እውነተኛውን ሕይወት እንደ ውድ ሀብት አድርገህ ያዝ
ሕይወት ይህ ብቻ ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ ‘እውነተኛውን ሕይወት አጥብቀን እንድንይዝ’ በማበረታታት ሌላም ሕይወት እንዳለ ይጠቁመናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:17–19) የአሁኑ ሕይወታችን እውነተኛው ሕይወት ካልሆነ እውነተኛው ሕይወት የትኛው ነው?
ከላይ በተጠቀሰው ጥቅስ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ይህ ሕይወት ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው አጥብቆ ሊይዘው የሚገባው “የዘላለም ሕይወት” እንደሆነ ያሳያል። (1 ጢሞቴዎስ 6:12) ይህም ለአብዛኞቹ ሰዎች በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ማለት ነው። የመጀመሪያው ሰው አዳም በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር ተስፋ ነበረው። (ዘፍጥረት 1:26, 27) የሚሞተው “መልካምንና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ” ከበላ ብቻ ነው። (ዘፍጥረት 2:17) ይሁን እንጂ አዳምና ሚስቱ ሔዋን በዓመፅ ከዛፉ ስለ በሉ አምላክ ሞት በየነባቸው። በአምላክ አመለካከት ‘በበሉበት ቀን’ ሞቱና ወደ ሥጋዊ ሞት ማሽቆልቆል ጀመሩ። ከዚያ ወዲያ ሕይወታቸው ቀደም ሲል የነበራቸው ዓይነት አል ሆነም።
ወደ “እውነተኛው ሕይወት” የሚወስደው መንገድ
“እውነተኛውን ሕይወት” ማግኘት እንዲቻል ይሖዋ አምላክ የሰው ልጆችን ለማዳን የሚያስችል ዝግጅት አደረገ። ይህን ዝግጅት ለመረዳት እንድንችል አንድ አነስተኛ ፋብሪካን እንውሰድ። ከዓመታት በፊት ይሠራባቸው የነበረው የመጀመሪያው ሰው የአጠቃቀም መመሪያውን ችላ ብሎ ማሽኖችን በሙሉ አበላሽቶ ስለ ነበረ በውስጡ ያሉት ማሽኖች በሙሉ ጉድለት ያለባቸውና ለሠራተኞቹ ችግር የሚፈጥሩ ናቸው። በወቅቱ ያሉት ሠራተኞች ማድረግ የሚችሉት ባላቸው ማሽን የሚችሉትን ያህል መጠቀም ብቻ ነው። የፋብሪካው ባለቤት ሠራተኞቹን ለመርዳት ሲል ማሽኖቹን መጠገን ስለፈለገ ለዚህ ዓላማ የሚያገለግል ገንዘብ መደበ።
የመጀመሪያው ‘ማሽን ላይ ይሠራ’ የነበረው ሰው አዳም የተሰጠውን ሕይወት እንደ ውድ ሀብት አድርጎ አልያዘም ነበር። ስለዚህ በትክክል ከማይሠራ ማሽን ጋር የሚመሳሰለውን ፍጹም ያልሆነ ሕይወት ለዘሮቹ አስተላለፈ። (ሮሜ 5:12) ለሁኔታው መፍትሔ ማምጣት ካልቻሉት የኋለኞቹ የፋብሪካው ሠራተኞች ጋር በሚመሳሰል መንገድ የአዳም ዘሮች በራሳቸው ጥረት እውነተኛውን ሕይወት ማግኘት አልቻሉም። (መዝሙር 49:7) ይህን ተስፋ አስቆራጭ የሚመስል ሁኔታ ለማስተካከል ይሖዋ ለሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት መልሶ እንዲገዛ አንድያ ልጁን ወደ ምድር ላከው። (ሉቃስ 1:35፤ 1 ጴጥሮስ 1:18, 19) የአምላክ አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል መሥዋዕታዊ ሞት በመሞት ገንዘቡን ማለትም አዳም ካጠፋው ሕይወት ጋር የሚመጣጠነውን ሕይወት ከፈለ። (ማቴዎስ 20:28፤ 1 ጴጥሮስ 2:22) አሁን በዚህ ውድ መሥዋዕት አማካኝነት ይሖዋ እውነተኛውን ሕይወት የሚሰጥበት መሠረት አግኝቷል።
ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች የኢየሱስ መሥዕዋት በምድር ላይ በገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ያስገኝላቸዋል። (መዝሙር 37:29) ይህ ተስፋ ሐርማጌዶን ተብሎ ከተጠራው ‘ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን ከሚሆነው ጦርነት’ ለሚተርፉት ሁሉ ተዘረግቶላቸዋል። (ራእይ 16:14–16) ይህ ጦርነት በምድር ላይ ያለውን ክፋት በሙሉ ያስወግዳል። (መዝሙር 37:9–11) ከሐርማጌዶን በፊት የሞቱና በአምላክ መታሰቢያ ውስጥ ያሉት በምድር ላይ በምትመለሰዋ ገነት ውስጥ ተነሥተው አምላክን ለሚታዘዙ በሙሉ የተዘጋጀላቸውን የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ይኖራቸዋል።—ዮሐንስ 5:28, 29
የአሁኑን ሕይወታችንን እንደ ውድ ሀብት አድርጎ የመያዝ አስፈላጊነት
ይህ ማለት ለአሁኑ ሕይወታችን ቅድስና አክብሮት አለማሳየት ተገቢ ነው ማለት አይደለም። የፋብሪካው ባለቤት ማሽኑን በደንብ የማይጠቀምበትን ሠራተኛ ማሽን በመጠገን ጊዜውንና ገንዘቡን ያጠፋልን? ከዚህ ይልቅ ቀጣሪው አሮጌውን ማሽን በደንብ ለመያዝ የሚችለውን ሁሉ ላደረገ ግለሰብ የተጠገነውን ማሽን በአደራ አይሰጠውምን?
ሕይወት ከይሖዋ የተገኘ ውድ ስጦታ ነው። የዚህ በጎ ስጦታ ምንጭ እንደመሆኑ መጠን እንደ ውድ ሀብት አድርገን እንድንይዘው ይፈልጋል። (መዝሙር 36:9፤ ያዕቆብ 1:17) ኢየሱስ በምድር ላሉ ሰዎች ይሖዋ ስላለው አሳቢነት ሲናገር “የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ የተቆጠረ ነው” ብሏል። (ሉቃስ 12:7) ይሖዋ እስራኤላውያንን ሰው እንዳይገድሉ አዝዟቸዋል፣ ይህም ራስን አለመግደልን እንደሚጨምር የታወቀ ነው። (ዘጸአት 20:13) ይህ ራስን መግደልን እንደ አንድ አማራጭ አድርገን እንዳንመለከት ይረዳናል።
ይሖዋ በፍቅር ስለ ደኅንነታችን እንደሚያስብ በማወቅ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ባሁኑ ጊዜ ያሉትን ልማዶች ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ያገናዝባሉ። ለምሳሌ እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረጉ ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳቸውን እንዲያነጹ’ ስለሚፈለግባቸው ከትንባሆና አስተሳሰብን ከሚያዛቡ ሱስ አስያዥ መድኃኒቶች ይርቃሉ።—2 ቆሮንቶስ 7:1
በተጨማሪም አምላክ “የተረጋጋ ልብ” እንዲኖረንና ከመጥፎ ሥነ ምግባር እንድንቆጠብ በሰጠው ምክር ላይ ለሰው ሕይወት ትኩረት እንደሚሰጥ ታይቷል። (ምሳሌ 14:30፤ ገላትያ 5:19–21) እነዚህን ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎች በመጠበቅ ጤናን ከሚጎዳ ቁጣ፣ በጾታ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎችና ከመሳሰሉት ነገሮች እንጠበቃለን።
ይሖዋ ለሕዝቦቹ ሕይወት ያለው አሳቢነት ከመጠን በላይ ከመብላትና ከመጠን በላይ ከመጠጣት እንዲቆጠቡ በሰጠው ትእዛዝ ላይም ታይቷል። (ዘዳግም 21:18–21፤ ምሳሌ 23:20, 21) ክርስቲያኖች ስግብግብና ሰካራም ሰዎች የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ ማለትም እውነተኛውን ሕይወት ፈጽሞ እንደማያገኙ ማስጠንቀቂያ ተስጥቷቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ 1 ጴጥሮስ 4:3) ልከኝነትን በማበረታታት ይሖዋ ራሳችንን እንድንጠቅም ያስተምረናል። —ኢሳይያስ 48:17
የአምላክን የአቋም ደረጃዎች እያከበርን ስንኖር የአሁኑን ሕይወታችንን እንደ ውድ ሀብት አድርገን እንደምንይዝ እናሳያለን። እርግጥ እውነተኛው ሕይወት ከዚህ የበለጠ ትርጉም አለው። እውነተኛው ሕይወት የዘላለም ሕይወት ስለሆነ እውነተኛ ክርስቲያኖች ካሁኑ ሕይወታቸው የበለጠ ግምት ይሰጡታል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን መሥዋዕት ሲያደርግ ራሱን ለይሖዋ ፈቃድ አስገዝቷል። ለእሱ ለአባቱ መታዘዝ እዚህ ምድር ላይ ከነበረው ሕይወቱ ይበልጥበት ነበር። ኢየሱስ የተከተለው አካሄድ ትንሣኤ እንዲያገኝና በሰማይ የማይጠፋ ሕይወት እንዲቀበል አብቅቶታል። (ሮሜ 6:9) ሞቱ በቤዛዊ መሥዋዕቱ ለሚያምኑ ታዛዥ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወትም ያስገኝላቸዋል።—ዕብራውያን 5:8, 9፤ 12:2
ስለ ደም የተሰጠ እጅግ አስፈላጊ ሕግ
የኢየሱስ ተከታዮች የእሱን ምሳሌ እንደሚያንጸባርቁ የታወቀ ነው። ኢየሱስ እንዳደረገው በሁሉም ነገር አምላክን ማስደሰት ይፈልጋሉ። ይህ በአንድ በኩል አንዳንድ ዶክተሮች ሕይወት አድን ብለው የሚጠሩትን ደምን ለምን እንደማይወስዱ ይጠቁማል። አንድ ሰው ደምን ባለመውሰድ እውነተኛውን ሕይወት እንዴት እንደ ውድ ሀብት አድርጎ ሊይዝ እንደሚችል እስቲ እንመልከት።
እንደ ኢየሱስ ሁሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች በአምላክ ፊት ሕያዋን ሆነው መታየት ይፈልጋሉ፤ ይህም የተሟላ ታዛዥነትን ይጠይቃል። የአምላክ ቃል “ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደምም፣ ከታነቀም፣ ከዝሙትም” ራቁ ሲል የክርስቶስ ተከታዮችን ያዛል። (ሥራ 15:28, 29) ስለ ደም የተሰጠው ይህ ሕግ በክርስቲያኖች ላይ ከሚሠሩት ትእዛዞች መካከል አንዱ የሆነው ለምንድን ነው?
ለእስራኤላውያን የተሰጠው ሕግ ከደም እንዲርቁ ይጠይቅባቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 17:13, 14) ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር አይደሉም። ይሁን እንጂ ደም እንዳይበላ የተሰጠው ትእዛዝ ከሕጉ በፊት እንደነበረ ይገነዘባሉ፤ ይህ ትእዛዝ ቀደም ሲል ከጥፋት ውኃ በኋላ ለኖኅ ተሰጥቶት ነበር። (ዘፍጥረት 9:3, 4፤ ቆላስይስ 2:13, 14) ይህ ትእዛዝ የሁሉም የምድር ብሔራት ወላጅ ለሆነው ለኖኅ ዝርያዎች በሙሉ ይሠራል። (ዘፍጥረት 10:32) በተጨማሪም የሙሴ ሕግ አምላክ ደምን እንደ ቅዱስ ነገር አድርጎ ማየቱን የቀጠለበትን ምክንያት እንድናውቅ ይረዳናል። ከማንኛውም ዓይነት ደም እንዲርቁ አምላክ እስራኤላውያንን ካዘዛቸው በኋላ እንዲህ አለ፦ “የሥጋ ሁሉ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ ደሙ ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት።” (ዘሌዋውያን 17:11) ደም በመሠዊያው ላይ ለመሥዕዋት ብቻ እንዲቀርብ አምላክ አዝዞ ነበር። ስለ ደም ቅድስና የሰጠው ሕግ በምድር ላይ ባለው ሕይወት ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዳለው ያሳያል። (ሕዝቅኤል 18:4፤ ራእይ 4:11) ሕይወታችንን ከይሖዋ አመለካከት አንፃር ስናየው ሕይወታችን የእኛ ሳይሆን አምላክ ለእኛ በአደራ የሰጠን ብቻ መሆኑን እንገነዘባለን።
በምሳሌያችን ላይ የተጠቀሰው ሠራተኛ ለማሽኑ ኃላፊነት እንዳለበት ሁሉ እኛም የአሁኑ ሕይወታችን በአደራ ተሰጥቶናል። ማሽንህ ጥገና ካስፈለገውና መካኒኩ በአጠቃቀም መመሪያው ላይ በግልጽ የተከለከሉ ዕቃዎችን ተጠቅሜ ልሥራ ቢል ምን ታደርጋለህ? ማሽኑ የአጠቃቀም መመሪያው በሚለው መሠረት መጠገን ይችል እንደሆነ ለመረዳት ሌሎች መካኒኮችን አታማክርምን? የሰው ሕይወት ከማሽን ይበልጥ አስፈላጊና የተወሳሰበ ነው። ሰዎችን በሕይወት ለማቆየት የሚያገለግል መመሪያ በሆነው በመንፈስ አነሣሽነት በተጻፈው ቃሉ ላይ ፈጣሪያችን ሕይወትን ለማራዘም ሲባል በደም መጠቀምን ከልክሏል። (ዘዳግም 32:46, 47፤ ፊልጵስዩስ 2:16) የዚህን መመሪያ ብቃቶች በጥብቅ መከተል ምክንያታዊ አይደለምን?
ያለ ደም ሕክምና እንዲደረግላቸው የሚጠይቁ ክርስቲያን ሕሙማን ሁሉንም የሕክምና ዓይነት አንቀበልም አይሉም። ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ ሕይወታቸው ያላቸውን አክብሮት የሚያሳይ ሕክምና እንዲደረግላቸው መጠየቃቸው ብቻ ነው። ክርስቲያኖች የወሰዱትን አቋም በድፍረት ያከበሩ ዶክተሮች ከጥያቄያቸው ጋር በሚስማማ መንገድ ማከም የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች መሥክረዋል። “ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘቴ አዲስ የሥነ ምግባር እሴቶች አስገኝቶልኛል” ሲሉ ብዙ ጊዜ ታካሚዎች ደም እንዲወስዱ ያደርጉ የነበሩ አንድ የቀዶ ሕክምና ሐኪም ተናግረዋል። አሁን የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑትንም እንኳን ያለ ደም ለማከም ይሞክራሉ።
እውነተኛውን ሕይወት እንደ ውድ ሀብት አድርጎ መያዝ
እኚህ የቀዶ ሕክምና ሐኪም የይሖዋ ምሥክሮችን ሲያክሙ ያገኟቸው አዲስ የሥነ ምግባር እሴቶች ምንድን ናቸው? አሁን አንድን በሽተኛ ማከም በበሽታ የተጎዳውን አካሉን ብቻ ሳይሆን ግለሰቡን ማከም መሆኑን ተገንዝበዋል። በሽተኛው ለአካላዊ፣ ለመንፈሳዊና ለስሜታዊ ደህንነቱ የተሻለ እንክብካቤ እንዲደረግለት ራሱ መጠየቅ እንዲችል ሊፈቀድለት አይገባምን?
ለ15 ዓመቷ ኩሚኮ ሉኪሚያ የተባለውን ገዳይ በሽታ ለመታከም ሲባል ደም መውሰድ ከሁሉ አስከፊ ምርጫ ነበር። በዚህ መንገድ ለጥቂት ሳምንታት፣ ወራት፣ ወይም ዓመታት ሕይወቷን ለማራዘም መጣር ለወደፊቱ ከሚያስገኝላት ውጤት አንፃር ሲታይ ምንም አልነበረም። ከምሥክሮቹ አንዷ በመሆን የአሁኑን ሕይወቷን ለይሖዋ አምላክ የወሰነች እንደመሆኗ መጠን የሕይወትንና የደምን ቅድስና ታከብራለች። አባቷና ሌሎች ዘመዶቿ አቋሟን ክፉኛ ቢቃወሙም እንኳን ኩሚኮ ጽኑ ነበረች። ዶክተሯ በአንድ ወቅት “አምላክሽ ስሕተቶችን ይቅር የሚል ከሆነ ደም ብትወስጂ ይቅር አይልሽም?” በማለት ጠይቋት ነበር። ኩሚኮ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነቷን ለመካድና ወደ ጎን ገሸሽ ለማድረግ አልፈለገችም። “የሕይወትን ቃል አጥብቃ በመያዝ” አቋሟን ጠበቀች። (ፊልጵስዩስ 2:16 አዓት) አማኝ ያልሆኑ አያቷ እንዳሉት “ኩሚኮ እምነቷን አልተወችም።” ብዙም ሳይቆይ የአባቷና የአያቷም ሆነ የሚያክሟት ዶክተሮች አመለካከት ተለወጠ።
ኩሚኮ በትንሣኤ ሊያስነሣት በሚችለው በይሖዋ አምላክ ላይ የነበራት ጠንካራ እምነት የብዙዎችን ልብ ነክቶ ነበር። ገና በሕይወት ሳለች አባቷን እንዲህ ስትል ትለምነው ነበር፦ “ብሞት እንኳን በገነት ውስጥ ትንሣኤ አገኛለሁ። ሆኖም በአርማጌዶን ከጠፋህ አላገኝህም። ስለዚህ እባክህ መጽሐፍ ቅዱስን አጥና።” አባቷ “ሲሻልሽ አጠናለሁ” ይላት ነበር። ይሁን እንጂ ኩሚኮ በማይሽር ሕመሟ ስትሞት አባቷ በሬሳ ሳጥኗ ውስጥ “ኩሚኮ በገነት አገኝሻለሁ” የሚል ማስታወሻ አስፍሮ ነበር። ከቀብሩ ንግግር በኋላ በቀብሩ ላይ ለተገኙት ሲናገር እንዲህ አለ፦ “ኩሚኮን በገነት አገኝሻለሁ ብዬ ቃል ገብቼላታለሁ። ምንም እንኳን በቂ ጥናት ባለማድረጌ እስካሁን ባላምንበትም በጥንቃቄ ልመረምረው ወስኛለሁ። እባካችሁ እርዱኝ።” ሌሎች የቤተሰቧ አባሎችም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረዋል።
ኩሚኮ ለሕይወት እውነተኛ አክብሮት የነበራት ሲሆን መኖር ትፈልግ ነበር። ዶክተሮቿ የአሁኑን ሕይወቷን ለማዳን ያደረጉላትን ጥረት ሁሉ አድንቃለች። ሆኖም ፈጣሪ በሰጠው መመሪያ መጽሐፍ ውስጥ ካሉት መመሪያዎች ጋር በመስማማት እውነተኛውን ሕይወት እንደ ውድ ሀብት አድርጋ እንደምትይዝ አረጋግጣለች። ይህም በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች በምድር ላይ በገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ያስገኛል። አንተስ ከእነሱ መካከል ትሆናለህን?