“ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነው”
“ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ።”—ማቴዎስ 11:29
1, 2. (ሀ) በሕይወት ውስጥ ዕረፍት የሚሰጥ ምን ነገር አጋጥሞህ ያውቃል? (ለ) አንድ ሰው ኢየሱስ ቃል የገባውን ዕረፍት ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርበታል?
ቀኑ ሞቃት እና በጣም የሚወብቅ ሆኖ ከዋለ በኋላ አመሻሹ ላይ በቀዝቃዛ ውኃ መታጠብ ወይም ደግሞ ረጅምና አድካሚ ጉዞ ካደረጉ በኋላ ጥሩ እንቅልፍ መተኛት እንዴት ያለ ሰውነትን የሚያድስ ነገር ነው! ከባድ ሸክም ከትከሻ ላይ ሲወርድ ወይም ኃጢአትና መተላለፍ ይቅር ሲባልም እንደዚሁ ነው። (ምሳሌ 25:25፤ ሥራ 3:19) እንደነዚህ ያሉ አስደሳች ተሞክሮዎች የሚያመጡልን ዕረፍት ጉልበታችንን የሚያድስ ከመሆኑም በላይ የበለጠ ለመሥራት የሚያስችል ኃይል ያስገኝልናል።
2 ሸክማቸው እንደከበዳቸውና እንደ ደከሙ የሚሰማቸው ሰዎች ሁሉ ኢየሱስ ይህን ዕረፍት እንደሚያገኙ ቃል ስለገባላቸው ወደ እርሱ ሊመጡ ይችላሉ። ሆኖም በጣም አስፈላጊ የሆነውን ይህን ዕረፍት ለማግኘት አንድ ሰው ማድረግ ያለበት ነገር አለ። ኢየሱስ “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ . . . ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” ብሏል። (ማቴዎስ 11:29) ይህ ቀንበር ምንድን ነው? ዕረፍት የሚያስገኘውስ እንዴት ነው?
ልዝብ ቀንበር
3. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይሠራባቸው የነበሩት ምን ዓይነት ቀንበሮች ነበሩ? (ለ) ቀንበር ምን ምሳሌያዊ ትርጉም አለው?
3 ኢየሱስና አድማጮቹ የግብርና ሥራ በተስፋፋበት ኅብረተሰብ ውስጥ ይኖሩ ስለ ነበር ቀንበር ምን እንደሆነ አሳምረው ያውቃሉ። በመሠረቱ ቀንበር ከግራና ከቀኝ ባሉ ሁለት ማነቆዎች አማካኝነት ጥንድ እንስሳት አብዛኛውን ጊዜም በሬዎች ማረሻ፣ ጋሪ ወይም ሌላ ነገር እንዲጎትቱ አንድ ላይ የሚጠመዱበት ረጅም እንጨት ነው። (1 ሳሙኤል 6:7) ሰዎችም ቀንበር ይሸከሙ ነበር። ሰዎች የሚሸከሟቸው ቀንበሮች በሁለቱም ጫፎች ዕቃ ተንጠልጥሎባቸው በትከሻቸው ላይ የሚያደርጓቸው እንጨቶች ነበሩ። የቀን ሙያተኞች በእነዚህ ቀንበሮች አማካኝነት ከባድ ሸክሞችን መሸከም ይችሉ ነበር። (ኤርምያስ 27:2፤ 28:10, 13) ቀንበር ከሸክምና ከከባድ ሥራ ጋር ስለ ተያያዘ ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መግዛትንና መጨቆንን ለማመልከት በምሳሌያዊ መንገድ ይሠራበታል።—ዘዳግም 28:48፤ 1 ነገሥት 12:4፤ ሥራ 15:10
4. ኢየሱስ ወደ እርሱ ለሚመጡ ሰዎች በሚሰጣቸው ቀንበር የተመሰለው ምንድን ነው?
4 ታዲያ ኢየሱስ ዕረፍት ለማግኘት ወደ እርሱ እንዲመጡ የጋበዛቸው ሰዎች የሚሸከሙት ቀንበር ምንድን ነው? ኢየሱስ “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ” እንዳለ አስታውስ። (ማቴዎስ 11:29) የሚማር ሰው ደግሞ ደቀ መዝሙር ነው። ስለዚህ በቀላል አነጋገር የኢየሱስን ቀንበር መሸከም ማለት የእርሱ ደቀ መዝሙር መሆን ማለት ነው። (ፈልጵስዩስ 4:3) ሆኖም ይህ የኢየሱስ ትምህርቶችን ከማወቅ የበለጠ ነገርን ይጠይቃል። ከትምህርቶቹ ጋር የሚስማሙ ነገሮችን ማድረግ ማለትም እርሱ የሠራውን ሥራ መሥራትንና አኗኗሩን መከተልን ይጨምራል። (1 ቆሮንቶስ 11:1፤ 1 ጴጥሮስ 2:21) ለሥልጣኑና በውክልና ሥልጣን ለሰጣቸው ሰዎች በፈቃደኝነት መገዛትን ይጠይቃል። (ኤፌሶን 5:21፤ ዕብራውያን 13:17) ይህ ማለት ራሱን የወሰነ የተጠመቀ ክርስቲያን ሆኖ ከዚህ ዓይነቱ ውስንነት ጋር የሚመጡትን መብቶችና ኃላፊነቶች መቀበል ማለት ነው። ኢየሱስ መጽናናትና ዕረፍት ለማግኘት ወደ እርሱ ለሚመጡ ሰዎች ሁሉ እንደሚሰጣቸው ቃል የገባላቸው ቀንበር ይህ ነው። ይህን ቀንበር ለመሸከም ፈቃደኛ ነህን?—ዮሐንስ 8:31, 32
5. የኢየሱስን ቀንበር መሸከም የማይጎዳው ለምንድን ነው?
5 ቀንበር ተሸክሞ ዕረፍት ማግኘት የሚለው ሐሳብ እርስ በርሱ አይቃረንምን? በፍጹም አይቃረንም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ቀንበሩ “ልዝብ” እንደሆነ ተናግሯል። ቃሉ ለስላሳ፣ ደስ የሚል፣ ተስማሚ የሚል ትርጉም አለው። (ማቴዎስ 11:30፤ ሉቃስ 5:39፤ ሮሜ 2:4፤ 1 ጴጥሮስ 2:3) ኢየሱስ የአናጺነት ሙያ የነበረው እንደመሆኑ መጠን ሞፈሮችንና ቀንበሮችን ሳይሠራ አይቀርም፤ በተጨማሪም አብዛኛውን ሥራ በሚያመች መንገድ ለመሥራት የሚያስችል ቀንበር እንዴት መበጀት እንዳለበት ያውቅ ነበር። ቀንበሮቹን ጨርቅ ጠምጥሞባቸው ወይም ቆዳ አድርጎባቸው ሊሆን ይችላል። ብዙዎች የእንስሳውን አንገት እንዳያቆስል ወይም እንዳይልጥ ብለው ቀንበሩን በዚህ መንገድ ይሠሩት ነበር። በተመሳሳይም ኢየሱስ እንድንሸከመው የጋበዘን ምሳሌያዊ ቀንበር “ልዝብ” ነው። ደቀ መዝሙሩ መሆን አንዳንድ ግዴታዎችንና ኃላፊነቶችን መወጣት የሚጠይቅ ቢሆንም ዕረፍት የሚሰጥ እንጂ የሚጎዳ ወይም የሚጨቁን ነገር አይደለም። የሰማያዊ አባቱ የይሖዋ አምላክ ትእዛዛትም ቢሆኑ ከባዶች አይደሉም።—ዘዳግም 30:11፤ 1 ዮሐንስ 5:3
6. ኢየሱስ “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ” ያለው ምን ለማለት ፈልጎ ሊሆን ይችላል?
6 የኢየሱስን ቀንበር “ልዝብ” እንዲሆን ወይም ለመሸከም እንዲቀል የሚያደርገው ሌላም ነገር አለ። ኢየሱስ “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ” ሲል ከሚከተሉት ሁለት ነገሮች አንዱን ማለቱ ሊሆን ይችላል። ሁለት እንስሳት አንድ ላይ ተጠምደው ሸክም የሚጎትቱበትን ቀንበር በአእምሮው ይዞ ከሆነ አብረነው በአንድ ቀንበር ሥር እንድንገባ መጋበዙ ነው። ኢየሱስ ከጎናችን ሆኖ አብሮን ሸክማችንን ሲጎትት እንዴት ያለ በረከት ይሆናል! በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ በአእምሮው የያዘው ተራ የቀን ሙያተኛ የሚጠቀምበትን ቀጥ ያለ ቀንበር ከሆነ ማናቸውንም ሸክም በቀላሉ ወይም አመቺ በሆነ መንገድ መሸከም የምንችልበትን ዘዴ ይጠቁመናል። “እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና” የሚል ማረጋገጫ ስለሰጠን በሁለቱም መንገድ ቢሆን ቀንበሩ የእውነተኛ ዕረፍት ምንጭ ነው።
7, 8. አንዳንዶች ሲጨነቁ ምን ስሕተት ይሠራሉ?
7 ታዲያ የተሸከምናቸውን የኑሮ ችግሮች ልንሸከማቸው እንደማንችላቸው ከተሰማንና ከመጠን በላይ ከተጨነቅን ምን ማድረግ ይኖርብናል? አንዳንዶች ዕለታዊ ኑሮ ሸክም ሆኖባቸው ሳለ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር የመሆን ቀንበር በጣም ከባድ ወይም ከአቅም በላይ እንደሆነ አድርገው በተሳሳተ መንገድ ሊረዱት ይችላሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦች እፎይታ እናገኝ ይሆናል ብለው በማሰብ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ያቆማሉ ወይም በአገልግሎት ከመሳተፍ ይታቀባሉ። ሆኖም ይህ ከባድ ስሕተት ነው።
8 ኢየሱስ የሰጠን ቀንበር “ልዝብ” እንደሆነ እንገነዘባለን። ቀንበሩን በትክክል ካልተሸከምነው ሊያቆስለን ይችላል። ስለዚህ በትከሻችን ላይ የተሸከምነውን ቀንበር በጥንቃቄ መመርመር ያስፈልገናል። በአንድ ምክንያት ያልተጠገነ ወይም ተስተካክሎ ያልተገጠመ ከሆነ ቀንበሩን መጠቀም በበኩላችን ብዙ ጥረት እንድናደርግ የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ ሁኔታው ሥቃይ ያስከትልብናል። በሌላ አነጋገር ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎቻችን ሸክም እንደሆኑብን ከተሰማን በትክክል የተሸከምናቸው መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብናል ማለት ነው። አንድን ሥራ እንድንሠራ የሚገፋፋን ነገር ምንድን ነው? ወደ ስብሰባዎች የምንሄደው ተገቢውን ዝግጅት አድርገን ነውን? በመስክ አገልግሎት የምንሳተፈው በአካል እና በአእምሮ ዝግጁ ሆነን ነውን? በጉባኤ ውስጥ ካሉ ሌሎች ሰዎች ጋር ጤናማና የተቀራረበ ዝምድና አለንን? ከሁሉም በላይ ደግሞ ከይሖዋ አምላክና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለን የግል ዝምድና እንዴት ነው?
9. የክርስትና ቀንበር ልንሸከመው ከምንችለው በላይ የሆነ ሸክም ሊሆንብን የማይገባው ለምንድን ነው?
9 ኢየሱስ የሰጠንን ቀንበር በሙሉ ልባችን ስንቀበልና በተገቢው መንገድ መሸከምን ስንማር ቀንበሩን መሸከም እንደማንችል ሆኖ እንዲሰማን የሚያደርግ አንዳችም ምክንያት አናገኝም። እንዲያውም ከኢየሱስ ጋር በአንድ ቀንበር ሥር መሆንን በዓይነ ሕሊናችን ከተመለከትነው የሸክሙን አብዛኛውን ክፍል ማን እንደተሸከመ ለመረዳት አያስቸግረንም። ሁኔታው ወላጁ እየገፋለት ሳለ ራሱ የሚነዳ የሚመስለው አንድ ትንሽ ልጅ በሕፃናት ጋሪ ላይ ተቀምጦ ከጎንና ከጎኑ ያለውን ብረት ከመጨበጡ ጋር ይመሳሰላል። ይሖዋ አምላክ አፍቃሪ አባት እንደመሆኑ መጠን አቅማችንና ድክመቶቻችንን ጠንቅቆ ያውቃል፤ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነትም የሚያስፈልጉንን ነገሮች ያሟላልናል። ጳውሎስ “[አምላክ] እንደ ባለጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል” ብሏል።—ፈልጵስዩስ 4:19፤ ከኢሳይያስ 65:24 ጋር አወዳድር።
10. ደቀ መዝሙርነትን በቁም ነገር የምትመለከት አንዲት ሴት ምን ተሞክሮ አግኝታለች?
10 አያሌ ክርስቲያኖች ይህን ሁኔታ ከግል ተሞክሯቸው ተረድተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ጄኒ በየወሩ ረዳት አቅኚ ሆና ማገልገሏና ውጥረት የተሞላበት ዓለማዊ ሥራዋን ሙሉ ቀን መሥራቷ ከፍተኛ ጭንቀት አስከትሎባታል። ይሁን እንጂ ሚዛኗን እንድትጠብቅ የረዳት የአቅኚነት ሥራ እንደሆነ ይሰማታል። ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ መርዳቷና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲሉ ሕይወታቸውን ሲለውጡ ማየቷ በሥራ በተጠመደ ሕይወቷ ውስጥ የላቀ ደስታ እንድታገኝ ረድቷታል። “የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፣ ኀዘንንም ከእርሷ ጋር አይጨምርም” ከሚሉት የምሳሌ ቃላት ጋር ሙሉ በሙሉ ትስማማለች።—ምሳሌ 10:22
ቀላል ሸክም
11, 12. ኢየሱስ ‘ሸክሜ ቀላል ነው’ ሲል ምን ማለቱ ነበር?
11 ኢየሱስ ቀንበሩ “ልዝብ” እንደሆነ ቃል ከመግባቱም በተጨማሪ “ሸክሜ ቀሊል ነውና” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። ቀንበሩ “ልዝብ” መሆኑ ሥራውን ቀላል አድርጎታል፤ ሸክሙ ቀላል ከሆነ ደግሞ ሥራው በእርግጥም አስደሳች ነው ማለት ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህን ሲናገር በአእምሮው ይዞት የነበረው ነገር ምንድን ነው?
12 አንድ ገበሬ ለከብቶቹ ሥራ ለመለወጥ ሲፈልግ ምን እንደሚያደርግ አስብ፤ ሥራቸውን ከእርሻ ሥራ ወደ ጋሪ መጎተት ለመለወጥ ፈለገ እንበል። በመጀመሪያ ሞፈሩን ይፈታና ጋሪውን ያስራል። ጋሪውንና ማረሻውን ከብቶቹ በአንድ ላይ እንዲጎትቱት ማድረግ ቂልነት ይሆንበታል። በተመሳሳይም ኢየሱስ ሰዎች ቀደም ሲል በተሸከሙት ላይ ደርበው ሌላ ሸክም እንዲሸከሙ አላዘዘም። ለደቀ መዛሙርቱም “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ባሪያ ማንም የለም” ብሏቸው ነበር። (ሉቃስ 16:13) ስለዚህ ኢየሱስ ለሰዎች ምርጫ እያቀረበላቸው ነበር። ቀደም ሲል ተሸክመውት የነበረውን ከባድ ሸክም መሸከማቸውን ይቀጥላሉ ወይስ እሱን አውርደው ያቀረበላቸውን ግብዣ ይቀበላሉ? ኢየሱስ ‘ሸክሜ ቀላል ነው’ በማለት ፍቅራዊ ማበረታቻ ሰጣቸው።
13. በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ሰዎች ይሸከሙ የነበሩት ሸክም ምንድን ነው? ይህስ ምን ውጤት አስከትሎባቸዋል?
13 በኢየሱስ ዘመን ሕዝቡ ጨቋኝ የሮም ገዢዎችና ወግ አጥባቂና ግብዞች የሆኑት የሃይማኖት መሪዎች ከጫኑባቸው ከባድ ሸክሞች ጋር እየታገሉ ነበር። (ማቴዎስ 23:23) አንዳንዶች ከሮማውያን የአገዛዝ ቀንበር ለመላቀቅ ሲሉ በግላቸው ለውጦችን ለማምጣት ጥረዋል። መጨረሻ ላይ አስከፊ ውጤት ባስከተሉባቸው የፖለቲካ ትግሎች ውስጥ ተጠላልፈው ነበር። (ሥራ 5:36, 37) ሌሎች ደግሞ ያሉበትን ሁኔታ ለማሻሻል ሲሉ ቁሳዊ ነገሮችን ለማካበት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጀመሩ። (ማቴዎስ 19:21, 22፤ ሉቃስ 14:18–20) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲሆኑ በመጋበዝ እፎይታ የሚያገኙበትን መንገድ ሲጠቁማቸው ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጁት ሁሉም አልነበሩም። የተሸከሙት ሸክም ከባድ ቢሆንም እንኳ እሱን አውርደው የኢየሱስን ሸክም ለመሸከም ያመነቱ ነበር። (ሉቃስ 9:59–62) እንዴት ያለ ከባድ ስሕተት ነው!
14. የኑሮ ጭንቀቶችና ሥጋዊ ምኞቶች ሸክማችንን ሊያከብዱብን የሚችሉት እንዴት ነው?
14 ጥንቃቄ ካላደረግን በአሁኑ ወቅትም ቢሆን ተመሳሳይ ስሕተት ልንሠራ እንችላለን። የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናችን ዓለማውያን የሚከተሏቸውን ግቦችና የሥነ ምግባር ደረጃዎች ለመከተል ከመጣር ነጻ ያደርገናል። ለዕለት ተለት ኑሮ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማግኘት ጠንክረን መሥራት ቢኖርብንም በሕይወታችን ውስጥ ለእነዚህ ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት አንሰጥም። ሆኖም የኑሮ ጭንቀቶችና የቁሳዊ ምቾት ማራኪነት ሐሳባችንን ሊሰርቅብን ይችላል። ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ ምኞቶች ቦታ ከሰጠናቸው በጉጉት የተቀበልነውን እውነት ሊያንቁት ይችላሉ። (ማቴዎስ 13:22) እንደነዚህ ያሉ ምኞቶችን ለማሳካት ከመጠን በላይ ከመጨነቃችን የተነሣ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻችን ቶሎ ሠርተን መገላገል የምንፈልጋቸው አሰልቺ ግዴታዎች ይሆኑብናል። አምላክን የምናገለግለው ይህንን ዓይነት መንፈስ ይዘን ከሆነ ከአገልግሎታችን ዕረፍት ለማግኘት መጠበቅ እንደማንችል የተረጋገጠ ነው።
15. ኢየሱስ ሥጋዊ ምኞቶችን በተመለከተ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል?
15 ኢየሱስ እርካታ የተሞላበት ሕይወት የሚገኘው በሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በመመርመር እንጂ የራሳችንን ፍላጎት ለማሟላት በመጣር እንዳልሆነ ጠቁሟል። “ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፣ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን?” በማለት አጥብቆ መከረ። ከዚያም በሰማይ ወፎች ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ “አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፣ የሰማዩ አባታቸሁም ይመግባቸዋል” አለ። የሜዳ አበቦችን ጠቅሶም “አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም” ሲል ተናግሯል።—ማቴዎስ 6:25–29
16. ከዚህ በፊት ያጋጠሙ ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት ቁሳዊ ነገሮችን ማሳደድ ምን ውጤቶችን ያስከትላል?
16 ከእነዚህ በሚታዩ ነገሮች ከተሰጡ ቀላል ምሳሌዎች መማር የምንችለው ነገር አለን? አንድ ሰው ኢኮኖሚውን ለማሻሻል ብዙ በጣረ መጠን ዓለማዊ ነገሮችን በማሳደድ ረገድ በይበልጥ መጠመዱና በትከሻው ላይ ያለው ሸክም ይበልጥ እየከበደ መምጣቱ የተለመደ ነው። ቁሳዊ ነገሮችን ለማካበት ሲሯሯጡ ቤተሰቦቻቸው የተበታተኑባቸው፣ ጋብቻቸው የፈረሰባቸው፣ ጤናቸው የተቃወሰባቸውና ሌሎች ከዚህ የባሱ ችግሮች ያጋጠሟቸው ቱጃሮች በዓለም ውስጥ ሞልተዋል። (ሉቃስ 9:25፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ የሆኑት ሎሬት አልበርት አንስታይን በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፦ “ሀብትን፣ በሥጋዊ ነገሮች ረገድ የሚገኝ ስኬትን፣ ታዋቂነትንና ቅንጦትን ምን ጊዜም ቢሆን እንቃቸዋለሁ። ሁሉም ሰው ቀላልና ልከኛ የሆነ ኑሮ ቢኖር የተሻለ እንደሆነ አምናለሁ።” ይህ “ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል [ለአምላክ ያደሩ መሆን አዓት] እጅግ ማትረፊያ ነው” የሚለውን የጳውሎስን ቀላል ምክር የሚያስተጋባ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 6:6
17. መጽሐፍ ቅዱስ ምን ዓይነት ሕይወት እንዲኖረን ያበረታታል?
17 ቸል ልንለው የማይገባ አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር አለ። “ቀላልና ልከኛ የሆነ ኑሮ” ብዙ ጥቅሞች ቢኖሩትም ቀላል ኑሮ መኖር ብቻውን እርካታ አያመጣም። በአንዳንድ ሁኔታዎች አስገዳጅነት ምክንያት ቀላል ኑሮ የሚኖሩ አያሌ ሰዎች አሉ፤ ሆኖም እነዚህ ሰዎች እርካታም ሆነ ደስታ የላቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ በቁሳዊ ነገሮች መደሰትን አያወግዝም ወይም ደግሞ ባሕታዊ እንድንሆን አይመክረንም። እዚህ ላይ ለማጉላት የተፈለገው ያለኝ ይበቃኛል የሚለውን አመለካከት ሳይሆን ለአምላክ ያደሩ መሆንን ነው። “እጅግ ማትረፊያ” የሚሆነው ሁለቱን አንድ ላይ አጣምረን ስንይዛቸው ብቻ ነው። ይህ የሚያስገኘው ጥቅም ምንድን ነው? በተጨማሪም በዚሁ ደብዳቤ ላይ ‘በሚያልፍ ባለጠግነት ሳይሆን በሕያው እግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉ’ ሰዎች ‘እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ እንዳሉ’ ጳውሎስ ጠቁሟል።—1 ጢሞቴዎስ 6:17–19
18. (ሀ) አንድ ሰው እውነተኛ ዕረፍት ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ማድረግ የሚገቡንን ለውጦች መመልከት ያለብን እንዴት ነው?
18 ዕረፍት የምናገኘው በግላችን የተሸከምነውን ከባድ ሸክም አውርደን ኢየሱስ የሚሰጠንን ቀላል ሸክም መሸከምን ከተማርን ነው። በመንግሥቱ አገልግሎት ይበልጥ በተሟላ መልኩ ለመሳተፍ ሲሉ አንዳንድ ነገሮችን ያስተካከሉ ብዙ ሰዎች ደስታና እርካታ ወደተሞላበት ሕይወት የሚወስደውን መንገድ አግኝተዋል። እርግጥ አንድ ሰው ይህን እርምጃ እንዲወስድ እምነትና ድፍረት ያስፈልገዋል፤ አንዳንድ እንቅፋቶችም ሊያጋጥሙት ይችላሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፣ ደመናትንም የሚመለከት አያጭድም” በማለት ያሳስበናል። (መክብብ 11:4) ብዙውን ጊዜ አንዴ ከቆረጥን አንድን ነገር መሥራት ያን ያህል አያስቸግረንም። ችግሩ መቁረጡ ላይ ነው። አንድን አስቸጋሪ ሥራ ለመቀበል ወይም ላለመቀበል ከሐሳባቸን ጋር ስንታገል እንደክማለን። አእምሯችንን ካዘጋጀንና ተፈታታኙን ሁኔታ ከተቀበልን ግን ችግሩ ወደ በረከትነት ሲለወጥ በማየት ልንደሰት እንችላለን። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም” በማለት አጥብቆ መክሯል።—መዝሙር 34:8፤ 1 ጴጥሮስ 1:13
“ለነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ”
19. (ሀ) የዓለም ሁኔታዎች እያዘቀጡ ሲሄዱ ምን ልንጠብቅ እንችላለን? (ለ) በኢየሱስ ቀንበር ሥር ስንሆን ስለ ምን ነገር ልንተማመን እንችላለን?
19 ሐዋርያው ጳውሎስ “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” በማለት በመጀመሪያ መቶ ዘመን የነበሩ ደቀ መዛሙርትን አሳስቧቸዋል። (ሥራ 14:22) ይህ ዛሬም ቢሆን እውነት ነው። የዓለም ሁኔታዎች እያዘቀጡ መሄዳቸውን እስካላቆሙ ድረስ ጽድቅ ለማድረግና ለአምላክ ያደሩ በመሆን ለመቀጠል በቆረጡ ሁሉ ላይ የሚመጡባቸው ተጽዕኖዎች ከምን ጊዜውም የበለጠ እየጨመሩ ይሄዳሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:12፤ ራእይ 13:16, 17) ሆኖም ጳውሎስ “በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም” በማለት ሲናገር እንደተሰማው ዓይነት ስሜት አለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ከወትሮው በላይ የሆነ ኃይል ስለሚሰጠን ልንተማመን እንችላለን። (2 ቆሮንቶስ 4:7–9) የደቀ መዝሙርነትን ቀንበር ሙሉ በሙሉ ስንቀበል ኢየሱስ “ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” ሲል የሰጠው ተስፋ ሲፈጸምልን መመልከት እንችላለን።—ማቴዎስ 11:29
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ ኢየሱስ እንድንሸከመው የጋበዘን የለዘበ ቀንበር ምንድን ነው?
◻ ቀንበራችን ሸክም እንደሆነብን ከተሰማን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
◻ ኢየሱስ ‘ሸክሜ ቀላል ነው’ ሲል ምን ማለቱ ነበር?
◻ ሸክማችን ቀላል እንደሆነ እንደሚቀጥል ልንተማመን የምንችለው እንዴት ነው?