ወላጆች—ልጆቻችሁን ከጨቅላነታቸው ጀምሮ አሠልጥኗቸው
“እነሆ፤ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፤ የማሕፀንም ፍሬ ከቸርነቱ የሚገኝ ነው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (መዝ. 127:3) ከዚህ አንጻር ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጅ ሲወልዱ በደስታ መፈንደቃቸው አያስገርምም።
እርግጥ ነው፣ ልጅ መውለድ የሚያስደስት ነገር ቢሆንም ከባድ ኃላፊነትም ያስከትላል። ልጁ ሲያድግ ጤናማ ሰው እንዲሆን የተመጣጠነ ምግብ አዘውትሮ መመገብ ያስፈልገዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ልጁ እውነተኛውን አምልኮ እንዲይዝ መንፈሳዊ ምግብና የወላጆቹ ሥልጠና ያስፈልገዋል፤ ወላጆቹ የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች በውስጡ ሊቀርጹ ይገባል። (ምሳሌ 1:8) ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና መጀመር ያለበት መቼ ነው? ምን ነገሮችንስ ሊያጠቃልል ይገባል?
ወላጆች መመሪያ ያስፈልጋቸዋል
ከዳን ነገድ የሆነውን ማኑሄን እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ ማኑሄ የሚኖረው በጥንቷ እስራኤል በምትገኘው ጾርዓ የተባለች ከተማ ነበር። የይሖዋ መልአክ፣ መካን ለሆነችው የማኑሄ ሚስት ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ነገራት። (መሳ. 13:2, 3) ታማኙ ማኑሄና ሚስቱ ይህን ሲሰሙ በጣም ተደስተው መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ያሳሰቧቸው ነገሮችም ነበሩ። ስለዚህ ማኑሄ እንዲህ ብሎ ጸለየ፦ “ጌታ ሆይ፤ የሚወለደውን ልጅ እንዴት አድርገን ማሳደግ [እ]ንዳለብን እንዲያስተምረን ያ ወደ እኛ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እንደ ገና እንዲመጣ ታደርግ ዘንድ እለምንሃለሁ።” (መሳ. 13:8) ማኑሄና ሚስቱ ልጃቸውን የሚያሳድጉበት መንገድ አሳስቧቸው ነበር። ለልጃቸው ለሳምሶን የአምላክን ሕግ እንዳስተማሩት ምንም ጥርጥር የለውም፤ ደግሞም ከሁኔታዎቹ ማየት እንደሚቻለው ጥረታቸው መና አልቀረም። መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔርም መንፈስ . . . [ሳምሶንን] ያነቃቃው ጀመር” ይላል። በመሆኑም ሳምሶን የእስራኤል መስፍን ለመሆን የበቃ ሲሆን በርካታ አስገራሚ ነገሮችን አከናውኗል።—መሳ. 13:25፤ 14:5, 6፤ 15:14, 15
ወላጆች ለልጆቻቸው ሥልጠና መስጠት መጀመር ያለባቸው መቼ ነው? የጢሞቴዎስ እናት ኤውንቄና አያቱ ሎይድ፣ ጢሞቴዎስን ‘ከጨቅላነቱ ጀምሮ ቅዱሳን መጻሕፍትን’ አስተምረውታል። (2 ጢሞ. 1:5፤ 3:15) በመሆኑም ጢሞቴዎስ ቅዱሳን መጻሕፍትን መማር የጀመረው ገና በሕፃንነቱ ነው።
ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጃቸውን ‘ከጨቅላነቱ ጀምሮ’ ለማሠልጠን እንዲችሉ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት መጸለያቸውና አስቀድመው እቅድ ማውጣታቸው ጥበብ ነው። ምሳሌ 21:5 “የትጕህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል” ይላል። ወላጆች፣ ገና ልጁ ከመወለዱ በፊት የታሰበበት ዝግጅት እንደሚያደርጉ የታወቀ ነው። እንዲያውም ሕፃኑ የሚያስፈልጉትን ነገሮች በዝርዝር ጽፈው ይይዙ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ መንፈሳዊ ሥልጠና ስለሚሰጡበት መንገድ አስቀድመው ማሰብ ይኖርባቸዋል። ዓላማቸው ልጃቸውን ገና ከጨቅላነቱ ጀምሮ ማሠልጠን ሊሆን ይገባል።
ኧርሊ ቻይልድሁድ ካውንትስ—ኤ ፕሮግራሚንግ ጋይድ ኦን ኧርሊ ቻይልድሁድ ኬር ፎር ዴቨሎፕመንት የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ልጅ ከተወለደ በኋላ ያሉት የመጀመሪያዎቹ ወራት ከአእምሮ እድገት ጋር በተያያዘ ወሳኝ ናቸው። በእነዚህ ወራት፣ [የነርቭ ሴሎችን ጫፍ የሚያገናኙት] ሲናፕሶች ማለትም ትምህርት ለመቅሰም የሚያስችሉን የነርቭ ጫፎች ቁጥር በሃያ እጥፍ ይጨምራል።” ወላጆች፣ ከልጃቸው የአእምሮ እድገት ጋር በተያያዘ ወሳኝ በሆነው በዚህ አጭር ጊዜ ተጠቅመው በልጃቸው አእምሮ ውስጥ መንፈሳዊ ነገሮችን ለመቅረጽ ጥረት ማድረግ መጀመራቸው ምንኛ ብልህነት ነው!
አቅኚ የሆነች አንዲት እናት ስለ ልጇ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ወር ከሆናት ጊዜ አንስቶ ይዣት አገልግሎት እወጣ ነበር። በወቅቱ ምንም የምታውቀው ነገር ባይኖርም ገና በጨቅላነቷ እንዲህ ያለ አጋጣሚ ማግኘቷ በጣም እንደጠቀማት ይሰማኛል። ሁለት ዓመት ሲሆናት አገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች ትራክት ለማበርከት አትፈራም ነበር።”
ልጆችን ገና ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ማሠልጠን ጥሩ ፍሬ ያስገኛል። ያም ቢሆን ለልጆች መንፈሳዊ ሥልጠና መስጠት ተፈታታኝ ነው።
“አመቺ የሆነውን ጊዜ ግዙ”
ወላጆች ከሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች አንዱ ልጆች የሚቁነጠነጡ ወይም ትኩረታቸውን ሰብስበው ለመቀመጥ የሚቸገሩ መሆኑ ነው። ልጆች ትኩረታቸው በቀላሉ ሊሰረቅ ይችላል። የማወቅ ጉጉት ያላቸው ከመሆኑም ሌላ በአካባቢያቸው ያሉትን ነገሮች በሙሉ መመልከት ይፈልጋሉ። ታዲያ ወላጆች፣ ልጃቸው የሚያስተምሩትን ነገር በትኩረት እንዲያዳምጥ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?
ሙሴ ምን እንዳለ እስቲ እንመልከት። ዘዳግም 6:6, 7 ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር።” በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው “አስጠናቸው” የሚለው ቃል አንድን ነገር ደግሞ ደጋግሞ ማስተማርን ያመለክታል። ትናንሽ ልጆች፣ በየተወሰነ ጊዜ ውኃ መጠጣት እንደሚያስፈልገው ችግኝ ናቸው። መደጋገም፣ አዋቂዎች አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን እንዳይረሱ የሚረዳቸው ከሆነ ልጆችንም እንደሚረዳቸው ጥርጥር የለውም!
ወላጆች የአምላክን እውነት ለልጆቻቸው ለማስተማር ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስፈልጋቸዋል። በውጥረት በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ ይህን ለማድረግ ጊዜ መመደብ ተፈታታኝ እንደሚሆን የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ጳውሎስ፣ ለክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች “አመቺ የሆነውን ጊዜ [እንድንገዛ]” አበረታቶናል። (ኤፌ. 5:15, 16) ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? የአንድን ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ምሳሌ እንመልከት፤ የዚህ ወንድም ባለቤት የዘወትር አቅኚ በመሆኗ ፕሮግራሟ የተጣበበ ነው፤ ይህ ወንድም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የወላጅነትና የጉባኤ ኃላፊነቱን መወጣት እንዲሁም ሰብዓዊ ሥራውን ማከናወን ተፈታታኝ ሆኖበት ነበር። ታዲያ እነዚህ ባልና ሚስት ልጃቸውን ለማሠልጠን ጊዜ ማግኘት የቻሉት እንዴት ነው? አባትየው እንዲህ ብሏል፦ “በየዕለቱ ጠዋት ላይ ወደ ሥራ ከመሄዴ በፊት እኔና ባለቤቴ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ ከተባለው መጽሐፍ ወይም ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር ከተሰኘው ቡክሌት ላይ ለልጃችን እናነብላታለን። ምሽት ላይም ከመተኛቷ በፊት እናነብላታለን፤ እንዲሁም አገልግሎት ስንሄድ ይዘናት እንወጣለን። ልጃችንን ገና በሕፃንነቷ ለማሠልጠን የሚያስችለን ይህ አጋጣሚ እንዲያመልጠን አንፈልግም።”
‘ወንዶች ልጆች እንደ ፍላጾች ናቸው’
ልጆቻችን ሲያድጉ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች እንዲሆኑ እንደምንፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና ልጆቻችንን የምናሠለጥንበት ዋነኛ ምክንያት አምላክን ከልባቸው እንዲወዱ መርዳት ስለምንፈልግ ነው።—ማር. 12:28-30
መዝሙር 127:4 “በወጣትነት የተገኙ ወንዶች ልጆች፣ በጦረኛ እጅ እንዳሉ ፍላጾች ናቸው” ይላል። እዚህ ጥቅስ ላይ ልጆች፣ ዒላማውን ለመምታት በጥንቃቄ መነጣጠር ካለበት ፍላጻ ጋር ተመሳስለዋል። ቀስተኛው፣ ፍላጻውን ካስወነጨፈው በኋላ ሊመልሰው አይችልም። ወላጆችም በተመሳሳይ ‘ፍላጾቹን’ ይዘው የሚቆዩት ማለትም ከልጆቻቸው ጋር የሚኖሩት በአንጻራዊ ሁኔታ ለአጭር ጊዜ ነው። ወላጆች በዚህ አጭር ጊዜ ተጠቅመው በልጆቻቸው አእምሮና ልብ ላይ የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሊቀርጹ ይገባል።
ሐዋርያው ዮሐንስ፣ መንፈሳዊ ልጆቹን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ልጆቼ አሁንም በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ እንዳሉ ከመስማት የበለጠ አመስጋኝ እንድሆን የሚያደርገኝ ምንም ነገር የለም።” (3 ዮሐ. 4) ክርስቲያን ወላጆችም ልጆቻቸው “በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ እንዳሉ” ሲመለከቱ እንደዚህ እንደሚሰማቸው የታወቀ ነው።