ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ የምትችለው እንዴት ነው?
ገንዘብን መውደድና ቁሳዊ ሃብት የማግኘት ፍላጎት እንግዳ ነገሮች አይደሉም። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ከጊዜ በኋላ ብቅ እንዳሉ ክስተቶች በመቁጠር ስለ እነርሱ ከመናገር አልተቆጠበም። ብዙ ዘመን ያስቆጠሩ ናቸው። አምላክ ለእስራኤላውያን በሰጣቸው ሕግ ላይ “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ . . . ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር።—ዘጸአት 20:17
ገንዘብንና ቁሳዊ ሃብትን መውደድ በኢየሱስ ዘመንም የተለመደ ነበር። በኢየሱስና “እጅግ ባለጠጋ” በነበረው ወጣት መካከል የተደረገውን የሚከተለውን ውይይት ተመልከት። “ኢየሱስም . . . አንዲት ገና ቀርታሃለች፤ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፣ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፣ መጥተህም ተከተለኝ አለው። እርሱ ግን ይህን ሰምቶ እጅግ ባለ ጠጋ ነበርና ብዙ አዘነ።”—ሉቃስ 18:18-23
ለገንዘብ ተገቢ የሆነ አመለካከት መያዝ
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብን ራሱን ወይም ገንዘብ የሚያስገኛቸውን ማናቸውንም መሠረታዊ ጥቅሞች ያወግዛል ብሎ መደምደሙ ስህተት ይሆናል። ገንዘብ ሰዎች የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን ድህነትንና ከእርሱ ጋር አብረው የሚመጡትን ችግሮች በማስወገድ ረገድ ተግባራዊ ጠቀሜታ እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የጥበብ ጥላ እንደ ገንዘብ ጥላ ናትና።” በተጨማሪም “እንጀራን ለሳቅ የወይን ጠጅንም ለሕይወት ደስታ ያደርጉታል፣ ሁሉም ለገንዘብ ይገዛል [“ይህ ሁሉ ያለ ገንዘብ አይገኝም፣” የ1980 ትርጉም ]” ሲል ጽፏል።—መክብብ 7:12፤ 10:19
አምላክ ተገቢ በሆነ መንገድ በገንዘብ መጠቀምን አያወግዝም። ለምሳሌ ኢየሱስ ‘በዓመፃ ገንዘብ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ’ ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 16:9) አምላክ ወዳጃችን እንዲሆን መፈለጋችን ምንም ጥርጥር ስለሌለው ይህ ለእርሱ እውነተኛ አምልኮ መስፋፋት የምናደርገውን የገንዘብ መዋጮም ይጨምራል። ሰሎሞን ራሱም የአባቱን የዳዊትን ምሳሌ በመከተል ለይሖዋ ቤተ መቅደስ ግንባታ የሚሆን ብዙ ገንዘብና ውድ እቃዎች ሰጥቷል። ሌላው የክርስቲያን ኃላፊነት ደግሞ ችግር ላይ የወደቁትን በቁሳዊ መንገድ መደገፍ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ” ሲል ተናግሯል። አክሎም “እንግዶችን ለመቀበል ትጉ” ብሏል። (ሮሜ 12:13) ይህም ባብዛኛው ገንዘብ ማውጣትን ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ገንዘብን ስለመውደድስ ምን ሊባል ይችላል?
‘ብርን መውደድ’
ጳውሎስ በዕድሜ ለሚያንሰው ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‘ገንዘብን ስለመውደድ’ ወይም ቃል በቃል ‘ብርን ስለመውደድ’ በሰፊው አብራርቷል። የጳውሎስን ማስጠንቀቂያ 1 ጢሞቴዎስ 6:6-19 ላይ ማግኘት ይቻላል። ጳውሎስ ስለ ቁሳዊ ነገሮች ከሰጠው ሰፊ ማብራሪያ መካከል “ገንዘብን ስለመውደድም” ተናግሯል። ዛሬ ያለው ኅብረተሰብ ለገንዘብ ከሚሰጠው ግምት አንፃር ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት የሰጣቸውን ሐሳቦች በጥንቃቄ መመርመሩ ተገቢ ነው። እንዲህ ያለው ምርምር ‘እውነተኛውን ሕይወት መያዝ’ የምንችልበትን ምስጢር ስለሚገልጥልን በእርግጥም ጠቃሚ ነው።
ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል አስጠንቅቋል:- “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ፣ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።” (1 ጢሞቴዎስ 6:10) ይህም ሆነ ሌሎች ጥቅሶች ገንዘብ በራሱ መጥፎ ነው አይሉም። ጳውሎስም ቢሆን ገንዘብ “የክፋት ሁሉ” ሥር ነው ወይም የእያንዳንዱ ችግር መንስኤ ነው አላለም። ገንዘብን መውደድ ‘የክፋት ሁሉ’ ብቸኛ መንስኤ ባይሆንም መንስኤ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ግን አለ።
ከስግብግብነት ተጠበቁ
ገንዘብ በራሱ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አለመወገዙ የጳውሎስን ማስጠንቀቂያ አስፈላጊነት አይቀንሰውም። ገንዘብን መውደድ የጀመሩ ክርስቲያኖች ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ሲሆን ከሁሉ የከፋው ግን ከእምነት የመወሰድ አደጋ ነው። ይህ እውነታ ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ተጠናክሮ እናገኘዋለን። “እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ . . . ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ መጐምጀት ነው።” (ቆላስይስ 3:5) መጎምጀት፣ ስግብግብነት ወይም “ገንዘብን መውደድ” እንደ ጣዖት አምልኮ ሊቆጠር የሚችለው እንዴት ነው? እንዲህ ሲባል ትልቅ ቤት፣ አዲስ መኪናና ጥሩ ክፍያ ያለው ሥራ እንዲኖረን መፈለግ ስህተት ነው ማለት ነውን? አይደለም። ከእነዚህ ውስጥ አንዳቸውም ቢሆኑ በራሳቸው መጥፎ ነገሮች አይደሉም። ጥያቄው ግን አንድ ሰው እነዚህን ነገሮች እንዲፈልግ ያነሳሳው የልብ ዝንባሌ ምንድን ነው? እንዲሁም በእርግጥ አስፈላጊ ናቸውን? የሚለው ነው።
በተለመደው ዓይነት ፍላጎትና በስግብግብነት መካከል ያለው ልዩነት በሽርሽር ወቅት ምግብ ለማብሰል ተብሎ ከሚነድደው እሳትና ጥቅጥቅ ያለውን ደን ከሚያጋይ እሳት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ጤናማና ተገቢ ፍላጎት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። እንድንሠራና ፍሬያማ እንድንሆን ያነሳሳናል። ምሳሌ 16:26 “የሠራተኛ ራብ ለእርሱ ይሠራል፣ አፉ ይጐተጉተዋልና” በማለት ይናገራል። ይሁን እንጂ ስግብግብነት አደገኛና አጥፊ ከመሆኑም ሌላ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ፍላጎት ነው።
መሠረታዊው ችግር የገንዘብ ፍላጎታችንን መቆጣጠር አለመቻላችን ነው። ያከማቸነው ገንዘብም ሆነ ቁሳዊ ንብረት ፍላጎታችንን ያሟሉልናል ወይስ ፍላጎቶቻችን የገንዘብ ባሪያዎች ያደርጉናል? ጳውሎስ ‘ስግብግብ ሰው ጣዖትን የሚያመልክ ነው’ ብሎ የተናገረው ለዚህ ነው። (ኤፌሶን 5:5) እንደ እውነቱ ከሆነ ለአንድ ነገር መስገብገብ ማለት ፈቃዳችንን ለዛ ነገር ማስገዛት ወይም በሌላ አባባል ጌታችንና አምላካችን ማድረግ እንዲሁም ያንን ነገር ማገልገል ማለት ነው። ከዚህ በተቃራኒ ግን አምላክ “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ” ሲል አጥብቆ አሳስቧል።—ዘጸአት 20:3
በተጨማሪም ስግብግብ መሆናችን አምላክ የሚያስፈልገንን እንደሚያሟላልን በገባው ቃል ላይ ትምክህት እንደሌለን ያሳያል። (ማቴዎስ 6:33) ስለዚህ ስግብግብነት ከአምላክ እንድንርቅ ያደርገናል። በዚህ መሠረት ስግብግብነት “የጣዖት አምልኮ” ነው። ጳውሎስ ከዚህ እንድንርቅ ግልጽ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ያለ ምክንያት አይደለም!
ኢየሱስም ስግብግብነትን በተመለከተ ቀጥተኛ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። የሌለንን ነገር ከመመኘት እንድንጠበቅ በማስጠንቀቅ የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቷል:- “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፣ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ አላቸው።” (ሉቃስ 12:15) ከዚህ ዘገባና ኢየሱስ ቀጥሎ ከሰጠው ምሳሌ መረዳት እንደሚቻለው ስግብግብነት፣ በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ግለሰቡ ምን አለው በሚለው የሞኝነት አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ ደግሞ ገንዘብ፣ ከፍ ያለ ቦታ፣ ሥልጣን ወይም ከዚያ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ሊገኝ ለሚችል ለማንኛውም ነገር ስግብግብ መሆን አስቸጋሪ አይደለም። የፈለግነውን ማግኘታችን ደግሞ ያረካናል ብለን እናስብ ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለውና ከልምድም እንደታየው እውነተኛ ፍላጎታችንን ሊያሟላልን የሚችለውና የሚያሟላልንም አምላክ ብቻ ነው። ኢየሱስም ለተከታዮቹ ያስረዳቸው ይህንኑ ነው።—ሉቃስ 12:22-31
የስግብግብነትን እሳት በማቀጣጠል ረገድ ለሸቀጦች ግብይት የተጋነነ አመለካከት ያለውን የዛሬውን ሕብረተሰብ የሚያህለው የለም። ብዙዎች ረቂቅ ሆኖም ኃይለኛ በሆኑ መንገዶች ተጽእኖ ስለሚደረግባቸው ያላቸው ማንኛውም ነገር በቂ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ተጨማሪ፣ ትላልቅና የተሻሉ ነገሮችን ይፈልጋሉ። በዙሪያችን ያለውን ዓለም ለመለወጥ ባንችልም በግላችን እንዲህ ያለውን ዝንባሌ መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
ያለኝ ይበቃኛል ማለት እና ስስት
ጳውሎስ የስስት ተቃራኒ የሆነውን ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ዝንባሌ አስተዋውቋል። እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል።” (1 ጢሞቴዎስ 6:8) “ምግብና ልብስ” ካለን ሌላ ምንም አያስፈልገንም የሚለው አባባል እጅግ የተጋነነ ሊመስል ይችላል። ብዙ ሰዎች ለመዝናናት በሚመለከቷቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች አማካኝነት ምቾትና ውበት ባላቸው ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ዝነኛ ሰዎችን ይመለከታሉ። ያለኝ ይበቃኛል የምንለው እንዲህ ዓይነት ኑሮ ስናገኝ ነው ማለት አይደለም።
እርግጥ የአምላክ አገልጋዮች ራሳቸውን በድህነት የማኖር ግዴታ የለባቸውም። (ምሳሌ 30:8, 9) ይሁን እንጂ ጳውሎስ ድህነት ማለት በእርግጥ ምን ማለት እንደሆነ ያስታውሰናል። ድህነት ሲባል በሕይወት ለመቆየት የሚያስፈልገውን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ማጣት ማለት ነው። በሌላው በኩል ግን እነዚህ ነገሮች ካሉን ያለኝ ይበቃኛል ማለት እንችላለን።
ጳውሎስ በዚህ መንገድ ረክቶ መኖር ይቻላል ብሎ ሲናገር ከልቡ ነውን? ምግብ፣ ልብስና መጠለያ በመሳሰሉት መሠረታዊ ነገሮች ብቻ ረክቶ መኖር ይቻላል? ጳውሎስ የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ አለበት። ጳውሎስ በአይሁድ ማኅበረሰብ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታና የሮማ ዜግነት የነበረው በመሆኑ ሃብትና ልዩ መብት ማግኘት ምን እንደሚመስል አይቷል። (ሥራ 22:28፤ 23:6፤ ፊልጵስዩስ 3:5) በተጨማሪም ጳውሎስ በሚስዮናዊ አገልግሎቱ ወቅት ከባድ ችግሮች ደርሰውበታል። (2 ቆሮንቶስ 11:23-28) ጳውሎስ በእነዚህ ሁሉ አጋጣሚዎች ባለው ነገር የመርካትን ዝንባሌ ጠብቆ እንዲቆይ የረዳውን ምስጢር ተምሯል። ይህ ምስጢር ምን ነበር?
‘ምስጢሩን ተምሬአለሁ’
ጳውሎስ ከጻፋቸው ደብዳቤዎች ውስጥ በአንደኛው እንደሚከተለው ሲል ገልጿል:- “መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጒደልን [“የማግኘትንና የማጣትን ምስጢር፣” NW ] ተምሬአለሁ።” (ፊልጵስዩስ 4:12) ጳውሎስ በጣም እርግጠኛና አዎንታዊ አስተሳሰብ ያለው ይመስላል! ጳውሎስ እነዚህን ቃላት ሲጽፍ ጥሩ ኑሮ ነበረው ብሎ ማሰቡ ቀላል ሊሆን ይችላል። ሆኖም እውነታው ከዚያ የራቀ ነው። ጳውሎስ እነዚህን ቃላት የጻፈው ሮም ውስጥ ታስሮ በነበረበት ወቅት ነው!—ፊልጵስዩስ 1:12-14
ይህንን እውነታ ግምት ውስጥ ካስገባነው ዘገባው በቁሳዊ ሃብት ረገድ ያለኝ ይበቃኛል ማለትን ብቻ ሳይሆን በሁኔታዎች መርካትንም አስመልክቶ ጠንካራ መልእክት ያስተላልፋል። ከመጠን ያለፈ ሃብትም ሆነ ችግር ቅድሚያ በምንሰጠው ነገር ረገድ ሊፈትነን ይችላል። ጳውሎስ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ የነበረበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ያለኝ ይበቃኛል ብሎ እንዲኖር ስላስቻለው መንፈሳዊ ኃይል እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል:- “ኃይልን በሚሰጠኝ በእርሱ [በአምላክ] ሁሉን እችላለሁ።” (ፊልጵስዩስ 4:13 NW ) ጳውሎስ ባሉት ብዙ ወይም ጥቂት ቁሳዊ ነገሮች ወይም ደግሞ በሚገኝበት ጥሩ ወይም መጥፎ ሁኔታ ላይ ከመመካት ይልቅ አምላክ የሚያስፈልገውን እንደሚያሟላለት እርግጠኛ ነበር። በዚህም ምክንያት ያለኝ ይበቃኛል ለማለት ችሏል።
የጳውሎስ ምሳሌነት በተለይ ለጢሞቴዎስ በጣም ጠቃሚ ነበር። ሐዋርያው ከገንዘብ ይልቅ ለአምላክ ማደርንና ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረትን በአንደኛ ደረጃ የሚያስቀምጥ የአኗኗር መንገድ እንዲከተል ወጣቱ ጢሞቴዎስን አሳስቦታል። ጳውሎስ የሚከተለውን ብሏል:- “አንተ ግን፣ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፣ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል [“ለአምላክ ያደሩ መሆንንም፣” NW ] እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል።” (1 ጢሞቴዎስ 6:11) ይህ ምክር የተሰጠው ለጢሞቴዎስ ቢሆንም አምላክን ለማክበርና እውነተኛ ደስታ ያለበት ሕይወት ለመምራት ለሚፈልጉ ሰዎች በሙሉ ይሠራል።
እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ሁሉ ጢሞቴዎስም በስስት ወጥመድ ውስጥ እንዳይወድቅ መጠንቀቅ ነበረበት። ጳውሎስ ደብዳቤውን ሲጽፍለት ጢሞቴዎስ በሚገኝበት በኤፌሶን ጉባኤ ውስጥ ሃብታም የሆኑ አማኞች የነበሩ ይመስላል። (1 ጢሞቴዎስ 1:3) ጳውሎስ የንግድ ማዕከል ወደሆነችው ኤፌሶን የክርስቶስን ምሥራች ይዞ በመምጣት ብዙዎችን አማኝ አድርጓል። ዛሬ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንደሚታየው ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ ሃብታሞች እንደነበሩ አያጠራጥርም።
በ1 ጢሞቴዎስ 6:6-10 ላይ በቀረበው ትምህርት መሠረት አሁን የሚነሣው ጥያቄ ሃብታም የሆኑ ሰዎች አምላክን ማክበር ከፈለጉ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? የሚል ነው። ጳውሎስ እንዲህ ያሉት ሰዎች በመጀመሪያ ዝንባሌያቸውን መመርመር እንደሚኖርባቸው ገልጿል። ገንዘብ በሰዎች ልብ ውስጥ ምንም አይጎድለኝም የሚል ስሜት የመፍጠር አዝማሚያ አለው። ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል:- “በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው።” (1 ጢሞቴዎስ 6:17) ሃብታም የሆኑ ሰዎች ከገንዘባቸው ባሻገር መመልከትን መማር ይኖርባቸዋል። ለሃብት ሁሉ መሠረት የሚሆኑት ነገሮች ምንጭ የሆነውን አምላክ ተስፋ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ሆኖም የልብን ዝንባሌ መመርመሩ ብቻውን አይበቃም። ውሎ አድሮ ሃብታም የሆኑ ክርስቲያኖች ሃብታቸውን በተገቢው መንገድ መጠቀምን ሊማሩ ይገባል። ጳውሎስ እንዲህ በማለት አሳስቧል:- “መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፣ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው።”—1 ጢሞቴዎስ 6:18
“እውነተኛው ሕይወት”
የጳውሎስ ምክር ዋነኛ ዓላማ ቁሳዊ ነገሮች የሚያስገኙት ጥቅም አንጻራዊ እንደሆነ ማስገንዘብ ነው። የአምላክ ቃል “ለባለጠጋ ሰው ሀብቱ እንደ ጸናች ከተማ ናት፣ በአሳቡም እንደ ረጅም ቅጥር” ናት በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 18:11) አዎን፣ ሃብት እንዲሰማን የሚያደርገው የደህንነት ስሜት እንዲሁ የማይጨበጥና ከንቱ ማባበያ ነው። ሕይወታችንን የአምላክን ሞገስ ሊያስገኝልን በሚችል መንገድ ከመምራት ይልቅ በእነዚህ ነገሮች ዙሪያ መገንባታችን ስህተት ነው።
ቁሳዊ ሃብት አስተማማኝ ካለመሆኑ የተነሣ ተስፋችንን በእርሱ ላይ መጣል አንችልም። ለእውነተኛ ተስፋ መሠረት መሆን ያለበት ጠንካራ፣ ትርጉም ያለውና ዘላቂ የሆነ ነገር ነው። ክርስቲያናዊ ተስፋችን ደግሞ ፈጣሪያችን በሆነው በይሖዋ አምላክ ላይና ለዘላለም ሕይወት በገባው ቃል ላይ የተመሠረተ ነው። ገንዘብ ደስታን መግዛት እንደማይችል ሁሉ መዳንንም አይገዛም። እንዲህ ያለውን ተስፋ ሊሰጠን የሚችለው በአምላክ ላይ ያለን እምነት ብቻ ነው።
ስለዚህ ሃብታምም ሆንን ድሃ “በእግዚአብሔር ዘንድ ባለ ጠጋ የሚያደርገንን” የአኗኗር መንገድ እንከተል። (ሉቃስ 12:21) በፈጣሪ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አቋም ከማግኘት የበለጠ ምንም ነገር የለም። ይህንን ጠብቆ ለመቆየት የሚደረገው ማንኛውም ጥረት ‘እውነተኛውን ሕይወት እንይዝ ዘንድ ለሚመጣው ዘመን ለራሳችን መልካም መሠረት የሚሆንልንን መዝገብ ለመሰብሰብ’ አስተዋጽኦ ያደርጋል።—1 ጢሞቴዎስ 6:19
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ ኑሮዬ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር ተምሯል
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባሉን ነገሮች መደሰትና ረክተን መኖር እንችላለን