የጥናት ርዕስ 3
ኢየሱስ እንባውን ማፍሰሱ ምን ያስተምረናል?
“ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።”—ዮሐ. 11:35
መዝሙር 17 “እፈልጋለሁ”
ማስተዋወቂያa
1-3. የይሖዋ አገልጋዮች እንባቸውን እንዲያፈስሱ የሚያደርጓቸው የትኞቹ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ናቸው?
መጨረሻ ያለቀስክበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ የደስታ እንባ እናነባለን። ብዙውን ጊዜ ግን የምናለቅሰው ከልባችን ሐዘን የተነሳ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ እናለቅሳለን። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ሎሬሊ የተባለች እህት እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “አንዳንዴ ልጄን በማጣቴ ምክንያት የሚሰማኝ ሐዘን በጣም ስለሚበረታብኝ ምንም ነገር ሊያጽናናኝ እንደማይችል የሚሰማኝ ጊዜ ነበር። ልቤ በሐዘን ከመሰበሩና ከመደቆሱ የተነሳ ጨርሶ የሚያገግም አይመስለኝም ነበር።”b
2 እንድናለቅስ የሚያደርጉን ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። ሂሮሚ የተባለች በጃፓን የምትኖር አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “አገልግሎት ላይ የማገኛቸው ሰዎች ግድየለሽነት ተስፋ የሚያስቆርጠኝ ጊዜ አለ። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ እውነትን ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር እንዲያገናኘኝ እያለቀስኩ እለምነዋለሁ።”
3 አንተስ እንደ እነዚህ እህቶች ተሰምቶህ ያውቃል? ብዙዎቻችን እንዲህ የተሰማን ጊዜ አለ። (1 ጴጥ. 5:9) ፍላጎታችን “ይሖዋን በደስታ” ማገልገል ነው፤ ሆኖም በደረሰብን ሐዘን፣ በተስፋ መቁረጥ ወይም ታማኝነታችንን በሚፈትን አንድ አስጨናቂ ሁኔታ የተነሳ እያለቀስን ይሖዋን የምናገለግልበት ጊዜ አለ። (መዝ. 6:6፤ 100:2) ታዲያ በሐዘን በምንዋጥበት ጊዜ ሁኔታውን ለመቋቋም ምን ማድረግ እንችላለን?
4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
4 ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ኢየሱስ ስሜቱ በጣም ከመረበሹ የተነሳ ‘እንባውን ያፈሰሰባቸው’ ወቅቶች ነበሩ። (ዮሐ. 11:35፤ ሉቃስ 19:41፤ 22:44፤ ዕብ. 5:7) እስቲ እነዚህን ወቅቶች መለስ ብለን እንመልከት። ከእነዚህ ታሪኮች ምን ትምህርት እንደምናገኝም እናያለን። በተጨማሪም እንባችንን እንድናፈስ የሚያደርጉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚረዱ ጠቃሚ ሐሳቦችን እንመለከታለን።
ለወዳጆቹ እንባውን አፍስሷል
5. በዮሐንስ 11:32-36 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው ታሪክ ስለ ኢየሱስ ምን እንማራለን?
5 በ32 ዓ.ም. የክረምት ወቅት፣ የኢየሱስ ወዳጅ የነበረው አልዓዛር ታመመ እና ሞተ። (ዮሐ. 11:3, 14) አልዓዛር ማርያምና ማርታ የተባሉ ሁለት እህቶች ነበሩት፤ ኢየሱስም ይህን ቤተሰብ በጣም ይወደው ነበር። ማርያምና ማርታ የሚወዱት ወንድማቸው ሲሞት በሐዘን ልባቸው ተሰበረ። አልዓዛር ከሞተ በኋላ ኢየሱስ ማርያምና ማርታ ወደሚኖሩባት ወደ ቢታንያ መንደር ሄደ። ማርታ ኢየሱስ እየመጣ መሆኑን ስትሰማ ወዲያውኑ ልትቀበለው ወጣች። ከዚያም “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው፤ ማርታ ይህን ስትል ምን ያህል በሐዘን ተውጣ እንደሚሆን አስበው። (ዮሐ. 11:21) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ማርያምና ሌሎቹ ሲያለቅሱ ሲመለከት እሱም “እንባውን አፈሰሰ።”—ዮሐንስ 11:32-36ን አንብብ።
6. ኢየሱስ በዚህ ወቅት ያለቀሰው ለምንድን ነው?
6 ኢየሱስ በዚያ ወቅት ያለቀሰው ለምንድን ነው? ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ለዚህ ጥያቄ እንዲህ ሲል መልስ ይሰጣል፦ “የወዳጁ የአልዓዛር ሞትና ይህ በአልዓዛር እህቶች ላይ ያስከተለው ሐዘን ኢየሱስ ‘እጅግ እንዲያዝን እና እንባውን እንዲያፈስስ’ አድርጎታል።”c ኢየሱስ ወዳጁ አልዓዛር በታመመበት ወቅት ምን ያህል ተሠቃይቶ እንደሚሆን እንዲሁም ሕይወቱ ሊያልፍ መሆኑን ሲገነዘብ ምን ተሰምቶት እንደሚሆን አስቦ ሊሆን ይችላል። ማርያምና ማርታ በወንድማቸው ሐዘን ምን ያህል እንደተደቆሱ ማየቱም እንባውን እንዲያፈስስ አድርጎት መሆን አለበት። አንተም የቅርብ ወዳጅህን ወይም የቤተሰብህን አባል በሞት አጥተህ ከሆነ እንዲህ ተሰምቶህ እንደሚሆን ጥያቄ የለውም። ከዚህ ታሪክ የምናገኛቸውን ሦስት ትምህርቶች እስቲ እንመልከት።
7. ኢየሱስ ለወዳጆቹ እንባውን ማፍሰሱ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?
7 ይሖዋ ስሜትህን ይረዳልሃል። ኢየሱስ የአባቱ “ትክክለኛ አምሳያ” ነው። (ዕብ. 1:3) ኢየሱስ እንባውን ሲያፈስስ የአባቱን ስሜት አንጸባርቋል። (ዮሐ. 14:9) የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ከሆነ ይሖዋ ማዘንህን እንደሚያስተውል እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ከዚህም ባለፈ ግን ስሜትህን ይጋራል፤ የተሰበረውን ልብህን ሊጠግንልህ ይፈልጋል።—መዝ. 34:18፤ 147:3
8. ኢየሱስ በሞት ያጣናቸውን ሰዎች እንደሚያስነሳቸው እርግጠኛ የሚያደርገን ምንድን ነው?
8 ኢየሱስ በሞት ያጣኸውን ሰው ማስነሳት ይፈልጋል። ኢየሱስ እንባውን ከማፍሰሱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለማርታ “ወንድምሽ ይነሳል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷት ነበር። ማርታም ኢየሱስ የተናገረውን አምናለች። (ዮሐ. 11:23-27) ማርታ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆኗ መጠን ኤልያስ እና ኤልሳዕ የተባሉት ነቢያት ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ስለፈጸሟቸው ትንሣኤዎች እንደምታውቅ ጥያቄ የለውም። (1 ነገ. 17:17-24፤ 2 ነገ. 4:32-37) ኢየሱስ ስላከናወናቸው ትንሣኤዎችም ሳታውቅ አትቀርም። (ሉቃስ 7:11-15፤ 8:41, 42, 49-56) አንተም በሞት ያጣሃቸውን የምትወዳቸውን ሰዎች እንደገና እንደምታገኛቸው እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ኢየሱስ በሐዘን ልባቸው የተሰበረ ወዳጆቹን ሲያጽናና እንባውን ማፍሰሱ ትንሣኤ በጉጉት የሚጠብቀው ነገር እንደሆነ ያረጋግጥልናል!
9. ሐዘን የደረሰባቸውን እንደ ኢየሱስ መደገፍ የምትችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
9 ሐዘን የደረሰባቸውን መደገፍ ትችላለህ። ኢየሱስ ከማርታና ከማርያም ጋር አልቅሷል፤ ከዚህም በተጨማሪ አዳምጧቸዋል እንዲሁም በሚያጽናና መንገድ አነጋግሯቸዋል። እኛም ሐዘን ለደረሰባቸው ይህን ማድረግ እንችላለን። በአውስትራሊያ የሚኖር ዳን የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴን በሞት ካጣሁ በኋላ የሌሎች ድጋፍ አስፈልጎኝ ነበር። ብዙ ባለትዳሮች ቀንም ሆነ ማታ ጊዜያቸውን ሰጥተው ያዳምጡኝ ነበር። ሐዘኔን እንድገልጽ አጋጣሚ ሰጥተውኛል፤ ማልቀሴም አላሳፈራቸውም። ከዚህ በተጨማሪ ተግባራዊ እርዳታ ለማድረግ ራሳቸውን ያቀርቡ ነበር። ለምሳሌ እኔ እንደማልችል በሚሰማኝ ጊዜ መኪናዬን ያጥቡልኝ፣ አስቤዛ ይገዙልኝ እንዲሁም ምግብ ያበስሉልኝ ነበር። ደግሞም ብዙ ጊዜ አብረውኝ ይጸልዩ ነበር። እውነተኛ ወዳጆች እንዲሁም ‘ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም’ ሆነውልኛል።”—ምሳሌ 17:17
ለባልንጀሮቹ እንባውን አፍስሷል
10. በሉቃስ 19:36-40 ላይ የተገለጸውን ዘገባ ተርክ።
10 ጊዜው ኒሳን 9, 33 ዓ.ም. ሲሆን ኢየሱስ ኢየሩሳሌም የደረሰው በዚህ ዕለት ነበር። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲቃረብ ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ፤ ሕዝቡ ኢየሱስን እንደ ንጉሣቸው እንደተቀበሉት ለማሳየት መደረቢያቸውን በመንገዱ ላይ ማነጠፍ ጀመሩ። በእርግጥም ይህ የደስታ ወቅት ነበር። (ሉቃስ 19:36-40ን አንብብ።) በመሆኑም ከዚያ በኋላ የሆነው ነገር ደቀ መዛሙርቱን አስገርሟቸው መሆን አለበት። ኢየሱስ “ወደ ኢየሩሳሌም በተቃረበ [ጊዜ] ከተማዋን አይቶ አለቀሰላት።” ኢየሱስ እንባውን እያፈሰሰ፣ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ስለሚጠብቃቸው መከራ ትንቢት ተናገረ።—ሉቃስ 19:41-44
11. ኢየሱስ ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ያለቀሰላቸው ለምን ነበር?
11 ኢየሱስ ሕዝቡ ሞቅ ያለ አቀባበል ቢያደርግለትም አብዛኞቹ የአገሩ ሰዎች መልእክቱን ለመቀበል ፈቃደኞች እንዳልሆኑ ያውቅ ነበር፤ ልቡ ያዘነው ለዚህ ነው። በዚህ አካሄዳቸው የተነሳ ኢየሩሳሌም ጥፋት እንደሚደርስባት፣ ከጥፋቱ የተረፉት አይሁዳውያንም ቢሆኑ በግዞት እንደሚወሰዱ ያውቅ ነበር። (ሉቃስ 21:20-24) የሚያሳዝነው ልክ ኢየሱስ እንደጠበቀው ሕዝቡ በአብዛኛው አልተቀበሉትም። አንተ በምትኖርበት አካባቢ ሰዎች በአብዛኛው ለመንግሥቱ መልእክት ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣሉ? እውነትን ለማስተማር ለምታደርገው ጥረት በጎ ምላሽ የሚሰጡት ጥቂቶች ናቸው? ከሆነ ኢየሱስ እንባውን እንዳፈሰሰ ከሚገልጸው ታሪክ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ? አሁንም የምናገኛቸውን ሦስት ትምህርቶች እንመልከት።
12. ኢየሱስ ለባልንጀሮቹ እንባውን ማፍሰሱ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?
12 ይሖዋ ለሰዎች ያስባል። የኢየሱስ እንባ ይሖዋ ለሰዎች ምን ያህል እንደሚያስብ ያስታውሰናል። ይሖዋ “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ [አይፈልግም]።” (2 ጴጥ. 3:9) በዛሬው ጊዜም ለሰዎች ምሥራቹን ለመንገርና ልባቸውን ለመንካት በምናደርገው ጥረት እስከ መጨረሻው በመቀጠል ባልንጀሮቻችንን እንደምንወድ እናሳያለን።—ማቴ. 22:39d
13-14. ኢየሱስ ለሰዎች ርኅራኄ ያሳየው እንዴት ነው? እኛስ ይህን ባሕርይ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ አገልግሎቱን በትጋት አከናውኗል። ሰዎችን ይወድ ስለነበር ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያስተምራቸው ነበር። (ሉቃስ 19:47, 48) ይህን ለማድረግ ያነሳሳው ምንድን ነው? ኢየሱስ ለሰዎች ርኅራኄ ነበረው። አንዳንድ ጊዜ ኢየሱስን ለመስማት በጣም ብዙ ሰዎች ይመጡ ስለነበር እሱና ደቀ መዛሙርቱ “እህል እንኳ መቅመስ አልቻሉም” ነበር። (ማር. 3:20) በአንድ ወቅት፣ ከሚያስተምራቸው ሰዎች አንዱ የሚመቸው ምሽት ላይ ስለነበር በዚያ ሰዓት ሊያስተምረው ፈቃደኛ ሆኗል። (ዮሐ. 3:1, 2) ኢየሱስ ሲያስተምር ከሰሙት ሰዎች አብዛኞቹ ደቀ መዛሙርቱ አልሆኑም። ያም ቢሆን ኢየሱስ ለሰሙት ሰዎች ሁሉ የተሟላ ምሥክርነት ሰጥቷል። እኛም በዛሬው ጊዜ ሁሉም ሰው ምሥራቹን ለመስማት አጋጣሚ እንዲያገኝ ማድረግ እንፈልጋለን። (ሥራ 10:42) ለዚህም ሲባል አገልግሎታችንን የምናከናውንበትን መንገድ ማስተካከል ሊያስፈልገን ይችላል።
14 እንደ ሁኔታው ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኛ ሁኑ። ለምሥራቹ በጎ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎችን ማግኘት የምንችለው አገልግሎታችንን በተለያየ ሰዓት ለማከናወን ፈቃደኞች ከሆንን ነው። ማቲልዳ የተባለች አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ በተለያየ ሰዓት ለመስበክ እንጥራለን። ማለዳ ላይ በንግድ አካባቢዎች እንሰብካለን። እኩለ ቀን አካባቢ ብዙ ሰዎች ውጭ ስለሚሆኑ የጽሑፍ ጋሪ እንጠቀማለን። አመሻሽ ላይ ደግሞ ብዙ ሰዎች ቤታቸው ስለሚሆኑ ከቤት ወደ ቤት መስበኩን ውጤታማ ሆኖ አግኝተነዋል።” ሁልጊዜ እኛ በሚመቸን ሰዓት ላይ ከማገልገል ይልቅ ሰዎች ሊገኙ በሚችሉበት ሰዓት ላይ ለመስበክ ፕሮግራማችንን ማስተካከል አለብን። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ይደሰትብናል።
የአባቱ ስም ስላሳሰበው እንባውን አፍስሷል
15. ሉቃስ 22:39-44 እንደሚያሳየው ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ምን አድርጓል?
15 ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. ምሽት ላይ ኢየሱስ ወደ ጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሄደ። በዚያም የልቡን አውጥቶ ወደ ይሖዋ ጸለየ። (ሉቃስ 22:39-44ን አንብብ።) ኢየሱስ “በከፍተኛ ጩኸትና እንባ ብዙ ምልጃ” ያቀረበው በዚህ ከባድ ወቅት ነው። (ዕብ. 5:7) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ የጸለየው ስለ የትኛው ጉዳይ ነው? ይሖዋ በታማኝነት ለመጽናት እና የእሱን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስችለው ጥንካሬ እንዲሰጠው ጸልዮአል። ይሖዋም የልጁን የጭንቅ ጸሎት ሰምቶ እሱን ለማበረታታት መልአኩን ልኮለታል።
16. ኢየሱስ በጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ በሚጸልይበት ወቅት የተጨነቀው ለምን ነበር?
16 ኢየሱስ በጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሲጸልይ ያለቀሰው፣ የአምላክን ስም ተሳድቧል በሚል ክስ መወንጀሉ አስጨንቆት እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። ኢየሱስ ከባድ ኃላፊነት ጫንቃው ላይ እንደወደቀም ያውቅ ነበር፤ ይህም የአባቱን ስም ከነቀፋ ነፃ ማድረግ ነው። አንተም ለይሖዋ ያለህን ታማኝነት የሚፈትን አስጨናቂ ሁኔታ ገጥሞህ ከሆነ ከኢየሱስ እንባ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ? አሁንም የምናገኛቸውን ሦስት ትምህርቶች እንመልከት።
17. ይሖዋ ኢየሱስ ያቀረበውን ልባዊ ጸሎት መስማቱ ስለ እሱ ምን ያስተምረናል?
17 ይሖዋ የምታቀርበውን ምልጃ ይሰማል። ይሖዋ ኢየሱስ ያቀረበውን ከልብ የመነጨ ልመና ሰምቷል። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስን በዋነኝነት ያሳሰበው ለአባቱ እስከ መጨረሻው ታማኝ መሆኑ እና ስሙን ማስቀደሱ ነበር። እኛም በዋነኝነት የሚያሳስበን እስከ መጨረሻው ለይሖዋ ታማኝ መሆናችን እና ስሙን ማስቀደሳችን ከሆነ እርዳታ ለማግኘት የምናቀርበውን ጸሎት ይሰማናል።—መዝ. 145:18, 19
18. ኢየሱስ ስሜታችንን የሚረዳ ወዳጅ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
18 ኢየሱስ ስሜትህን ይረዳልሃል። በጭንቀት በምንዋጥበት ጊዜ ስሜታችንን የሚረዳልን ወዳጅ ሲኖረን በጣም ደስ ይለናል፤ በተለይ ደግሞ ይህ ወዳጃችን እኛ ያጋጠመን ዓይነት ችግር ያሳለፈ ከሆነ ይበልጥ ያጽናናናል። ኢየሱስ እንዲህ ያለ ወዳጅ ነው። በራሳችን አቅም ልንወጣው የማንችለው ችግር ሲያጋጥመን የሚሰማንን ስሜት እሱም አልፎበታል። ኢየሱስ ድካማችንን ይረዳል፤ እንዲሁም “እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ” ድጋፍ እንድናገኝ ያደርጋል። (ዕብ. 4:15, 16) ኢየሱስ በጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ አንድ መልአክ ያደረገለትን ድጋፍ እንደተቀበለ ሁሉ እኛም ይሖዋ እኛን ለመርዳት ያደረገውን ዝግጅት ለመቀበል ፈቃደኞች መሆን ይኖርብናል። ይሖዋ እንዲህ ዓይነቱን ድጋፍ የሚያደርግልን በጽሑፎቻችን፣ በቪዲዮዎች፣ በንግግሮች ወይም አንድ የጉባኤ ሽማግሌ አሊያም የጎለመሰ ወዳጃችን በሚያካፍለን የሚያበረታታ ሐሳብ አማካኝነት ሊሆን ይችላል።
19. ለአምላክ ያለህን ታማኝነት የሚፈትን አስጨናቂ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ብርታት ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
19 ይሖዋ ‘ከእሱ የሚገኘውን ሰላም’ ይሰጥሃል። ይሖዋ የሚያበረታን እንዴት ነው? ስንጸልይ “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ [የሆነውን] የአምላክ ሰላም” እናገኛለን። (ፊልጵ. 4:6, 7) ከይሖዋ የምናገኘው ሰላም ልባችንን ያረጋጋልናል፤ አስተሳሰባችንንም ያስተካክልልናል። ሉዝ የተባለች እህት ይህን በሕይወቷ ተመልክታለች፤ እንዲህ ብላለች፦ “የብቸኝነት ስሜት በጣም ያስቸግረኛል። በዚህ የተነሳ አንዳንዴ ‘ይሖዋ አይወደኝም’ ብዬ አስባለሁ። እንዲህ ሲሰማኝ ግን ወዲያውኑ ለይሖዋ ስሜቴን እነግረዋለሁ። ጸሎት ስሜቴን መቆጣጠር እንድችል ይረዳኛል።” የሉዝ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ጸሎት ሰላም እንድናገኝ ይረዳናል።
20. ኢየሱስ እንባውን እንዳፈሰሰ ከሚገልጹት ታሪኮች ምን ትምህርት አግኝተናል?
20 ኢየሱስ እንባውን እንዳፈሰሰ ከሚገልጹት ታሪኮች እንዴት ያሉ የሚያጽናኑና ጠቃሚ ትምህርቶች አግኝተናል! ሐዘን የደረሰባቸውን ወዳጆቻችንን መደገፍ እንዳለብን እንዲሁም እኛ ራሳችን ሐዘን ሲደርስብን ይሖዋ እና ኢየሱስ እንደሚደግፉን መተማመን እንደምንችል ተምረናል። ይሖዋ አምላክ እና ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል በርኅራኄ ተነሳስተን መስበክና ማስተማር እንዳለብን ተመልክተናል። ይሖዋ እና ውድ ልጁ ስሜታችንን እና ድካማችንን እንደሚረዱልን ብሎም ለመጽናት የሚያስፈልገንን ድጋፍ ሊያደርጉልን እንደሚፈልጉ ማወቃችንም አጽናንቶናል። እንግዲያው ይሖዋ ‘እንባን ሁሉ ከዓይናችን እንደሚያብስ’ የሰጠው አስደሳች ተስፋ እስከሚፈጸምበት ጊዜ ድረስ የተማርነውን ተግባራዊ ማድረጋችንን እንቀጥል።—ራእይ 21:4
መዝሙር 120 እንደ ክርስቶስ ገር መሆን
a ኢየሱስ ስሜቱ ፈንቅሎት እንባውን ያፈሰሰባቸው ጊዜያት አሉ። በዚህ ርዕስ ውስጥ ኢየሱስ እንባውን ያፈሰሰባቸውን ሦስት አጋጣሚዎች እንዲሁም ከእነዚህ የምናገኘውን ትምህርት እንመለከታለን።
b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
c ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 69ን ተመልከት።
d በማቴዎስ 22:39 ላይ “ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የሚያመለክተው የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ አይደለም፤ ቃሉ ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።
e የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢየሱስ ማርያምን እና ማርታን አጽናንቷቸዋል። እኛም የሚወዱትን በሞት ላጡ እንዲሁ ማድረግ እንችላለን።
f የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢየሱስ ኒቆዲሞስን በማታ ለማስተማር ፈቃደኛ ነበር። እኛም ሰዎችን በሚመቻቸው ሰዓት መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ፈቃደኞች መሆን አለብን።
g የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢየሱስ ለይሖዋ እስከ መጨረሻው ታማኝ ለመሆን የሚያስፈልገውን ጥንካሬ ለማግኘት ጸልዮአል። እኛም ፈተና ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ እንዲሁ ልናደርግ ይገባል።