የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 56—ቲቶ
ጸሐፊው:- ጳውሎስ
የተጻፈበት ቦታ:- መቄዶንያ (?)
ተጽፎ ያለቀው:- ከ61–64 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
“የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነው ጳውሎስ . . . የጋራችን በሆነው እውነተኛ እምነት ልጄ ለሆነው ለቲቶ።” (ቲቶ 1:1, 4) ጳውሎስ፣ የሥራ ባልደረባውና የረጅም ጊዜ ወዳጁ ለሆነው ለቲቶ የላከው ደብዳቤ የሚጀምረው በዚህ መንገድ ነው። ጳውሎስ፣ ጉባኤዎችን በተሻለ መንገድ እንዲያደራጅ ቲቶን በቀርጤስ ደሴት ትቶት ነበር። ቲቶ የተጣለበት ኃላፊነት ከባድ ነበር። ይህች ደሴት “የአማልክትና የሰዎች አባት” ጥንታዊ መኖሪያ እንደሆነች ይነገርላት የነበረ ሲሆን “ቀርጤሳዊውን ቀርጤስ ማድረግ” ማለትም “አታላይን ማታለል” የሚለው አባባል የመነጨውም ከዚህች ደሴት ነው።a በደሴቲቱ የሚኖሩት ሰዎች ውሸት በመናገር የታወቁ በመሆናቸው ጳውሎስ እንኳ የራሳቸው ነቢይ የተናገረውን በመጥቀስ እንደሚከተለው ብሎ ነበር:- “የቀርጤስ ሰዎች ዘወትር ውሸታሞች፣ ክፉ አውሬዎችና ሰነፍ ሆዳሞች ናቸው።” (1:12) በጳውሎስ ዘመን ይኖሩ የነበሩት ቀርጤሳውያን እንደሚከተለው ተብለውም ተገልጸዋል:- “ወረተኞች፣ ቅንነት የጎደላቸውና ጠበኞች እንዲሁም ከመጠን በላይ ስግብግቦች፣ ልቅ ሥነ ምግባር ያላቸው፣ ሐሰተኞችና ሰካራሞች ነበሩ፤ በመካከላቸው የሚኖሩት አይሁዳውያን ደግሞ በሥነ ምግባር ብልግና ከአገሬው ሰው የባሱ ነበሩ።”b በቀርጤስ የሚገኙ ጉባኤዎች የተቋቋሙት ይህን በመሰለው አካባቢ ነበር፤ በዚህም የተነሳ በዚያ የሚኖሩት አማኞች የጳውሎስን ማሳሰቢያ በመከተል ‘በኀጢአት መኖርንና ዓለማዊ ምኞትን ክደው፣ ራሳቸውን በመግዛትና በጽድቅ እንዲሁም በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት’ ለመኖር የተለየ ጥረት ማድረጋቸው አስፈላጊ ነበር።—2:12
2 የቲቶ መጽሐፍ በጳውሎስና በቲቶ መካከል ስላለው ቅርርብ የሚሰጠው መግለጫ በጣም አነስተኛ ነው። ሆኖም ጳውሎስ በሌሎቹ ደብዳቤዎቹ ላይ ስለ ቲቶ ከተናገራቸው ሐሳቦች ብዙ መረጃ ማግኘት ይቻላል። ግሪካዊ የነበረው ቲቶ ከጳውሎስ ጋር ብዙ ጊዜ ይጓዝ የነበረ ሲሆን ቢያንስ አንድ ጊዜ አብሮት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዷል። (ገላ. 2:1-5) በመሆኑም ጳውሎስ “አብሮኝ የሚሠራ ባልደረባዬ” በማለት ገልጾታል። ጳውሎስ፣ በኤፌሶን ሆኖ ለቆሮንቶስ ሰዎች የመጀመሪያውን ደብዳቤ ከጻፈ በኋላ ወደ ቆሮንቶስ የላከው በቲቶ በኩል ነበር። ቲቶ በቆሮንቶስ እያለ በኢየሩሳሌም ለሚገኙ ወንድሞች ይደረግ ከነበረው መዋጮ ጋር ተያይዞ የተገለጸ ሲሆን በኋላም መዋጮ የማሰባሰቡን ሥራ እንዲያጠናቅቅ ጳውሎስ እንደገና ወደ ቆሮንቶስ ልኮታል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የጻፈውን ሁለተኛ ደብዳቤ እንዲያደርስ ለቲቶ የሰጠው በመቄዶንያ ከተገናኙ በኋላ ቲቶ ወደ ቆሮንቶስ በድጋሚ በተጓዘበት ወቅት ነበር።—2 ቆሮ. 8:16-24፤ 2:13፤ 7:5-7
3 ጳውሎስ በሮም መጀመሪያ ታስሮ ከተፈታ በኋላ በአገልግሎቱ የመጨረሻ ዓመታት ላይ ከጢሞቴዎስና ከቲቶ ጋር እንደገና ተገናኝቶ ነበር። ይህም በቀርጤስ፣ በግሪክና በመቄዶንያ ያገለገሉበትን ጊዜ የሚያካትት ይመስላል። በመጨረሻም ጳውሎስ ከግሪክ በስተ ሰሜን ምዕራብ ወደምትገኘው ወደ ኒቆጵልዮን እንደሄደ ተገልጿል፤ ጳውሎስ የተያዘውና ለመጨረሻ ጊዜ ታስሮ ወደተገደለበት ወደ ሮም የተወሰደው ከዚህ ቦታ ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ ‘ያልተስተካከለውን ነገር እንዲያስተካክል’ እንዲሁም እሱ በሰጠው መመሪያ መሠረት ‘በየከተማው ሽማግሌዎችን እንዲሾም’ ቲቶን በቀርጤስ የተወው በዚህ የጉብኝቱ ወቅት ነበር። ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው ቲቶን በቀርጤስ ትቶት ከሄደ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በመቄዶንያ እያለ ሳይሆን አይቀርም። (ቲቶ 1:5፤ 3:12፤ 1 ጢሞ. 1:3፤ 2 ጢሞ. 4:13, 20) ደብዳቤው ከአንደኛ ጢሞቴዎስ ጋር ተመሳሳይ ዓላማ ያለው ይመስላል፤ ይኸውም የጳውሎስን የሥራ ባልደረባ ለማበረታታትና ለሚሠራቸው ሥራዎች ሥልጣን ለመስጠት ነበር።
4 ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው በሮም ለመጀመሪያ ጊዜ ከታሰረ በኋላና ለሁለተኛ ጊዜ ከመታሰሩ በፊት ባለው ወቅት ወይም ከ61 እስከ 64 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ባለው ጊዜ ውስጥ መሆን አለበት። በዚሁ ጊዜ አካባቢ ለጢሞቴዎስ የተላኩትን ደብዳቤዎች ትክክለኝነት ለማረጋገጥ የቀረበው ጠንካራ ማስረጃ ለቲቶ ለተላከው ደብዳቤም ይሠራል፤ እነዚህ ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አብዛኛውን ጊዜ የጳውሎስ “አባታዊ ደብዳቤዎች” በመባል ይታወቃሉ። የእነዚህ መጻሕፍት የአጻጻፍ ስልት ተመሳሳይ ነው። ኢራኒየስና ኦሪጀን ከቲቶ ጠቅሰው የጻፉ ሲሆን ሌሎች የታወቁ ብዙ ጥንታውያን ምንጮችም መጽሐፉ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል መሆኑን ይመሰክራሉ። በሳይናይቲክ እና በአሌክሳንድራይን ጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ ይገኛል። በጆን ራይላንድስ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ P32 የተባለ አንድ የፓፒረስ ቁራጭ ያለ ሲሆን ይህ ቁራጭ በሦስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ የተጻፈና ቲቶ 1:11-15ን እንዲሁም 2:3-8ን የያዘ በኮዴክስ መልክ ተዘጋጅቶ የነበረ ነጠላ ወረቀት ነው።c የቲቶ መጽሐፍ ትክክለኛ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ስለመሆኑ ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለውም።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
8 የቀርጤስ ክርስቲያኖች የሚኖሩት ውሸት፣ ምግባረ ብልሹነትና ስስት በተስፋፋበት አካባቢ ነበር። ታዲያ እነዚህ ክርስቲያኖች ሕዝቡን መስለው መኖር ይኖርባቸዋል? ወይስ ለይሖዋ አምላክ የተቀደሰ ሕዝብ ሆነው ለማገልገል እንዲችሉ ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ለመለየት ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋቸው ይሆን? ጳውሎስ፣ ቀርጤሳውያን “መልካሙን ነገር ለማድረግ ራሳቸውን አሳልፈው ይሰጡ ዘንድ” እንዲያሳስባቸው ለቲቶ ከነገረው በኋላ “ይህ መልካምና ለማንኛውም ሰው የሚጠቅም ነው” ብሏል። ዛሬም በውሸትና በማጭበርበር ድርጊቶች በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ እውነተኛ ክርስቲያኖች በአምላክ አገልግሎት ፍሬያማ በመሆን “ለመልካም ሥራ መትጋትን [መማራቸው]” ‘መልካምና ጠቃሚ’ ነው። (3:8, 14) ጳውሎስ በቀርጤስ ለነበሩት ጉባኤዎች አደገኛ የሆነውንና በከተማዋ ውስጥ የሚታየውን የሥነ ምግባር ብልግና እንዲሁም ክፋትን በማውገዝ የጻፈው ሐሳብ ‘የእግዚአብሔር ጸጋ በኀጢአት መኖርንና ዓለማዊ ምኞትን ክደን፣ በአሁኑ ዘመን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ፣ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት እንድንኖር እያስተማረን’ ባለበት በዚህ ጊዜ ለምንገኘው ለእኛም ማስጠንቀቂያ ይሆነናል። በተጨማሪም ክርስቲያኖች ለመንግሥታት በመታዘዝና ጥሩ ሕሊና እንዲኖራቸው ለማድረግ በመጣር “መልካም የሆነውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ” መሆን ይገባቸዋል።—2:11, 12፤ 3:1
9 መንፈስ ቅዱስ ከበላይ ተመልካቾች የሚጠብቃቸውን ብቃቶች በተመለከተ በቲቶ 1:5-9 ላይ ያለው ሐሳብ በ1 ጢሞቴዎስ 3:2-7 ላይ የተዘረዘሩትን ሐሳቦች የሚያጠናክር ነው። በቲቶ ላይ የሚገኘው ሐሳብ የበላይ ተመልካቹ “በታመነ ቃል የሚጸና” እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ አስተማሪ በመሆኑ ላይ ትኩረት ያደርጋል። ይህ ሁሉም ወደ ጉልምስና እንዲደርሱ በመርዳት ረገድ ምንኛ አስፈላጊ ነው! እንዲያውም ትክክለኛ ትምህርት የመስጠትን አስፈላጊነት ለቲቶ በተላከው ደብዳቤ ውስጥ በተደጋጋሚ ጎላ ተደርጎ ተጠቅሷል። ጳውሎስ ቲቶን “ከትክክለኛው ትምህርት ጋር ተስማሚ የሆነውን አስተምር” በማለት መክሮታል። በዕድሜ የገፉ ሴቶች “በጎ የሆነውን የሚያስተምሩ” ሊሆኑ ይገባል፤ እንዲሁም ባሪያዎች ‘በሁሉም መንገድ የአዳኛችን የእግዚአብሔር ትምህርት እንዲወደድ’ የሚያደርጉ መሆን አለባቸው። (ቲቶ 1:9፤ 2:1, 3, 10) ቲቶ የበላይ ተመልካች እንደመሆኑ መጠን በማስተማር ረገድ ጥብቅና ደፋር መሆን እንደሚያስፈልገው ጳውሎስ ጎላ አድርጎ ሲገልጽ “ልታስተምር የሚገባህ እነዚህን ነው፤ በሙሉ ሥልጣን ምከር፤ ገሥጽም” ብሎታል። እንዲሁም የማይታዘዙትን በተመለከተ “አጥብቀህ ገሥጻቸው፤ ይኸውም ትክክለኛ እምነት እንዲኖራቸው [ነው]” የሚል ምክር ሰጥቶታል። ከዚህ መመልከት እንደምንችለው ጳውሎስ ለቲቶ የጻፈው ደብዳቤ በተለይ “ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር [ይጠቅማል]።”—ቲቶ 2:15፤ 1:13፤ 2 ጢሞ. 3:16
10 ለቲቶ የተጻፈው ደብዳቤ “የተባረከ ተስፋችን የሆነውን የታላቁን የአምላካችንንና የአዳኛችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ በመጠባበቅ” ላይ ባለንበት በአሁኑ ጊዜ አምላክ ላሳየን ጸጋ ያለን አድናቆት እንዲጨምር የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ኃጢአተኛ ከሆነው ዓለም እንድንርቅ ያበረታታናል። በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ጻድቅ ተደርገው የተቆጠሩት ሰዎች እንዲህ በማድረግ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ‘የዘላለምን ሕይወት ተስፋ ይዘው ወራሾች ይሆናሉ።’—ቲቶ 2:13፤ 3:7
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የማክሊንቶክና ስትሮንግ ሳይክሎፒዲያ፣ በ1981 በድጋሚ የታተመ፣ ጥራዝ 2 ገጽ 564፤ ዘ ኒው ሻፍ-ሄርዞግ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጂየስ ኖውሌጅ፣ 1958 ጥራዝ 3 ገጽ 306
b የማክሊንቶክና ስትሮንግ ሳይክሎፒዲያ፣ በ1981 በድጋሚ የታተመ፣ ጥራዝ 10 ገጽ 442
c ዘ ቴክስት ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት፣ በኩርትና ባርባራ ኦላንድ ተዘጋጅቶ በኢ ኤፍ ሮድስ በ1987 የተተረጎመ ገጽ 98