‘የአምላክ ቃል ይሠራል’
1 ሐዋርያው ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም” ነው ሲል ጽፏል። (ዕብ. 4:12) እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የአምላክ ቃል ወይም መልእክት በሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደር ይችላል። ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኘው ጥበብ በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ በጎ ለውጥ የማስከተል ኃይል አለው። የሚሰጠው መጽናኛና ተስፋ ሰዎች ሕይወት ሰጪ ወደሆነው ወደ ይሖዋ አምላክ እንዲቀርቡ ይረዳቸዋል። በውስጡ ያዘለው መልእክት ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ ዘላለም ሕይወት በሚመራው መንገድ ላይ መጓዝ እንዲጀምሩ ያነሳሳቸዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለውን ውጤት ለማግኘት ለሌሎች በምንመሠክርበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም ይገባናል።
2 በእያንዳንዱ አጋጣሚ አንድ ጥቅስ አንብብ:- አንዳንድ አስፋፊዎች ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም ትተዋል ማለት ይቻላል። እናንተስ እንዴት ናችሁ? ብዙ ሰዎች ረዘም ያለ ውይይት ለማካሄድ ጊዜ ያላቸው ስለማይመስል ጽሑፍ አበርክታችሁ ወይም በቃላችሁ ብቻ አንድ ጥቅስ ጠቅሳችሁ መሄዱን ልማድ አድርጋችሁት ይሆናል። ግለሰቡ የምንናገረው መልእክት በእርግጥ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኝ መሆኑን እንዲገነዘብ ለመርዳት ምሥራቹን በምትሰብኩበት ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቢያንስ አንድ ጥቅስ አውጥታችሁ ለማንበብ ከልብ ጥረት እንድታደርጉ ሁላችሁንም እናበረታታችኋለን።
3 ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የማንበብ ልምድ ባይኖራቸውም እንኳ አክብሮቱ አላቸው። ሌላው ቀርቶ ሥራ የሚበዛባቸው ሰዎች እንኳ ብዙውን ጊዜ ከአምላክ ቃል ላይ አንድ መልእክት በቀጥታ ሲነበብ ለመስማት አንድ ወይም ሁለት ደቂቃ አያጡም። ተስማሚ የሆነ አንድ ጥቅስ በግለት ሲነበብና በአጭሩ ሲብራራ የይሖዋ ቃል ያለው ኃይል በአድማጩ ላይ በጎ ውጤት ይኖረዋል። ሆኖም የመግቢያ ሐሳብ ከተናገራችሁ በኋላ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ወደምታነቡት ጥቅስ መሸጋገር የምትችሉት እንዴት ነው?
4 መጽሔት ስታበረክቱ ልትሞክሩት ትችላላችሁ:- አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በመጽሔት ዘመቻ ሲካፈል ጥቅሶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ይጠቀማል። አነስተኛ መጽሐፍ ቅዱስ በኪሱ ይይዛል። መጽሔቶቹን አውጥቶ አንድ ርዕስ በአጭሩ ካስተዋወቀ በኋላ ያለምንም ማመንታት መጽሐፍ ቅዱስ ገልጦ ከርዕሱ ጋር የሚያያዝ አንድ ጥቅስ ያነብባል። በአጭሩ “አጽናኝ ስለሆነው ስለዚህ ተስፋ ምን ይሰማሃል?” ብሎ በመጠየቅ የተመረጠውን ጥቅስ ማንበብ ይቻላል።
5 እያንዳንዱን ሰው ስታነጋግር ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ወይም ሁለት ጥቅስ የማንበብ ግብ ይኑርህ። መጽሐፍ ቅዱስ ያለው ለተግባር የሚያንቀሳቅስ ኃይል ብዙ ሰዎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ መንገድ ሊከፍትላቸው ይችላል።—ዮሐ. 6:44