ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር መማር
ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በላከው የማበረታቻ ደብዳቤ ላይ “በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ያለኝ ይበቃኛል ማለትን፣ . . . ብጠግብም ሆነ ብራብም፣ ባገኝም ሆነ ባጣ በማንኛውም ሆነ በየትኛውም ሁኔታ ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር ተምሬያለሁ” በማለት ጽፏል።—ፊልጵስዩስ 4:11, 12 አ.መ.ት
ጳውሎስ ያለኝ ይበቃኛል እንዲል ያስቻለው ምስጢር ምንድን ነው? በጊዜያችን ካለው የኑሮ ውድነትና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት አንጻር ሲታይ እውነተኛ ክርስቲያኖች ለአምላክ በሚያቀርቡት አገልግሎት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዲችሉ ያለኝ ይበቃኛል ማለትን መማራቸው እንደሚጠቅማቸው ምንም ጥርጥር የለውም።
ጳውሎስ ያለኝ ይበቃኛል የሚለውን ሐሳብ ከመጥቀሱ በፊት ቀደም ሲል በተለያየ መስክ ያገኘውን ስኬት ገልጿል። “ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት እንዳለው ቢመስለው፣ እኔ እበልጠዋለሁ። በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፣ ከእስራኤል ትውልድ፣ ከብንያም ወገን፣ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፣ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፣ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፣ ያለ ነቀፋ ነበርሁ።” (ፊልጵስዩስ 3:4-6) ከዚህም በላይ ጳውሎስ ቀናተኛ የአይሁድ እምነት ተከታይ በመሆኑ በኢየሩሳሌም ከነበሩት የካህናት አለቆች የተቀበለው ተልዕኮና የእነርሱ ድጋፍ ነበረው። ይህ ሁሉ ጳውሎስ በአይሁድ ሥርዓት ውስጥ በፖለቲካም ሆነ በሃይማኖት መስክ ሥልጣንና ክብር እንዲሁም ቁሳዊ ብልጽግና ሊያገኝ ይችል እንደነበር ያሳያል።—ሥራ 26:10, 12
ሆኖም ጳውሎስ ቀናተኛ ክርስቲያን አገልጋይ ከሆነ በኋላ በሕይወቱ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ አደረገ። ለምስራቹ ሲል ጥሩ ሥራውን እንዲሁም በፊት ትልቅ ግምት የሚሰጠውን ማንኛውንም ነገር በገዛ ፈቃዱ እርግፍ አድርጎ ተወው። (ፊልጵስዩስ 3:7, 8) ታዲያ ጳውሎስ በምን ሊተዳደር ነው? አገልጋይ በመሆኑ ደመወዝ ይከፈለው ይሆን? የሚያስፈልጉት ነገሮች ሊሟሉለት የሚችሉት እንዴት ነው?
ጳውሎስ አገልግሎቱን ያከናወነው ያለ ምንም ክፍያ ነው። ምሥራቹን በሚሰብክላቸው ሰዎች ላይ ሸክም ላለመሆን ሲል በቆሮንቶስ እያለ ከአቂላና ከጵርስቅላ ጋር ድንኳን ይሰፋ ነበር፤ ከዚህም ሌላ ራሱን ለመቻል ሌሎች ሥራዎችም ሠርቷል። (ሥራ 18:1-3፤ 1 ተሰሎንቄ 2:9፤ 2 ተሰሎንቄ 3:8-10) ጳውሎስ ረጅም ርቀት የሚሸፍኑ ሦስት ሚስዮናዊ ጉዞዎች ያደረገ ከመሆኑም በላይ እርዳታ ወደሚያስፈልጋቸው ጉባኤዎችም ተጉዟል። ለአምላክ በሚያቀርበው አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተጠምዶ ስለነበር ብዙም ቁሳዊ ንብረት አልነበረውም። አብዛኛውን ጊዜ ወንድሞች የሚያስፈልገውን ነገር ያሟሉለት ነበር። አንዳንድ ጊዜ ግን ካጋጠሙት መጥፎ ሁኔታዎች የተነሳ ለችግርና ለእጦት ተዳርጓል። (2 ቆሮንቶስ 11:27፤ ፊልጵስዩስ 4:15-18) ያም ሆኖ ጳውሎስ በደረሰበት መከራ ፈጽሞ አላማረረም እንዲሁም የሌሎች ሃብት ምቀኝነት አላሳደረበትም። ክርስቲያን ባልንጀሮቹን ለመጥቀም ሲል ትጋት በተሞላበት ሁኔታ በፈቃደኝነትና በደስታ አገልግሏል። እንዲያውም በሰፊው የሚታወቀውን “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” የሚለውን የኢየሱስን አባባል ጠቅሶ የተናገረው ጳውሎስ ነው። ይህ ለሁላችንም የሚጠቅም እንዴት ያለ የላቀ ምሳሌ ነው!—ሥራ 20:33-35
ያለኝ ይበቃኛል ሲባል ምን ማለት ነው?
ለጳውሎስ ደስታና እርካታ አስተዋጽኦ ያበረከተው ዋነኛው ነገር ያለኝ ይበቃኛል የሚለው አስተሳሰብ ነው። ይሁን እንጂ ያለኝ ይበቃኛል ሲባል ምን ማለት ነው? በቀላል አማርኛ መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች ረክቶ መኖር ማለት ነው። ጳውሎስ ይህንን አስመልክቶ የአገልግሎት ጓደኛው ለነበረው ለጢሞቴዎስ እንዲህ ብሎታል:- “ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፣ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል።”—1 ጢሞቴዎስ 6:6-8
ጳውሎስ ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ባሕርይ ለአምላክ ያደሩ ከመሆን ጋር አያይዞ እንደገለጸው ልብ በል። እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ለአምላክ በማደር ማለትም ለአምላክ የምናቀርበውን አገልግሎት በአንደኛ ደረጃ በማስቀመጥ እንጂ ንብረት ወይም ሃብት በማካበት አለመሆኑን ተገንዝቧል። “ምግብና ልብስ” ማግኘቱ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ እንዲከታተል ከመርዳት ያለፈ ቦታ የላቸውም። በመሆኑም ጳውሎስ ያለኝ ይበቃኛል እንዲል ያስቻለው ምስጢር በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆን በይሖዋ መታመኑ ነበር።
ዛሬ ያሉ ብዙ ሰዎች አንድም ይህን ምስጢር ባለማወቃቸው አሊያም ችላ በማለታቸው ምክንያት ለብዙ ጭንቀትና ሐዘን ተዳርገዋል። ያለኝ ይበቃኛል የሚል ባሕርይ ከማዳበር ይልቅ ትምክህታቸውን በገንዘብና ገንዘብ ሊገዛው በሚችለው ነገር ላይ ይጥላሉ። የማስታወቂያው ኢንዱስትሪና መገናኛ ብዙኃን ሰዎች ዘመናዊ የሆኑ እንዲሁም በጣም ምርጥ የሚባሉ ምርቶችና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ከሌሏቸው ደስተኛ ሊሆኑ እንደማይችሉ እንዲሰማቸው ያደርጋሉ። ከዚህም የተነሳ ብዙዎች ገንዘብንና ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ ወጥመድ ይያዛሉ። ደስታና እርካታ ከማግኘት ይልቅ “በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ።”—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10
ይህን ምስጢር የተማሩ ሰዎች
ዛሬስ ለአምላክ በማደርና ያለኝ ይበቃኛል በማለት ደስታና እርካታ አግኝቶ መኖር በእርግጥ የሚቻል ነገር ነው? አዎን፣ ይቻላል። እንዲያውም ዛሬ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደዚህ እያደረጉ ነው። ባላቸው ነገር ረክቶ የመኖርን ምስጢር ተምረዋል። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው ፈቃዱን የሚያደርጉትና በየትኛውም ቦታ የሚገኙ ሰዎችን ስለ ዓላማው የሚያስተምሩት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።
ሚስዮናዊ ለመሆን ከሠለጠኑ በኋላ ወደማያውቁት አገር በመሄድ የአምላክን መንግሥት ምስራች ለመስበክ ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀረቡትን ሰዎች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። (ማቴዎስ 24:14) ብዙውን ጊዜ በሚመደቡበት አገር ውስጥ ያለው የኑሮ ሁኔታ እነርሱ ይኖሩበት እንደነበረው አገር በሥልጣኔ ያደገ አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ በ1947 መጀመሪያ ላይ ሚስዮናውያን በተመደቡበት አንድ የእስያ አገር ሲደርሱ ጦርነት ያስከተለው ችግር እንዳለ የነበረ ሲሆን የኤሌክትሪክ መብራት የሚያገኙ ቤቶችም ጥቂት ነበሩ። ሚስዮናውያኑ በብዙ አገሮች ውስጥ ልብስ የሚታጠበው በኤሌክትሪክ በሚሠራ ማሽን ሳይሆን በሳፋ ወይም ወንዝ ዳር ድንጋይ ላይ መሆኑን ተገንዝበዋል። ሆኖም ወደዚያ የሄዱት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች ለማስተማር ስለሆነ ራሳቸውን ከሁኔታዎቹ ጋር አስማምተው አገልግሎታቸውን በትጋት ማከናወን ቀጥለዋል።
ሌሎች ደግሞ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተሰማርተዋል ወይም ምስራቹ ገና ወዳልተሰበከባቸው አካባቢዎች ተዛውረዋል። አዱልፎ በተለያዩ የሜክሲኮ ግዛቶች ውስጥ ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሠርቷል። እንዲህ ይላል:- “እኔና ባለቤቴ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ ራሳችንን ከሚያጋጥሙን ሁኔታዎች ጋር ማስማማትን ተምረናል። ለምሳሌ ያህል፣ ከጐበኘናቸው ጉባኤዎች መካከል አንዱ ከየትኛውም ከተማ ሆነ የገበያ ቦታ በጣም የራቀ ነበር። ወንድሞች በቁርስም ሆነ በምሳ እንዲሁም በእራት ሰዓት የሚመገቡት አንድ ቂጣ፣ ትንሽ የአሳማ ቅቤና ጨው ከአንድ ኩባያ ቡና ጋር ነበር። ሆኖም በዚህ ረክተው ይኖራሉ። እኛም እንደ ወንድሞቻችን መኖር ለመድን። ይሖዋን በሙሉ ጊዜ ባገለገልኩባቸው 54 ዓመታት ውስጥ ይህን የመሰሉ በርካታ ተሞክሮዎች አጋጥመውኛል።”
ፍሎሬንቲኖ ከቤተሰቡ ጋር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመላመድ የተገደዱበትን አጋጣሚ ያስታውሳል። በልጅነቱ ስላሳለፈው ጊዜ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “አባቴ ሃብታም ነጋዴ ነበረ። ብዙ መሬትም ነበረው። በግሮሰሪያችን ውስጥ የነበረው የገንዘብ መቀበያ ማሽን እስካሁን ድረስ ትዝ ይለኛል። በግምት 50 ሴንቲ ሜትር ስፋትና ወደታች ደግሞ 20 ሴንቲ ሜትር ርዝመት እንዲሁም አራት ክፍሎች ያሉት መሳቢያ ነበረው። በቀን ውስጥ የምናገኘውን ገቢ የምናስቀምጠው እዚያ ውስጥ ነበር። ሁልጊዜ ማታ ማታ መሳቢያው በገንዘብ ይታጨቅ ነበር።
“ከዚያም በድንገት የኢኮኖሚ ቀውስ አጋጠመንና ለድህነት ተዳረግን። ከመኖሪያ ቤታችን በስተቀር የነበረንን ሁሉ አጣን። ይባስ ብሎም አንደኛው ወንድሜ በደረሰበት አደጋ ሁለት እግሩ ሽባ ሆነ። ሕይወታችን እንደ ድሮው ሊሆን አልቻለም። ለተወሰነ ጊዜ ፍራፍሬና ሥጋ እሸጥ ነበር። በተጨማሪም በጥጥ ለቀማ፣ ወይንና አልፋልፋ በመሰብሰብ እንዲሁም የእርሻ ቦታዎችን በመስኖ በማልማት ሥራ ተሰማርቼ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ሁለገብ እንደሆንኩ ይናገራሉ። እናቴ ብዙ ሰዎች ያላገኙት መንፈሳዊ ሃብት እንዳለን ይኸውም እውነትን እንደምናውቅ በመናገር ብዙ ጊዜ ታጽናናን ነበር። ምቾትን እንዲሁም መቸገርንና ማጣትን አይቻለሁ። ይሖዋን በሙሉ ጊዜ በማገልገል ወደ 25 ዓመታት ገደማ ያሳለፍኩ ሲሆን ከሁሉ የተሻለውን የሕይወት ጎዳና እንደመረጥኩ ይሰማኛል። በመሆኑም ሁልጊዜ ደስተኛ ነኝ ማለት እችላለሁ።”
መጽሐፍ ቅዱስ “የዚች ዓለም መልክ አላፊ” እንደሆነ አበክሮ ይገልጻል። በዚህም ምክንያት “ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፣ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፣ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ” በማለት አጥብቆ ያሳስበናል።—1 ቆሮንቶስ 7:29-31
እንግዲያው አኗኗርህን በጥሞና የምትመረምርበት ጊዜ አሁን ነው። ኑሮ የሚከብድህ ከሆነ በሁኔታው ላለመበሳጨት ብሎም የምሬትና የምቀኝነት ስሜት እንዳያድርብህ ጥንቃቄ አድርግ። በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ያህል ቁሳዊ ሃብት ቢኖርህ በሕይወትህ ውስጥ ጌታ እንዳይሆንብህ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝህ የጥበብ አካሄድ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሰጠው ማሳሰቢያ መሠረት “ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት” ተስፋ አታድርግ። እንደዚህ ካደረግህ አንተም ብትሆን ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር ተምሬያለሁ ብለህ መናገር ትችላለህ።—1 ጢሞቴዎስ 6:17-19
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ በሌሎች ላይ ሸክም ላለመሆን በገዛ እጆቹ ሠርቷል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ‘ለአምላክ በማደራቸውና ያለኝ ይበቃኛል በማለታቸው’ ደስታ አግኝተዋል