ይሖዋ የዓላማ አምላክ ነው
“እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፣ እንደ አሰብሁም እንዲሁ ይቆማል።”—ኢሳይያስ 14:24
1, 2. ስለ ሕይወት ዓላማ ብዙ ሰዎች ምን ይላሉ?
በየትም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች “የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?” በማለት ይጠይቃሉ። አንድ ምዕራባዊ የፖለቲካ መሪ “ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ብዙ ሰዎች ‘እኛ ምንድን ነን? ዓላማችንስ ምንድን ነው?’ እያሉ ይጠይቃሉ” በማለት ተናግረዋል። አንድ ጋዜጠኛ ወጣቶችን ስለ ሕይወት ዓላማ ጠይቆ “ልብህ የተመኘውን ማንኛውንም ነገር ማድረግ”፤ “በእያንዳንዱ አጋጣሚ በደንብ መደሰት”፤ “እንደፈለገህ ሆነህ መኖር”፤ “ልጆች ወልደህ ተደስተህ ከዚያ መሞት” የሚሉ መልሶችን አግኝቷል። ብዙዎቹ ከሕይወት የሚገኘው ይህ ብቻ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። አንዳቸውም ቢሆኑ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ዓላማ እንዳላቸው አልተናገሩም።
2 አንድ የኮንፊሽየስ እምነት ምሁር “ከፍተኛው የሕይወት ትርጉም እኛ ሰው ሆነን በምናሳልፈው ተራ ኑሮ ውስጥ ይገኛል” ብሏል። በዚህ አባባል መሠረት ሰዎች ተወልደው ለ70 ወይም ለ80 ዓመት ሲፍጨረጨሩ ይኖሩና ይሞታሉ፣ ከዚያም ሕልውናቸው ለዘላለም ያከትማል ማለት ነው። አንድ የዝግመተ ለውጥ አማኝ የሆኑ ሳይንቲስት “‘ከፍተኛ’ መልስ ለማግኘት እንመኝ ይሆናል፣ ነገር ግን ከዚህ የበለጠ መልስ የለውም” ብለዋል። ለእኚህ የዝግመተ ለውጥ አማኝ ሕይወት በሞት የሚያበቃና ለጊዜው ብቻ ለመኖር የሚደረግ ትግል ነው። እንደነዚህ ያሉት ፍልስፍናዎች ለሕይወት ተስፋ የሌለው አመለካከት እንዲኖር የሚያደርጉ ናቸው።
3, 4. የዓለም ሁኔታዎች ብዙዎች ለሕይወት ያላቸውን አመለካከት የነካባቸው እንዴት ነው?
3 ብዙ ሰዎች የሰው ኑሮ በብዙ መከራዎች የተሞላ መሆኑን ሲመለከቱ ሕይወት ዓላማ ያለው ስለ መሆኑ ይጠራጠራሉ። ሰው በኢንዱስትሪ እና በሳይንሳዊ ክንውኖች ከፍተኛ ወደሆነው ደረጃ ደርሷል በሚባልበት በእኛ ዘመን ወደ አንድ ቢልዮን የሚጠጉ ሰዎች በሕመም ወይም በምግብ እጥረት ይሠቃያሉ። በዚህ ምክንያት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት በየዓመቱ ይሞታሉ። በተጨማሪም በ20ኛው መቶ ዘመን በተደረጉት ጦርነቶች የሞቱት ሰዎች ብዛት ባለፉት አራት መቶ ዓመታት በተደረጉት ጦርነቶች የሞቱትን ሰዎች በአራት እጥፍ ይበልጣል። ወንጀል፣ ረብሻ፣ በዕፅ አላግባብ መጠቀም፣ የቤተሰብ መፈራረስ፣ ኤድስ እና ሌሎች በጾታ የሚተላለፉ በሽታዎች እንዲሁም ሌሎች ብዙ ችግሮች እየጨመሩ መጥተዋል። የዓለም መሪዎች ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ የላቸውም።
4 አንዲት ሴት እነዚህን ሁኔታዎች በመመልከት “ሕይወት ዓላማ የለውም። እነዚህ ሁሉ መጥፎ ነገሮች እየተከናወኑ ሕይወት ትርጉም ሊኖረው አይችልም” በማለት ብዙዎች ያላቸውን እምነት ገልጻለች። በዕድሜ ሸምገል ያሉ አንድ ሰውም “‘በአብዛኛው የሕይወቴ ዘመን ለምንድን ነው የምኖረው?’ ብዬ ራሴን ስጠይቅ ኖሬአለሁ። አሁን ግን ሕይወት ዓላማ ይኑረው አይኑረው አያሳስበኝም” ብለዋል። ስለዚህ ብዙ ሰዎች አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት ባለማወቃቸው አስጨናቂው የዓለም ሁኔታ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ተስፋ እንዳይኖራቸው አድርጓል።
5. የዓለም ሃይማኖቶች ሰዎች ስለ ሕይወት ዓላማ ይበልጥ ግራ እንዲጋቡ ያደረጉት እንዴት ነው?
5 የሃይማኖት መሪዎችም እንኳ ስለ ሕይወት ዓላማ የተከፋፈለና እርግጠኛ ያልሆነ እምነት አላቸው። በለንደን የሚገኘው የቅዱስ ጳውሎስ ካቴድራል የቀድሞ ዲን “በሕይወቴ ሁሉ የመኖር ዓላማ ምን እንደሆነ ለማወቅ ብዙ ሞክሬያለሁ። . . . ነገር ግን አላገኘሁም” ብለዋል። እውነት ነው፣ ብዙ ቄሶች ደጋግ ሰዎች ወደ ሰማይ፣ መጥፎዎች ደግሞ ወደ እሳታማ ሲኦል ይሄዳሉ ብለው ያስተምራሉ። ይሁን እንጂ ይህም አመለካከት ቢሆን የሰው ዘሮች በምድር ላይ ተሠቃይቶ ከመኖር የሚወጡበትን መንገድ አያመለክትም። ደግሞም ሰዎች በሰማይ እንዲኖሩ የአምላክ ዓላማ ከሆነ ከመጀመሪያው እንደ መላእክት ሰማያዊ ፍጥረታት እንዲሆኑ አድርጎ በመፍጠር ከዚህ ሁሉ ሥቃይ ለምን አይገላግላቸውም ነበር? ስለዚህ ስለ ምድራዊው ሕይወት ዓላማ ብዙ ግራ መጋባት መኖሩና ሕይወት ዓላማ አለው ብሎ አለማመን የተለመደ ነገር ሆኗል።
የዓላማ አምላክ
6, 7. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ምን ይነግረናል?
6 ይሁን እንጂ ከማንኛውም መጽሐፍ የበለጠ ስርጭት ያለው መጽሐፍ ቅዱስ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ይሖዋ የዓላማ አምላክ መሆኑን ይነግረናል። አምላክ በምድር ላይ ላለው የሰው ዘር የረጅም ጊዜ እንዲያውም ዘላለማዊ የሆነ ዓላማ እንዳለው ያሳየናል። ይሖዋ የሰጠውን ዓላማ መፈጸሙ አይቀርም። ዝናብ ዘር እንዲበቅል እንደሚያደርግ ሁሉ “ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም” ይላል። (ኢሳይያስ 55:10, 11) ይሖዋ አደርገዋለሁ ያለው ሁሉ “እንዲሁ ይቆማል።”—ኢሳይያስ 14:24
7 እኛ ሰዎች አምላክ የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም ሙሉ ትምክህት ሊኖረን ይችላል። ምክንያቱም ‘አምላክ ሊዋሽ አይችልም።’ (ቲቶ 1:2፤ ዕብራውያን 6:18) አምላክ አንድን ነገር አደርጋለሁ ካለ ይህ ቃሉ ብቻ የተናገረው ነገር እንደሚፈጸም ዋስትና ይሆነናል። እንደተፈጸመ ያህል የተረጋገጠ ነው። ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። በመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ። . . . ተናግሬአለሁ እፈጽምማለሁ፤ አስቤአለሁ አደርግማለሁ።”—ኢሳይያስ 46:9–11
8. አምላክን በቅንነት ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች እርሱን ሊያገኙት ይችላሉን?
8 ከዚህም በላይ ይሖዋ “ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ” ይፈልጋል። (2 ጴጥሮስ 3:9) በዚህ ምክንያት ማንም ሰው ስለ እርሱ የማያውቅ እንዲሆን አይፈልግም። ዓዛርያስ የተባለ ነቢይ “[አምላክን] ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል” ብሏል። (2 ዜና መዋዕል 15:1, 2) ስለዚህ አምላክንና ዓላማውን ለማወቅ በቅንነት የሚፈልጉ ሰዎች አስፈላጊውን ጥረት ካደረጉ ስለ አምላክና ስለ ዓላማው ለማወቅ ይችላሉ።
9, 10. (ሀ) አምላክን ማወቅ ለሚፈልጉት ምን ተዘጋጅቶላቸዋል? (ለ) የአምላክን ቃል ማጥናታችን ምን እንድናደርግ ያስችለናል?
9 ይህን እውቀት የሚፈልጉት ከየት ነው? አምላክን ከልብ ለሚፈልጉ ሰዎች ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን አዘጋጅቶላቸዋል። ጽንፈ ዓለምን በፈጠረበት አንቀሳቃሽ ኃይሉ ማለትም በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት የታመኑ ሰዎች ስለ ዓላማዎቹ እንድናውቅ የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ እንዲጽፉ መርቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት በተመለከተ ሐዋርያው ጴጥሮስ “ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ” ብሏል። (2 ጴጥሮስ 1:21) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ “ቅዱስ መጽሐፍ በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እርሱ እውነትን ለማስተማር፣ የተሳሳቱትን ለመገሠጽ፣ ስሕተትን ለማረምና ለትክክለኛ ኑሮ የሚበጀውን መመሪያ ለመስጠት ይጠቅማል። የሚጠቅመውም የእግዚአብሔር ሰው ፍጹም እንዲሆንና ማንኛውንም መልካም ሥራ ለመሥራት ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17 የ1980 ትርጉም፤ 1 ተሰሎንቄ 2:13
10 የአምላክ ቃል በከፊል ወይም ባልተሟላ መንገድ ሳይሆን “ማንኛውንም መልካም ሥራ ለመሥራት ብቁ” ሆነን እንድንገኝ ያስችለናል። አንድ ሰው አምላክ ማን እንደሆነ፣ ዓላማዎቹ ምን እንደሆኑና ከአገልጋዮቹ ምን እንደሚፈልግባቸው በእርግጠኝነት እንዲያውቅ ያስችለዋል። በአምላክ ደራሲነት የተዘጋጀ መጽሐፍ ይህን ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ የሚጠበቅ ነገር ነው። ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት የምንችልበት መጽሐፍ ይህ ብቻ ነው። (ምሳሌ 2:1–5፤ ዮሐንስ 17:3) ይህንን መጽሐፍ ካጠናን “እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኰል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት” አንሆንም። (ኤፌሶን 4:13, 14) መዝሙራዊው “ሕግህ [የአምላክ ቃል] ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው” በማለት ሊኖረን የሚገባውን ትክክለኛ አመለካከት ገልጿል።—መዝሙር 119:105
የአምላክ ዓላማዎች የተገለጡት ደረጃ በደረጃ ነው
11. ይሖዋ ለሰው ልጆች ዓላማውን የገለጠው እንዴት ነው?
11 ይሖዋ ለምድርና ለሰዎች ያለውን ዓላማ የገለጠው ገና ሰብአዊውን ቤተሰብ በፈጠረበት ጊዜ ነበር። (ዘፍጥረት 1:26–30) የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የአምላክን ሉዓላዊነት አንቀበልም ባሉ ጊዜ ግን የሰው ዘር በመንፈሳዊ ጨለማና በሞት ውስጥ ወደቀ። (ሮሜ 5:12) ይሁን እንጂ ይሖዋ እርሱን ሊያገለግሉ የሚፈልጉ ሰዎች እንደሚኖሩ ከመጀመሪያው አውቆ ነበር። ስለዚህ ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ ለታመኑ አገልጋዮቹ ዓላማውን ደረጃ በደረጃ ሲገልጥላቸው ቆይቷል። ዓላማውን ከገለጠላቸው ሰዎች መካከል ሄኖክ (ዘፍጥረት 5:24፤ ይሁዳ 14, 15)፣ ኖህ (ዘፍጥረት 6:9, 13)፣ አብርሃም (ዘፍጥረት 12:1–3) እና ሙሴ (ዘጸአት 31:18፤ 34:27, 28) ይገኙባቸዋል። የአምላክ ነቢይ የነበረው አሞጽ “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም” በማለት ጽፏል።—አሞጽ 3:7፤ ዳንኤል 2:27, 28
12. ኢየሱስ ስለ አምላክ ዓላማ ተጨማሪ እውቀት እንድናገኝ ያስቻለው እንዴት ነው?
12 በኤደን ዓመፅ ከተፈጸመ ከ4,000 ዓመታት በኋላ፣ የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ከዚህ በፊት ያልታወቁ የይሖዋ ዓላማዎች ተገልጠዋል። በተለይ አምላክ በምድር ላይ የሚገዛ ሰማያዊ መንግሥት ለማቋቋም ባለው ዓላማ ረገድ ብዙ ነገሮች ተገልጠዋል። (ዳንኤል 2:44) ኢየሱስ የትምህርቱ ዋነኛ መልእክት ያደረገው ይህን መንግሥት ነበር። (ማቴዎስ 4:17፤ 6:10) እርሱና ደቀ መዛሙርቱ በዚህ መንግሥት ግዛት ሥር አምላክ ለምድርና ለሰው ዘር ያወጣው የመጀመሪያ ዓላማ እንደሚፈጸም አስተምረዋል። ምድር ለዘላለም በሚኖሩ ፍጹማን ሰዎች የምትሞላ ገነት ትሆናለች። (መዝሙር 37:29፤ ማቴዎስ 5:5፤ ሉቃስ 23:43፤ 2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:4) ከዚህም በላይ ኢየሱስ እና ደቀ መዛሙርቱ በአምላክ ኃይል በፈጸሟቸው ተአምራት አማካኝነት በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚሆኑትን ነገሮች አሳይተዋል።—ማቴዎስ 10:1, 8፤ 15:30, 31፤ ዮሐንስ 11:25–44
13. አምላክ ከሰው ልጆች ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ረገድ በ33 እዘአ የጰንጠቆስጤ ዕለት ምን ለውጥ ተደረገ?
13 በ33 እዘአ ኢየሱስ ከሞተ ከ50 ቀን በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት የአምላክ መንፈስ በክርስቶስ ተከታዮች ጉባኤ ላይ ፈሰሰ። በዚህ ቀን ከዳተኛይቱ እስራኤል የአምላክ ቃል ኪዳን ሕዝብ መሆንዋ አከተመ። (ማቴዎስ 21:43፤ 27:51፤ ሥራ 2:1–4) በዚያ ወቅት መንፈስ ቅዱስ መፍሰሱ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አምላክ ዓላማዎቹን የሚገልጠው በዚህ አዲስ ድርጅት አማካኝነት መሆኑን አረጋግጧል። (ኤፌሶን 3:10) የክርስቲያን ጉባኤ ድርጅታዊ መዋቅር በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ተመሠረተ።—1 ቆሮንቶስ 12:27–31፤ ኤፌሶን 4:11, 12
14. እውነት ፈላጊዎች እውነተኛውን የክርስቲያን ጉባኤ እንዴት ለይተው ማወቅ ይችላሉ?
14 በዛሬው ጊዜ እውነትን የሚፈልጉ ሰዎች እውነተኛውን የክርስቲያን ጉባኤ ዘወትር በዚህ ጉባኤ ውስጥ በሚታየውና የአምላክ ዋነኛ ባሕርይ በሆነው በፍቅር ለይተው ሊያውቁት ይችላሉ። (1 ዮሐንስ 4:8, 16) የእውነተኛ ክርስትና መታወቂያ ልዩ ምልክት የጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ ነው። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ፤” “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35፤ 15:12) ኢየሱስ አድማጮቹን “እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ” በማለት አስገንዝቧቸዋል። (ዮሐንስ 15:14) ስለዚህ የአምላክ እውነተኛ አገልጋዮች በፍቅር ሕግ መሠረት የሚኖሩት ናቸው። ስለ ፍቅር የሚያወሩ ብቻ አይደሉም፤ ምክንያቱም “ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።”—ያዕቆብ 2:26
ተጨማሪ እውቀት
15. የአምላክ አገልጋዮች ስለ ምን ነገር እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ?
15 ኢየሱስ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ የአምላክን ዓላማ በተመለከተ እየጨመረ የሚሄድ እውቀት እንደሚያገኝ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። ለተከታዮቹ “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል። (ዮሐንስ 14:26) በተጨማሪም ኢየሱስ “እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ብሏል። (ማቴዎስ 28:20) ከዚህም የተነሣ የአምላክ አገልጋዮች ስለ አምላክና ስለ ዓላማው እውነት ያላቸው እውቀት ጨምሯል። አዎን፣ “የጻድቃን መንገድ እንደ ንጋት ብርሃን ነው፣ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል።”—ምሳሌ 4:18
16. ተጨማሪ መንፈሳዊ እውቀት ማግኘታችን በየትኛው የአምላክ ዓላማ ክፍል ላይ እንደምንገኝ ያሳውቀናል?
16 አሁን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በሚፈጸሙበት ወይም ለመፈጸም በተቃረቡበት ጊዜ ላይ ስለምንኖር ይህ መንፈሳዊ ብርሃን ከምንጊዜውም ይበልጥ ብሩኅ ሆኗል። ይህም በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት “መጨረሻ ቀኖች” ውስጥ እንደምንኖር ያመለክታል። ይህ ጊዜ ‘የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ ተብሎ የተነገረለት ዘመን ነው። ይህ ጊዜ ካከተመ በኋላ የአምላክ አዲስ ዓለም ይቋቋማል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5, 13፤ ማቴዎስ 24:3–13) በዳንኤል እንደተነገረው የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት በቅርቡ “እነዚያንም መንግሥታት [አሁን ያሉትን] ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።”—ዳንኤል 2:44
17, 18. በአሁኑ ጊዜ በመፈጸም ላይ ያሉ ምን ታላላቅ ትንቢቶች አሉ?
17 በአሁኑ ጊዜ በመፈጸም ላይ ካሉት ትንቢቶች አንዱ በማቴዎስ ምዕራፍ 24 ቁጥር 14 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ነው። እዚህ ላይ ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ብሏል። ይህ የመንግሥት ስብከት ሥራ በመላው ምድር ላይ በሚልዮን በሚቆጠሩ የይሖዋ ምስክሮች በመሠራት ላይ ይገኛል። በየዓመቱም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞች ይጨመራሉ። ይህም በኢሳይያስ 2:2, 3 ላይ “በዘመኑም ፍጻሜ” ማለትም በዚህ ክፉ ዓለም ፍጻሜ ከብዙ ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ወደ ይሖዋ እውነተኛ አምልኮ እንደሚመጡና ይሖዋም ‘መንገዱን እንደሚያስተምራቸውና በጎዳናውም እንደሚሄዱ’ ከተነገረው ትንቢት ጋር የሚስማማ ነው።
18 እነዚህ አዲስ ሰዎች በኢሳይያስ ምዕራፍ 60 ቁጥር 8 ላይ በትንቢት እንደተነገረው “እንደ ደመና” ወደ ይሖዋ አምልኮ በመጉረፍ ላይ ናቸው። ቁጥር 22 ደግሞ ይቀጥልና “ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ” ይላል። አሁን የምንኖረው በዚህ ዘመን እንደሆነ ማስረጃዎቹ ያረጋግጣሉ። አዲሶችም ከይሖዋ ምስክሮች ጋር ሲተባበሩ ከእውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ ጋር መተባበራቸው እንደሆነ እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ።
19. ከይሖዋ ምስክሮች ጋር የሚተባበሩ አዲሶች ወደ እውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ በመምጣት ላይ ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?
19 እንደዚህ ብለን በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እነዚህ አዲሶችም ሆኑ ቀደም ሲል ወደ ይሖዋ ድርጅት የመጡት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ወስነው የአምላክን ፈቃድ እያደረጉ ነው። ይህም ከአምላካዊው የፍቅር ሕግ ጋር ተስማምቶ መኖርን ይጨምራል። በፍቅር ሕግ እንደሚኖሩ ከሚያሳዩት ማስረጃዎች አንዱ እነዚህ ክርስቲያኖች ‘ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ አድርገው ስለቀጠቀጡ ጦርነትን ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።’ (ኢሳይያስ 2:4) ፍቅርን በተግባር ስለሚያሳዩ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች ሁሉ ይህንን እርምጃ ወስደዋል። ይህም የጦር መሣሪያዎችን አንሥተው እርስ በርሳቸው ወይም ከሌላ ከማንኛውም ሰው ጋር አይዋጉም ማለት ነው። በዚህም ከዓለም ሃይማኖቶች ሁሉ የተለዩ ናቸው። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ 1 ዮሐንስ 3:10–12, 15) “የፍጹም አንድነት ማሰሪያ” በሆነው በፍቅር የተገነባ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ስላላቸው ሰዎችን የሚከፋፍለው ብሔራዊ ስሜት የላቸውም።—ቆላስይስ 3:14 አዓት፤ ማቴዎስ 23:8፤ 1 ዮሐንስ 4:20, 21
ብዙ ሰዎች ላለማወቅ መርጠዋል
20, 21. አብዛኛው የሰው ዘር በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ የሚገኘው ለምንድን ነው? (2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 5:19)
20 በአምላክ አገልጋዮች መካከል ያለው መንፈሳዊ ብርሃን ይበልጥ እየደመቀ ሲሄድ ቀሪው የምድር ሕዝብ ግን ይበልጥ ድቅድቅ ወደሆነ መንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ እየገባ ነው። ይሖዋንም ሆነ ዓላማዎቹን አያውቅም። የአምላክ ነቢይ ስለዚህ ዘመን ሲናገር “እነሆ፣ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል” ብሏል። (ኢሳይያስ 60:2) ይህ የሆነው ሰዎች ስለ አምላክ ለማወቅ ልባዊ ፍላጎት ስለማያሳዩ ወይም አምላክን የማስደሰት ፍላጎት ስለሌላቸው ነው። ኢየሱስ “ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፣ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም” ብሏል።—ዮሐንስ 3:19, 20
21 እንደዚህ ያሉ ሰዎች የአምላክን ፈቃድ የማወቅ እውነተኛ ፍላጎት የላቸውም። ከዚህ ይልቅ ሕይወታቸው ያተኮረው የራሳቸውን ፈቃድ በማድረግ ላይ ነው። የአምላክን ፈቃድ ቸል በማለታቸው ራሳቸውን በአደገኛ ሁኔታ ላይ ይጥላሉ። ምክንያቱም ቃሉ “ሕግን ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ ጸሎቱ አስጸያፊ ናት” ይላል። (ምሳሌ 28:9) የመረጡት መንገድ የሚያስከትልባቸውን ውጤት ለመቀበል ይገደዳሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” በማለት ጽፏል።—ገላትያ 6:7
22. አምላክን ለማወቅ የሚፈልጉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምን በማድረግ ላይ ናቸው?
22 ይሁን እንጂ የአምላክን ፈቃድ ለማወቅ፣ የእርሱን መንገድ ለማግኘት ከልብ የሚፈልጉና ወደ እርሱ የሚጠጉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” በማለት ያዕቆብ 4:8 ይናገራል። እንደዚህ ስላሉት ሰዎች ኢየሱስ “እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል” ብሏል። (ዮሐንስ 3:21) አምላክ ወደ ብርሃኑ ለሚመጡ ሁሉ እንዴት ያለ አስደናቂ የወደፊት ጊዜ አዘጋጅቶላቸዋል! የሚቀጥለው ርዕስ ይህንን አስደሳች የወደፊት ጊዜ የሚያብራራ ይሆናል።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ስለ ሕይወት ዓላማ ብዙ ሰዎች ምን ይላሉ?
◻ ይሖዋ የዓላማ አምላክ መሆኑን የገለጠው እንዴት ነው?
◻ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ምን ዓይነት ከፍተኛ እውቀት ተገኘ?
◻ እውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ በአሁኑ ጊዜ ተለይቶ ሊታወቅ የሚችለው እንዴት ነው?