የጥናት ርዕስ 1
“ይሖዋን የሚሹ . . . መልካም ነገር አይጎድልባቸውም”
የ2022 የዓመት ጥቅስ፦ “ይሖዋን የሚሹ . . . መልካም ነገር አይጎድልባቸውም።”—መዝ. 34:10
መዝሙር 4 “ይሖዋ እረኛዬ ነው”
ማስተዋወቂያa
1. ዳዊት ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር?
ዳዊት ሕይወቱን ለማትረፍ እየሸሸ ነው። ኃያል የሆነው የእስራኤል ንጉሥ ሳኦል፣ ዳዊትን ለመግደል ቆርጦ ተነስቷል። በአንድ ወቅት ዳዊት ምግብ ሲያልቅበት ወደ ኖብ ከተማ ሄዶ አምስት ዳቦ እንዲሰጡት ጠየቀ። (1 ሳሙ. 21:1, 3) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ዳዊትና አብረውት ያሉት ሰዎች በዋሻ ውስጥ ለመሸሸግ ተገድደው ነበር። (1 ሳሙ. 22:1) ዳዊት እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ የወደቀው እንዴት ነው?
2. ሳኦል ራሱን ችግር ውስጥ የከተተው እንዴት ነው? (1 ሳሙኤል 23:16, 17)
2 ዳዊት በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅ መሆኑ እና ብዙ ድሎች ማግኘቱ ሳኦልን በቅናት አሳብዶት ነበር። በተጨማሪም ሳኦል፣ ባለመታዘዙ የተነሳ የእስራኤል ንጉሥ እንዳይሆን ይሖዋ እንደናቀው እንዲሁም ዳዊትን ንጉሥ አድርጎ እንደቀባው ያውቅ ነበር። (1 ሳሙኤል 23:16, 17ን አንብብ።) ሳኦል የእስራኤል ንጉሥ በመሆኑ ታላቅ ሠራዊት እና ብዙ ደጋፊዎች ነበሩት፤ በመሆኑም ዳዊት ሕይወቱን ለማትረፍ መሸሽ ነበረበት። ሳኦል አምላክ ዳዊትን ለማንገሥ ያለውን ዓላማ ማክሸፍ እንደሚችል አስቦ ይሆን? (ኢሳ. 55:11) መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምንም አይልም። አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት እናውቃለን፦ ሳኦል ራሱን ችግር ውስጥ እየከተተ ነበር። ምክንያቱም ከአምላክ ጋር የሚዋጉ መቼም ቢሆን አያሸንፉም!
3. ዳዊት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?
3 ዳዊት የሥልጣን ጥመኛ አልነበረም። የእስራኤል ንጉሥ ልሁን ብሎ ራሱን የሾመ ሰው አልነበረም። ይህን ኃላፊነት የሰጠው ይሖዋ ራሱ ነው። (1 ሳሙ. 16:1, 12, 13) በዚህ የተነሳ ሳኦል፣ ዳዊትን ቀንደኛ ጠላቱ አድርጎ ይመለከተው ጀመር። ይሁንና ዳዊት እንዲህ ዓይነት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ በመግባቱ ይሖዋን አላማረረም፤ አሊያም ደግሞ ‘ምግብ አጣሁ’ ወይም ‘ዋሻ ውስጥ ለመኖር ተገደድሁ’ ብሎ አላጉረመረመም። እንዲያውም ዋሻ ውስጥ ተሸሽጎ በነበረበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም አንድ ውብ የሆነ የውዳሴ መዝሙር አቀናብሯል፤ “ይሖዋን የሚሹ . . . መልካም ነገር አይጎድልባቸውም” የሚለው የጭብጡ ጥቅሳችንም የዚህ መዝሙር ክፍል ነው።—መዝ. 34:10
4. የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን? ይህን ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
4 በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ብዙ የይሖዋ አገልጋዮች ምግብና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን የሚቸገሩበት ጊዜ አለ።b በተለይ በቅርቡ ከተከሰተው ወረርሽኝ ወዲህ ይህ በይበልጥ እየታየ ነው። ወደ ‘ታላቁ መከራ’ ይበልጥ እየቀረብን ስንሄድ ደግሞ ከዚህ የባሱ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሙን እንጠብቃለን። (ማቴ. 24:21) ይህንን በአእምሯችን ይዘን እስቲ የሚከተሉትን አራት ጥያቄዎች እንመርምር፦ ዳዊት ‘መልካም ነገር አልጎደለበትም’ ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው? ባለን መርካትን መማር ያለብን ለምንድን ነው? ይሖዋ እንደሚንከባከበን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? ለወደፊቱ ጊዜ ከአሁኑ መዘጋጀት የምንችለውስ እንዴት ነው?
“የሚጎድልብኝ ነገር የለም”
5-6. መዝሙር 23:1-6 ዳዊት የአምላክ አገልጋዮች “መልካም ነገር አይጎድልባቸውም” ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ለመረዳት የሚያስችለን እንዴት ነው?
5 ዳዊት የይሖዋ አገልጋዮች ‘መልካም ነገር እንደማይጎድልባቸው’ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? በመዝሙር 23 ላይ የሚገኘውን ተመሳሳይ አገላለጽ መመርመራችን ዳዊት ምን ማለቱ እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል። (መዝሙር 23:1-6ን አንብብ።) ዳዊት መዝሙር 23ን የጀመረው “ይሖዋ እረኛዬ ነው። የሚጎድልብኝ ነገር የለም” በሚሉት ቃላት ነው። በቀጣዮቹ ቁጥሮች ላይ ዳዊት እውነተኛና ዘላቂ ዋጋ ያላቸውን ነገሮች ጠቅሷል፤ እነሱም ይሖዋን እንደ እረኛው አድርጎ በመቀበሉ ያገኛቸው የተትረፈረፉ መንፈሳዊ በረከቶች ናቸው። ይሖዋ ዳዊትን “በጽድቅ መንገድ [ይመራዋል]” እንዲሁም በክፉም ሆነ በደጉ ጊዜ በታማኝነት ይደግፈዋል። ዳዊት ‘በለመለመው የይሖዋ መስክ’ ላይ ቢሰማራም ሕይወቱ አልጋ በአልጋ እንደማይሆን ያውቅ ነበር። አንዳንድ ጊዜ፣ “ድቅድቅ ጨለማ በዋጠው ሸለቆ ውስጥ” የሚሄድ ያህል ተስፋ ይቆርጥ ይሆናል፤ ጠላቶችም ይኖሩታል። ሆኖም ዳዊት ይሖዋ እረኛው ስለሆነ ‘ጉዳት ይደርስብኛል ብሎ አይፈራም።’
6 ስለዚህ ዳዊት ‘መልካም ነገር አልጎደለበትም’ ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ አግኝተናል። በመንፈሳዊ ረገድ የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ተሟልቶለታል። ደስተኛ መሆኑ በቁሳዊ ነገሮች ላይ የተመካ አልነበረም። ዳዊት ይሖዋ በሰጠው ነገር ረክቶ ይኖር ነበር። ከምንም በላይ ትልቅ ቦታ የሰጠው ከአምላክ ለሚያገኘው በረከትና ጥበቃ ነበር።
7. ሉቃስ 21:20-24 እንደሚያሳየው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የይሁዳ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር?
7 ዳዊት የተናገረው ነገር ለቁሳዊ ነገሮች ተገቢውን አመለካከት መያዛችን ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል። ቁሳዊ ንብረት ቢኖረን ይህ ስህተት አይደለም፤ ሆኖም ንብረታችን በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊይዝ አይገባም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሁዳ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ይህን አስፈላጊ እውነት ተገንዝበዋል። (ሉቃስ 21:20-24ን አንብብ።) ኢየሱስ “ኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት [የምትከበብበት]” ጊዜ እንደሚመጣ አስቀድሞ አስጠንቅቋቸው ነበር። ይህ በሚሆንበት ጊዜ “ወደ ተራሮች [መሸሽ]” ነበረባቸው። ከተማዋን ለቅቀው መሸሻቸው ሕይወታቸውን ያተርፍላቸዋል፤ ያም ቢሆን መሥዋዕት የሚያደርጉት ነገር ነበር። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የወጣ መጠበቂያ ግንብ ሁኔታውን እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል፦ “እርሻቸውንና ቤታቸውን የተዉ ሲሆን ንብረታቸውን ለመሰብሰብ ሲሉ እንኳ ወደ ቤታቸው አልተመለሱም። በይሖዋ ጥበቃና ድጋፍ በመታመን ጠቃሚ ከሚመስል ከማንኛውም ነገር ሁሉ በፊት የእሱን አምልኮ አስቀድመዋል።”
8. በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሁዳ ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች ያጋጠማቸው ነገር፣ ልናስብበት የሚገባ ምን ቁም ነገር ያስጨብጠናል?
8 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሁዳ ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች ያጋጠማቸው ነገር፣ ልናስብበት የሚገባ ምን ቁም ነገር ያስጨብጠናል? ቀደም ሲል የተጠቀሰው መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ይላል፦ “ለቁሳዊ ነገሮች ባለን አመለካከት ረገድ ወደፊት የሚመጡ ፈተናዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ በጣም አስፈላጊ የሆኑት ያሉን ቁሳዊ ነገሮች ናቸው ወይስ ይበልጥ አንገብጋቢ የሆነው በአምላክ ጎን ለቆሙ ሰዎች የሚመጣው መዳን ነው? አዎን፣ ሽሽታችን አንዳንድ ችግሮችን ወይም እጦትን የሚጨምር ሊሆን ይችላል። ከይሁዳ . . . እንደ ሸሹት እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ዝግጁዎች መሆን አለብን።”c
9. ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ከሰጠው ምክር ምን ማበረታቻ ማግኘት እንችላለን?
9 እነዚያ ክርስቲያኖች ያላቸውን ነገር ሁሉ ጥለው መጥተው እንደ አዲስ ኑሮን መጀመር ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው መገመት ትችላለህ? ይሖዋ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን እንደሚያሟላላቸው መተማመን ነበረባቸው። ሆኖም ይህን ለማድረግ ሊረዳቸው የሚችል ነገር ነበር። ሮማውያን ኢየሩሳሌምን ከመክበባቸው ከአምስት ዓመታት በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የሚከተለውን ጠቃሚ ምክር ሰጥቷቸው ነበር፦ “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ። እሱ ‘ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም’ ብሏልና። ስለዚህ በሙሉ ልብ ‘ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?’ እንላለን።” (ዕብ. 13:5, 6) ከሮማውያን ወረራ በፊት የጳውሎስን ምክር ተግባራዊ አድርገው የነበሩ ክርስቲያኖች በአዲሱ አካባቢ ቀለል ያለ ኑሮ መልመድ ከባድ እንደማይሆንባቸው የታወቀ ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ይሖዋ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን እንደሚያሟላላቸው እርግጠኞች ነበሩ። ጳውሎስ የተናገረው ነገር እኛም በዚህ መተማመን እንደምንችል ያረጋግጥልናል።
“በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል”
10. ጳውሎስ ምን “ሚስጥር” ነግሮናል?
10 ጳውሎስ ለጢሞቴዎስም ተመሳሳይ ምክር ሰጥቶታል፤ ይህ ምክር ለእኛም ይሠራል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ስለዚህ ምግብና ልብስ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።” (1 ጢሞ. 6:8) ታዲያ ይህ ሲባል ጥሩ ምግብ ብንበላ፣ ምቹ መኖሪያ ቢኖረን ወይም አንዳንድ ጊዜ አዲስ ልብስ ብንገዛ ስህተት ነው ማለት ነው? ጳውሎስ እንዲህ ማለቱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ያለን ነገር ምንም ይሁን ምን በዚያ ረክተን ልንኖር እንደሚገባ መግለጹ ነበር። (ፊልጵ. 4:12) የጳውሎስ “ሚስጥር” ይህ ነበር። ከሁሉ የላቀው ውድ ንብረታችን ከአምላክ ጋር የመሠረትነው ዝምድና እንጂ ያሉን ቁሳዊ ነገሮች አይደሉም።—ዕን. 3:17, 18
11. ሙሴ ለእስራኤላውያን የተናገረው ነገር ባለን ረክተን ስለመኖር ምን ያስተምረናል?
11 የሚያስፈልጉንን ነገሮች በተመለከተ ያለን አመለካከት ከይሖዋ የተለየ ሊሆን ይችላል። እስራኤላውያን በምድረ በዳ 40 ዓመታት ካሳለፉ በኋላ ሙሴ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “አምላክህ ይሖዋ የእጅህን ሥራ ሁሉ ባርኮልሃልና። በዚህ ጭልጥ ያለ ምድረ በዳ እንደተጓዝክ በሚገባ ያውቃል። በእነዚህ 40 ዓመታት አምላክህ ይሖዋ ከአንተ ጋር ስለነበር ምንም የጎደለብህ ነገር የለም።” (ዘዳ. 2:7) በእነዚያ 40 ዓመታት ይሖዋ ለእስራኤላውያን መና ሰጥቷቸዋል። ከግብፅ ሲወጡ ለብሰውት የነበረው ልብስ እንኳ አላለቀባቸውም። (ዘዳ. 8:3, 4) አንዳንዶች ይህ በቂ እንዳልሆነ ሊሰማቸው ቢችልም ሙሴ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በሙሉ እንዳገኙ እስራኤላውያንን አስታውሷቸዋል። ይሖዋ ባለን ነገር ረክተን ስንኖር ደስ ይለዋል፤ ምንም ያህል ትንሽ ቢመስልም እንኳ እሱ የሚሰጠንን ነገር እንድናደንቅ፣ ከእሱ እንዳገኘነው በረከት አድርገን እንድንመለከተው እንዲሁም ለስጦታው እንድናመሰግነው ይፈልጋል።
ይሖዋ እንደሚንከባከባችሁ ተማመኑ
12. ዳዊት በራሱ ሳይሆን በይሖዋ እንደተማመነ የሚያሳየው ምንድን ነው?
12 ዳዊት ይሖዋ ታማኝ እንደሆነና ለሚወዱት አገልጋዮቹ በጥልቅ እንደሚያስብላቸው ያውቅ ነበር። ዳዊት መዝሙር 34ን ያቀናበረው ሕይወቱ አደጋ ላይ በወደቀበት ወቅት ነበር፤ ሆኖም በእምነት ዓይኑ ‘የይሖዋ መልአክ ዙሪያውን እንደሰፈረ’ ታይቶታል። (መዝ. 34:7) ዳዊት ስለ ይሖዋ መልአክ ይህን ያለው ጦር ሜዳ ላይ የሰፈረንና የጠላትን እንቅስቃሴ በንቃት የሚከታተልን ወታደር በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። ዳዊት ኃያል ተዋጊ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ ንጉሥ እንደሚያደርገው ቃል ገብቶለት ነበር። ያም ቢሆን ዳዊት ‘ወንጭፍ አስፈንጥሬ ወይም ሰይፍ መዝዤ ጠላቶቼን ድል አደርጋለሁ’ ብሎ በራሱ ችሎታ አልተማመነም። (1 ሳሙ. 16:13፤ 24:12) ከዚህ ይልቅ ‘የይሖዋ መልአክ አምላክን የሚፈሩትን እንደሚታደጋቸው’ በመተማመን በይሖዋ ላይ እምነት ጥሏል። እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ ይሖዋ በተአምራዊ ሁኔታ ጥበቃ ያደርግልናል ብለን አንጠብቅም። አንድ ነገር ግን እናውቃለን፦ በይሖዋ የሚታመን ሰው መቼም ቢሆን ዘላቂ ጉዳት አይደርስበትም።
13. የማጎጉ ጎግ ጥቃት በሚሰነዝርበት ጊዜ በቀላሉ የምንጠፋ መስለን የምንታየው ለምንድን ነው? ሆኖም እንዳንፈራ የሚያደርገን ምን ምክንያት አለን? (ሽፋኑን ተመልከት።)
13 ይሖዋ እኛን የመጠበቅ ችሎታ እንዳለው ያለን እምነት በቅርቡ ይፈተናል። የማጎጉ ጎግ ማለትም ግንባር የፈጠሩ ብሔራት በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ሕይወታችን አደጋ ላይ የወደቀ ሊመስል ይችላል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ይሖዋ እኛን ለማዳን ችሎታው እንዳለውና ይህንንም እንደሚያደርግ ልንተማመን ይገባል። ብሔራት፣ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች ሆነን እንታያቸው ይሆናል። (ሕዝ. 38:10-12) የጦር ትጥቅም ሆነ የውጊያ ተሞክሮ አይኖረንም። ብሔራት በቀላሉ ሊደመስሱን እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። እኛ በእምነት ዓይናችን የሚታየን ነገር ለእነሱ አይታያቸውም፤ ለአምላክ ሕዝብ ጥበቃ ለማድረግ ተዘጋጅቶ በሕዝቡ ዙሪያ የሰፈረውን የመላእክት ጭፍራ ማየት አይችሉም። ደግሞስ እንዴት ሊታያቸው ይችላል? እነሱ መንፈሳዊ እይታ የላቸውም። የሰማይ ሠራዊት እኛን ለማዳን እርምጃ ሲወስዱ ብሔራት ምን ያህል እንደሚደናገጡ አስቡት።—ራእይ 19:11, 14, 15
ለወደፊቱ ጊዜ ከአሁኑ ተዘጋጁ
14. ለወደፊቱ ጊዜ ከአሁኑ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
14 ለወደፊቱ ጊዜ ከአሁኑ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ለቁሳዊ ነገሮች ተገቢውን አመለካከት ማዳበር ይኖርብናል፤ ያሉንን ቁሳዊ ነገሮች ወደፊት ልናጣቸው እንደምንችል መገንዘብ ይኖርብናል። ከዚህም በተጨማሪ ባለን ነገር መርካት እንዲሁም ከሁሉ በላቀው ሀብታችን ይኸውም ከይሖዋ ጋር ባለን ዝምድና መደሰት ይኖርብናል። አምላካችንን ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ፣ የማጎጉ ጎግ ጥቃት በሚሰነዝርበት ወቅት እኛን ለመጠበቅ ችሎታ እንዳለው ያለን እምነት ይበልጥ ይጠናከራል።
15. ዳዊት ይሖዋ እንደማያሳፍረው እንዲተማመን ያደረጉት በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠሙት የትኞቹ ነገሮች ናቸው?
15 ዳዊትን የረዳውን ሌላም ነገር እንመልከት፤ ይህ ነጥብ እኛንም ለመከራ ለመዘጋጀት ይረዳናል። ዳዊት “ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም፤ እሱን መጠጊያ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው” ብሏል። (መዝ. 34:8) ይህ ሐሳብ ዳዊት፣ ይሖዋ እንደሚደግፈው የተማመነው ለምን እንደሆነ ይጠቁመናል። ዳዊት ሁልጊዜም በይሖዋ ይታመን ነበር፤ አምላክም አሳፍሮት አያውቅም። ዳዊት ወጣት እያለ ግዙፉን ፍልስጤማዊ ጎልያድን ገጥሞት ነበር፤ ይህን ኃያል ተዋጊ “ዛሬ ይሖዋ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጥሃል” ብሎታል። (1 ሳሙ. 17:46) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ዳዊት ንጉሥ ሳኦልን በሚያገለግልበት ወቅት ሳኦል እሱን ለመግደል ብዙ ጊዜ ሙከራ አድርጓል፤ ይሖዋ ግን ‘ከዳዊት ጋር ነበር።’ (1 ሳሙ. 18:12) ዳዊት ቀደም ሲል ካጋጠሙት ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ የይሖዋን እጅ ስላየ አሁን የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ለመወጣትም እንደሚረዳው ተማምኖ ነበር።
16. የይሖዋን ጥሩነት በየትኞቹ መንገዶች ‘የመቅመስ’ አጋጣሚ አለን?
16 በአሁኑ ጊዜ በይሖዋ በመታመን የእሱን መመሪያ የመከተል ልማድ ካለን ወደፊትም እኛን ለማዳን ችሎታው እንዳለው ይበልጥ እንተማመናለን። ለምሳሌ በወረዳ ወይም በክልል ስብሰባ ላይ ለመገኘት አሠሪያችን እረፍት እንዲሰጠን መጠየቅ ያስፈልገን ይሆናል፤ አሊያም ደግሞ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና በአገልግሎት የበለጠ ተሳትፎ ለማድረግ የሥራ ፕሮግራማችንን እንዲያስተካክልልን አሠሪያችንን ማነጋገር ያስፈልገን ይሆናል። እነዚህን ነገሮች ማድረግ እምነትና በይሖዋ መታመን ይጠይቃል። አሠሪያችን ጥያቄያችንን ባይቀበለውና ከሥራ ብንባረርስ? ይሖዋ መቼም ቢሆን እንደማይጥለንና እንደማይተወን እንዲሁም መሠረታዊ ፍላጎታችንን ሁልጊዜ እንደሚያሟላልን እንተማመናለን? (ዕብ. 13:5) በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ያሉ ብዙዎች ይሖዋ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ እንዴት እንደደረሰላቸው የሚገልጹ ተሞክሮዎችን ሲናገሩ እንሰማለን። በእርግጥም ይሖዋ ታማኝ ነው።
17. የ2022 የዓመት ጥቅስ ምንድን ነው? ይህ ጥቅስ መመረጡ ተገቢ የሆነውስ ለምንድን ነው?
17 ይሖዋ ከእኛ ጋር ስለሆነ የወደፊቱን ጊዜ የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለንም። በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን ፈቃድ እስካስቀደምን ድረስ አምላካችን መቼም ቢሆን አይተወንም። ወደፊት ለሚጠብቁን አስቸጋሪ ሁኔታዎች እኛን ለማዘጋጀት እንዲሁም ይሖዋ መቼም ቢሆን እንደማይተወን እንድንተማመን ለመርዳት ሲባል የበላይ አካሉ መዝሙር 34:10 የ2022 የዓመት ጥቅስ እንዲሆን መርጧል። ጥቅሱ “ይሖዋን የሚሹ . . . መልካም ነገር አይጎድልባቸውም” ይላል።
መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል
a የ2022 የዓመት ጥቅስ የተወሰደው ከመዝሙር 34:10 ሲሆን ጥቅሱ “ይሖዋን የሚሹ . . . መልካም ነገር አይጎድልባቸውም” ይላል። ብዙዎቹ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በቁሳዊ ነገር ረገድ ድሆች ናቸው። ታዲያ “መልካም ነገር አይጎድልባቸውም” ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? የዚህን ጥቅስ ትርጉም መረዳታችን ከፊታችን ለሚጠብቀን አስቸጋሪ ጊዜ ለመዘጋጀት የሚረዳንስ እንዴት ነው?
b በመስከረም 15, 2014 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።
c የግንቦት 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 19ን ተመልከት።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ ዳዊት ከንጉሥ ሳኦል ሸሽቶ በዋሻ ውስጥ ተደብቆ በነበረበት ጊዜም እንኳ ይሖዋ ለሰጠው ነገር አድናቆት ነበረው።
e የሥዕሉ መግለጫ፦ እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ ይሖዋ የሚበሉት መና ሰጥቷቸዋል፤ እንዲሁም ልብሳቸው እንዳያልቅ አድርጓል።