አጵሎስ አንደበተ ርቱዕ የሆነ የክርስትና እውነት ሰባኪ
ሁሉም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች የክርስቲያን ጉባኤ አባሎች ከሆኑ ጥቂት ዓመት የሆናቸውም ሆኑ በርካታ፣ በምሥራቹ ስብከት ረገድ እድገት ለማድረግ ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል። ይህም ስለ አምላክ ቃል ያለንን እውቀትና ለሌሎች የማስተማር ችሎታችንን እንድናሳድግ ይጠይቅብናል። ይህን ለማድረግ አንዳንዶች ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም፣ ችግሮችን ማሸነፍ ወይም ራሳቸውን ለተጨማሪ ሥራ ማዘጋጀት ይኖርባቸው ይሆናል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ከፍተኛ መንፈሳዊ እድገት ያሳዩና ከዚህም ጥረታቸው ብዙ ጥቅም ያገኙ በርካታ የጥንት ወንዶችና ሴቶች ተጠቅሰዋል። ከእነዚህ አንዱ አጵሎስ ነው። ቅዱስ ጽሑፉ ይህን ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያስተዋውቀን ስለ ክርስትና ትምህርቶች ያልተሟላ እውቀት የነበረው ግለሰብ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤ ተጓዥ ወኪል ሆኖ ያገለግል ነበር። እንዲህ ያለ ፈጣን እድገት እንዲያደርግ ያስቻለው ነገር ምን ነበር? ሁላችንም ልንኮርጃቸው የሚገቡ ግሩም ባሕርያት ነበሩት።
“ቅዱሳት መጻሕፍትን ጠንቅቆ የተማረ”
በ52 እዘአ ገደማ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ እንደሚተርክልን “የእስክንድርያ ተወላጅ የሆነ አጵሎስ የተባለ አንድ አይሁዳዊ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ እርሱ ቅዱሳት መጻሕፍትን ጠንቅቆ የተማረና ጥሩ የአነጋገር ችሎታ ያለው ሰው ነበረ። ስለ ጌታ መንገድ የተማረና በመንፈስም የተቃጠለ ሆኖ ስለ ኢየሱስ በትክክል ይሰብክና ያስተምር ነበር። ይሁን እንጂ እርሱ የሚያውቀው የዮሐንስን ጥምቀት ብቻ ነበር። እርሱ በድፍረት በምኩራብ መናገር ጀመረ።”—ሥራ 18:24-26 የ1980 ትርጉም
የግብጽዋ እስክንድርያ ከሮም ቀጥላ በዓለም ሁለተኛዋ ሰፊ ከተማ ስትሆን በዘመኑ ለአይሁዳውያንም ሆነ ለግሪካውያን በጣም ትልቅ ደረጃ ካላቸው የባሕል ማዕከሎች አንዷ ነበረች። አጵሎስ ስለ ዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የነበረውን ጥልቅ እውቀትና ጥሩ የንግግር ችሎታ ያገኘው በዚህች ከተማ ከሚኖረው በርካታ የአይሁድ ማኅበረሰብ ካገኘው ትምህርት ሳይሆን አይቀርም። አጵሎስ ስለ ኢየሱስ ያወቀው የት እንደሆነ በእርግጠኝነት ለመናገር ያስቸግራል። ኤፍ ኤፍ ብሩስ የተባሉ ምሁር እንደሚሉት “ከአገር ወደ አገር የሚዘዋወርና ምናልባትም ተዘዋዋሪ ነጋዴ ስለነበረ ከተጓዘባቸው ቦታዎች በአንዱ ክርስቲያን ሰባኪዎችን ሊያገኝ ይችል ነበር።” ያም ሆነ ይህ ስለ ኢየሱስ ይናገርና በትክክል ያስተምር የነበረ ቢሆንም “የዮሐንስን ጥምቀት ብቻ” ያውቅ ስለነበር በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን በፊት የተመሠከረለት ይመስላል።
ዮሐንስ መጥምቁ የኢየሱስ መንገድ ጠራጊ እንደመሆኑ መጠን ለመላው የእስራኤል ብሔር ጠንካራ ምስክርነት የሰጠ ሲሆን ብዙዎችም ንስሐ ለመግባታቸው ምልክት እንዲሆን በእጁ ተጠምቀዋል። (ማርቆስ 1:5፤ ሉቃስ 3:15, 16) በርካታ ታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚሉት በሮማ ግዛት ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያን ስለ ኢየሱስ የነበራቸው እውቀት በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻዎች ከተሰበከላቸው አላለፈም ነበር። ደብልዩ ጄ ኮኒቢር እና ጄ ኤስ ሃውሰን እንዳሉት “ክርስትናቸው ጌታችን አገልግሎት በጀመረበት ወቅት ከነበረው እልፍ አላለም። የክርስቶስ ሞት ስላለው ሙሉ ትርጉም ደንቆሮዎች ነበሩ። እንዲያው ከሙታን ስለመነሳቱ እንኳን ያወቁ አይመስልም።” አጵሎስም መንፈስ ቅዱስ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን ስለመፍሰሱ ያወቀ አይመስልም። ይሁን እንጂ ስለ ኢየሱስ መጠነኛ የሆነ ትክክለኛ እውቀት አግኝቶ ስለነበረ ይህንን ያገኘውን እውቀት ለራሱ ብቻ ይዞ ለመኖር አልፈለገም። እንዲያውም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለሚያውቀው ነገር በድፍረት ይናገር ነበር። ይሁን እንጂ ቅንዓቱና ግለቱ ገና በትክክለኛ እውቀት ላይ አልተመሠረተም ነበር።
ቀናተኛ ግን ትሁት
የሉቃስ ትረካ በመቀጠል “ጵርስቅላና አቂላም በሰሙት ጊዜ፣ ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል ገለጡለት” ይላል። (ሥራ 18:26) አቂላና ጵርስቅላ የአጵሎስ እምነት ከእነርሱ እምነት ጋር የሚመሳሰልባቸው ብዙ መንገዶች እንዳሉ ቢገነዘቡም ያልተሟላ እውቀቱን በሕዝብ ፊት ለማረም አልሞከሩም። አጵሎስን ለመርዳት ብዙ ጊዜ በግል አነጋግረውት እንደነበረ ልንገምት እንችላለን። ታዲያ ይህ “ቅዱሳት መጻሕፍትን ጠንቅቆ የተማረው” አጵሎስ የተሰጠውን እርዳታ እንዴት ተቀበለው? (ሥራ 18:24 የ1980 ትርጉም) አጵሎስ አቂላንና ጵርስቅላን ከማግኘቱ በፊት የነበረውን ያልተሟላ መልእክት ለሕዝብ ሲሰብክ ቆይቶ እንደነበረ መገመት አያዳግትም። ኩሩ ሰው ቢሆን ኖሮ ምንም ዓይነት እርማት ለመቀበል እምቢተኛ ይሆን ነበር። እርሱ ግን እውቀቱን የተሟላ እንዲያደርግ የቀረበለትን እርዳታ በትህትናና በአመስጋኝነት ተቀበለ።
በተጨማሪም አጵሎስ ትሁት ሰው መሆኑ የኤፌሶን ወንድሞች የቆሮንቶስ ጉባኤ እንዲቀበለው የጻፉትን ደብዳቤ ለመቀበል ፈቃደኛ በመሆኑ ታይቷል። ታሪኩ “እርሱም ወደ አካይያ ማለፍ በፈቀደ ጊዜ፣ ወንድሞቹ አጸናኑት፣ ይቀበሉትም ዘንድ ወደ ደቀ መዛሙርት ጻፉለት” ይላል። (ሥራ 18:27፤ 19:1) አጵሎስ በትህትና የክርስቲያን ጉባኤን ዝግጅት ተቀበለ እንጂ በእርሱነቱ ብቻ እንዲቀበሉት አልጠየቀም።
በቆሮንቶስ
አጵሎስ በአገልግሎቱ ያገኘው የመጀመሪያ ውጤት በጣም ግሩም ነበር። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ “በደረሰም ጊዜ አምነው የነበሩትን በጸጋ እጅግ ይጠቅማቸው ነበር፤ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ከመጻሕፍት እየገለጠ ለአይሁድ በሁሉ ፊት በጽኑ ያስረዳቸው ነበርና” ይላል።—ሥራ 18:27, 28
አጵሎስ በዝግጅቱና በቅንዓቱ ወንድሞችን እያበረታታ ራሱን ለጉባኤ አገልግሎት ሰጥቶ ነበር። የተሳካ ውጤት ያገኘበት ቁልፍ ምን ነበር? አጵሎስ የተፈጥሮ ችሎታ ያለው ከመሆኑም በላይ ከአይሁዳውያን ጋር በድፍረት ለመከራከር ችሏል። ከዚህ በላይ ግን ከቅዱሳን ጽሑፎች ምክንያቱን ያስረዳ ነበር።
ምንም እንኳ አጵሎስ በቆሮንቶስ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ውጤት ያስገኘ አገልግሎት ቢፈጽምም ስብከቱ ያልተጠበቀ አሉታዊ ውጤት አስከትሏል። እንዴት? ጳውሎስም ሆነ አጵሎስ የመንግሥቱን እውነት ዘር በቆሮንቶስ በመዝራት ረገድ ብዙ መልካም ሥራ ሠርተዋል። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ከተማ በ50 እዘአ ገደማ፣ ማለትም አጵሎስ ከመምጣቱ ከሁለት ዓመት በፊት ሰብኳል። የመጀመሪያ መልእክቱን ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈበት በ55 እዘአ ገደማ ላይ በመካከላቸው መከፋፈል ተፈጥሮ ነበር። አንዳንዶች አጵሎስን መሪያቸው አድርገው ሲመለከቱ ሌሎች ጳውሎስን ወይም ጴጥሮስን፣ ሌሎች ደግሞ ክርስቶስን መሪያቸው አድርገው ይመለከቱ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 1:10-12) አንዳንዶች ‘እኔ የአጵሎስ ነኝ’ ይሉ ነበር። ለምን?
ጳውሎስም ሆነ አጵሎስ ይሰብኩት የነበረው መልእክት አንድ ነበር። ይሁን እንጂ ሁለቱም የተለያዩ ባሕርያት ነበሯቸው። ጳውሎስ ራሱ “በአነጋገሬ ያልተማርሁ” ነኝ ብሏል። አጵሎስ ግን “አንደበተ ርቱዕ” ነበር። (2 ቆሮንቶስ 10:10፤ 11:6) በቆሮንቶስ ይኖሩ በነበሩ አንዳንድ የአይሁድ ማኅበረሰብ አባሎች ዘንድ ተደማጭነት ለማግኘት ያበቃው ችሎታ ነበረው። አይሁዳውያን የተሳሳቱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ችሏል። ጳውሎስ ግን ከዚህ እምብዛም ባልራቀ ጊዜ ከምኩራብ ልብሱን አራግፎ ወጥቷል።—ሥራ 18:1, 4-6
አንዳንዶች ወደ አጵሎስ ዘንበል እንዲሉ ያደረጋቸው ምክንያት ይህ ይሆን? ግሪካውያን ፍልስፍና ነክ ውይይት የማድረግ ፍቅር ስለነበራቸው አንዳንዶች ይበልጥ አእምሮ ቀስቃሽ የሆነውን የአጵሎስ አቀራረብ እንዲወዱ ሳያደርጋቸው እንዳልቀረ በርካታ ተንታኞች ይናገራሉ። ጁዜፔ ሪቾቲ “[የአጵሎስ] በውብ ቃላት ያሸበረቀውና በምሳሌዎች የበለጸገ አነጋገሩ ብዙዎች የተራቀቀ ተናጋሪ ካልነበረው ከጳውሎስ ይልቅ እሱን እንዲያደንቁ አድርጓቸዋል” የሚል ሐሳብ አቅርበዋል። አንዳንዶች እውነት እንዲህ ባለው የግል ምርጫ ምክንያት በወንድሞች መካከል መከፋፈል እንዲኖር ፈቅደው ከነበረ ጳውሎስ “የጥበበኞችን ጥበብ” ከፍ አድርጎ መመልከት የተሳሳተ መሆኑን አምርሮ የገለጸበትን ምክንያት ለመረዳት አያዳግትም።—1 ቆሮንቶስ 1:17-25
ይሁን እንጂ እንዲህ ሲል መተቸቱ በጳውሎስና በአጵሎስ መካከል መቃቃር መኖሩን አያመለክትም። አንዳንዶች በራሳቸው ግምታዊ አስተሳሰብ በመነሳት እነዚህ ሁለት ሰባኪዎች የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ፍቅር ለማትረፍ እርስ በርሳቸው አምርረው የሚፎካከሩ ጠበኞች ነበሩ ቢሉም ቅዱሳን ጽሑፎች ይህን የሚያመለክት ነገር አይናገሩም። አጵሎስ ራሱን የአንድ ኑፋቄ መሪ ከማድረግ ይልቅ ወደ ኤፌሶን ተመለሰ። ጳውሎስ የመጀመሪያ መልእክቱን ለተከፋፈለው የቆሮንቶስ ጉባኤ በጻፈ ጊዜም አጵሎስ ከጳውሎስ ጋር ነበር።
በመካከላቸው ምንም ዓይነት ፉክክርም ሆነ መከፋፈል አልነበረም። ሁለቱም እርስ በርሳቸው በመተማመን በቆሮንቶስ የተነሣውን ችግር ለማስወገድ ተባብረው ይሠሩ ነበር። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ስለነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ጥርጣሬ ሊኖረው ቢችልም ስለ አጵሎስ ግን ምንም ዓይነት ጥርጣሬ አልነበረውም። የሁለቱ ሰዎች ሥራ ሙሉ በሙሉ የተስማማ ከመሆኑም በላይ ትምህርታቸውም ቢሆን እርስ በርሱ የሚደጋገፍ ነበር። የራሱን የጳውሎስን ቃል ብንጠቅስ “እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ” “ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና” ብሏል።—1 ቆሮንቶስ 3:6, 9, 21-23
የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ልክ እንደ ጳውሎስ ለአጵሎስ ከፍተኛ ግምት ስለነበራቸው እንዲጎበኛቸው አጥብቀው ይፈልጉ ነበር። ጳውሎስ አጵሎስን ወደ ቆሮንቶስ እንዲመለስ በጠየቀው ጊዜ ግን ይህ እስክንድርያዊ ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ጳውሎስ “ስለ ወንድማችን ስለ አጵሎስ ግን ከወንድሞቹ ጋር ወደ እናንተ ሊሄድ እጅግ አድርጌ ለምኜው ነበር፤ ዛሬም ለመምጣት ከቶ ፈቃድ አልነበረውም፣ ሲመቸው ግን ይመጣል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 16:12) አጵሎስ ወደ ቆሮንቶስ ለመመለስ ያመነታው ተጨማሪ መከፋፈል እንዳይፈጠር ሰግቶ ወይም በሌላ አካባቢ የሚሠራው ሥራ ስለኖረው ብቻ ሊሆን ይችላል።
ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ አጵሎስ ለመጨረሻ ጊዜ የሚገልጹልን ወደ ቀርጤስና ምናልባትም ከዚያም አልፎ በመጓዝ ላይ እንዳለ ነው። ጳውሎስ አሁንም በድጋሚ ለወዳጁና ለሥራ ባልደረባው ከፍተኛ ግምት እንዳለው ገልጾ ቲቶ ለአጵሎስና ለጉዞ ጓደኛው ለዜማስ ለጉዟቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንዲሰጣቸው ጠይቋል። (ቲቶ 3:13) በዚህ ጊዜ አጵሎስ አሥር ዓመት ለሚያህል ጊዜ ክርስቲያናዊ ሥልጠና አግኝቶ ስለነበረ የጉባኤው ተጓዥ ወኪል ለመሆን የሚያስችለውን እድገት አግኝቷል።
መንፈሳዊ እድገት የሚያፋጥኑ አምላካዊ ባሕርያት
እስክንድርያዊው ሰባኪ በዘመናችን ለሚኖሩ የምሥራቹ ሰባኪዎች በሙሉ፣ በጠቅላላው መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ ጥሩ ምሳሌ ትቷል። እኛ የእርሱን ያህል አንደበተ ርቱዕ ላንሆን እንችላለን። ይሁን እንጂ በቅዱሳን ጽሑፎች በመጠቀም ረገድ የነበረውን እውቀትና ችሎታ ልንቀዳና ቅን ልብ ያላቸውን እውነት ፈላጊዎች ልንረዳ እንችላለን። አጵሎስ ቅንዓት በተሞላበት እንቅስቃሴው “አምነው የነበሩትን በጸጋ እጅግ” ሊጠቅማቸው ችሏል። (ሥራ 18:27) አጵሎስ ትሁት፣ ራሱን መሥዋዕት የሚያደርግና ሌሎችን ለማገልገል ፈቃደኛ የመሆን መንፈስ የነበረው ሰው ነበር። ሁላችንም “ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ ነንና” በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለፉክክር ወይም የበላይነት ለመፈለግ ምንም ዓይነት ቦታ እንደሌለው ተረድቶ ነበር።—1 ቆሮንቶስ 3:4-9፤ ሉቃስ 17:10
እኛም እንደ አጵሎስ መንፈሳዊ እድገት ለማግኘት እንችላለን። ቅዱስ አገልግሎታችንን ለማሻሻል ወይም ለማስፋት፣ ራሳችንን ይሖዋና ድርጅቱ ይበልጥ እንዲጠቀሙብን በሚያስችል ሁኔታ ላይ ለማስገኘት ፈቃደኞች ነንን? ከሆንን የክርስትና እውነት ቀናተኛ ተማሪዎችና ሰባኪዎች እንሆናለን።