መለኮታዊ ብርሃን ጨለማን ገፍፎ ይጥላል!
“እግዚአብሔርም ጨለማዬን ያበራል።”—2 ሳሙኤል 22:29
1. ብርሃን ከሕይወት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?
“እግዚአብሔርም:- ብርሃን ይሁን አለ፤ ብርሃንም ሆነ።” (ዘፍጥረት 1:3) በእነዚህ ከፍተኛ ትርጉም ያዘሉ ቃላት አማካኝነት በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው የፍጥረት ዘገባ ይሖዋ የብርሃን ምንጭ እንደሆነ ይገልጻል። ያለ ብርሃን በምድር ላይ ሕይወት ሊኖር አይችልም። ይሖዋ የመንፈሳዊም ብርሃን ምንጭ ሲሆን ይህ ብርሃን ሕይወታችንን ለመምራት በጣም ይጠቅመናል። (መዝሙር 43:3) ንጉሥ ዳዊት “የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፤ በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን” ብሎ በመጻፍ በመንፈሳዊ ብርሃንና በሕይወት መካከል የቅርብ ዝምድና እንዳለ ገልጿል።—መዝሙር 36:9
2. ጳውሎስ እንደገለጸው ብርሃን ከምን ጋር በቅርብ የተዛመደ ነው?
2 ዳዊት ከኖረበት ዘመን ከ1, 000 ዓመት ገደማ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ የፍጥረት ዘገባን ጠቅሶ ተናግሯል። በቆሮንቶስ ለሚገኘው የክርስቲያን ጉባኤ “በጨለማ፣ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና” ሲል ጽፏል። ከዚያም ጳውሎስ መንፈሳዊ ብርሃን ይሖዋ ከሚሰጠው እውቀት ጋር የቅርብ ትስስር እንዳለው ሲገልጽ “በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ [አ]በራ” በማለት አክሎ ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 4:6) ይህ ብርሃን ወደ እኛ የሚደርሰው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ —ብርሃን የሚያስተላልፍ መሣሪያ
3. ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የሰጠን ብርሃን ምንድን ነው?
3 ይሖዋ በአንደኛ ደረጃ መንፈሳዊ ብርሃን የሚያስተላልፈው በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠናና የአምላክን እውቀት ስንቀስም ብርሃኑን እንዲያበራልን ፈቅደናል ማለት ነው። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት በዓላማዎቹ ላይ ብርሃን የሚፈነጥቅልን ከመሆኑም በላይ ፈቃዱን እንዴት መፈጸም እንደምንችል ያሳውቀናል። ይህም ሕይወታችን ዓላማ እንዲኖረውና መንፈሳዊ ፍላጎቶቻችንን እንድናረካ ይረዳናል። (መክብብ 12:1፤ ማቴዎስ 5:3) ኢየሱስ የሙሴን ሕግ ጠቅሶ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል” ብሎ በመግለጽ ለመንፈሳዊ ፍላጎቶቻችን ትኩረት መስጠት እንዳለብን አበክሮ ተናግሯል።—ማቴዎስ 4:4፤ ዘዳግም 8:3
4. ኢየሱስ “የዓለም ብርሃን” የሆነው በምን መንገድ ነው?
4 ኢየሱስ መንፈሳዊ ብርሃን እንደሆነ ተናግሯል። እንዲያውም ራሱን “የዓለም ብርሃን” በማለት ጠርቷል። ደግሞም “የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:12) ይህ አባባል ኢየሱስ የይሖዋን እውነት ለሰው ልጆች በማስተላለፍ ረገድ ያለውን ቁልፍ ሚና እንድንገነዘብ ይረዳናል። ከጨለማ ለመውጣትና በአምላክ ብርሃን ለመመላለስ ኢየሱስ የተናገረውን በሙሉ ማዳመጥና መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ምሳሌውንና ያስተማራቸውን ትምህርቶች በጥብቅ መከተል ይኖርብናል።
5. ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ተከታዮቹ ምን ኃላፊነት ተቀብለዋል?
5 ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ብርሃን እንደሆነ በድጋሚ በመግለጽ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው:- “ገና ጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው። ጨለማ እንዳይደርስባችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማም የሚመላለስ ወዴት እንዲሄድ አያውቅም። የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃኑ እመኑ።” (ዮሐንስ 12:35, 36) የብርሃን ልጆች የሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስን “ጤናማ ቃል ምሳሌ” ተምረዋል። (2 ጢሞቴዎስ 1:13, 14) ከዚያም ይህን ጤናማ ቃል በመጠቀም በጨለማ የሚገኙትን ልበ ቅን የሆኑ ግለሰቦች ወደ አምላክ ብርሃን እንዲመጡ ይረዷቸዋል።
6. ብርሃንና ጨለማን በተመለከተ በ1 ዮሐንስ 1:5 ላይ ምን መሠረታዊ እውነት እናገኛለን?
6 ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 1:5) እዚህ ላይ የሰፈረውን በብርሃንና በጨለማ መካከል ያለውን ልዩነት ተመልከት። ይሖዋ የመንፈሳዊ ብርሃን ምንጭ ሲሆን በእርሱ ዘንድ መንፈሳዊ ጨለማ ፈጽሞ የለም። ታዲያ የጨለማው ምንጭ ማን ነው?
የመንፈሳዊ ጨለማ ምንጭ
7. ዓለምን ከሸፈነው መንፈሳዊ ጨለማ በስተጀርባ ያለው ማን ነው? ምንስ ተጽዕኖ ያሳድራል?
7 ሐዋርያው ጳውሎስ “የዚህ ዓለም አምላክ” በማለት ተናግሯል። በዚህ አባባሉ ሰይጣን ዲያብሎስን ማመልከቱ ነው። በመቀጠልም ጳውሎስ ‘የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፣ የማያምኑትን አሳብ እንዳሳወረ’ ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ብዙ ሰዎች በአምላክ እንደሚያምኑ ቢናገሩም ከእነዚህ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እያደገ የመጣ ብዙዎች በዲያብሎስ መኖር አያምኑም። ለምን? ከሰው በላይ ኃይል ያለው አንድ ክፉ ፍጡር ሊኖር እንደሚችልና በአስተሳሰባቸው ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር መቀበል አይፈልጉም። ይሁን እንጂ ጳውሎስ እንደገለጸው ዲያብሎስ በእርግጥ ሕልውና ያለው ከመሆኑም በላይ ሰዎች የእውነትን ብርሃን ማየት እንዳይችሉ ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል። “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው” ከሚለው ትንቢታዊ መግለጫ ሰይጣን በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ የማሳደር ኃይል እንዳለው ማየት ይቻላል። (ራእይ 12:9) ሰይጣን ከሚያደርገው እንቅስቃሴ የተነሳ ነቢዩ ኢሳይያስ “እነሆ፣ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል” ሲል የተናገረው ትንቢት ይሖዋን ከሚያገለግሉ ሰዎች በስተቀር በመላው የሰው ዘር ላይ ተፈጻሚነት አለው።—ኢሳይያስ 60:2
8. በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ያሉ ሰዎች ግራ መጋባታቸው የሚታየው በምን መንገዶች ነው?
8 ድቅድቅ ባለ ጨለማ ውስጥ ምንም ነገር ማየት ስለማይቻል አንድ ሰው በቀላሉ አቅጣጫውን ይስታል ወይም ግራ ይጋባል። በተመሳሳይም በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ያሉ ሰዎች ማስተዋል አጥተው በመንፈሳዊ ሁኔታ ሊዳክሩ ይችላሉ። እውነቱን ከውሸት፣ መልካሙን ከክፉ የመለየት ችሎታቸውን ሊያጡ ይችላሉ። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ባለው ጨለማ ውስጥ ስላሉ ሰዎች ሲጽፍ “ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፣ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ፣ ጣፋጩን መራራ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!” ብሏል። (ኢሳይያስ 5:20) በመንፈሳዊ ጨለማ የሚኖሩ ሰዎች የጨለማ አምላክ በሆነው በሰይጣን ዲያብሎስ ተጽዕኖ ሥር ያሉ ሲሆን በዚህም ምክንያት ከብርሃንና ከሕይወት ምንጭ ርቀዋል።—ኤፌሶን 4:17-19
ከጨለማ ወደ ብርሃን ለመምጣት ያለው ትግል
9. ክፉ አድራጊዎች ቃል በቃልም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ ጨለማን የሚወዱ መሆናቸውን የሚያሳዩት እንዴት እንደሆነ ግለጽ።
9 ታማኙ ኢዮብ “የአመንዝራም ዓይን ድግዝግዝታን ይጠብቃል:- የማንም ዓይን አያየኝም ይላል፣ ፊቱንም ይሸፍናል” ብሎ በተናገረ ጊዜ ክፉዎች ቃል በቃል ለጨለማ ያላቸውን ፍቅር ገልጿል። (ኢዮብ 24:15) በተጨማሪም ክፉ አድራጊዎች በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን እንዲህ ዓይነቱ ጨለማ በጣም የከፋ ሊሆን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ ጨለማ አጥምዶ በያዛቸው ሰዎች ዘንድ የፆታ ብልግና፣ ስርቆት፣ ስግብግብነት፣ ስካር፣ ስድብና ቀማኛነት የተለመዱ ነገሮች መሆናቸውን ተናግሯል። ሆኖም ወደ አምላክ ቃል ብርሃን የሚመጣ ማንኛውም ሰው ለውጥ ማድረግ ይችላል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈላቸው ደብዳቤ ላይ ይህ ዓይነቱን ለውጥ ማድረግ የሚቻል እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። በቆሮንቶስ የነበሩ በርካታ ክርስቲያኖች የጨለማ ሥራዎችን ይፈጽሙ የነበረ ቢሆንም እንኳ ጳውሎስ “ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል” ሲል ነግሯቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11
10, 11. (ሀ) ኢየሱስ የማየት ችሎታውን ለመለሰለት ሰው አሳቢነት ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ብዙዎች ብርሃኑን የማይመርጡት ለምንድን ነው?
10 አንድ ሰው ከድቅድቅ ጨለማ ወጥቶ ወደ ብርሃን ሲመጣ ዓይኑ ከብርሃኑ ጋር እስኪላመድ ድረስ ጥቂት ጊዜ ሊወስድበት ይችላል። በቤተ ሳይዳ ኢየሱስ አንድን ዓይነ ስውር የፈወሰ ሲሆን ይህንንም ያደረገው በአሳቢነት ደረጃ በደረጃ ነበር። “ዕውሩንም እጁን ይዞ ከመንደር ውጭ አወጣው፣ በዓይኑም ተፍቶበት እጁንም ጭኖበት:- አንዳች ታያለህን? ብሎ ጠየቀው። አሻቅቦም:- ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አያለሁ አለ። ከዚህም በኋላ ደግሞ እጁን በዓይኑ ላይ ጫነበት አጥርቶም አየ ዳነም ከሩቅም ሳይቀር ሁሉን ተመለከተ።” (ማርቆስ 8:23-25) ኢየሱስ የሰውዬውን የማየት ችሎታ ቀስ በቀስ የመለሰለት ሰውዬው ከፀሐይ ብርሃኑ ጋር ራሱን ማላመድ እንዲችል እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህ ሰው ማየት በመቻሉ የተሰማውን ደስታ መገመት አይከብደንም።
11 ይሁን እንጂ ከመንፈሳዊ ጨለማ ደረጃ በደረጃ ወጥተው ወደ እውነት ብርሃን እንዲመጡ እርዳታ ያገኙ ሰዎች የሚሰማቸው ደስታ ይህ ሰው ከተሰማው ደስታ እጅግ የላቀ ነው። እነሱ የተሰማቸውን ደስታ ስንመለከት ብዙ ሰዎች በብርሃኑ ተማርከው የማይመጡት ለምን እንደሆነ ይገርመን ይሆናል። ኢየሱስ የዚህን ምክንያት ተናግሯል:- “ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፣ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም።” (ዮሐንስ 3:19, 20) አዎን፣ ብዙዎች እንደ ሥነ ምግባር ብልግና፣ ጭቆና፣ ውሸት፣ ማጭበርበርና ስርቆት ያሉትን ‘ክፉ ነገሮች’ ማድረግ ይወድዳሉ። በዚህም የተነሳ የሰይጣን መንፈሳዊ ጨለማ የፈለጉትን ሁሉ ለማድረግ የሚያስችላቸው አመቺ ቦታ ነው።
በብርሃኑ ውስጥ እድገት ማድረግ
12. ወደ ብርሃኑ በመምጣታችን የተጠቀምነው በምን መንገዶች ነው?
12 የብርሃንን እውቀት ካገኘንበት ጊዜ አንስቶ በራሳችን ላይ ምን ዓይነት ለውጦችን አይተናል? አንዳንድ ጊዜ ወደኋላ መለስ ብለን ያደረግነውን መንፈሳዊ እድገት ማየት ብንችል ጥሩ ይሆናል። የትኞቹን መጥፎ ልማዶች አስወግደናል? በሕይወታችን ያጋጠሙንን የትኞቹን ችግሮች ማስተካከል ችለናል? ለወደፊቱ ጊዜ አውጥተናቸው በነበሩን እቅዶች ላይ ለውጥ ያደረግነው እንዴት ነው? ይሖዋ በሚሰጠን ብርታትና በቅዱስ መንፈሱ ድጋፍ አማካኝነት ብርሃኑን እንደተቀበልን በሚያሳይ መንገድ በባሕርያችንና በአስተሳሰባችን ላይ ለውጥ ማድረጋችንን መቀጠል እንችላለን። (ኤፌሶን 4:23, 24) ጳውሎስ ጉዳዩን እንዲህ በማለት አስቀምጦታል:- “ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፣ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤ የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና . . . እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ።” (ኤፌሶን 5:8-10) የይሖዋ ብርሃን እንዲመራን መፍቀዳችን ተስፋና ዓላማ የሚያስገኝልን ከመሆኑም በላይ ከእኛ ጋር ላሉ ሰዎች ደስታ ይጨምርላቸዋል። እንዲሁም እንዲህ ዓይነቱ ለውጥ የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኛል!—ምሳሌ 27:11
13. ይሖዋ ለሰጠን ብርሃን አመስጋኝነታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? እንደዚህ ያለውን አካሄድ ለመከተልስ ምን ይጠይቃል?
13 የይሖዋን ብርሃን በማንጸባረቅ ማለትም ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘናቸውን ትምህርቶች ለቤተሰባችን አባሎች፣ ለጓደኞቻችንና ለጎረቤቶቻችን በማካፈል ላገኘነው ደስታ ለተሞላበት ሕይወት ያለንን አመስጋኝነት እናሳያለን። (ማቴዎስ 5:12-16፤ 24:14) ለማዳመጥ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች በክርስቲያናዊ አኗኗራችን የተደገፈው የስብከት ሥራችን ይኮንናቸዋል። ጳውሎስ “ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፣ . . . ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፣ ይልቁን ግለጡት እንጂ” ሲል ተናግሯል። (ኤፌሶን 5:10, 11) ሌሎች ከጨለማ ወጥተው ብርሃንን እንዲመርጡ ለመርዳት ድፍረት ይጠይቅብናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለዘላለማዊ ጥቅማቸው ስንል ለሌሎች ርኅራኄና አሳቢነት እንዲሁም የእውነትን ብርሃን ለማካፈል ልባዊ ምኞት እንድናሳይ ይጠይቅብናል።—ማቴዎስ 28:19, 20
አሳሳች ከሆነ ብርሃን ተጠበቁ!
14. ብርሃንን በተመለከተ የትኛውን ማስጠንቀቂያ መከተል አለብን?
14 በባሕር ላይ በጨለማ የሚጓዙ ሰዎች የብርሃን ጭላንጭል ሲያዩ ይደሰታሉ። በድሮ ጊዜ በእንግሊዝ አገር ከማዕበል መሸሽ የሚቻልበትን ቦታ ለመጠቆም በገደል አፋፍ ላይ እሳት ያነድዱ ነበር። መርከበኞች በዚህ ብርሃን እየተመሩ በሰላም ወደብ ላይ ይደርሳሉ። ሆኖም አንዳንዶቹ እሳቶች አሳሳች ናቸው። ብዙ መርከቦች ወደብ ላይ በመድረስ ፋንታ አቅጣጫቸውን ስተው ይሄዱና ከዐለት ጋር ይላተማሉ። እዚያም የጫኑትን ዕቃ ይዘረፉ ነበር። በዚህ አታላይ ዓለም ውስጥ እኛም መንፈሳዊ የመርከብ አደጋ እንዳይደርስብን አሳሳች በሆኑ ብርሃኖች ተታልለን እንዳንወሰድ መጠንቀቅ አለብን። “ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣል” ተብሎ ተነግሮናል። በተመሳሳይ ከሀዲዎችን ጨምሮ “ተንኰለኞች ሠራተኞች” የሆኑት አገልጋዮቹ ‘የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ይለውጣሉ።’ እነዚህ ሰዎች የሚናገሩትን የምንቀበል ከሆነ በይሖዋ የእውነት ቃል ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለን ትምክህት ሊዳከምና እምነታችን ሊጠፋ ይችላል።—2 ቆሮንቶስ 11:13-15፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:19
15. ወደ ሕይወት ከሚወስደው መንገድ እንዳንወጣ የሚረዳን ምንድን ነው?
15 መዝሙራዊው “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴ ብርሃን ነው” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 119:105) አዎን፣ አፍቃሪው አምላካችን ይሖዋ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ ስለሚወድድ’ ‘ወደ ሕይወት የሚወስደው የጠበበ ደጅ’ ፍንትው ብሎ እንዲበራ አድርጎታል። (ማቴዎስ 7:14፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል ከጠባቡ መንገድ ወጥተን ጨለማ ወደሆነው ጎዳና እንዳንሄድ ይጠብቀናል። ጳውሎስ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል” ሲል ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በመንፈሳዊ እያደግን ስንሄድ ከአምላክ ቃል ትምህርት እናገኛለን። በአምላክ ቃል ብርሃን አማካኝነት ራሳችንን መገሠጽ እንችላለን አሊያም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በጉባኤ ውስጥ ያሉ አፍቃሪ እረኞች ሊገሥጹን ይችላሉ። እንዲሁም ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ መጓዛችንን እንድንቀጥል ነገሮችን ማቅናትና በጽድቅ የሚሰጠንን ምክር በትሕትና መቀበል እንችላለን።
በአመስጋኝነት በብርሃኑ ተጓዙ
16. ይሖዋ ለሰጠን ድንቅ ብርሃን አመስጋኝነታችንን መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው?
16 ይሖዋ ለሰጠን ድንቅ ብርሃን አመስጋኝነታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ዮሐንስ ምዕራፍ 9 እንደሚነግረን ኢየሱስ ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው በፈወሰው ጊዜ ሰውዬው አመስጋኝነቱን በከፍተኛ ስሜት ገልጿል። እንዴት? ኢየሱስ የአምላክ ልጅ መሆኑን አምኖ የተቀበለ ከመሆኑም በላይ “ነቢይ” መሆኑን በይፋ ገልጿል። በተጨማሪም ኢየሱስ ያከናወነውን ተአምር ለማጣጣል የሞከሩትን ሰዎች በድፍረት ተቃውሟቸዋል። (ዮሐንስ 9:17, 30-34) ሐዋርያው ጴጥሮስ የተቀቡትን የክርስቲያን ጉባኤ አባላት “ለርስቱ የተለየ ወገን” ሲል ጠርቷቸዋል። ለምን? ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደውና በኋላም እንደተፈወሰው ሰው ዓይነት የአመስጋኝነት መንፈስ ስላላቸው ነው። ‘ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራቸውን የእርሱን በጎነት በመንገር’ ደጋፊያቸው ለሆነው ለይሖዋ ያላቸውን አመስጋኝነት ያሳያሉ። (1 ጴጥሮስ 2:9፤ ቆላስይስ 1:13) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎችም ተመሳሳይ የአመስጋኝነት መንፈስ የሚያሳዩ ሲሆን የይሖዋን “በጎነት” ለሕዝብ በማወጁ ሥራ በመካፈል ቅቡዓን ወንድሞቻቸውን ይደግፋሉ። አምላክ ፍጹማን ላልሆኑ ሰዎች የሰጠው መብት ምንኛ ታላቅ ነው!
17, 18. (ሀ) እያንዳንዱ ክርስቲያን ምን ኃላፊነት አለበት? (ለ) እያንዳንዱ ክርስቲያን የጢሞቴዎስን ምሳሌ በመከተል ምን እንዲያስወግድ ተበረታቷል?
17 ላገኘነው የእውነት ብርሃን ከልብ አመስጋኝ መሆናችን በጣም አስፈላጊ ነው። ማናችንም ብንሆን እውነትን አውቀን እንዳልተወለድን እናስታውስ። አንዳንዶች እውነትን የተማሩት በጉልምስና ዕድሜያቸው ሲሆን ብርሃኑ ከጨለማው የበለጠ ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው ወዲያውኑ መገንዘብ ችለዋል። ሌሎች ደግሞ ፈሪሃ አምላክ ባላቸው ወላጆች ሥር የማደግ ልዩ አጋጣሚ አግኝተዋል። እንደዚህ ያሉት ልጆች የብርሃኑን ዋጋማነት አቅልለው ሊመለከቱ ይችላሉ። ከመወለዷ በፊት ወላጆቿ ይሖዋን ያገለግሉ የነበሩ አንዲት ምሥክር ከሕፃንነቷ ጀምሮ የተማረችውን እውነት ትርጉምና ጠቀሜታ ለመረዳት ብዙ ጊዜና ከፍተኛ ጥረት እንደጠየቀባት በግልጽ ተናግራለች። (2 ጢሞቴዎስ 3:15) ወጣቶችም ሆን አዋቂዎች፣ ሁላችንም ይሖዋ ለገለጠው እውነት ከፍተኛ የአድናቆት ስሜት ማዳበር ይኖርብናል።
18 ወጣቱ ጢሞቴዎስ ከሕፃንነቱ ጀምሮ “ቅዱሳን መጻሕፍትን” የተማረ ቢሆንም እንኳ ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ሊደርስ የቻለው በአገልግሎቱ በትጋት በመካፈሉ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:15) ይህን በማድረጉም “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፣ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ” በማለት አጥብቆ ያሳሰበውን ሐዋርያው ጳውሎስን የመደገፍ ብቃት ሊኖረው ችሏል። እኛም እንደ ጢሞቴዎስ እንድናፍር የሚያደርገንን ወይም ይሖዋ እንዲያፍርብን የሚያደርገውን ማንኛውንም ነገር ከማድረግ እንቆጠብ!—2 ጢሞቴዎስ 2:15
19. (ሀ) እንደ ዳዊት እኛም ምን እንድንል የሚያነሳሳ ምክንያት አለን? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
19 የእውነቱን ብርሃን የሰጠንን ይሖዋን እንድናመሰግን የሚያደርጉን በርካታ ምክንያቶች አሉን። እንደ ንጉሥ ዳዊት እኛም “አቤቱ፣ አንተ መብራቴ ነህና፤ እግዚአብሔርም ጨለማዬን ያበራል” እንላለን። (2 ሳሙኤል 22:29) ይሁንና ባለን ረክተን መቀመጥ የለብንም። እንዲህ ያለው ስሜት ጥለነው ወደመጣነው ጨለማ እንድንመለስ ሊያደርገን ይችላል። በመሆኑም ቀጥሎ ያለው ርዕስ በሕይወታችን ውስጥ መለኮታዊውን እውነት ምን ያህል ከፍ አድርገን እንደምንመለከት እንድንመረምር ይረዳናል።
ምን ተምረሃል?
• ይሖዋ መንፈሳዊ ብርሃን የሚሰጠው እንዴት ነው?
• በዙሪያችን ያለው መንፈሳዊ ጨለማ ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ይደቅንብናል?
• የትኞቹን አደጋዎች ማስወገድ ይገባናል?
• ለእውነት ብርሃን ያለንን አመስጋኝነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ የግዑዙም ሆነ የመንፈሳዊ ብርሃን ምንጭ ነው
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው ቀስ በቀስ እንደፈወሰው ሁሉ እኛንም ከመንፈሳዊ ጨለማ እንድንወጣ ይረዳናል
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሰይጣን የማሳሳቻ መብራቶች መታለል መንፈሳዊ ውድቀት ያስከትላል