በዛሬው ጊዜ የአምላክ አገልጋዮች እነማን ናቸው?
“ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው . . . እርሱም ደግሞ . . . ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን።”—2 ቆሮንቶስ 3:5, 6
1, 2. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች በሙሉ በጋራ የሚካፈሉት ምን ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር? ሆኖም ሁኔታዎች የተለወጡት እንዴት ነው?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የነበሩ ክርስቲያኖች በሙሉ በጋራ የሚያከናውኑት ትልቅ ኃላፊነት ተጥሎባቸው ማለትም ምሥራቹን የመስበክ ሥራ ተሰጥቷቸው ነበር። ሁሉም የተቀቡና የአዲሱ ቃል ኪዳን አገልጋዮች ነበሩ። አንዳንዶች በጉባኤ ማስተማርን የመሳሰሉ ተጨማሪ ኃላፊነቶች ነበሩባቸው። (1 ቆሮንቶስ 12:27-29፤ ኤፌሶን 4:11) ወላጆች በቤተሰብ ውስጥ ከባድ ኃላፊነት ነበረባቸው። (ቆላስይስ 3:18-21) ሆኖም ሁሉም መሠረታዊና ወሳኝ በሆነው የስብከት ሥራ ይካፈሉ ነበር። ክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች በተጻፉበት በመጀመሪያው ግሪክኛ ቋንቋ ይህ ኃላፊነት ዲያኮኒያ ሲሆን አገልግሎት ማለት ነው።—ቆላስይስ 4:17
2 ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ነገሮች ሁሉ እየተለወጡ መጡ። የመስበክን መብት ለራሱ ብቻ የሚይዝ የቀሳውስት ክፍል ተፈጠረ። (ሥራ 20:30) ቀሳውስት ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው ከሚጠሩት መካከል አናሳዎቹ ሲሆኑ ብዙሃኑ ደግሞ ምእመናን ተብለው ይጠራሉ። ምእመናኑ ቀሳውስቱን ለመደገፍ መዋጮ ማድረግን ጨምሮ አንዳንድ ግዴታዎች እንዳሉባቸው ትምህርት ቢሰጣቸውም በስብከት ረገድ ዳር ሆነው ከመመልከት ያለፈ ምንም ነገር አያደርጉም።
3, 4. (ሀ) በሕዝበ ክርስትና ግለሰቦች አገልጋይ የሚሆኑት እንዴት ነው? (ለ) በሕዝበ ክርስትና እንደ አገልጋይ የሚቆጠረው ማን ነው? በይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ ሁኔታው ከዚህ የተለየ የሆነውስ ለምንድን ነው?
3 ቀሳውስቱ አገልጋይ (በላቲን ትርጉም ዲያኮኖስ) እኛ ነን ይላሉ።a ይህን ሹመት ለማግኘትም ከኮሌጅ ወይም ከመንፈሳዊ ትምህርት ቤት ይመረቃሉ። ዘ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒድያ “[መሾም እና ሹመት የሚል ትርጉም ያላቸው] ‘ኦርዴይን’ እና ‘ኦርዲኔሽን’ የሚሉት [የእንግሊዝኛ] ቃላት በአንድ ኦፊሴላዊ በሆነ ሃይማኖታዊ የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት ለአገልጋዮች ወይም ለቀሳውስት የሚሰጠውን ቃሉን ከመስበክ ወይም ሥርዓተ ቁርባን ከማካሄድ አሊያም ሁለቱንም ከማከናወን ጋር የተያያዘውን ልዩ የኃላፊነት ቦታ ያመለክታሉ” በማለት ይገልጻል። አገልጋዮችን የሚሾመው ማን ነው? ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “ታሪካዊውን የኤጲስቆጶሳዊ ሥርዓት እንደያዙ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋይ አድርጎ የሚሾመው ጳጳሱ ነው። በፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን ሹመት የሚሰጠው የቀሳውስቱ የአስተዳደር አካል ነው።”
4 ስለዚህ በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አገልጋይ መሆን ለተወሰነ ቡድን ብቻ የሚሰጥ መብት ነው። በይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም። ለምን? ምክንያቱም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤ ሁኔታው እንዲህ ስላልነበረ ነው።
በእርግጥ የአምላክ አገልጋዮች እነማን ናቸው?
5. በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት እነማን ጭምር አገልጋዮች ናቸው?
5 በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ ሁሉም የይሖዋ አምላኪዎች አገልጋዮች ናቸው። መላእክት ኢየሱስን አገልግለውታል። (ማቴዎስ 4:11፤ 26:53፤ ሉቃስ 22:43) በተጨማሪም መላእክት ‘መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ሰዎች’ ያገለግላሉ። (ዕብራውያን 1:14፤ ማቴዎስ 18:10) ኢየሱስ አገልጋይ ነበር። “የሰው ልጅ ሊያገለግል . . . እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 20:28፤ ሮሜ 15:8) ስለዚህ የኢየሱስ ተከታዮች ‘ፈለጉን በቅርብ መከተል’ ካለባቸው እነርሱም አገልጋዮች ናቸው መባሉ ምንም የሚያስደንቅ አይደለም።—1 ጴጥሮስ 2:21
6. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ አገልጋይ መሆን እንዳለባቸው የጠቆመው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ጥቂት ቀደም ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ደቀ መዝሙር አድራጊዎች ማለትም አገልጋዮች መሆን ነበረባቸው። እነሱ የሚያፈሯቸው አዲሶቹ ደቀ መዛሙርት ሄዳችሁ ደቀ መዝሙር አድርጉ የሚለውን ትእዛዝ ጨምሮ ሁሉንም ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ መማር ነበረባቸው። ወንድ፣ ሴት፣ ልጅ፣ አዋቂ ሳይል እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሁሉ አገልጋይ መሆን ነበረበት።—ኢዩኤል 2:28, 29
7, 8. (ሀ) ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች አገልጋዮች መሆናቸውን የሚያሳዩት ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) አገልጋይ ሆኖ መሾምን በተመለከተ ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?
7 ከዚህ ጋር በመስማማት በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በዚያ የተገኙት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሁሉ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ‘የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ’ ተናግረዋል። (ሥራ 2:1-11) በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ “ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 10:10) ጳውሎስ እነዚህን ቃላት የተናገረው ለተወሰነ የቀሳውስት ክፍል ሳይሆን ‘በእግዚአብሔር ለተወደዱ በሮሜ ላሉ ሁሉ’ ነበር። (ሮሜ 1:1, 7) በተመሳሳይም ‘በኤፌሶን ያሉ ቅዱሳንና በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉ ታማኞች’ ሁሉ ‘እግሮቻቸው በሰላም ወንጌል መጫማት’ ነበረባቸው። (ኤፌሶን 1:1 NW ፤ 6:15, 16) እንዲሁም ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የተጻፈውን ደብዳቤ የሰሙ ሁሉ ‘የተስፋቸውን ምሥክርነት ሳያወላውሉ አጥብቀው መያዝ’ ነበረባቸው።—ዕብራውያን 10:23
8 ሆኖም አንድ ሰው አገልጋይ የሚሆነው መቼ ነው? በሌላ አነጋገር አገልጋይ ሆኖ የሚሾመው መቼ ነው? የሚሾመውስ ማን ነው?
አገልጋይ ሆኖ መሾም—መቼ?
9. ኢየሱስ አገልጋይ ሆኖ የተሾመው መቼ ነው? የተሾመውስ በማን ነው?
9 አንድ ሰው አገልጋይ ሆኖ የሚሾመው መቼ እንደሆነና ማን እንደሚሾመው ለማወቅ የኢየሱስን ሁኔታ እንመርምር። ኢየሱስ አገልጋይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ከመንፈሳዊ ትምህርት ቤት የተሰጠው የሹመት ሰርተፊኬት ወይም ዲግሪ አልነበረውም፤ በማንም ሰውም አልተሾመም። ታዲያ አገልጋይ ነበር ብለን መናገር የምንችለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፣ . . . ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛል” የሚሉት በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት የኢሳይያስ ቃላት በእሱ ላይ ፍጻሜያቸውን በማግኘታቸው ነው። (ሉቃስ 4:17-19፤ ኢሳይያስ 61:1) እነዚህ ቃላት ኢየሱስ ወንጌልን የመስበክ ተልዕኮ ተሰጥቶት እንደነበረ በማያሻማ መንገድ ይገልጻሉ። ይህን ተልዕኮ የሰጠው ማን ነው? ለዚህ ሥራ የቀባው የይሖዋ መንፈስ እስከሆነ ድረስ ኢየሱስን አገልጋይ አድርጎ የሾመው ይሖዋ አምላክ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ የሆነው መቼ ነው? የይሖዋ መንፈስ በኢየሱስ ላይ ያረፈው በተጠመቀበት ጊዜ ነበር። (ሉቃስ 3:21, 22) ስለዚህ አገልጋይ ሆኖ የተሾመው በተጠመቀበት ጊዜ ነው።
10. አንድ ክርስቲያን አገልጋይ ‘ብቃቱን’ የሚያገኘው ከማን ነው?
10 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለነበሩት የኢየሱስ ተከታዮችስ ምን ለማለት ይቻላል? የእነሱም የአገልጋይነት ሹመት ቢሆን የመጣው ከይሖዋ ነው። ጳውሎስ “ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው . . . እርሱም ደግሞ . . . ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን” ሲል ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 3:5, 6) ይሖዋ አምላኪዎቹን ለአገልጋይነት ብቁ የሚያደርጋቸው እንዴት ነው? ጳውሎስ ‘በክርስቶስ ወንጌል የእግዚአብሔር አገልጋይ’ ሲል የጠራውን የጢሞቴዎስን ሁኔታ እንመርምር።—1 ተሰሎንቄ 3:2
11, 12. ጢሞቴዎስ አገልጋይ ወደመሆን እድገት ያደረገው እንዴት ነው?
11 ለጢሞቴዎስ የተነገሩት የሚከተሉት ቃላት እንዴት አገልጋይ ሊሆን እንደበቃ እንድናስተውል ይረዱናል:- “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት [“እንድታምን በተደረግህበት፣” NW ] ነገር ጸንተህ ኑር፣ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፣ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) ለሌሎች እንዲመሰክር የሚገፋፋው የጢሞቴዎስ እምነት የተመሠረተው ከቅዱሳን ጽሑፎች ባገኘው እውቀት ላይ ነበር። ይህን ለማድረግ የሚያስፈልገው በግል ማንበብ ብቻ ነበር ማለት ነው? አይደለም። ጢሞቴዎስ ትክክለኛ እውቀትና ስላነበበው ነገር መንፈሳዊ ማስተዋል እንዲያገኝ የሌሎች እገዛ አስፈልጎት ነበር። (ቆላስይስ 1:9) ስለዚህ ጢሞቴዎስ ‘እንዲያምን ተደርጎ’ ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎችን ያወቀው ‘ከሕፃንነቱ’ ጀምሮ ስለሆነ ከሁኔታዎች ለመረዳት እንደሚቻለው አባቱ የሚያምን ስላልነበር የመጀመሪያ አስተማሪዎቹ እናቱና ሴት አያቱ መሆን አለባቸው።—2 ጢሞቴዎስ 1:5
12 ሆኖም ጢሞቴዎስ አገልጋይ እንዲሆን ያበቃው ይህ ብቻ አልነበረም። አንደኛ ነገር አቅራቢያው በሚገኙ ጉባኤዎች ከነበሩ ክርስቲያኖች ጋር በመሰብሰብ እምነቱን አጠንክሮ ነበር። ይህን እንዴት እናውቃለን? ምክንያቱም ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ ጢሞቴዎስን ሲያገኘው ‘በልስጥራንና በኢቆንዮን ያሉ ወንድሞች በመልካም የመሰከሩለት’ ወጣት ነበር። (ሥራ 16:2) ከዚህም በተጨማሪ በዚያ ዘመን አንዳንድ ወንድሞች ጉባኤዎችን ለማጠንከር ደብዳቤዎችን ይጽፉ ነበር። እንዲሁም እነርሱን ለመገንባት የበላይ ተመልካቾች ጉባኤዎችን ይጎበኙ ነበር። እንዲህ ያሉት ዝግጅቶች እንደ ጢሞቴዎስ ያሉ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ እንዲያድጉ እገዛ አድርገዋል።—ሥራ 15:22-32፤ 1 ጴጥሮስ 1:1, 2
13. ጢሞቴዎስ አገልጋይ ሆኖ የተሾመው መቼ ነው? መንፈሳዊ እድገቱ በዚያ አላበቃም የምትለው ለምንድን ነው?
13 በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ከሚገኘው የኢየሱስ ትእዛዝ አንጻር ሲታይ ጢሞቴዎስ የነበረው እምነት የኢየሱስን ምሳሌ እንዲኮርጅና እንዲጠመቅ እንዳነሳሳው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ማቴዎስ 3:15-17፤ ዕብራውያን 10:5-9) ይህም ጢሞቴዎስ በሙሉ ነፍስ ራሱን ለአምላክ መወሰኑን የሚያሳይ እርምጃ ነበር። ጢሞቴዎስ ሲጠመቅ አገልጋይ ሆነ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሕይወቱ፣ ጉልበቱና ያለው ማንኛውም ነገር ሁሉ የአምላክ ንብረት ሆነ። ይህም የአምልኮቱ ማለትም የሚያቀርበው “ቅዱስ አገልግሎት” አብይ ክፍል ነበር። ሆኖም ጢሞቴዎስ አገልጋይ በመሆኑ ብቻ ረክቶ ቁጭ አላለም። በመንፈሳዊ ማደጉን በመቀጠል የጎለመሰ ክርስቲያን አገልጋይ ሆኗል። ጢሞቴዎስን ለዚህ የረዳው እንደ ጳውሎስ ከመሳሰሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር መቀራረቡ፣ የግል ጥናት ማድረጉና በቅንዓት መስበኩ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 4:14፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:2፤ ዕብራውያን 6:1, 2
14. ዛሬ ‘ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ ያለው’ አንድ ሰው አገልጋይ ለመሆን እድገት የሚያደርገው እንዴት ነው?
14 ዛሬም አንድ ሰው ለክርስቲያናዊ አገልግሎት የሚሾምበት መንገድ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። ‘ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ’ ያለው ሰው ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ እንዲማር በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት እርዳታ ይሰጠዋል። (ሥራ 13:48) ግለሰቡም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሕይወቱ ላይ ተግባራዊ ማድረግንና ለአምላክ ትርጉም ያለው ጸሎት ማቅረብን ይማራል። (መዝሙር 1:1-3፤ ምሳሌ 2:1-9፤ 1 ተሰሎንቄ 5:17, 18) ከሌሎች የእምነት አጋሮች ጋር አብሮ መሰብሰብና “ታማኝና ልባም ባሪያ” ካደረጋቸው ዝግጅቶች መጠቀም ይጀምራል። (ማቴዎስ 24:45-47፤ ምሳሌ 13:20፤ ዕብራውያን 10:23-25) በዚህ መንገድ ወጥ በሆነ የትምህርት መርሐ ግብር እድገት እያደረገ ይሄዳል።
15. አንድ ሰው በሚጠመቅበት ጊዜ ምን ይከናወናል? (በተጨማሪ የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
15 በመጨረሻም ለይሖዋ አምላክ ፍቅር ያዳበረውና በቤዛዊ መሥዋዕቱ ላይ ጠንካራ እምነት የገነባው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ራሱን ሙሉ በሙሉ ለሰማያዊ አባቱ መወሰን ይፈልጋል። (ዮሐንስ 14:1) ይህንንም ውሳኔውን በግል በሚያቀርበው ጸሎት ከገለጸ በኋላ ይህንን በግሉ የወሰደውን እርምጃ ይፋ ለማድረግ ይጠመቃል። ሙሉ በሙሉ ራሱን የወሰነ የአምላክ አገልጋይ ማለትም ዲያኮኖስ መሆኑ የሚታወቀው በዚህ ጊዜ ስለሆነ ጥምቀቱ አገልጋይ ሆኖ የሚሾምበት ሥርዓት ነው ሊባል ይችላል። ከዓለም የተለየ ሆኖ መኖር አለበት። (ዮሐንስ 17:16፤ ያዕቆብ 4:4) ያለገደብ ወይም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ራሱን “እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት” አድርጎ አቅርቧል። (ሮሜ 12:1)b አሁን የክርስቶስን ምሳሌ በመኮረጅ የአምላክ አገልጋይ ሆነ ማለት ነው።
ክርስቲያናዊ አገልግሎት ምንድን ነው?
16. የጢሞቴዎስ አንዳንድ የአገልጋይነት ኃላፊነቶች ምን ነበሩ?
16 የጢሞቴዎስ አገልግሎት ምንን የሚጨምር ነበር? የጳውሎስ የጉዞ ጓደኛ የመሆን ልዩ ሥራ ነበረው። ሽማግሌ ከሆነም በኋላ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን ለማስተማርና ለማጠንከር ብዙ ደክሟል። ሆኖም እንደ ኢየሱስና እንደ ጳውሎስ ሁሉ የእሱም አገልግሎት ያተኮረው ምሥራቹን በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ ነበር። (ማቴዎስ 4:23፤ 1 ቆሮንቶስ 3:5) ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፣ መከራን ተቀበል፣ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፣ አገልግሎትህን ፈጽም” ብሎት ነበር።—2 ጢሞቴዎስ 4:5፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
17, 18. (ሀ) ክርስቲያኖች የተሰማሩት በየትኛው አገልግሎት ነው? (ለ) ለአንድ ክርስቲያን አገልጋይ የስብከቱ ሥራ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
17 ዛሬ ባለው ክርስቲያናዊ አገልግሎትም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ወደሚገኘው መዳን ሌሎችን በመምራትና ገር የሆኑ ሰዎች የይሖዋን ስም እንዲጠሩ በማስተማር በወንጌላዊነት ሥራ ማለትም ለሕዝብ በሚሰጥ አገልግሎት ይካፈላሉ። (ሥራ 2:21፤ 4:10-12፤ ሮሜ 10:13) በሥቃይና በመከራ ላይ ለሚገኘው የሰው ልጅ ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት እንደሆነና አምላካዊ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመላለስ አሁንም እንኳ የተሻለ ሕይወት ለመምራት እንደሚያስችል ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሱ ያስረዳሉ። (መዝሙር 15:1-5፤ ማርቆስ 13:10) ሆኖም የአንድ ክርስቲያን አገልጋይ ስብከት በማኅበራዊ ኑሮ ችግሮች ላይ ያተኮረ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘ለአምላክ ያደሩ መሆን ለአሁኑም ሆነ ለሚመጣው ሕይወት ተስፋ እንደሚሰጥ’ ያስተምራል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8 NW
18 እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ አገልጋዮች ከክርስቲያን ወደ ክርስቲያን ሊለያዩ የሚችሉ ተጨማሪ የአገልግሎት መብቶችም አሏቸው። ብዙዎቹ የቤተሰብ ግዴታዎች አሉባቸው። (ኤፌሶን 5:21–6:4) ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች የጉባኤ ኃላፊነቶች አሉባቸው። (1 ጢሞቴዎስ 3:1, 12, 13፤ ቲቶ 1:5፤ ዕብራውያን 13:7) ብዙ ክርስቲያኖች የመንግሥት አዳራሽ በመገንባት ሥራ ያግዛሉ። አንዳንዶች ደግሞ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የቤቴል ቤቶች ውስጥ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነው የማገልገል ግሩም መብት አግኝተዋል። ሆኖም ሁሉም ክርስቲያን አገልጋዮች ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ይካፈላሉ። ከዚህ ሥራ ነፃ የሆነ ማንም የለም። አንድ ሰው እውነተኛ ክርስቲያን አገልጋይ መሆኑ የሚታወቀው በዚህ ሥራ ሲካፈል ነው።
አንድ ክርስቲያን አገልጋይ ሊኖረው የሚገባ ዝንባሌ
19, 20. ክርስቲያን አገልጋዮች ምን ዝንባሌ መኮትኮት አለባቸው?
19 አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ልዩ ክብር እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፤ ስለሆነም “ቄስ” እና “አባ” እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ ስሞች ይጠራሉ። ሆኖም አንድ ክርስቲያን አገልጋይ ልዩ ክብር ሊሰጠው የሚገባው ይሖዋ ብቻ መሆኑን ያውቃል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) እንዲህ ያለውን ከፍ ያለ ክብር ወይም ልዩ ማዕረግ ካልተሰጠኝ የሚል ክርስቲያን አገልጋይ የለም። (ማቴዎስ 23:8-12) ዲያኮኒያ የሚለው ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ “አገልግሎት” የሚል እንደሆነ ያውቃል። ከዚህ ቃል ጋር ተዛማጅ የሆነው ግስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማዕድ ከማገልገል ጋር በተያያዘ ተሠርቶበታል። (ሉቃስ 4:39፤ 17:8፤ ዮሐንስ 2:5) ምንም እንኳ ከክርስቲያናዊ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የቃሉ አገባብ ከፍ ያለ ደረጃን የሚያመለክት ቢሆንም ዞሮ ዞሮ ዲያኮኖስ ማለት አገልጋይ ማለት ነው።
20 ስለዚህ የትኛውም ክርስቲያን አገልጋይ ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከትበት ምንም ምክንያት የለውም። እውነተኛ ክርስቲያን አገልጋዮች በጉባኤ ውስጥ ልዩ ኃላፊነት ያላቸውም እንኳ ትሑት አገልጋዮች ናቸው። ኢየሱስ “ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፣ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 20:26, 27) ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ማለትም የመጨረሻ ዝቅተኛ ባሪያ የሚሠራውን ሥራ በመሥራት ሊያዳብሩት የሚገባቸውን ትክክለኛ ዝንባሌ አሳይቷቸዋል። (ዮሐንስ 13:1-15) እንዴት ያለ የትሕትና አገልግሎት ነው! ስለዚህ ክርስቲያን አገልጋዮች ይሖዋ አምላክንና ኢየሱስ ክርስቶስን በትሕትና ያገለግላሉ። (2 ቆሮንቶስ 6:4፤ 11:23) አንዳቸው ሌላውን በሚያገለግሉበት ጊዜም የትሕትናን ባሕርይ ያንጸባርቃሉ። እንዲሁም ምሥራቹን በመስበክ ያለምንም ራስ ወዳድነት የማያምኑ ጎረቤቶቻቸውን ያገለግላሉ።—ሮሜ 1:14, 15፤ ኤፌሶን 3:1-7
በአገልግሎቱ መጽናት
21. ጳውሎስ በአገልግሎቱ በመጽናቱ የተካሰው እንዴት ነው?
21 አገልጋይ መሆን ለጳውሎስ ጽናት ጠይቆበታል። ምሥራቹን ለእነሱ ለመስበክ ሲል ብዙ መከራ እንደተቀበለ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ነግሯቸዋል። (ቆላስይስ 1:24, 25) ሆኖም በአገልግሎቱ በመጽናቱ ብዙዎች ምሥራቹን ተቀብለው አገልጋዮች ሊሆኑ ችለዋል። መንፈሳዊ ፍጥረታት ሆነው ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የመሆን ተስፋ በመያዝ የአምላክ ልጆችና የኢየሱስ ወንድሞች የመሆን መብት አግኝተዋል። ጽናት የሚያስገኘው እንዴት ያለ ክብራማ ሽልማት ነው!
22, 23. (ለ) ዛሬ ያሉት ክርስቲያን አገልጋዮች መጽናት የሚያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያናዊ ጽናት ምን ግሩም ውጤት ያስገኛል?
22 በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮችም ጽናት ማሳየታቸው አስፈላጊ ነው። ብዙዎች ከበሽታ አሊያም የዕድሜ መግፋት ከሚያስከትለው ሥቃይ ጋር በየዕለቱ ይታገላሉ። ወላጆች፣ ብዙዎቹም የትዳር ጓደኛቸው ከጎናቸው ሳይኖር ልጆቻቸውን ለማሳደግ ሌት ተቀን ደፋ ቀና ይላሉ። ልጆች በትምህርት ቤት የከበቧቸውን መጥፎ ተጽዕኖዎች በድፍረት ይቋቋማሉ። ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ከባድ የኑሮ ትግል አለባቸው። እንዲሁም ብዙዎች በሚደርስባቸው ስደት ይሠቃያሉ ወይም ያለንበት ‘አስጨናቂ ዘመን’ የሚያስከትልባቸውን መከራ ይጋፈጣሉ! (2 ጢሞቴዎስ 3:1) አዎን፣ ዛሬ ያሉ ስድስት ሚልዮን የሚያህሉ የይሖዋ አገልጋዮች እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በብዙ መጽናት በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን’ ሊሉ ይችላሉ። (2 ቆሮንቶስ 6:4) ክርስቲያን አገልጋዮች ተስፋ አይቆርጡም። ለጽናታቸው በእርግጥም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።
23 ከዚህም በላይ በጳውሎስ ሁኔታ እንደታየው መጽናት ግሩም ውጤት አለው። በመጽናት ከይሖዋ ጋር ያለን የጠበቀ ዝምድና እንዲቀጥል ከማድረጋችንም በላይ ልቡን ደስ እናሰኘዋለን። (ምሳሌ 27:11) የራሳችንን እምነት እናጠነክራለን እንዲሁም ደቀ መዛሙርት በማፍራት ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት በቁጥር እንዲጨምር እናደርጋለን። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ይሖዋ አገልጋዮቹን እየደገፈ ሲሆን አገልግሎታቸውንም እየባረከው ነው። ከዚህም የተነሳ የ144, 000ዎቹ ቀሪዎች የተሰበሰቡ ሲሆን በሚልዮን የሚቆጠሩት ሌሎች ደግሞ ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት የተረጋገጠ ተስፋ እንዲኖራቸው አድርጓል። (ሉቃስ 23:43፤ ራእይ 14:1) በእርግጥም ክርስቲያናዊ አገልግሎት የይሖዋ ምሕረት መግለጫ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:1) ሁላችንም እንደ ውድ ነገር አድርገን እንመልከተው፤ እንዲሁም የሚያስገኘው ውጤት ዘላለማዊ ስለሆነ አመስጋኞች እንሁን።—1 ዮሐንስ 2:17
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድ ራሱን የቻለ ሹመት የሆነው “ዲያቆን” የሚለው ቃል የመጣው ዲያኮኖስ ከሚለው ግሪክኛ ቃል ነው። ሴቶች ዲያቆን ሆነው ሊሾሙ በሚችሉባቸው አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ሴቶቹ ዲያቆኒት ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ።
b ምንም እንኳ ሮሜ 12:1 በቀጥታ የሚያመለክተው ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ‘በሌሎች በጎችም’ ላይ ይሠራል። (ዮሐንስ 10:16) እነዚህም ‘ያገለግሉት ዘንድ የእግዚአብሔርንም ስም ይወድዱ ዘንድ ባሪያዎቹም ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ይጠጋሉ።’—ኢሳይያስ 56:6
ልታብራራ ትችላለህ?
• የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በሙሉ በጋራ የሚካፈሉት ምን ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር?
• አንድ ክርስቲያን አገልጋይ የሚሾመው መቼና በማን ነው?
• አንድ ክርስቲያን አገልጋይ ምን ዓይነት ዝንባሌ መኮትኮት አለበት?
• አንድ ክርስቲያን አገልጋይ የተለያዩ ችግሮች ቢደርሱበትም መጽናት ያለበት ለምንድን ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጢሞቴዎስ የአምላክን ቃል ከሕፃንነቱ ጀምሮ ተምሯል። በተጠመቀ ጊዜ የተሾመ አገልጋይ ሆነ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥምቀት አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ መወሰኑን የሚያሳይበት እርምጃ ሲሆን አገልጋይ ሆኖ የሚሾመውም በዚሁ ወቅት ነው
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን አገልጋዮች ለማገልገል ፈቃደኞች ናቸው