መንፈሳዊ እድገት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማሃል?
“ለሰዎች ለማንበብ፣ አጥብቀህ ለመምከርና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ።”—1 ጢሞ. 4:13
1, 2. (ሀ) በዚህ የመጨረሻ ዘመን የኢሳይያስ 60:22 ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ውስጥ ምን እንደሚያስፈልግ እየታየ ነው?
“ጥቂት የሆነው ሺህ፣ ትንሽ የሆነውም ኃያል ብሔር ይሆናል።” (ኢሳ. 60:22) ይህ ትንቢት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ፍጻሜውን እያገኘ ነው። በ2015 የአገልግሎት ዓመት 8,220,105 የመንግሥቱ አስፋፊዎች በዓለም ዙሪያ በቅንዓት ምሥራቹን መስበካቸው ይህን ያሳያል! የትንቢቱ የመጨረሻ ክፍል፣ ሁሉንም ክርስቲያኖች በግለሰብ ደረጃ ይመለከታል፤ ምክንያቱም ሰማያዊ አባታችን “እኔ ይሖዋ፣ ይህን በራሱ ጊዜ አፋጥነዋለሁ” ብሏል። አንድ መኪና ፍጥነቱን እየጨመረ ሲሄድ ተሳፋሪዎቹ ይህን እንደሚያስተውሉ ሁሉ እኛም ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ይበልጥ እየተጧጧፈ እንደሆነ ማስተዋላችን አይቀርም። ታዲያ በዚህ ረገድ ምን እያደረግን ነው? የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት ለመስበክ የቻልነውን ያህል እየጣርን ነው? ብዙ ወንድሞችና እህቶች በዘወትር ወይም በረዳት አቅኚነት እያገለገሉ ነው። ሌሎች ደግሞ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውረን እንድናገለግል ወይም በሌሎች ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች እንድንካፈል ለሚቀርበው ጥሪ ምላሽ እየሰጡ ነው፤ ታዲያ ይህ የሚያስደስት አይደለም?
2 በሌላ በኩል ደግሞ ተጨማሪ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ እያስተዋልን ነው። በየዓመቱ 2,000 ገደማ የሚሆኑ ጉባኤዎች ይመሠረታሉ። አዲስ በሚቋቋመው በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ 5 ሽማግሌዎች ያገልግሉ ቢባል እንኳ በየዓመቱ 10,000 የጉባኤ አገልጋዮች፣ የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞች የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ማሟላት አለባቸው። ከዚህም በተጨማሪ ወንድሞችም ሆንን እህቶች ‘ከጌታ ሥራ’ ጋር በተያያዘ ልናከናውነው የምንችለው ብዙ ነገር አለ።—1 ቆሮ. 15:58
መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ሲባል ምን ማለት ነው?
3, 4. ምን ዓይነት መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣት ትችላለህ?
3 አንደኛ ጢሞቴዎስ 3:1ን አንብብ። እዚህ ላይ ‘መጣጣር’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ፣ አንድን ነገር ምናልባትም በቀላሉ የማይደረስበትን ነገር ለመያዝ መንጠራራት የሚል መልእክት ያስተላልፋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ቃል የተጠቀመው መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ጥረት እንደሚጠይቅ ለማጉላት ነው። በጉባኤው ውስጥ ወደፊት ሊያከናውን ስለሚችለው ነገር እያሰበ ያለን አንድ ወንድም ወደ አእምሯችን እናምጣ። በአሁኑ ጊዜ የጉባኤ አገልጋይ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ክርስቲያናዊ ባሕርያት ማዳበር እንዳለበት ይገነዘባል። መጀመሪያ፣ የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ለማሟላት ይጥራል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ለማሟላት ግብ ያወጣል። ይህ ወንድም፣ የጉባኤ አገልጋይም ሆነ ሽማግሌ ለመሆን ጥረት በሚያደርግበት ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነት ለመሸከም የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ለማሟላት ተግቶ ይሠራል።
4 በተመሳሳይም አቅኚ፣ ቤቴላዊ እንዲሁም የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው ማገልገል የሚፈልጉ ወንድሞችና እህቶች፣ ግባቸው ላይ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው። የአምላክ ቃል፣ ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች እድገት እንዲያደርጉ የሚያበረታታው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
በመንፈሳዊ ይበልጥ ለማደግ ተጣጣር
5. ወጣቶች ጉልበታቸውን ለመንግሥቱ አገልግሎት ማዋል የሚችሉት እንዴት ነው?
5 ወጣቶች በይሖዋ አገልግሎት ብዙ ነገር ለማከናወን የሚያስችል ጉልበት አላቸው። (ምሳሌ 20:29ን አንብብ።) በቤቴል የሚያገለግሉ አንዳንድ ወጣቶች፣ መጽሐፍ ቅዱሶችንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማተሙና በመጠረዙ ሥራ ይካፈላሉ። ጥቂት የማይባሉ ወጣት ወንድሞችና እህቶች የመንግሥት አዳራሾችን በመገንባትና በማደስ ሥራ ይሳተፋሉ። የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ ወጣቶች፣ ተሞክሮ ካላቸው ወንድሞች ጋር በመሆን በአደጋው ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ ይሰጣሉ። እንዲሁም በርካታ ወጣት አቅኚዎች ምሥራቹን ለመስበክ ሲሉ ሌላ ቋንቋ ይማራሉ፤ ወይም ወደ ሌላ አካባቢ ተዛውረው ያገለግላሉ።
6-8. (ሀ) አንድ ወጣት አምላክን ከማገልገል ጋር በተያያዘ የአመለካከት ለውጥ እንዲያደርግ የረዳው ምንድን ነው? ይህስ ምን ውጤት አስገኘለት? (ለ) ‘ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቀምሰን ማየት’ የምንችለው እንዴት ነው?
6 አምላክን በሙሉ ልባችን ማገልገል አስፈላጊ መሆኑን እንደምትገነዘብ የታወቀ ነው። ሆኖም አሮን የተባለ ወንድም የነበረው ዓይነት ስሜት ቢያድርብህ ምን ታደርጋለህ? አሮን ያደገው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ቢሆንም “በስብሰባዎች ላይ መገኘትና በመስክ አገልግሎት መካፈል ይሰለቸኝ ነበር” በማለት በሐቀኝነት ተናግሯል። አምላክን በደስታ ማገልገል እየፈለገ ደስተኛ መሆን ያልቻለው ለምን እንደሆነ ያሳስበው ነበር። ታዲያ ምን አደረገ?
7 አሮን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብን እንዲሁም ለስብሰባዎች መዘጋጀትንና በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠትን የመሳሰሉ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን በቋሚነት ማከናወን ጀመረ። ከሁሉ በላይ ደግሞ አዘውትሮ መጸለይ ጀመረ። ለይሖዋ ያለው ፍቅር ሲጨምር በመንፈሳዊም ጥሩ እድገት እያደረገ ሄደ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ አሮን አቅኚ ሆኖ በማገልገል፣ አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎች እርዳታ በመስጠት እንዲሁም ወደ ሌላ አገር ሄዶ በመስበክ ደስታ ማግኘት ችሏል። አሮን በአሁኑ ጊዜ ቤቴላዊና የጉባኤ ሽማግሌ ነው። እስከ አሁን ስላከናወነው ነገር ምን ይሰማዋል? እንዲህ ብሏል፦ “‘ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቀምሼ አይቻለሁ።’ ይሖዋ ስለባረከኝ ለእሱ ባለዕዳ እንደሆንኩና በእሱ አገልግሎት የበለጠ መሥራት እንዳለብኝ ይሰማኛል፤ ይህ ደግሞ ተጨማሪ በረከቶች ያስገኝልኛል።”
8 መዝሙራዊው “ይሖዋን የሚሹ . . . መልካም ነገር አይጎድልባቸውም” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 34:8-10ን አንብብ።) በእርግጥም ይሖዋ በቅንዓት የሚያገለግሉትን ፈጽሞ አያሳፍራቸውም። በይሖዋ አገልግሎት የቻልነውን ሁሉ ስናደርግ በግለሰብ ደረጃ፣ ‘ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቀምሰን ማየት’ እንችላለን። አምላክን በሙሉ ነፍሳችን ማገልገላችን ተወዳዳሪ የሌለው ደስታ ያስገኝልናል።
ቶሎ ተስፋ አትቁረጥ
9, 10. ‘በትዕግሥት የመጠበቅ’ ዝንባሌ ማዳበርህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
9 ግብህ ላይ ለመድረስ በምትጣጣርበት ጊዜ ‘በትዕግሥት የመጠበቅ’ ዝንባሌ ማዳበር ሊያስፈልግህ ይችላል። (ሚክ. 7:7) ይሖዋ፣ ታማኝ አገልጋዮቹ አንዳንድ መብቶችን እስኪያገኙ አሊያም ደግሞ ያሉበት ሁኔታ እስኪስተካከልላቸው ድረስ የተወሰነ ጊዜ እንዲያልፍ ሊፈቅድ ቢችልም ምንጊዜም እነሱን ከመደገፍ ወደኋላ አይልም። ይሖዋ፣ ለአብርሃም ወንድ ልጅ እንደሚሰጠው ቃል ቢገባለትም ይህ የአምላክ አገልጋይ በእምነትና በትዕግሥት መጠበቅ አስፈልጎታል። (ዕብ. 6:12-15) ይስሐቅ እስኪወለድ ድረስ ዓመታት ቢያልፉም አብርሃም ተስፋ አልቆረጠም፤ ይሖዋም አላሳፈረውም።—ዘፍ. 15:3, 4፤ 21:5
10 እርግጥ ነው፣ በትዕግሥት መጠበቅ ቀላል አይደለም። (ምሳሌ 13:12) የጠበቅነው ነገር አለመሳካቱን እያሰብን የምንብሰለሰል ከሆነ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። ከዚህ ይልቅ ጊዜያችንን መንፈሳዊ ብቃቶችን ለማዳበር ብንጠቀምበት ጥበብ ይሆናል። ይህን ማድረግ የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች እንመልከት።
11. የትኞቹን ክርስቲያናዊ ባሕርያት ለማዳበር ጥረት ማድረግ እንችላለን? እነዚህ ባሕርያት አስፈላጊ የሆኑትስ ለምንድን ነው?
11 ክርስቲያናዊ ባሕርያትን አዳብር። የአምላክን ቃል በማንበብና ባነበብነው ላይ በማሰላሰል ጥበብን፣ ጥልቅ ማስተዋልን፣ እውቀትን፣ የማመዛዘን ችሎታንና ጤናማ አስተሳሰብን ማዳበር እንችላለን። በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚያገለግሉ ወንድሞች እነዚህን ባሕርያት ማዳበራቸው በጣም አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 1:1-4፤ ቲቶ 1:7-9) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችንን ማንበባችንም አምላክ ስለተለያዩ ጉዳዮች ያለውን አመለካከት ለመገንዘብ ያስችለናል። መዝናኛን፣ አለባበስንና አጋጌጥን፣ የገንዘብ አያያዝን እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት በተመለከተ ውሳኔ የሚጠይቁ ነገሮች በየዕለቱ ያጋጥሙናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርነውን ነገር በተግባር በማዋል ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን ማድረግ እንችላለን።
12. ሁሉም የጉባኤ አባላት እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን ማስመሥከር የሚችሉት እንዴት ነው?
12 እምነት የሚጣልብህ መሆንህን አስመሥክር። ወንድሞችም ሆንን እህቶች፣ የሚሰጠንን ማንኛውንም ቲኦክራሲያዊ ሥራ በሚገባ ለመወጣት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ አለብን። አገረ ገዢ የነበረው ነህምያ፣ በአምላክ ሕዝቦች መካከል በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚያገለግሉ ሰዎችን መሾም ነበረበት። ታዲያ የሾመው እነማንን ነበር? ፈሪሃ አምላክ ያላቸውና እምነት የሚጣልባቸው ሰዎችን መርጧል። (ነህ. 7:2፤ 13:12, 13) ዛሬም ቢሆን “መጋቢዎች ታማኝ ሆነው መገኘት ይጠበቅባቸዋል።” (1 ቆሮ. 4:2) መልካም ሥራችንን ሌሎች ማስተዋላቸው አይቀርም።—1 ጢሞቴዎስ 5:25ን አንብብ።
13. ሌሎች ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲፈጽሙብህ የዮሴፍን ምሳሌ መኮረጅ የምትችለው እንዴት ነው?
13 ይሖዋ እንዲያጠራህ ፍቀድ። ሌሎች ተገቢ ያልሆነ ነገር ቢፈጽሙብህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ምናልባት ግለሰቦቹን በማነጋገር ጉዳዩን ወዲያውኑ መፍታት ትችል ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ግን ትክክል መሆንህን ለማሳወቅ ሙግት መግጠምህ ችግሩን ያባብሰዋል። ዮሴፍ ወንድሞቹ ቢበድሉትም ቂም አልያዘባቸውም። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ዮሴፍ በሐሰት የተወነጀለ ሲሆን ያለ ጥፋቱ ወህኒ ቤት ገባ። ሆኖም በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ይሖዋ እንዲመራው ፈቅዷል። ይህ ምን ውጤት አስገኘ? ‘የይሖዋ ቃል አጥርቶታል።’ (መዝ. 105:19) ዮሴፍ እነዚህን ፈተናዎች ካለፈ በኋላ ለአንድ ልዩ ኃላፊነት ብቁ ሆኗል። (ዘፍ. 41:37-44፤ 45:4-8) አንተም ከባድ ችግሮች ሲያጋጥሙህ ጥበብ ለማግኘት ጸልይ፣ በድርጊትህና በንግግርህ ገርነትን አንጸባርቅ እንዲሁም ይሖዋ ኃይል እንዲሰጥህ ጠይቀው። እሱም ይረዳሃል።—1 ጴጥሮስ 5:10ን አንብብ።
በመስክ አገልግሎት እድገት አድርግ
14, 15. (ሀ) ለምንሰብክበት መንገድ ‘ምንጊዜም ትኩረት መስጠት’ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) አንዳንድ ሁኔታዎች ሲለወጡ የስብከት ዘዴያችንን ማስተካከል የምንችለው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ እና “የተለያዩ ዘዴዎችን ለመሞከር ፈቃደኛ ነህ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
14 ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንደሚከተለው በማለት አሳስቦታል፦ “ለሰዎች ለማንበብ፣ አጥብቀህ ለመምከርና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ። ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ።” (1 ጢሞ. 4:13, 16) በወቅቱ ጢሞቴዎስ ተሞክሮ ያለው የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ነበር። ሆኖም በአገልግሎቱ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ለሚያስተምረው ትምህርት ‘ምንጊዜም ትኩረት ከሰጠ’ ብቻ ነው። አዘውትሮ በሚጠቀምበት መንገድ መስበኩን ቢቀጥል፣ ሰዎች ሁልጊዜ ጥሩ ምላሽ እንደሚሰጡት መጠበቅ አይችልም። የሰዎችን ልብ መንካት እንዲችል የማስተማር ዘዴዎቹን እንደ ሰዎቹ ሁኔታ መቀያየር ነበረበት። እኛም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንደመሆናችን መጠን ተመሳሳይ ነገር ማድረግ አለብን።
15 ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ብዙ ጊዜ ሰዎችን ቤታቸው አናገኛቸውም። ወደ አፓርታማዎች ወይም ወደ አንዳንድ የታጠሩ መኖሪያ ሰፈሮች መግባት አስቸጋሪ የሚሆንባቸው አካባቢዎች አሉ። አንተም በክልልህ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚያጋጥምህ ከሆነ ምሥራቹን ለመስበክ ለምን የተለያዩ ዘዴዎችን አትሞክርም?
16. በአደባባይ በምንመሠክርበት ጊዜ ውጤታማ ለመሆን ምን ማድረግ እንችላለን?
16 ምሥራቹን ከምናዳርስባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ የአደባባይ ምሥክርነት ነው።[1] ብዙ አስፋፊዎች ይህን የአገልግሎት ዘዴ ውጤታማና አስደሳች ሆኖ አግኝተውታል። በባቡርና በአውቶቡስ ፌርማታዎች፣ በገበያ ቦታዎች፣ በመናፈሻዎችና ሰዎች በሚገኙባቸው ሌሎች ቦታዎች ምሥራቹን ለመስበክ ጥረት ያደርጋሉ። በዜና የሰሙትን ነገር በመጥቀስ፣ የግለሰቡን ልጆች በማድነቅ ወይም ስለ ሥራው ጥያቄ በመጠየቅ በዘዴ ውይይት መጀመር ይችላሉ። በውይይቱ መሃል አንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ ካነሱ በኋላ ግለሰቡ አመለካከቱን እንዲገልጽ ይጠይቁታል። አብዛኛውን ጊዜ ግለሰቡ የሚሰጠው መልስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ መንገድ ይከፍታል።
17, 18. (ሀ) በአደባባይ ስትመሠክር ይበልጥ ድፍረት እንድታዳብር ምን ሊረዳህ ይችላል? (ለ) በአገልግሎት ስትካፈል ይሖዋን በማወደስ ረገድ የዳዊት ዓይነት መንፈስ ማሳየት ጠቃሚ እንደሆነ የሚሰማህ ለምንድን ነው?
17 በአደባባይ መመሥከር ተፈታታኝ ከሆነብህ ተስፋ አትቁረጥ። በኒው ዮርክ ሲቲ የሚኖር ኤዲ የሚባል አቅኚ፣ ሰዎችን በአደባባይ ማነጋገር ከብዶት ነበር። በጊዜ ሂደት ግን ድፍረት ማግኘት ቻለ። የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “በቤተሰብ አምልኳችን ወቅት ከባለቤቴ ጋር ሰዎች ለሚሰነዝሯቸው ሐሳቦችና ተቃውሞዎች እንዴት መልስ መስጠት እንደምንችል ምርምር እናደርጋለን። እንዲሁም ሌሎች አስፋፊዎች ሐሳብ እንዲሰጡን እንጠይቃለን።” ኤዲ በአሁኑ ወቅት የአደባባይ ምሥክርነትን ወዶታል።
18 ምሥራቹን በመስበክ ረገድ ክህሎትና ድፍረት እያዳበርክ ስትሄድ መንፈሳዊ እድገትህ በግልጽ ይታያል። (1 ጢሞቴዎስ 4:15ን አንብብ።) በተጨማሪም እንደ መዝሙራዊው ዳዊት የሰማዩ አባታችንን እንደሚከተለው ብለህ ማወደስ ትችላለህ፦ “ይሖዋን ሁልጊዜ አወድሰዋለሁ፤ ውዳሴው ምንጊዜም ከአፌ አይለይም። በይሖዋ እኩራራለሁ፤ የዋሆች ሰምተው ሐሴት ያደርጋሉ።” (መዝ. 34:1, 2) የምታከናውነው አገልግሎት፣ የዋሆች ወይም ቅኖች አብረውህ ይሖዋን በደስታ እንዲያገለግሉ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።
መንፈሳዊ እድገት በማድረግ አምላክን ከፍ ከፍ አድርግ
19. አንድ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ የሚያቀርበውን አገልግሎት ሁኔታዎች ቢገድቡበትም ደስተኛ መሆን ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?
19 ዳዊት እንደሚከተለው በማለትም ዘምሯል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ሥራዎችህ ሁሉ ከፍ ከፍ ያደርጉሃል፤ ታማኝ አገልጋዮችህም ያወድሱሃል። የንግሥናህን ክብር ያውጃሉ፤ ስለ ኃያልነትህም ይናገራሉ፤ ይህም ለሰዎች ታላላቅ ሥራዎችህንና የንግሥናህን ታላቅ ክብር ያስታውቁ ዘንድ ነው።” (መዝ. 145:10-12) እነዚህ ቃላት የሁሉንም ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ስሜት በሚገባ ይገልጻሉ። ነገር ግን ሕመም ወይም የዕድሜ መግፋት የምታቀርበውን አገልግሎት ቢገድቡብህስ? ለሚንከባከቡህ ሰዎችና ለሌሎች ምሥራቹን ስትናገር የምታቀርበው ቅዱስ አገልግሎት ታላቁን አምላካችንን ከፍ ከፍ እንደሚያደርግ አትዘንጋ። በእምነትህ ምክንያት ታስረህ ከሆነ ደግሞ ሁኔታዎች በፈቀዱልህ መጠን ስለ እውነት መመሥከርህ አይቀርም፤ ይህም የይሖዋን ልብ ያስደስተዋል። (ምሳሌ 27:11) በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ሆነህ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን አዘውትረህ ለማከናወን ጥረት ስታደርግም ይሖዋን ታስደስታለህ። (1 ጴጥ. 3:1-4) በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ብትሆንም እንኳ ይሖዋን ማወደስ እንዲሁም መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ትችላለህ።
20, 21. በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ተጨማሪ ሥራ ለመቀበል ራስህን በማቅረብ ለሌሎች በረከት መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
20 መንፈሳዊ እድገት ማድረግህን ከቀጠልክ ይሖዋ እንደሚባርክህ ጥርጥር የለውም። ምናልባትም በፕሮግራምህ ወይም በአኗኗርህ ላይ ጥቂት ማስተካከያዎችን በማድረግ የአምላክን ውድ እውነትና እሱ የሰጠውን ተስፋ ለሰዎች በማካፈል ረገድ የበለጠ ተሳትፎ ማድረግ ትችላለህ። በተጨማሪም የምታደርገው መንፈሳዊ እድገትና የምትከፍለው መሥዋዕትነት የእምነት ባልንጀሮችህን በእጅጉ ሊጠቅማቸው ይችላል። ከዚህም ሌላ በጉባኤ ውስጥ በትሕትና የምታከናውነው ሥራ፣ ይሖዋን የሚወዱ ሌሎች ሰዎችን ፍቅርና አድናቆት ያተርፍልሃል፤ እንዲሁም የእነሱን ድጋፍ ያስገኝልሃል።
21 በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍነው ጊዜ ብዙ ዓመታትም ይሁን ጥቂት ወራት፣ ሁላችንም በመንፈሳዊ እድገት ማድረግ እንችላለን። ሆኖም የጎለመሱ ክርስቲያኖች አዲሶችን በመንፈሳዊ እንዲያድጉ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው? በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ይህን እንመለከታለን።
^ [1] (አንቀጽ 16) “የአደባባይ ምሥክርነት” የሚለው አገላለጽ በአብዛኛው የሚያመለክተው ከቤት ወደ ቤት ከምናደርገው አገልግሎት ውጭ ያሉትን የስብከት ዘዴዎች ይኸውም በመኪና ማቆሚያዎች፣ በንግድ አካባቢዎች፣ በመናፈሻዎች፣ በመንገድ ላይና ሰዎች ሊገኙባቸው በሚችሉ ሌሎች ቦታዎች የምናከናውነውን ስብከት ነው። ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ጋሪዎችን፣ ጠረጴዛዎችንና የመሳሰሉትን ተጠቅመን የምናከናውነው አገልግሎት የአደባባይ ምሥክርነት አንዱ ዘርፍ ነው።