በሠራተኛና በአሠሪ መካከል ስላለው ግንኙነት የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ልንሠራበት እንችላለን?
◻ በቤተሰብ ክልል ውስጥ አክብሮት ማሳየት የሚገባው እንዴት ነው?
◻ በጉባኤ ውስጥ እንዴት ያለ ልዩ አክብሮት ማሳየት ይገባል? ለምንስ?
◻ ሌሎችን በማክበር ረገድ የሚያጋጥመውን ሰብዓዊ ድካም እንዴት ማሸነፍ ይቻላል?