እናንተ ወላጆች፣ ምን ዓይነት ምሳሌ ናችሁ?
“እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ [“የምትመስሉ፣” NW] ሁኑ፣ በፍቅር ተመላለሱ።”—ኤፌሶን 5:1, 2
1. ይሖዋ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ምን ዓይነት መመሪያዎችን ሰጥቷቸው ነበር?
የቤተሰብ ዝግጅት መሥራች ይሖዋ ነው። የመጀመሪያውን ቤተሰብ የመሠረተውና ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስትም የመራባት አቅም የሰጣቸው እርሱ በመሆኑ እያንዳንዱ ቤተሰብ የተገኘው በእርሱ አማካኝነት ነው ሊባል ይችላል። (ኤፌሶን 3:14, 15) ለአዳምና ለሔዋን መሠረታዊ የሆኑ መመሪያዎችን በመስጠት ኃላፊነቶቻቸውን ያሳወቃቸው ከመሆኑም በላይ እነዚህኑ ኃላፊነቶች ለመፈጸም በራሳቸው ተነሳሽነት አንዳንድ ነገር ማድረግ የሚችሉበት አጋጣሚ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28-30፤ 2:6, 15-22) አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ግን ቤተሰቦችን የሚገጥሟቸው ችግሮች ይበልጥ እየተወሳሰቡ መጥተዋል። ዛሬም ቢሆን ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚገጥሟቸውን እነዚህን ችግሮች መቋቋም ይችሉ ዘንድ ፍቅራዊ መመሪያ መስጠቱን አላቆመም።
2. (ሀ) ይሖዋ በጽሑፍ የሰፈረ ምክርን በቃል በሚነገር መመሪያ ለማጠናከር ምን ዘዴ ተጠቅሟል? (ለ) ወላጆች ራሳቸውን ምን ብለው መጠየቅ ይኖርባቸዋል?
2 ይሖዋ ታላቁ አስተማሪያችን እንደመሆኑ መጠን ምን ማድረግ እንዳለብንና ምን ነገሮችን ከማድረግ መቆጠብ እንደሚገባን የሚገልጹ መመሪያዎችን በጽሑፍ ከማስፈር የበለጠ ነገርም አድርጎልናል። ጥንት በጽሑፍ የሰፈረው መመሪያ በካህናት፣ በነቢያትና በቤተሰብ ራሶች በኩል በሚሰጠው የቃል መመሪያ የተደገፈ ነበር። በጊዜያችን እንዲህ ዓይነቱን የቃል ትምህርት ለማስተላለፍ በእነማን ይጠቀማል? በክርስቲያን ሽማግሌዎችና በወላጆች ይጠቀማል። ወላጅ ከሆንክ ቤተሰብህ በይሖዋ መንገዶች እንዲጓዝ በማስተማር ረገድ የበኩልህን እያደረግህ ነው?—ምሳሌ 6:20-23
3. ውጤታማ አስተማሪ በመሆን ረገድ የቤተሰብ ራሶች ከይሖዋ ምን ሊማሩ ይችላሉ?
3 በቤተሰብ ውስጥ እንደዚህ ያለው መመሪያ እንዴት መሰጠት ይኖርበታል? ይሖዋ ምሳሌ ይሆነናል። ምን ነገር ጥሩ ምን ነገር ደግሞ መጥፎ እንደሆነ ግልጽ አድርጎ ከማስቀመጡም በላይ በደግነት ተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎችን ይሰጣል። (ዘጸአት 20:4, 5፤ ዘዳግም 4:23, 24፤ 5:8, 9፤ 6:14, 15፤ ኢያሱ 24:19, 20) ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጉ ጥያቄዎችን ይጠይቃል። (ኢዮብ 38:4, 8, 31) ምሳሌዎችንና እውነተኛ የሕይወት ታሪኮችን በመጠቀም ስሜታችን እንዲነሳሳና ልባችን እንዲቀረጽ ያደርጋል። (ዘፍጥረት 15:5፤ ዳንኤል 3:1-29) እናንተ ወላጆችስ ልጆቻችሁን በምታስተምሩበት ጊዜ ይህንን ዘዴ ለመከተል ትጣጣራላችሁ?
4. ተግሣጽ በመስጠት ረገድ ከይሖዋ ምን እንማራለን? ተግሣጽ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
4 ይሖዋ ትክክል ለሆኑ ነገሮች ያለው አቋም ጥብቅ ነው። ሆኖም አለፍጽምና የሚያሳድረውን ተጽእኖ ይገነዘባል። ስለዚህ ፍጹም ያልሆኑትን የሰው ልጆች ከመቅጣቱ በፊት ያስተምራል እንዲሁም ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎችንና ማሳሰቢያዎችን ይሰጣል። (ዘፍጥረት 19:15, 16፤ ኤርምያስ 7:23-26) የሚሰጠውም ተግሣጽ መጠኑን የማይስት ልከኛ ነው። (መዝሙር 103:10, 11፤ ኢሳይያስ 28:26-29) እኛም ልጆቻችንን በዚህ መንገድ መያዛችን ይሖዋን እንደምናውቀው ማረጋገጫ ከመሆኑም ሌላ እነርሱም በቀላሉ ይሖዋን እንዲያውቁት ይረዳቸዋል።—ኤርምያስ 22:16፤ 1 ዮሐንስ 4:8
5. ማዳመጥን በሚመለከት ወላጆች ከይሖዋ ምን ሊማሩ ይችላሉ?
5 ይሖዋ እንደ አንድ አፍቃሪ ሰማያዊ አባት የሚያዳምጠን መሆኑም የሚያስደንቅ ነው። ትእዛዝ መስጠት ብቻ ሳይሆን ልባችንን ለእርሱ እንድናፈስለት ያበረታታናል። (መዝሙር 62:8) የለመንነው ነገር የተሳሳተ እንኳ ቢሆን ከሰማይ ሆኖ በቁጣ አይገስጸንም። በትዕግሥት ያስተምረናል። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ “እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ [“የምትመስሉ፣” NW] ሁኑ” በማለት መምከሩ ምንኛ የተገባ ነው! (ኤፌሶን 4:31–5:1) ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር በሚያደርጉት ጥረት ይሖዋ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ይሆናቸዋል! ይህ ልባችንን የሚነካና በእርሱ የሕይወት መንገድ እንድንሄድ የሚያነሳሳን ምሳሌ ነው።
ምሳሌነት ያለው ኃይል
6. የወላጆች ዝንባሌና ምሳሌ በልጆቻቸው ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት ነው?
6 በቃል ከሚሰጥ መመሪያ በተጨማሪ የሌሎች ምሳሌነት በወጣቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የማሳደር ኃይል አለው። ወላጆች ወደዱም ጠሉ ልጆቻቸው እነርሱን መምሰላቸው የማይቀር ነው። እነርሱ ራሳቸው የተናገሯቸውን ነገሮች ልጆቻቸው ደግመው በሚናገሩበት ጊዜ ወላጆችን ሊያስደስት አንዳንድ ጊዜም ሊያስደነግጥ ይችላል። ወላጆች በአኗኗራቸውና በዝንባሌያቸው ለመንፈሳዊ ነገሮች የጠለቀ አድናቆት እንዳላቸው የሚያሳዩ ከሆነ በልጆቻቸው ላይ አዎንታዊ የሆነ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ ያስችላቸዋል።—ምሳሌ 20:7
7. ዮፍታሔ ለሴት ልጁ ምን ዓይነት ምሳሌ ሆኗታል? ከምንስ ውጤት ጋር?
7 የወላጆች ምሳሌነት የሚያስከትለውን ውጤት መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል። እስራኤልን እየመራ አሞናውያንን ድል እንዲያደርግ ይሖዋ የተጠቀመበት ዮፍታሔ የልጅ አባትም ነበር። በጽሑፍ ተመዝግቦ ከሚገኘውና ለአሞን ንጉሥ ከላከው መልስ ለመረዳት እንደሚቻለው ዮፍታሔ፣ ይሖዋ ለእስራኤላውያን ስላደረገላቸው ነገሮች የሚናገሩ ታሪኮችን በተደጋጋሚ አንብቦ መሆን አለበት። እነዚያን ታሪኮች ያለ ችግር መጥቀስ ችሎ ነበር፤ እንዲሁም በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳለው አሳይቷል። ሴት ልጁ በሕይወት ዘመኗ ሁሉ ለይሖዋ ያደረች ነጠላ ሴት ሆና ለመኖር እንድትወስን ያስቻላትን እምነትና የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ እንድታዳብር የእርሱ ምሳሌነት እንደረዳት ምንም ጥርጥር የለውም።—መሳፍንት 11:14-27, 34-40፤ ከኢያሱ 1:8 ጋር አወዳድር።
8. (ሀ) የሳሙኤል ወላጆች እንዴት ያለ ጥሩ ዝንባሌ አሳይተዋል? (ለ) ይህስ ሳሙኤልን የጠቀመው እንዴት ነው?
8 ሳሙኤል ገና በለጋ ዕድሜው ጥሩ ምሳሌ የነበረ ሲሆን ነቢይ ሆኖ ባገለገለበት በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለአምላክ የታመነ ሆኖ ተመላልሷል። ልጆቻችሁ ልክ እንደ ሳሙኤል እንዲሆኑላችሁ ትፈልጋላችሁ? የሳሙኤልን ወላጆች የሕልቃናን እና የሃናን ምሳሌ ተመልከት። በቤተሰባቸው ውስጥ ችግር የነበረ ቢሆንም እንኳ የመገናኛው ድንኳን ወደሚገኝበት ወደ ሴሎ አዘውትረው በመሄድ አምልኳቸውን ያከናውኑ ነበር። (1 ሳሙኤል 1:3-8, 21) ሃና ምን ያህል በስሜት ተውጣ ትጸልይ እንደነበር ልብ በል። (1 ሳሙኤል 1:9-13) ለአምላክ የገቡትን ቃል የመፈጸሙን አስፈላጊነት ሁለቱም ምን ያክል አክብደው እንደተመለከቱት ልብ በል። (1 ሳሙኤል 1:22-28) ያሳዩት መልካም ምሳሌ ሳሙኤል ትክክለኛውን አቅጣጫ ለመከተል የሚያስችሉት ባሕርያት እንዲያዳብር ሌላው ቀርቶ አምላክን እናገለግላለን የሚሉ ሆኖም ለአምላክ መንገዶች ምንም ዓይነት ደንታ ያልነበራቸው ሰዎች አብረውት በነበሩበት ጊዜ እንኳ ሳይቀር እንደረዳው ምንም ጥርጥር የለውም። ቆየት ብሎም ይሖዋ የእርሱ ነቢይ እንዲሆን በማድረግ ኃላፊነቶችን ሰጥቶታል።—1 ሳሙኤል 2:11, 12፤ 3:1-21
9. (ሀ) በጢሞቴዎስ ላይ በጎ ውጤት የነበረው የትኛው በቤት ውስጥ የነበረ ተጽእኖ ነው? (ለ) ጢሞቴዎስ ምን ዓይነት ሰው ለመሆን በቃ?
9 ወንድ ልጅህ ገና በወጣትነቱ የሐዋርያው ጳውሎስ የሥራ ባልደረባ የሆነውን ጢሞቴዎስን እንዲመስል ትፈልጋለህ? የጢሞቴዎስ አባት አማኝ አልነበረም፤ ሆኖም እናቱና ሴት አያቱ ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት በማሳየት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ሆነውለታል። ይህም ጢሞቴዎስ ክርስቲያን ሆኖ ለሚያሳልፋቸው የወደፊት ጊዜያት ጥሩ መሠረት እንደሆነለት ምንም አያጠራጥርም። የእናቱ የኤውንቄም ሆነ የሴት አያቱ የሎይድ ‘እምነት ግብዝነት የሌለበት እንደነበረ’ ተነግሮናል። ክርስቲያን ሆነው ያሳለፉት ሕይወት የታይታ አልነበረም። ካመኑበት ነገር ጋር ተስማምተው ኖረዋል። ወጣቱ ጢሞቴዎስም እንዲሁ እንዲያደርግ አስተምረውታል። ጢሞቴዎስ እምነት የሚጣልበትና ለሌሎች ደህንነት ከልቡ የሚጨነቅ ሰው መሆኑን አስመስክሯል።—2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ ፊልጵስዩስ 2:20-22
10. (ሀ) በልጆቻችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉት ከቤት ውጭ ያሉ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) እነዚህ ተጽዕኖዎች በልጆቻችን ንግግር ወይም ዝንባሌ ቢንጸባረቁ የእኛ ምላሽ እንዴት ያለ መሆን አለበት?
10 ልጆቻችን የሚነኩት ቤት ውስጥ በሚያዩት ምሳሌ ብቻ አይደለም። ትምህርት ቤት አብረዋቸው የሚማሩ ልጆች፣ የልጆችን ለጋ አእምሮ የመቅረጽ ኃላፊነት የተጣለባቸው አስተማሪዎች፣ እያንዳንዱ ሰው ከጎሳው ወይም ከአካባቢው ልማዶች ጋር ተስማምቶ መኖር አለበት የሚል ጠንካራ ስሜት ያላቸው ሰዎች፣ ያገኙት ውጤት ተጋንኖ የሚነገርላቸው የስፖርት ኮከቦችና ስለ ምግባራቸው በዜና ማሰራጫዎች የሚነገርላቸው የመንግሥት ባለ ሥልጣናትም አሉ። ከዚህም በተጨማሪ በሚልዮን የሚቆጠሩ ልጆች ጭካኔ የተሞሉ ጦርነቶች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች ይኖራሉ። እነዚህ ተጽዕኖዎች ልጆች በሚናገሯቸው ቃላት ወይም በሚያሳዩት ዝንባሌ ቢንጸባረቁ ሊያስገርመን ይገባልን? በዚህ ወቅት የምንሰጠው ምላሽ እንዴት ያለ ነው? በቁጣ መገሰጽ ወይም ኃይለ ቃል የታከለበት ወቀሳ ለችግሩ መፍትሄ ይሆናልን? እንዲያው ተቻኩለን ልጆቻችንን አንድ ነገር ከማለታችን በፊት ‘ይሖዋ እኛን ከያዘበት መንገድ ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሆን ማስተዋል ማግኘት እችል ይሆን?’ በማለት ራሳችንን መጠየቁ የተሻለ አይሆንም?—ከሮሜ 2:4 ጋር አወዳድር።
11. ወላጆች የሚሠሩት ስህተት በልጆቻቸው ዝንባሌ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?
11 እርግጥ ነው ፍጹማን ያልሆኑ ወላጆች ችግሮችን በተሻለ መንገድ በመፍታት ረገድ ሁልጊዜ ይሳካላቸዋል ማለት አይደለም። እነርሱም ስህተቶችን ይፈጽማሉ። ልጆች ይህንን ሁኔታ መመልከታቸው ለወላጆቻቸው የሚኖራቸውን አክብሮት ይቀንስባቸው ይሆን? ወላጆች ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም የሠሯቸውን ስህተቶች ለመሸፋፈን የሚሞክሩ ከሆነ ይህ ሁኔታ ሊደርስ ይችላል። ይሁን እንጂ ወላጆች ትሑት ቢሆኑና ስህተቶቻቸውን በግልጽ ቢያምኑ ውጤቱ ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ሊሆን ይችላል። በዚህ መንገድ ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ለሚጠብቁባቸው ልጆቻቸው ጠቃሚ የሆነ ምሳሌ ሊተዉ ይችላሉ።—ያዕቆብ 4:6
ምሳሌ መሆናችን ምን ሊያስተምር ይችላል?
12, 13. (ሀ) ልጆች ፍቅርን በተመለከተ ምን መማር ይኖርባቸዋል? ይህንንስ ውጤታማ በሆነ መንገድ ሊማሩ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ልጆች ስለ ፍቅር መማር የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
12 በቃል የሚሰጥ መመሪያ ከጥሩ ምሳሌነት ጋር ከተጣመረ ጠቃሚ የሆኑ በርካታ ትምህርቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተማር ይቻላል። ጥቂቶቹን እንመልከት።
13 ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማሳየት:- ምሳሌነት ሊታከልባቸው ከሚገቡ በጣም አስፈላጊ ትምህርቶች መካከል አንዱ የፍቅር ትርጉም ነው። “እርሱ [አምላክ] አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን።” (1 ዮሐንስ 4:19) እርሱ የፍቅር ምንጭና ከሁሉ የላቀ የፍቅር ተምሳሌት ነው። ይህ በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራው አጋፔ የተባለው የፍቅር ዓይነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ100 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል። እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለይቶ የሚያሳውቃቸው ይህ ባሕርይ ነው። (ዮሐንስ 13:35) ይህን ፍቅር ለአምላክና ለኢየሱስ ማሳየት ያለብን ከመሆኑም በላይ እንደኛው ላሉ ሰዎች ሌላው ቀርቶ ለማንቀርባቸው ሰዎች እንኳ ማሳየት ይኖርብናል። (ማቴዎስ 5:44, 45፤ 1 ዮሐንስ 5:3) እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር በልባችን ውስጥ መኖር ያለበት ከመሆኑም በላይ ለልጆቻችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ከማስተማራችን በፊት በአኗኗራችን ጉልህ ሆኖ መታየት ይኖርበታል። ከቃላት ይልቅ ተግባር የጎላ ድምፅ አለው። ልጆች በቤት ውስጥ ፍቅርንና ከዚያ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን የፍቅር መግለጫ ባሕርያት ማየትና ማጣጣም ይኖርባቸዋል። እነዚህ ነገሮች ከሌሉ አንድ ልጅ በአካል፣ በአእምሮና በስሜት የሚያደርገው እድገት ሊገታ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ልጆች ከቤተሰብ ውጭ ላሉ መሰል ክርስቲያኖች ተገቢ በሆነ መንገድ ፍቅርና የመውደድ ስሜት እንዴት ማሳየት እንደሚችል ማየትም ይኖርባቸዋል።—ሮሜ 12:10፤ 1 ጴጥሮስ 3:8
14. (ሀ) ልጆች እርካታ የሚያስገኝ ጥራት ያለው ሥራ እንዲሠሩ እንዴት ሊማሩ ይችላሉ? (ለ) በእናንተ የቤተሰብ ሁኔታ ይህን እንዴት ማከናወን ይቻላል?
14 እንዴት መሥራት እንደሚቻል መማር:- ሥራ የሕይወት አብይ ክፍል ነው። አንድ ሰው ለራሱ ጥሩ ግምት እንዲኖረው ከተፈለገ ጥራት ያለው ሥራ እንዴት ማከናወን እንደሚቻል መማር ይኖርበታል። (መክብብ 2:24፤ 2 ተሰሎንቄ 3:10) አንድ ልጅ በቂ መመሪያ ሳይሰጠው አንድ ተግባር እንዲያከናውን ቢደረግና ሥራውን ጥሩ አድርጎ ባለመሥራቱ ምክንያት ነቀፋ ቢሰነዘርበት ጥሩ ሥራ ማከናወንን አይማርም። ሆኖም ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር አብረው እየሠሩ ቢማሩና ተገቢው ምስጋና ቢሰጣቸው እርካታ የሚያስገኝ ሥራ ማከናወን የመማራቸው አጋጣሚ ከፍተኛ ይሆናል። ወላጆች የሚያሳዩት ምሳሌ በማብራሪያ ከታገዘ ልጆች አንድን ሥራ እንዴት አድርገው ማጠናቀቅ እንደሚችሉ ብቻ ሳይሆን ችግሮችን እንዴት መወጣት እንደሚችሉ፣ አንድ ሥራ እስኪያልቅ ድረስ እንዴት መሥራት እንደሚችሉና እንዴት አድርገው በምክንያት ማሰብና ውሳኔ ላይ መድረስ እንደሚችሉም ይማራሉ። በዚህ ሁኔታ ይሖዋ ራሱ ሠራተኛ እንደሆነ፣ ሥራውም መልካም እንደሆነና ኢየሱስም የአባቱን ፈለግ የሚከተል መሆኑን እንዲገነዘቡ እርዳታ ሊሰጣቸው ይችላል። (ዘፍጥረት 1:31፤ ምሳሌ 8:27-31፤ ዮሐንስ 5:17) አንድ ቤተሰብ እርሻ ወይም ሌላ ንግድ ካለው ጥቂት የቤተሰቡ አባላት በአንድነት ሊሠሩ ይችላሉ። ወይም ምናልባት እናትየው ምግብ ማብሰልንና ከምግብ በኋላ ዕቃዎችን በቦታ በቦታቸው ማስቀመጥን ለወንድ ወይም ለሴት ልጅዋ ልታስተምር ትችላለች። ከቤቱ ራቅ ባለ ቦታ የሚሠራ አንድ አባት እቤት ውስጥ ከልጆቹ ጋር አንድ ላይ ሆኖ የሚሠራቸውን ሥራዎች ሊያዘጋጅ ይችላል። ወላጆች በወቅቱ ያሉት ሥራዎች ተሠርተው መጠናቀቃቸውን ብቻ ሳይሆን ልጆቹ በቀሪው የሕይወት ዘመናቸው የሚጠቅማቸውን ሥልጠና ማግኘታቸውን ጭምር ማሰባቸው ምንኛ ጠቃሚ ነው!
15. ስለ እምነት በምን መንገዶች ማስተማር ይቻላል? አብራራ።
15 በመከራ ወቅት እምነት ማሳየት:- እምነትም ቢሆን አንዱ በጣም ወሳኝ የሆነ የሕይወታችን ክፍል ነው። እምነትን በማስመልከት በቤተሰብ ጥናት ላይ ውይይት በሚደረግበት ጊዜ ልጆቹ የእምነትን ፍቺ ይማሩ ይሆናል። በልባቸው ውስጥ እምነት እንዲያድግ የሚያደርጉት ነገሮች ምን እንደሆኑ ይገነዘቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ ወላጆቻቸው በከባድ መከራ ሥር ሆነው የማይናወጥ እምነት መያዛቸውን መመልከታቸው ዕድሜ ልክ የማይረሱት ነገር ይሆናል። በፓናማ የምትኖር አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ይሖዋን ማገልገሏን የማታቆም ከሆነ ከቤት እንደሚያባርራት ባሏ ይዝትባታል። እንዲህም ሆኖ አራት ትንንሽ ልጆቿን ይዛ 16 ኪሎ ሜትር የሚያክል ርቀት በእግሯ ከተጓዘች በኋላ ቀሪውን 30 ኪሎ ሜትር ደግሞ አውቶቡስ ተሳፍራ አቅራቢያዋ ወደሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ መሄዷን አላቋረጠችም። ባሳየችው በዚህ ምሳሌነት የተነኩ 20 የሚያክሉ የቤተሰቧ አባላት የእውነትን መንገድ ተቀብለዋል።
መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብ ምሳሌ መሆን
16. በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጥሩ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
16 ማንኛውም ቤተሰብ ሊያዳብራቸው ከሚችላቸው ጠቃሚ ልማዶች መካከል አንዱ ዘወትር የሚደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ልማድ ለወላጆች ጥቅም የሚያስገኝ ከመሆኑም በላይ ለልጆችም ምሳሌ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። በተቻለ መጠን በየቀኑ ጥቂት ክፍሎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንብቡ። ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የምታነቡት ብዛት አይደለም። ከሁሉም ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ንባቡ የሚዘወተር መሆኑና የሚነበብበት መንገድ ነው። ልጆች የሚያደርጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የቴፕ ክሩ በቋንቋችሁ የሚገኝ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን የያዘው መጽሐፌ በተባለው የቴፕ ክር ሊደገፍ ይችላል። የአምላክን ቃል በየዕለቱ ማንበብ የአምላክን አስተሳሰብ በግልጽ እንድንረዳ ያደርገናል። በተጨማሪም እንዲህ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በተናጠል ከማድረግ ይልቅ በቤተሰብ መልክ አንድ ላይ ማድረጉ መላው የቤተሰቡ አባል በይሖዋ መንገዶች እንዲጓዝ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። በቅርቡ ባደረግነው “የአምላክ የሕይወት መንገድ” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የቀረበው ቤተሰቦች—በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሕይወታችሁ መንገድ ይሁን! የሚለው ድራማ እንዲህ ዓይነቱን ንባብ ልማድ እንድናደርግ የሚያበረታታ ነበር።—መዝሙር 1:1-3
17. በቤተሰብ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ቁልፍ ጥቅሶችን በቃል መያዝ በኤፌሶን 6:4 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዳው እንዴት ነው?
17 በቤተሰብ መልክ አንድ ላይ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች “እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን በይሖዋ ተግሣጽና የእርሱን አስተሳሰብ በአእምሯቸው ውስጥ በመቅረጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው” በማለት በመንፈስ ተነሳስቶ ከጻፈው መልእክት ጋር የሚስማማ ነው። (ኤፌሶን 6:4 NW) ይህ ምን ማለት ነው? “አስተሳሰብን በአእምሮ ውስጥ መቅረጽ” የሚለው ሐረግ ቃል በቃል ሲተረጎም “አስተሳሰብን መክተት” ማለት ነው። ስለዚህ ልጆች የአምላክን አስተሳሰብ ማወቅ ይችሉ ዘንድ ክርስቲያን ወላጆች የይሖዋ አምላክን አስተሳሰብ በልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ መክተት እንዳለባቸው በጥብቅ ተመክረዋል። ልጆቹ ቁልፍ የሆኑ ጥቅሶችን በቃላቸው እንዲይዙ ማበረታታቱ ይህን ለማከናወን ሊረዳ ይችላል። ዋነኛው ዓላማ ልጆች ከወላጆቻቸውም ጋር ሆነ ብቻቸውን በሚሆኑበት ጊዜ በምኞታቸውና በጠባያቸው ቀስ በቀስ የይሖዋን የአቋም ደረጃዎች በማንጸባረቅ በይሖዋ አስተሳሰብ እንዲመሩ ማድረግ ነው። ለዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።—ዘዳግም 6:6, 7
18. የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በሚደረግበት ጊዜ (ሀ) በግልጽ ለመረዳት (ለ) ከያዛቸው ምክሮች ተጠቃሚ ለመሆን (ሐ) ስለ ይሖዋ ዓላማ ለሚገልጸው ነገር ጥሩ ምላሽ ለመስጠት (መ) ስለ ሰዎች ዝንባሌና ድርጊት ከሚናገረው ነገር ለመጠቀም ምን ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል?
18 እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ከተፈለገ የሚናገረውን ነገር መረዳት ይኖርብናል። ይህ ለብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ከአንድ ጊዜ በላይ ማንበብን ሊጠይቅባቸው ይችላል። የአንዳንድ መግለጫዎች ትክክለኛ ትርጉም ግልጽ ሆኖ እንዲገባን ከፈለግን የአንዳንድ ቃላትን ፍቺ ከመዝገበ ቃላት ወይም ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ከተባለው መጽሐፍ መመልከት ሊያስፈልገን ይችላል። የምናነበው ጥቅስ ምክር ወይም ትእዛዝ አዘል ከሆነ በየትኞቹ ወቅቶች ተግባራዊ ልናደርጋቸው እንደምንችል ጊዜ ወስዳችሁ ተነጋገሩባቸው። ከዚያም ‘ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን እንዴት ሊጠቅመን ይችላል?’ በማለት ልትጠይቁ ትችላላችሁ። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ጥቅሱ ስለ ይሖዋ ዓላማ አንድ ዘርፍ የሚናገር ከሆነ ‘ይህ ሕይወታችንን የሚነካው እንዴት ነው?’ ብላችሁ ጠይቁ። ምናልባት ስለ ሰዎች ዝንባሌና ድርጊት የሚገልጽ ዘገባ እያነበባችሁ ነው እንበል። በሕይወታቸው ውስጥ ምን ዓይነት ተጽዕኖዎች አጋጥመዋቸዋል? እንዴትስ ተወጧቸው? ከእነርሱ ምሳሌ እንዴት ልንጠቀም እንችላለን? ዘገባው በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛ ምን ትርጉም እንዳለው ጊዜ ወስዳችሁ ተወያዩበት።—ሮሜ 15:4፤ 1 ቆሮንቶስ 10:11
19. አምላክን በመምሰል ለልጆቻችን ምን ልንተውላቸው እንችላለን?
19 የአምላክን አስተሳሰብ በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ ለመትከል የሚያስችል እንዴት ያለ ግሩም መንገድ ነው! በዚህ መንገድ ‘እንደ ተወደዱ ልጆች አምላክን ለመምሰል’ የሚያስችል እውነተኛ እርዳታ እናገኛለን። (ኤፌሶን 5:1 NW) እንዲሁም ልጆቻችን ሊቀስሙት የሚችሉት ጥሩ ምሳሌ ልንተውላቸው እንችላለን።
ታስታውሳለህ?
◻ ይሖዋ ከተወልን ምሳሌ ወላጆች መጠቀም የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ ለልጆች የሚሰጠው የቃል መመሪያ በጥሩ የወላጃዊ ምሳሌነት መደገፍ ያለበት ለምንድን ነው?
◻ በወላጃዊ ምሳሌነት የትኞቹን ትምህርቶች በተሻለ መንገድ ማስተማር ይቻላል?
◻ ከቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ሙሉ ተጠቃሚ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ብዙዎች በቤተሰብ መልክ አንድ ላይ ሆነው መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብ ይደሰታሉ