አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለውን ልዩነት አስተውሉ
‘በጻድቁና በክፉው መካከል ያለውን ልዩነት ታያላችሁ።’—ሚል. 3:18
1, 2. በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች ምን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል? (በመግቢያው ላይ ያሉትን ፎቶግራፎች ተመልከት።)
በሕክምና መስክ የተሰማሩ በርካታ ባለሙያዎች ተላላፊ በሽታ የያዛቸውን ሰዎች ያክማሉ። እነዚህ ባለሙያዎች ለሕመምተኞቹ እንክብካቤ የሚያደርጉት ሊረዷቸው ስለሚፈልጉ ነው። ይህን ሲያደርጉ ግን በሽታው ወደ እነሱም እንዳይጋባ መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል። በተመሳሳይም ብዙዎቻችን የምንኖረውና የምንሠራው አምላክ የማይወዳቸውን ባሕርያት ከሚያንጸባርቁ ሰዎች ጋር ነው። በመሆኑም የእነዚህ ሰዎች አመለካከትና ዝንባሌ እንዳይጋባብን መጠንቀቅ ይኖርብናል።
2 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ከፍተኛ የሥነ ምግባር ውድቀት ይታያል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ ከአምላክ የራቁ ሰዎች ስለሚያሳዩአቸው ባሕርያት ጠቅሷል፤ ጳውሎስ ወደዚህ ሥርዓት መጨረሻ እየተቃረብን በሄድን መጠን እነዚህ መጥፎ ባሕርያት ይበልጥ እንደሚታዩ ጠቁሟል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13ን አንብብ።) እንደነዚህ ዓይነት ባሕርያት እየተስፋፉ መሄዳቸው በጣም እንደሚረብሸን የታወቀ ነው፤ ያም ሆኖ እንዲህ ያሉት መጥፎ ባሕርያትና ዝንባሌዎች ወደ እኛም ሊጋቡ እንደሚችሉ ማስታወስ ይኖርብናል። (ምሳሌ 13:20) በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ በመጨረሻው ዘመን በሚኖሩ ሰዎች ባሕርያትና የአምላክ ሕዝቦች በሚያሳዩአቸው ባሕርያት መካከል ያለውን ልዩነት እንመረምራለን። በተጨማሪም ሰዎች አምላክን እንዲያውቁ በምንረዳበት ጊዜ የእነሱ መጥፎ ባሕርይ እንዳይጋባብን መከላከል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
3. በ2 ጢሞቴዎስ 3:2-5 ላይ የተዘረዘሩትን ባሕርያት የሚያንጸባርቁት ሁሉም ሰዎች ናቸው?
3 ሐዋርያው ጳውሎስ “በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ” ጽፏል። ከዚያም በዚህ ዘመን በሚኖሩ ሰዎች ላይ የሚታዩ 19 መጥፎ ባሕርያትን ዘርዝሯል። እዚህ ላይ የተጠቀሱት ባሕርያት በሮም 1:29-31 ላይ ከተዘረዘሩት ጋር ተመሳሳይ ናቸው፤ እርግጥ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ በሌሎች የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የማይገኙ ተጨማሪ መጥፎ ባሕርያትን ጠቅሷል። ጳውሎስ የዘረዘራቸውን ባሕርያት የሚያንጸባርቁት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። የክርስቲያኖች ባሕርይ ከዚህ በጣም የተለየ ነው።—ሚልክያስ 3:18ን አንብብ።
ለራሳችን ያለን አመለካከት
4. በኩራት የተወጠሩ ሰዎችን እንዴት ትገልጻቸዋለህ?
4 ጳውሎስ በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ ሰዎች ራሳቸውንና ገንዘብን የሚወዱ እንደሚሆኑ ከገለጸ በኋላ ብዙዎች ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች እና በኩራት የተወጠሩ እንደሚሆኑ ተናግሯል፤ አንድ ሰው እነዚህን ባሕርያት የሚያሳየው በችሎታው፣ በመልኩ፣ በሀብቱ አሊያም በማኅበረሰቡ ውስጥ ባለው ቦታ የተነሳ ከሌሎች እንደሚበልጥ አድርጎ የሚያስብ ከሆነ ነው። እንዲህ ዓይነት ሰዎች፣ ሁልጊዜ ሌሎች እንዲያደንቋቸውና ከፍ ያለ ቦታ እንዲሰጧቸው ይፈልጋሉ። አንድ ምሁር፣ እብሪተኛ ስለሆነ ሰው ሲናገሩ “በልቡ ውስጥ ትንሽ መሠዊያ ሠርቶ ለራሱ ተንበርክኮ ይሰግዳል” ብለዋል። ከልክ ያለፈ ኩራት በጣም የሚጠላ ባሕርይ በመሆኑ፣ ኩሩ የሆኑ ሰዎችም እንኳ እንዲህ ያለ ባሕርይ ያላቸውን ሰዎች እንደማይወዱ አንዳንዶች ሲናገሩ ይሰማል።
5. ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችም እንኳ በኩራት ወጥመድ ሊወድቁ እንደሚችሉ የሚያሳየው ምንድን ነው?
5 ይሖዋ ኩራትን እንደሚጸየፍ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። በተጨማሪም ‘ትዕቢተኛ ዓይንን’ እንደሚጠላ ተገልጿል። (ምሳሌ 6:16, 17) ኩራት ወደ አምላክ እንዳንቀርብ እንቅፋት ይሆናል። (መዝ. 10:4) ይህ ባሕርይ የዲያብሎስ መገለጫ ነው። (1 ጢሞ. 3:6) የሚያሳዝነው ግን ታማኝ ከሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች መካከል አንዳንዶቹም በኩራት ወጥመድ ወድቀዋል። የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ዖዝያ ለዓመታት ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል። “ይሁን እንጂ ዖዝያ በበረታ ጊዜ ለጥፋት እስኪዳረግ ድረስ ልቡ ታበየ፤ በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ በመግባት በአምላኩ በይሖዋ ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈጸመ።” ንጉሥ ሕዝቅያስም በአንድ ወቅት ልቡ ታብዮ ነበር።—2 ዜና 26:16፤ 32:25, 26
6. ዳዊት እንዲኮራ የሚያደርጉ ምን ነገሮች ነበሩት? ሆኖም ትሑት እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው?
6 አንዳንድ ሰዎች የሚኮሩት መልከ መልካም ወይም ታዋቂ ስለሆኑ አሊያም ጥሩ የሙዚቃ ችሎታ፣ ሥልጣን ወይም ደግሞ አካላዊ ጥንካሬ ስላላቸው ሊሆን ይችላል። ዳዊት እነዚህ ሁሉ ነገሮች ቢኖሩትም በሕይወቱ ሙሉ ትሑት ነበር። ጎልያድን ከገደለ በኋላ ንጉሥ ሳኦል ልጁን ሊድርለት እንደሚፈልግ ሲነግረው ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “ለንጉሡ አማች እሆን ዘንድ እኔም ሆንኩ የአባቴ ቤተሰቦች የሆኑት ዘመዶቼ በእስራኤል ውስጥ ከቶ ማን ሆነን ነው?” (1 ሳሙ. 18:18) ዳዊት ምንጊዜም ትሑት እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው? እነዚህ ባሕርያት፣ ችሎታዎችና መብቶች የኖሩት አምላክ ‘ወደ ታች በማጎንበስ’ ወይም ራሱን ዝቅ በማድረግ ትኩረት ስለሰጠው መሆኑን መገንዘቡ ነው። (መዝ. 113:5-8) ዳዊት ያሉትን መልካም ነገሮች ሁሉ ያገኘው ከይሖዋ እንደሆነ ያውቅ ነበር።—ከ1 ቆሮንቶስ 4:7 ጋር አወዳድር።
7. ትሑት ለመሆን ምን ይረዳናል?
7 እንደ ዳዊት ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮችም ትሑት ለመሆን ይጥራሉ። ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀው አካል ቢሆንም እንኳ ግሩም የሆነውን የትሕትና ባሕርይ ያንጸባርቃል፤ ይህን ማወቃችን በአድናቆት እንድንዋጥ ያደርገናል። (መዝ. 18:35) ይህ ደግሞ “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ያነሳሳናል። (ቆላ. 3:12) በተጨማሪም ፍቅር ‘ጉራ እንደማይነዛና እንደማይታበይ’ እንገነዘባለን። (1 ቆሮ. 13:4) ትሑት መሆናችን ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲሳቡ ሊያደርግ ይችላል። ባሎች በሚስቶቻቸው ምግባር የተነሳ ያለቃል ሊማረኩ እንደሚችሉ ሁሉ የአምላክ ሕዝቦች የሚያሳዩት ትሕትናም ሌሎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል።—1 ጴጥ. 3:1
ሌሎችን የምንይዝበት መንገድ
8. (ሀ) በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች ለወላጆች አለመታዘዝን እንዴት ይመለከቱታል? (ለ) ቅዱሳን መጻሕፍት ለልጆች ምን ምክር ይሰጣሉ?
8 ጳውሎስ በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ ሰዎች እርስ በርስ ስለሚኖራቸው ግንኙነት ተናግሯል። በመጨረሻዎቹ ቀናት ልጆች ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ እንደሚሆኑ ጽፏል። በምንኖርበት ዘመን እንዲህ ያለው ምግባር በመጻሕፍት፣ በፊልሞችና በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ ምንም ችግር እንደሌለው እንዲያውም ተቀባይነት እንዳለው ተደርጎ የሚቀርብበት ጊዜ አለ፤ ይሁንና ለወላጆች አለመታዘዝ የማኅበረሰቡ መሠረት የሆነውን የቤተሰብ ሕይወት ያናጋል። ለወላጆች አለመታዘዝ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ችግር እንደሚፈጥር ቀደም ባሉት ዘመናትም ይታወቅ ነበር። በጥንቷ ግሪክ ወላጆቹን የሚመታ ሰው በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉትን መብቶች በሙሉ ያጣ ነበር፤ በሮም ሕግ መሠረት ደግሞ አባትን መምታት ከግድያ የማይተናነስ ወንጀል ነበር። የዕብራይስጥም ሆነ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩ ይመክራሉ።—ዘፀ. 20:12፤ ኤፌ. 6:1-3
9. ልጆች ለወላጆቻቸው እንዲታዘዙ ምን ሊረዳቸው ይችላል?
9 ልጆች፣ ወላጆቻቸው ስላደረጉላቸው ነገሮች ማሰባቸው በዓለም ላይ የሚታየው ያለመታዘዝ ዝንባሌ እንዳይጋባባቸው ለመከላከል ይረዳቸዋል። በተጨማሪም ልጆች፣ የሁላችንም አባት የሆነው ይሖዋ ለወላጆቻቸው እንዲታዘዙ እንደሚጠብቅባቸው ማስታወሳቸው የመታዘዝን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል። ልጆች ስለ ወላጆቻቸው መልካም ነገር መናገራቸው፣ እኩዮቻቸውም ለራሳቸው ወላጆች አክብሮት እንዲኖራቸው ሊያደርጋቸው ይችላል። እርግጥ ነው፣ ወላጆች ለልጆቻቸው ተፈጥሯዊ ፍቅር ከሌላቸው ልጆቹ ከልባቸው መታዘዝ ይከብዳቸው ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ልጅ ወላጆቹ ከልባቸው እንደሚወዱት የሚሰማው ከሆነ መመሪያቸውን ለመጣስ በሚፈተንበት ጊዜም እንኳ እነሱን ለማስደሰት ሲል ይታዘዛቸዋል። ኦስተን የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ትክክል ያልሆነ ነገር ለማድረግ የምፈተንበት ጊዜ እንዳለ አልክድም። ሆኖም ወላጆቼ የሚያወጡት መመሪያ የማያፈናፍን አይደለም፤ ደግሞም መመሪያዎቹን ለምን እንዳወጡ ያስረዱኛል፤ እኔም ሐሳቤን ስገልጽ ያዳምጡኛል። ይህም እንድታዘዛቸው ያነሳሳኛል። ወላጆቼ እንደሚወዱኝ አልጠራጠርም፤ ይህ ደግሞ እነሱን ለማስደሰት እንድጥር ያደርገኛል።”
10, 11. (ሀ) በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ ሰዎች እርስ በርስ ፍቅር እንደማይኖራቸው የሚያሳዩት የትኞቹ ባሕርያት ናቸው? (ለ) እውነተኛ ክርስቲያኖች እነማንን ጭምር ይወዳሉ?
10 ጳውሎስ የዘረዘራቸው ሌሎች መጥፎ ባሕርያትም በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ ሰዎች አንዳቸው ለሌላው ፍቅር እንደማይኖራቸው ያሳያሉ። ሐዋርያው፣ ልጆች “ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ” እንደሚሆኑ ከተናገረ በኋላ የማያመሰግኑ ግለሰቦች እንደሚኖሩ መጥቀሱ ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ሰዎች እንዲህ ያለ ባሕርይ የሚያንጸባርቁት ሌሎች ላሳዩአቸው ደግነት አድናቆት ስለሚጎድላቸው ነው። ጳውሎስ አክሎም አንዳንዶች ታማኝ እንደማይሆኑ ተናግሯል። በተጨማሪም ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ ሰዎች ይኖራሉ፤ በሌላ አባባል ከሌሎች ጋር ለመታረቅ እንቢተኞች ይሆናሉ። ከዚህም ሌላ ተሳዳቢዎች እና ከዳተኞች ይሆናሉ፤ ይህም ሰዎችን ሌላው ቀርቶ አምላክን እንኳ እንደሚተቹና የሚያዋርድ ቃል እንደሚናገሩ የሚያሳይ ነው። ጳውሎስ ስም አጥፊ የሆኑ ሰዎች እንደሚኖሩም ተናግሯል፤ እንዲህ ያሉት ግለሰቦች የሌሎችን መልካም ስም የሚያጎድፍ ወሬ ያናፍሳሉ።a
11 በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች ፍቅር የጎደላቸው ቢሆኑም የይሖዋ አገልጋዮች ግን ለሌሎች ልባዊ ፍቅር ያሳያሉ። ከጥንትም ጀምሮ የአምላክ ሕዝቦች ይህን በማድረግ ይታወቃሉ። ኢየሱስ እንደተናገረው በሙሴ ሕግ ውስጥ፣ ባልንጀራን መውደድ (አጋፔ) አምላክን ከመውደድ ቀጥሎ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ትእዛዝ ነበር። (ማቴ. 22:37-39) በተጨማሪም ኢየሱስ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች እርስ በርስ ባላቸው ፍቅር ተለይተው እንደሚታወቁ ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:34, 35ን አንብብ።) ክርስቲያኖች ጠላቶቻቸውንም ጭምር እንዲወዱ ይጠበቅባቸዋል።—ማቴ. 5:43, 44
12. ኢየሱስ ለሌሎች ፍቅር እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ ለሌሎች ጥልቅ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። ከከተማ ወደ ከተማ እየሄደ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ይናገር ነበር። ዓይነ ስውሮችን፣ አንካሶችን፣ የሥጋ ደዌ የያዛቸውን እንዲሁም መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ፈውሷል። ሙታንንም አስነስቷል። (ሉቃስ 7:22) ኢየሱስ፣ ብዙዎች ቢጠሉትም እንኳ ለሰው ልጆች ሲል ሕይወቱን ጭምር ሰጥቷል። በእርግጥም ክርስቶስ ፍቅር በማሳየት ረገድ አባቱን ፍጹም በሆነ መንገድ መስሏል። በመላው ዓለም የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ለሌሎች ፍቅር ያሳያሉ።
13. ፍቅር ማሳየታችን ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ ሊረዳቸው እንደሚችል የሚያሳየው ምንድን ነው?
13 ፍቅር ማሳየታችን ሰዎች በሰማይ ወዳለው አባታችን እንዲቀርቡ ሊያደርግ ይችላል። በታይላንድ የሚኖርን አንድ ሰው እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህ ግለሰብ በክልል ስብሰባ ላይ በወንድሞች መካከል በተመለከተው ፍቅር ልቡ ተነካ። በመሆኑም ወደ ቤቱ ከተመለሰ በኋላ በሳምንት ሁለት ቀን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደሚፈልግ ገለጸ። ግለሰቡ ለዘመዶቹ በሙሉ ምሥራቹን የተናገረ ሲሆን በክልል ስብሰባ ላይ ከተገኘ ከስድስት ወራት በኋላ በጉባኤ ስብሰባ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል አቀረበ። እኛስ ለሌሎች ፍቅር በማሳየት ረገድ እንዴት ነን? ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ቤተሰቤን፣ የጉባኤውን አባላት እንዲሁም በአገልግሎት የማገኛቸውን ሰዎች ለመርዳት የምችለውን ያህል ጥረት አደርጋለሁ? ለሌሎች የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ለማዳበር እሞክራለሁ?’
ተኩላና በግ
14, 15. ብዙዎች የትኞቹን መጥፎ ባሕርያት ያንጸባርቃሉ? አንዳንዶች ግን ምን ዓይነት ለውጥ አድርገዋል?
14 በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚኖሩ ሰዎች የሚያንጸባርቋቸው ሌሎች መጥፎ ባሕርያትም አሉ፤ ክርስቲያኖች እነዚህ ባሕርያት እንዳይጋቡባቸው ሊጠነቀቁ ይገባል። ከአምላክ የራቁ ሰዎች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ ወይም አንዳንድ ትርጉሞች እንዳስቀመጡት “መልካም የሆነውን ነገር የሚጠሉ” እንደሚሆኑ ጳውሎስ ተናግሯል። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን የማይገዙ እና ጨካኞች ናቸው። አንዳንዶች ደግሞ ግትሮች ይሆናሉ፤ ይህ ቃል “ችኩሎች” ወይም “ጥንቃቄ የሌላቸው” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል።
15 የአራዊት ዓይነት ባሕርይ የነበራቸው ብዙ ሰዎች ለውጥ ማድረግ ችለዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን ለውጥ ግሩም አድርጎ የሚገልጽ ትንቢት ይገኛል። (ኢሳይያስ 11:6, 7ን አንብብ።) ትንቢቱ እንደ ተኩላና አንበሳ ያሉት የዱር እንስሳት የበግ ጠቦትንና ጥጃን ከመሳሰሉ የቤት እንስሳት ጋር በሰላም እንደሚኖሩ ይናገራል። እንዲህ ያለ የተረጋጋ ሁኔታ የሚኖረው ‘ምድር በይሖዋ እውቀት ስለምትሞላ’ እንደሆነ ልብ እንበል። (ኢሳ. 11:9) እንስሳት ስለ ይሖዋ መማር ስለማይችሉ ይህ ትንቢት በምሳሌያዊ ሁኔታ ፍጻሜውን የሚያገኘው በሰዎች ላይ መሆን አለበት።
16. ሰዎች በባሕርያቸው ላይ ለውጥ ማድረግ እንዲችሉ መጽሐፍ ቅዱስ የረዳቸው እንዴት ነው?
16 በአንድ ወቅት እንደ ተኩላ ጨካኞች የነበሩ ብዙ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር ችለዋል። ከእነዚህ መካከል የአንዳንዶቹን ተሞክሮ jw.org/am ላይ “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” በሚሉት ርዕሶች ሥር ማግኘት ይቻላል። (የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > ሰላምና ደስታ በሚለው ሥር ይገኛል።) ይሖዋን አውቀው እሱን ማገልገል የጀመሩት እነዚህ ሰዎች ለአምላክ ያደሩ መስለው ከሚታዩ ሆኖም በሥራቸው ኃይሉን ከሚክዱ ግለሰቦች ፈጽሞ የተለዩ ናቸው፤ ለአምላክ ያደሩ መስለው የሚታዩት ሰዎች ይሖዋን የሚያመልኩ ቢመስሉም ምግባራቸው ግን ይህን የሚያሳይ አይደለም። ቀደም ሲል ጨካኝ የነበሩትና ለውጥ ያደረጉት ሰዎች ግን “እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና [ለብሰዋል]።” (ኤፌ. 4:23, 24) እነዚህ ሰዎች ስለ አምላክ ይበልጥ እያወቁ ሲሄዱ እሱ ያወጣቸውን መሥፈርቶች መከተል እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። በመሆኑም ከሚያምኑባቸው ነገሮች፣ ከአመለካከታቸውና ከምግባራቸው ጋር በተያያዘ ለውጥ ለማድረግ ይነሳሳሉ። እንዲህ ያሉ ለውጦችን ማድረግ ቀላል ባይሆንም የአምላክን ፈቃድ የማድረግ ልባዊ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ይሖዋ በመንፈሱ ይረዳቸዋል።
‘ከእነዚህ ራቅ’
17. አምላክን የማያገለግሉ ግለሰቦች መጥፎ አመለካከት ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን ምን ማድረግ እንችላለን?
17 አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው ሰው መካከል ያለው ልዩነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በግልጽ የሚታይ ሆኗል። ክርስቲያኖች፣ አምላክን የማያገለግሉ ግለሰቦች መጥፎ አመለካከት ተጽዕኖ እንዳያሳድርባቸው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። በ2 ጢሞቴዎስ 3:2-5 ላይ የተገለጹትን ባሕርያት ከሚያሳዩ ሰዎች እንድንርቅ በመንፈስ መሪነት የተሰጠንን ምክር መከተላችን የጥበብ አካሄድ ነው። መጥፎ ባሕርያት ካላቸው ሰዎች ጨርሶ መራቅ እንደማንችል የታወቀ ነው። እንደነዚህ ካሉት ሰዎች ጋር በሥራ ቦታና በትምህርት ቤት መገናኘታችን አይቀርም፤ አሊያም አብረናቸው እንኖር ይሆናል። ሆኖም የእነሱ አስተሳሰብ እንዳይጋባብንና ባሕርያቸውን መኮረጅ እንዳንጀምር መጠንቀቅ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና ይሖዋን ከሚያገለግሉ ሰዎች ጋር በመቀራረብ መንፈሳዊነታችንን ማጠናከራችን ይህን ለማድረግ ይረዳናል።
18. ንግግራችንና ምግባራችን ሌሎች አምላክን ለማወቅ እንዲነሳሱ ሊያደርጋቸው የሚችለው እንዴት ነው?
18 በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች አምላክን እንዲያውቁ መርዳት ይኖርብናል። ምሥራቹን ለመስበክ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን እንፈልግ፤ በተጨማሪም እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ በምናገኝበት ጊዜ የሰዎችን ልብ የሚነካ ነገር ለመናገር እንዲረዳን ይሖዋን እንጠይቀው። የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ሌሎች ሰዎች እንዲያውቁ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ ካደረግን መልካም ምግባራችን ለራሳችን ሳይሆን ለአምላክ ክብር ያመጣል። ይሖዋ “ፈሪሃ አምላክ በጎደለው መንገድ መኖርና ዓለማዊ ምኞቶችን መከተል ትተን አሁን ባለው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ፣ በጽድቅና ለአምላክ በማደር እንድንኖር” አሠልጥኖናል። (ቲቶ 2:11-14) አምላክን የሚያስደስቱ ባሕርያትን የምናንጸባርቅ ከሆነ ሌሎች ሰዎች ምግባራችንን ማስተዋላቸው አይቀርም፤ እንዲያውም አንዳንዶች “አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን” ሊሉ ይችላሉ።—ዘካ. 8:23
a “ስም አጥፊ” ወይም “ከሳሽ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ዲያቦሎስ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ ቃል የአምላክን ስም ያጠፋው የሰይጣን መጠሪያ ሆኖ ተሠርቶበታል።