የሃይማኖት የወደፊቱ ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንጻር ሲታይ
ክፍል 12:-100–476 እዘአ—የወንጌሉን ብርሃን ማዳፈን
“ሰዎች ራሳቸውን ከማጥራት ይልቅ እውነትን መበረዝ በጣም ቀላል ሆኖ አግኝተውታል።”—ቻርልስ ካሌብ ኮልተን፣ የ19ኛው መቶ ዘመን እንግሊዛዊ ቄስ
በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ስድስተኛ የዓለም ኃያል መንግሥት የሆነው የሮማ መንግሥት የክርስትናን መስራች ከገደለበት ከ33 እዘአ ጀምሮ የክርስቲያኖች ባላጋራ ሆኖ ቆይቷል። ክርስቲያኖችን ከማሰሩም በላይ አንዳንዶቹ በአንበሶች እንዲበሉ አድርጓል። ይሁን እንጂ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ሮማውያን ክርስቲያኖች ለኔሮ የአትክልት ሥፍራ መብራት እንዲሆኑ እንደችቦ ተቃጥለው እንደሚሞቱ በተዛተባቸው ጊዜ እንኳን መንፈሳዊ ብርሃናቸው እንዲታይ ከማድረግ ወደኋላ አላሉም። (ማቴዎስ 5:14) ከጊዜ በኋላ ግን ሁኔታው ተለወጠ።
ፍሮም ክራይስት ቱ ኮንስታንታይን የተባለው መጽሐፍ “በሦስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ቤተ ክርስቲያን ከበሬታ ማግኘት ጀምራ ነበር” ይላል። ይሁን እንጂ ከበሬታ ለማግኘት መክፈል የነበረባት ዋጋ ነበር። ሃይማኖታዊ “አቋሟን ዝቅ” ማድረግ ነበረባት። በዚህ ምክንያት “ለክርስቲያናዊው እምነት ክርስቲያናዊ አኗኗር እንደ ግዳጅ መታየቱ ቀረ።”
የወንጌል ብርሃን በጣም ተዳክሞ ጭል ጭል ማለት ጀመረ። ኢምፔሪያል ሮም የተባለው መጽሐፍ ደግሞ እንደሚከተለው ይላል:- “በአራተኛው መቶ ዘመን ላይ ክርስቲያን ጸሐፊዎች በአንድ ጊዜ ክርስቲያንም ሮማዊም መሆን ከመቻሉም በላይ ረዥሙ የሮማ ታሪክ የክርስትና ምዕራፍ መጀመሪያ ነው ማለት ጀምረው ነበር። . . . ይህም የሮማን መንግሥት ያቋቋመው አምላክ ነው የሚል አንድምታ ያለው አባባል ነው።”
የሮማ ንጉሠ ነገሥት የነበረው ታላቁ ቆስጠንጢኖስ ይህን የመሰለ አመለካከት ነበረው። ቆስጠንጢኖስ በ313 እዘአ ክርስትና ሕጋዊ ሃይማኖት እንዲሆን አደረገ። ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት እንዲጣመሩ፣ ሃይማኖታዊ መሪዎችም የመንግሥት አገልጋዮች እንዲሆኑ በማድረጉና በዚህም ድርጊቱ መንግሥት ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን እንዲቆጣጠር በመፍቀዱ በክርስትና ላይ ታላቅ በደል ፈጽሟል።
ከዚህ ቀደም ሲል በሁለተኛው መቶ ዘመን የአንጾኪያ ጳጳስ የነበረው ኢግናሽየስ አዲስ ዓይነት የጉባኤ አስተዳደር ጀምሮ ነበር። ጉባኤዎች በሽማግሌዎች ቡድን መተዳደራቸው ቀርቶ በእያንዳንዱ ጉባኤ ሙሉ ሥልጣን የሚኖረው ግለሰብ የንግሥና ደረጃ በተሰጠው መንበረ ጵጵስና መሾም ጀመረ። ከአንድ መቶ ዘመን በኋላ ደግሞ የካርቴጅ ጳጳስ የነበረው ሲፕሪያን ይህን የማዕረግ ተዋረድ ያለውን የቤተ ክህነት አስተዳደር አስፋፍቶ ሰባት የሥልጣን ተዋረድ እንዲኖርና የመጨረሻው ከፍተኛ ደረጃ በጳጳሱ እንዲያዝ አድርጓል። ከጳጳሱ በታች ቄሶች፣ ሊቀ ዲያቆናት፣ ዲያቆናትና ሌሎች ማዕረጎች ያላቸው ካህናት ይኖራሉ። የምዕራብ ቤተ ክርስቲያን ከጊዜ በኋላ ስምንተኛ ደረጃ ስትጨምር የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ግን በአምስት የማዕረግ ደረጃዎች ጸንታለች።
ይህ የመንግሥት ድጋፍ የተሰጠው የቤተ ክርስቲያን አመራርና አስተዳደር ወደ ምን ነገር አመራ? ኢምፔሪያል ሮም የተባለው መጽሐፍ እንዲህ በማለት ያብራራል:- “በክርስቲያኖች የመጨረሻውና ታላቁ የስደት ማዕበል ከወረደ ከ80 ዓመት በኋላ ቤተ ክርስቲያን ራስዋ መናፍቃንን ማሳደድ ጀመረች። ቀሳውስትዋም ከንጉሠ ነገሥቱ የማይተናነስ ፍጹም ሥልጣን አገኙ።” ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ‘የዚህ ዓለም ክፍል እንዳይሆኑና’ ዓለምን በኃይል ሳይሆን በእምነታቸው ድል እንዲነሱ የተናገረው ቃል ከዚህ ሁኔታ ጋር የማይስማማ እንደሆነ ግልጽ ነው።— ዮሐንስ 16:33፤ 17:14፤ ከ1 ዮሐንስ 5:4 ጋር አወዳድር።
“ቅዱሳን” እና የግሪክ አማልክት
ከቆስጠንጢኖስ ዘመን በፊትም እንኳን ቢሆን አረመኔያዊ አስተሳሰቦች የክርስትናን ሃይማኖት መበከል ጀምረው ነበር። በሮማውያን ሃይማኖት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድረው የነበሩት የግሪክ አፈታሪካዊ አማልክት በክርስትና ሃይማኖት ላይ ተጽእኖ አሳድረዋል። ሮማን ሚቶሎጂ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ሮም አፄያዊ ኃያል መንግሥት በሆነችበት ጊዜ ጁፒተር የግሪካውያን አምላክ ከሆነው ዘዩስ ጋር አንድ ሆኖ ነበር። . . . ቆየት ብሎም ጁፒተር ኦፕቲመስ ማክሲመስ፣ ከሁሉ የተሻለውና የበለጠው ተብሎ መመለክ ጀመረ። ይህ ስያሜ ወደ ክርስትና ከመግባቱም በላይ በብዙ የሐውልት ቅርጾች ላይ ይገኛል።” ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ በማከል “በክርስትና ውስጥ የግሪካውያን ጀግኖችና አማልክት የቅድስና ቦታ ተሰጣቸው” ይላል።
ኤም ኤ ስሚዝ የተባሉት ጸሐፊ በዚህ ምክንያት የተፈጠረውን ሁኔታ እንደሚከተለው በማለት አብራርተዋል:- “የተለያዩ አገሮች አማልክት አንዳቸው ከሌላው ጋር መደባለቅና በየአገሮቹ መካከል ያለው የአማልክት ልዩነት መጥፋት ጀመረ። . . . ሰዎች የተለያዩት የአማልክት ስሞች ለአንድ ታላቅ ኃይል የተሰጡ የተለያዩ ስሞች እንደሆኑ አድርገው መመልከት ጀመሩ። . . . የግብጻውያን አይሲስ፣ የኤፌሶን ሰዎች አርጤምስና የሶርያውያን አስታሮት በእኩልነት ደረጃ ሊታዩ ይችሉ ነበር። የግሪካውያን ዘዩስ፣ የሮማውያን ጁፒተር፣ የግብጻውያን አሞን ረ እና የአይሁዳውያን ያህዌህ እንኳ ለአንዱ ታላቅ ኃይል ሊሰጡ እንደሚችሉ ስሞች ተደርገው ሊታዩ ይችሉ ነበር።”
ክርስትና በሮማ ግዛት ከግሪካውያንና ከሮማውያን አስተሳሰብ ጋር እየተዋሃደ በነበረበት በዚህ ጊዜ በሌሎች አካባቢዎችም ለውጥ ማድረጉ አልቀረም። የሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ማዕከላት በሆኑት በእስክንድርያ፣ በአንጾኪያ፣ በካርቴጅና በኤዴሳ የተለያዩ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች መስፋፋት ጀምረው ነበር። ለምሳሌ የካንተርበሪ ገዳም አንግሊካዊ አለቃ የነበሩት ኸርበርት ዋዳምስ የእስክንድርያ ክርስቲያኖች አብዛኞቹ “የብሉይ ኪዳን” መግለጫዎች ምሳሌያዊ ትርጉም ብቻ እንዳላቸው ያምኑ የነበረ ሲሆን “የፕላቶ ፍልስፍናም ከፍተኛ ተጽእኖ” አሳድሮባቸው እንደነበረ ተናግረዋል። የአንጾኪያ ክርስቲያኖች ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን መግለጫዎች ይረዱ የነበረው ቃል በቃል ከመሆኑም በላይ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጠንከር ያለ አመለካከት ነበራቸው።
በመካከላቸው የነበረው ልዩነት በቦታ ርቀት፣ በመገናኛ መታጣትና በቋንቋ አለመግባባት ምክንያት እየተስፋፋ ሄደ። ይሁን እንጂ ለዚህ ሁኔታ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ለግል ጥቅማቸው ሲሉ እውነትን ለመበረዝና የወንጌልን ብርሃን ለማዳፈን ፈቃደኛ የሆኑት የሃይማኖት መሪዎች የነበራቸው በራስ አስተሳሰብ የመመራትና የራስ ወዳድነት መንፈስ ነው።
“በውሸት ‘እውቀት’ ከተባለ”
ክርስትና ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ጀምሮ በሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶች መነካቱ አልቀረም። በዚህም ምክንያት ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “በውሸት እውቀት ከተባለ . . . መለፍለፍና መከራከር” እንዲርቅ አስጠንቅቆታል። (1 ጢሞቴዎስ 6:20, 21) ይህን ያለው በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ ምናልባትም ሳይመን ማገስ በተባለ ግለሰብ ተጀምሮ በሁለተኛው መቶ ዘመን በጣም ተስፋፍቶ ስለነበረው የግኖስቲስዝም እንቅስቃሴ ሳይሆን አይቀርም። አንዳንድ ሊቃውንት ይህ ግለሰብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሥራ 8:9 ላይ የተጠቀሰው ሲሞን ሳይሆን አይቀርም ይላሉ።
ግኖስቲስዝም የተባለው ስያሜ የተገኘው “እውቀት” የሚል ትርጉም ካለው ግኖሲስ ከተባለ የግሪክኛ ቃል ነው። የግኖስቲስዝም ተከታዮች መዳን ለተራ ክርስቲያኖች ባልታወቀና ምሥጢራዊ በሆኑ መንገዶች በሚገለጥ ጥልቅ እውቀት ላይ የተመካ ነው ብለው ይከራከሩ ነበር። ይህን እውቀት ማግኘታቸው ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪልጅን እንደሚለው “በክርስቶስ የተገለጠውን ውስጣዊ እውነት” ለማስተማር እንደሚያስችላቸው ያምኑ ነበር።
የግኖስቲስዝም አስተሳሰብ ምንጮች በርካታ ናቸው። የግኖስቲስዝም ተከታዮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለተጠቀሱ ቁጥሮች ስውር ትርጉም የመስጠትን ልማድ ከባቢሎን ወስደዋል። ይህም ምሥጢራዊ እውነቶችን እንደሚገልጥላቸው ያምኑ ነበር። በተጨማሪም መንፈስ ጥሩ ሲሆን ቁስ አካል ግን በባሕርዩ ክፉ እንደሆነ ያስተምሩ ነበር። ካርል ፍሪክ የተባሉት ጀርመናዊ ደራሲ እንደሚሉት “ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ከፋርሳውያን የሁለት ባሕርይ እምነትና ከሩቅ ምሥራቁ የቻይናውያን ‘ይን’ እና ‘ያንግ’ ፍልስፍና ጋር አንድ ነው።” በግኖስቲክ ጽሑፎች ላይ የተገለጸው “ክርስትና” በክርስቲያናዊ መረጃዎች ላይ የተመሠረተ አልነበረም። ታዲያ እንዴት “ክርስቶስ የገለጠው ውስጣዊ እውነት ሊሆን ይችላል”?
አር ኢ ኦ ዋይት የተባሉት ምሁር ግኖስቲስዝም “የግምታዊ ፍልስፍና፣ የአጉል እምነት፣ የከፊል ጥንቆላ፣ አንዳንድ ጊዜም የጭፍንና የብልግና አምልኮ ሥርዓቶች ውህደት ነው” ብለዋል። የአሪዞና ዩኒቨርሲቲው አንድሩ ኤም ግሪሊ እንዲህ ብለዋል:- “የግኖስቲኮች ኢየሱስ አንዳንድ ጊዜ ራሱን በራሱ የሚቃረን፣ አንዳንድ ጊዜ ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከወፈፍተኛ ያልተሻለ ነው።”
ስለ ክርስቶስ የተገለጸውን እውነት ማጣመም
ስለ ክርስቶስ የተገለጸውን እውነት ያጣመሙት ግኖስቲኮች ብቻ አልነበሩም። በአምስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ የነበረው ኔስቶሪየስ ክርስቶስ ሁለት ባሕርይ በአንድ አካል የተዋሃደው፣ ማለትም ሰው የሆነው ኢየሱስና መለኮታዊው የአምላክ ልጅ በአንድነት የተዋሃዱበት እንደሆነ አስተማረ። ማርያም ክርስቶስን በወለደች ጊዜ የወለደችው ሰው የሆነውን ኢየሱስ እንጂ መለኮታዊውን ልጅ አልነበረም። ይህ አመለካከት በአምላክና በልጁ መካከል ያለው ውህደት አንዳቸው ከሌላው ሊነጠል የማይችል፣ ኢየሱስ ሁለት ባሕርያት ያሉት ቢሆንም ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው የሆነ አንድ አካል ብቻ ያለው እንደሆነ ከሚያምኑት የተዋህዶ አማኞች ጋር አልተስማማም። በዚህ መሠረት ማርያም የወለደችው ሰው የሆነውን ኢየሱስ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ነበር።
ሁለቱም ንድፈ ሐሳቦች በአራተኛው መቶ ዘመን ተነስቶ ከነበረው ውዝግብ ያቆጠቆጡ ናቸው። የእስክንድርያ ካህን የነበረው አርዮስ ክርስቶስ ከአብ ያነሰ ነው ብሎ ተከራከረ። በዚህም ምክንያት ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ዝምድና በሚገልጽበት ጊዜ ሆሞኡሲዮስ (የባሕርይና የሕልውና አንድነት) በተባለው ቃል ለመጠቀም አልፈቀደም። በ325 እዘአ የተደረገው የኒቂያ ጉባኤ ኢየሱስ ‘ከአብ ጋር በባሕርይም ሆነ በሕልውና አንድ እንደሆነ’ በመደንገግ የአርዮስን እምነት ተቃወመ። በ451 እዘአ የተደረገው የኬልቄዶን ጉባኤ ክርስቶስ ሥጋ የለበሰ እግዚአብሔር እንደሆነ ገለጠ። በዚህ ጊዜ ክርስቶስ እርሱና አባቱ ሁለት የተለያዩ አካላት እንደሆኑና በምንም ዓይነት መንገድ እኩል እንዳልሆኑ ያስተማረው ትምህርት ባቢሎናውያን፣ ግብጻውያንና ግሪካውያን ያምኑ በነበረው ሦስትነት በአንድነት ያለው አምላክ ተዋጠ።— ማርቆስ 13:32፤ ዮሐንስ 14:28
እንደ እውነቱ ከሆነ አርዮስ ከመወለዱ ጥቂት ቀደም ብሎ የክርስቲያኖች ቋንቋ ክፍል በሆነው “ትሪኒታስ ” የተባለ ቃል መጠቀም የጀመረው የሰሜን አፍሪካ ቤተ ክርስቲያን አባል የነበረው ተርቱሊያን (160–230 አዘአ ገደማ) ነው። ከግሪክኛ ቋንቋ ይልቅ በላቲን ቋንቋ በርካታ መጻሕፍትን ለመጻፍ የመጀመሪያ የሆነው ተርቱሊያን ለምዕራባውያን ሃይማኖት መሠረት በመጣል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረገ ሰው ነበር። ሁለት መቶ ዓመታት ያህል ቆይቶ የተነሳው ሌላው የሰሜን አፍሪካ ሃይማኖታዊ ሊቅ “ቅዱስ” አውግስጦስ ነው። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንደሚለው “[አውግስጦስ] ከጥንት የክርስትና ሊቃውንት አንዱ እንደሆነ ይታሰባል።” ይሁን እንጂ ይህ ኢንሳይክሎፔድያ ቀጥሎ የሚናገረው ቃል ሁሉንም ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች ሊያሳስብ የሚገባ ነው። “የዚህ ሰው አእምሮ የአዲስ ኪዳን ሃይማኖት ከፕላቶ የግሪካውያን ፍልስፍና ጋር ሙሉ በሙሉ የተዋሃደበትና የዚህ ውህደት ውጤት የሆነው ትምህርት ወደ መካከለኛው ዘመን የካቶሊክ እምነትና ወደ ተሐድሶ ዘመን የፕሮቴስታንት እምነት የተላለፈበት ነው።”
የካቶሊክ እምነት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ወደቀ
በአራተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ገደማ ላይ ንጉሠ ነገሥት ቴዎዶስየስ ቀዳማዊ የካቶሊክ ሃይማኖት የመንግሥት ሃይማኖት እንዲሆን በማወጅ ቆስጠንጢኖስ ጀምሮት የነበረውን ሥራ ፍጻሜ ላይ አደረሰ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ቆስጠንጢኖስ ፈርቶ የነበረው ሁኔታ ደረሰ። የሮማ ግዛት ለሁለት ተከፈለ። በ410 እዘአ የሮም መንግሥት ለብዙ ዘመናት ጥቃት ለመሰንዘር ሲያስፈራሩት በነበሩት ቪሲጎት በተባሉ ጀርመናውያን ሕዝቦች ተወረረ። በ476 እዘአ ኦዶአሰር የተባለው ጀርመናዊ ጄኔራል የምዕራቡን ንጉሠ ነገሥት ገልብጦ ራሱን ንጉሥ ስላደረገ የምዕራቡ የሮማ ግዛት ፍጻሜ ሆነ።
የካቶሊክ ሃይማኖት በዚህ በተፈጠረው አዲስ ሁኔታ ምን ይደርስበት ይሆን? በ500 እዘአ ላይ 22 በመቶ የሚሆኑትን የዓለም ሕዝቦች እቆጣጠራለሁ ይል ነበር። ይሁን እንጂ ከእነዚህ 43 ሚልዮን እንደሚደርሱ ከሚገመቱት ሰዎች አብዛኞቹ ራሳቸውን ከማጥራት ይልቅ እውነትን መበከል ይበልጥ አመቺ ሆኖላቸው በነበሩት ሃይማኖታዊ መሪዎች ከፍተኛ በደል ይፈጸምባቸው ነበር። የእውነተኛው ክርስትና ብርሃን ተዳፈነ። ይሁን እንጂ በሚቀጥለው እትማችን እንደሚገለጸው ብዙም ሳይቆይ “ከዚህ ድቅድቅ ጨለማ” ውስጥ “ቅዱስ” የሆነ ነገር ይወለዳል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዳንድ የግኖስቲስዝም እምነቶች
ማርሲዮን (ሁለተኛ መቶ ዘመን) ከኢየሱስና ከኢየሱስ አባት የሚያንሰውና ፍጹም ያልሆነው “የብሉይ ኪዳን” አምላክ ከማይታወቀውና የፍቅር አምላክ ከሆነው “የአዲስ ኪዳን” አምላክ የተለየ እንደሆነ ገልጾ ነበር። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪልጅን “የግኖስቲስዝም መሠረቱ ያልታወቀ አምላክ አለ” የሚለው እምነት ነው ይላል። ይህ የማይታወቅ አምላክ “የሰው አእምሮ ሊደርስበት የማይችል የመጨረሻው ታላቅ ጥበበኛ” ነው ተብሏል። በሌላው በኩል ግን የግዑዙ ዓለም ፈጣሪ ከዚህ አምላክ ያነሰና እውቀቱ ፍጹም ያልሆነ ዴሚኡርጅ ተብሎ የሚጠራ ነው ይላሉ።
ሞንታነስ (ሁለተኛ መቶ ዘመን) ታላቁን የክርስቶስ መመለስና የአዲሲቱን ኢየሩሳሌም ዛሬ ቱርክ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መቋቋም ይሰብክ ነበር። ትልቅ ትኩረት ይሰጥ የነበረው ከመሠረተ ትምህርት ይልቅ ለምግባር ስለነበረ የጥንቱን የክርስትና የአኗኗር ሥርዓት ለመመለስ ሞክሯል። ይሁን እንጂ የዚህ ሰው እንቅስቃሴ በነበረው የአክራሪነት ባሕርይ ተውጦ ራሱ ያወግዝ በነበረው ልቅ ምግባር ተሸነፈ።
ቫለንቲኑስ (ሁለተኛ መቶ ዘመን) ግሪካዊ ባለ ቅኔና በዘመናት ከተነሱት ግኖስቲኮች በሙሉ ታላቅ ሲሆን ረቂቅና መንፈሣዊ የሆነው የኢየሱስ አካል በማርያም አካል ውስጥ አለፈ እንጂ ከእርሷ አልተወለደም ይል ነበር። ግኖስቲኮች ሥጋዊ አካል ያለው ነገር ሁሉ ክፉ ነው ብለው ያምኑ ስለነበረ ነው። በዚህ ምክንያት ኢየሱስ ሥጋዊ አካል ቢኖረው ኖሮ ክፉ ይሆን ነበር። ክርስቶስ በሥጋ አልመጣም ብለው ያምኑ የነበሩት ግኖስቲኮች ኢየሱስ በሰብዓዊነት ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በማስመሰል ብቻ የተደረጉ ናቸው ብለው ያስተምራሉ። ይህም ሞቱንና ትንሣኤውን ይጨምራል።
ማነስ (ሦስተኛ መቶ ዘመን) ራሱን “ወደ ባቢሎን የመጣ የአምላክ መልእክተኛ” ብሎ ይጠራ ስለነበረ በአረብኛ “ባቢሎናዊ” የሚል ትርጉም ባለው አልባቢሊዩ በተባለ ስም ይጠራ ነበር። የክርስትናን፣ የቡድሂዝምንና የዞሮአስተርያኒዝምን አንዳንድ ገጽታዎች በማዋሃድ ለመላው ዓለም የሚሆን ሃይማኖት ለመመስረት ሞክሮ ነበር።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቆስጠንጢኖስ ክርስትናን ከአረማውያን አምልኮ ጋር በማጣመር የወንጌል ብርሃን እንዲዳፈን ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል