አስተማማኝ የወደፊት ተስፋ ያላቸው ወጣቶች
በቅርቡ ተሰይሞ በነበረ አንድ ችሎት ላይ የመሀል ዳኛ የነበሩት ሰው የተፈጸመውን ወንጀል የገለጹት “እጅግ አሰቃቂና ዘግናኝ ከሆኑት [አስገድዶ የመድፈር ወንጀሎች] መካከል የሚመደብ” በማለት ነበር። ከ14 እስከ 18 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ስምንት ዱሪዬዎች አንዲትን አገር ጎብኚ ከመሀል የለንደን ከተማ አፍነው በመውሰድ በተደጋጋሚ ከደፈሯት በኋላ መዋኘት እንደማትችል እየነገረቻቸው በአቅራቢያው በሚገኝ አንድ ትልቅ ቦይ ውስጥ ከተቷት። የአንደኛው ልጅ እናት ልጅዋ ያደረገውን ነገር በቴሌቪዥን የዜና ዘገባ ላይ ስትመለከት በጣም ከመደንገጧ የተነሣ እንዳመማት ተናግራለች።
ይህ ድርጊት ዛሬ ባለው ኅብረተሰብ ውስጥ እየተከሰተ ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ ያሳያል። በወንጀል እንቅስቃሴዎች፣ በቤት ውስጥ በሚነሱ ግጭቶች ወይም ደግሞ በባልካን ግዛቶች፣ በመካከለኛውና በምዕራብ አፍሪካ እንዲሁም በሌሎችም ቦታዎች በሚካሄዱት የዘር ግጭቶች ውስጥ የሚፈጸመው የጭካኔ ድርጊት የተለመደ ነገር ሆኗል። ወጣቶች እንዲህ በመሰሉ ሁኔታዎች ውስጥ ያድጋሉ ወይም ስለነዚህ ነገሮች በተደጋጋሚ ይሰማሉ። ስለዚህ ብዙዎች ጨካኞች፣ ‘የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸው’ እና “ራሳቸውን የማይገዙ” ቢሆኑ ምንም አያስደንቅም።—2 ጢሞቴዎስ 3:3
“ክፉዎች”
ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ አብሮት ያገለግል ለነበረው ሽማግሌ ለጢሞቴዎስ ሁለተኛውን ደብዳቤ በሚጽፍበት ወቅት ሮም ታላቅ የዓለም ኃይል ነበረ። በሮማ ግዛት ውስጥ የነበሩት የመዝናኛ ሥፍራዎች አሰቃቂ የጭካኔ ተግባር የሚፈጸምባቸው ቦታዎች ሆነው ነበር። ይሁንና ጳውሎስ የወደፊቱ ጊዜ “የሚያስጨንቅ” ዘመን እንደሚሆን ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) “የሚያስጨንቅ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ቀኖቹ “ክፉዎች” እንደሚሆኑ የሚገልጽ ሐሳብም በውስጡ ያዘለ መሆኑ ትኩረትን የሚስብ ነው። ከ30 ዓመታት በፊት፣ በኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ወቅት የደረሰ አንድ ሁኔታ በእሱ ዘመን ለነበረው ክፋት ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ያሳያል።
ኢየሱስ በጀልባ ተጉዞ በገሊላ ባሕር ምሥራቃዊ ዳርቻ ገና መድረሱ ነበር። ወደ ባሕሩ ዳርቻ እየወጣ ሳለ ሁለት ሰዎች አጋጠሙት። አረመኔያዊ ገጽታቸውና ጩኸታቸው አንድ ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው ያሳያል። እነዚህ ሰዎች አጋንንት የሰፈሩባቸው “እጅግ ክፉዎች” ነበሩ።a የሚናገሩት ነገር ጠበኛ አድራጎታቸውን ከሚቆጣጠሩት ክፉ መናፍስት የመነጨ ነበር። ሰዎቹ “የእግዚአብሔር ልጅ፣ ከአንተ ጋር ምን አለን?” እያሉ ጮኹ። “ጊዜው ሳይደርስ ልትሣቅየን ወደዚህ መጣህን?” ሰዎቹ ላይ የሰፈሩት ክፉ መናፍስት አምላክ በአጋንንት ላይ የፍርድ እርምጃ ለመውሰድ ጊዜ መቁረጡን በሚገባ ያውቁ ነበር። ይህ ደግሞ ዘላለማዊ ጥፋት ያስከትልባቸዋል። እስከዚያው ድረስ ግን ከሰው አቅም በላይ በሆነው ችሎታቸው ተጠቅመው አስከፊ የሆነ የጠበኝነት ድርጊት ያነሣሣሉ። ኢየሱስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ አጋንንቱን በማስወጣት ለእነዚህ ሁለት ሰዎች እረፍት ሊሰጣቸው ችሏል።—ማቴዎስ 8:28-32፤ ይሁዳ 6
ዛሬ ወጣቶችን ጨምሮ ሰዎች ብልሹ በሆነ መንገድ ሲመላለሱ ስናይ ይህን ሁኔታ ልናስታውስ እንችላለን። ለምን? ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ የሆነው ራእይ በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ተመሳሳይ የሆነ አደጋ መኖሩን እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።” (ራእይ 12:12) ሰይጣን ውርደት ከመከናነቡም በላይ የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን በማወቁ ምክንያት “በታላቅ ቁጣ” እንደ ወረደ ልብ በሉ።
የጥቃት ዒላማ
በዚህ መጽሔት ላይ ተደጋግሞ እንደተገለጸው ክርስቶስ ኢየሱስ የሰማያዊው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በመሆን በ1914 ተሹሟል። ኢየሱስ የአምላክ ቀንደኛ ጠላት በሆነው በሰይጣን ላይ ወዲያውኑ እርምጃ ወሰደ። በመሆኑም ዲያብሎስና አጋንንቱ ከሰማይ ስለተባረሩ በአሁኑ ጊዜ ትኩረታቸውን በምድር ላይ አድርገዋል። (ራእይ 12:7-9) ሰይጣን ተጽእኖ የሚያሳድርበት ቦታ በከፍተኛ መጠን በመገደቡ ‘የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ በመዞር ላይ ይገኛል።’ (1 ጴጥሮስ 5:8) በቀላሉ በእጁ ሊወድቁለት የሚችሉት እነማን ናቸው? በተለይ በሕይወትና በሰብዓዊ ግንኙነቶች ተሞክሮ የሌላቸው አይደሉምን? ስለዚህ ዛሬ ወጣቶች የዲያብሎስ ጥቃት ዒላማ ሆነዋል። አብዛኞቹ ሙዚቃዎችና የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች በዚህ በማይታየው ሸረኛ ፍጡር ቁጥጥር ሥር በቀላሉ እንዲወድቁ ያደርጓቸዋል።—ኤፌሶን 6:11, 12
ሕይወታቸውን በተሳካ ሁኔታ ለመምራት የሚጥሩ ወጣቶች እንኳ ብዙ ደንቃራዎች ያጋጥሟቸዋል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በጦርነቱ ተካፋይ በነበሩ በብዙዎች አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቤተሰቦቻቸው የተደላደለ ኑሮ እንዲኖሩ በማድረግ በጦርነቱ ወቅት ያጡትን ነገር ለማካካስ ሞክረዋል። ንብረት ማካበት፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያና መዝናኛ ዋነኛ ግቦች ሆኑ። ይህ ደግሞ በብዙዎች ላይ ሥቃይ አስከትሏል። ጳውሎስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ለጢሞቴዎስ ሰጥቶት ነበር:- “ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ . . . በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ . . . በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።” (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) በአጠቃላይ ሲታይ በጊዜያችን ባለው ፍቅረ ነዋይ የተጠናወተው ኅብረተሰብ ውስጥ የሚገኙት ሰዎች በኢኮኖሚና በገንዘብ ችግር እንዲሁም በስሜት ሥቃይ ውስጥ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል የአምላክ ቀንደኛ ጠላት የሚሰነዝረው የዚህ ጥቃት ሰለባ የሆኑ በርካታ ወጣቶች ይገኙበታል።
ቢሆንም መልካም ዜና መኖሩ ያስደስታል። ይህ ደግሞ አስተማማኝ የወደፊት ተስፋ ያላቸውን ወጣቶች የሚመለከት ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?
ፈልጉ ታገኙማላችሁ
ብዙ ወጣቶች የተሻሉ ነገሮችን ይመኛሉ። አዋቂዎች የሚከተሉትን እያዘቀጠ ያለ የሥነ ምግባር መስፈርት አይቀበሉም። የሥልጣን ጥመኛ የሆኑ የፖለቲካና የንግድ ሰዎች የሚፈጽሙት ግፍና ጭቆና ያንገሸግሻቸዋል። ወጣት ከሆንክ ምናልባት አንተም እንዲህ ሳይሰማህ አይቀርም።
በአሥራዎቹ እድሜ ማገባደጃ ላይ የሚገኘውን ወጣቱን ሴድሪክ ተመልከቱ። የእሱ ተሞክሮ እንግዳ አይደለም።b ትንሽ ልጅ በነበረበት ጊዜ ሞትን ጨምሮ ብዙ ነገሮች ያስፈሩት ነበር። ብዙ ጊዜ የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው እያለ ራሱን ይጠይቅ ነበር። ምንም መልስ ለማግኘት ባለመቻሉ 15 ዓመት ሲሆነው የራሳቸው መላምቶች ካሏቸው ጓደኞቹ ጋር በመሆን ስለ ሕይወት ትርጉም ማሰላሰል ጀመረ። “አደንዛዥ ዕፅ እናጨስና አንድ ላይ ተቀምጠን ለሰዓታት እንወያይ ነበር” ሲል ያስታውሳል። “ሁሉም የእናንተው ዓይነት ስሜት የሚሰማው ይመስላችኋል፤ ይሁን እንጂ መልስ ያለው ሰው አልነበረም።”
እንደ ሌሎች ወጣቶች ሁሉ ሴድሪክም ደስታ የሚሰጥ ነገር ማድረግ ይፈልጋል። አደንዛዥ ዕፅ መውሰዱ ብቻ አላረካውም። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በስርቆትና በአደንዛዥ ዕፅ አመላላሽነት መካፈል ጀመረ። አሁንም በዚህ አላበቃም፤ ሌሎች ፈታኝ የሆኑ ነገሮችንም ለማድረግ ፈለገ። ሌሎች እንዲሰርቅላቸው የሚጠይቁትን ነገር መስረቅ ጀመረ። “ይህን በማድረጌ እደሰት ነበር” ብሏል። “ነገር ግን ምስኪን ከሆኑ ሰዎች ምንም ነገር አልወስድም ነበር። መኪና ከሰረቅሁ፣ ከተጠቀምኩበት በኋላ በጥሩ ሁኔታ እተወዋለሁ። አንድን የንግድ ቤት የምሰርቀው እቃዎቹ የመድን ዋስትና ያላቸው መሆናቸውን ካረጋገጥሁ በኋላ ነበር። ይህም፣ የማደርገው ነገር ተገቢ መስሎ እንዲታየኝ አድርጎ ነበር።” ልትገምቱ እንደምትችሉት ሴድሪክ በመጨረሻ ታሰረ።
ሴድሪክ እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “አብሮኝ የታሰረ ማርክ የሚባል አንድ እስረኛ ቀርቦ አነጋገረኝ። በክንዴ ላይ ትልቅ የመስቀል ንቅሳት ስለነበረኝ ለምን ይህን እንዳደረግሁ ጠየቀኝ። ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ምክንያት ያደረግሁት መስሎት ነበር።” ከሁለት ሳምንታት በኋላ ማርክ ለሴድሪክ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ አንድ ቅጂ ሰጠው።c “‘ለዘላለም መኖር ትችላለህ’ የሚሉት ጥቂት ቃላት ወዲያውኑ ነኩኝ። መቋጫውን ለማግኘት ባንችልም ሁልጊዜ እንወያይበት የነበረው ነጥብ ይህ ነበር።” ሴድሪክ ወደ እስር ቤቱ ይመጣ ከነበረ አንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር በርካታ ውይይቶችን ካደረገ በኋላ ያልመው የነበረው ነገር አምላክ ባወጣው እቅድ አማካኝነት እውን ሊሆን እንደሚችል ተገነዘበ።
ሴድሪክ “ከቀድሞ ጓደኞቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ማቋረጤ ፈጣን እድገት ለማድረግ አስችሎኛል” ብሏል። ማስተዋል ለማግኘትና ደስተኛ ለመሆን ብዙ ጥረት ጠይቆበታል። “አሁንም የበለጠ እድገት ለማድረግ በመጣጣር ላይ እገኛለሁ” በማለት ተናግሯል። “አስተሳሰቤን መጠበቅ ይኖርብኛል።” አዎን፣ ሴድሪክ ግቦቹን ለማሟላት የሚችለው ደስታን ይሰጣሉ ተብለው በሚታሰቡ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመካፈል እንደሆነ አድርጎ በማሰብ የራሱን መላምት መከተሉ በዲያብሎስ ወጥመድ ውስጥ እንደጨመረው ሊገነዘብ ችሏል።
ደስ የሚለው ነገር ሴድሪክ ከረዥም ጊዜ በፊት ከእስር ቤት የተፈታ ሲሆን ሲፈልጉት የቆዩትን ነገር ካገኙ ሰዎች ጋር ቋሚ ወዳጅነት መመሥረት ችሏል። በአሁኑ ጊዜ ሴድሪክ በምድር ላይ በገነት የመኖር ተስፋ ካላቸው የይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ሆኗል። ሰይጣናዊ ተጽእኖ ከነማታለያዎቹ የሚጠፋበትንም ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃል።
እርግጥ ነው፣ አስተማማኝ የወደፊት ተስፋ ያላቸው እንደ ሴድሪክ ያሉት ወጣቶች ብቻ አይደሉም፤ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍቅር እንዲያድርባቸው በረዷቸው ፈሪሃ አምላክ ባላቸው ወላጆች ተኮትኩተው ያደጉ ወጣቶችም አሉ።
አምላካዊ ሥልጠና ይክሳል
የጥንቱ ጠቢብ ንጉሥ ሰሎሞን “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፣ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 22:6) የመጽሐፍ ቅዱስን የአቋም ደረጃ ለማሟላት ቆርጠው የተነሱ በርካታ ወጣቶች የዚህን አባባል እውነትነት አረጋግጠዋል።
ሺላ፣ ጎርደንና ሳራ እንዲህ አድርገዋል። ወላጆቻቸው የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ ‘ሂዱና ደቀ መዛሙርት አድርጉ’ የሚለውን የክርስቶስ ትእዛዝ የማክበርን አስፈላጊነት ከፍ አድርገው ይመለከቱ እንደነበር ያስታውሳሉ። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ሺላ እንዲህ ብላለች:- “እናቴና እኔ ማንኛውንም ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ‘ይህ ጉዳይ የስብከቱን ሥራ እንዴት ይነካል?’ ብለን እርስ በርሳችን እንጠያየቃለን። በዚህ ምክንያት በርካታ ውጥኖችን የተውን ቢሆንም ብዙ በረከቶችን አግኝተናል!” ሺላና እናቷ ለሰዎች በየቤታቸው እየሄዱ ምሥራቹን በመናገር ረዥም ሰዓታት ባሳለፉባቸው ቀናት እንኳ ወደ ቤታቸው የሚመለሱት እየዘመሩ ነበር። “የነበረኝን ደስታ ልነግራችሁ አልችልም። አሁንም እንኳ ያ ደስታ ይሰማኛል” ብላለች።
ጎርደን ቅዳሜ ቅዳሜ ያሳልፋቸው የነበሩትን በርካታ አስደሳች ምሽቶች ያስታውሳል። “የጉባኤው ሽማግሌዎች ወደ ቤታቸው ይጋብዙኝ የነበረ ሲሆን በዚያም ጠቃሚ የሆኑ ጥያቄዎችን እያነሳን እንጠያየቅ እንዲሁም ጥሩ ውይይት እናደርግ ነበር” በማለት ተናግሯል። ጎርደን ወደኋላ መለስ ብሎ በማስታወስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃላችን እንድንይዝ፣ በቅዱስ ጽሑፋዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ግልጽ ውይይት እንድናደርግና በመስክ ላይ ያገኘነውን ተሞክሮ እንድንናገር ማበረታቻ ይሰጠን የነበረ ሲሆን የመንግሥቱ ሥራ እንዴት እየተስፋፋ እንዳለም እንወያይ ነበር። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ጥሩ መሠረት እንዲኖረኝና ለይሖዋ አምላክ ፍቅር እንድኮተኩት ረድተውኛል።”
ሳራ ሊጠይቋቸው ይመጡ ከነበሩ ምሥክሮች ጋር ያሳለፈቻቸውን አስደሳች ምሽቶች ታስታውሳለች። “አንድ ላይ እንመገብ ነበር። ከዚያም በፒያኖ እያጀብናቸው ወንድሞች ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገሩ መዝሙሮችን ከዘመሩ በኋላ እንለያይ ነበር። በተለይ ተማሪዎች በነበርንባቸው ጊዜያት ሙዚቃ የቤተሰባችን አባላት ሁሉ አንድ ላይ ሆነን አንዳንድ ነገሮችን ለመሥራት እንድንችል ረድቶን ስለነበር በጣም ጠቅሞናል።”
እርግጥ ነው፣ ይሖዋን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሁሉም ወጣቶች ለዚህ ዓላማ ምቹ የሆነ ቤተሰብ አላቸው ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ በጉባኤው ከሚገኙ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑ ቤተሰቦች ጋር መቀራረባቸው ደህንነትና ተቀባይነት እንዳገኙ ሆኖ እንዲሰማቸው ያደርጋል።
ለወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ የሆነ መሠረት ጣል
በጊዜያችን የሚገኙ ወጣቶች ምርጫ አላቸው። ኢየሱስ ትንቢት በተናገረለት በመጪው “ታላቅ መከራ” ከሚጠፋው ከዚህ ክፉ ዓለም ጋር አብረው ሊቀጥሉ ይችላሉ። ወይም መዝሙራዊው አሳፍ በመንፈስ ተገፋፍቶ እንደዘመረው ‘ተስፋቸውን በእግዚአብሔር ሊያደርጉ . . . ትእዛዙንም ሊጠብቁ’ ይችላሉ። ለአምላክ ታዛዥ መሆናቸው ‘ጠማማና የሚያስመርር ትውልድ እንዲሁም ልቡን ያላቀናና ነፍሱ በእግዚአብሔር ዘንድ ያልታመነ ትውልድ’ ከመሆን ይጠብቃቸዋል።—ማቴዎስ 24:21፤ መዝሙር 78:6-8
በዓለም ዙሪያ ከ80,000 በሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ልታደንቋቸው የምትችሉ በርካታ ወጣቶችን ታገኛላችሁ። “ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፣ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፣ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው” ሲል ጳውሎስ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ የሰጠውን ምክር በተግባር ላይ አውለዋል። በዚህም ምክንያት አሁን ‘እውነተኛውን ሕይወት አጥብቀው ለመያዝ ችለዋል።’ (1 ጢሞቴዎስ 6:18, 19) በስብሰባዎቻቸው ላይ በመገኘት ስለነዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ይበልጥ ለማወቅ ጣር። ያኔ አንተም እንደነሱ አስተማማኝ የሆነ የወደፊት ተስፋ ሊኖርህ ይችላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “ክፉዎች” የሚለው ቃል በማቴዎስ 8:28 እና በ2 ጢሞቴዎስ 3:1 ላይ የሚገኘውን ግሪክኛ ቃል ለመተርጎም ተሠርቶበታል።
b ስሞቹ ተቀይረዋል።
c ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የፈወሳቸው “እጅግ ክፉዎች” የነበሩት ሰዎች ክፉ መናፍስት የሰፈሩባቸው ነበሩ
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ለሚመጣው ዘመን መልካም መሠረት” መገንባት