ቃልህን መጠበቅ የሚኖርብህ ለምንድን ነው?
“በኋላ ጸጸት ውስጥ እንዳትገባ ብዙ ነገር እንደሚያደርግ ቃል የሚገባን ሰው አትምረጥ” በማለት ሟቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ አማካሪ የነበሩት በርናንድ ባሩክ ተናግረዋል። በዛሬው ጊዜ እንደማይፈጽሙት እያወቁ ቃል መግባት የተለመደ ነገር የሆነ ይመስላል። እነዚህም የጋብቻ መሐላዎች፣ የንግድ ስምምነቶች ወይም ከልጆች ጋር ተጨማሪ ጊዜ ለማሳለፍ የሚገቡ ቃሎች ሊሆኑ ይችላሉ። “ትልቅ ሰው ማለት ቃሉን የሚጠብቅ ሰው ነው” የሚለው የተለመደ አባባል በሰፊው ቸል እየተባለ መጥቷል።
እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ ሰዎች ቃላቸውን ስለመጠበቅ ጨርሶ አይጨነቁም። ሌሎች ደግሞ ሊፈጽሙ የማይችሉትን ነገር በችኮላ ቃል ይገባሉ ወይም ደግሞ ቀላል አማራጭ ሆኖ የሚያገኙት እሱን ስለሆነ የገቡትን ቃል ማፍረስ ይቀናቸዋል።
የአንድ ያልታሰበ ሁኔታ መከሰት አንድ ሰው የገባውን ቃል እንዳይፈጽም እንቅፋት ሊሆንበት እንደሚችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ የገቡትን ቃል አለመጠበቅ ይህን ያህል የሚያስከትለው ጉዳት ይኖራልን? የገባኸውን ቃል አክብደህ መመልከት ይኖርብሃልን? በዚህ ረገድ ይሖዋ አምላክ የተወውን ምሳሌ መለስ ብሎ መቃኘቱ ይህን ጉዳይ አክብደን መመልከት ያለብን ለምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል።
ይሖዋ የገባውን ቃል ይፈጽማል
የምናመልከው አምላክ ስሙ ራሱ የገባውን ቃል ከመፈጸሙ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ለአንድ ሰው የሚወጣው ስም ስለ ሰውዬው ማንነት የሚገልጽ ነበር። ‘እንዲሆን ያደርጋል’ የሚል ትርጉም ያለው የይሖዋ ስምም ስለ ይሖዋ ማንነት ይገልጻል። (ዘጸአት 3:14) ስለዚህ መለኮታዊው ስም አምላክ የገባቸውን ቃሎች የሚፈጽምና ዓላማዎቹን ዳር የሚያደርስ መሆኑን ጭምር የሚያመለክት ነው።
ይሖዋ ልክ እንደ ስሙ ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር ገብቶ የነበረውን ቃል በሙሉ ፈጽሟል። እነዚህን ይሖዋ የገባቸውን ቃሎች በተመለከተ ንጉሥ ሰሎሞን “እንደ ተናገረው ተስፋ ሁሉ ለሕዝቡ ለእስራኤል ዕረፍትን የሰጠ እግዚአብሔር ይመስገን፤ በባሪያው በሙሴ ከሰጠው ከመልካም ተስፋ ሁሉ አንድ ቃል አልወደቀም” በማለት ማረጋገጫ ሰጥቷል።—1 ነገሥት 8:56
ይሖዋ ከፍተኛ እምነት የሚጣልበት አምላክ በመሆኑ ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ:- በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ እያበዛሁም አበዛሃለሁ ብሎ፣ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ፣ በራሱ ማለ” ብሎ ለመናገር ችሏል። (ዕብራውያን 6:13) አዎን፣ ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቅበት ቢሆንም እንኳ ይሖዋ የገባቸውን ቃሎች እንደሚፈጽም ስሙና ባሕርይው ዋስትና ይሰጡናል። (ሮሜ 8:32) ይሖዋ የገባውን ቃል የሚፈጽም መሆኑ ለነፍሳችን ወይም ለሕይወታችን እንደ መልሕቅ ሆኖ የሚያገለግለንን ተስፋ ይሰጠናል።—ዕብራውያን 6:19
ይሖዋ የገባው ቃልና የወደፊት ዕጣችን
ተስፋችን፣ እምነታችን ሌላው ቀርቶ ሕልውናችን የተመካው ይሖዋ የገባውን ቃል በመፈጸሙ ላይ ነው። የትኛውን ተስፋ በጉጉት እንጠባበቃለን? “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።” (2 ጴጥሮስ 3:13) በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎች “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን” እንደሚነሱ በመግለጽ ለእምነታችን መሠረት ይሰጡናል። (ሥራ 24:15) ስለሆነም ወደፊት ከአሁኑ ሕይወት እጅግ የሚልቅ ሕይወት እንደሚመጣ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። በእርግጥም ሐዋርያው ዮሐንስ “የሰጠን ተስፋ” ብሎ የጠራው ነገር “የዘላለም ሕይወት ነው።” (1 ዮሐንስ 2:25) ሆኖም ይሖዋ በቃሉ ውስጥ ያሰፈራቸው የተስፋ ቃላት ወደፊት ለምንጠብቀው ሕይወት ብቻ የሚሠሩ አይደሉም። አሁን ያለውን የዕለት ተዕለት ሕይወታችንንም ትርጉም ያለው ያደርጉልናል።
መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣ . . . ቅርብ ነው። . . . ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 145:18, 19) በተጨማሪም አምላክ “ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፣ ጉልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል።” (ኢሳይያስ 40:29) እንዲሁም አምላክ ‘ከሚቻለን መጠን ይልቅ እንፈተን ዘንድ የማይፈቅድና ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ የሚያዘጋጅልን’ መሆኑን ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው! (1 ቆሮንቶስ 10:13) ከእነዚህ አምላክ ከገባቸው ቃሎች መካከል በእኛ ሕይወት ላይ የደረሱ ነገሮች ካሉ ይሖዋ ሙሉ በሙሉ እምነት ሊጣልበት የሚችል አምላክ መሆኑን አውቀናል ማለት ነው። አምላክ ቃል ገብቶ በመፈጸሙ የተነሳ እኛ ከተጠቀምን እኛስ ለእርሱ ለምንገባው ቃል ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምን መሆን አለበት?
ለአምላክ የምንገባውን ቃል መጠበቅ
እስከ አሁን ከገባነው ቃል ሁሉ ትልቁን ቦታ የሚይዘው ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን የገባነው ቃል እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ይህን እርምጃ በመውሰዳችን ይሖዋን ለዘላለም ማገልገል የምንፈልግ መሆናችንን አሳይተናል። የአምላክ ትእዛዛት ከባዶች ባይሆኑም እንኳ በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት እየኖርን ፈቃዱን ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12፤ 1 ዮሐንስ 5:3) ይሁን እንጂ አንድ ጊዜ ‘ዕርፉን ከጨበጥንና’ ራሳችንን ወስነን የይሖዋ አገልጋዮችና የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከሆንን በኋላ ትተናቸው ወደመጣናቸው ወደዚህ ዓለም ነገሮች ፈጽሞ መመለስ አይኖርብንም።—ሉቃስ 9:62
ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ያለብንን ድክመት ተዋግተን ለማሸነፍ፣ አንድን ክርስቲያናዊ ባሕርይ ለማዳበር ወይም በአንዱ የቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴ መስክ እድገት ለማድረግ ቃል እንገባ ይሆናል። ታዲያ ይህን የገባነውን ቃል ወደ ፍጻሜው ለማድረስ ምን ይረዳናል?—ከመክብብ 5:2-5 ጋር አወዳድር።
የምንገባው ቃል እውነተኛ ከሆነ የሚመነጨው ከልብና ከአእምሮአችን ነው። ስለዚህ ፍርሃታችንን፣ ምኞታችንንና ድክመታችንን በሐቀኝነት በመግለጽና ልባችንን በጸሎት ለእርሱ በማፍሰስ፣ ለይሖዋ የምንገባውን ቃል ሁሉ የምንፈጽም ለመሆናችን ማረጋገጫ እንስጥ። ስለ ገባነው ቃል መጸለያችን ቃላችንን ለመጠበቅ ያለንን ቁርጠኝነት ያጠነክረዋል። ለአምላክ የገባነውን ቃል መክፈል እንዳለብን ዕዳ ልንቆጥረው እንችላለን። አንድ ዕዳ በጣም ብዙ ከሆነ ከስር ከስር መከፈል ይኖርበታል። በተመሳሳይም ለይሖዋ የገባነውን ቃል ሁሉ ለመፈጸም ጊዜ ይወስዳል። ይሁን እንጂ የተናገርነውን የምንፈጽም ሰዎች መሆናችንን እናሳይ፤ እርሱም በምላሹ ይባርከናል።
ስለ ገባነው ቃል አዘውትረን ምናልባትም በየቀኑ በመጸለይ የገባነውን ቃል በቁምነገር እንደምንመለከተው ልናሳይ እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን የሰማዩ አባታችን ከልባችን ቃል መግባታችንን እንዲያይ ያደርገዋል። በተጨማሪም ጸሎት የገባነው ቃል ዘወትር ትዝ እንዲለን ያደርጋል። በዚህ ረገድ ዳዊት ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። “አምላክ ሆይ፣ ልመናዬን ስማ፣ ጸሎቴንም አድምጥ። . . . እንዲሁ ለስምህ ለዘላለም እዘምራለሁ ስእለቴን ሁልጊዜ እፈጽም ዘንድ” በማለት በመዝሙር ይሖዋን ተማጽኗል።—መዝሙር 61:1, 8
የገባነውን ቃል መጠበቃችን አመኔታን ያተርፍልናል
ለአምላክ የምንገባውን ቃል አቅልለን መመልከት የማይገባን ከሆነ ለክርስቲያን ወንድሞቻችን የምንገባውንም ቃል በተመለከተ ተመሳሳይ ነገር ለማለት ይቻላል። ለይሖዋ ሌላ፣ ለወንድሞቻችን ደግሞ ሌላ መሆን የለብንም። (ከ1 ዮሐንስ 4:20 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:37፤ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) የምንናገረው ቃል ሁልጊዜ እምነት የሚጣልበት እንዲሆን ማድረጋችን ‘ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም የምናደርግበት’ አንደኛው መንገድ ነው። (ገላትያ 6:10) የገባነውን ቃል ሁልጊዜ መጠበቃችን በሌሎች ዘንድ አመኔታን ያተርፍልናል።
ቃልን አለመጠበቅ የሚያስከትለው ጉዳት ብዙውን ጊዜ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ከሆነ ጉዳቱ ያይላል። አንድ ክርስቲያን የተበደረውን ገንዘብ በመክፈልም ይሁን አንድ ዓይነት አገልግሎት በመስጠት ወይም የገባውን የንግድ ውል በመፈጸም ቃሉን መጠበቅ ይኖርበታል። ይህ አምላክን የሚያስደስት ከመሆኑም በላይ “ወንድሞች ስምም ሆነው በአንድነት እንዲቀመጡ” ለማድረግ የግድ አስፈላጊ የሆነውን እርስ በርስ የመተማመን መንፈስ ያጎለብታል።—መዝሙር 133:1
አንድ ሰው የገባውን ስምምነት አለማክበሩ ጉባኤውንም ሆነ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን ግለሰቦች ሊጎዳ ይችላል። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች የታዘበውን እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “በንግድ ጉዳይ አንደኛው ወገን ታማኝነቱን እንዳጎደለ አድርጎ ሌላኛው ወገን በሚያስብበት ወቅት የሚፈጠር ውዝግብ ብዙውን ጊዜ ወደ ሌሎች ጆሮ ይደርሳል። በዚህም ሳቢያ በወንድሞች መካከል መከፋፈል ይፈጠራል፤ እንዲሁም በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ውጥረት ሊከሰት ይችላል።” የምንገባውን የንግድ ስምምነት በጥንቃቄ መመርመርና በጽሑፍ ማስፈሩ ምንኛ አስፈላጊ ነው!a
በተለይ ከትርፉ እኛም ተጠቃሚ የምንሆን ከሆነ ውድ ዋጋ ያላቸውን ምርቶች በምንሸጥበት ወይም ሌሎች መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈስሱ በምናበረታታበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። በተመሳሳይም አንዳንድ ዕቃዎች ወይም ለጤና ይበጃሉ የሚባሉ ነገሮች የሚሰጡትን ጥቅም አጋኖ ከመናገር ወይም ስለሚያስገኘው ትርፍ ሌሎችን ወደ ቅዠት ዓለም ከመጨመር መቆጠብ ያስፈልጋል። ክርስቲያኖች አንድ ነገር ሊያስከትል ስለሚችለው አደጋ ምንም ሳይሸሽጉ የተሟላ መረጃ እንዲሰጡ ፍቅር ሊገፋፋቸው ይገባል። (ሮሜ 12:10) ብዙ ወንድሞች በንግድ እንቅስቃሴ ያላቸው ተሞክሮ አነስተኛ በመሆኑ በእምነት የምንዛመዳቸው ስለሆንን ብቻ የምንሰጣቸውን ምክር ሁሉ ሳይጠራጠሩ ሊቀበሉ ይችላሉ። ታዲያ ይህ በእኛ ላይ የጣሉት ትምክህት እንደ ጠበቁት ሆኖ ባይገኝ ምንኛ አሳዛኝ ይሆናል!
ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሐቀኝነት በጎደለው የንግድ እንቅስቃሴ አንካፈልም ወይም ሌሎች ሊያገኙት የሚገባቸውን ጥቅም አንነፍጋቸውም። (ኤፌሶን 2:2, 3፤ ዕብራውያን 13:18) ይሖዋ ‘በድንኳኑ ውስጥ እንደ እንግዶቹ’ አድርጎ እንዲቀበለን ከፈለግን እምነት የሚጣልብን ሰዎች መሆን አለብን። ‘በእኛ ላይ ጉዳት የሚያስከትል እንኳ ቢሆን መሐላችንን አናጥፍም።’—መዝሙር 15:1, 4
የእስራኤል መስፍን የነበረው ዮፍታሄ ይሖዋ በአሞናውያን ላይ ድል ከሰጠው ከውጊያ ሲመለስ መጀመሪያ ወጥቶ የሚቀበለውን ለይሖዋ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ እንደሚያቀርብ ተሳለ። ወደ ቤት ሲመለስ በመጀመሪያ ወጥታ የተቀበለችው አንድያ ልጁ ነበረች፤ ሆኖም ቃሉን ፈጽሞ አላጠፈም። ልጁም በጉዳዩ ከልቧ በመስማማቷ ዮፍታሄ ሥቃይ የሚያስከትልበትና በብዙ መንገዶች ጉዳት የሚያመጣበት ቢሆንም እንኳ እንደሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ ለዘላለም እንድታገለግል አሳልፎ ሰጣት።—መሳፍንት 11:30-40
በተለይ ደግሞ የጉባኤ የበላይ ተመልካቾች የገቡትን የስምምነት ቃል የማክበር ኃላፊነት አለባቸው። በ1 ጢሞቴዎስ 3:2 መሠረት አንድ የበላይ ተመልካች በሌሎች ዘንድ “የማይነቀፍ” መሆን አለበት። ይህ “የሚያዝበት ነገር የሌለ፣ ከነቀፋ ነፃ የሆነ፣ የማይወቀስ” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ነው። ቃሉ “ሰውየው ጥሩ ስም ያለው መሆኑ ብቻ ሳይሆን የሚገባው መሆኑን ያመለክታል።” (ኤ ሊንጉዊስቲክ ኪ ቱ ዘ ግሪክ ኒው ቴስታመንት) አንድ የበላይ ተመልካች የማይነቀፍ መሆን ስላለበት ቃል ሲገባም ሁልጊዜ እምነት የሚጣልበት መሆን ይኖርበታል።
ቃላችንን የምንጠብቅባቸው ሌሎች መንገዶች
የእምነት ባልደረቦቻችን ላልሆኑ ሰዎች ስለምንገባው ቃልስ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ኢየሱስ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:16) ቃላችንን የምናከብር ሰዎች መሆናችንን በማስመስከር ሰዎችን ወደምንናገረው የክርስትና መልእክት መሳብ እንችላለን። በዓለም ዙሪያ ሃቀኝነት እየጠፋ ያለ ቢሆንም በአቋም መጽናትን ከፍ አድርገው የሚመለከቱ በርካታ ሰዎች አሁንም አሉ። የገባነውን ቃል መጠበቃችን ለአምላክና ለጎረቤቶቻችን ፍቅር የምናሳይበት እንዲሁም ጽድቅ ወዳድ የሆኑ ሰዎችን የምንማርክበት አንዱ መንገድ ነው።—ማቴዎስ 22:36-39፤ ሮሜ 15:2
የይሖዋ ምሥክሮች በ1998 የአገልግሎት ዓመታቸው የአምላክን መንግሥት ለሕዝብ በማወጁ ሥራ ከአንድ ቢልዮን የሚበልጥ ሰዓት አሳልፈዋል። (ማቴዎስ 24:14) በንግድ ወይም በሌሎች ጉዳዮች ረገድ ቃላችንን የማንጠብቅ ሆነን ብንገኝ ስብከታችን መና ሆኖ ይቀር ነበር። የእውነትን አምላክ የምንወክል እንደመሆናችን መጠን በሃቀኝነት እንደምንመላለስ አድርገው ሰዎች እኛን መቁጠራቸው የተገባ ነው። እምነት የሚጣልብንና ሃቀኞች በመሆን “የአዳኛችን የእግዚአብሔር ትምህርት በሁሉ ነገር እንዲከበር” እናደርጋለን።—ቲቶ 2:9-11 የ1980 ትርጉም
በአገልግሎት ላይ ስንሆን ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተመልሰን በማነጋገር በኩል ቃላችንን የምንጠብቅ ለመሆናችን ማረጋገጫ መስጠት እንችላለን። ተመልሰን እንደምንሄድ ከነገርናቸው በኋላ መቅረት የለብንም። በገባነው ቃል መሠረት ተመልሰን መሄዳችን “ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ማድረግ” የምንችልበት አንደኛው መንገድ ነው። (ምሳሌ 3:27) አንዲት እህት ሁኔታውን እንዲህ በማለት አስቀምጣዋለች:- “አንድ የይሖዋ ምሥክር ተመልሶ እንደሚጠይቃቸው ቃል ገብቶላቸው ሳይመለስ እንደቀረ የሚናገሩ ፍላጎት ያላቸው በርካታ ሰዎች በተለያዩ ወቅቶች ያጋጥሙኛል። እርግጥ ነው፣ የቤቱ ባለቤት በተባለው ቀን እቤቱ ሳይገኝ ቀርቶ ይሆናል፤ ወይም ተመልሶ መጠየቁን የሚያስተጓጉሉ ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች አጋጥመው ይሆናል። ሆኖም ማንም ሰው እንዲህ ብሎ ስለ እኔ እንዲናገር ስለማልፈልግ ግለሰቡን እቤቱ ለማግኘት የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ። አንድ ሰው ቅር ቢሰኝብኝ በይሖዋና በአጠቃላይ በወንድሞቼ ላይ መጥፎ ስም እንደማመጣ አውቃለሁ።”
አንዳንድ ጊዜ ግለሰቡ ምንም ዓይነት ፍላጎት የለውም በሚል ተመልሰን ለመሄድ እናመነታ ይሆናል። ይህችው እህት ደግማ ስትናገር “ግለሰቡ ያለውን ፍላጎት እኔ ልወስን አልችልም። ከራሴ ተሞክሮ እንዳየሁት ብዙ ጊዜ ሰዎች መጀመሪያ ላይ የሚያሳዩት ስሜት ይለወጣል። ስለዚህ እያንዳንዱ ግለሰብ ወደፊት ወንድም ወይም እህት ይሆናል የሚል አመለካከት በመያዝ አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ እጥራለሁ” ብላለች።
በክርስቲያናዊ አገልግሎትም ሆነ በሌሎች በርካታ መስኮች ቃላችን ሊታመን እንደሚችል ማረጋገጫ መስጠት ይኖርብናል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ነገሮች እንደምንናገረው ቀላል ላይሆኑ ይችላሉ። ጠቢቡ ሰው “ብዙ ሰዎች ቸርነታቸውን ያወራሉ፤ የታመነውን ሰው ግን ማን ያገኘዋል?” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 20:6) በቁርጠኝነት በመነሳት ለቃላችን ታማኞችና እውነተኞች መሆን እንችላለን።
አምላክ የሚሰጠው የተትረፈረፈ በረከት
ሆነ ብሎ ባዶ ቃል መግባት አታላይነት ከመሆኑም በላይ በባንክ ምንም ተቀማጭ ገንዘብ ሳይኖር ቼክ ፈርሞ እንደመስጠት ሊቆጠር ይችላል። ይሁን እንጂ ቃላችንን የምንጠብቅ ከሆነ ይህ ነው የማይባል ሽልማቶችንና በረከቶችን እናገኛለን! ቃልን በመጠበቅ የሚገኘው አንደኛው በረከት ጥሩ ሕሊና ማግኘት ነው። (ከሥራ 24:16 ጋር አወዳድር።) በማይሽር ጸጸት ከመሠቃየት ይልቅ እርካታና ሰላም ይኖረናል። ከዚህም በላይ ቃላችንን የምንጠብቅ በመሆን እርስ በርስ በመተማመን ላይ ለተመሠረተው የጉባኤ አንድነት አስተዋጽኦ እናበረክታለን። ‘የእውነት ቃል’ መናገራችን የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች ለመሆናችን ማረጋገጫ ይሆናል።—2 ቆሮንቶስ 6:3, 4, 7
ይሖዋ የሚናገረው ሁሉ እውነት ከመሆኑም በላይ “ሐሰተኛ ምላስ”ን ይጠላል። (ምሳሌ 6:16, 17) የሰማዩ አባታችንን በመምሰል ወደ እርሱ ይበልጥ እንቅረብ። በእርግጥም ቃላችንን እንድንጠብቅ የሚያስገድደን ጥሩ ምክንያት አለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “በጽሑፍ አስፍሩት!” የሚለውን የካቲት 8, 1983 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 13-15 ላይ የወጣውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ዮፍታሄ ሥቃይ የሚያስከትልበት ቢሆንም እንኳ ቃሉን ከመጠበቅ ወደኋላ አላለም
[በገጽ 11 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ተመልሰህ እንደምትሄድ ቃል ገብተህ ከነበረ ፈጽሞ አትቅር