በእርግጥ የምንኖረው “በመጨረሻው ዘመን” ውስጥ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ዘመን ብሎ የሚጠራውን ጊዜ ለመለየት የሚረዱንን በሁለት አቅጣጫ የተከናወኑ ለውጦች እንመልከት። ቅዱሳን ጽሑፎች ‘በዓለም መጨረሻ’ ማለትም በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ላይ የሚኖሩ ክስተቶችን ተንብየዋል። (ማቴዎስ 24:3) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻው ዘመን” የሚኖሩ ሰዎች ባሕርያቸውም ሆነ ድርጊታቸው የተለየ እንደሚሆን ይናገራል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1
የዓለም ሁኔታዎች ከሰዎች ባሕርይና ድርጊት ጋር ሲጣመሩ በመጨረሻው ዘመን ውስጥ እንደምንኖር ከማረጋገጣቸውም በላይ የአምላክ መንግሥት በቅርቡ አምላክን ለሚወዱ ዘላለማዊ ደስታን እንደሚያመጣ ያሳያሉ። ኢየሱስ የመጨረሻውን ዘመን እንደሚጠቁሙ ከገለጻቸው ምልክቶች ውስጥ ሦስቱን እንመርምር።
“የምጥ ጣር መጀመሪያ”
ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በተለያየ ስፍራም ራብና የመሬት መንቀጥቀጥ ይሆናል።” አክሎም “እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው [የ1954 ትርጉም]” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:7, 8) ‘እነዚህን’ ነገሮች አንድ በአንድ እየተመለከትን እንሄዳለን።
ባለፈው መቶ ዘመን በጣም ብዙ ሰዎች በጎሳ ግጭቶችና በጦርነቶች አልቀዋል። ወርልድዎች የተባለው ተቋም ያወጣው ዘገባ እንዲህ ይላል:- “[በ20ኛው] መቶ ዘመን በጦርነት ሕይወታቸውን ያጡት ሰዎች ቁጥር፣ ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ አንስቶ እስከ 1899 ድረስ በተካሄዱት ጦርነቶች ሁሉ ከሞቱት ሰዎች በሦስት እጥፍ ይበልጣል።” ጆናታን ግለቨር ሂውማኒቲ—ኤ ሞራል ሂስትሪ ኦቭ ዘ ትዌንቲዝ ሴንቸሪ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “ከ1900 እስከ 1989 ባሉት ዓመታት ውስጥ በግምት 86 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች በጦርነት አልቀዋል። . . . በ20ኛው መቶ ዘመን በተካሄዱት ጦርነቶች የተገደሉትን ሰዎች ብዛት ለመረዳት ይከብዳል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ሁለት ሦስተኛ (58 ሚሊዮን) የሚሆኑት ያለቁት በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች በመሆኑ የሟቾቹን ቁጥር በክፍለ ዘመኑ ውስጥ ለመከፋፈል መሞከር እውነታውን ለማወቅ አይረዳም። ሆኖም በእነዚህ ጦርነቶች የሞቱትን ሰዎች ቁጥር በክፍለ ዘመኑ ውስጥ እኩል እንከፋፍል ብንል በየቀኑ 2,500 የሚያህሉ ሰዎች በጦርነት ያልቁ ነበር ማለት ነው፤ ይህም ለ90 ዓመታት ያህል በየሰዓቱ ከ100 በላይ ሰዎች ሞተዋል ማለት ይሆናል።” ዘመዶቻቸውንና ጓደኞቻቸውን ያጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ሰዎች የሚደርስባቸውን ሐዘንና ሥቃይ መገመት ትችላለህ?
ዓለማችን እህል በብዛት እንደምታመርት ባይካድም የመጨረሻው ዘመን ምልክት ከሆኑት ነገሮች መካከል የምግብ እጥረት ይገኝበታል። ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ የእህል ምርት ከሕዝብ ብዛት እድገት ጋር ሲወዳደር በከፍተኛ ደረጃ እንደጨመረ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ይሁንና ብዙ ሰዎች እህል ለመሸመት የሚያስችል በቂ ገንዘብ አሊያም ለእርሻ የሚሆን በቂ መሬት ስለሌላቸው በብዙ የዓለም ክፍሎች የምግብ እጥረት ይታያል። በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ 1.2 ቢሊዮን የሚያክሉ ሰዎች በቀን በአንድ የአሜሪካ ዶላር ወይም ከዚያ ባነሰ ገንዘብ ለመኖር ይገደዳሉ። ከእነዚህ ውስጥ 780 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በከፍተኛ ረሃብ ይሠቃያሉ። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚገምተው ከሆነ በየዓመቱ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሕፃናት ሞት ዋነኛው መንስኤ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነው።
ስለ መሬት መናወጥ የተነገረውን ትንቢት አስመልክቶስ ምን ለማለት ይቻላል? የዩናይትድ ስቴትስ የጂኦሎጂ ጥናት ተቋም እንዳለው ከ1990 ወዲህ ብቻ በሕንፃዎች ላይ ጉዳት የማድረስ ኃይል ያላቸው የምድር ነውጦች ቁጥር በየዓመቱ በአማካይ 17 ደርሷል። እንዲሁም ሕንፃዎችን ሙሉ ለሙሉ የማውደም ኃይል ያላቸው የምድር ነውጦች በአማካይ በየዓመቱ ተከስተዋል። አንድ ሌላ የመረጃ ምንጭ ደግሞ “የምድር ነውጦች ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እንደቀጠፉ” ዘግቧል። ለዚህ አንደኛው ምክንያት ከ1914 ወዲህ ባሉት ዓመታት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የምድር ነውጦች ሊከሰቱ በሚችሉባቸው አካባቢዎች መስፈራቸው ነው።
ጉልህ ሥፍራ የሚሰጣቸው ሌሎች ክንውኖች
ኢየሱስ “ቸነፈር በተለያየ ስፍራ ይከሠታል” ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) ዛሬ በሕክምናው መስክ ከመቼውም ጊዜ በላይ እድገት ቢታይም ከዚህ በፊት የነበሩትም ሆኑ አዳዲስ በሽታዎች የሰውን ዘር በከፍተኛ ደረጃ በማጥቃት ላይ ናቸው። የዩናይትድ ስቴትስ ናሽናል ኢንተለጀንስ ካውንስል ያቀረበው መረጃ እንዲህ ይላል:- “ሳንባ ነቀርሳን (ቲቢ)፣ የወባ በሽታንና ኮሌራን ጨምሮ በደንብ የሚታወቁ 20 በሽታዎች ከ1973 ወዲህ እንደገና እያገረሹ ወይም በብዙ ቦታዎች እየተስፋፉ ከመምጣታቸውም በላይ እነዚህ በሽታዎች ገዳይና መድኃኒት የማይበግራቸው ሆነዋል። ከ1973 ወዲህ ኤች አይ ቪን፣ ኢቦላን፣ ሄፐታይተስ ሲን እና ኒፓህ ቫይረስን ጨምሮ ቢያንስ 30 የሚሆኑ አዳዲስ በሽታ አምጪ ሕዋሳት የተገኙ ሲሆን ለእነዚህም ፈውስ አልተገኘላቸውም።” ቀይ መስቀል ሰኔ 28, 2000 ባወጣው ዘገባ መሠረት ባለፈው ዓመት በተላላፊ በሽታዎች ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በተፈጥሮ አደጋዎች ከሞቱት በ160 እጥፍ ይበልጣል።
ሌላው ትኩረት የሚስበው የመጨረሻው ዘመን ምልክት ደግሞ ‘የክፋት መግነን’ ነው። (ማቴዎስ 24:12) በዛሬው ጊዜ በአብዛኛው የምድር ክፍል ሰዎች ቤታቸውን ሳይቆልፉ ለመቀመጥ ወይም በምሽት ለመጓዝ አይደፍሩም። ብዙውን ጊዜ ሕገ ወጥ በሆኑ ድርጊቶች ምክንያት ስለሚከሰተው የአየር፣ የውኃና የምድር ብክለትስ ምን ለማለት ይቻላል? ይህ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ነው። የራእይ መጽሐፍ አምላክ ‘ምድርን ያጠፏትን የሚያጠፋበት ዘመን’ እንደቀጠረ ይናገራል።—ራእይ 11:18
በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ ሰዎች ባሕርይ ምን ይመስላል?
መጽሐፍ ቅዱስህን ግለጥና 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5ን አንብብ። ሐዋርያው ጳውሎስ “በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ” ተናግሯል። ከዚያም በአምላክ መሠረታዊ ሥርዓት የማይሄዱ ሰዎች ተለይተው የሚታወቁባቸውን ወደ 20 የሚጠጉ ባሕርያት ዘርዝሯል። በአካባቢህ ያሉ ሰዎች እንደነዚህ ዓይነት ባሕርያትን ሲያንጸባርቁ ተመልክተሃል? በዘመናችን የሚኖሩ ሰዎችን አስመልክቶ በቅርብ ጊዜ የተሰጡ አስተያየቶችን እንመልከት።
“ራሳቸውን የሚወዱ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:2) “[በዘመናችን ሰዎች] ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የፈለጉትን ለመፈጸም ከፍተኛ ትግል ያደርጋሉ። . . . ሰዎች እንደ አማልክት እየሆኑ መጥተዋል፤ ሌሎችም በዚህ መንገድ እንዲይዟቸው ይፈልጋሉ።”—ፋይናንሻል ታይምስ የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ
“ገንዘብን የሚወዱ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:2) “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ልክን ማወቅ በፍቅረ ንዋይ ዝንባሌ እየተዋጠ ነው። በኅብረተሰቡ ዘንድ እንደ ሀብታም የማትታይ ከሆነ በሕይወት መኖርህ ትርጉም የለውም።”—ጃካርታ ፖስት የተባለው የኢንዶኔዥያ ጋዜጣ
“ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:2) “ወላጆች የአራት ዓመት ልጃቸው ልክ እንደ [ፈረንሣዊው ንጉሥ] ሉዊ አሥራ አራተኛ ሲያዛቸው ወይም የስምንት ዓመት ልጃቸው ‘አልወድህም!’ ብሎ ሲጮኽባቸው ምን እንደሚያደርጉ ግራ ይጋባሉ።”—አሜሪካን ኤዱኬተር የተባለው የዩናይትድ ስቴትስ መጽሔት
“ታማኝ ያልሆኑ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:2 NW) “የትዳር ጓደኞቻቸውንም ሆነ ልጆቻቸውን ለመተው ፈቃደኛ የሆኑ ወንዶች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ በሥነ ምግባር እሴቶች ረገድ [ባለፉት 40 ዓመታት] ውስጥ የተካሄደ ትልቅ ለውጥ ነው።”—ዊልሰን ኳርተርሊ የተባለው የዩናይትድ ስቴትስ መጽሔት
“ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው።” (2 ጢሞቴዎስ 3:3 NW) “በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ በየዕለቱ የሚፈጸም የኃይል ድርጊት በዓለም ዙሪያ ጎልቶ የሚታይ ነገር ሆኗል።”—ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶስዬሽን የተባለ የዩናይትድ ስቴትስ መጽሔት
“ራሳቸውን የማይገዙ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:3) “በየዕለቱ በጋዜጦች ላይ በሚወጡ ርዕሰ ዜናዎች ላይ የሚቀርቡ ታሪኮች ሰዎች ራሳቸውን እንደማይገዙ፣ የሥነ ምግባር ጥንካሬ እንደሌላቸው እንዲሁም ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች የርኅራኄ ስሜት እንደጎደላቸው የሚያንጸባርቁ ናቸው። . . . ማኅበረሰባችን አሁን እንደሚያደርገው ጠብ አጫሪነትን ማበረታታቱን ከቀጠለ በምንኖርበት ኅብረተሰብ ውስጥ ሥነ ምግባር ከናካቴው ይጠፋል።”—ባንኮክ ፖስት የተባለው የታይላንድ ጋዜጣ
“ጨካኞች።” (2 ጢሞቴዎስ 3:3) “በመንገድ ላይ [በሹፌሮች መካከል]፣ በቤተሰብ ውስጥ ጥቃት ሲፈጸም፣ . . . እንዲሁም ብዙውን ጊዜ ወደ ወንጀል የሚያመራ መሠረተ ቢስና አላስፈላጊ የሆነ ጠብ በሚነሳበት ጊዜ ሰዎች ንዴትና ግልፍተኝነት ይታይባቸዋል። ወንጀል የሚፈጸመው በዘፈቀደና በድንገት በመሆኑ ሰዎች ብቻቸውን እንደሆኑ ብሎም ለአደጋ እንደተጋለጡ ሆኖ ይሰማቸዋል።”—ቢዝነስ ዴይ የተባለው የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ
“ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:4) “የፆታ ነጻነት፣ ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ጋር የሚጋጭ ንቅናቄ ሆኗል።”—ባውንድለስ የተባለው የኢንተርኔት መጽሔት
“ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:5) “[በኔዘርላንድ ትኖር የነበረች አንዲት የቀድሞ ሴተኛ አዳሪ] እንደገለጸችው [ዝሙት አዳሪነት] ሕጋዊ እንዳይሆን በሠፊው ተቃውሟቸውን የሚያሰሙት የሃይማኖት ቡድኖች ናቸው። ከዚያም ትንሽ ቆም ካለች በኋላ፣ ዝሙት አዳሪ በነበረችበት ጊዜ ከዘወትር ደንበኞቿ መካከል በርካታ [የሃይማኖት] አገልጋዮች እንደነበሩ ተናገረች። አክላም ‘ዝሙት አዳሪዎች ከሁሉ የተሻሉ ደንበኞቻቸው ሃይማኖተኞች እንደሆኑ ሁልጊዜ ይናገራሉ’ በማለት እየሳቀች ተናግራለች።”—ናሽናል ካቶሊክ ሪፖርተር የተባለው የዩናይትድ ስቴትስ ጋዜጣ
ወደፊት ምን ይጠብቀናል?
መጽሐፍ ቅዱስ እንደተነበየው በዛሬው ጊዜ ዓለም በመከራ ተሞልቷል። ሆኖም ‘የክርስቶስ መምጣትና የዓለም መጨረሻ ምልክት’ የሚሆኑትን ነገሮች በተመለከተ የተነገረው ትንቢት ጥሩ ገጽታም አለው። ኢየሱስ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:3, 14) የአምላክ መንግሥት ምሥራች ከ230 በሚበልጡ አገሮችና ደሴቶች እየተሰበከ ነው። “ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ” የተውጣጡ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ስለ መንግሥቱ በማወጁ ሥራ እየተካፈሉ ነው። (ራእይ 7:9) በዚህ ረገድ ያደረጉት ቅንዓት የታከለበት እንቅስቃሴ ምን ውጤት አስገኝቷል? ስለ መንግሥቱ ምንነት፣ ምን እንደሚያከናውንና የሚያመጣቸውን በረከቶች ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚገልጸው መልእክት በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ደርሷቸዋል ሊባል ይችላል። እውነትም፣ ‘በፍጻሜው ዘመን ዕውቀት በዝቷል።’—ዳንኤል 12:4
ይህንን እውቀት ለማግኘት ልትጥር ይገባል። ምሥራቹ ይሖዋ በሚፈልገው መጠን ከተሰበከ በኋላ ምን እንደሚሆን ተመልከት። ኢየሱስ “ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:14) በዚህ ጊዜ አምላክ ክፋትን ከምድር ላይ ያስወግዳል። ምሳሌ 2:22 እንዲህ ይላል:- “ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ።” ሰይጣንና አጋንንቱስ ምን ይሆናሉ? አሕዛብን ከዚያ በኋላ እንዳያስቱ ወደ ጥልቁ ይወረወራሉ። (ራእይ 20:1-3) ከዚያም ‘ቅኖችና ነቀፋ የሌለባቸው በምድር ላይ ጸንተው ይኖራሉ።’ እዚያም ግሩም የሆኑትን የመንግሥቱን በረከቶች ያገኛሉ።—ምሳሌ 2:21፤ ራእይ 21:3-5
ምን ማድረግ ትችላለህ?
የሰይጣን ሥርዓት መደምደሚያ በጣም እንደቀረበ ምንም ጥርጥር የለውም። በመጨረሻው ዘመን እንደምንኖር የማያስተውሉ ሰዎች መጨረሻው ሳይዘጋጁ ይመጣባቸዋል። (ማቴዎስ 24:37-39፤ 1 ተሰሎንቄ 5:2) በመሆኑም ኢየሱስ ለአድማጮቹ እንዲህ ብሏቸዋል:- “በገደብ የለሽ ሕይወት፣ በመጠጥ ብዛትና ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝልና ያ ቀን እንደ ወጥመድ ድንገት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ ይህ በመላው ምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ ይደርሳልና። ስለዚህ ከሚመጣው ሁሉ እንድታመልጡና በሰው ልጅ ፊት መቆም እንድትችሉ ሁልጊዜ ተግታችሁ ጸልዩ።”—ሉቃስ 21:34-36
የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት የሚያልፉት በሰው ልጅ ማለትም በኢየሱስ ፊት ሞገስ የሚያገኙ ብቻ ናቸው። በቀረን ጊዜ በይሖዋ አምላክና በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መጣራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ኢየሱስ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ እንዲህ ብሏል:- “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” (ዮሐንስ 17:3) እንግዲያው ስለ ይሖዋ አምላክና ስለሚፈልግብህ ነገር መማርህ የጥበብ እርምጃ ነው። በአካባቢህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ሊያስተምሩህ ፈቃደኞች ናቸው። ከእነርሱ ጋር እንድትገናኝ ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች እንድትጽፍ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልሃለን።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የመጨረሻው ዘመን ገጽታዎች
ትላልቅ ክስተቶች:-
▪ ጦርነት።—ማቴዎስ 24:6, 7
▪ የምግብ እጥረት።—ማቴዎስ 24:7
▪ የመሬት መንቀጥቀጥ።—ማቴዎስ 24:7
▪ ቸነፈር።—ሉቃስ 21:11
▪ የክፋት መግነን።—ማቴዎስ 24:12
▪ የምድር መበከል።—ራእይ 11:18
ሰዎች:-
▪ ራሳቸውን የሚወዱ። —2 ጢሞቴዎስ 3:2
▪ ገንዘብን የሚወዱ። —2 ጢሞቴዎስ 3:2
▪ ትዕቢተኞች።—2 ጢሞቴዎስ 3:2
▪ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ።—2 ጢሞቴዎስ 3:2
▪ የማያመሰግኑ።—2 ጢሞቴዎስ 3:2
▪ ታማኝ ያልሆኑ። —2 ጢሞቴዎስ 3:2 NW
▪ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው።—2 ጢሞቴዎስ 3:3 NW
▪ ራሳቸውን የማይገዙ።—2 ጢሞቴዎስ 3:3
▪ ጨካኞች።—2 ጢሞቴዎስ 3:3
▪ ተድላን የሚወዱ። —2 ጢሞቴዎስ 3:4
▪ በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ረገድ ግብዞች።—2 ጢሞቴዎስ 3:5
እውነተኛ አምላኪዎች:-
▪ የተትረፈረፈ እውቀት ያገኛሉ። —ዳንኤል 12:4
▪ በዓለም ዙሪያ ምሥራቹን ይሰብካሉ።—ማቴዎስ 24:14
[ምንጭ]
UNITED NATIONS/Photo by F. GRIFFING